የሌለኝን የ IT ግንዛቤ ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እነሆ ደብረዘይት ከከተምኩ አስር ቀናት ሆኑኝ፡፡ ጓደኞቼ ሲደውሉልኝ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት እንዳለሁ እገልጽ ነበር፡፡
‹‹ እህ ምግብ ለስራ ነሃ! ›› ነበር ቀጣይ ምላሻቸው
ይህን ስያሜ እንዴት ሳልሰማሁ ቀረሁ በሚል ተገረምኩ፡፡ ‹‹ ምግብ ለስራ ›› እና ‹‹ ስራ ለምግብ ›› የሚባሉ ቋንቋዋችን የማውቅበት መልኩ ሌላ ነበር፡፡
መቼም ለምቾት ሩብ ጉዳይ የቀረውን ይህን ግቢ ይህን ስያሜ ማሸከም ጡር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ግቢው በሚያምሩ ዘንባባዋች፣ የተለያዩ የደን እጽዋትና ለአይን ማራኪ በሆኑ አበባዋች የተሞላ ነው፡፡ እነዚህ ደኖች ላይ በልጅነቴ ሳድን የነበርኳቸው ፒተር፣ ዋሽንት፣ ፍላይ ካውቸር፣ ግንደ ቆርቁር፣ ቀሳሚና ቢጮሌ የምንላቸው ወፎች ጣእመ ዜማቸውን እስከምሽቱ ድረስ ይለግሳሉ፡፡ ርግጠኛ ነኝ እንደ እኔ ስራዬ ብሎ የሚያጣጥማቸው ሰው የለም፡፡ ዘወትር ውሃ የሚረጩት ጎማዋች የሳሩ ገላ ትንቡኬ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ምናለፋችሁ ግቢው እንደ ህጻን ገላ የለሰለሰ፣ ሌላው ቀርቶ ልክ እንደ ህጻን ልጅ ዘወትር ሲስቅ የሚሰማ ነው፡፡
77 ደብልና 67 ሲንግል አልጋ የያዙ የሚያምሩ ቤቶችን ይዟል፡፡ በርካታ መማሪያ ክፍሎች፣ መሰብሰቢያ አዳራሾችና መወያያ ክፍሎች አሉት፡፡ ኮምፒውተርና አያሌ መጻህፍትን ያቀፈ ቤተ መጻህፍት፣ ሽንጠ ረጃጅም የምግብና የመዝናኛ አዳራሾች ከህንጻው ቁጥር ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡
የመዝናኛ ነገር ከተነሳ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳሰና የቴኒስ መጫወቻ ሜዳዋች በሚያምሩ ጽዶችና ሳሮች ታጅበው ይቀበልዋታል፡፡ የኮኔክሽን ጉዳይ ገባ - ወጣ የማለት ችግር ቢኖርበትም ቤተመጻኅፍት ቁጭ ብለው ከኢንተርኔት ጋር ያወጋሉ፡፡ላፕቶፕ ከያዙ ደግሞ የተወሰነው የግቢ ክፍል ጋር ተሰይመው በገመድ አልባው ግንኙነት ሩቅ የሚገኝውን ሰርቨር መረጃ አንጣ በማለት ይኮረኩሩታል፡፡
ታዲያ የግቢው እድሜ ቀላል እንዳይመስሎት!! በተመድ የልማት ድርጅት ድጋፍ በ1949 አም ነው የተቋቋመው፡፡ በወቅቱ የተሰጠው ስም ፐብሊክ አድሚንስትሬሽን ኢንስቲትዬት የሚል ነበር፡፡ ‹‹ ስምን መልአክ ያወጣዋል ›› የሚል አባባል ነበር የማውቀው፡፡ ይህን ግቢ ሰይጣን ተተናኩሎት ነው መሰለኝ ከሃትሪክ በላይ አራት ግዜ ስሙን ፐዋውዞታል፡፡
በ1961 - የስራ አስኪያጆች ማሰልጠኛ ማእከል ተባለ
በ1962- የመርሀ ሙያ ማሻሻያና መመዘኛ ማእከል እንደሚገባው ተነገረው
በ1968- የስራ አመራር ማሰልጠኛ መካነ ጥናት እንደሚሻለው ተገለጸለት
ከ1977 በኋላ ደግሞ- የኢትዬጽያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ተብሏል፡፡ በነዚህ ጊዜያት ሁሉ ተጠሪነቱና አላማው ለየቅል ነበር፡፡ አሁን ግን በአጭሩ ምርምር፣ ምክርና ስልጠናን በስፋት እየሰራበት ነው፡፡ የመ/ቤትዋን በጀት ይጭነቀው እንጂ ከሚሰጡት 51 አይነት አጫጭር ስልጠናዋች የፈለጉትን መውሰድ ይችላሉ፡፡
እና እላችኋለሁ ለምሳ 84፣ ለእራት 84፣ ለቁርስ 50፣ በቀን ሁለት ጊዜ ቡናና ሻይ 65 ፣ ለአልጋ 100 ብር ከተመደበ ሲበሉ መዋል ነው፡፡ ለካስ ምድረ ቀጭንና ወፍራም ባስስልጣን እንደ ቀስት እየተወረወረ ይህን ግቢ የሚወረው ለዚህ ነው - ወይ አለማወቅ ደጉ፡፡ መቼም የቡፌ አቀራረባቸው የሚታማ አይደለም፡፡ በሻይ ሰዓት የሚቀርቡ ኩኪሶች ራሱ ራሳቸውን የቻሉ ምሳና ራት መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡ እዚህ ግቢ ከመጣው ጀምሮ የኑሮም ሆነ የኢኮኖሚ ኢንፍሌሽንና ዲፍሌሽን ትዝ ብለውኝ አያውቁም ፡፡ ‹‹ ሆድ ፕላስቲኩ! ከአምስት ቀናት በኋላ ደግሞ እንደ አሪፍ ፓለቲከኛ ሽብልል ብለህ ወደ ቀድሞህ ይዞታህ መመለስን ትችልበታለህ ›› ስል ወቀሳ ቢጤ አቀረብኩለት፡፡
የመንግስት ሰራተኛው ይህን ምርጥ ግቢ ‹‹ ምግብ ለስራ ›› ሲል የሰየመው እንድም ወቅታዊ የምግብ ጥያቄን ስለሚያስረሳ በሌላ በኩል ደግሞ ወደዚህ ስልጠና የተላከ ሰራተኛ የኪስ አበል ስለማያገኝ ነው ፡፡ የሞላውን ሆድ በቢራ ለመሸርሸር አይቻልም ማለት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment