ዘራ ያዕቆብ፣
ሀዲስና ብሉይ ኪዳናትን ፣የቤተክርስቲያን አባቶችን ታሪክና ቀኖናዊ ህግጋትን ጠንቅቆ የሚያውቀው ንጉስ ዘራ ያዕቆብ ‹‹ መጽሀፈ ልደት ›› እና ‹‹ መጽሀፈ ብርሃን ›› የተሰኙ መጽሀፍትን ጨምሮ የስርዓተ ቅዳሴ ደንብና መመሪያዋችን የተመለከቱ ሰራዋችን ማበርከቱ ይታወቃል፡፡ የቤተመንግስቱን መቀመጫ ያደረገው ደብረ ብርሃን ውስጥ ሲሆን ህንጻውን እንዲሰሩ ያደረገውም በቤተመንግስቱ ታላላቅ መኳንንቶች ነው፡፡ ስራውን ሳያጠናቅቁም የማዕረግ ልብሳቸውን እንዳያደርጉ ተከልክለው ነበር፡፡ ፍጹም ጀግና እንደነበረና በርካታ አስተዳደራዊ መሻሻል እንዳደረገ የሚነገርለት ዘርያቆብ በርኩስ መናፍስት ፍርሀት ዘወትር ይሸበር ነበር፡፡
መላ ሀገሪቱን ዳር እስከ ዳር ሰጥ ለጥ አድርጎ የመግዛት ችሎታ የነበረው ይህ ሰው፣ ህዝብ በፍርሃትና በስጋት እንዲኖር ያደርግ የነበረ፣ ማንም እንደሚቀበለው ከኤዛና እና ከላሊበላ ቀጥሎ ታላቁ የክርስትና እምነት ሊቅ የሆነው ይህ መሪ፣ በቆራጥነት ሲዋጋቸው የኖሩት የምድራዊና የርኩስ መንፈስ ኅይላት ጉዳት እንዳያደርስቡት በፍርሃት ተውጦ ይኖር እንደነበር ለማመን በርግጥ ይከብዳል፡፡
ጠጉራቸው ከጠንቋዮች እጅ ገብቶ በዚህ ፈሪሀ እግዚሀብሄር ባደረበት መሪና በቤተ መንግስቱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከሚል ፍርሃት የተነሳ፣ የልፍኝ አሽከሮቹ ራሳቸውን እንዳይላጩ ክልክል ነበር፡፡ መነኮሳት በግቢው ውስጥ እየዞሩ ርኩሳን መናፍስትን ለመከላከል ሌትና ቀን ከጠዋት እስከ ማታ ፣ ከምሽት እስከ ንጋት ያለማሰለስ መዝሙረ ዳዊትንና ሌሎች መዝሙሮችን፣ በተለይም ራሱ የቀመረውን ‹‹ አምላክ ገዥ ነው ›› የተሰኝውን መዝሙር እያዜሙ የንጉሱን መኖሪያ ቤት ጸበል ሲረጩ ያድራሉ ይውላሉ፡፡
አስማትን በመፍራት ከቅጥር ግቢው ውስጥ አንድ ትልቅ ጉድጓድ አስቆፍሮ፣ የግቢው ነዋሪ ሁሉ ባለማቋረጥ ጸበል እያመጣ እንዲሞላው ያደርግ ነበር፡፡ ይህ ውሃ ከአስማት ይጠብቃል፣ ከደዌ ይፈውሳል ተብሎ የሚታመን ሲሆን ስርዓተ ጥምቀቱም ይፈጸምበታል፡፡
የኢትዮጽያ ታሪክ / ትርጉም ዓለማየሁ አበበ /
No comments:
Post a Comment