Saturday, October 14, 2017

የ « ማዕቀብ » መሳጭ ሀሳቦች


« ማዕቀብ » ከእንዳለጌታ ከበደ ግሩም ስራዎች አንደኛው ነው ። መጽሐፉ በዋናነት ‹ ዴሞክራት ገዢዎቻችን › በድርሰት ፣ ደራሲያንና ተደራሲያን ላይ ስላስከተሉት አሉታዊ ተጽዕኖ ይተርካል ። ከዚያ በመለስ የተመረጡ ደራሲያንና መጻህፍት ሻጮችን የህይወት ውጣ ውረድ ያመላክታል ።

በመጽሐፉ ከአዳዲስ መረጃዎችና ሀሳቦች ጋር እንተዋወቃለን ፤ ከመሳጭና ሞጋች ሀሳቦች ጋር እንፋጠጣለን ። በመሳጭ ሀሳቦች እየተብሰከሰክን ከሞጋቾቹ ጋር የከረረ ምናባዊ ምልልስ እናደርጋለን ።

ከተነሱት ሞጋች ሀሳቦች አንዱ የአቶ መለስ ዜናዊ ልቦለድ ደራሲነት ጉዳይ ነው ። አቶ መለስ በብዕር ስም ‹ መንኳኳት ያልተለየው በር › እና ‹ ገነቲና › የተሰኙ ሁለት መጻህፍትን ለንባብ አብቅተዋል ። እንዳለጌታ ተማሪ በነበረበት ወቅት አንድ ተጋባዥ መምህር ስለ ትግርኛው ስነጽሁፍ የማብራራት እድል ያገኛሉ ። እኚህ ምሁር « በአማርኛው ስነጽሁፍ በቋንቋ ፣ በጭብጥ ፣ በአጻጻፍ ቴክኒክ ታዋቂ የሆነው ዳኛቸው ወርቁ እንደሆነ ሁሉ የትግርኛው ዳኛቸው ደግሞ መለስ ዜናዊ ነው » በማለት ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ ።

ሲጀመር በዳኛቸው ላይ የተሰጠው ዳኝነት ትክክል አይመስለኝም ። እንዳለጌታ እንደሚለው ደግሞ መለስን እንደልቦለድ ደራሲነት ማወቅ እና ማሰብ ይከብዳል ። ደራሲ የደራሲን ህይወት ያውቃል ... ይረዳል ... ባይረዳ እንኳ ያበረታታል ... ጥበብ እንዲያድግ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል ። የነበሩ ቤተመጻህፍትን እንዲጨምሩ እንጂ እንዲጠፉ አያደርግም ። ሰውየው በስልጣን ዘመናቸው ለደራሲያን ሲቆረቆሩ አልታየም ። በአንድ ወቅት አስታዋሽ ስላጡ አንጋፋ ደራሲያን ሲጠየቁ ከአንድ አርሶአደር ለይተን አናያቸውም ነበር ያሉት - በርግጥ ከአድካሚ ስራ ጋር የሚተዋወቅ ደራሲ ደራሲነትን በዚህ መልኩ ብቻ ነው የሚረዳው ? እናም ሰውየው ስለጭብጥ እና ገጸባህሪያት ቀረጻ ይበሰለሰላሉ ብሎ ማሰብ ቁንጫ ቆሞ ሲቀድስ ፣ አህያ ሞቶ ጅብ ሲያለቅስ የመስማት ያህል ነው ይላል - እንዳለጌታ ።

በርግጥ ደራሲያን እሳቸው ‹ መንኳኳት ያልተለየው በር › እንዳሉት የድርሰት ስያሜ ሁሌም ሃሳብ እንዳንኳኳ የሚኖር ነው ። እሳቸው የቤተመንግስት በር ወለል ብሎ ከተከፈተላቸው በኋላ ሰለተዘጉ በሮች አለማሰብ ፍትሃዊ አይሆንም - በር የሚያንኳኳውን እንዳልሰማ መዘንጋት ፣ ባስ ካለም በውሻና በጥበቃ ማባርረ ከባለ ብዕረኛ አይጠበቅም ።

ሌላኛው ሞጋች ሀሳብ ሳንሱር ዛሬም ቢሆን የለም ማለት ይቻላል ወይ የሚለው ጉዳይ ነው ። ሳንሱር በአዋጅ በግልጽ ይደንገግ እንጂ በውስጥ ከሳንሱር የሚተካከሉ አሰራሮች አሉ ።

ሜጋ የመጻህፍት ማከፋፈያ ስራው መጽሐፍ በአደራ ተቀብሎ ማሰራጨት ቢሆንም ይዘታቸውን እየገመገመ የሚመልሳቸው ስራዎች አሉ ። ይህ ቁልጭ ያለ እውነት ነው ። ማተሚያ ቤቶች ህትመት ከጀመሩ በኋላ የሚቋረጡ ስራዎች አሉ ። ይህም እንዳይታተሙ የሚል ቀጭን የቃል መመሪያ ከነጌቶች ስለሚደርሳቸው ነው ። አንዳንድ ማተሚያ ቤቶች የመንግስትን ቅጣት በመፍራት ያተሙት መጽሐፍት ጀርባ ላይ ድርጅታቸውን ከመጻፍ ይቆጠባሉ ። 

ፓለቲካ ነክ ፊልሞች ከተሰሩ በኋላ እንዳይተላለፉ ታግደዋል ። የቴዲ አፍሮና የአንዳንድ ሙዚቀኞች ስራ በመገኛኛብዙሃን እንዳይተላለፉ ተደርጓል ። ዝግጅት አጠናቀው መድረክ የጀመሩ ቲአትሮች መጋረጃ ተዘግቶባቸዋል ። ጋዜጦች በጻፉት ጉዳይ መጠየቅ ሲገባቸው ገና ማተሚያ ቤት እንደደረሱ ቀኝ ኋላ ዙር ተብለዋል ።
ታዲያ ይህ ሁሉ ጉዳይ ክፍል ሁለት ሳንሱር ነው የሚባለው ወይስ የዚያኛው ሳንሱር ሁለተኛው ገጽታ ? ሀገሬው አጠናክሮ ሊወያይበት የሚገባ የቤት ስራ ይመስለኛል ።

አንዳንድ መሳጭ ሃሳቦችን ደግሞ እንመልከት ።

በርግጥ የዳኛቸው ወርቁ ‹ አደፍርስ › አከራካሪ ስራ ነው ። ለዚያም ነው አንባቢያን በብዙሃን ድምጽ ጥሩነቱን መመስከር የተሳናቸው ። ደራሲው ግን ጠመንጃ ባነገበው አንባቢ አንጻር ጦርና ጋሻ ይዞ ቆመ ። እጅና እግር ለሌለው መጽሐፍህ አምስት ብር አይገባውም እያለ በሚዘምተው ተደራሲ ፊት « ዋጋውን አስር ብር አድርጌብሃለሁ ! » ሲል የተሳለ ውሳኔውን እንደ ጦር እየነቀነቀ አሰማ ። ታዳሚውና ነጋዴው የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል አሉ ።

ቆይቶ ብቅ አለና ደግሞ አንባቢው ምን እንደሚል ጠየቀ ። ማንበብ ስላልቻለ ምን ሊል ይችላል ሲሉ ነጋዴዎች መለሱ ፤ ቅናሽ እንዲያደርግም ሃሳብ አቀረቡ ። ዳኛቸው ጦሩን ነቅንቆ እረ ጎራው አለ ፤ እረ ወንዱ አለ ። የጀግንነቱን ልክ ለማሳየትም ዋጋው ወደ 15 ብር ከፍ ማለቱን አበሰረ ። በአንባቢውና በደራሲው መሃል እንደ አሸማጋይ የቆሙት ነጋዴዎች ማሰራጨት አንደማይፈልጉ ነገሩት ። ዳኛቸው ከፉከራ በላይ ተቆጣ ። ጦሩን መሬት ላይ ቸንክሮ « ንሳ ! » ሲል ትዕዛዙን አሰማ « ከእንግዲህ መጽሃፍቶቼን ለማንም እንዳትሽጥ ! ያሰራጨሃቸውን በሙሉ ሰብስበህ አስረክበኝ ! »

ማንም ያልጠበቀው ሃሳብ ነበር ። የኢትዮጽያ ደራሲ ነጋዴ ዋጋ ቀንስ ሲለው የሚቀንስ ፣ ኮንሳይመንት ጨምሯል ሲሉት እሺ የሚል ፣ የወረቀት ክምርህ ስላልተሸጠ ይዘህ ጥፋ ሲባል ተሽክሞ የሚሮጥ ነው ። ይሄኛው ደራሲ ግን ነጋዴውን የሚያሽቆጠቁጥ ሆነ ፣ ይሄኛው ደራሲ አንባቢ ካልገባው መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት የሚል ሆነ ። ይሄኛው ደራሲ ፍጹም አፈንጋጭ ነው ። ይሄኛው ደራሲ በክብሩም ሆነ በመንፈስ ልጁ ላይ የመጣን ጥቃት ለመመከት ቆርጦ የተነሳ ነው ። ይሄኛው ደራሲ የኢትዮጽያዊያንን ለንቋሳ አንባቢነት እና እውቀት የሚራገም ሆነ ። ምንም ሳይፈራና ሳይጠራጠር ቀጥታ ወደ ህዝቡ የሚተኩስ ሆነ « እኔን ለመረዳት 20 አመት ይቀርሃል ! » እያለ ። አደፍርስ የፈለገ ባይመች የዳኛቸው ልበ ሙሉነት ግን ይደላል ባይ ነኝ ።

በኢትዮጽያ ስነጽሑፍ ታሪክ ትልቅ  ቦታ ከሚሰጣቸው ደራሲያን መካከል አንዱ ብርሃኑ ዘሪሁን ነው ። ይህ ደራሲ በርካታ ስራዎችን ቢያቀርብልንም  በርካታ ስራዎች መስራት በሚችልበት እድሜው ላይ ነበር /54 / ያለፈው ።

አሁን እኔ ማውራት የፈለኩት ሰለ ብርሃኑ ሳይሆን ብርሃን ስለፈጠረችለት ሚስቱ ነው ። ስለ ብርሃኑ ምርጥ ባለቤት ስለ ወ/ሮ የሺ ። ዘወትር የብርሃኑ አምሽቶ መምጣት ያሰጋት ሚስት አንድ ነገር እንዳይሆን በመፍራት መጠጡን እንዲተው ትጨቃጨቅ ነበር ። እሱ ግን በደሙ ስለተዋሃደ ያለጂን ብእር ማንሳት አልቻለም ። አልኮል እያጣጣሙ  ከ 10 በላይ ግሩም መጻሕፍትን መድረስ በራሱ ገራሚ ነው ። ምክንያቱም ለብዙዎች አልኮል እንቅልፍ መጥሪያ እንጂ ለስነጽሑፍ ከራማ መዘየጃ ሲሆን አልታየምና ።

ግራ ቢገባት ጂን እየገዛች ቤት ውስጥ ትቀዳለት ጀመር ፤ አላስደሰተውም ። ምነው ? ብትለው ብቻዪን እንዴት እጠጣለሁ ? የመጠጥ ቤት ድባብ ያስፈልገኛል አላት ። ፈተና ሆነባት ። ጎረቤት እየጠራች ቤቷን እንደ ቡናቤት አታሟሙቀው ነገር ሃብት ይፈልጋል ። ቡቡዋ ሚስት መንገድ ወድቆ ከሚቀር በሚል ‹ እኔ አጣጣሃለሁ › አለችው ። ለእሱ ብላ የጠላችውን ወደደች ። ቀስ በቀስ ጨዋታውን ለመደች :: ምን ያደርጋል ታዲያ ታላቁ ደራሲ በዚሁ ጦስ ከሞተ ጥቂት ቆይቶ የእሷም ጉበት መበላሸቱ ተነገራት ። በአንድ በኩል የባለቤቷ ሀዘን በሌላ በኩል የራሷ ህመም ተባብረው ገደሏት ።

ለባሏ ብላ መስዋዕት ሆነች ። በኢፍትሃዊ መንገድ ተቀጣች ። የደራሲ ሚስቶች ታይፕ በመምታትና በመናበብ ፣ ቡና በማፍላትና ጋቢ በመደራረብ ሲተጉ ነው የምናውቀው ። የሺ ግን ለእነዚያ ለሚያምሩ ድርሰቶች ሻማ ሆና ቀለጠች ። የዓለም አስደናቂ ስራዎች መመዝገቢያ መጽሐፍ ያላየው ታሪክ ።

ማዕቀብ ብዙ አዲስ መሳጭ ታሪኮችን ይዛለች ። ስብሃትና ባለቤቱ ዋሴ በተባለው ህመምተኛ ልጃቸው እንዴት እንደተሸነፉ ... አዲሱን መጽሐፌን አይቼውና ዳብሼው ልሙት እያሉ በጉጉት ስላለፉት ማሞ ውድነህ እና ስለሌሎችም ተረክ አላት ። ማዕቀብ የአዝናኝ መልኮችም ባለቤት ናት ። አድሃሪያን በህይወት ብቻ ሳይሆን በልቦለዱ አለምም መኖር አይፈቀድላቸውም ተብሎ በግድ ስለተገደሉት ገጸባህሪም ትሰማላችሁ ። ሰው ሲሞት ይናዘዛል ፤ ስብሃት ከመሞቱ በፊት እንደምንም ተነስቶ የተናገረው ምን ይመስላችኋል ?

« እኔ የምለው መለስ ዜናዊና ሰይፉ ፋንታሁን አሁንም በኢትዮጽያ ህዝብ ላይ እየቀለዱበት ነው ወይስ አዲስ ነገር አለ ? »
ሃሃሃሃሃሃሃሃ .... ‹ ማዕቀብ › የሌለው ንግግር ይልሃል ይሄ ነው !



No comments:

Post a Comment