Sunday, April 15, 2012

‎ዳንዲ የነጋሶ መንገድ‎



‹ዳንዲ የነጋሶ መንገድ›› በዳንኤል ተፈራ የተዘጋጀ ፣በዶክተር ነጋሶ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ፓለቲካ ቀመስ መጽሀፍ ነው፡፡ በመጽሀፉ ትረካ መሰረት የምናስብ ከሆነ ዶክተሩ ምስኪን ወይም ታማኝ ፓለቲከኛ መስለው ይታዩናል፡፡ በርግጥ ታማኝነት እንዴትና ለማን የሚሉ መሰረታዊ ጥቄዋችን መመለስ ይኖርብናል፡፡ ዶክተሩ በፍጹም ብልጣብልጥ አይደሉም፣ ዲፕሎማት አይደሉም፣ ብዙ ግዜ ፓለቲካ የሚጠይቀውን አስመሳይነት፣ ፈጣጣነት፣ ዋሾነትና ጨካኝነት ዕውን የሚያደርግ ነፍስ የላቸውም፡፡ ታዲያ እንዴት ፓለቲከኛ ሆኑ? ይህን ስራ እንደማይተውም ይናገራሉ- እንዴት ይዘልቁት ይሆን? ለግዜው ቅርብ የሆነው መልስ እንጃ በመሆኑ እንጃ ብያለሁ እኔም፡፡ ለማንኛውም አንዳንድ ሀሳባቸውን እነሆ…….የነጋሶ መንገድ…..

ሲጋራ እንዴት እንደጀመሩ

በእደ ማርያም አዳሪ ትምህርት ቤት ተደራራቢ አልጋ ላይ ተኝተን አለማየሁ ከታች ሆኖ ቫይስሮይውን ሲያቦነው እኔ ከላይ ሆኜ አሸታለሁ፡፡ በኋላ ‹‹ እንካ እስኪ ሞክረው›› ብሎ ይሰጠኝና ስሞክረው ጣመኝ፡፡ በዚያው አጫሽ ሆንኩ፡፡ ‹‹ እንካ አጭስ›› ሲለኝ የነበረው በኋላ ‹‹ እኔ አልሰጥህም እራስህ ግዛና አጭስ›› ማለት ጀመረ፡፡ በኋላ ኒያላ መጣ፡፡ ኒያላ መመረት ከጀመረ አንስቶ ነው ደንበኛ አጫሽ የሆንኩት፡፡ ባለቤቴም ከኒያላ ሌላ አጢሳ አትውቅም

የብሔር ጭቆና አጀማመር

አጼ ምኒሊክ ይከተሉት የነበረው ስርዓት ባላባታዊ ነው፡፡ ይህ ገዥ መደብ የመጣው አማርኛ ተናጋሪ ከሆኑ ህዝቦች ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የበላይነትን እንዲያገኝ ክርስትያን ያልሆኑትን ሁሉ በግድ ያጠምቁ ነበር፡፡የአስተዳደሩ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ሌሎች ሃይማኖታቸውን፣ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲተው የተደረገበት ሁኔታ ነበር፡፡ በኢትዮጽያ የብሄር ጭቆና የተጀመረው ያን ጊዜ ይመስለኛል፡፡

የተቃውሞ ሰልፍ እንዴት ይበተን ነበር?

ያኔ ተቃውሞን ለመከላከል በጣም ከበዛባቸው አንዳንድ ተማሪዋችን ያስራሉ፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ከኛ ጋር ግብግብ በመግጠም ወይ በጭስ ነበር የሚበትኑት፡፡ አሁን ግን ተቃዋሚ ሰልፈኞች በጥይት ተቆልተዉ የሚበተኑበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ያውም በዚህ ዘመን…

መንግስት ህዝብን ይፈራ/ያከብር ነበር?!

ዙምባቤ ነጻ ትውጣ በማለት እንግሊዝ ኤምባሲ ፊት ለፊት ተሰለፍን፡፡ ያኔም ከፓሊስ ጋር ተጋጭተናል፡፡ እነዋለልኝን አስረዋቸው ነበር፡፡ እኛ ደግሞ እነዋለልኝ ይፈቱ ብለን ሰልፍ ወጣን፡፡ አፍሰው ወደ ሰንሳፋ ሲወስዱን ኮተቤ ላይ ስንደርስ አንድ ልጅ ከመኪና ላይ ወድቆ ይሞታል፡፡ ወሪው በአዲስ አበባ ይዛመትና ከተማዋ ቀውጢ ሆነች፡፡ ፈርተው በማግስቱ ፈቱን፡፡

ሚሲዮኖች በወለጋ እንዴት በዙ?

ሚሲዮኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሸዋ መጥተው ለመንቀሳቀስ አጼ ሚኒሊክን ፈቃድ እንዲሰጧቸው ሲጠይቋቸው እሳቸውም ‹‹ ሸዋ፣አርሲ፣ሀረርና ጅማ ክርስቲያኖችና እስላሞች ስለሆኑ የሚሲዮን ትምህርት አያስፈልጋቸውም እናንተ መሄድ ያለባችሁ ገና ወዳልሰለጠነውና አሁንም አረመኔ ወደሆነው ጠረፍ አካባቢ ነው አሏቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ወለጋ ሄደው አስተማሩ

የመጀመሪያው የኦሮሞ የትግል እንቅስቃሴ

የኦሮሞን ህዝብ እግዚሀብሄር ከሰማይ መጥቶ አይታደገውም ስለዚህ ራሱ ተደራጅቶ ለመብቱ መታገል አለበት…. የሚል አቋም ይዘን መቀስቀስ አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ጽሁፎችን ማዘጋጀት ይኖርብናል ብለን ርዕሰ ጉዳይ ተከፋፍለን መጽሔት ለማዘጋጀት በቃን፡፡ መጽሔቱ ‹‹ oromo voice against tyranny›› የሚል ነበር፡፡ በኋላ በአማርኛና በኦሮምኛ ተተርጉማ  ቀርባለች፡፡ የሚያሳዝነው በመጽሔቷ የተነሳ ብዙዋች ለእስር ተዳርገው ነበር፡፡

የመጀመሪያ ፍቅር

በ13 ዓመቴ ከሚዛን ወደ ደምቢዶሎ የተባረርኩት በፍቅር ምክንያት ነው፡፡ ከበቡሽ ሀብት ይመር የምትባል የመንደራችን ልጅ እና እኔ በጣም እንወደድ ነበር፡፡ የ18 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ አቶ ከበደ ጨብራሻ አገባት፡፡ ስታገባ ድንግል አልነበረችም፡፡ ለካ የአካባቢው ሰው ድንግልናዋን የወሰደው ነጋሶ ነው ብለው ያሙኝ ኖሯል፡፡ እኔና አቶ ከበደ ኳስ ሜዳ የተጣላን ጊዜ በዚህ ምክንያት ነው ብለው ሰዋች ለአባቴ ሲነግሯቸው ‹‹ ይሄንን አድርጎ ከሆነ እቀጣዋለሁ›› ብለው ወደ ደምቢዶሎ መለሱኝ፡፡

የመጀመሪያው ትዳር

በ1964 ዓም ክረምት ላይ ደሲቱን አገባሁ፡፡ በዓመቱ በ1965 ኢብሳ ተወለደ፡፡ ኢብሳ ያልንበት ምክንያት ለሁለት ሳምንት ተቋርጦ የነበረው መብራት ልክ እሱ በተወለደ ማታ ስለበራ ነው፡፡ ኢብሳ ማለት ደግሞ የሚያበራ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛዋ ልጃችን ጃለሌ ናት…
የኦነግ መቋቋም

እዚህ በነበርኩ ጊዜ አዲሱ፣ ጸጋዬ፣ዮሀንስ፣ለታና ዮሀንስ ኖጎ የሚባሉ የድሮ ጓደኞቼን አግኝቻቸው አወራን፡፡ ማታ ማታ ይጠፋሉ፡፡ ‹‹ ማታ የት ሄዳችሁ?›› ስላቸው ‹‹ ስበሰባ ነበረን›› ይሉኛል፡፡ ለካ ኦነግን እያቋቋሙ ነበር፡፡ እኔን ግን ስብሰባቸው ላይ አይጠሩኝም፡፡ በህብዑ ነበር የሚሰሩት፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እነ ባሮ ቱምሳ ፣ጄኔራል ታደሰ ብሩ፣ ዲማ ነጋዋ፣ ዮሀንስ ለታ ዮሀንስ ኖጎ እና አዲሱ ቶሎሳ አዲስ ፕሮግራም በማዘጋጀት ስራ ላይ ተጠምደው ነበር፡፡

ታሪክ ሰሪው ሌንጮ

በ1967 ዓም መጀመሪያ ንጉሱ ከተወገዱ በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ በተደረገ በሳምንቱ ወደ ጀርመን ሄድኩ፡፡ ሌንጮ/ዮሀንስ ለታ ወደ ጀርመን እሄዳለሁ ብዮው ሲሸኘኝ፣
‹‹ ምን ለመማር ነው የምትሄደው?›› አለኝ
‹‹ ታሪክ››
‹‹ አንተ ሄደህ ታሪክ ተማር፣ እኛ እዚህ ታሪክ እንሰራለን!›› ብሎ አሾፈብኝ

ለዶክትሬትዲግሪ ያቀረቡት የመመረቂያ ጽሁፍ

<<The history of seyyoo oromo of south western wallaga, Ethiopia from 1730 to 1986>>
ዲግሪውን ያገኙት በ1977 ዓም ነው፡፡

የአልማዝ መኮ/የፓለቲከኞች/ ሁለት መልክ

አልማዝ ኦሮሞ ስለሆነች የኦህዴድ አባል እንድትሆን ለማግባባት ሞክሬ ነበር፡፡ እምቢ አለች፡፡ ቆይቶ የኦሮሚያ አስተዳደር ስራ አስፈጻሚዋች፣ የኦሮሚያ ሴቶች ቢሮ ሃላፊ ሆና አየኋት፡፡ ሰኔ 15 ቀን 1993 ዓም እኔ ከኢህአዴግ ስብሰባ በለቀቅኩ ዕለት ታዲያ ለኢህአዴግ ተቆርቋሪ ሆና ‹‹ ነጋሶ ሂሳቡን ሳያወራርድ እንዴት ይወጣል?›› ብላ ትችት ሰነዘረች፡፡ የሚገርመው ይህን ባለች በሳምንቱ ለስብሰባ ወደ ብራዚል ተልካ፣ በኒውዬርክ ስታልፍ እዛው ጥገኝነት ጠይቃ መቅረቷን ሰማን፡፡ ብዙም ሳትቆይ የኦነግ አባል መሆኗ ተወራ፡፡

የደስታ እንባ?

ኢህአዴግ አዲስ አበባን የተቆጣጠረ ጊዜ መለስ ለንደን ሆኖ ምን እንደተሰማው የነገረኝን አስታውሳለሁ፡፡ ‹‹ አሜሪካኖች ‹ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ› ሲሉን ከደስታዬ ብዛት አለቀስኩ!›› ነበር ያለኝ

ማስተከከያ

በኤርትራ ሪፈረንደሙ በሚካሄድ
በት ጊዜ ድምጽ መስጫው ‹‹ ባርነት ወይስ ነጻነት›› የሚል ነው ተብሎ የተወራው ትክክል አይደለም፡፡ የድምጽ መስጫው ‹‹ ነጻነት ትፈልጋለህ ወይስ አትፈልግም;› ›› የሚል ምርጫ ነበር፡፡

ሽርሽር በነጠላ ጫማ

የነጻነትቸው ቀን ሲከበር መለስ ኤርትራ ሄዶ በትግርኛ ንግግር ሲያደርግ  እኔም ነበርኩ፡፡ እኔ፣ መለስና ኢሳያስ / ስሊፐር ጫማ አድርጎ/ ከተማ ውስጥ ዞረናል፡፡ በእውነት ትልቅ ነጻነት ነበር የተሰማኝ፡፡ ሱቅ እየገባን፣ ማታ ማታ እየዞርን አንድ ሁለት ቦታ መጠጥ እየተጎነጨን ተዝናንተናል፡፡ ያረፍነው በራሰው ካሳ ቤት ውስጥ ነበር፡፡

የመምሪያ ሃላፊዋቹ እንዴት ተባረሩ?

ኢህአዴግ በ1983 ዓም ሀገሪቱን ሲቆጣጠር ከማስታወቂያ ሚኒስትሩ ዲማ ነጋዋ በቀር የመምሪያ ሃላፊዋች በሙሉ  የኢህአዴግ ታጋዬች ነበሩ፡፡ የፕሬስ መምሪያ ተስፋዬ ገብረአብ፣ የቴሌቪዥን አማረ አረጋዊ፣ የኢዚአ መዝሙር ፋንቴ፣ የኦሮምኛ ፕሮግራም ሃላፊ ደግፌ ቡላ እና የኦሮምኛ ራዲዬ ፕሮግራም ሱሌይማን ደደፎ ነበሩ፡፡…. ታዲያ ባደረግናቸው ግምገማዋች አንዳንዶቹ የአቅም ፣ ሌሎቹ የሙያ ፣ ቀሪዋቹ ደግሞ የስነምግባር ችግር ነበረባቸው፡፡ ለምሳሌ ሙስናን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለዜና ስራ አበልና መኪና ተመድቦላቸው እነሱ ማስታወቂያ ይሰራሉ፡፡ በሰራተኛው ላይ አምባገነን የመሆንና ሌሎች ችግሮችንም ይፈጥራሉ፡፡ ሴቶችን ያመናጭቃሉ፣ በዘመድ ይሰራሉ፡፡ የአመለከከትም ችግር ነበረባቸው፡፡ ለስሙ የኢህአዴግን ነገር ያስቀድማሉ፣ የብሄሮችን መብት በተመለከተ ግን ትምክህተኝነትና ጠባብነት የሚያራምዱ ነበሩ፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ሁሉንም እንዲለቁ አድርገናል፡፡ በዙዋችን ወደ ኢህአዴግ ተቋማት -ፋና፣ ዋልታ፣ ሲዛወሩ ተስፋዬ ገብረአብ ወደ እፎይታ መጽሄት ተልኳል፡፡ ከነአካቴው እንዳይባረሩ ደግሞ ሁሉም ታጋዬች ናቸው፡፡

ዝነኛው አንቀጽ 39

እኔና ዳዊት አንቀጽ 39 መኖር አለበት፣ መሬትም መሸጥ መለወጥ የለበትም የሚል አቋም ይዘን ተከራክረናል፡፡ የብሄር ጥያቄን በተመለከተ የኦሮሞ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብቱ እስከመገንጠል መከበር አለበት የሚል ነበር አቋሜ፡፡ እዚህ ጋ መገንጠል አለበት ማለትና የመገንጠል መብቱ ይከበርለት ማለት ልዩነት እንዳለው ልብ ማለት ያሻል፡፡ አሁንም የህዝቡ የራሱን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱ መከበር ትክክለኛ ነው፣ ዴሞክራሲያዊም ነው እላለሁ፡፡

የፕሬዝዳንቱ ቤት

ይገርምሃል ! ሌላ ሀገር አንድ ርዕሰ- ብሄርን እንዲህ አድርገው ይይዛሉ? አላውቅም፡፡ እነዛ አሮጌ ቤቶች በራቸው ሲዘጋ ከስር አይጦች ያስገባ ነበር፡፡

እጅ መንሻ

ባለስልጣኖች ጉብኝት በሚያደርጉበት ጊዜ የአካባቢው ትናንሽ ባለስጣናት ከአካባቢው ነዋሪዋች ላይ ቅቤ፣ በግ፣ ከብት እና ሌላም ሌላ ነገር እየሰበሰቡ ሲሰጧቸው ታዝቤያለሁ፡፡ በእኔ ስም ይዘው እንዳይመጡ በጥበቅ አስጠነቅቃቸው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ግን ከባሌ አገልግል ጭነው ይዘውልኝ እንደመጡ አስታውሳለሁ፡፡ አሁን እነ አባዱላና እነ መለስ በየአካባቢው አንዴ ጋቢ፣ሌላ ጊዜ በሬ ተበረከተላቸው የሚባለውን ስሰማ ‹‹ ወዴት እየሄድን ነው? ›› እላለሁ፡፡ እንደኔ እንደኔ ትክክል አይደለም፡፡

የግም-ገማ ጣጣ

የፋይናንስ ቢሮን  ይመራ የነበረውን አቶ አለማየሁ ደሳለኝን ስንገመግም ቆይተን ሳንጨርስ ለምሳ ወጣን፡፡ ከምሳ ስንመለስ አለማየሁ ቤተመንግስት  ግቢ ውስጥ  ራሱን በሽጉጥ ገደለ፡፡ የሚያሳዝነው አለማየሁ በግምገማው ምንም አልተገኘበትም፣ ንጽህነቱን ልንነግረው ነበር፡፡ ግምገማው እጅግ ከባድ ስለሆነ የሚያለቅሱና እንደ እብድ  የሚያደርጋቸው ነበሩ፡፡

በሰው ልክ የሚሰፉ አዋጆች

አቶ ስዬ አብርሃ ተከስሶ ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ ፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበረችው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በዋስ ልትለቀው እንደሆነ ታወቀ፡፡ ይሔኔ ‹‹ አቶ ስዬ በዋስ እንዳይለቀቅ ቶሎ አዋጅ መውጣት አለበት›› ተባለና የወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተፈራ ዋልዋ ደወለልኝና ‹‹ እባክህ በፓርላማ በኩል ጸድቆ የመጣውን አዋጅ ቶሎ ፈርምልን›› አለኝ

የአልጀርሱ ስምምነት

የአልጀርሱን ስምምነት ለመፈረም በተስማማንበት ወቅት አዲሱ ለገሰ መናደዱ ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹ ከዚህ በኋላ በሻዕቢያና በህውኀት መካከል ችግር ተፈጥሮ ወደ ጦርነት የምንገባ ከሆነ የኛን ህዝብ ሂዱና ተዋጉ ብዬ አልቀሰቅስም!›› አለ፡፡ የሆኖ ሆኖ የአልጀርሱ ስምምነት በፓርላማ ጸድቀ፡፡ እኔም በስነስርዓቱ መሰረት ፈርሜያለሁ፡፡ ‹‹ ያለ ቅድመ ሁኔታ የአልጀርሱን ስምምነት እንቀበላለን›› ብለን ለመፈረም መወሰናችን ትልቅ ስህተት ነበር፡፡

የነስዩም ስህተት

ስዬም መስፍንና አሊ አብዶ ህዝቡን አስወጥተው ‹‹ ባድሜ ለኛ ተፈረደ›› ብለው ሲያውጁና ሲያስጨፍሩ እኔ ወለጋ ነበርኩ፡፡ እነሱ ያደረጉት ትክክል አልነበረም፡፡….. እኛን በሚጎዳ መልኩ መወሰኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡

የመለስ ደብዳቤ

በክፍፍሉ ወቅት መለስ ለኦህዴድ ደብዳቤ ሲጽፍ የኢህአዴግ ማህተሞች በውህዳኑ እጅ ስለነበሩ በህወሃት ማህተም ይጠቀም ነበር፡፡ ይሄን በተመለከተ በደብዳቤው መጨረሻ ያሰፈረው ሃሳብ ዘና የሚያደርግ ነው፡፡ ‹‹ አንጃው ማህተሞቹን ህገወጥ በሆነ መንገድ ስለዘረፈ የኢህአዴግን ማህተም ላሰፍር አልቻልኩም›› ይልና ‹‹ የመንግስት ማህተም ያለበት ደብዳቤ ከዚህ ቀደም ጽፌ በናንተ በኩል ሂስ ስለቀረበብኝ ፣ ማህተም የሌለው ደብዳቤ መጻፍም የሚያስከትለውን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት በኢህአዴግ ሊቀመንበርነቴ በምጽፈው ደብዳቤ ላይ የማሰፍረው ማህተም በማጣቴ፣ በህወሀት ማህተም ለመጠቀም ተገድጃለሁ››

ነጭ ካፒታሊዝም

ከሁሉም በላይ ግን ከዚህ ድርጅት ጋር መቀጠል የለብኝም ብዬ እንድወስን ያስገደደኝ ፣ ኢህአዴግ የሚመራበትን ርዕዮተ ዓለም እንደቀየረ በተገለጸ ጊዜ ነው፡፡ በስብሰባው ‹‹ ማርክሲስት ሌኒኒስት አለ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ‹‹ የሶሻሊዝም ጉዳይ ቀረ ወይ?>>
‹‹ ማርክሲስት ሌኒንስት ከ1983 ዓም ጀምሮ የለም፡፡ ሰዋች ቢኖሩም እንደ ቡድን ኢህአዴግን የሚመራ ርዕዬተ ዓለም መሆኑ ቀርቷል፡፡ ሶሻሊዝምን በተመለከተ ከ1983 ጀምሮ ጠረጼዛ ስር ደብቀነዋል፡፡ ከምዕራባዊያን ድጋፍ ለማግኝትና የኢትጽያ ሀዝብ በደርግ የተነሳ ስለጠላው ነጭ ካፒታሊዝም ነው የምናራምደው›› አለ መለስ
‹‹ እስከ መቼ››
‹‹ ይሄ የኔ ጉዳይ አይደለም፡፡ እስከ ልጅ ልጅ ሊዘልቅ ይችላል፡፡ ምናልባት በልጆቼና በልጅ ልጆቼ ዘመን ሊሆን ይችላል፡፡›› አለ መለስ ሲመልስ
‹‹ ይሄን መቼ ወሰናችሁ?›› ተብሎ ሲጠየቅ ደግሞ ‹‹ ከ1983 ዓም ጀምሮ ነው›› አለ፡፡ ብዙ ሰው ነው ብግን ያለው፣ ምክንያቱም የኢህአዴግ ፕሮግራም እንዲህ አይልማ፡፡ እኔማ ቅ-ጥ-ል አልኩ፡፡ ለካ አስር አመት ሙሉ አታሎን ነበር፡፡



No comments:

Post a Comment