Sunday, April 15, 2012

‎‹‹ አንደኛው ዝሆን ››‎





ሰሞኑን ጎን ለጎን ሳነባቸው ከነበሩት መጽሀፍት መካካል ሁለቱን አጠናቀቅኩ፡፡ የአቶ ስዬ አብርሃ እና የዶ/ር ያእቆብ ሃይለማርያምን፡፡ የአቶ ስዬ መጽሀፍ ‹‹ ነጻነት እና ዳኝነት በኢትዮጽያ ›› ይሰኛል ርእሱ፡፡ ባለ 440 ገጽ ሲሆን ዋጋው 70 ብር ነው፡፡

አቶ ስዬ ከፍተኛ የመንግስት አመራር ከመሆናቸው ውጪ የተዘረዘረ ስብዕናቸውን / የአንድ ወገን መረጃ ቢሆንም / በከፊል እንዳውቅ ያደረጉኝ የተስፋዬ ገ/አብ መጽሀፍት ናቸው፡፡ በተለይም በደራሲው ማስታወሻ ላይ ‹‹ ሁለቱ ዝሆኖች ›› በሚል ርዕስ በቀረበው ጽሁፍ፡፡

በጽሁፉ ላይ አቶ ስዬ ወይም ‹‹ አንደኛው ዝሆን ›› ለስልጣን የሚተጉ፣ ጠብ አፍቃሪ፣ የህክምናን ሙያን በከፊል ያጠኑ፣ ዲፕሎማሲ የማያውቁ፣ ተቆጪ፣ ሰውን የሚንቁ፣ ወታደራዊ ብቃት ያላቸው፣ ለይቅርታ የራቁ፣ በምንወደው የቶም ኤንድ ጄሪ ፊልም ላይ እንደ ቶም የተወከሉ መሆናቸውን እናነባለን፡፡

ይህ መነሻ የሚሰጠው አንድ ደራሲ ምናልባት ጥቂት ለየት ያሉ ነገሮችን ጨማምሮበት በአንድ መጽሀፍ ወይም ቴአትር ውስጥ አሪፍ ገጸባህሪ መሳል ይችላል፡፡ እንግዲህ እኔም ይህን ቀመር እያስታወስኩ ነበር ከላይ የተጠቀሰውን መጽሀፍ ማንበብ የጀመርኩት፡፡

በኮሌጅ ቆይታ ወቅት የመጽሀፉን አጠቃላይ ጭብጥ በአንድ ወይም ሁለት መስመር አስረዳ ? የምትል ጥያቄ እንጠየቅ ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ አሁን ተውሼ የአቶ ስዬን መጽሀፍ ባስረዳ ‹‹ እኔ የታሰርኩት በሙስና ሳይሆን ከጠ/ሚ/ር መለስ ጋር በነበረኝ የፓለቲካ መስመር ልዬነት ነው፡፡ ፍ/ቤቱም ሙሰኛ መሆኔን በበቂ ሁኔታ ሊያሳይ አይችልም ›› የሚል መልእክት እናገኛለን፡፡
በርግጥ ይህ ቱባ መልእክት የተገኘው በየምዕራፉ ሀሳቡን ለማዳበር በተጠነጠኑ ቀጫጭን ድውሮች ድምርነት ነው፡፡ አቶ  ስዬ በየምእራፉ ሰለማስረጃ፣ መቃወሚያ መግለጫ፣ የመከላከያ ማስረጃ፣ የሰነድ ማስረጃ፣ የሰዋች ምስክርነትና የቅጣት ውሳኔ አካሄድ ደረጃ በደረጃ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

ወታደራዊ ስብዕናው ጎልቶ ከሚነገርለት አንድ ሰው ይህ መጽሀፍ መመረቱ ያስገርማል፡፡ የሚገርመው አንድም ያልተጠበቀ በመሆኑ ሲሆን በዋናነት ግን መጽሀፉን ጅማት ሆነው ሊያቆሙት የቻሉት እውነታዋች ናቸው፡፡ እነዚህ እውነታዋች የአቶ ስዬ የማስታወስ ብቃት፣ ማስታወሻ የመያዝና መረጃዋችን ስብስቦ እንዳግባቡ የመስፋት፣ ለህግ ያላቸው ግንዛቤ የማይናቅ መሆኑና ብዙም ሊታማ የማይችለው የትረካ አቀራረባቸው በግልጽ መታየታቸው ናቸው፡፡

ዝሆን እጅግ አደገኛ በሆኑት አንበሳና አዞ ፊት እንኳ የተለየ ድፍረት የሚያሳይ እንሰሳ ነው፡፡ የራበው አዞም ሆነ አንበሳ ግን አዘናግቶና ልዬ ስልት ተጠቅሞ ገቢ ሊያደርገው ይችላል፡፡ አቶ ስዬ የሚያስቡትን ሁሉ ያለ ፍርሃት ይናገራሉ፡፡ በፍ/ቤት ከዋናው ርዕስ በመውጣት የፓለቲካ ጉዳዬች ሲናገሩ በዳኞች በተደጋጋሚ እየተገሰጹ ያስቆሟቸው እንደነበር እናነባለን - በርግጥም እኔም በአንድ የግል ጋዜጣ ውስጥ ስሰራና ጉዳዩን ለመዘገብ ስከታተል ይህን አይቻለሁ፡፡

ከድፍረቱ በተጨማሪ እንደ ቶም ሳይሆን እንደ ጄሪ ብልጠት የተላበሰ የአዳኝ - ታዳኝ ስልት ይከተሉ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በፍ/ቤት ባገኙት የመናገር አጋጣሚ  ክሱ የፓለቲካ መሆኑን ሳይጠቁሙ አያልፉም፡፡ ጎን ለጎን ግን የሚቀርብባቸውን የተለያዬ ክሶች ሁሉ  በሰውና በጽሁፍ ማስረጃዋች ለመከላከል ከፍተኛ ትግል ሲያካሄዱ ይታያል፡፡ ጉዳዩ የፓለቲካ ከሆነ ያለቀለት በመሆኑ መልፋት ላይስፈልግ ይችላልና፡፡

አቶ ስዬ በመጽሀፋቸው ደጋግመው ሲያደንቁት የተሰማ ተቋምም አለ፡፡ እንደውም ‹‹ መተኪያ የሌላቸው ተቋማት ›› በማለት ነው የግሉን ፕሬስ ሚና የገለጹት፡፡ ምናልባትም ቀድሞ ከነበራቸው አመለካከት አንጻር የሚፈተሸ ከሆነ ወደ ‹ ይቅርባይነት › ወይም ‹ አድናቂነት › ተሸጋግረዋል ማለት ነው፡፡ በርግጥ ወደዚህ አቅጣጫ ለማምራት የሚያስችሉ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ተጽእኖዋች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡

ከዋና ጉዳያቸው ጎን ለጎን ስለዳኝነትና ፓሊስ አሰራር፣ ስለፍትህ መጎደል፣ ስለምርጫ ቦርድ ነገር፣ ስለእስረኞች አያያዝ፣ ስለ ምርጫ 97 አንድምታዋች፣ ህወሃትን ጨምሮ ስለ ፓለቲካ ድርጅቶች ድክመትና ጥንካሬ ቀደም ብሎ በተገለጸው ‹‹ ዝሆናዊ ›› መንገድ እምነታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጥቅሉ ወንድ ልጅ ሀዘናዊ ስሜትን ደብቆ መያዝ ይችላል ይባላል፡፡ በተናጥል ስናይ ደግሞ ፓለቲከኞችና ወታደሮች ልበ ደንዳኖች እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ለሞትና ለሌሎች ውጣ ውረዶች ቅርብ በመሆናቸውና ጉዳዩን በመለማመዳቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሀሳብ ግን ሁልግዜ ትክክል አይደለም፡፡ ለምሳሌ አቶ ታምራት ላይኔ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በአንድ የእምነት አዳራሽ ተገኝተው ስለ ፈጣሪ ቃል ያስተምሩ ነበር፡፡ ቪዲዮውን የተመለከትኩ ግዜ እጅግ ብዙ ነገሮች አስገርመውኝ ነበር፡፡ የገረመኝ ሰሜን ዋልታ ይገኝ የነበረ አንድ አለማዊ ፓለቲከኛ በምንም ወደ ማይዋሰነው ሃይማኖታዊ የደቡብ ጫፍ የመምጣቱ ገዳይ አልነበረም፡፡ የገረመኝ የአቶ ታምራት ምላስና እንባ ጣፋጭ መሆናቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚሰብከው አንደበታቸውና በተወሰነ ርቀት ከአይናቸው የሚወርደው መጠነ ሰፊ እንባ በእጅጉ የተናበቡ ነበር የሚመስሉት፡፡ ንግግራቸው የትምክህትን ኮፍያ ያወለቀ ነበር፡፡ አንደበታቸው  ይቅርታን ወደ ነፍሳቸው ለማስገባት የሚካድም ነበር፡፡ አንደበታቸው ታላቅ ‹ ፈጣሪ › መሆኑን፣ በምድር ላይም የሰው ታላቅ ካለ  በ ‹ግዜ › ድጋፍ የቆመ ብቻ መሆኑን የሚያስረዳ ነበር፡፡ እናም ይህን አንደበታቸውን ሲያስፈልግ በጥያቄ ምልክት፣ ሲያስፈልግ በቃለ አጋኖ፣ ሲያስፈልግ በትምህርተ ጥቅስ፣ ሲያስፈልግ እንደ አራት ነጥብ ሆኖ ሲያስረዳ የነበረው እንባቸው ነበር፡፡ በቃ ! ስሜት የሚንጥ ንግግር ሰፈልቅ….የሌሎችን ስሜት የሚያሸብር እንባ ይከተላል ፤ እስከማስታውሰው ድረስ ፍሰቱ እንዲህ ነበር፡፡ አቤት እንዴት ነበር የሚወርደው ? የወንድ ልጅ ለዚያውም የፓለቲከኛ፣ ለዚያውም የወታደር…

በአቶ ስዬ መጽሀፍ ውስጥ ግልጽ እንባ ባይታይም ለቤተሰባቸው ያለቸውን ጥልቅ ፍቅርና ስስ ነፍስ እንመለከታለን፡፡ እሳቸው እስር ቤት ገብተው ሲጨነቁ የሚታዩት ለወንድሞቻቸውና ለእህታቸው ነበር፡፡ምን ሆነው ይሆን ? በማለት ብዙ ይቆዝማሉ፡፡ ለእናታቸው የነበራቸው ስስትና ፍቅር ደግሞ የተለየ ይመስላል፡፡ በልጆቹ የእስር ምክንያት ህይወታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ስጋታቸውን፣ ፍርሃታቸውን፣ የውስጥ ጩኅታቸውን ሳይቀር በእንባ ሳይሆን በቃላት በመግለጽ ለአንባቢ ሲያጋቡት ይታያል፡፡
በአቶ ስዬ መጽሀፍ ውስጥ ያልታየ ጉዳይ አለ ከተባለ አውቀውም ሆነ በስራ ስህተት ምክንያት ያጠፉትን ወይም ካነሱት ትልቅ ርእስ አንጻር የእሳቸውን  አሉታዊ አስተዋጽኦ አለመጠቆማቸው ነው፡፡

በማጠቃለያ ምዕራፍ ያቀረቧቸው ሀሳቦች የተነሱበትን የዳኝነት ነጻነት /ነጻነትና ዳኝነት የሚለው የእሳቸው ርዕስ በተለይም ነጻነት ሰፊ ሃሳብ በመሆኑ ለኔ አልተመቸኝም / መርሆዋች እውን ለማድረግ የምሶሶ ያህል የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ ችግሩ እነዚህን ጸጋዋች እንዴትና በነማን እናግኝ የሚለው ነው፡፡በቅድሚያ እነማን መስዋእትነት ይክፈሉ ነው፡፡ ቢፒአር የተማሩ ትናንሽና ትላልቅ መሪዋችም በሙሉ የሚከተለውን የሃሪ ትሩማን ጥቅስ ሰምተውታል  << A leader is a person who knows the road, who can keep a head, and who can pull others after him. >>

በርግጥ ይህን መሰረታዊ መመሪያ ለማስፈጸም ብዙ፣ ምናበ ሰፊና ሰላማዊ ዝሆኖች ያስፈልጉናል፡፡




No comments:

Post a Comment