‹‹ ዳዊት እጁን ወደ ኮሮጆው አግብቶ አንድ
ድንጋይ ወሰደ ፤ ወነጨፈውም ፡፡ ድንጋዩ በግዙፉ ጎልያድ ግንባር ተቀረቀረ፡፡ በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው ››
ይህ ጥቅስ የአድዋ ድል መግለጫ ወይም Synopsis ሊሆን ይችላል ። በርግጥም ለእኔ የኢትዮጽያና የኢጣሊያ
ጦርነት የዚህ ጥቅስ ሃሳብ እኩያ ነው ፡፡ ጦር ፣ ጎራዴና ውስን ቆመህ ጠብቀኝን የያዘ ህዝብ በውትድርና ጥበብ ከላቀ ፣
በትላልቅ መድፎች በታጠረ በአጠቃላይ ዘመናዊነትን ከታጠቀ
አስገባሪ ጦር ጋር ተናንቆ ድል ጨበጠ ፡፡ ጎልያድ ዳዊትን በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝ ? ወደ እኔ ና ስጋህንም
ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ ብሎት ነበር ። የኢጣሊያ ወታደሮችም ቆመህ ጠብቀኝና ጉራዴ ታጥቀው የሚያቅራሩትን
ጀግኖች በንቀት እያዩ በሳቅ ይዝናኑባቸው እንደነበር ግልጽ ነው ። የተናቀ ያስረግዛል እንዲሉ የማይታመን ፣ ብዙዋችን
የሚያስደምም ፣ ከአንጸባራቂ ማዕድናት የላቀ ዋጋ ያለው ክስተት በአድዋ ተራራ ተገኘ፡፡
በአድዋ ተራራ ላይ አያሌ ዳዊቶች ተፈጠሩ ።
· .
አዋጅ አዋጅ የደበሎ ቅዳጅ
የሰማህ ላልሰማ አሰማ…..
በሚል ነጋሪት የሚኒሊክ ታማኞች ለህዝቡ ቀጭን ጥሪ ማስተላለፍ ጀመሩ ፡፡
ኢትዮጽያና ጣሊያን ውጫሌ ላይ የተፈራረሙት ስምምነት በተለይም አንቀጽ 17 ሁለት ትርጉም በመያዙ ሀገሮቹ ትታዘዘኛለህ -
አልታዘዝህም በሚል ወደለየለት ግጭት ለመግባት ተገደዱ ፡፡ ንጉሱም ‹‹ ጉልበት ያለህ በጉልበት እርዳኝ ፣ ጉልበት የሌለህ
ለልጅህ ፣ ለምሽትህ ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በጸሎት እርዳኝ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ ፡፡ አልተውህም …. ዘመቻዬ
በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እሰከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ ›› ሲሉ አዘዙ ፡፡
·
ወደ አድዋ የተመመው የአጼ ሚኒሊክ ጦር በ10 የጦር መሪዋች የተከፈለ ሲሆን ቁጥሩም ከ73 ሺህ በላይ
ነበር ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ፣ ራስ መኮንን ፣ ራስ መንገሻ ፣ ራስ ሚካኤል ፣ ራስ ወሌ ፣ ራስ ወ/ጊዮርጊስ ፣ አዛዥ ወ/ጻዲቅና
ደጃች ተሰማ ናደው ዋናዋቹ ነበሩ ፡፡ በጣሊያን በኩል በአራት ጄኔራሎች ተዋቅሮ ቁጥሩ 22ሺህ የሚደርስ ነበር ፡፡ ባራቲየሪ ፣
አልቤርቶኒ ፣ ባልዲሴራና ዳቦርሜዳ አዛዦቹ ነበሩ ፡፡ በኢትዮጽያ በኩል የነበረው አቅም 22ሺህ ፈረሰኛ እዚህ ግባ ከማይባል
የጦር መሳሪያ ፣ ጋሻና ጦር ጋር ሲሆን ጣሊያን 20ሺህ ዘመናዊ ጠመንጃዋች ከ66 መድፎች ጋር አሰልፋ ነበር፡፡
የአድዋ ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓም በዕለተ እሁድ በጠዋቱ ተጀመረ ፡፡ በብዙ መስዋዕትነትም
ምሽት ላይ በኢትዮጽያ አሸናፊነት ተደመደመ ፡፡ ድራማው አሰቃቂ ነበር ፡፡ ፊታውራሪ ገበየሁ ጉራዴ መዘው ሲገቡ በጥይት ተመቱ
፡፡ ይሄኔ የኢትየጽያ ጦር መደናገጥና መረበሽ ታየበት ፡፡ የጄኔራል አልበርቶኒ በቅሎ በጥይት ሲመታ ጄኔራሉ ወደቀ ፡፡ ወዲያው
በኢትዮጽያ አርበኞች ቁጥጥር ስር ዋለ ፡፡
አሁን ደግሞ የጣሊያን ጦር ተፈታ ፡፡ እረ ጎራውና የፍየል ወጠጤው በአንድ በኩል ሲሰማ የቁስለኛው
የድረሱልኝ ጩሀት በሌላ በኩል አካባቢውን ገሃነም አደረገው ፡፡ በኢትዮጽያ በኩል 4ሺህ ሰው ሲሞት 6ሺው ቆሰለ ፡፡ በጣሊያን
በኩል 5179 ሲሞት 1429 ያህሉ ቆሰለ ፡፡ 1865 ያህሉ ተማረከ ፡፡ በኢትዮጽያ በኩል የደስታ ፈንጠዝያ ሲከበር ጣሊያኖች
ሮምን በተቃውሞ ሰልፍ ደበላለቁት ፡፡ አጼ ሚኒልክ በሀገር በቀል ሻምፓኝ ሲታጠቡ ጠ/ሚ/ር ክሪስፒ ሽምቅቅ እንዳለ ስራውን
ለቀቀ ፡፡
ጄኒራል ባራቲየሪ ለሮም ህዝብ ‹‹ በቅርብ ቀን ሚኒልክን በቀፎ ውስጥ አስሬ ሮማ አመጣዋለሁ !! ››
በማለት ፎክሮ ነበር ፡፡ በወቅቱ ከነበረው የሁለቱ ሀገራት ልዩነት አንጻር ለዚህ ንግግር ድጋፉን መቶ መቶ የማይሰጥ ማነው ?
ጸሃይ በምስራቅ አቅጣጫ መውጣት ታቆማለች የሚል ቋሚ እውነት ለመሻር የሚከጅል እብድ ከየት ማግኝት ይቻላል ?
ግና ዕድሜ ልክ ልናከብራቸው በሚገባን የቀድሞ ትውልዶች ልዩ መስዋትነት የማይታመን ድል ተገኘ ፡፡ ይህ
እንዴት ይሆናል ? ዓለም በተገቢና በጦርነት መስፈሪያ ሂደቱን ለክቶ ውጤቱን አስልቷል ፡፡ የኢትዮጽያን ሩጫ በፎርፌ ከመሸነፍ
ይልቅ ተሳትፎን ለማጠናከር የሚረዳ ያህል ነበር የታመነበት ፡፡ ታዲያ ፍጥጥ ያለው ውጤት እንዴት ተቀየረ ? ዳኛው ምን ነካው
? ለድሃ ፣ ጉቦ ለማይሰጥ ፣ ዘመድ ወዳጅ ለሌለው ተከሳሽ አይደለም ትናንት ዛሬስ ቢሆን ፈርዶ ያውቃል እንዴ ? ይሄ
ተጠራጣሪነትን / skepticism / የሚያጠናክር ፍልስፍና ነው ? ይሄ ልክ እንደ አሰምፕቶት / asymptote /
መስመር ላይ ለመተኛት የማይችል አልጄብራ ነው ? ይሄ በነሌኒንም ሆነ በነ ጆህን ሎኬ የፓለቲካ አስተምህሮ ውስጥ
ምዕራፍ ያላገኝ አጀንዳ ነው፡፡
ለዚህም ነው ብዙ ጸሀፍት የአድዋን
ድል የሚገልጹበት ቋንቋ አስገራሚ የሚሆነው ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ የተወላጅ ሃይል መነሳቱ ታወቀ ያለው በርክሊይ አበሾች
አደገኛ ህዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል በማለት የተዘነጋ እውነት እንዲዋጥ የገፋፋው ፡፡ ማርገሪ
ፐርሃምም አድዋ ኢትዮጽያን የዓለም ካርታ ውስጥ አስገባት በማለት መሳጭ አስተያየት ሰጥቷል ፡፡
ይህን ታሪክ ለምን ማኮሰስ
አስፈለገ ?
እስካሁን ይህን አንጸባራቂ ድል ስናከብር ያላጓደልነው ዓመታቱን መቁጠር ላይ ነው ፡፡ እያከበርን
የምንገኝው አድዋ አደባባይ በመገኘት የማርሽ ባንድ ማሰማት ፣ የአርበኞችን ቀረርቶ መከታተል ፣ የአስተዳደሩ ተወካይ ያበባ
ጉንጉን ሲያስቀምጡ መታዘብ ፣ ግንኙነቱ የራቀ ንግግር ማዳመጥ ነው ፡፡ የቀጣዩም ዓመት መርሃ ግብር ከዚህ አይርቅም ፡፡ እውነት ይህን
ታሪክ እንዴት እያነው ነው ? እንደምን እየተረጎምነው ነው ? በምን አይነት መልኩስ እያከበርነው እንገኛለን ?
እንደ ድሉ ታላቅነት ለምን አድዋ ተራራዋች ስር አላከብርንም ? የአባቶቻችንን ክብር የሚያጎላና
የመጪውን ትውልድ መንፈስ የሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶቸን ማቅረብ እየተቻለ አልተደረገም ፡፡ እንደ ካፓርት የሚሞቁ ታሪክ ቀመስ ጥናቶችን ማስተላለፍ እየተቻለ
አልተፈለገም ፡፡ የውጪ ቱሪስቶች እንደ ጥምቀትና መስቀል እንዲጎርፉ የሚያደርግ ቋሚ ስራዋችን መስራት ቢፈለግ የሚከብድ ባልሆነ
ነበር ፡፡ የአድዋን ሜዳዋች በሙዚየምና በመዝናኛ አገልግሎቶች ፣ የታሪካዊ ተራራዋቹን ግርማ ሞገስ ደግሞ እንደ ገና ዛፍ
ማብረቅረቅ ወገቤን የሚያሰኝ አይደለም - ቢያንስ ለአንድ ሁለት ተሃድሶ የሚወጣውን ወጪ ቆንጠጥ አድርጎ መያዝን ነው የሚጠይቀው
፡፡ እንደ ቻይና ግንብ መወጣጫ ሰርቶም መዳረሻው ላይ የፈለገ እንደ ጀግኖቹ ዘራፍ እያለ እንዲያቅራራ ፣ ያልፈለገ ደግሞ
የአባቶቻችንን የከበረ መስዋዕትነት ከልቡ ተመስጦ እንዲያስብ ማድረግ ፍጹም የሚያስደስት ነው ።
ሞኝ አሞራ ያባቱን ዋሻ ይጠየፋል አሉ ። አሞራው ዋሻው የቀፈፈው በተራ ጅልነቱ ነው ። እኛ የቀድሞ
ማንነታችንን ጥቂት እንደቀረው ደናችን እየጨፈጨፍን ነገ የሚያጠፋንን በረሃ ለመፍጠር የምንተጋው ባለማወቅ ሳይሆን በተራ ጥላቻና
ትዕቢተኝነት በወለደው የዘቀጠ አስተሳሰብ ነው ።
ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንዲሉ ከታላቁ የአድዋ ድል ጀርባ ታላቁ አጼ ሚኒሊክ አሉ በሚል
የተጃጃለ ሃሳብ የህዝቡን መብትና ጥያቄም እየጨፈለቅን ነው ። በርግጥም አፍሪካዊ ድሉን አስተባብረው ኩራት እንዲፈጠር
የአንበሳውን ድርሻ የወሰዱት አጼ ሚኒሊክ ናቸው ። ታላቅን ጀግና እንደታላቅነቱ ማክበር እንጂ በሀገር ውስጥ ጦርነት ... ቆርጧል ፣ ... ተርትሯል እያሉ በታሪክ ውስጥ እንዳላለፈ
ሁሉ ስሙን ለመደምሰስ የሚደረግ ሩጫ የትም አያደርስም ። ምክንያቱም ሰቅጣጭ የጦርነት ታሪክ ባላት ኢትዮጽያ ግዜ ሰጥቶት
የነገሰው መሪ ሁሉ የራሱን ስርዓት ለማስጠበቅ ንጹሃንን ገድሏል ፣ ጨፍጭፏል … እስኪ ይህን አላደረኩም የሚል የፖለቲካ ስርዓት
/ ሌላው ቀርቶ ጠመንጃ የታጠቀ አማጺ ድርጅት / እጁን ያውጣ - በፍጹም አይገኝም ።
ይህ እንዲሆን ባይፈለግም ሆኗል ። ካለፈ ስህተት ተምሮ ማለፍ ይሻላል ወይስ ታሪካዊ ድሉን በመጨፍለቅ
የማጣጣት ስራ መስራት ? ሚኒሊክ ሰዎችን ስለገደሉ ሃውልታቸው ይፍረስ ? የአድዋ ድል ትቢያ ይልበስ ? ጀግንነታቸውን ከርቸሌ
አስረን ስማቸውን በየሚዲያውና በየስብሰባው እናጥፋ ?
ይህን ሁሉ በማድረግ በህዝቡ ውስጥ ያላቸውን ሚዛን ደፊ ፍቅርና ክብር መቀነስ አይቻልም ። ምናልባት
ይበልጥ በጣም እየገነኑ ይሄዳሉ እንጂ ። ስለዚህ አስተዳደራዊ ችግራቸውን እንደመማማሪያ እያነሳን ዓለም የተቀበለውን ድልም
በተገቢው መልኩ ማስተናገዱ ይበጃል ። ለፖለቲካ ፍጆታም ሆነ ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳን የተሻለው መንገድ ይኀው ነውና ።
የድህረ ታሪኩ አስኴል
የአድዋ ድል ውጤቱ ብዙ ነው ፡፡
ባህልን ለመውረር የተደረገ ስልትን ያኮላሸ ድርጊት ነው….. ትልቅ ስብዕናና ድፍረት ያላቸውን ህዝቦችንና የጦር መሪዋችን
ለአለም አስተዋውቋል….. በጭቆና ስር ለነበሩ ጥቁር ህዝቦች በሙሉ ተስፋና መነቃቃትን ፈጥሯል….. የአውሮፓ ተስፋፊዎች በሰው
ልጆች ላይ ሲፈጽሙት የነበሩትን ኢ- ሰብአዊና ኢ- ፍትሃዊ ስርዓት ቆም ብለው እንዲመረምሩ ያሰገደደ ነው ፡፡ ይህ ድል ክብርና
ነጻነታቸውን የተገፈፉ የዓለም ህዝቦች በሙሉ ከጭቆና ቀንበር እንዴት መውጣት እንደሚችሉ የሚያስተምር ባለ ሺህ ገጽ ምርጥ
መጽሀፍ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment