የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ህጋዊ የሆነበትን ቀን ተንተርሶ እንግሊዝ ሰሞኑን በግብረሰዶማዊያን ሰርግ ፈንጠዚያ
ላይ ነበረች ። በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት ዴቪድ ካሜሮን ጥምረቱን « ታሪካዊ » ሲሉ አወድሰውታል ። በምድረ እንግሊዝ ይህን መሰሉ
ጥምረት በ2004 የተጀመረ ቢሆንም ወደ ህጋዊ ጋብቻነት የተቀየረው አሁን ነው ።
ይህ ጋብቻ እውን የሆነው የካቶሊኩ ሊቀጻጻስ ፍራንሲስ
ታዋቂ አምስት ቃላቶች « ውዳሴ » ገና ባልከሰመበት ወቅት ነው « WHO AM I TO JUDGE » ይላሉ ጆርጅ ማሪዮ በርጎሊዬ
- ለመፍረድ እኔ ማነኝ ? እንደማለት ።
ከዛሬ 24 ዓመታት በፊት ናዚር ጋይድ ሩፋኤል
በበኩላቸው በእንግሊዝ ተገኝተው የግብረሶዶማዊነትን ኀጢያታዊ ተግባርና የወደፊት አደገኛነት ለታዋቂ ሰዎችና ምዕመናን ትምህርት እየሰጡ
ነበር « HOMOSEXUALITY IS AGAINST NATURE » በማለት - ግብረሶዶማዊነት ተፈጥሮን ይቃረናል እንደማለት ። ይህን
አባባል ግን ጋዜጠኞች ታዋቂው ባለአራት ቃላቶች በማለት አላወደሱትም ። ደግነቱ ሊቀጻጻስ ሺኖዳ ዛሬ በህይወት ስለሌሉ በዚህ ዜና
አያዝኑም ።
እነዚህ ሁለት ጻጻሳት በትህትናቸውና አንቱ በሚያሰኝ
ስራዎቻቸው ይመሳሰላሉ ።
ጻጻስ ፍራንሲስ የአርጀንቲና ሊቀ ጻጻስ በነበሩት
ግዜ የተለየ ጥቅማጥቅም አያስፈልገኝም በማለት ተራ አፓርታማ ላይ ክፍሎች ተከራይተው ምግባቸውን ራሳቸው እያበሰሉ ፣ ህዝብን መስለው
በአውቶብስ እየተጋፉ ነበር የሚጔጔዙት ። የካቶሊክ ሊቀጻጻስ ሆነው ሲሾሙም ቤተመንግስት ከመግባት ይልቅ የቫቲካን ሰራተኞች በሚኖሩበት
ህንጻ ላይ መኖርን መርጠዋል ። ለሳቸው ይወጣ የነበረውን የትየለሌ ገንዘብ ለሰብዓዊ ርዳታ እያዋሉ ይገኛሉ ።
ጻጻስ ሽኖዳ የግብጽን በረሃ በመምረጥ የምንኩስና
ህይወትን ለብዙ አመታት አጣጥመዋል ። ከግብጽ ውጭ ገዳማትንና መንፈሳዊ ኮሌጆችን በማሰፋፋት መንፈሳዊ እውቀት እንዲጎለበትና ቁጥሩ
እንዲጨምር ልዩ ሚና ተጫውተዋል ። ኢል ከራዛ የተባለ ሃይማኖታዊ መጽሄት በማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ከሰፊው ዕውቀታቸው በመጨለፍ
101 የሚደርሱ መጽሃፍትን ለንባብ አብቅተዋል ። ስራዎቹም በልዩ ልዩ ቌንቌዎች ተተርጉመዋል ።
እነዚህ ሁለት ጻጻሳት ከክርስትና ባህር የተቀዱ
ቢሆንም ዛሬ አለምን በስፋት እያነጋገረ በሚገኘው ግብረሶዶማዊነት ዙሪያ ያላቸው አመለካከት በፍጹም አይገናኝም ።
ለምን ?
አይታወቅም ።
አንድ መሆን ይጠበቅበት ነበር ?
ቢያንስ በጣም መራራቃቸው እንዴት ? የሚል ጥያቄ
እንዲወለድ ምክንያት ይሆናል ።
የአሌክሳንደሪያው ጻጻስ ሽኖዳ ግብረሶዶማዊነት
ከተፈጥሮና ከመጽሀፍ ቅዱስ ቃል የሚቃረን በመሆኑ ሃጢያት መሆኑንና አባላቱ መንግስተ ሰማያት እንደማይገቡ ያስረዳሉ ። የካቶሊኩ
ጻጻስ ፍራንሲስ የቤተክርስቲያኒቱን መመሪያ በመንተራስ ግብረሶዶማዊነትን በሁለት ከፍለው ነው ሀሳብ የሚሰጡት ። የግብረሶዶማዊነት
ዝንባሌ ያለው እንደሃጢያተኛ አይቆጠርም ። ግብረሶዶማዊ ተግባርን የሚፈጽም ግን ሃጢያተኛ ነው ። < ዝንባሌ > የሚለው
ቃል እንዴት ሊፈጠር ቻለ ? በግርድፉም ደጋፊነትንና አድናቂነትን ይገልጻል ። የድጋፉ መነሻስ ከምንም ተነስቶ ነው ማለት ይቻላል
? ምናልባት ይህ ደጋፊ ነገ ተጨዋች ለመሆን በእጅጉ የቀረበ ይመስላል ። መገመት የማይቻለው አሰላለፉን ነው - ተመላላሽ አጥቂ
ነው ወይስ ቌሚ ተከላካይ ? ወይም እንደ ሚስት ነው የሚተውን እንደ ባል እንደማለት ።
ቅጣቱን በተመለከተም የጻጻሳቱ አመለካከት እንደሰሜንና
ደቡብ ዋልታ ጫፎች የተራራቀ ነው ። ሺኖዳ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን የተወገዘና ክፉ ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ያስረዳሉ
። በኦሪት ዘሌላዊያን ምዕራፍ 20 ፡ 13 « አንድ ወንድ ከሌላው ወንድ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ቢፈጽም ሁለቱም አስከፊ ነገር
ስላደረጉ በሞት ይቀጡ ። ስለመሞታቸውም ኃላፊነታቸው የራሳቸው ይሆናል » የሚለውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።
የአዲስ ኪዳኖቹ
ወደ ሮም ሰዎች 1 ፡ 27
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6 ፡ 9
የይሁዳ መልዕክት 7 የግብረሶዶማዊነትን ቅጣትና
የእግዚአብሄርን መንግስት አለመውረስ የሚያስረዱ ናቸው ።
ፍራንሲስ እነዚህን ጥቅሶች በመተው የተለየ ምላሽ
መስጠትን መርጠዋል ። ታዋቂ የተባለውን who am i to judge ? በርግጥ እነዚህ ተሳቢ ቃላቶች ነገር ለማሳመር ተከርክመው
ቀረቡ እንጂ ሪሞርኬው ከፊት አለ - እንዲህ ነው ያሉት « አንድ ግብረሶዶማዊ ፈጣሪን ከተቀበለና መልካም ስነምግባር ካለው እኔ
ማነኝ እና ነው የምዳኘው ? » አንዳንዶች ይህን አባባል የተጠቀሙት ትህትናን ለማሳየት ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ህገ መጽሀፉን ለመሸሽ
ነው ብለዋቸዋል ።
እዚህ ጋ ፍጥነታችንን አቀዝቅዘን ከሀሳቦቹ ጀርባ ሊሆን ስለሚችለው ጉዳይ የሆነ ነገር እንበል ። ሽኖዳ መጽሀፍ ቅዱስን
ቃል በቃል ጠቅሰው ሞት ይገባል ነው ያሉት ። ኃላፊነቱም የሟቹ ነው ። ህግ ከውሃ የቀጠነ መሆኑ ቢታወቅም እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች
ወዳልተፈለገና የከፋ ጫፍ እንደሚያደርሱም ይታወቃል ። ምክንያቱም ስሜታዊነትን አቅፈዋልና ። ለአብነት ያህል ኡጋንዳ የጸረ ግብረሶዶማዊነት
ህግን ባጸደቀች ማግስት በተነሳ አመጽ አንድ ግብረሶዶማዊ ተቃጥሎ እንዲሞት ተደርጔል ። መቼም የሶዶምና ገሞራ ሰዎችም በዚህ መልኩ
ነው የተፈጁት ብለን የምንከራከር ከሆነ የጻጻስ ፍራንሲስ አምስት ቃላቶች ትክክል ናቸው ማለት ነው ። እኛ ማነንና ነው ህግን የተላለፈ
ሰው በጣም በተጋነነና ለቀሪው ትምህርት ሳይሆን በሽታ ሊፈጥር በሚችል መልኩ በእሳት የምናቃጥለው ? ህግ በቀለኛ መሆኑ ይታወቃል
። የበቀሉን ጉማሬ ከኃላ ኪሱ የሚያወጣው ግን መጀመሪያ ገስጾና አስተምሮ ነው ። ሰው ሲሞት እንኴን አስከሬኑን የማቃጠል ባህል
መቅረት አለበት በሚባልበት ዘመን ህይወት ያለውን ሰው እንደዳመራ በመለኮስ ሰብሰብ ብሎ ወደ ሰሜን ይወድቃል ወይስ ወደ ምዕራብ
እያሉ መወራረድ እንዴት ያስደስታል ? ያሰቅቃል እንጂ ።
በሌላ በኩል ጻጻስ ፍራንሲስ እንደቀድሞው ጻጻስ
ተጽዕኖው በዝቶባቸዋል አሊያም የሳይንሱን እውነታ እየሸራረፉም ቢሆን መቀበል ጀምረዋል ። እንደሚታወቀው ግብረሶዶማዊነት የምርጫ
ጉዳይ ሳይሆን ሆኖ የመፈጠር ነው የሚሉ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ጣጣውን የጄኔቲክና ሆርሞን ውጤት አድርገውታል ። ለዚህም ማሳያ ይሆን
ዘንድ በክሮሞዞምስ ፣ አእምሮና ሆርሞኖች ላይ ጥናቶች አከናውነዋል ። ለአብነት ያህል 400 የሚደርሱ መንታ ልጆች ላይ የተደረገ
ጥናት Xq28 የተባለውን ክሮሞዞም እንደሚጋሩት ያሳያል ። ይህን ክሮሞዞምስ ጥንድ ያልሆኑ ወንድሞች አይጋሩትም ወይም በጥቂቱ ነው
የታየው ። በዚህም መሰረት አንዱ ልጅ ግብረሶዶማዊ ከሆነ ሌላኛው ጥንድ የመሆን እድሉ 50 ከመቶ ይደርሳል ። እነዚህና የመሳሰሉት
ጥናቶች እውነት ይኖራቸው እንዴ የሚያሰኝ ጥያቄ እየፈጠረባቸው ይመስላል ።
ዛሬ አለምን ጉድ እያሰኘ የሚገኘው ግብረሶዶማዊነት
ሳይሆን የግብረሶዶማዊያን የጋብቻ ጥያቄ ነው ። ምክንያቱም ጋብቻ የተባለውን አንጋፋና ህጋዊ ተቌም እየተጋፋ በመሆኑ ። አለም ተቀብሎት
የኖረው የጋብቻ ብይን እድሜያቸው ለአቅመ አዳም / ሄዋን በደረሰና በፍቅር በተግባቡ አንድ ወንድና ሴት መካከል የሚደረገው ማህበራዊ
ጥምረት ነው ። እነዚህ ጥምሮች ውለዱ ክበዱ የሚለውን የሰርግ ላይ ምርቃት ከአመት በኃላ ተግባራዊ ያደርጋሉ ። ፍሬና ፍቅር ማየት
የሰው ልጆች ሁሉ ጸጋ ነውና ።
ዛሬ አንድ ተማሪ « ጋብቻ የሁለት ጺማም ሰዎች
ቁርኝት ነው ፣ በፍቅር ለመደንገጥና ለመሳሳብም አጔጊ ዳሌ ፣ እንቡጥ ከንፈር ፣ የተቀሰሩ ጡቶች ፣ ገዳይ አይን ፣ አመለሸጋነትም
ሆነ የጎን አካልነት ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም ። በግብረስጋ ለመርካት የግድ ወርቃማ ምንተሃፍረቶች አያስፈልጉንም - ማንኛውም ቀዳዳ
እንጂ » የሚል መመረቂያ ጽሁፍ ቢሰራ ማነው ትክክል አይደለም የሚለው ? ጋብቻ በትርጉም ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ በሚመጣው ቤተሰባዊ
ተቌምነቱም እየተኮማተረ ነው ። ህንጻው ውስጥ ከወጉ ፣ ከእምነትና ስርዓቱ ፣ ከባህሉና ከአኗኗር ዘይቤው ጋር የማይመሳሰል ምናልባትም
የሚቃረን ደባል ሰተት ብሎ ገብቷል ። ትግሉ ከቀዝቃዛው ጦርነት በላይ የጦዘውም ለዚህ ነው ።
ውጣልኝ ! - አልወጣም !
በህግ አምላክ ?! - በህግማ ነው የመጣሁት !
እረ የሀገር ያለህ ? የመንግስት ያለህ ? -
ነባሩ ትዳር በስቃይ ተተብትቦ ነጋ ጠባ ሊጮህ ነው ። ቆይቶ የሚያገኘው ፖለቲካዊ ምላሽ « ተቻችላችሁ ኑሩ - ተከባበሩ » የሚል መሆኑ አያጠራጥርም ።
እዚህ ላይ ጻጻስ ፍራንሲስ ጋብቻን በተመለከተ
አስገራሚ ለውጥ ማድረጋቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል ። የአርጀንቲና ጻጻስ በነበሩበት ግዜ « ይህ የፈጣሪን እቅድ የማጥፋት ዘመቻ
ነው » በማለት ነው ተቃውሟቸውን በግልጽ አሰምተዋል ። የካቶሊክ ሊቀ ጻጻስ ሆነው ከኢጣሊያኑ ኮሬ ዴላ ሴራ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት
ቃለ ምልልስ « ጋብቻ በአንድ ወንድና ሴት የተወሰነ ነው ፣ ነገር ግን ቤተክርስቲያናችን የተመሳሳይ ጾታን ጥምረት በተለይም ከህክምና
አገልግሎትና ከንብረት ባለቤትነት አንጻር መደገፍ አለባት » በማለት ልዩ ጉዳዮች በልዩነት የሚመዘኑበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል
።
ሺኖዳ ፍቅር መንፈሳዊና ንጽህ ከመሆኑ አንጻር
በሁለት ተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚደረግ ጥምረትን የሚበይኑት ዝሙት በማለት ነው < ግብረሰዶማዊነት ተፈጥሯዊ እኮ ነው ? >
የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር ። አንድ ሰው በዚያ መልኩ ከተፈጠረ መጸለይ ፣ መፈወስ በህክናም ማስተካከል ይቻላል ባይ ናቸው
። ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያን ሰዎች በዚህ መልክ ይፈጠራሉ ብላ እንደማታምን ይልቁንም ዝሙት መሆኑን በምሳሌ ማስረዳት መርጠዋል
። ቅዱስ አውግስቶ እና ቅዱስ ፓለጊያ ዝሙት ፈጻሚዎች ነበሩ ። ኃላ ቅዱስ እስከመባል የደረሱት በመጥፎ ተግባራቸው ተጸጸተው ራሳቸውን
በማስተካከላቸው ነው ።
የግብረሶዶማዊያን ነገር « ምላጭ ቢያብጥ በምን
ይበጡ ? ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡ ? » አይነት ደረጃ የደረሰ ይመስላል ። ምክንያቱም የተቀጣጠለውን እሳት በማጥፋት ረገድ የእሳት
አደጋ ተከላካይ ባልደረባ በመሆን ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብለው የሚገመቱት ቄሶች ራሳቸው የእሳት ራት በመሆናቸው ።
ልክ እንደ ሺኖዳ ሁሉ የቀድሞው ጻጻስ ቤንዲክት
XVI የግብረሶዶማዊነት ጥልቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ቄሶች ሊሆኑ አይችሉም ብለው ፈርመው ነበር ። ጻጻስ ፍራንሴስ ግን ግብረሶዶማዊያን
ቄሶች ይቅርታ ያገኛሉ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ። ጻጻሱ እንዲህ የተናገሩት ተቸግረው ይመስላል ። ምክንያቱም በሮማን ካቶሊክ
የግብረሶዶማዊያን ቄሶችን ቁጥር በትክክል ማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም በርካታ መሆናቸው ብዙዎችን ያስማማልና ። ሌላው ቀርቶ በአሜሪካ
ከ1970 እስከ 80ዎቹ በነበሩት ግዜያት በሎስ አንጀለስ ታይምስ በተደረገ ጥናት 1854 ቄሶች ራሳቸውን ግልጽ አድርገዋል ። ይህም
በአሜሪካ ብቻ 33 ከመቶ የሚደርሱ ቄሶች ግብረሶዶማዊያን መሆናቸውን ያመለክታል ። ይህን አሃዝ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ተከታዮችን
በምትመራው ካቶሊክ መካከል መመዘን የአደጋውን ስፋት በግልጽ ሊያመላክት ይችላል ።
በርግጥ የሁለቱ ጻጻሳት የተለያየ ምስጢር ምንድነው
?
አንዱ ለዘብተኛ ሌላው አክራሪ ስለሆነ ?
አንዱ የምዕራቡ ዓለም የስልጣኔ ውጤት ሌላው የአፍሪካ
ኃላቀር ባንዲራ አራጋቢ ስለሆነ ?
አንዱ የተጽዕኖ ውጤት ሌላኛው በራሱ የቆመ ስለሆነ
?
ከእነሱ እምነትና አስተሳሰብ በመነሳት የነገዋን
አፍሪካ መገመት ይቻላል ?
አይታወቅም ።
No comments:
Post a Comment