Wednesday, April 25, 2012

ቴዲ አፍሮ ምን ዘፈነ ? እንዴት አቀነቀነ ?


እነሆ አገሬው የቴዲ አፍሮን ‹‹ ጥቁር ሰው ›› ከፋሲካ ጀምሮ እስካሁን እያጣጣመ ይገኛል፡፡ አድማጩ ሙዚቃው የፈጠረበትን ስሜትም በተለያዩ መንገዶች እየገለጸ ነው፡፡ እንደጠበኩት አላገኘሁትም…ከማውቀው ደረጃ ወርዶብኛል… ጥሩ ነው… በጣም አርክቶኛል… የሚሉ ናቸው አስተያየቶቹ፡፡ በርግጥ የአብዛኛው ሰው ፍላጎት ወደየትኛው ይወድቃል የሚለውን መልስ ለማግኘት እንደ አውሮፓ መገናኛ ብዙሃን አስተያት አሰባስቦ ደምሮና ቀንሶ የሚነግረን አካል የለንም፡፡ ስለዚህ አስተያየታችን የግምት ትራስ ላይ የተደገፈ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
በደምሳሳው ከሚገለጹ ሃሳቦች በተጨማሪ የተወሰኑ ዘፈኖች ላይ ከረር ያሉና ምናልባትም ታሪካዊ ማስረጃዋችን የተደገፉ ክርክሮችና ውይይቶችም በማህበራዊ ገጾች አንብበናል፡፡ በዚህ ረገድ የካሴቱ መጠሪያ የሆነው ‹‹ ጥቁር ሰው ›› የታሪክና የስም መዛባት ችግር እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ የቴዲ አብዛኛው ዘፈኖች ርዕሰ ጉዳይ ‹‹ ፍቅር ›› ላይ መውደቃቸውም እየተነገረ ነው፡፡ የግጥሞቹም ጥንካሬና ብስለት የእሱ አልመስልህ እያለን ነው የሚሉ ወገኖችም ጥቂት አይደሉም፡፡ እነዚህና ሌሉች ደቃቅ አስተያቶች  መኖራቸው እውነት ነው፡፡
በርግጥ ቴዲ አፍሮ ምን ዘፈነ  ? እንዴትስ አቀነቀነ ? በአዲሱ አልበሙ ምንስ ነገረን  ? የሚለው አጀንዳ ብዙ የሚያከራክርና የሚያጽፍ በመሆኑ እኔም ስሜቴን ላካፍል ፈለግኩ፡፡ የሙዚቃ ንጥረ ነገር ስለሆኑት ፒች፣ ስኬል፣ ሀርመኒ፣ ሪትምና ሜሎዲ በዝርዝር የምለው ነገር ግን አይኖርም፡፡
                            አጠቃላይ ምልከታ
የቴዲን ሙዚቃዋች ከአቅጣጫ አንጻር እንመድባቸው ብንል ፍቅር፣ ታሪክ፣ ተስፋና ፓለቲካ ላይ ይወድቃሉ፡፡ እነዚህን አንጓዋች እንዴት ሰነጣጠቃቸው ስንል ደግሞ ስልቱን እናገኛለን፡፡ የዘይቤ አጠቃቀሙ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዘይቤ ግጥም ብሩህ ሆኖ ለአይነ ህሊና እንዲታይ፣ ለእዝነ ህሊና ኮለል ብሎ እንዲሰማ በአጠቃላይ ጣዕምና ለዛው እንዲታወቅ የማድረግ ኃይል አለው፡፡
የቴዲ ሙዚቃዋች በሙሉ በዘይቤ የበለጸጉ ናቸው ማለት ባያስደፍርም ንጽጽር፣ ደጋጋሚ፣ ተምሳሌት በተለይም ደግሞ አሊጎሪ የተሰኙት ዘይቤዋች በስራዋቹ ውስጥ ይታያሉ፡፡ ለአብነት ስለፍቅር፣ ባሻው፣ ኃይል እና ፊዮሪናን አሊጎሪ ውስጥ መመደብ ይቻላል፡፡ አሊጎሪ ማለት አንድ ትርጉም ያለው የሚመስለን ነገር ግን ውስጡ ሲመረመር የማይታይ ትርጉም ያለው ሀሳብ ነው፡፡
የጥቁር ሰው አልበም ሌላኛው የጎላ ስልት ዜማዋቹ እንዲወደዱ የአጃቢዋቹ ሚና እንዲጎላ መደረጉ ነው፡፡ ከ 11 ዱ ዘፈኖች ውስጥ ከአጃቢ ሚና  የጸዱት ‹ ህልም አይደገምም › እና ‹ ጨዋታሽ › ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎቹ በመደበኛ አጃቢዋች ፣ በሆታ፣ በቀረርቶ፣ በጸናጽል፣ በሌሎች ቋንቋዋችና በጸጋዬ ግጥም የታቀፉ ናቸው፡፡
 ‹‹ ቴዲ እንደዚህ ዓይነት ነገር ያበዛል- ለምንድነው  ?›› ስል አንድ ጓደኛዬን ጠይቄው ነበር
 ‹‹ ብቻውን መብላት ስለማይፈልግ ! ›› አለኝ እየሳቀ
መልሱ ቀልድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እውነታው ግን የሙዚቃውን ቅርጽ ለማሳመር፣ ዘፈኑን ለማድመቅና በአድማጩ እዝነ ህሊና ውስጥ ሰምጦ እንዲቀር ለማድረግ ነው፡፡ ጥቂት እውነት ከፈለጋችሁ ፊዬሪና፣ ስለፍቅር፣ ጸባዬ ሰናይና ኃይል የሚባሉት ሙዚቃዋች ውስጥ አጃቢዋችን ደጋግማችሁ ስሙ፡፡ በማግስቱ ብቻችሁን እነዚያን ቃላት ትደጋግማላችሁ፡፡ ምናልባትም የጥንቱን ኮረስ / chorus / ለየት ባለ ስልት እየተጠቀመበት ይመስለኛል፡፡ በ5ኛውና በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በግሪክ ታዋቂ ቲያትሮች ውስጥ ለድምቀት የሚጠቀሙበት ኮረስ ወደ ሙዚቃው የተሸጋገረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በርግጥ ኮረስ በአንድ ሙዚቃ ላይ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዋች ሲያቀነቅኑት ነው፡፡ ቴዲ በስልቱ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ በጥቂት ቦታ ነገር ግን በአስፈላጊው ምዕራፍ ላይ አጃቢዋች ጎልተው እንዲወጡ አድርጓል፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን እጀባን ከመጠን በላይ በመጠቀሙ ጩኀት የበዛ አስመስሎታል፡፡
ዝርዝር እይታዋች
ሀ . ታሪክ ቀመስ ሙዚቃዋች
‹ ጥቁር ሰው › እና ‹ ስለ ፍቅር › የብዙዋች መነጋገሪያ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ካነሱት  ጭብጥ አንጻር ትልቅ ትኩረት የሚደረግባቸው ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ስለፍቅር ከላይ እንደገለጽኩት ከመልዕክት አንጻር አሊጎራዊ ይዘት ያለው ነው፡፡ በጥቁር ሰው ሙዚቃ ውስጥ ባልቻ፣ ፊታውራሪ ኃ/ጊዮርጊስ፣ አሉላ፣ መንገሻ፣ ገበየሁና ጣይቱ ተጠቅሰዋል፡፡ ታሪኩ የሚጀምረው የአጼ ሚኒልክን የክተት ጥሪ በማቅረብ ነው፡፡ ወዲያው የእያንዳንዱ ገድል ይቀርባል፡፡ ቴዲ
            ‹ ባልቻ አባቱ ነፍሶ
             መድፉን ጣለው ተኩሶ ›  ባለው አቀራረብ ላይ መድፉን የጣለው አባተ ቧ ያለው መሆኑና ባልቻ መድፍ ተኳሽ እንዳልነበር የቀረቡ ክርክሮች ነበሩ፡፡ በርግጥ አባተ ይህን መሰሉ ገድል ነበረው
            ‹‹ በሰራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ
              ተፈጠመ ጣሊያን አበሻ እንዳይደርስ
              አባተ በመድፉ አምሳውን ሲጥል
              ባልቻ በመትረየስ ነጥሎ ሲጥል… ››  በሚለው ግጥም ውስጥ የስራ ድርሻው የተጠቆመ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ በጦርነቱ ጠዋት ላይ ገበየሁ ሲሞት የተተካው ባልቻም ሌላ ተግባር እንደነበረው የሚጠቁም ሀሳብ አለ፡፡
            ‹‹ ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
              መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ ››  ቴዲ በግጥሙ ላይ ሰፋ ያለ ድርሻ የሰጠውን ባልቻ ከዚህ አንጻር ማጉላት ፈልጎ ሊሆን ይችላል ብለን ለማሰብ መንገዱ ዝግ አይደለም፡፡ እንደ ባልቻ ሁሉ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የአድዋ ሚና ትልቅ አልነበረም የሚሉ መከራከሪያዋችም ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ ሀብተጊዮርጊስ በጦርነቱ ዋዜማ ላይ በሰጡት ምክር፣ ኋላም ባሳዩት የጦር ስልት የጦሩ መሪ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ እኚህ ሰው ቀደም ባለው የወላሞና የእምባቦ ጦርነት ላይ
            ‹‹ የሀብቴ ጦረኛ አጋም መቁረጥ ያውቃል
             የሚኒልክን ጠላት ልመንጥረው ይላል ›› ተብሎ ተዘፍኖላቸዋል፡፡ በጦር ስልት ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲና በፍርድ አሰጣጥ የነበራቸው ችሎታም  ከሌሎቹ የላቀ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ሁለት እንግሊዞች ያለፍቃድ በኬንያ በኩል ወደ ግዛታቸው ሲገቡ ተገደሉ፡፡ ቆንሲሉ ‹‹ ኡ ኡ  ›› አለ፡፡ ሚኒልክ ጉዳዩን መክረን መልስ እንሰጣለን በማለት አባ መላን ያስጠራሉ፡፡ አባ መላ አልተጨነቁም፡፡ ሰውየውን ወደኔ ላከውና አነጋግረዋለሁ አሏቸው፡፡ ቆንሲሉ አባ መላ ፊት እንደቀረበ
 ‹‹ ዜጎቼ ደማቸው ስለፈሰሰ መሬቱ ይሰጠኝ ›› አለ፡፡
 ‹‹ በሀገራችሁ ይህን መሳይ ደንብ አለ ? ›› ጠየቁ
 ‹‹ አዋ ! ›› መለሰ ቆንሲሉ
 ‹‹ እንግዲያውስ የቴዋድሮስ ልጅ አለማየሁ በሀገራችሁ ስለሞተ ለእኛ ለንደንን ስጡን፡፡ እናንተም ይህን ውሰዱ ›› ብለው ወረቀት ላይ ጽፈው ከፈረሙ በኋላ ‹‹ በል ፊርማህን አኑር ! ›› ይሉታል፡፡ ቆንስሉ አልፈርምም ብሎ ወጣ፡፡ ሚኒሊክና ጣይቱ ከደስታቸው ብዛት አንገታቸውን አቅፈው ሳሟቸው፡፡ በመሆኑም ያለው ታሪክ ከቴዲ ግጥም ጋር የሚፋለስ አይደለም፡፡ በርግጥ በአድዋ ዘመቻ ወቅት  ትልቅ ጦር ይዘው የዘመቱት ራስ መኮንን፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ ወሌ፣ ራስ ወ/ጊዮርጊስ፣ አዛዥ ወ/ጻዲቅና ደጃች ተሰማ ናደው በግጥሙ ውስጥ ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡ በአንድ ዘፈን ይህን ሁሉ ነገር ማካተት ይከብዳል፡፡ በሌላ በኩል በስነ ጽሁፍ ‹‹ የገጣሚው መብት ›› የሚባል ሀሳብ አለ፡፡ ቴዲ በዚህ መብቱ ተጠቅሞ ለስራው የሚያመቹትን ብቻ ለቅሞ ያስገባ ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ይልቅ ስለ ሚኒሊክ እንደ መዝፈኑ ላይቀር የሳቸውን ስራ ለምን አጉልቶ አላቀረበውም ? የሚለው ሀሳብ መነሳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለአድዋ ድል ትልቅ መሰረት በጣለው የአምባላጌ ድል ላይ ሚኒሊክና የጦር አዛዦቹ ምርጥ ታሪክ ነበራቸው፡፡ በድል ውስጥ ጀግኖች መፈጠራቸው አይቀሬ  የመሆኑን ያህል ድሉ ሲነሳ ውጤቱ ገዝፎ የሚታየው ከሚኒሊክ አመራር፣ አስተሳሰብና አስተዳደር አንጻር ነው፡፡ ቴዲ ሚኒሊክ ጥሪ ብቻ እንዲያቀርቡ አድርጎ የግጥሙን ደምና ስጋ የሞላው በሌሎች ብዙ ቅርንጫፎች ነው፡፡ ይህም ሚናቸው እንዲደበዝዝ አድርጎታል፡፡ ግጥሙን ዝም ብሎ ያየ ሰው የተጻፈው ለባልቻ ነው - ለሚኒልክ ? ብሎ ሊጠይቅ ይቸላል፡፡
በተረፈ ግን ጥቂትም ቢሆን የሚኒሊክ የክተት ጥሪና የተሰጠው ምላሽ መልዕክቱ ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡
                                    ‹‹ አድዋ ሲሄድ ምኒሊክ ኑ ካለ
                                      አይቀርም በማርያም ስለማለ
                                      ታደያ ልጁስ ሲጠራው ምን አለ ?
                                      ወይ
                                      ወይ ሳልለው ብቀር ያኔ
                                      እኔ አልሆንም ነበር እኔ ››
ጥሪው ብቻ ሳይሆን ህዝቡ የተጠራበት ስልት የሚኒሊክን የአመራር ጥበብ ያሳያል፡፡  ህዝቡ ሚኒሊክንም ሆነ ማርያምን ሳይፈራ/ ሳያከብር ቢቀር ኖር ውጤቱ ምን ይሆን ነበር  ? በቀላሉ ኢትዮጽያ የነጻነት ተምሳሌት፣ የአፍሪካም ሆነ የዓለም ጭቁን ህዝቦች ሞዴል አትሆንም ነበር፡፡
‹‹ ስለ ፍቅር ›› በንጽጽራዊ ዘይቤ ጎልብቶ አሊጎራዊ ውጤት ላይ የሚያርፍ ስራ ነው ፡፡
 ‹‹ እግር ይዞ እንዴት አይሄድም
               ሰው ወደፊት አይራመድም
             አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ
   ለምን ይሆን የራበው ሆዴ ››
 የቴዲ ዋና ጥያቄ ያለው እነዚህ ስንኞች ውስጥ ነው፡፡ እግር የርምጃና የዕድገት ምልክት ነው ፡፡ በርግጥ እግር ይሄድ ዘንድ የተመዛዘነ ፍቃድ ከአእምሮ ይፈልጋል፡፡ አእምሮአችን በዕውቀትም ሆነ በቅንነት ደምና ነርቮች ስላልተሞላ እያለን ተርበናል፤ እያለምን ከድህነት ወለል ፈቅ አላልንም፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹ ፍቅር ›› ካለ በጋራ ማቀድ፣ መስራትና ዕውቀትን መጨበጥ እንደሚቻልም ይጠቁመናል፡፡ ጥቁምታው ወደ 17ኛው ክ / ዘመን የሚያሻግር ነው፡፡ ቴዲ የጥበብ መሰረት እንደነበር ሊያሳየን የሞከረው በንጉስ ፋሲለደስ አማካኝነት ነው፡፡
  እንደሚታወቀው ፋሲለደስ በ 1636 ዓ.ም አስደናቂዋቹን ግንቦች ገንብቷል፡፡ ከዚያ በፊት በድንጋይ መስራት የተለመደ አልነበረም፡፡ ጎንደር እንደ አውሮፓ እውነተኛ የከተማ ቅርጽ ለመያዝ የበቃቸው ከፋሲለደስ በኃላ የመጡ መሪዋቸ እዛው መክተም መቻላቸውና የባህል፣ የንግድና አስተዳደር ማዕከል በመሆኗ ነው፡፡ በፋሲለደስ ዘመነ መንግስት የሸዋው ስብስብ የሆኑት ‹‹ ተዋህዶ›› እና የጎጃምና ትግሬው ስብስቦች የነበሩት ‹‹ ቅባቶች ›› በፈጠሩት ውዝግብ የሀገሪቱ ፓለቲካ ተመሰቃቅሎ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ቴዲ አፍሮ የሃይማኖት እውቀት የነበረውንና ጎበዝ ጸሀፊ የሆነውን ‹‹ ዘርያቆብ ›› ወይም ዓለም አንቱ ያለውን ‹‹ ላሊበላ ›› ለጥበብ ምሳሌነት ለምን አልመረጠም ብሎ መከራከር አይቻልም ፤ ይህም ‹‹ የገጣሚ መብት ›› ነውና፡፡
የጥበብ መሰረት ነበርን ፣ ይህን ሀብት መነሻ በማድረግ ዛሬ የሀገር ጅራት የሆነቸውን ሀገር ማሳደግ እንችላለን ነው የሚለው፡፡
‹‹ የት ጋር እንደሆን ይታይ የኛ ጥበብ መሰረቱ
  የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ
  ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ
  ሰው አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ ›› በማለት ነው፡፡ ይህ የፓለቲካ ሰዋችን አስተሳሰብ የሚሞግት ሀሳብ ነው፡፡ አካሄዳችን ደርግ ዘውዱን አበሻቅጦ ፣ ኢህአዴግ ደርግን ረግሞና አስረግሞ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኃለኞቹን ለዛሬው ድክመት መሸፈኛ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ እድገትና ንጽጽር ከራስ ጋር ሳይሆን ካለፈውና ከወደቀው ስርኣት ጋር ነው፡፡ ቴዲ ሁልግዜም ከኃለኛው ራሱን የቻለ ምርጥ ተሞክሮ ስላለ እናክብረው፣ መነሻ እናድርገው የሚል ይመስላል፡፡
የዚህ ዘፈን ንጽጽር ከፓለቲካው ዓለም አልፎም መንፈሳዊውን እውነት ያሳያል፡፡
‹‹ አንተ አብርሃም የኦሪት ስባት
  የነ እስማኤል የይሳቅ አባት
  ልክ እንደ አክሱም ራስ ቀርጸሃት ራሴን
  በፍቅር ጧፍ ለኩሳት ነፍሴን ››
ቴዲ አብርሃምን ለምን ተጠቀመ ብለን ስንጠይቅ የነበረውን ከፍተኛ ፍቅርና በፍቅርም ያገኘውን የድል አክሊል እንመለከታለን፡፡ አብርሃም በ 86 ዓመቱ እስማኤልን የወለደው ከሚስቱ ሳራ ሳይሆን ከሰራተኛይቱ ነበር፡፡ ‹‹ ካረጀሁ በኃላ እንዴት ፍትወት ይሆንልኛል ? ›› የሚል አስጨናቂ ጥያቄ ራሱን በሚጠይቅበት ግዜ ደግሞ ከሳራ ይስሀቅን መውለድ ችሏል፡፡ ለእግዚአብሄር ፍቅር ሲል ደግሞ በስንት መከራ የተወለደውን ይስሀቅን ለመስዋትነት እንደ በግ ሊያርድ በሞርያ ተራራ ተገኘ፡፡ ልጄ ለምን ተመታ ብሎ ጦርነት የሚያውጅ እንጂ የሚወደውን ልጅ ለመሰዋትነት የሚያቀርብ ቤተሰብ ይኖር ይሆን ? እውነተኛ ፍቅር በመኖሩ ግን አብርሃም ራሱም ሆነ ልጁ ተባረኩ፡፡ የሚፈልገውን አግኝቶም 175 ዓመታት ኖሯል፡፡
ቴዲ ከታሪክም ሆነ ከመንፈሳዊ አንጻር የሚነግረን እንግዲህ ፍቅርን ነው፡፡ ርስ በርስ እንዲሁም ወደ ኋላ እየሄዱ ከመወነጃጀል ፍቅርን አጀንዳ በማድረግ ችግሮቻችንን እንፍታ ነው የሚለው፡፡ ይህን አለማድረግ ደግሞ ያሉብንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይባስ የሚያወሳስብና የምናልመውን እድገት የማያመጣ ነው፡፡ ይህን ለመስራት ‹ ግዜው አይደለም፣ ያለፈበት ነው፣ አሰልቺ ነው › በማለት በሮች መዘጋት እንደማይገባቸውም ተከታዩን ስንኞች እንካችሁ ብሎናል፡፡
‹‹ ሰው ለመውደድ ካልኩኝ ደከመኝ
  ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ ››
በ‹‹ ስለፍቅር ›› ም ሆነ በ ‹‹ ጥቁር ሰው ›› ሙዚቃዋች ውስጥ ደጋሚ ድምጽ / Alliteration / የተሰኘው ዘይቤ ጎልቶ መታየቱ መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ ባልቻ ሆሆ፣ ሳልል ዋይ፣ አመመኝ የሚሉ ቃላቶች ተደጋግመው ይሰማሉ፡፡ ድግግሞሹ ያለ ምክንያት ቢገባ ኖሮ የግጥሙን ውበትና መልዕክት ያፈዘው ነበር፡፡ ነገር ግን ቀረርቶው የውጊያው ማቀጣጠያ ፣ ሳልል ዋይ የዘመቻው ምላሽ፣ አመመኝ ህዝቡም ሆነ ሀገሪቱ አሁን ያሉበት ሁኔታ ምናልባትም ነገም ፍቅር ከጠፋ ከህመሙ ማገገም ያለመቻልን የሚጠቁም ቁልፍ ቃላቶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ለ . ፍቅር ቀመስ ሙዚቃዋች
 ደስ የሚል ስቃይ፣ ስቴድ፣ ህልም አይደገምም እና ጸባየ ሰናይን በገራገር አይን ካየናቸው የፍቅር ይዘታቸው ከፍ ያለ ይመስላል፡፡ ምልከታችን ጠለቅ የሚል ከሆነ ግን ሌላ ምላሽ ልናገኝ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ‹‹ ደስ የሚል ስቃይ ›› በተባለው ዘፈን ውስጥ ስለሰው የሚያነሳው ስንኝ አንድ ቦታ ብቻ ነው የሚገኘው፡፡
‹‹ ምን ይዞ ነው ለመንገዱ
  እንዲህ አርቆ ሰው መውደዱ ››  በዚህም ምክንያት የዘፈኑ ጭብጥ ፍቅር ነው ይባል ይሆናል ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዘፈን የእናት ወይም የሀገር ፍቅርን የማይወክልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ‹‹ ሰው ›› በሰውኛ ዘይቤ ተወክሎም ሀገርን ሊወክል ይችላልና፡፡ዞሮ ዞሮ የፍቅሩ ግለት ከፍተኛ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ገጣሚው የፍቅሩን ግለት ለመለካት የሚያስችል ቃላት እንደሌለው፣ ፍቅር እንደ ኩፍኝ ወጥቶ የማያልቅ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ሙዚቃው የያዘው ሀሳብ በጥልቅ ስንኞች የጠነከረ ነው፡፡
“‹‹ ከሚገባሽ በታች ከምችለው በላይ
   እስኪወድሽ ልቤ ደስ በሚል ስቃይ ››  ይህን ሃሳብ ለማፍታታት ሰፊ ተመስጦ ወይም ቁዘማ ሳያስፈልግ አይቀርም ፡፡
‹‹ ህልም አይደገምም ›› የሚለው ሙዚቃ ፍቅርን በዕውኑ ዓለም ደፍረው ለማሸነፍ ለሚቸገሩ አፍቃሪያን የተሰጠ ገጸ በረከት ይመስላል፡፡ በርግጥ ፍቅርን በሙሉ ዓይን ለማየት የማይደፍሩ ብዙ ምስኪኖች ጋሻ የሚያደርጉት ደብዳቤን፣ ህልምንና አማላጆችን ነው፡፡ የቴዲ ‹ ህልም አይደገምም › ከሄለን በርሄ ‹ የህልሜ ጓደኛ ትመጣለህ ዛሬ በግዜ ልተኛ › ከተሰኘው ሙዚቃ ብዙም የማይራራቅ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
‹‹ ጸባዬ ሰናይ ›› ምርጥ ውበት ብቻ ሳይሆን የሚደነቅ ጸባይ የተላበሰች ሴት የተገለጸበት ሙዚቃ ነው፡፡ ቴዲ ምርጥ ውበትና ጸባይን እንድንቀበል ያደረገው የግጥሞቹ ሀሳብ በንጽጽርና ተምሳሌት ዘይቤ ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ ነው፡፡ ውበቷ ከገሊላ ቁንጅና ጋር ተወዳድሯል፡፡ ንጉስ ሰለሞንን ያንበረከከችው ንግስት ሳባና ጁሊየስ ቄሳርንና ማርክ አንቶኒን ያብረከረከቸው የግብጽዋ ንግስት ክሊዋፓትራ ቴዲ ለሳላት ቆንጆ ምን ያህል ግዙፍ የተጽዕኖ ጥላ እንደፈጠሩም መመልከት ይቻላል፡፡
‹‹ አየን ጀምበር ወዳለም አጎንብሳ
  ያይንሸን ብሌን ዉሃ ለብሳ
  ገጥሞሽ የሳባ ሞገስ የክልዮፓትራ
  አምረሽ ትታይ ጀመር በራስሽ ተራ ››
መ . ተስፋ ጠሪ ሙዚቃዋች
‹ ባሻው ›  እና  ‹ ኃይል › ለዚህ ምድብ የሚስማሙ ይመስላል ፡፡ ‹‹ ባሻው ›› በኑሮ ውድነት ተስፋ ለቆረጡ፣ በስራ ማጣት ተስፋ ላጡ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ለተንገላቱ፣ በስራ አለመርካት ለሚጨነቁ፣ በሀገር ናፍቆትና ፍቅር ለሚብሰለሰሉ ሁሉ መድህን መስሎ ታይቶኛል ፡፡
‹‹ ቢከፋም ቢለማም ያለም ኑሮህ ምን ባይቀና
  ሁን አንተ ጤና
  ቸር አስብበት በሰጠህ እድሜ
  አይዞህ ወንድሜ ››
በርግጥም በባህላችን ትልቁ ምርቃት ዕድሜና ጤና ይስጥህ የሚለው ነው ፡፡ ሁለቱ ካሉ ወልዶ መሳም ዘርቶ መቃም ይቻላል፡፡ ወጣቱ ቴዲ እንደ ሽማግሌ ጭራና ከዘራ ይዞ አይዟችሁ ብሎ ሲያጽናና ደምቆ ይታያል፡፡ ነገ የፈለጉበት ቦታ ለመድረስ ለዛሬ መስጠት የሚገባውን ክብር የሚገልጽበት ሀሳብ የረቀቀ ነው ፡፡
‹‹ ዓመት ያህላል ቀን እየዞረ
 ዛሬም ራሱ ነገ ነበረ
 የግዜ ሚዛን አይላወስም
 ዛሬን የሌለ ለነገ አይደርስም ››
‹ ዛሬም ራሱ ነገ ነበረ › የሚለው ትንቢት አመልካች ሀሳብ ብዙዋቻችን ከምናውቀው ብሂል 360 ድግሪ ተጠማዞ ቁጭ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም ትናንት ነበር ብለን ነው የምናስበው፡፡ ግን የቀንን ኡደትንና መልክን በጥሞና ስናስብ አባባሉ ባይባል እንጂ ልክ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እናም በአንድ በኩል እያጽናና በሌላ በኩል ነገን ሳይሆን ዛሬን ጠንክረን እንድንሰራበት፣ አሰፈላጊ ከሆነ ጠንክረን መብቶቻችንን እንድናስከብርበት ያሳስበናል፡፡
‹‹ ኃይል ›› ከመልእክት አንጻር የባሻው ቀጣይ ክፍል ነው የሚመስለው፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታዋች ቢኖሩም ‹ አይዞን ቀላል ይሆናል › እያለ ነው የሚያጽናናን፡፡ ሆኖም የአገላለጹ ዘዴ የተለያየ ነው፡፡ ቴዲ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ፍቅር ሲል የደረሰበትን ጥቃት ገና በመክፈቻው በምሳሌነት ማሳየት የፈለገ ይመስላል፡፡
 ‹‹ ዳገት ላይ አትዛል ጉልበቴ
   የተራራው ጫፍ ፍቅር ናት ርስቴ
  ቀላል ይሆናል ቀና አርገኝ ጽናቴ ››
እነዚህ ስንኞች ፈጣሪ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ተራራ ያደረገውን ከባድና ፈታኝ ጉዞ የሚወክሉ ናቸው፡፡ የተራራው ጫፍ ከሸክም ያረፈበት ብቻ ሳይሆን ለፍቅር ሲል ነፍሱን ያጣበት ቦታ ነው፡፡ በጎኑ የተሰቀሉት ሁለት ሌቦች በሳዩት ምግባር አንዱ ለገነት ሌላው ለውድቀት ተዳርገዋል፡፡ ገነት የገባው ሰው ጽናት ላላቸው ሁሉ ፍሬያማ ውጤት ማሳይ ሆኖ የተወከለ ነው፡፡ ከፈጣሪ እልፈት በኃላ ሰማይና ምድር በአስደንጋጭ ትዕይንት ተመሰቃቅለው ነበር፡፡ በዚህም  ኃጢያተኞች ሳይቀሩ ዓለም ያከተመላት መስሏቸው ነበር፡፡
‹‹ ደመና ሲያይ መስሎት የጨለመ
  አለ ቂል ሰው ሁሉም አከተመ ›› ይለዋል ቴዲ ይህን ሀሳብ ለማጠናከር፡፡ ሆኖም ፈጣሪ መሃሪ ነውና ሌላ አዲስ ቀን፣ ሌላ አዲስ ኪዳን አስተዋውቋል፡፡ እናም በፓለቲከኞች ፍላጎት ሳይሆን ፈጣሪ ያለ ዕለት ሁሉም ነገር ቀላል እንደሚሆን አብራርቷል፡፡ ይህ ግጥም በዚህ መልኩ ተፍታቶ ተገለጸ እንጂ ከሚገባው በላይ በማጠሩ ሀሳቡን በአግባቡ የገለጸ አይደለም፡፡ ነገሮች ቀላል የሚሆኑበት አመላካች ማብራሪያዋች አልገቡበትም፡፡ የጸጋዬ ገ/ መድህን ግጥም ጉልበት ይሆነው ዘንድ ተፈልጎ ነው መሰለኝ በድምጽ ቢገባም በዘፈኑ ሀሳብና በግጥሙ መልእክት መካከል ሊነገር የሚያሰቸግር ክፍተት ይታያል፡፡ ይህን ክፍተት በቴዲ ሀሳብ ግለጽ ብባል ደስ የሚል ስቃይ በሚለው ዘፈን ውስጥ የመጀመሪያውን አንቀጾች በአስረጅነት እጠቅሳለሁ፡፡ ‹ ከሚገባሽ በታች ከምችለው በላይ › የሚለውን ቃል፡፡ እኔ ይህ ቃል መሃሉ እንደ ሸንበቆ ክፍት ነው የሚመስለኝ፡፡
ሰ . ፓለቲካ ቀመስ ሙዚቃዋች
ፊዮሪና በዜማም ሆነ በግጥም ውበት የደመቀ ሙዚቃ ነው፡፡ ፊዮሪና በዋናው ፍቅርን፣ ፊዮሪና በተሳቢው አሰመራን ለመጫኑ ግልጽ ነው፡፡ ቴዲ ለኤርትራ ያለው ፍቅር የጠነከረ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ‹ ዳህላክ › በሚለው ስራው የሁለቱ ወንድማማቾች ሀገሮች መለያየትና ይህም ያስከተለውን ስነ ልቦናዊ ቀውስ በተሳካ መልኩ መግለጹ ይታወቃል፡፡
በዚህም ስራው የሁለቱ ሀገራት መለያየት ውስጡ ያለውን የፍቅር እሳተ ጎመራ ለግዜው አዳፈነው እንጂ ፈንድቶ ከመውጣት የማያግደው መሆኑን አብራርቷል፡፡
‹‹ ጋራው ቢከልለን ያ ተራራ
   አትወጪም ከሃሳቤ ጓል አስመራ ›› በማለት
እንደ ሌሎቹ ስራዋቹ ሁሉ እዚህም ውስጥ ፍቅርና ተስፋ የሃሳቡ ምርኩዝ ሆነው ይታያሉ፡፡ ብሩህ ቀን መጥቶ ፊዮሪናንም ሆነ አስመራን እንደሚመለከት ተስፋ ያደርጋል፡፡
‹‹ ዘመን አልፎ ዘመን እስኪታደስ
  ቀን ቢመስልም የማይደርስ
  በፍቅር ሲቃና መሰረቱ
  ደሞ እንዳዲስ አንድ ይሆናል ቤቱ ››
በርግጥም የጀርመን፣ ጣሊያን፣ ቻይና፣ ቬትናም፣ የመን፣ የወዘተ ሀገሮች የውህደት ታሪኮች መነሻ ሆነውት ይሆናል - ቴዲ አፍሮን፡፡ በአጠቃላይ ስቴድ፣ ኦ አፍሪካ፣ ጨዋታሽና ህልም አይደገምም የሚሉት ስራዋቹ ከሌሎቹ አንጻር ሲታዩ ያልታሹ ይመስላሉ፡፡ በአንዳንድ ሙዚቃዋቹ ውስጥ የሀሳብ መመሳሰል ይታያል ፡፡ በድምሩ ሲታይ ግን የቴዲ ስራዋች ባነሱት ሀሳብ፣ በቴክኒክ፣ በጆሮ ገብነታቸው ዛሬም ልዩነት የፈጠሩ ናቸው ፡፡  በዚህ አልበሙ ስለፍቅር፣ ታሪክ፣ ተስፋ፣ ማንነትና ውህደት ዘፍኗል፡፡ ያቀነቀነውም ጥሩ ዜማን ከሚስብ የዘይቤ ቀለም ጋር በማዋሃድ ነው፡፡ የነገረን ደግሞ ፍቅር እንዲኖረን፣ ተስፋ እንዳንቆርጥ፣ ስለ አንድነት እንድናስብና በእጃችን የሚገኘውን ዛሬን በአግባቡ እንድንጠቀምበት ነው ፡፡


2 comments:

  1. What a great analysis,interpritation of the Crowen prince of Ethioopian Music, Teddy afro.Alemayehu has showen us his all rounded observation,interpritation and historical side of the album.and it pointout the dinotative and conotative part of it as well.,,,keep it up sir,,,Fasika

    ReplyDelete
  2. Good analysis brother If you can please send it to newspaper.

    ReplyDelete