Monday, July 13, 2020

መንግስት ለእውነተኛ ፍትህ ይቁም !



በኦሮሚያ በተለያዩ ከተሞች የደረሰውን አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊት ስመለከት እንደወንድ ልጅ አዘንኩ ። በድንጋይ ፣ በዱላ፣ በሜንጫ ፣ በእሳት …  የሰው ልጅ የሰው ልጅን አጠፋው ። ይህን መሰል የመንጋ ፍጅት በቡራዩ ከተማ ሲጀመር ‹ እንዴት ወንድም በወንድሙ ላይ ይጨክናል ? › ነበር ያልኩት ። በአዲስ አበባና በደቡብ ክልሎች ተመሳሳይ ጥፋት ሲፈጸም ‹ እንዴት ወገን በወገኑ ላይ ይጨክናል ? › ነበር ያልኩት ። የአሁኖቹን ገዳዮች ግን ወንድምም ሆነ ወገን ለማለት ድፍረት አጣሁ ። ቄሮ ነን ለሚሉ ወገኖች / ከደሙ ንጽህ የሆናችሁትን አይመለከትም /  የክፋታቸውን ልክ የሚመጥን ስያሜ ለመፈለግ ብዙ ባዘንኩ ። ገዳይ ፣ ጨፍጫፊ ፣ አረመኔ ፣ ዘረኛ ፣ አሸባሪ፣ ርጉም ፣ አውሬ … ብዙ መገለጫዎችን ብደረድርም ልካቸውን ያገኘሁላቸው አልመሰለኝም ።

እነዚህ አውሬዎች እኩይ ተግባራቸውን አንዴ ብቻ ሳይሆን ደጋግመው አሳይተውናል ። ሰላማዊውን የሰው ልጅ ከላይ በገለጽኩት መንገድ አጥፍተዋል ። አሁንም ራሴን ጠይቄ መልስ ያጣሁለት ነገር ከዚህ በላይ ምን ቀርቷቸው ይሆን ? የሚል ነው ። በሚቃጠል ሬሳ እየጨፈሩ ተደስተዋል ። የሞተ አስከሬን መንገድ ለመንገድ በመጎተት ፌሽታ አድርገዋል ። እናትን እናከብራለን እያሉ እናቶችን ልጆቻቸው ፊት ገድለዋል ። እህቶች አለን እያሉ ሴቶችን በጭካኔ ደፍረዋል ። አባት ዘውድ ነው እያሉ በእርጅና የተጎዱ አረጋዊያንን ጨፍጭፈዋል ። ሰላሳና አርባ አመታት በስንት ላብና ድካም የተገነቡ ተቋማትን አቃጥለዋል ። የሚጠራጠሩትን መታወቂያ ካርዱን በማየት ፣ የሚለዩትን ደግሞ ከአማራና ጉራጌ ወገን ነው በማለት ቤታቸውን አንድደው እንደ ዳመራ ሞቀዋል ። ነገ የተሻለ ዜጎች እንዲሆኑ መሰረት የሚጥልላቸውን የራሳቸውን ትምህርት ቤቶች አውድመዋል ።

ይሄን ሁሉ አድርገው ግን ገና አልረኩም ። አሁንም ይፎክራሉ … አሁንም ያስፈራራሉ ። ታዲያ ምን ቀራቸው ? እንደ ህንዶች ያቃጠሉትን የሬሳ አመድ ተራራ አናት ላይ ወጥተው መበተን ? … የገደሏቸውን ህፃናትና ሴቶች ደም እንደ ቫምፓየር መመጠጥ ?… በሚጎትቱት የወጣቶች ሬሳ እግር ኳስ መጫወት ? … ዱላና ሜንጫቸውን በእሳት አግለው የንጽሃን ገላ ላይ ቄሮ የሚል ንቅሳት መጻፍ ?…
ነው ከዚህ የላቀ ሌላ የርካታ ጣራ አላቸው ? እንዴትስ ከሰው ተፈጥረው በተለይ መከላከል የማይችለውን ሰላማዊ ዜጋ ያጠፋሉ ? ይህስ በባህላቸው ‹ ጀግና ወይም አንበሳ ገዳይ › የሚያስብል ነው ? ኦሮሞ አቃፊ ነው የሚባለው ነገር ለተወሰኑ ቡድኖች ብቻ ነው የሚሰራው ? ይህ አባባል መፈክር ካልሆነ በስተቀር ትንች ኮሽ ባለ ቁጥር ‹ ነፍጠኛና መጤ › በሚል ታርጋ እንዴት ወገንን ለማረድ መጣደፍ ይኖራል ? ድርጊቱ የአንድ ሰሞን ወይም የአንድ ግዜ አጋጣሚ ቢሆን ጥሩ ፤ ካልሆነ እንዴትስ በተደጋጋሚ የሰው ጎርፍ ሲፈስ ተመለክትን ? ለዚህ ወሳኝ ጥያቄዬ ወሳኝ መልስ የሚሰጠኝ አለ ?

አንዳንዶች በመጥፎ ትርክት ስላደጉ … ሌሎች ደግሞ የግብረገብና የፖለቲካ ብስለት ስለሌላቸው ነው የተቀባበለ ጠመንጃ ሆነው የሚኖሩት ይላቸዋል ። ለዚህም ነው የሆነ ቡድን ተነስ ! በለው ! ካላቸው ለምን እና እንዴት የሚሰኙ ህሊናዊ ጥያቄዋችን ሳይመረምሩ ዱላና ገጀራቸውን ይዘው የሚሮጡት በማለት ። አንዳንዶች ከሃይማኖት የራቁና ፈሪሃ እግዚአብሄር ስለሌላቸው የጭካኔን ዜማ ለማንጎራጎር ተገደዋል ባይ ነው ። ብዙ ብዙ ይባላሉ ። ነገር ግን በቅርቡ ከአርሲ በተለቀቀ አንድ ቪዲዮ ላይ የንጽሃንን ቤት እያቃጠሉ ‹ አላሁ አክበር › የሚሉ ቄሮዎችንም ታዝበናል ። ይህን ቪዲዮ ያየሁ ግዜ ይበልጥ ነው የተሸማቀቅኩት ። መጥፎ ተግባር እየተከናወነ እንዴት የፈጣሪ ስም ይጠራል ? ለሃይማኖታቸው የቆሙ ቀናኢ ሙስሊም ወገኖች ይህን ተግባር የግድ ሲያወግዙ መስማት ያስፈልጋል ። አሊያ የቄሮን ክፉ ተግባር እንደመጋራት ነው የሚያስቆጥረው ።

አረመኔው ቡድን በተድጋጋሚ ንጽሃንን ሲገድልና ንብረት ሲያውድም እንዴት መከላከል አልተቻለም ? ወይም ለምን መከላከል አልተፈለገም ? የሚለው ጥያቄ አብሮ ይመጣል ። የኛ ሀገር የፖለቲካ ዘውግ ከቧልት ቦሃቃ የሚቀዳ ነው ። በኦሮሚያ ክልል ለበርካታ ዙሮች በርካታ ፖሊሶች ተመርቀው ሲወጡ አይተናል ። አንዳንዶች እንደውም ‹ ወደ አጎራባች ክልሎች ዘመቻ ሳይኖር አይቀርም › በማለት ሲያሸሟጥጡ ነበር ። ሰልጥኖ የወጣው የፓሊስ ቁጥር የኦርሚያን ሰላምና ድህንነት ለማስጠበቅ የሚያንስ አልነበረም ። ይሁንና በአዳማ ፣ በዝዋይ ፣ በአርሲ ፣ በሻሸመኔ ፣ በጅማና በሌሎች ከተሞች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ህንጻዋችና ቤቶች ሲነዱ ይህ ‹ የሰለጠነ › ሃይል ተደብቆ ነበር ። ወይም ልብሱን አውልቆ ለአውዳሚዎቹ ክብሪት እየጫረ ነበር ። ወይም ደግሞ ዱላ የያዘውን መንጋ ከያዘው ጠመንጃ ጋር ሲያነጻጽረው አንሶበት ጥሎ ለመሄድ ተገዶ ይሆናል ። በእውነት ሌላው አሳፋሪና አሸማቃቂ ጉዳይ ይሄ ነበር ። ሰላምን ለማስጠበቅ ሰልጥኖ ከተማው ጦር ሜዳ ስትሆን እያየ እጅን አጣጥፎ በ‹ ሰላም › መቀመጥ በአለም ያልተመዘገበ ቧልት ነው ። ከተማውን ሊጠብቅ የነበረው ኦሮምኛ ተናጋሪ ያልሆኑ አካላት ከተማውን ሊያወድሙ ሲመጡ ብቻ ነበር እንዴ ? ኦሮምኛ ተናጋሪዎች እሳት ሲለኩሱና ንጽሃንን እያጋደሙ ሲያርዱ የሰላም መናጋት አይደለም እንዴ ? ነው በክልሉ ህገመንግስት ኦሮምኛ ተናጋሪ ወንጀለኛና አሸባሪ እንዳይቀጣ ተደንግጓል ?

ከፖሊሶቹ አጥፊ ተግባር ጎን ለጎንም የየከተሞቹ አስተዳዳሪዎችና ባለስልጣናት የፈጸሙት ሀገራዊ ክህደት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። የጭፍጨፋው ተግባር ክስድስት ሰዓታት በላይ በግልጽ ሲከናወን የራሳቸውን ፖሊሶች አስተባብረው ለመከላከል ያደረጉት ጥረት የይስሙላ ነው ወይም የለም ። አቅም ቢያንሳቸው እንኳ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት አድርገው የጥፋቱን መጠን ለመቀነስ ሲተጉ አልታየም ። እንደማንኛውም ነዋሪ ከሳቱ ዳር ቆመው ‹ ወይ ጉድ › ማለት አሊያም ሬሳ ሲጎተት ክንፈር መምጠጥ ህዝብን እናስተዳድራለን ብለው ሃላፊነት ከወሰዱ ዜጎች የሚጠብቅ አልነበረም ። እንዳልኩት የኢትዮጽያ በተለይ የኦሮሚያ ፖለቲካ ከቧልትም የዘለለ ነው ። ራስንና ህዝብን መከላከያ ጠመንጃ ይዞ ለዱላ የሚማረክ ወይም በግልባጩ ጠመንጃውን ተደግፎ አጥፊዎች ሲያጠፉ ጥርሱን እየፋቀ የሚታዘብ ፖሊስ ነው ያለን ። ይህን አይነቱን ፖሊስ ነው እንግዲህ ‹ ህዝባዊ › እያልን ማእረግ የምንሰጠው ። ይህንኑ ፖሊስ ወይም መከላከያን ጠርቶ ወንጀልን መከላከል ሲገባው ያላደረገን ባለስልጣናት ነው እንግዲህ  የ ‹ ለውጥ አቀንቃኝ › እያልን የምንጠራው ።

ነገሩ በእንቁላሉ ግዜ በቀጣሽኝ አይነት ነው ። መንግስት ገና በማለዳው የጃዋርና የኦነግ ቡድን የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች እያየ እንዳላየ ይክድ ነበር ። ህግ ይከበር … የህግ አለመከበር ንጽሃንን ብቻ ሳይሆን መንግስትን ያጠፋል እያልን ስንጮህ ምህዳሩን እናስፋ… ሆደ ስፊ እንሁን … ትእግስት ይኑረን እያለ ሲመልስ ነበር ። ምህዳር የሚሰፋው ህጉ በሚያዘው ህጋዊ ሜዳ ላይ እንጂ ህገወጥነትን እሹሩሩ በማለት አልነበረም ። በአንድ ሰው ሰበብ 86 ንጽሃን ሲገደሉ የህጋዊነት ጥያቄ እየተካደ ቆይቷል ። ማንም ክህግ በላይ አይደለም እያሉ የተወሰኑ ቡድኖች ሲገድሉ ፣ ሲዘርፉ ፣ ህዝብን በህዝብ ላይ ሲያነሳሱ ‹ እንታገሳቸው › የሚል ቀልድ እንሰማ ነበር ። ይህ ደግሞ ህግን አለማክበር ብቻ ሳይሆን ሚዛናዊነትን ማንሻፈፍ ለተለዩ ቡድኖች የተለይ ጥቅም የመስጠት ያህል ነበር ። ለዚያም ነው በግሌ ዶክተር አብይ ብዙ በጎነቶች ያሉት ቢሆንም ብዙ ድክመቶችም አሉበት ስል የነበረው ። ብዙ ድክመት ያልኩት በቁጥር ብዙ ሆነው ሳይሆን ‹ ህግ ማስከበር ያለመቻል › ጽንሰ ሀሳብ እንደ ብዙ ችግሮች ሊመነዘር በመቻሉ ነው ።

የዶ/ር አብይ መንግስት ለሀገር የሚያስፈልጉ ሶስት ማእዘኖችን ደጋግሞ ሲጠራ ይሰማል ። ሰላም ፣ ልማትና ዴሞክራሲ ። ልማትና ዴሞክራሲ እውን ሊሆኑ የሚችሉት ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው ። ሰላም የሚረጋገጠው ደግሞ በመፀለይ ብቻ አይደለም ፤ ይልቁንም ህግን በአስተማማኝ መልኩ አክብሮ ማስከበር ሲቻል ነው ። ሀገር የሚቆመው ቁጥር አንድ በሚባለው ህግ የማስከበር ተልእኮ ነው ። ወንጀልና ስርዓት አልበኝነት ልማትና ዴሞክራሲን እያረደ ሲመጣ እያየህ ልታገሰው ማለት አራጁ የቤትህን በር እስኪያንኳኳ መጠበቅ ማለት ነው ። አራጁ የኦሮምኛ ተናጋሪ ስለሆነ አራት ኪሎ አይደርስም የሚል ፌዛዊ የገበጣ ጨዋታም መንግስት ሲጫወት ታዝበናል ። በዚች ገበጣ የታቆሩት ጠጠሮች ግን የጥይትን ሚና ተክተው የመንግስት ባለስልጣናትን ለመግደል ወይም የመንግስትን ህልውና ለማፈራረስ መወንጨፍ ደረጃ ደርሰዋል ። መንግስት ህዝብ የሚሰጠውን አስተያየት ቀድሞ ቢሰማ ፣ መስማት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ቢያደርግ ኖሮ ዛሬ የደረስንበት ወዳሚ ምእራፍ ላይ ባልደረስን ነበር ። መንግስት ከሆንክ ህግንና ስርዓትን እንጂ ይሉኝታን ፖሊሲ ወይም መመሪያ ማድረግ የለብህም ። አሁንም ቢሆን ከልብ የመነጨ ህጋዊ አሰራር እንዲሰፍን መጠየቅ ግድ ይላል ። የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ገዳዮች በማይታመን ፍጥነት አድኖ ለፍርድ ማቅረብ ቢገርምም  ያስደስታል ። ይህ ሙሉ የሚሆነው ግን በየከተማው ህይወታቸውን ላጡ ንጽህ ነፍሶች ፍትህ ሲገኝ ነው ። ንብረታቸውን ላጡ በርካታ ዜጎች የፍትህ ስርዓቱ ተደራሽ መሆን ሲችል ነው ። አጥፊዎች በፍትህ አደባባይ ‹ አጥፊ › ፣ ገዳዮች በፍትህ አደባባይ ‹ ነፍሰ ገዳይ › ተብለው ህጋዊውን ቅጣት ሲከናነቡ ነው ።

ይህን አለማድረግስ አልከኝ ? … ይህን አለማድረግማ ፖለቲካዊ ሽፍጥና ብቻ ሳይሆን ልማታዊ አስተሳሰብን መቅበር ነው ። ይህን አለማድረግ ዜጎች በተለይም ባለሃብቶች ከኦሮሚያ ክልል ጋ እንዲቆራረጡ ማድረግ ነው ። ይህን አለማድረግ በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ብሄሮች ነገንም ጭራቅ  አድርገው እንዲስሉና ለስነልቦና ቀውስ እንዲጋለጡ በር መክፈት ነው ። መንግስት በተደጋጋሚ ሊታደጋቸው አለመቻላቸውን ከተረዱ ራሳቸውን አስታጥቀው ለመከላከል ይገደዳሉ - ይህ ደግሞ የምናዜምለትን ሰላም የማናጋት አቅም አለው ። ይህን አለማድረግ የነገ ውጤቱን አደገኛ ማድረግ ነው ። ክልሉ ፍትህን ባለማረጋገጡ ‹ ገዳዩ ወይም አስገዳዩ ክልል › የሚል መጥፎ ስያሜ እንዲያገኝ ይለፍ መስጠት ነው  ። የአዲስ አበባ ነዋሪም  ከክፉ የማያድነውን አስተዳደር ወደጎን ትቶ በራሱ ጎበዞች አማካኝነት ሌላኛው ቄሮ እንዲሆን ማበረታታት ነው  በመሆኑም ከእንግዲህ ሁላችንንም መዝኖ መዳኘት ያለበት ህግ ብቻ እንዲሆን እንፍቀድለት - ሆደ ሰፊነት የሚል ዲስኩር ይቁም ! የብልጽግና መንገዳችንን ብሩህ ለማድረግ ለእውነተኛ ፍትህ እንቁም !

Wednesday, June 24, 2020

ተሰርቆ የታሰረው ልጅ ታሪክ



ጥቅል ታሪክ

 « My name is Why » የተሰኘው የለምን ሲሳይ መጽሀፍ በራሱ የልጅነት ህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ስራ ነው ። መንግስት ልጅ ሰርቆ እስር ቤት ከቷል ፣ የህይወት ታሪኩም እንዳይታወቅ ድብቋል ይላል ደራሲው ገና ከመነሻው ። የለምን  እናት እንግሊዝ ሀገር ለትምህርት የደረሰችው በ1966 ዓም  ነበር ። በወቅቱ ነፍሰ ጡር ነበረች ፣ መውለጃዋ ሲደርስ ዊጋን አካባቢ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ደራሲውን ተገላገለች ። ብዙም ሳይቆይ አባቷ ስለታመሙ  ወደ ኢትዮጽያ  መመለስ ነበረባት ፤ ያኔ ነው እንግዲህ ህጻኑ ለአሳዳጊ ተላልፎ የተሰጠው ። ኖርማን ግሪንውድ የተባለ ስምም  አገኘ  

ለለምን ሲሳይ ህይወት ፈተና ነበረች ። ገና በ12 አመቱ ነበር አሳዳጊዎቹ ከቤት ያባረሩት ።  ከ 12 እስከ 17 አመቱ ደግሞ በአራት የተለያዩ ማሳደጊያ ቦታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ተወርውሯል ። በግራ እጁ ላይ NG / Norman Green wood / የሚል ንቅሳት ቢያጽፍም እውነተኛ ስሙ ይህ ንቅሳት አለመሆኑን የተገነዘበው በ 17 አመቱ ነበር ።

ደራሲው ለ30 አመታት ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ትግል ገጥሟል ። ትግል የገጠመው ከልጅነት እስከ እውቀት ሲመዘገብ የቆየው የህይወቱ ታሪክ / ማንነት / ተላልፎ እንዲሰጠው ነበር ። በ2015 የዊጋን ካውንስል ሃላፊ አራት ትላልቅ ዶሴዎችን አስረከቡት ። ከዚህ በኋላ ነበር ይህ መጽሀፍ የተወለደው ። ማንነቱን ለአለም ለማብሰር ስሙ ኖርማን ሳይሆን ለምን መሆኑን ለማስረዳት  ይደክማል ... MY Name is Why…

ስለ ልጅነቱ ፣ ስለትምህርቱ ፣ ስለ አሳዳጊዎቹ ስብእና ፣ ስለ ባህሪው ፣ እናቱ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ስለተፃፃፈቻቸው ደብዳቤዎች  ምን አለፋችሁ እያንዳንዱ ትንፋሹ ዶሴው ውስጥ እየተመዘገበ ነው የቆየው ። ደራሲው ደብዳቤዎቹን አባሪ በማድረግ ነው እንግዲህ ታሪኩን በቅደም ተከተል የሚተርክልን ።

ለአሳዳጊዎቹ ስለመተላለፍ

ህፃኑ ለምን ሲሳይ ሆስፒታሉ ውስጥ ለ 228 ቀናት ብቻውን ተኝቶ ነበር ። የዚህ መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ ዘረኝነት ነው ። ህፃኑን የጎበኘ ሁሉ ጥቁር መሆኑን በማየት ብቻ ቀኝ ኋላ ዙር ይላል ። መጨረሻ ላይ የግሪንውድ ቤተሰቦች እያመንቱ ‹ እስኪ ለማንኛውም በጥልቀት እንፀልይበት ›  ሲሉ መከሩ ፣ ከቆይታ በኋላም ፍቃደኝነታቸውን  ገልፀው ህፃኑን ተረከቡ ።

ይህ ሁሉ ፍጥጥም ጥር 3 ቀን 1968 የተደረገው  ያለእናቱ  ስምምነት ነው ። እናቱ ለአጭር ግዜ ትምህርት ስትመጣ ችግር ላይ ነበረች ። በመሆኑም የምትማርበት ኮሌጅ ርግዝናዋን አስመልክቶ ወደ ቅዱስ ማርጋሬት ነበር የላካት ። ለምንን በሰላም ከተገላገለች በኋላ የማደጎ ስምምነቱን ትፈርማለች ተብሎ ይጠበቅ ነበር ። ነገር ግን ማደጎ ምን እንደሆነ በሚገባ ታውቅ ስለነበር ስምምነቱን አልፈረመችም ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ አባቷ  በፀና በመታመማቸው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ነበረባት ። ቆይቶም ለምንን ጥላ በመሄዷ ልጁ በመንግስት ሃላፊነት ስር መውደቁን የሚገልፅ  ደብዳቤ በምትከታተልበት ቤተክርስትያን በኩል ተላከላት ። ተቃውሞ ካላትም በ30 ቀናት ውስጥ ብቻ እንድታቀርብ ያስጠነቀቀ ነበር መልእክቱ ።

ደራሲው ይህ ደብዳቤ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል በማስላት የተላከ ነው ባይ ነው ። ምክንያቱም ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለማስረዳት ብቻ  14 ቀናት ያስፈልጋል ፣ የተላከው መልእክት ኢትዮጵያ ለመድረስ አንድ ወር ወስዶበታል ይህ ማለት የእሷም ምላሽ ወይም አቋም እንግሊዝ ለመድረስ አንድ ወር ይፈጅበታል ። በሌላ በኩል በግዜው ከአዲስ አበባ ለንደን ቀጥታ በረራ አልነበረም ። ቦታው ለመድረስ ከአዲስ አበባ አቴንስ ፣ ከአቴንስ ደግሞ ለንደን መብረር ያስፈልጋል ፣ ይህ ማለት በተሰጠው የግዜ ገደብ መድረስ የማይቻል ነው በማለት ። ለምን ቅዱስ ማርጋሬት ሃውስን ከሚሰጠው ተግባር አንጻር በሚከተለው መንገድ ያጣጥለዋል

 « በመሰረቱ ይህ ቦታ የልጆች እርሻ ነው ። እናቶች መሬት ሲሆኑ ልጆች ደግሞ ሰብል ናቸው ። ቤተክርስቲያንና መንግስት ገበሬዋች ሲሆኑየማደጎ አሳዳጊዎች ደግሞ ተጠቃሚዋች ናቸው »

 ሰቆቃና መከራ

መምህርና ነርስ የሆኑት አሳዳጊዎቹ ሁለት ልጆች አላቸው ። ክርስቶፈርና ሄለን የተባሉ ። ለምን ክርስቶፈርን በአንድ አመት ይበልጠዋል -  ሄለን  በጣም ትንሽ ናት ። ክወንድሙ ጋር ጠረጴዛ ቴንስ ሲጫወቱ አውቆ ይሸነፍለት ነበር - እንዳይናደድ ።

ለምን በሰባት አመቱ ጠያቂ መሆን ጀምሯል ። ቤተክርስቲያን ሲሄድ ያልገቡትንና ቅር የሚሉትን  ነገሮች ሁሉ እንዴት  እያለ ይጠይቃል ። ጥያቄዋቹ  ምላሾች ነበራቸው « ሁላችንም ሃጢያቶች ስለሆንን » የሚል ። ትምህርት ቤት አካባቢ ለሚፈጠሩበት የዘርና የቀለም ጥያቄ ግን ምላሸ አላገኘም ። « እናትህ ጥላህ ሄደች … አትፈልግህም … እኔ ባገኘት አይኗን እቦጫጭረው ነበር … እንዴት አይነት ክፉ እናት ናት … » በትንሸ ጭንቅላቱ ይህን ጥያቄ ቤት ይዞ ይሄዳል - ምላሸ ለማግኘት ። የአሳዳጊው እናት መልስ ግን ወላጅ እናቱን አበክራ እንደምትጠላት የሚያስረዳ  ነበር ።

የህይወት ፋይሉ ላይ እንደተመዘገበው በስምንት አመቱ ብስኩት ሰርቆ በልቷል ፣ ቁራጭ ኬክ ሲወስድም ‹ እባክህ › እና ‹ አመሰግናለሁ › ሳይል ነው ። ሰርቆ መብላቱ ወላጆቹን ያበሳጫቸው ሲሆን ሰይጣን ውስጡ እንደገባ ያምኑ ነበር ። ደራሲው ኋላ ላይ High Profiles ለተባለ መጽሄት በስጠው ቃለመጠይቅ  « እጃቸውን ጭንቅላቴ ላይ ጭነው ሰይጣን ከዚህ ልጅ ላይ ውጣ ! » ይሉ ነበር ብሏል ።

አይወደንም ፣ ሰይጣናም ሆኗል ከሚሉ ምክንያቶች በተጨማሪ በ 12 አመቱ ለመባረሩ ምክንያት የሆነው የትንሿን ሄለንን ወሬ በመስማታቸው ነው ። ሄለን ለወላጆችዋ  ‹ ኖርማን ከእኔ በስተቀር ሁላችሁንም እገላለሁ ሲል ሰምቼያለሁ › ብላ ታወራለች ። ይህ ወቅት ገና ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተሸጋገረበት ነበር ። የስምንት አመት ልጅ ቤተሰቡን ሊጨርስ እየዛተ ነው ብሎ ማመን ብሎም የከፋ ርምጃ ይወስዳል ብሎ መደምደም ተቀባይነት እንደሌለው ደራሲው ይናገራል ።

አሳዳጊዎቹ ይህ ሰይጣንም ልጅ እንደማያስፈልጋቸው ውሳኔ ላይ ደረሱ ። እናም አንጠልጥለው  ለአንድ አሳዳጊ ድርጅት አስረከቡት ፣ ዝም ብለው ቢሄዱም ጥሩ ነበር ። ከዚህ ይልቅ የማይታይ አርጩሜ ህሊናው ውስጥ አስቀመጡ « እየመጣን አንጠይቅህም ፤ ድብዳቤም አንጽፍልህም » በማለት ። በደህናው ዘመን ወንድም ፣ እህት ፣ አክስት ፣ አጎት እና  አያት እንዳለው እንዳልሰበኩት « አውጥተው ሲጥሉኝ ማንም ሰው እንዳይገናኘኝ አድርገው ነበር » ብሏል በቁጭት ። ጥር 3 ቀን 1968 ዓም ተግባራዊ የሆነው የማደጎ ወላጆች ስምምነት ሰባት አንቀፆችን ይዟል ። አንደኛው ኖርማንን ልክ እንደራሳቸው ልጆች ማሳደግ እንደሚኖርባቸው ይደነግጋል  ። ሁለተኛው ደግሞ ልጁ የራሱን ሃይማኖት እንዲከተል ማድረግን ይመለከታል ። ክነዚህ ድንጋጌዋች አንፃር በለምን ላይ የደረሰው ቅጣት ከሚታሰበው በላይ ነው ። ለመሆኑ ለምን ስለአሳዳጊዎቹ ምን አስተያየት አለው የሚል ጥይቄ ቢነሳ የሚከተለውን የሚገርም ምላሸ ሲሰጥ እናገኘዋለን « በጣም ጥሩ ሰዎች ነበሩ ፣ መጥፎ ነገርን የሚያደርጉ »

የቦብ ማርሌይ ሞራላዊ ድጋፍ

በ 12 አመቱ ውድፊልድ ወደተባለ ማሳደጊያ ተቋም ሲገባ የእድሜ አቻዎቹ ቾኪኋይት የሚል ቅጽል ስም ሰጥተውት ነበር ። በዚህ ስፍራ ሰራተኞቹ ልጆች ሲጋራ ማጨስ እንደሌለባቸው አይመክሩም ይልቁንም የማጨሻ ልዩ ስፍራ አዘጋጀተዋል - እናም ማጨስ ለመደ ። በዚህ ስፍራ መፅሀፍ የለም ፣ አንብብ የሚል አበረታችም አይገኝም - በተቃራኒው ግን ለመጀመሪያ ግዜ ግጥም መፃፍ ጀመረ ። ግጥሙም ስለ ዛፍ የምታወሳ እንደነበረች ያስታውሳል ። ባልተጠበቀ መልኩ ግን ገጣሚ መሆኑን የተረዳችው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር « The Mersey sound » የተባለ የግጥም መፅሀፍ እንዲያነብ ሰጥተዋለች ። አሁንም በተቃራኒ እይታ ደራሲው ስለግጥሙ ይዘት አይደለም የሚነግረን - ገጣሚው በመጀመሪያ ገጹ ላይ ስለ ሙት ልጆች መፃፉን እንጂ ።

በአንድ ወቅት በጓደኛው ምክንያት ከቦብ ማርሌይ ስራዋች ጋር ተዋወቀ ። ቦብ ማርሌይ የመጀመሪያው ጥቁር ጓደኛ ፣ የመጀመሪያው ጥቁር መምህር ሆነለት ። በርግጥ ከ ቦብ የወሰደው ዘፈኑን ብቻ ሳይሆን አደገኛ እፅንም ጭምር ነበር ። ቦብ ለሰው ልጆች እኩልነትና ነፃነት ይጮሃል ፣ ስለ ጭቆና ስለ ታሪክ ስለ አለም እውነት ይናገራል ። ደራሲው ቦብን የወደደበት ሌላኛው ምክንያት በዘይቤያዊ አነጋገር የሚያስተላልፋቸው ውብ መልእክቶች ናቸው ። በዚህ ረገድ Ride Natty Ride በሚለው ዘፈን ውስጥ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ የሚለውን መጽሀፍ ቅዱሳዊ አባባል ለጉድ ይወደዋል ።

But the stone that the builder refuse
Shall be the head cornerstone
And no matter what game they play
We’ve got something they could never take away .

እናም ለመጀመሪያ ግዜ ከነጮች ባህር ውስጥ የተገኘ ጥቁር ሰው መሆኑን አመነ « በኔ ዙሪያ የተሰበሰቡ ሰዎች ሁሉ የኔን ዘርና ቀለም የካዱት የቀለም አይነስውርነት ስላለባቸው መሆኑን  አመንኩ » ብሏል

ጥቅል መደምደሚያ

በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ አውቶባዮግራፊና ሚሞይር ስለ አንድ ሰው ህይወት ስለሚያትቱና በአንደኛ ደረጃ የአጻጻፍ ይትበሃል ስለሚዋቀሩ የመመሳሰል ጸባይ ያላቸው ይመስላል ። ፈታ አድርገን ስንመለከታቸው ግን መሰረታዊ ልዩነት አላቸው ። አውቶባዮግራፊ የደራሲውን መላ ህይወት በቅደም ተከተል የሚዳሥስ ሲሆን ሚሞይር የደራሲው የተወሰነ የህይወት ክፍል ላይ አጠንጥኖ ይሰራል ። አውቶባዮግራፊ ታዋቂ ሰዎች ላይ ሲያተኩር ሚሞይር ሰው አይመርጥም ። ሰዎች ለማንበብ የሚፈልጉት አጠቃላይ ህይወቱን ቢሆን ከርእሰ ጉዳዩ ወይም ከጭብጡ አንፃር በመነሳት ነው ። አውቶባዮግራፊ ለእውነትና ታሪክ ልዩ ትኩረት ሲሰጥ ሚሞይር ስሜት ነክ ልምዶችን ይቃኛል ።

በዚህ ረገድ የለምን ሲሳይ ሚሞይር የማንነት ፍለጋ ላይ ላይ ያነጣጠረ ነው ማለት ይቻላል ። እናት ብትርቀው ፣ አሳዳጊ ቢገፋው ፣ ማህበረሰቡ ቢያገለው እንኳ ያላሰለሰ የራስ ጥረት ካለ ውጤት እንደሚገኝ ያስተምራል ። ለምን ሲሳይ እስከ 17 አመቱ አንድ አይነት ፣ ከ 17 አመቱ በኋላ ደግሞ ሌላ አይነት ሰው ነበር ። በ 14 አመቱ እጁ ላይ የነቀሰው Norman Greenwood አንደኛው ሲሆን ከ 17 አመት ጀምሮ ያወቀው ‹ ለምን ሲሳይ › ደግሞ ሁለተኛው ማንነት ነው ። ሁለተኛውን ማንነቱን ሲያገኝ የተረዳው ስሙን ብቻ ሳይሆን እውነተኛ እናቱን ፣ እውነተኛ ሀገሩን ፣ የጥቁርነቱን ምክንያትና የግጭቱን መሰረት ነው ። ለዚያም ነው ገጽ 137 እና 138 ላይ « የልደት ማስረጃዬ ላይ ያለው ስም ለምን ሲሳይ መሆኑን ለሚጠቁኝ ሁሉ እነግራቸዋለሁ » በማለት 90 ያህል ግዜ My name is Lemn Sisay ተደጋግሞ ተጽፎ የምናየው ። የድግግሞሹ ወይም / Alliteration / ሚና ትኩረት መጠቆሚያ ነው ።

ለምን ሲሳይ እውነተኛ ስሙንና ማንነቱን ካወቀ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ያልመለሰልን አንድ ጥያቄ አለ ። ርግጥ ነው በቅጣይ / Epilogue / ምእራፍ ላይ እናቱ የማርሸት ከአማራ ህዝቦች እንደተገኘች በዚሁ ክልል ባህል ደግሞ በመጀመሪያ ልጅ መልእክት ማስተላለፍ የተለመደ መሆኑን በመጠቆም ለምን ‹ Why › የሚል ፍቺ እንዳለው ያሰረዳናል ። ጥያቄው ግን ይህ አይደለም ። ጥያቄው እናቱ እንዴት ‹ ለምን › አሉት የሚለው ነው ። ከስሙ ፍካሬያዊ ፍቺ ከተነሳን ለምን ትምህርቴን ሳልጨርስ … ለምን በውጭ ሀገር …. ለምን ከጋብቻ በፊት … ወዘተ የተሰኙ ህሊናዊ ሙግቶች እንዳሉበት እንገነዘባለን ።

ስለምንነት ካወራን ደግሞ እናቱን አስታውሶ አባቱን መግደፉ መሉ አያደርገውም ። ለምን ሲሳይ ከመጽሀፉ ህትመት በኋላ በሰጣቸው ቃለመጠይቆች አበቱ የኢትዮጽያ አየር መንገድ አብራሪ እንደነበር ፣ በ1973 ከኢትዮጽያ ወደ ኤርትራ እየበረረ መብረቅ ክንፉን መቶት በሰሜን ተራሮች ላይ መሰዋቱን ተናግሯል ። ሰሜን ተራራሮችን ከጎበኘ በኋላም ለአባቱ ግጥም መጻፉን አስረድቷል ። እነዚህ ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች በድሉ የመጨረሻ ምእራፍ ላይ ቢዳሰሱ የበለጠ ጠንካራ ያደርገው ነበር ።

ደራሲው በዚህ ስራው የተበላሸ የማደጎ ስርአት አሰራርን አጋልጦበታል ። የቸልተኛ ባልስልጣናትን የተረገመ ተግባር እንዲሁም የቢሮክራሲን ጭካኔ አሳይቶበታል ።  በዘር ፣ በቀለምና በሞራል ላይ የሚደረገውን ልዩነት ኮንኖበታል ። በ 30 ምእራፎች የተከፋፈለው ስራ ሁለት ልዩ ባህሪያት አሉት ። የመጀመሪያው አብዛኛው ምእራፍ ከመረጃ ጋር ተሰናስሎ የመቅረቡ ጉዳይ ነው ። ሁለተኛውና ዋነኛው ሀሳብ ሁሉም ምእራፎች የሚጀምሩት በ ኳትሬይን / Quatrain / አይነት ግጥሞች መሆኑ ነው ። ለአብነት ያህል በምእራፍ  14 ላይ የሚከተለውን  ግጥም እናገኛለን
 
Night can’t drive out night
Only the light above
Fear can’t drive out fear
Only love

ጨለማን ጨለማ አያባርረውም
ብርሃን እንጂ
ፍርሃትን ፍርሃት አያባርረውም
ፍቅር እንጂ

ግጥሞቹ በቀጣይ ከምናነበው ታሪክ / ሃሳብ / መረጃ ጋር እናገናኘው ካልን ሊገኛኝ ይችላል ። እነዚህ  ባለ አራት መስመር የግጥም ስንኞች በተለይ በእንግሊዝ ስነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ላቅ ያለ ሚና አላቸው ። ርግጥ ነው ይህ ስነጽሁፋዊ ዘውግ በጥንታዊ ቻይና ፣ ሮም ፣ ግሪክ እና ህንድ ቀደምት ልእልና ነበረው ። ቀጥሎም በአውሮፓ የጨለማው ዘመን በስፋት ተሰርቶበታል ። በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ኦማር ካያም ሩባያ በሚል ስያሜ ገኖበታል ። በተመሳሳይ መልኩም ኖስትራዳመስ ለዝነኛ ትንቢቶቹ መጠቀሚያ አድርጓቸዋል ።

ታዲያ ለምን ሲሳይ እነዚህን የግጥም አይነቶች በምን አላማ ተጠቀመባቸው ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል ። ግጥም ያለውን ትልቅ ጉልበት ለማሳየት … ግጥም መጻፍ የጀመረው እስር ቤትን በሚስተካከሉ/ እንደርሱ አመለካከት /  የህጻናት ማቆያ ቦታዎች መሆኑን ለመዘከር … በስቃይና ችግር ያሳለፈውን የልጅነት ህይወት ያቃለለት ኪነጥበብ / ግጥምና ሙዚቃ / መሆኑን አስረግጦ ለማስረዳት … ጽሁፉን ተነባቢ ለማድረግ … ወዘተ ማለት ይቻላል ። እንደ እኔ እምነት ግን ባለአራቱ ስንኞች ገዝፈው የተቀረጹት በአራት አስቸጋሪ ማሳደጊያ ቦታዎች ህይወቱን መምራቱን ተምሳሌታዊ ለማድረግ በመፈለጉ ነው ።

Friday, June 19, 2020

የፍትህ መዶሻ ይዛ ፍትህ የምትጠይቅ ሀገር



ኢትዮጽያ አይኗን በጨው ካጠበችው  ግብፅና አይኗን በአግባቡ መታጠብ ካቃታት ሱዳን ጋር እሰጥ አገባ ከገባች አመታትን አስቆጠረች ። ድርድሩ የፓለቲካውና ዲፕሎማሲውን መንገድ ይከተል በሚል እንጂ በጉንጭ አልፋው ንግግር  ውጤት ይገኛል ተብሎ አይጠበቅም ።

ፈጣጣዋ ግብፅ የቅኝ ግዛቶችን ውል ከትከሻዋ ላይ ማውረድ አትፈልግም ። ከግፈኛዋ እንግሊዝ የተቀበለችውን የውሃ ድርሻ እንደ ጄነራል ክፍ አድርጎታል ። ይህን ማእረግ ወደ ሻምበልነት የሚያወርድ ተጋፊ ሃይልን አትቀበልም ። እናም በእሷ ቀመር የውሃው ባለቤትነት የሚመዘነው ከሚመነጭበት ቦታ ሳይሆን በተፈጥሮ ቀድሞ በያዘ ነው - ላለው ይጨመርለታል የሚባለውን የወንጌል ጥቅስ እንድናስታውስ በማድረግ ።

ሱዳን ከቅኝ ገዢዋ መሃንዲስ የሚበቃትን ያህል ድርሻ ተቀብላለች ። የአባይ ወንዝና የግድቡ ወሬ ሲነሳ የምታዳምጠው አይናር የማይጠፋውን አይኗን እየሞዥቀች ነው ። አይናሩ ሲለቃት ግድቡ ይጠቅመኛል ከኢትዮጽያ ጎን ነኝ ትላለች ። አይናሩ አንቆ ሲይዛት የግብጽ ማስፈራሪያ ነው ቀድሞ የሚሰማት ። ያኔ ግብፅን በአረብኛ ማናገር ትጀምራለች - አቋም እንዲኖራት አትፈልግም ።
እነዚህ ሀገሮች ከያዙት ሀገወጥ ጥቅምም ሆነ ከሚያስተሳስረቸው ፖለቲካዊ ውግንና አንጻር ወደ መሃል ተስበው የሚመጡ አይደሉም ። ወደታች ወርደው የእውነት ባልጩት ላይ ከቆሙ ድንጋዩ ያበቀለው አልጌ አዳልጦ እንደሚጥላቸው ይረዳሉ ። የሚደራደሩት አዲሱን እውነት ለመቀበልና የቆየውን ክብር ለማጣት አይደለም ።

ለዚያም ነው በተለይ ግብፅ ከድርድር ይልቅ አደራዳሪን ምርኩዝ ማድረግ የምትመርጠው ። ለቡራኬ ሰጪዎች ትልቅ ቦታ አላት ። ድሮ ለዚህ ያበቃቻት እንግሊዝ ዛሬ ባትጠቅማትም አሜሪካንን መተካት አላቃታትም ። ትላልቆቹ በስሟ እንዲያስፈራሩላትና የረባሽ ሀገራትን ጆሮ እንዲቆነጥጡላት ትፈልጋለች ። የያዘችው እውነት ለዛሬው አለም ባይሰራም አይኗን አፍጣ አለም መንግስታት ፊት ስሞታ ታቀርባለች ። ጩኸቷን እንዲጮሁላት አጥብቃ ነው የምትሰራው ። አልፋም ትሄዳለች - ሁሉንም አማራጮች እጠቀማለሁ የሚል ማስፈራሪያ በመልቀቅ ።

እንደሚታወቀው የውሃው መነሻም ሆነ የግድቡ መድረሻ ከኢትዮጽያ ነው ወይም ኢትዪጽያ ናት ። በውሃ የመጠቀም አለማቀፋዊ መብቷ ጥያቄ ውስጥ ባይገባም የምትደራደረው ግን በድርድር ተጎጂልን ከሚሏት ፈጣጣ ሀገራት ጋ ነው ። ድርድሩን አለም ይውቅልኝ ፣ ፍትሃዊነቱንም ይገንዘብልኝ የምትለው የሌሎችም አጋር መሆናን ለማሳየት ነው ። ሀገሬ ግን ነገ ጠባ እየከሰሷት ፣ አለፍ ሲልም እያስፈራሯት ፍትሃዊ አካሄዴ ይታወቅልኝ በሚል ባዘነች ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግድቡን ለመስራትም ሆነ ውሃውን ለመሙላት የማንንም ፍቃድ መጠየቅ አያስፈልግም ። መጠንቀቅ ያለብን ሌሎችን በጭፍን ጥላቻ ላለመጉዳታችን ብቻ  ነው ። ከዚያ ውጪ ወንዙም ግድቡም የኛ ነው ። በያዝነው ነገር ላይ መያዛችንን ከማይቀበል ቡድን ጋር ለምን ሃይላችንን እናጠፋለን ? ብለህ ብለህ አልቀበል ካለህ የያዝከውን አስተማማኝ የፍትህ መዶሻ በራስህ ጠረጼዛ ላይ መምታት ተገቢ ነው ። ከዚያ ለፍርድ አፈጻጸም ወደሚመለከተው አካል በየአድራሻው መላክ - ይኅው ነው ። ውሃውን መሙላት ስትጀምር ትላንት አልቀበል ያለህ ሁሉ ሰልፉን ካንተ ጋ ያሳምራል ፤ ቋንቋውንም ይለውጣል ። ዋ ! የሚልህን ረስቶ ‹ እባክህ › ማለት ይጀምራል ። አለም የምታሳየን እውነት ይሄንን ነው ። ከወሬው ቀንሰን ይህን ለማድረግ እንፍጠን ። ያኔ የመታኸው መዶሻ ጠብቆ መግባቱን ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ ትክክል መሆኑን ትገነዘባለህ ።

በርግጥ ሌሎችን ተደግፎም ሆነ በራሱ የሚያስፈራራው ቡድን ምንም አያመጣም ብሎ መዘናጋት ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ። ግልጽ ጦርነት ባይከፍትብህ እንኳ ሌሎችን በገንዝብ በመግዛት ጥቅምህን ለመናድ ሌት ተቀን ይሰራል ። ሱዳን እና የኛ ሀገር ባንዳዋችን በዋናነት እንደሚጠቀም መጠራጠር አይኖርብንም ። ግድቡ ድንበር ላይ እንዲሰራ መደረጉ ምናልባት የሚጎዳንም በዚህ መሰሉ አጣብቂኝ ግዜ ነው ። እናም በአንድ በኩል ግድቡን ለመጨረስ እየተጉ በሌላ በኩል ግድቡንና አካባቢውን በአስተማማኝ መከላከያ ማጠር ያስፈልጋል ። የሀገር ቤቶችን ባንዳዎች እግር በእግር ተከታትሎ ግባቸውን ለማጨናገፍ ፣ የጆሮ ጠቢውን መስሪያ ቤት ሚና ከመቼውም ግዜ በላቀ መልኩ ማሳደግ ተመራጭ ይሆናል ።

Sunday, June 7, 2020

የእንግሊዝ ሃውልቶች አዲስ ፈተና …




ኤድዋርድ ኮልስቶን የብሪስቶል ነዋሪዋች ኩራት ነበር ። ሲበዛ ቅን ነው ይሉታል - ተወላጆቹ ። ኋላ ላይ ከተማዋን እየተቀላቀሉ የመጡ ጥቁሮችና ሌሎች ግን የክፋት መጨረሻ እንደሆነ ነው የሚሰማቸው ። ከነጋዴ ቤተሰቦቹ በ 1636 ተወልዶ በ 1721 ዓም አረፈ ። እዚህ ከተማ ላይ ሃውልት የቆመለት በ 1895 ሲሆን መሰረታዊው ምክንያት በጎ አድራጊነቱ ነው ። በኖረበት ዘመን ለበጎ አድራጊ ድርጅቶች ከ 71 ሺህ ፓውንድ በላይ ለግሷል ። ለትምህርት ቤቶች ፣ ለእምነት ተቋማትና ለሆስፒታሎችም በመርዳት ስሙ ይጠቀሳል ። አንዳንዶች የገንዘብ ምንጩ ቱባ ነጋዴ በመሆኑ ነው ይበሉ እንጂ ብዙዋችን የሚያስማማው ጥቁሮችን በመሸጥ ያካበተው ነው ።

የዚህ ሃውልት ህጋዊነት ለበርካታ ግዜ የብርስቶል ከተማን ህዝብ አወያይቷል ፣ አጨቃጭቋል ። የሰውየው ሌጋሲ ለምሳሌነት አይበቃም በሚል የሃውልቱን መቆም የሚቃወሙት ሰሚ ሳያገኙ ቆይተዋል ። ዛሬ ከ 125 አመታት በኋላ ‹ ታላቁ › ኤድዋርድ ኮልስቶን አደባባይ ላይ በትዝብት እንደቆመ አልቀጠለም ። ዘረኝነትን በሚቃወሙ / Black Lives Matter / ሰልፈኞች እንደ በሬ በገመድ ተጠልፎ እንዲወድቅ ተደርጓል ። ከወደቀ በኋላ እንደ ሳዳም ሁሴን ሃውልት ተረግጧል ፣ ተተፍቶበታል ፣ ተረግሟል ። እንደ ጆርጅ ፍሎይድ ገዳይ አንገቱ ተረግጦ ‹ መተንፈስ አልቻልኩም › እንዲል ተጠብቋል ። በመጨረሻም ድሮ ባህር አቋርጠው አውሮፓና አሜሪካ የመጡ ጥቁሮችን ያስታውስ ዘንድ ይመስል ወደ ባህር ተጥሏል ።

ኤድዋርድ ኮልስቶን በ1689 ጥቁሮችን እያስመጣ በመሸጥ በሚታወቀው / Royal African Company / ድርጅት ውስጥ ምክትል ሃላፊ ነበር ። በዚህ ካምፓኒ ውስጥ እየሰራ 84 ሺህ 500 የሚደርሱ ጥቁሮችን በመርከብ አጓጉዟል ። ከዚህ ውስጥ 23 ከመቶ ወይም 19 ሺህ 300 ያህሉ ወደብ ሳይደርሱ መንገድ ላይ በውሃ እጥረት ፣ በተቅማጥና በንጽህና ጉደለት ሞተዋል ። ይህ ሰው ሌላም የሚታወቅበት ጉዳይ አለ ። በ 70ቹ እድሜው የፓርላማ አባልነቱን ተጠቅሞ የባሪያ ንግድ እንዲስፋፋ ፔቲሽን እስከ ማሰባሰብ ደርሷል ።

እንግሊዝ ለህብረተሰቡም ሆነ ለሀገር ጥሩ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብለው የሚታሰቡ / በክፉም ሆነ በደግ /  ስመጥር ዜጎችን ሃውልት በማቆም በቀጣዩ ትውልድ እንዲታወሱና እንዲዘከሩ የማድረግ የረጅም ግዜ ባህል አላት ። አንዳንድ መረጃዋች እንደሚጠቁሙት በመላው ሀገሪቱ ከ828 የሚበልጡ ሃውልቶች በተለያዩ ከተሞች ቆመዋል ። እስካሁንም አንዳቸውም ላይ በተቃውሞ መልኩ የመፍረስ አደጋ አላጋጠማቸውም ። ነገር ግን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ያልተለመዱ ትችቶችን ያስተናገዱ ሃውልቶች ታይተዋል ። ሁለተኛ አለም ጦርነትን ለማስታወስ በተደረግ ዝግጅት ላይ አንዳንድ ሃውልቶች ላይ ACAB የሚል ጽሁፎች ተነበዋል - All Cops are Bastars የሚል ትርጉሙ እንደያዙ ተገምቷል ።በቅርቡ ለንደን ውስጥ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍም የቀድሞው የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ሃውልት ላይ ዘረኛ ነበር የሚል ጽሁፍ ተለጥፎበት ነበር ።

በአንድ በኩል « የባሪያ ንግድ ውርስ ነው » በሌላ በኩል « አይደለም የበጎ አድራጎነት ምልክት ነው » እየተባለ ሲያጨቃጭቅ የኖረው ሃውልት መፍረሱ የእንግሊዝን መንግስት አስቆጥቷል ። የሆም ሴክሬቴሪ ሃላፊ ፕሪቲ ፓታል ድርጊቱን አሳፋሪ በማለት ተጠርጣሪዋቹን እንፋረዳለን ብለዋል ። በነገራችን ላይ ኤድዋርድ ኮልስቶን በብርስቶል ከተማ በስሙ የኮንሰርት አዳራሽ ፣ ጎዳና እና ትምህርት ቤት ተሰይመውለታል ። ትግሉ እነዚህም እንዲፈርሱ ይዋጋል ወይስ ባፈረሰው ሃውልት ተጠያቂ እስከመሆን ይደርሳል ? እየከረረ ከመጣው የእንግሊዝ ተቃውሞ አንጻር ይህን ጥያቄ በቀላሉ መመልስም ሆነ እንደዋዛ መተውም የሚቻል አይሆንም ።

Saturday, April 11, 2020

ከአዳም ረታ ‹ አፍ › እስከ መንጌ ‹ እንባ ›…



የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ የመከላከያው አንደኛው መንገድ በራስ ላይ ማእቀብ መጣል ነው ፤ ቤት ውስጥ መከተት ። ቀኑን ለመግፋት ታዲያ በሆነ ስራ መጠመድ ግድ ይላል ። የቤት ስራ ባይሆንልኝም የማንበብ ልምዴ ድብርትን ታድጎታል ። ምክንያቱም ሁለት ተጋምሰው የነበሩ እና ሁለት ያልታዩ መጽሃፍትን እንዳጣጥም ስለረዳኝ ። ስራዎቹ የዶ/ር አለማየሁ ዋሴ « እመጓ » ፣ የአዳም ረታ « አፍ » ፣ የለምን ሲሳይ « My name is Why » እና የሀብታሙ አለባቸው « የቄሳር እንባ » ናቸው ። በአንዳንዶቹ ላይ ሰፊ ትንታኔ ከመስራቴ በፊት አጭር ምልከታዬን እንካችሁ ፤ ታነቧቸው ዘንድም ስሜቴን ለመጋባት ።

 በቀላል አቀራረብና ቋንቋ የተጻፈው « እመጓ » ምርጥ ሃሳብ የያዘ ስራ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ። ይህ መጽሐፍ ያስታወሰኝ የግራም ሃንኩክን The Sign and The Seal  / ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ / የተባለ ስራ ነው ። ሃንኩክ ቅዱስ ጽዋ ሊገኝባቸው ይችላል ብሎ ከሚጠረጥራቸው ሃገሮች አንደኛዋ ኢትዮጽያ ናት ። የአለማየሁ ዋሴ « እመጓ »ግን ቅዱስ ጽዋ መንዝ ውስጥ ይገኛል የሚለው በርግጠኝነት ነው ። ይህን የሚያዳብሩት ታሪካዊ ፣ ሃይማኖታዊና መላምታዊ መረጃዋች በሚያስደምም ቅንብር ይተረካሉ  ። ቅዱስ ጽዋ የሚገኘው ቫቲካን ፣ ለንደን ፣ ማርሴይ ፣ ቆጽሮስ ፣ ደማስቆ ወይም ኬብሮን ሳይሆን ኢትዮጽያ ነው ይላል ተራኪው ሲሳይ ። እመጓ በእንግሊዘኛ ተተርጉሞ ሃንኩክም ሆነ ያገባናል የሚሉ ሀገሮች ቢያነቡት እንዴት መልካም ነበር ብያለሁ ።

የአዳም ረታን « አፍ » የጨረስኩት እንቅፋት እየቦዳደሰኝ ነው ። ዋናውን ታሪክ ይዤ ስጓዝ ድንገት ብቅ ከሚለው « የግርጌ ማስታወሻ » ጋር እጋጫለሁ ። ማስታወሻው በጣም ረዝሞ ዋናውን ታሪክ ይገዳደራል ፣ አንዳንዴ ደግሞ ማስታወሻ አይደለም ራሱን የቻለ ተዛማጅ ታሪክ እንጂ የሚያሰኝ ቅርጽ ይታይበታል ። ለምሳሌ ያህል ዋናው ታሪክ ላይ የገለታ ጉንጭ ስንቡክ ነው ይላል ። ስንቡክ የሚለው ቃል አናት ላይ አንድ ቁጥር ተጽፏል ። እንግዲህ ይህን ስንቡክ ይረዱ ዘንድ ነው ሶስት ገጽ የሚያነቡት ። አዳም ሰላሳ ያህል የማስታወሻ / የታሪክ / ቁጥሮችን ተጠቅሟል ። አንዳንዴ ለብቻው ተሰምሮ የተቀመጠውን « የግርጌ ማስታወሻ » ጨርሼ ወደ ኋለ ስመለስ ዋናው ታሪክ ይጠፋብኛል ። ። የልቦለዱን ቅርጽ ለየት የማድረግ መንገድ የመሻት ሃሳብ ይመስላል ። እንደሚታወቀው አዳም ብዙ ቅርጾችን አሳይቶናል - ጥሩዎችም ነበሩ ። ይህኛው ግን በጣም ያደክማል ። እንደኔ እንደኔ አዳም ረታ ታላላቅ ሃሳቦች /ይዘት / ላይ ቢያተኩር እመርጣለሁ ።

የለምን ሲሳይ « My name is Why » በራሱ የልጅነት ህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ስራ ነው ። መንግስት ልጅ ሰርቆ እስር ቤት ከቷል ፣ የህይወት ታሪኩም እንዳይታወቅ ድብቋል ይላል ደራሲው ገና ከመነሻው ። የሲሳይ እናት እንግሊዝ ለትምህርት የደረሰችው በ1966 ነበር ። በወቅቱ ነፍሰ ጡር ነበረች ። መውለጃዋ ሲደርስ ዊጋን አካባቢ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል በ1967 ደራሲውን ተገላገለች ። በወቅቱ አባቷ ስለሞቱ ወደ ሀገሯ መመለስ ነበረባት ፤ ያኔ ነው እንግዲህ ኖርማን ግሪንውድ ተበሎ ለአሳዳጊ የተሰጠው ። እናቱ ወደ ሀገሯ ስትመለስ ልጅዋ ለአሳዳጊ ተላልፎ እንዲሰጥ ፍቃድዋን አልሰጠችም ።

ለለምን ሲሳይ ህይወት ፈተና ነበረች ። ገና በ12 አመቱ ነበር አሳዳጊዎቹ ያባረሩት ። አሳዳጊዎቹ ለሁለቱ ልጆቻቸው የሚያሳዩት ፍቅር፣ ክብርና እንክብካቤ ለእሱ የራቀ በመሆኑ ነው ግጭቱ እንዲያድግ ምክንያት የሆነው ። ከ12 እስከ 17 አመቱ ደግሞ በአራት የተለያዩ ማሳደጊያ ቦታዎች ተወርውሯል ። በግራ እጁ ላይ NG የሚል ንቅሳት ቢያጽፍም እውነተኛ ስሙ ይህ ንቅሳት አለመሆኑን የተገነዘበው በ17 አመቱ ነበር ። ደራሲው ለ30 አመታት ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ትግል ገጥሟል ። ትግል የገጠመው ከልጅነት እስከ እውቀት ሲመዘገብ የቆየው የህይወቱ ታሪክ ተላልፎ እንዲሰጠው ነበር ። በ2015 የዊጋን ካውንስል ሃላፊ አራት ትላልቅ ዶሴዎችን አስረከቡት ። ከዚህ በኋላ ነበር ይህ መጽሀፍ የተወለደው ። ማንነቱን ለአለም ለማብሰር ስሜ ኖርማን ሳይሆን ለምን ነው በማለት የሚደክመው MY Name is Why…

ስለ ልጅነቱ ፣ ስለትምህርቱ ፣ ስለ አሳዳጊዎቹ ስብእና ፣ ስለ ባህሪው ፣ እናቱ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ስለተፃፃፈቻቸው ደብዳቤዎች  ምን አለፋችሁ እያንዳንዱ ትንፋሹ ዶሴው ውስጥ እየተመዘገበ ነው የቆየው ። ደራሲው ድብዳቤዎቹን አባሪ በማድረግ ነው እንግዲህ ታሪኩን በቅደም ተከተል የሚተርክልን ። በአሳዳጊዎቹ ብቻ ሳይሆን በቆዳ ቀለሙ ይደርስበት ስለነበረው ዘረኛ ጥላቻ ይነግረናል ። አካላዊና ሞራላዊ ጥቃቱን ሳያማርር ተርኳል ። እዚህና እዚያ የምትላጋው ህይወቱ ከክፋት አንፃር ከአንደንዥ እፅ ጋር ያስተዋወቀችውን ያህል ፤ በጥሩ ጎን ሲታይ ደግሞ ገና በ12 አመቱ ብእርና ወረቀት አዋዶ መግጠም እንዲችል ጥሪውን አሳይታዋለች ። ዛሬ ይህ ሰው በምድረ እንግሊዝ አንቱ የተባለ ገጣሚ ነው ። በ2015 ታላቅ ተግባር ለፈፀሙ ሰዎች የሚሰጠውን Order of the British Empire ተሽልሟል ።

የሀብታሙ አለባቸውን « የቄሳር እንባ »ን እንደተለመደው በተመስጦ ነው ያነበብኩት ። የቄሳር እንባ የውድቀትና የስንብት እንባ ነው ። የመጽሀፉ ዛቢያ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ሲሆኑ በእሳቸው ዙሪያ ቤተሰባቸውና ዘመዶቻቸው ፣ ደርግና ጦር ሰራዊቱ ሲሽከረከሩ እንመለከታለን ። ጦርነት ፣ ንቅዘት፣ በስልጣን መባለግና ፖለቲካዊ ድንቁርና ለአብዮታዊ ስህተት መነሻ ሆነው ብዙ ዋጋ ሲያስከፍሉ እንታዘባለን ። ደራሲው በሱፍ አበባ ላይ « ገበርዲን » እንዳለው የፍልስፍና ሃሳብ እዚህ ስራ ላይም « ልግመት ሶሻሊዝም»ን አስተዋውቆን የፓለቲካውን ግለትና ቆፈን እንዲሁም መነሻና መድረሻውን ያብጠረጥረዋል ። የቄሳር እንባ የሴራ አወቃቀርና የገፀባህሪ አሳሳል ድንቅ ነው ። ፓለቲካዊ ትንታኔውና የፍቅር በከራው አንባቢን ላይና ታች ይንጣል ።

በነገራችን ላይ ሀብታሙ አለባቸውን ለመጀመሪያ ግዜ በስራው ያወኩት በ « አውሮራ » ነው ። የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት መሰረት ባደረገው በዚህ ስራ ተደንቄ ነበር ። በድርጊትና በመረጃ የደነደነ ፈጣን ታሪክ አለው ። ፍቅርና ጦርነትን በእኩል ጥፍጥና ከሽኖ የቀረበ የምናብ ውጤት ነበር ማለት ይቻላል ። ቀጥሎ ደግሞ « የሱፍ አበባ» ን አነበብኩ ። የኢህአፓ ዘመንን ድብብቆሽና ፍልሚያ ። ይህም መጽሀፍ ፍልሚያና ፍቅርን ተራ በተራ እንኮኮ ሲያደርግ አይደነቃቀፍም ። በዚህ መጽሀፍ የፖለቲካ ቅኔ ብቻ ሳይሆን የፍልስፍና ጥብብም ሲደንስ ታይቷል -  የሚያምር ብእር ። ለሶስተኛ ግዜ ደግሞ የቄሳር እንባን ።

ደራሲዋች አንዳንዴ ጥሩ ስራ ሲያቀርቡ ሌላ ግዜ ደግሞ ከደረጃ ይወርዳሉ ። በሀብታሙ ስራዋች ላይ የወጥነት ችግር አላየሁም ። በተከታታይ ምርጥ መሆን መታደል ብቻ ሳይሆን ልዩ ችሎታን ይጠቁማል ። የሚያነሳቸው ርእሰ ጉዳዮች ወይም ጭብጦች ትላልቅ ናቸው ። በኢትዮጽያ ስነፅሁፍ ደረጃ ያጣናቸውን ወይም ያልታዩ ክፍተቶችን ነው እየሞላልን የሚገኘው ። ይህ ደራሲ ከምንም በላይ እውቀትን መሰረት አድርጎ ነው የሚጽፈው ። ብዙ ያነበበ ወይም ብዙ ለፍቶ የሚጽፍ መሆኑን ስራዎቹ አፍ አውጥተው ይናገራሉ ። ምናለፋችሁ የደራሲውን ቀሪ ስራዋች ማለትም ‹ ታላቁ ተቃርኖ › እና ‹ አንፋሮ ›ን ለማንበብ ቸኩያለሁ ።



Thursday, February 13, 2020

ተስፋዬ ገብሬ ያስፈልገናል



እናት ኢትዮጽያ ውዲቷ ሀገሬ
በጣም ይወድሻል ተስፋዬ ገብሬ

በዚህና በመሳሰሉት ጥቂት ዘፈኖቹ እኛም እንወደው እናከብረው ነበር ፡፡ ዛሬ ደግሞ ማርቆስ ተግይበሉ በተባለ አጥኚ አማካኝነት / የበጎ ሰው ሽልማት የሚገባው / በስፋት አወቅነው ፡፡ ያልተሰሙ ሙዚቃዎቹን አዳመጥን .... ያልተሰሙ የህይወት ታሪኮቹን ሰማን ... ያልተነገሩ ህመሙን ፣ ህልሙንና ስሜቱን ተጋራን ፡፡

ተስፋዬ ገብሬ በብዙ ቋንቋዋች ዘፍኗል ፡፡ ጥበቡን ለጥበብነት ማቀንቀኑ ብቻ ሳይሆን ብዙ ርምጃ ተጉዞ ስለ ሀገሩ ኢትዮጽያ ለውጩ አለም ሰብኳል ፡፡ የቀለምና ቋንቋ ልዩነት ሰብዓዊነትን በደፈጠጠበት በዛን ወቅት ሙያውን ለማንገስ ፣ ስውነቱን ለማስከበር  ብሎም ሀገራዊ ክብሩን እንደ ሰንደቅ ከፍ አድርጎ ለማውለብለብ የላቀ ሚና ተጫውቷል _ እሱ እንደሚለው በነጮች ሰፈር ብቸኛው ጥቁር አቀንቃኝ በመሆን ፡፡

በአርትስ ወግ ላይ የቀረበው የተስፋዬ ገብሬ ተከታታይ ፕሮግራም አስደሳች፣ አሳዛኝና ልብ የሚነካ ነበር ፡፡ ለሀገሩ፣ ለቤተስቡና ለህዝቡ  የነበረውን ጥልቅ ፍቅር በመለኪያ ቀምሮ ይሄን ያህል ነበር ለማለት ይከብዳል ፡፡ ሀገሩን ውዲቷ እንዳላት ሁሉ አባቱ አቶ ገብሬንም በስም እየጠቀሰ አወድሷል ፡፡ ሌላው ቢቀር የሀገሩ ተራራና ዛፎቹ ምን ያህል እንደናፈቁት እንዲያውቁለት ይመኝ ነበር ፡፡ እስትንፋሱ እስከተቋረጠበት እለት ድረስ ታላቅ ክብር ስለሚገባት ኢትዮጽያ ልብ በሚያርደው ድምፁ አቀንቅኗል ፡፡

ወደድንም ጠላንም የተስፋዬ ገብሬ ዜማና ሀሳብ ዛሬም ያስፈልገናል ፡፡ ለታመመችው ፣ ለቆሰለችው ከዚያም አልፎ ስጋት ተራራ ላይ አቁመው ክኋላ በርግጫ ቁልቁል ለመጣል ላሰፈሰፉት < እንክርዳድ > ልጆቿ የተስፋዬ ዜማና ሀሳብ መታደጊያ መንገድ አለው ፡፡ ተስፋዬ እናት ነው ነው የሚላት ፟ ኢትዮጽያን ፡፡ የላቀች መሆኗን ለማሳየት ውዲቷን ይጠቀማል ፡፡ ይሄ ሁሉ አልበቃ ብሎት በጣም እወድሻለሁ እያለ ነው ፡፡ በጣሊያንኛና በእንግሊዘኛ የሚወዳት ሀገሩን ሌሎች እንዲያውቁለትና እንዲወዷት መፅሀፍ አዘጋጅቷል / ወደፊት ያገባናል ባዮች ካሉ ሊታተም የሚችል / ካሴቱና መፅሃፉ ተሸጦ እንዲሰጥለት የተናዘዘው ደግሞ ውሃና መብራት ለሌላቸው ህዝቦች ነበር ፡፡

በተቃራኒው ዛሬስ ?...  < እቺ ሀገር ...  > እያለ የሚያንጠለጥላት ህዝብ ቁጥሩ ቀላል አይደለም ፡፡ ሀገሩን በእናቱ ለመመሰልም ሆነ ውዴ ብሎ ለመጥራት በራስ የመተማመን ትከሻ አጥቷል ፡፡ ወሽመጡ በራሱ አይናፋርነት ወይም በፖለቲካ ያገባናል ባዮች ሴራና ማስፈራሪያ ተበጥሷል ፡፡ ስለወለደችው ኢትዮጽያ ሳይሆን በማደጎነት ሰለተሾሙለት ክልሎች አብዝቶ ተጨናቂ ሆኗል ፡፡ እውነቱ ግን የሺህ እንጀራ እናቶች ልጥ የአንዷን ወላጅ እናት ፍልጥ ለማሰር አለመቻሉ ነው ፡፡

ዜማችንም ሆን ተግባራችን ከትልቁ ግንድ ወደ ቅርንጫፍች እንዲፈስ መትጋት ግድ ይላል ፡፡ የጋራ እናታችንን አንድም በሞራል  ሲቀጥልም በህግ የምናከብርበት አሰራር በሁሉም አካላት ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል ፡፡ ስለጋራ እናታችን ሳናዜም ሰላም እና ብልፅግን መመኝት ከንቱነት ነው ፡፡ እናም በልበ ሙሉነትና ሳንሸማቀቅ የተስፋ
ዬን ዜማ ተውሰን የሚከተለውን ማዜምም መሆንም ይጠበቅብናል ፡፡

እናት ኢትዮጽያ ውዲቷ ሀገራችን
እናስበልጥሻለን ከየክልሎቻችን