የደነበረ
በሬን የሚያረጋጋው ሁለተኛ አካል የለም ። በሬው መረጋጋት የሚችለው የራሱ የድንጋጤና የፍርሃት ድልቂያ በራሱ ግዜ እየሳሳ ሄዶ
ጸጥ ማለት ሲጀምር ነው ።
እንደእኔ
እምነት ኢህአዴግ ከደነበረው መንፈስ ገና አልተላቀቀም ። ድርጅቱ ገመድ በጥሶ መሮጥ የጀመረው በ1997 « እንከን የለሽ » ምርጫ
ወቅት ነበር ። ዘጠኝ የእፎይታ አመታት በማለፉ ረጅም ቢሆንም እስካሁን እንከን የለሽ መረጋጋት አልፈጠረለትም ። ምክንያቱም ጉዳቱ
ከስሜታዊ ቁስል ወደ ስነልቦና ጉዳት ሳይታወቅ ያደገ / Trauma / በመሆኑ ተመሳሳይ ግዜያትን ጠብቆ ሊገነፍል ስለሚችል ።
ያኔ በስንት
ደምና አጥንት ያመጣነው ድል ድንገት ከከተማ በበቀለ እንጉዳይ / ድርጅት / እንዴት ይነጠቃል ? በሚል የአጥቢያ ድል አለቆቻችን
ሳይቀሩ ቢሮ ዘግተው እዬዬ ብለዋል ። የቅንጅት ጉዳይ ያው በሚታወቀው መልኩ ከተዘጋ በኃላ በሬው እየፎገረ ማባረር የጀመረው «
ሀሳብ » ን ነበር - ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን ። በዚህም በርካታ የህትመት ውጤቶች ከገበያው ድራሻቸው ጠፋ ። በሬው ይህን
ርምጃ የወሰደው በግራና ቀኝ ጆሮው ላይ መርፌ እየወጉ ከሚያስፈረጥጡት አካላት አንደኛው መሆናቸውን በመረዳቱ ነው
።
ከዚያ
ወዲህም ከዴሞክራሲ መብቶች አንዱ የሆነው ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ከአደገኛ ቀጠና ውስጥ መውጣት አልቻለም ። አንዴ ፈንጂ
ወረዳ ስለሆንክ ግራና ቀኝህን ተመልከት ሲባል ሌላ ግዜ ቀይ መስመሩን አትጠጋ ወይም አትርገጥ ሲባል እየተሳቀቀ ቆይቷል ። በርግጥ
የሀገራችን ህገ መንግስት ለዚህ መብት መበልጸግና መፋፋት በጽሁፍ ደረጃ ድጋፍ ይሰጣል ። ጋዜጠኛው አንዳንዴ ይህን እያሰበ የተወሰነ
ርቀት ሲጔዝ ቢታይም ድንገት ከሩቅ የሚተኮስ ድሽቃ ከአፈር ይቀላቅለዋል ። ብእረኞቹ በሚደርስባቸው ተጽዕኖ ሲያማርሩና ሲያቃስቱ
፣ ከታፈረውና ከተከበረው ውክቢያ ጋር ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ፣ መፈክር ይሁን ቁጣ ባለየ መልኩ ሲገሰልባቸው ፣ አንዳንዴም
ሲታሰሩ ማየት ብርቅ አልሆነም ።
በመሰረቱ
ኦትዮጽያ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌን የህጔ አካል አድርጋ ተቀብላለች ። ይህም ግዙፍ ክሬዲት ሆኖ በየስብሰባው ምስጋና መወድስ ተዘርፎለታል
። አንዳንድ ነጭ ጥናት አቅራቢዎች < ኢትዬጽያን ተመልከቱ የህገ መንግስቷ አብዛኛው ገላ በሰብዓዊ መብት መልካም መዓዛ የታወደ
ነው ፣ የኢትዬጽያን መንገድ ተከተሉ በስብዕና ፍቅር ትሰክራላችሁና > በማለት ምስክርነት ሲያቀርቡ ... እሰይ አበጀሽ የኛ
ሎጋ አበጀሽ የኛ ልጅ .... እያልን ማስታወሻችን ላይ አንጎራጉረናል ። በየአለማቀፉ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ታዋቂው አንቀጽ /
19 / ሁሉም ሰው ሀሳቡንና አስተያየቱን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በማንኛውም ሚዲያ መግለጽ እንደሚችል ይደነግጋል ። ህገ መንግስታችን
አባባሉን እንዳለ ወስዶ የአንቀጹን ቁጥር ብቻ ነው 29 ያደረገው ። ውበት ነበረው ። መልክ ብቻ ምን ያደርጋል ሆነ እንጂ ። በነገራችን
ላይ ይህ መብት የተሰጠው ለጋዜጠኛው ብቻም አልነበረም ። በመሆኑም ሀሳብ መግለጫው ድልድይ በታሸገ ወይም በተሰበረ ቁጥር የመብት ግፊያና
ነጠቃ እየደረሰበት የሚገኘው ብዙሃኑ ጭምር ሆነ ማለት ነው ።
ለማደግ
በመፍጨርጨር ላይ በምትገኝ ሀገር ውስጥ ደፋር ፣ ነቃሽ ፣ እውነት አመላካችና ባለሶስት አይን ጋዜጠኛ አስፈላጊ ነው ። ምክንያቱም
ማደግ የሚቻለው የልማት አጀንዳን እያግበሰበሱ ዴሞክራሲንና ነጻነትን በማስራብ አይደለም ። ማደግ የሚቻለው በልዩ ተዓምር ሳይሆን
ጥሩና መጥፎውን ፣ ሜዳና ገደሉን ለይቶ ሚዛናዊ መስመር ማስመር ሲቻል ነው ። በተቃራኒው ለምን የድርጅቴ ሀሳብ ተብጠለጠለ ? ለምን
የድርጅቴ አመራር ተተቸ ? በተቌሜ ክፍተት ሳይሆን በተክለቁመናው ለምን የገነፈለ የብእር ቀለም ተደፋበት ? ወዘተ በሚሉ እፍኝ
ሰበቦች ጋዜጠኛውን ማስፈራራት ፣ ማሸማቀቅ ብሎም ወደ ወህኒ ቤት መወርወር በእውነት አሳፋሪ ተግባር ነው - መሰበር ያለበት ጭምር
።
ድርጅቱ
በዚህ ረገድ ያለው ስዕል የደበዘዘ ነው ። ሲፒጄ ታህሳስ 2013 ባወጣው መግለጫ ከአፍሪካ ብዙ ጋዜጠኞችን በማሰር ኤርትራ ፣ ኢትዬጽያና
ግብጽን የሚያህል የለም ። መንግስት በጸረ ሽብር ተግባር አንጂ በጋዜጠኝነት ያሰርኩት ሰው የለም ቢልም ማስተባበያው ለብዙዎች የተዋጠ
አልሆነም ። ይህን መረጃ እውነት ነው ብለን ብንቀበል እንኴ በተከታታይ የተፈጸሙ ሌሎች ተግባራት ጥርጣሬ ውስጥ እንድንገባ አድርገውናል
። ለምሳሌ ፍሪደም ሃውስ የተባለው ድርጅት መንግስት 65 የዜናና አስተያየት ፣ 14 የፖለቲካ ድርጅቶች እና 27 ብሎጎች መዘጋታቸውን
ግልጽ ማድረጉ ይታወቃል ። መንግስት ከድርጅቶች ጋር በርዕዬተ አለም ልዩነት ብቻ ሳይሆን ወንበርዋን ለዘለዓለም በማስጠበቅ ሹኽቻ
ሊኖቆር ቢችልም ከግለሰቦች ጋር ታች ወርዶ የሚፈጥረው ግርግር ግን አሳማኝ አይደለም ። በሌላ አነጋገር የግለሰቦችን ብሎግ መዝጋት
የግለሰቦችን እምነት ፣ አስተሳሰብና ፍልስፍና መርገጥ ነው ። የግለሰቦችን ብሎግ መዝጋት በሃሳብ ነጻነት አጀንዳ ዙሪያ ብዙ አለማወቅን
ወይም ደንታ ቢስነትን ያመላክታል ። እንደናንተ ሳይሆን እንደእኔ አስቡ ብሎ ፈላጭ ቆራጭ መንገድን ማሳየትን ያስገነዝባል ።
ጸሀፊዎች
አቌማቸው ግራም ሆነ ቀኝ ፣ ሊበራልም ሆነ ዴሞክራት ወይም እምነት የለሽ መከበር አለበት ። መንግስት በተሰደበና በተተቸ ቁጥር
ብዕረኛን የሚያስር ከሆነ በነጻ ሃሳብን የመግለጽ ትርጔሜ አረዳድ ላይ ችግር አለ ማለት ነው ። እንግዲህ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች
ከዚህም በላይ ነው የሚሉት ። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን መብቱን ከህገ መንግስቱ በድፍረት ልጦ ማንሳትን ይጠይቃል ።
መንግስት
በሪፖርቶቹና ለውጭ እንግዶች ፍጆታ የፕሬስ ነጻነት ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ መምጣቱን ከመናገር ተቆጥቦ አያውቅም ። አዳማጮቹም ዲፕሎማሲያዊ
ወጉን ለመከተል ያህል እንጂ ኢትዬጽያ በፕሬስ ነጻነት 137ኛ / ከ 179/ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ሳያነቡ ቀርተው አይደለም
- የአለማቀፉ ፕሬስ ነጻነት ሪፖርትን ። ምን ይሄ ብቻ በሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ተከታታይ ስኮር ካርድ ከ D በታች ውጤት ያላት
መሆኑንም ያውቃሉ ። ይህ ሪፖርት የሚዘጋጀው በዴሞክራሲ ፣ ፕሬስ ነጻነትና ሰብዓዊ ልማት ውጤቶች ላይ በመንተራስ ነው ። ቀጣዬቹ
አለማቀፍ ሪፖርቶች ደግሞ የከፋ ስዕል ይዘው ለመውጣት የተዘጋጁ ይመስላሉ ። ሰሞኑን ስድስት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች ባልታወቀ
ምክንያት እስር ቤት ተወርውረዋልና ።
ዜጎች
በታሰሩ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት እንዳላቸው ሁሉ የተያዙበትና የተጠረጠሩበት ምክንያት ወዲያው በግልጽ ሊነገራቸው
ይገባል ። ሃሳብን የመግለጽ ፣ የማስተላለፍና የማሳወቅ መብት ተገዢነቱም ለብዙሃኑ ነው ። በመሆኑም ቁጥሩ የበረከተ ብሎገርና ጋዜጠኞች
ሲታሰሩ ምክንያቱ በግልጽ መነገር ይኖርበታል ። አርብን እየጠበቁ ማሰር ግዜ ለመግዛት የተለመደ ፖሊሳዊ አሰራር እየሆነ መጥቷል
። ህዝብንና ህጋዊነትን ማዕከላዊ አድርጌያለሁ የሚል መንግስት ግን ይህም አንደኛው ተጠየቃዊ መርህ መሆኑን በመቀበል መረጃውን ማስተላለፍ
ግድ ይለዋል ።
ያም ሆነ
ይህ የዚህ ሁሉ ጠለፋ መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው ? እንዲህ ለማለት የምገደደው በመንግስት በኩል መረጃው ለህዝብ ይፋ ስላልሆነ
ነው ። የዚህ ክፍተት ተጠያቂ ደግሞ መንግስት ነው ። የማወቅ መብታችንን አፍኗልና ። ስለዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን ብሎ መጠየቅ
ብቻ ሳይሆን ምላሹን መገመትም ስህተት አይሆንም ።
ከፊታችን
ያለው ምርጫ ?
የሰማያዊ
ፓርቲ ትከሻ መስፋት ?
የዘጠኝ
አመቱ ቁስል ማገርሸት ? ታዲያ የዘጠኝ አመቱን ቁስል በዞን ዘጠኝ ብሎገሮች ማከም ይቻላል ወይም ማጣፋት ? ምንስ ያገናኘዋል ? ይህ ይህ ጠንካራ የጸሀፊዎች ቡድን
መርፌ ሲወጉ እንደነበሩ የቀድሞ ፕሬሶች አይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተሰግቶ ይሆን ? ይሄኛው ግምት ሚዛን የሚደፋ ይመስላል ። ምክንያቱም
እስካሁን ለንባብ ባበቋቸው ስራዎች ውስጥ የድርጅቱን ደካማ ጎን በአግባቡ ነቅሰው አውጥተዋልና ።
ወይ የሀገራችን
ፖለቲካ ... የአይኑ ቀለም ያላማረውን
ሁሉ ማባረር ... የጠረጠረውን ወይም ያስደነበረውን በተገኘው ስለት
መውጋት ወይም በሂሳብ ስሌት ማጣፋት ...
መውጋት ወይም በሂሳብ ስሌት ማጣፋት ...
በዘጠኝ
- አንድ ፣ በዘጠኝ - አንድ እንዲሉ ።
ያሳዝናል ።
No comments:
Post a Comment