Sunday, April 19, 2015

የረጋ ደም ፍትህ ይወጣዋል ?


 
ደቡብ አፍሪካው አሰቃቂ ፍጅትና ወንጀል ብዙ ጥያቄዎችን እንድናነሳ እያደረገን ነው ። የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ አንዳንድ ሀገሮች በተገቢው ፍጥነት ወንጀልን የመከላከል ተግባር ወስደዋል ። ወንጀልን መከላከል የሁሉም መንግስታት የጋራ ግዴታና ሃላፊነት ነውና ።
1 . ኢትዮጽያ ሀገራችን  ያው እንደልማዷ ጉዳዩን ግዜያዊ ክስተት በማድረግ የወንጀል መከላከል ተግባሩን በእርጋታ ለመፍታት እየሰራች መሆኗን በአስራ አንደኛው ሰዓት ገልጻለች ። በሀገራችን የእርጋታ ርምጃዎች ውስጥ የብሄራዊ ስሜት ቀለም መደብዘዝ ፣ የዲፕሎማሲ እውቀት እጥረት ፣ ስልጣንን በአግባቡ አለመወጣትና ህዝባዊ ሃላፊነትን አለመረዳት ፍንትው ብለው ታይተዋል ።
ለምሳሌ ያህል ከህዝብ ጋር በማህበራዊ ድረ ገጽ ቅርበት የፈጠሩት ዶክተር ቴዎድሮስ ችግሩን በእርጋታ ማየት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል - ይህን ሀሳብ የመንግስትም ሀሳብ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ። መንግስት ችግር አልደረሰም ብሎ ሁኔታውን ካልካደ በስተቀር እንደ አምቡላንስ ወይም እሳት አደጋ መኪና በፍጥነት መሮጥ ነበረበት ። ምክንያቱም ሰው እያለቀ ወይም ቤት እየተቃጠለ መጀመሪያ በጉዳዩ ዙሪያ አውደ ጥናት ይዘጋጅ ማለት አይቻልም ።
በነገራችን ላይ ልክ እንደ ዶክተር ቴዎድሮስ የዙምባብዌ የአካባቢና ማስታወቂያ ሚንስትሮች ትዊተራቸውን ይጠቀማሉ ። የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሩ ሳቪየር ጥቃቱን የገለጹት << አሳፋሪና ከአፓርታይድም የከፋ >> በማለት ሲሆን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ጆናታን ደግሞ << የዛሬ የዉጭ ሀገር ሰዎች ጥላቻ ነገ ወደ ጅምላ ጭፍጨፋ የሚያድግ ነው >> በማለት ነበር ። የባለስልጣናቱ አስተያየት ውስጥ ሀገራዊ መቆርቆር ብቻ ሳይሆን አሻግሮ የማየትንም ብስለት እንመለከታለን ። የአፍሪካ የግጭት መንስኤዎችንና አሰከፊ መዳረሻዎቻቸውን የምንፈትሽ ከሆነ የተጠቀሰው ስጋት ትክክል የማይሆንበት መሰረት አይኖረውም ።
ስለዚህ አርቆ በመመልከት ህዝባዊ ሃላፊነትን በትኩሱ መወጣት በአንድ በኩል ፣ ዲፕሎማሲው የሚፈልገውን የኤሊ ርምጃ ለግዜው ገለል አድርጎ እንደ አቦሸማኔ መወርወር በዚህ ግዜ ትክክል ይሆናሉ ። የዲፕሎማሲውን እሹሩሩ ከጀርባ ላይ አውርዶ አካፋን አካፋ ማለትም በዚህን ግዜ አስፈላጊ ነው ። ምክንያቱም ወንጀልንና ኢስብዓዊ ድርጊትን ያላወገዘ ብሎም ያላጋለጠ መንግስት ለሰው ልጆችና ለአለማቀፉ ህግ መቆሙ በምን ይረጋገጣል ?
2 . እንደ እኛ መንግስት ሁሉ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ታላላቅ የሰላም አባቶችና ስመ ጥር ፖለቲከኞች ድምጻቸውን ማጥፋታቸውም አጠያያቂ ነው ።
የማንዴላን መቀመጫ የተረከቡት ታምቦ ምቤኪ ልክ እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ << ህልም አለኝ >> ፣ እሳቸውም የሚታወቁበት << እኔ አፍሪካዊ ነኝ - I AM AN AFRICAN >> የሚል የሞራል ፍልስፍና አላቸው ። በዚህ መሳጭ ንግግር ውስጥ << እኔ የተወለድኩት ከአፍሪካ አህጉር ህዝቦች ነው >> ይላሉ - እኚህ ሰው ደቡብ አፍሪካዊ ብቻ አይደሉም ማለት ነው ። የብዙ አፍሪካዊያን ደም በሀገራቸው ሲፈስ ግን ቃል መተንፈስ አልቻሉም ። << የሶማሊያ ፣ የላይቤሪያ ፣ የሱዳን ፣ የቡሩንዲ ፣ የአልጂሪያ ህዝቦች በግጭት የሚደርስባቸው ሀመም እኔም የተሸከምኩት ህመም ነው >> ይላል ፍልስፍናቸው ። ዛሬ የቆንጨራ ስለት በየአስፋልቱ ሲፋጭ << እረ ህመሜ ጀመረኝ >> ማለት አልቻሉም ። ስቃይን ፣ ግርፋትን ፣ እስርን ፣ ስደትን ፣ አድልዋን ወዘተ የሚቃወመው ሀሳባቸው ለሰው ልጅ ክብርንና ልእልናም ያዜማል ። ቃናቸው ፣ የዜማቸው አወራረድ ፣ የቃላታቸው ከፍታ ፣ የሃሳባቸው ርቀት ለደቡብ አፍሪካ ብቻ አይደለም ምናልባትም ለአንድ ቀንዋ ፓን አፍሪካ መሪነት ያሳጫቸዋል ። አፍሪካዊው ታምቦ በሚስብ መልኩ ከጻፉት ሞራላዊ ህግጋት ውስጥ ጥቂት ስንኞችን ማንበቢያ ግዜያቸው አሁን ነበር - ግና ጉዳዩን << በእርጋታና በትዕግስት >>  እያጠኑት ይመስላል 
የሰላም ዘብ ናቸው ብሎ አለም በ1984 የሰላም ሽልማት አክሊል የደፋላቸው ዴዝሞን ቱቱም እንደኛ መንግስት ተመቻችተው የተኙ መስለዋል ። እኚህ ሰው አይደለም በርካታ አፍሪካዊያን እየተጨፈጨፉና እየተዋከቡ ባሉበት ወቅት ለግብረሶዶማዊያን መብት እንኳ ከልክ በላይ የተሟገቱ ነበር ። << ግብረሶዶማዊያንን ማግለል አፓርታይድን እንደመደገፍ ነው >> በሚለው ጥብቅ ሀሳባቸውም ይታወቃሉ ። ዛሬ የሀገራቸው ዜኖፊያ በርካታዎችን ሲረግጥና ሲያስጨንቅ << እርጋታ >> እያሉ ይመስላል ። የፍትህና የይቅርታን ፕሮጄክቶችን በመመስረት ትልቅ ስራም መስራታቸው ይታወቃል ። እነዚህ ፕሮጄክቶች ነገ የሀገራቸውን አጥፊዎች እንዲጠየቁ የማያደርግ ከሆነ ግን በሽልማታቸው ጉዳይ መጠያያቃችን አይቀሬ ይሆናል ።
በርግጥ የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል
የረጋ ደም ፍትህ ይወጣው ይሆን ?