Sunday, October 22, 2017

በአፍሪካ ጭንቅላት ዓለምን መምራት ?


« የማይቻለውን እንደሚቻል እናረጋግጥ » በሚል መሪ መፈክር ስር ተወዳድረው የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራልነትን ያሸነፉት አቶ ቴዎድሮስ አድሃኖም ፣ ሮበርቱ ሙጋቤን የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አድርገው መሾማቸው አለማቀፍ ተቃውሞ አስከትሎባቸዋል ። እኔም ሰውየው የሚመለከቱበት መነጽር እንዴት ሸውራራ ሆነ ብዪ ጥያቄ አንስቼያለሁ ።

አንዳንዶች ነጮች ሙጋቤን ስለማይወዱት በተራ ጥላቻ የተደረገ ተቃውሞ እንደሆነ ያስባሉ ። እውነቱ ግን ይሄ አይደለም ። ሙጋቤ የፈለገ ያህል ለነጭ ተንበርካኪ አይሁኑ እንጂ በሀገራቸውም የሚመሰገን የፖለቲካ ስብእና የላቸውም ። ሀገሪቱን ላለፉት ሰላሳ አመታት የገዙት የተቃዋሚዎቻቸውን ድምጽ ብቻ ሳይሆን የህዝባቸውን የዴሞክራሲ ጥማት ጨፈላልቀው ነው ። ለስሙ ያህል ምርጫ ያካሄዳሉ እንጂ ‹ በህይወት እስካለሁ ድረስ ፕሬዝዳንት ነኝ › የሚሉትን መርህ አጥብቀው እየተገበሩ የሚገኙ ሰው ናቸው ። ምን ይሄ ብቻ በቅርቡም ባለቤታቸው ግሬስ ፣ ሙጋቤ ቢሞት እንኳ ሬሳው ይወዳደራል ማለታቸው የሚዘነጋ አይደለም ። የሰው ልጆች በተፈጥሮ ያገኙትን የዴሞክራሲ መብቶች የግል በማድረግ ነጻነት እንዲጠፋ ፣ ጭቆና እንዲስፋፋ የሚተጉ ባለስልጣናትን እውቅና ከሚሰጠው ጎዳና ገለል አለማለታችን ያሳዝናል ።

  ከአፍሪካ የተገኙት ቴዎድሮስ የሙጋቤ አምባገነን መሆን ጉዳያቸው ላይሆን ይችላል - ስልጣንን አለመልቀቅ የአፍሪካ ያልተጻፈ ህግ ስለሆነ ። አንድ የአፍሪካ ባለስልጣን ወደ አለማቀፉ ደረጃ ከፍ ሲል ግን በዚያው የአሰራር ስርዓት ውስጥ ሊጓዝ ግድ ይለዋል - ምክንያቱም ከአፍሪካ መጣ እንጂ አፍሪካን ብቻ ሊመራ አይደለም እዛ የተወከለውና ። እና አንድ መሪ አዎንታዊ  ቅቡልና የሚያገኘው ለሰው ልጆች ካለው ክብርም አኳያ ነው ። ሙጋቤ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ የረባ ሰእል የላቸውም ። ተመድ በግልጽ ከሚመራባቸው መርሆዎች አንዱ ደግሞ ሰብዓዊ መብትን ማክበር ነው ። ታዲያ ሙጋቤ በምን አንጀታቸው ነው ርህራሄ የሚፈልገውን የጤና ተቋማት መደገፍ የሚችሉት ?

ሙጋቤ 93ተኛ አመታቸው ላይ ይገኛሉ ። አለመታደል ሆኖ እንጂ ይህ የማረፊያና የጥሞና ግዜ ነበር ። በየግዜው እንደምናያቸውም በአካልም ሆነ በአእምሮ ደክመዋል ። መራመድ ተስኗቸዋል ፣ ስብሰባ መቀመጥ ባለመቻላቸው በየሄዱበት ያንቀላፋሉ ። አንድ ሰው ንቁ ካልሆነ እንዴት ለሌላ ስራ ይታጫል ? አቶ ቴዎድሮስ ለዚህ ጥያቄ አሳማኝ ምላሽ የሚኖራቸው አይመስለኝም - በሙጋቤ ቃል አቀባይ ፎጋሪ አስተያየት ካልተስማሙ በስተቀር ። ፎጋሪው ሰውየ ምን አለ መሰላችሁ « ሮበርቱ ሙጋቤ በየስብሰባው የምታዩዋቸው እየተኙ አይደለም - አይናቸውን ስለሚያማቸው እያረፉ እንጂ »

አቶ ቴዎድሮስ ለዙምባቤ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ አዎንታዊ ድጋፍ እንዳላቸውም ተናገረዋል ። ይህ አስተያየታቸው ግን ከነባራዊው እውነታ ጋር የሚጣረስ ነው ። በርካታ መረጃዎች የሚያመለክቱት የዙምባቤ የጤና ስርአት እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው ። ሰራተኞች ያለ ደመወዝ የሚሰሩበት ግዜ ጥቂት አይደለም ፣ በመንግስት ሆስፒታሎች መድሃኒት ባለመኖሩ ሰራተኞች በቂ ህክምና ለመስጠት ተቸግረዋል ።

አቶ ቴዎድሮስ ሙጋቤ በዓለማቀፉ ጤና ድርጅት ተመርጠው መስራታቸው የሀገራቸውንም ሆነ የአፍሪካን የጤና አያያዝ ሊያሻሽሉ ይችላሉ ባይ ናቸው ። እውነቱ ግን ሙጋቤ በሀገራቸው ጤና ስርአት ላይ እምነት የሌላቸው መሆኑ ነው ። እምነት በማጣታቸውም ሲታመሙ እንኳ በሆስፒታላቸው ሊታከሙባቸው አይፈልጉም ።  አቶ ቴዎድሮስ ‹ የህክምና ቱሪስት ፕሬዝዳንቶች ›  / Medical Tourist Presidents / ስለተባሉት የአፍሪካ መሪዎች አንበው ቢሆን ኖሮ ይህን ከመሰለ ስህተት ውስጥ ባልገቡ ነበር ።

ዓለም የሚሳለቅባቸው እነዚህ የህክምና ቱሪስቶች የናይጄሪያው ሙሃመድ ቡሃሬ ፣ የአንጎላው ጆሴ ኤድዋርዶ ፣ የቤኒኑ ፓትሪስ ታሎን ፣ የአልጄሪያው አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ እና የዙምባቤው ሮበርቱ ሙጋቤ ናቸው ። እነዚህ መሪዎች በአመት ውስጥ ደጋግመው ውጭ ሀገር ለህክምና ስለሚመላለሱ በርካታ የሀገር ሃብት ያጠፋሉ ። ሙጋቤ ባለፈው አመት ብቻ ሶስት ግዜ ወደ ሲንጋፖር ለህክምና አቅንተዋል ፣ ለዚህም 50 ሚሊየን ዶላር ወጪ ያደረጉ ሲሆን ይህ ገንዘብ የሀገሪቱን ጤና ጣቢያዎች ለማስፋፋት ከተመደበው አመታዊ በጀት በሁለት እጥፍ ይበልጣል ። ሙጋቤ ሲንጋፖር ሄደው የሚታከሙትም በጥቁር ሀኪም ነው ። ነጭ ሁሉ ጠላት ነው የሚሉት ሙጋቤ በአለም አቀፍ የህክምና መድረክ ብቅ ቢሉ እንዴት ነው በፍቅር መስራት የሚችሉት የሚለውን ጥያቄ አቶ ቴዎድሮስ መመለስ ይኖርባቸው ነበር ።

ዞሮ ዞሮ የሙጋቤ አምባሳደርነት ተፍቋል ። አቶ ቴዎድሮስ ይህን በፍጥነት ማድረጋቸው መልካም ነው ፣ ነገር ግን በብዙ መልኩ ጥያቄና ጥርጣሬ ውስጥ ወድቀዋል ። ነገሮችን የሚያዩብት መነጽር ሸውራራ እንዳይሆን ተፈርቷል ። ስለ ተመድ ያላቸው እውቀትና አረዳድ አስጊ መስሏል ። በስሜት ሳይሆን በተጨባጭ መረጃ ውሳኔ ሰጪ አይሆኑ እንዴ አሰኝቷል ። የዴሞክራሲ ማእከል ውስጥ ገብተው ዴሞክራት ላልሆኑ ሰዎች መወገናቸው አስደንግጧል ። አቶ ቴዎድሮስ ከለመዱት ‹ አብዮታዊዊ › አሰራር በፍጥነት መላቀቅ ካልቻሉ ገና ከብዙ ጉዳዮች ጋር መላተማቸው አይቀርም ። በርግጥም በኢትዮጽያና አፍሪካ ባርኔጣ ዓለምን መምራት አይቻልም - ባርኔጣው ካልተስተካከለ ::


No comments:

Post a Comment