Sunday, April 15, 2012

‎የቆሰለ ስሜት‎

ሰሞኑን ፌስ ቡክ ላይ ያነበብኩት የደመወዝ ጭማሪ ቀልድ ብብቴን በሃይል በመኮርኮሩ ‹‹ ስቄያለሁ ›› ማለት ብቻ አይገልጸውም፡፡ የዚህ ቃል ሱፐርላቲቭ ዲግሪ ምን ይሆን ? አዋ ‹‹ በእጅጉ ተንፈቅፍቄያለሁ! ››

 ‹‹ ጤፍ 1780 ብር በደረሰበት በአሁኑ ወቅት መንግስት እንዴት 73 ብር ብቻ ይጨምራል ? ›› ይለዋል አንዱ ጨጎራው የቆሰለ
 ‹‹ መንግስት ደመወዝ የጨመረው ለጤፍ መግዣ እኮ አይደለም ›› ሌላኛው ቁስለኛ በማሾፍ መልክ ይመልሳል
 ‹‹ እናስ ለምንድነው የጨመረው ? ››
 ‹‹ ለጤፍ መግዣ ሳይሆን ለጤፍ ማስፈጫ ነው ››

መራር ቀልድ ቢሆንም ህይወትን ለማጣፈጥ መሳቅ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ቀልድ በመምህራን ቆዳና ጅማት የተሰራ ይምሰል እንጂ የሁላችንንም አዳርና ውሎ ይመለከታል፡፡ እንደውም እንደዚህ አይነት ጉዳዮች በማይታይ ቁጥርና ማህተም ከመዝገብ ቤት የሚወጡት ‹‹ ለሚመለከተው ሁሉ ! ›› በሚል ርዕስ ይመስለኛል፡፡

ነገሩ ወደው አይስቁ አይነት ነውና እንስቃለን፡፡ ግን ደግሞ ከአፍታ በኋላ እንቆዝማለን፡፡ የተወራውና የሆነውን እያነጻጸርን እንበሽቃለን፡፡ ውሃ በገመድ እንደሚወጣበት ግድጓድ ርቀን ከቆምንበት ሸለቆ ውስጥ፤ ኑሮ ተንደላቆ ወደተኛበት የዳሽን ተራራ አንጋጠን ለማየት እንሞክራለን፡፡ ጨረሩ፣ የሸረሪት ድሩም ሆነ የህይወት ዳመናው ርቀቱን ሲጋርደን ደግሞ ነገር አለሙ ይጨልምብናል፡፡ ያኔ በታችኛው ከንፈር ፈጣሪን በላይኛው ከንፈር መንግስትን እንራገማለን፡፡

የነበረን ተስፋ ካሉብን መቶ ያህል የችግር ቀዳዳዋች ውስጥ አስር ያህሉን እንኳን መድፈን ካልቻለ ስሜታችንን፣ ቁጣችንና ትዕግስታችንን እንዴት ማስተዳደር እንችላለን ? እናም ተድላን ሳይሆን ያለመራብ ሚዛንን የእምነት ያህል በአስተማማኝ መልኩ አንገታችን ላይ ማንጠልጠል ካልቻልን እንዴት አንሰጋም ? ለምን አያመንም ?

የሰሞኑን የመምህራን ስሜት በዚሁ አግባብ ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ሙያው የሚገባውን ሳይሆን ኑሮ ውድነትን ለማሸነፍ ይቻል ዘንድ ጭማሪ ጠየቁ፡፡ ጭማሪው ተፈቀደ፣ መጠኑና ወደፊት የሚራመዱበት መሰላል ጭምር ተገለጸ፡፡ የስኬል ማሻሻያውን ለግዜው ትተን የደመወዝ ጭማሪው ግን ግልጽ ነበር፡፡ አንድ አዲስ ነገር ብቅ ባለ ቁጥር ከበሮን በጣም የሚደልቁ ቡድኖች ሁሌም አሉ፡፡ ከበሮው ‹‹ የመምህራን ህይወት ተሻሻለ፣ መምህር አለፈለት! ›› የሚሉ ድምጾችን አስተጋባ፡፡ ከበሮ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር ነውና በትክክለኛው ሰው መዳፍና ጣቶች ባለመዳበሱ ቅኝቱን ጠብቆ መጓዝ አልቻለም፡፡ እናም ምቾት ነሳ፣ ቁጣን አስነሳ፡፡

ጭማሪው ‹‹ እንደ ጤፍ ማስፈጫ ማነሱ ሳይቀር በስማችን ተነገደበት አሉ፡፡ አንዳንዶቹም ተደፍረናል! ክብራችንና ለሰው ልጆች የምንሰጠው አገልግሎት ተንኳሷል ›› ነበር ያሉት፡፡ የከበሮው ድምጽ ግን ይገርማል፡፡ በዲያቆንና በቄሶች እጅ ሲመታ እንዴት ነበር ከፈጣሪ ጋር የሚቀራረበው ? በማርሽ ባንዶች ነፍስ ያላወቀች ብትር ሲኮረኮር እንዴት ነበር ስሜትን የሚፈነቅለው ? በኦርኬስትራ ቡድን ውስጥ ‹ ክሽ ክሽ › ከሚል ድምጽ ጋር ተዋህዶ ሲሰማ እንዴት ነበር ህብረ- ዜማውን የሚያራምደው ? ለካስ የከበሮ ድምጽ አንዳንዴ ያስጠላል ? ለካስ ከበሮ ሙያና እውነትን ካልያዘ ከሚንከባለል በርሜል አይሻልም ? ለካስ የከበሮ ድምጽ እንደ መብረቅ ያሸብራል ? ለካስ ከበሮ ጡሩንባና ቱሪናፋ! ከሚባሉ ስድቦች ጋርም የዝምድና ሀረግ አለው፡፡
አዋ! ለአነስተኛው ጭማሪ የደስታ መግለጫም ሆነ ማጣፈጫ አንድ ሆኖ ወፍራም ድምጽ የሚያወጣውን ከበሮ ከመምረጥ ይልቅ ፤ ብዙ ሆነው ስስ ድምጽን ሊያመርቱ የሚችሉ መሳሪያዋችን መጠቀም ይሻል እንደነበር ይሰማኛል፡፡ ይህን ድምጽ ‹ ክላሲካል › ወይም ለስላሳ ሙዚቃ ማለት እንችላለን፡፡ ያለ ምንም ጩኅት ረጋ ብሎ መልእክትን ያስተላልፋል፡፡ በርግጥ መልእክቱ አሳዛኝም ሆነ አስደሳች ሊሆን ይችላል፡፡

ግን በጥሞና ሰምቶ የተናደደ ሰው እንኳ መፍትሄውንም በጥሞና እንዲያስብ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የክላሲካል ተምሳሌነቱ ብዙ ነው፡፡ መንግስት የጭማሪውን ዜና በፓስታ አሽጎ ከሆነ አጽናኝ ጽሁፍ ጋር ለመምህራኑ በየአድራሻቸው ቢሰጥ በመጀመሪያ ጨዋነቱንና አክብሮቱን ሊያንጸባርቅ ይችላል፡፡ ሰዋች በተፈጥሮአቸው ክብርና ሞገስ ስለሚፈልጉ የብሩ ማነስ ሳይሆን የመንግስት ትህትና አሸንፏቸው ለሁለመናቸው ልጓም ያዘጋጃሉ፡፡ ነገሮች ሁሉ የጉዟቸውን ሃዲድ የሚይዙት ከግራና ቀኝ፣ ከፊትና ኋላ ምልከታና ውሳኔ በኋላ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ብሎም መልካም አስተዳደርን ለማሳደግ የማይናቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ርግጥ ፓለቲካው ይህን ለማድረግ አቅም ወይም የተዘረጋ ስርዓት አለው ወይ ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ቀላል አይደለም፡፡

የክላሲካሉ ሙዚቃ ሌላ ጥቅም ዛሬ በርካታ መምህራን ያሰጋቸውን ፍርሃት መቀነሱ ነው፡፡ ዛሬ ‹ ደመወዝ ተጨመረ! › የሚለውን ወሬ የሰማ ነጋዴ ወይም ቤት አከራይ በማግስቱ ከበሮውን የሚደልቀው ሰቅጣጭ በሆነ መልኩ መሆኑን ከልምድ እናውቃለን፡፡ ቢያንስ ጤፍ ላይ 400፣ የቤት ኪራይ ላይ 100 ብር ቢጨመር ውጤቱ ምን ይሆናል ? አሁን በተጨመረው ገንዘብ ላይ ሌላ ፐርሰንት ጨምሮ መስጠት ፡፡ ላለው ይጨመራል - ይላል መጽሀፉ ፤ የሌለው ከነገም ህይወቱ ተበድሮም ቢሆን ይከፍላል - መጽሀፉ ባይልም ግዴታው ይኅው ነው ፡፡ እንግዲህ ‹‹ ግፍ ›› በህግ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር ከዚህ የተሻለ ትርጉም ሊመጣለት አይችልም፡፡ መንግስት እነዚህን ግፎች መከላከል ያለበት ሰዶ- በማሳደድ ሳይሆን አስቀድሞ ብልጥ በመሆን ነው፡፡ ለድሃ አጋር የሆኑ ስልቶችን በመንደፍ ፡፡

በጥንታዊ ግሪክ፣ ቻይናና ህንድ ትምህርት የሚካሄደው በቄሶችና በአዋቂዋች ነበር፡፡ በጥንት ግሪክ የኪነጥበብ፣ ፓለቲካና ፍልስፍና ጉዳዬች ከፍተኛ ቦታ ስለነበራቸው ለልጆች ለማስተላለፍ ልዩ ጥረት ተደርጓል፡፡ በጥልቅ ፍልስፍናቸው የምናውቃቸው እነ ቴልስ፣ አናክስማንደር፣ ፓይታጎረስ፣ ሶቅራጥስ፣ ፕሌቶ፣ አሪስቶትል አንቱ የተባሉት በሚያነሱት ሀሳቦችና በሚፈጥሩአቸው አዳዲስ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ከሊቅ እሰከ ደቂቅ በማስተማራቸው ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅትም በቻይና፣ ታይዋን፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ኮሪያ፣ አሜሪካ፣ ደ/አፍሪካ በመሳሰሉ ሀገሮች መምህራን ምርጥ ተከፋይ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል በጃፓን የተራ መምህራን እርከን 36 ደረጃ አለው፡፡ ሁለተኛው እርከን ላይ የሚገኝ መምህር በወር 156 ሺህ 500 የን የሚያገኝ ሲሆን የመጨረሻው እርከን 455 ሺህ 900 ይደርሳል፡፡ ለመሪ መምህር 26 ለዳይሬክተር ደግሞ 15 እርከን የተፈቀደ ሲሆን እንደቅደም ተከተላቸው 488 ሺህ 400 እና 516 ሺህ 200 የን ያገኛሉ፡፡ በአውስትራሊያ አራት ዓመት የሰለጠነ መምህር በአመት 41 ሺህ 109 ዶላር ሲያገኝ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ 58 ሺህ 692 ዶላር ያገኛል፡፡ ዳይሬክተሩ እስከ 95 ሺህ 106 ዶላር ይከፈለዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ አምስት ዓመት ልምድ ያለው መምህር 115 ሺህ 276 ራንድ ሲያገኝ ከ5 – 9 ዓመት ልምድ ካለው 146 ሺህ 087 ይደርሳል፡፡ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚገኝ አንድ የአሜሪካ መምህር 43 ሺህ 695 ዶላር ነው በዓመት የሚያገኝው፡፡ ይህን ሂሳብ ወደ እኛ ብንቀይረው በወር 61 ሺህ 901 ብር አካባቢ ይመጣል፡፡ የአፍሪካ ሀገሮች አሀዝ ከዚህ ይነስ እንጂ የሚያበረታታ ነው፡፡ ይህም መንግስት የሰጠውን ቦታ የሚያመላክት ሲሆን በኢኮኖሚ የደረጀ መምህር በራሱ የሚተማመንና ምርታማ ዜጋ እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡ በእኛ እውነታ የእድገታችን ነገር ላይፈቅደው ይችላል….
የሀገራችን መምህራን ግን እንደስራቸው ተመጣጣኝ ተከፋይ አይደሉም፡፡ የኢኮኖሚ አቅማቸው ለንቋሳ በመሆኑ ደግሞ ለብዙ ችግሮች ተጋላጭ ናቸው፡፡ በሀገራችን በጋዜጠኝነትና በህዝብ ግንኙነት ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዋችን የኋላ ታሪክ ስናጠና የምናውቀው አብዛኛው መምህራን የነበሩ መሆናቸውን ነው፡፡ ለምን ሙያውን ቀየሩ ? ለሚለው ጥያቄ ቀድሞ የሚመጣው ምላሽ በህብረተሰቡም ሆነ በተማሪው ተፈላጊውን አክብሮት ባለመግኝታቸው ነው፡፡

አንዳንድ ተማሪ አስፈራርቶ ዘርቶ ያላጨደውን ማርክ ይቀበላቸዋል፡፡ ወር የማያደርሳቸውን ደመወዝ በማስላት ፍላጎቱን ይገዛቸዋል፡፡ ጎጃምና ሌሎች ከተሞች ብትሄዱ ተማሪና አስተማሪ እኩል እየተሳፈጡ ጠላ ይጠጣሉ፡፡ በብዙ ከተሞች ተማሪዋች አሰተማሪያቸውን ድራፍትም ሆነ ጫት ይጋብዛሉ፡፡

በአ/አበባና ትላልቅ ከተሞች ተማሪው ከመምህሩ የተሻለ ሞባይል፣ የተሻለ ላፕቶፕ፣ የተሻለ አልባሳት አለው፡፡ ሞባይላቸውን ክፍል ውስጥ እንዲዘጉ ለተማሪዋች የተናገሩ መምህራን ‹‹ እናንተ ስለሌላችሁ ነው! ›› ተብለው ተስቆባቸዋል፡፡ ጭንቅላቱን ሳይሆን ኪሱ በፈጠረበት የአቅም ችግር ሊሰደብ፣ ተገቢ ያልሆነ አግቦ ሊደርስበት ይችላል፡፡ ይህም በራስ መተማመኑ እንዲሸረሸር ያደርገዋል ፤ ይሸማቀቃል፡፡ ሌላ ምሳሌ ልጨምር፡፡ አንድ ጎረምሳ አንዲት ወጣት ሰሌዳውን ካጠፋች በኋላ ከንፈሯን ይስማል፡፡ አስተማሪ ከሆናችሁ

‹‹ ምን እያደረክ ነው አንተ?! ›› ማለታችሁ በጣም የግድ ነው
‹‹ ቾኩን እየጠረኩላት ! ›› ጎረምሳው ሳይጨነቅ ይመልሳል
‹‹ በእጅህ አትጠርግም እንዴ ታዲያ ?! ›› ንዴቶት ጨምሯል
‹‹ አይ ቲቸር እጅ እጅ እንዳይል ብዬ ነው! ››

ይህ ምላሽ ያስቅዋታል ወይስ ያበሽቅዋታል፡፡ አሁንም ወደው አይስቁ ማለታችን አይቀርም፡፡ ክፍለግዜው የቲያትር ቢሆን ይህ ምላሽ ባልገረመ ነበር፡፡ ግን መምህር ፊት በድፍረት ብዙ ነገር ይደረጋል፡፡ መምህር የሚያስተምረው ቀለምን ብቻ ሳይሆን ስነ ምግባርን ነው፡፡ በጉዳዩም ይጨቃጨቃል፤ ይሰደባል፤ ይመታል፡፡ እናም ሁልግዜ ስራውን ሳይሆን ከኋላ የሚሰለፉ አላስፈላጊ ጉዳዬች ላይ እንዲያተኩር ያደርገዋል፡፡ ደረጃ በደረጃም ሙያውንና ራሱን መጥላትና ሃላፊነቱን በአግባቡ አለመወጣት ይከተላል፡፡

ታዲያ የትምህርት ጥራት እንዴት ይፈጠራል ? የነገ ሀገር ተረካቢው ትውልድ ምግባርና ብቃት እንዴት ይረጋገጣል ? እናም የመምህራንን ክብርና አቅም አንድም ለተገቢነቱ በጣም ቢያንስ ግን ለልጆቻችንና ለነገው ዜጋ ስንል እናሰድግ፤ እናለምልም፡፡

No comments:

Post a Comment