Wednesday, December 18, 2013

ሊቨርፑል በገና ዋዜማ





ሰማዩ እጅግ ከፍቶታል ...

እንዲህ መሆን ከጀመረ ቆየ ።

አምቆ የያዘውን ጥቁር እባጭ የመሰለ ነገር ዘርግፎ ቢጨርሰው ሰላም ባገኘ ነበር ። ግና ቁጣ እንዳስበረገገው የአበሻ ህጻን ቆይቶ - ቆይቶ ነው ጠብ የሚያደርገው - ርግጥ ነው እንደ ህጻን ችክ ያለ ማላዘን አይታይበትም ።

ተጠሪነቱ ለደመናው ይሁን ለምድሪቱ ያልታወቀው ብርድ ግን የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል ። አንዳንዴ በግልጽ እንደ ውሻ ይናከሳል ... አንዳንዴ እንደ ስለታማ ቢላ አካልን ይሰነጥቃል ። በግላጭ በሚያገኛቸው ጆሮ ፣ አፍንጫና የእጅ ጣቶች ላይ ደግሞ ጥቃቱ ለጉድ ነው ። እንደ ንብ ነድፎ - ነድፎ በረዶ ቤት የተቀመጡ ዕቃዎች ያደርጋቸዋል ።

ምድሪቱ ጉንጭ ላይ ስስ ፈገግታ ይታያል ...

ዓላማና ግቧ ግን ሙሉ ፊቷ ላይ ሳቅ እንደፈንዲሻ እንዲተራመስ ማስቻል ነው ። እናም ግብግብ ላይ ናት ። በረዶው ፣ ንፋሱ ፣ ብርዱ ፣ ዝናብና ጭጋጉ የቱንም ያህል ጥቃት ቢያደርስብን የገና በዓላችንን ከማድመቅ አይገድብንም የሚሉት ሊቨርፑዲያንስ ሙሉ ከተማውን ሞልተው ይሮጣሉ ። ሩጫቸውን ከንግድ ቤቶች የሚወጣው የገና ሙዚቃ ያግዛቸዋል ። ታላቅ ቅናሽ እያሉ በማይክራፎን የሚያላዝኑት ሱቆችም በረከቱ እንዳያመልጣቸው አጥብቀው ይወተውታሉ ። እዚህ እንደ እኛ ሀገር ዶሮና በግ ጥጋቸውን ይዘው አይጮሁም ። ሳርና ችቦ የሚቸረችሩ ወቅታዊ ነጋዴዎች ማየት አይቻልም ፤ አየሩ በተነጠረ ቅቤ ፣ በኮባና ኩበት ጢሳጢስ የተሞላ አይደለም ።

በርግጥም አየሩን የተቆጣጠሩት አብረቅራቂ መብራቶችና ሙዚቃዎች ናቸው ። መኖሪያ ቤቶች ፣ ህንጻዋችና « ሲቲ ሴንተር » የተባለው የገበያ ቦታ ለአይን በሚማርኩ የመብራት ውጤቶች ተንቆጥቁጧል ። ከሱቆቹ በተጨማሪ እዚህም እዚያም የተለያዩ የሙዚቃ ስራዋችን የሚያሳዩ ግለሰቦች እንደ አሸን ፈልተዋል ። ትላልቅ ሴቶች ሳይቀር አኮርዲዮን እጥፍ ዘርጋ እያደረጉ ሳንቲም ይሰበስባሉ ። ሁለት ሶስት ሆነው ቆርቆሮን እንደ ከበሮ በመጠቀም የመንግስት ማርሽ ባንድን የሚያስንቁ ሰዋችም ይታያሉ ። በአርሞኒካ ብቻ የብዙዋቹን ትዝታ የሚያማልል ፣ እንዲሁም ከውሻው ጋር ቁጭ ብሎ የሚመስጥ መሳሪያ የሚጫወት ሌላ ሰው በሌላ ክንፍ አይታጡም ።

በስነስርዓት ማይክራፎንና ኪቦርድ አዘጋጅቶ የፈረንጆቹን ሙዚቃ የሚጫወት አንድ አፍሪካዊ ግን ብዙ ግዜ የብዙዋችን ትኩረት ሲስብ ተመልክቼያለሁ ። ተመልካቹ ክብ ሰርቶ አፉን ከፍቶ ፣ አንገቱን ግራና ቀኝ እየናጠ ይመለከተዋል ። አንዳንዶቹ ደግሞ መሃል ገብተው ይወዛወዛሉ ። ይህን ሰው X – Factor አያውቀውም ወይስ X – Factor / የእንግሊዞች ታዋቂ አይዶል ሾው / አንጋሎ የተፋው ነው ? ድምጹ ብርዱንና ውሽንፍሩን በታትኖ ከጆሮ የሚደርሰው ሳይደናቀፍ ነው - አይጎረብጥም ። የዳጎሰ ልምድ ያለው መሆኑ ለተራ ሰውም ግልጽ ነው  - አንዳንዶች ሊወኒልን ሪቼ እያሉ ይጠሩታል ። በርግጥም የታዋቂውን አቀንቃኝ አንድ ሙዚቃ ሲያቀነቅን ነበር ፣

Good bye  ይለዋል ታዳሚውን እንደሚሰናበት ሁሉ  

I wanted you for life
You and me
In the wind
I never thought there come a time
That our story would end
It’s hard to understand
But I guess I’ll have to try
It’s not easy
To say good bye ... good bye ... good bye ..


ሙዚቃውን ሲጨርስ ታዲያ የሚሰሙት ጭብጨባ አንድ ትልቅ ቲያትር ቤት የታደሙ ያህል ነው ። ከዚያም ፊት ለፊት ባስቀመጠው ሻንጣ ውስጥ የእንግሊዝ ነጭና ቀይ ሳንቲሞች ሲንቦጫረቁ ይሰማል ።

አፍሪካዊው አቀንቃኝ

ሙዚቃ ወዳዱ የሊቨርፑል ነዋሪ ሲጋራውን እያቦነነ ፣ ሀምበርገሩን እየገመጠ ፣ የሚጠጣውንም እየተጎነጨ ያዳምጣል ። የዚህ ከተማ ሃምሳ የሚደርሱ አቀንቃኞች በምድረ እንግሊዝ ብቻ ሳይሆን በዓለማቀፍ ደረጃም ትልቅ ስም ያላቸው ናቸው ። ሙዚቃዋቹ ለጆሮ በደረሱበት ዘመን በሽያጭ ረገድ ቁጥር አንድ በመባላቸው ከተማዋ በጊነስ ቡክ ላይ የሙዚቀኞች ሀገር ለመባል አስችሏታል። በ1960 የተመሰረተውን The Beatles ብቻ ለአብነት ማንሳት ይቻላል ። አራቱ የቡድኑ አባላት ጆን ሊኖን ፣ ፓውል ማካትኒ ፣ ጆርጅ ሀሪሰን እና ሪጎን ስታር በ1962 « Love Me Do » የሚለውን አልበም እንደለቀቁ ነበር ታዋቂነትን የተጎናጸፉት ። ሮሊንግ ስቶን ሙዚቀኞቹን የምንግዜም ትልቅ አርቲስቶች ብሏቸዋል ። ታይም መጽሄት በበኩሉ የሃያኛው መቶ ክፍለዘመን መቶ ተጽዕኖ ፈጣሪ ብሎ ከዘረዘራቸው ግለሰቦች መካከል አስፍሯቸዋል ። የፈረደበት ጊነስ ቡክ ወርልድ የሙዚቀኞቹን « Yesterday » የተባለው ሙዚቃ ከሶስት ሺህ አርቲስቶች በላይ ከእንደገና ተጫውተውታል ይለናል ። አስደናቂው ነገር እንዲህ ተደጋግሞ የተዘፈነበት ሌላ ሙዚቃ አለመኖሩ ነው ።

በከተማው መሃል ለገና እየቀረበ ያለው ሌላው ስጦታ የግለሰቦች « ምትሃታዊ » ስራ ነው ። ለነገሩ አስማት ይባል ሌላ ጥበብ በድፍረት መናገር ቸግሮኛል ። እስኪ አንድ አጭር « ሾው » በጽሁፍ እንከታተል ፤

 አንድ ሰው ሻንጣ ይዞ መጣ ።
ከሻንጣው ውስጥ የሚያብረቀርቅ ልብስ አውጥቶ ለበሰ ።
 አናቱ ላይ  ቀንድ ያለው ማክስ አጠለቀ ።
ፊቱንም ልብሱን የመሰለ ነገር ተቀብቶታል ።
የልብሱን ቀለም የመሰለች ብትር አወጣ ።
ዙሪያ ገባውን ማትሮ በፈገግታ እጁን አወዛወዘ ።
በአካባቢው መንኮራኮር የለም እንጂ ወደ ላይ ለመምጠቅ የመጨረሻ ሰላምታ የሚሰጥ ነበር የሚመስለው ።
 መሬቱ ላይ ጥቁር ጨርቅ አነጠፈ ።

የፈራነው ደረሰ ?

እንዴ ? ... ዱላውን ተሞርኩዞ በአየር ላይ ቁጭ አለ ። በቃ ! ... ይወርዳል ብለን ብንጠብቅ - ብንጠብቅ ቁጭ እንዳለ ቀረ ። መቼም ይህ ሰው ሊንሳፈፍ የቻለው ጭንቅላቱን « ጨረቃ ላይ ነህ » ብሎ በማሳመኑ ሊሆን አይችልም ። ብዙዋቹ በጥበቡ በመገረም ሳይሆን በፍርሃትና በጥራጣሬ ነበር የሚመለከቱት ። እንዴት ሊሆን ቻለ ? ሰውነቱ ውስጥ የቀበረው ነገር ይኖር ይሆን ? በዜና ያልሰማነው ምን የሚያንሳፍፍ መሳሪያ ተገኘ ? መልስ አልነበረም ። ሳንቲም ወርወር ሲያደርጉለት ብቻ እጁን በአፉ እየሳመ ፈገግ ይላል ። ከዚያ ውጪ ኮስተር ስላለ ጥሩ ቀራጺ የሰራው ሃውልት ነው የሚመስለው ።

ተንሳፋፊው ሰው

 « ይገርማል » እያልኩ ሌላውን የገበያ አቅጣጫ መከተል ጀመርኩ ። የማስበው ስለ ምትሃት ነበር ። አስማት ጥበብ ነው ፣ ሳይንስ ነው ፣ ፈጣን የጭንቅላት ጨዋታ ነው ፣ በባዕድ አምልኮ ጋር የተገናኘ መንፈሳዊ ስራ ነው ... ብዙ ብዙ ይባላል ። ድንገት አባባ ተስፋዬ ሳህሉ በአእምሮዬ ጔዳ ብቅ አሉ ። በቴሌቪዥን መስኮት የምትሃት ጥበብ እያሉ ገመድ ሲቌጥሩና ሲፈቱ ፣ ጨርቅ ሲያሳዩና ሲሰውሩ  ብዙዎቻችን ተመልክተናቸዋል ። ምናልባትም ለአስማትና ምትሃት ያለን የእውቀት ጥግ ያንን ያህል በመሆኑ ሊሆን ይችላል አድናቆታችን አለቅጥ የሚረዝመው ።

ስለ አስማት የሚያውጠነጥነው አእምሮዬ ተጨማሪ ነገር የፈለገ ይመስል ከሌላ ምትሃተኛ ጋር ተገጣጠምኩ ። ይሄኛው ደግሞ በሙሉ ልብስ ዝንጥ ያለ ነው ። የያዛትን ዣንጥላ አንዴ ይደገፋታል ፣ ሌላ ግዜ ይዘረጋታል ። እየሰራ ያለውን ነገር በግልጽ እንድትረዱት ለማድረግ የግድ ስዕላዊ ገለጻ መጠቀም አለብኝ ። ለምሳሌ ያህል መደገፊያው ራቅ ያለ ምርጥ ሶፋ ላይ እግራችሁን አንፈራጣችሁ ቁጭ ብላችኃል እንበል ። ቀስ ተብሎ ሶፋው ከስራችሁ ሸርተት ቢደረግ ቁጭ እንዳላችሁ ትቀራላጭሁ ወይስ ሚዛን ስለማይኖራችሁ ትወድቃላችሁ ? መልሱ ግልጽ ነው ። እንግዲህ ይህ ምትሃተኛ አየር ላይ የተቀመጠው ሶፋው ከተነሳበት በኃላ መሆኑ ነው ። ሙሉ ሚዛኑን እየተቆጣጠረ ያለው በሁለት እግሩ ነው ። እስኪ ሞክሩት ።
ወገብዋ እንክትክት ቢል ግን የለሁበትም ።

አየርን ተደግፎ መቀመጥ

ከገበያው ግርግር ወጥቼ አስገራሚ ስነጥበብ ያረፈባቸውን ህንጻዋች ፣ ሙዚየሞችና የስዕል ጋለሪዋች እየተመለከትኩ ስጔዝ እግሬን አልበርት ወደብ አካባቢ አገኘሁት ። እየቸኮልኩ ነበር ። ምክንያቱም እዚህ ሀገር የሚጨልመው ከቀኑ አራት ሰዓት / በእኛ 10 /  ጀምሮ በመሆኑ ብርሃንን መሻመት አለብኝ ። ጠዋት አንድ ሰዓት ሆኖም ጨለማው እንደተዘፈዘፈ ነው ። ካላወቁ ጠዋት ቀጠሮ ይዘው እንኴ « እረ አልነጋም » ብለው ይተኛሉ ። አስራ ሁለት ሰዓት ሲሆን የምሽት ስንብትንና የመንጋት መምጣትን ወፎች በጨኀት አያበስሩም ። ለነገሩ የቤት ርግብ እንጂ ወፍ ይኑር አይኑር ርግጠኛ መሆን አልቻልኩም ። ውስን ወፎች ቢኖሩ እንኴ እንቅልፋሙን ሰው የመቀስቀስ ግዴታ የሌለባቸው ይሆናል ። ምክንያቱም ይህ ዴሞክራሲ የበዛበት እንግሊዝ ነውና ። ስለዚህ ጠዋት ስራ ገቢ ከሆኑ ሰዓት ሞልተው ጆሮዎ ስር አላርሙን በወፍ ዜማ ማስጮህ ይኖርቦታል ።

ይሄ የመምሸት ነገር ግን እንደሚመስለኝ ቀን ያለ ሰዓቱ ወደ ምድር የሚወረወረው ተፈጥሯዊ ሬንጅ በማግስቱም ከመሬት ለመላቀቅ የሚገጥመው ፍትጊያ ቀላል አይደለም ። እጅ ላይ የፈሰሰ የበረሃ ሙጫ በሉት ። « ወግድልኝ » ብትሉትም ሙጭጭ ብሎ እየተሳበ የሚልመጠመጥ ። እናም እስከ የካቲት ድረስ ጸሃይ ብቻ ሳትሆን ቀንም ራሱ ብርቅ ይሆናል ነው የሚባለው ።

በስመዓም ... አልበርት ወደብ በጣም ይጎበኛል ። ከጥንታዊነቱም ከዘርፈ ብዙ አገልግሎት ሰጪነቱ አኴያ ሊሆን ይችላል ። በ1846 ነው የተገነባው ። ይሁን እንጂ ቡና ቤቶች ፣ ሱቆች ፣ ሆቴሎች ፣ የባህር ትራንዚትና የአለማቀፍ ባርነት ሙዚየሞች እንዲሁም የ ዘ ቢትልሶችን ታሪክ አቅፎ ይዟል ። በግዜውም በያዘው ሰፊ ቦታና ተግባር ከዓለማችን ቁጥር አንድ ነበር ።

የከተማው አዛውንቶች ታዲያ ዉሻ እያስከተሉ ነው ወደቡን የሚጎበኙት - በልብስ ያጌጡ ውሾች ። ውሾቹ ግን የሌላ ሀገር ምርጥ ተሞክሮ እጥረት ያለባቸው ነው የሚመስሉት ። ምክንያቱም መናከስ፣ ማስደንገጥ ቢያንስ መጮህ የተባለውን የዘመዶቻቸውን ቌንቌ የት እንዳደረሱት አይታወቅም ። ማንም ቢያባብላቸውና ቢደባብሳቸው ግድ የላቸውም ። የሚታያቸው ቶሎ ብሎ የውስጥ ገላቸውን ፈርከስከስ አድርጎ ማቅረቡ ነው ። ዉሻ ካልጮኀ ደግሞ በግ ሊመስል ይችላል ። የሀገሬ ሰው ግድጔድ ቆፍሮ ቀብሮ ፣ ቢቻል ተርብ እያበላ አሳድጎ ዉሻው ጸጉረ ልውጥ ሰው ጅርባ ላይ ፊጥ ሲልማ መመልከት ይፈልጋል ። አለዚያማ እንደ አውደልዳይ ዉሻ መንገድ ላይ ይጣላል ። የዚህ ሀገር ዉሾች ውሎአቸው መኪናና ቡናቤት አዳራቸው ደግሞ ሳሎን ነው ። ውሻ የሚያሳድጉበት ዋና አላማም ሰውንም ሆነ ሌባ ማስደንገጥ አይመስልም ። ታዲያ ምንድነው ከተባለ የእንስሳት ፍቅር ወይም ሆቢ ብሎ ማለፍ ይቻላል ።

         እንዳልኴችሁ የሊቨርፑል ወደብ ከተማዋ እንድታድግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጔል ። ይህን ወደብ ጨምሮ ስድስት የሚደርሱ አካባቢዋችም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ የሰፈሩ ናቸው ። ታዋቂው ብዕረኛ ቻርልስ ዲከንስም  ወደቡን « ሃብታሙና ማራኪው » በማለት ነበር የገለጸው ።

አልበርት ዶክ 

በነገራችን ላይ ዳንኤል ዴፎ ፣ ዋሽንግተን ኢርቪንግ ፣ ቻርልስ ዲከንስና ሌሎች ታዋቂ የጥበብ ሰዋች ሊቨርፑልን ጎብኝተዋል ። ደጋግሞ በመጎብኘት ምናልባትም አስራ ሁለት ግዜ ዲከንስን የሚያህል የለም ። ደራሲው ደጋግሞ የሚመጣው መጽሀፎቹን ለመጻፍ ይረዳው ዘንድ አንዳንድ ነገሮችን ለመመርመር ፣ መድረክ ላይ ተጋብዞ ለመናገርና የራሱን ስራዎች ለማንበብ ነው ። እንደሚታወቀው ሃያ የሚደርሱ መጽሀፍትን ለአንባቢያንን አበርክቶ ነው ያለፈው ። ስነጽሁፍ በኮሌጅ የተማረም Great expectation , Oliver twist , A tale of two cities , Hard times እና The pick wick papers የተባሉ ስራዎቹን አይረሳም ። እኔ በወቅቱ ዲክንስ ከአደፍርሱ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ጋር ይመሳሰልብኝ ነበር ። ሁለቱም ቃላትን አጥብቀው የሚወዱ ፣ በቃላት መራቀቅ የሚፈልጉ « Wordy » የሚባሉ አይነቶች ናቸው ። ጹሁፉን በአግባቡ ተረድተን የቤት ስራችንን ለመስራት በጣም እንቸገር ነበር ። አደፍርስንስ ስንት ግዜ ነው እየጀመርኩ የተውኩት ? የቁጠኛውን ዳኛቸውን ባላውቅም ዲክነስ ፍጹም የመድረክ ተናጋሪና ተከራካሪ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ ። ዲክነስ እንደ ንግግሩ ሁሉ ጹሁፎቹ ለጥቅስ የሚበቁ ናቸው ። ለዛሬ ግን የሚከተለውን ላስታውስለት ፣

« No one is useless in this world who lightens the burden of another . »

ከአልበርት ወደብ አካባቢ ሆኖ ጀምስ መንገድ ላይ የሚገኘው የአልቢዎን ሀውስ ይታያል ። ይህ ህንጻ ሲነሳ ደግሞ ሊቨርፑልና ታይታኒክ የተባለችው ታሪካዊ መርከብ የነበራቸውን ጥብቅ ቁርኝት መረዳት ያስችላል ። እንደሚታወቀው ከመርከቧ የፈት ገጽ ላይ ታይታኒክ ከሚለው ጽሁፍ በታች Liver Pool የሚል ጽሁፍ ይታያል ። ይህ የሆነው የካምፓኒው ጽ/ቤት / አልቢዎን  ሀውስ / እዚህ በመገኘቱ መርከቧ የተመዘገበችው በከተማው ስም ስለሆነ ነው ።

የታይታኒክ ማዋለጃ ቤት

ታይታኒክ የተጸነሰችውም ሆነ የመጨረሻውን ዲዛይን የያዘችው በሊቨርፑል ይሁን እንጂ ነፍስ ዘርታ መንቀሳቀስ በጀመረችበት ወቅት ሊቨርፑልን ማየት አልቻለችም ። ሌላው ቁርኝት ከመርከቧ ሰራተኞች 90 ያህሉ በተለይም ታይታኒክ ከበረዶ ጋር ስትጋጭ የተመለከቱትን ሁለት ሰዋች ጨምሮ የተቀጠሩት ከሊቨርፑል መሆኑ ነው ። ፊልሙን ባየነው መሰረት የሰውየው አጯጯህ  እንዴት ነበር ? « የበረዶ ቌጥኝ ይታየኛል ! ... የበረዶ ቌጥኝ ይታየኛል ! ... » ምን ዋጋ አለው አንዳንዶች ዘግይቶ ሪፖርት አድርጔል በማለት ከርፋፋ ሲሉት ሌሎች ደግሞ ስራውን በአግባቡ የተወጣ ጀግና ያደርጉታል ። መርከቧ ስትሰምጥ ምንም ሳያቌርጡ ሲዘፍኑ የነበሩ ሙዚቀኞችን እንዲሳፈሩ ያደረጋቸው ወኪል የሚገኘውም በሊቨርፑል ነው ። ባይሆን የሙዚቀኞቹ ነገር እጅግ ይገርማል ። ሰው ህይወቱን ለማትረፍ ላይ ታች ሲራኮት የእነሱ ነፍስ ግን በሙዚቃው ሃይል ውስጥ ተውጦ ነበር ። ሊቨርፑልና የሙዚቃ ፍቅርን በማያያዝ እነዚህ ሰዎች ሊቨርፑዲያን ነበሩ ማለት አይቻል ይሆን ? አላውቅም ። የመርከቧ የሞተር ክፍል / Engine / የተሰራውም ሊቨርፑል በሚገኝ ድርጅት ነው ። ለታይታኒክ ሞተር ክፍል ሰራተኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በዋተር ፍሮንት ሃውልት ቆሟል ።

ይህ ታሪካዊ ህንጻ በአሁኑ ወቅት ምን እየተሰራበት እንደሆነ ባላውቅም / ምናልባትም ለሽያጭ ቀርቦ ይሆናል / እንደ ታሪካዊነቱ በአግባቡ የተያዘ አይመስልም ። ሶስቱ በግማሽ ጨረቃ ቅርጽ የተሰሩት የፊት ለፊት በሮቹ ተዘግተዋል ። በጎን በኩል የሚገኘውም እንደዚሁ የታሸገ ነው - የዚህኛው ልዩነቱ ከበሩ ጀርባ የቆሻሻ ክምር መታየቱ ነው ። ምናልባትም የታይታኒክ ቅርጽ ይኖረው ይሆን በሚል ጥርጣሬ ራቅ ብዬ አጠናሁት ። ባለ ሶስቱ ፎቅ ህንጻ በምንም ተዓምር መርከቢቷን አይመስልም ። እረ ታይታኒክ ቅንጡ ህንጻ ነበረች ። ለነገሩ ለግንባታዋ የፈሰሰው ዶላር ቀላል አይደለም -  7.5 ሚሊየን ። 3547 ሰዎችን አሳፍራ በኩራት ነበር ባህሩን የምትሰነጥቀው ። አጠቃላይ ቁመቷም ቢሆን 11 ፎቅ ርዝመት ካለው ህንጻ ጋር የሚተካከል ነው ። ውስጧስ ቢሆን ዘመናዊ ሆስፒታልን ጨምሮ ምን የሌላት ነገር አለ ?

ህንጻውን እየራቅኩት ስሄድ በሆነ ነገር ላመሳስለው እየፈለኩ ነበር ። በል ቻዎ ስለው የታይታኒክ ማጀቢያ የሆነው የሴሊንዲዮን my heart will go on የሚለው ዜማ ከየት አባቱ እንደመጣ አላውቅም ። ውስጤ ለአፍታ ያህል የተንጫጫ መሰለኝ ፣

Every night in my dream
I see you , I feel you
That is how I know you go on
Far across the distance
And spaces between us
You have come to show you go on
Near , far , wherever you are
I belive that the heart does go on
Once more you open the door
And you’re here in my heart
And my heart will go on and on


እቺ ከአየርላንዱ ደብሊን እና ከጀርመኗ ኮሎኝ መሃል የምትገኝ መካከለኛ ከተማ የፊልም አምራች ድርጅቶችንም ቀልብ መግዛት የቻለች ናት ። captain America , In the name of the father , Sherlock holmes , Fast and furious 6 , Harry potter and the dealthy hallows የተባሉ ትላልቅ ስራዋችን ጨምሮ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ፊልሞች ተቀርጾባታል ።

ዛሬ እነዚህ ታሪካዊ ቦታዋች በሙሉ ዋና ትኩረታቸው የፊልም ኢንዱስትሪውንና ጊነስ ቡክን መሳብ ሳይሆን በቅርቡ የሚከበረውን የገና በዓል ደማቅ ማድረግ ይመስላል ። Remember , if Christmas isn’t found in your heart , you won’t find it under a tree . የሚለው አባባልም ለበዓሉ የሚሰጠውን ግዙፍ ክብር አመልካች ነው ። ለማንኛውም መልካም ገና ይሁንላቸው ማለት ይገባል ።

ግልባጭ ፣
ጥቂት ቆይቶ ብቅ ለሚለው አትዮጽያዊው ገና ።

No comments:

Post a Comment