Wednesday, September 2, 2015

ኢትዮጽያዊው < ኢንደሚክ > ጎሳ


 

                    ኢትዮጽያን በብሮሸር ፣ በበራሪ ወረቀት ፣ በቀን መቁጠሪያ ፣ በመጽሄትና ጋዜጣ የሚያስተዋውቁ ብዙዎቹ ጽሁፎቻችን እንዲህ ብለው የሚጀምሩ ናቸው
                   « ኢትዮጽያ የቱባ ባህል ፣ ወግ ፣ ትውፊት እና መልከዓምድር መገኛ ምድር ናት »
ሀገራችን በደን ሀብትዋ አርባ በመቶ ከነበረው ተራራ ቁልቁል ተምዘግዝጋ ሶስት በመቶ ላይ ተሰባብራ የተኛች ብትሆንም ፣ ያሏትን ጥቂት ዝሆኖች ጥርሳቸውን በጥይት አራግፋ በድዳቸው እንኴ እንዳይኖሩ ያልፈቀደች  ብትሆንም ፣ አውራሪስ የተባለውን እንስሳ ከምድረ ገጽ አጥፍታ « አቶ አውራሪስ » በሚባሉ ሰዎች ተጽናኑ የምትል  ብትሆንም በሁለተኛው አንቀጽ ላይ የሚከተለው እየተጻፈላት ይገኛል ።
« ኢትዮጽያ የብርቅዬ አእዋፋት ፣ ዕጽዋትና እንስሳት መናኀሪያ ሀገር ናት »
በተለይም ቁጥራቸው እየተመናመነ የሚገኙት ዋሊያ ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ ፣ የሚኒሊክ ድኩላ ፣ ቀይ ቀበሮ ፣ የስዋይን ቆርኬና የደጋ አጋዘን በሌላው ዓለም የማይገኙ ብቸኛ አንጡራ ሃብቶቻችን ቱሪስቶችን በመሳብና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ይለናል ማስታወቂያው ። 
 እኔ ደግሞ ይህ የዘወትር ጽሁፍ የዘነጋው አንድ አቢይ ነገር አለ በማለት በቀጣዩ አንቀጽ ጣልቃ መግባት ፈልጌያለሁ ። የፅሁፉ እንድርድሮሽም « ልዩ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ እያሳዩ የሚገኙ ማህበረሰቦች < Endemic Race  > ተብለው መጠራት ይኖርባቸዋል የሚል ነው ።

‹‹ Endemic ›› ከሆኑ የሃገራችን ጎሳዎች አንደኛው ደግሞ  በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙት ሙርሲዎች  ናቸው :: እንዴት ቢባል ከንፈሩን ተልትሎ / በአሁኑ ወቅት / ገል የሚያስቀምጥ ፣  ራቁቱን በዱላ የሚከታከት እና  ሙሉ ብሄረሰብ  ሰዓሊ የሆነበት ሀገር በየትኛውም የዓለም ጫፍ አይገኝምና  ፡፡  የሙርሲን ኢንደሚክነት እያነሳሁ መሞገት ልጀምር ።

የብርቅዬነት መገለጫ አንድ - ከንፈር
የሙግቴ ማጠንጠኛ - ያላለቀ ውበት

የሙርሲ ብሄረሰብ ልዩ ከሆነበት አንደኛው ገጽታ የሴቶች ከንፈር ጉዳይ ነው ፡፡ አብዛኛው ሴቶች ከንፈራቸውን ሲተለተሉ የታችኛዎቹን ጥርሶችም ያስወግዳሉ ፡፡ ምክንያቱም ጥርሱ ካለ ገሉን በአግባቡ ለማስቀመጥ ስለማይቻል ፡፡ አንድ ሴት ገል በሚያንጠለጥለው ከንፈር ትወደስ እንጂ ጥርሷን በመንቀሏ የምታገኘው ሞራላዊ ጥቅም የለም ፡፡ ጥርስ ለከንፈር ውበት ሲል ራሱን መስዋእት ያደረገ አካል በመሆኑ ሊታዘንለት በተገባ ነበር ፡፡

በታሪክ ሱያ የተባሉ የብራዚል ወንዶች ፣ ሳራ የተባሉ የቻድ ሴቶች ፣ ማኮንዴ የተባሉ የሞዛምቢክ ሴቶች ከንፈራቸውን ይተለተሉ ነበር ፡፡ ይህ ድርጊት ግን ዛሬ ቆሟል ፡፡ ያልቆመው በኢትዮጽያ ብቻ ነው ፡፡ በርግጥ በሀገራችን ድርጊቱ ከመጥፎ ባህላዊ ድርጊቶች ጎራ የተቀላቀለ ቢሆንም መጥፎነቱ ተጨብጭቦለት ፍጻሜ ማግኘት አልቻለም ፡፡ በቦታው ስገኝ ለምን ? የሚለውን ጥያቄ ለነዋሪዎቹ አንስቼያለሁ ።

ሙርሲዎች እኛ መጥፎ ያልነውን ድርጊት ገልብጠው አይደለም ዘቅዝቀው ለመመልከት እንኴን ፍቃደኞች  አይደሉም ፡፡ በርግጥ ማነው ዛሬ በጣም ከረፈደ ተነስቶ ሺህ ዘመናት ያሳለፈውን ‹ እውነት › - ‹ እውሸት › መሆኑ የተገለጠለት ? የዛሬ ወጣቶች በትምህርትና ባህል ፍትጊያ መሃል የሆነ አዲስ ሀሳብ ፈንጥቆ ሊታያቸው ቢችልም ማህበረሰቡን የሚመራው አዛውንት ክፍል አንድም ለቆየው ባህሉ በሌላ በኩል እያገኘ ካለው ጥቅም አኳያ ከንፈር ትልተላን የተመለከተ አዲስ አንቀጽ ለመጨመር ከልቡ ፍቃደኛ አይሆንም ፡፡ ጠንካራው እውነት ይህ ነው ። በዚያ ላይ ቱሪስቶች ብርቅዬ እንስሳቶቻችንን ከማየት በበለጠ ትኩረት የሚሰጡት የሰው ልጅ ልዩ ባህል ወይም ባህሪ ላይ ነው ። በየቀኑ እንደ አሸን እየፈሉ የሚገኙት አስጎብኚ ድርጅቶች ዓመታዊ የገቢ እቅዳቸው ግቡን የሚመታው በሰሜን ተራራዎችና ሶፉመር  ድንቅ ውበቶች ብቻ እንዳልሆነ ያውቁታል ። አቌም መያዝ ያልቻለው መንግስት ደግሞ መሃል ላይ አለላችሁ ። ከንፈር መተልተል ጎጂ ባህል ነው እያለ በስሱ ያስተምራል ፣ ታይተው የማይጠገቡትን ሙርሲዎች ሳትመለከቱ ወደ ሀገራችሁ እንዳትመለሱ እያለ ደግሞ በወፍራም ድምጽ ፈረንጅ በተገኘበት ሁላ ይሰብካል ። እነዚህ አገም ጠቀም አሰራሮች በሙሉ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ለመቀየር የሚያስችሉ አይሆኑም ፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ የሙርሲ ሴቶች ከንፈርና ገል እንደ አክሱም ሃውልቶችና ላሊበላ ውቅሮች የገዘፈ ስም አግኝተዋል ፡፡ ይህ እስከ 16 ሴ.ሜ ሰፍቶ ገል የሚሸከመው ከንፈር በግርማ ሞገሱ ትንሽ ትልቁን ቀኑን ሙሉ እንዳስደመመ ይቀጥልና አመሻሹ ላይ ሌላ ገጽታ ይላበሳል  ፡፡ ገሉ ከመሃሉ ሲለየው ለባለጌጧ እፎይ ቀለለኝ አይነት ስሜት ሊፈጥር ይችል ይሆናል ለሌላው ተመልካች ግን አሳዛኝ ስሜት ነው የሚያሳድረው ። ቋንጣ የመሰለው ከንፈር ይሄኔ  ምቾት አይሰጥም ፡፡ ምናልባትም ውበቱ መጀመርን እንጂ ማለቅን አያሳይም ።

ከንፈራቸውን ለመተልተል ፣ የሚያጠልቁትን ገል ውበት በተላበሰ መልኩ ለመስራት የማይሰንፉት የሙርሲ ሴቶች ከንፈራቸው ደምቆ ውሎ ደምቆ እንዲያድር የሆነ መላ አለመፍጠራቸው ግን ይገርማል ፡፡ ከሰሩ ላይቀር አገጫቸውን ሰንጠቅ አድርገው የተንዘለዘለውን ስጋ ተጠቅልሎ እንዲደበቅ ቢያደርጉ ምን ነበረበት ? ለካስ ካንጋሮን አያው
ትም …

የብርቅዬነት መገለጫ ሁለት - ዶንጋ
የሙግቴ መዳረሻ - ያልተሰራበት ኢንቨስትመንት

ሙርሲዎች ጨካኝ የሆነ ባህል ተከታይ መሆናቸውን ብዙዎች ይናገራሉ ፡፡ በተለይም በረጃጅም ዱላ የሚያደርጉት ድብድብ ወይም ዶንጋ ለወንድ ልጆች የጀግንነት ክብር መግለጫ ፣ የሚስት ማግኛ ብሎም የመከራ መቁጠሪያ ምዕራፍ ነው ፡፡ ለዚህ ባህላዊ ውድድር ጎረምሶች ተደራጅተው ይቀለባሉ ፡፡ ሙገሳና ጭፈራ ያጅባቸዋል ፡፡  የሙርሲ ወንድ ቢያንስ ከአንድ ወንድ ጋር ይህን ግጥሚያ ማከናወን አለበት ፡፡ አሸናፊው በሴቶች ተከቦ ወደፊት የሚፈልጋትን ሴት እንዲመርጥ ዕድል ያገኛል ፡፡ በዚያው ልክ ተቀልበውም እስከወዲያኛው ሊያሸልቡ ይችላሉ ፡፡የሀዘን ጥላም ዘወትር  ጎናቸው ነው ፡፡  

የአማራው ብሄረሰብ ‹ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ ! › እንደሚለው ሁሉ ሙርሲዎችም በዶንጋ ለሚሞቱ ወጣቶች ጥብቅና አይቆሙም ፡፡ መቼም ነጭ የኖራ ስዕል ብቻ በለበሰ ባዶ ገላ በቀላሉ በማይሰበር ዱላ ከመከትከት አንደኛውን የስፔን ቀውስ ሊግ ውስጥ ገብቶ በበሬ መወጋት ሳይሻል አይቀርም ፡፡

ሽማግሌዎች ዶንጋ ወጣቱ ህብረተሰብ መከራን እንዲችልና ጠላትም እንዳይፈራ ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዎጽኦ ይፈጥራል ባይ ናቸው ፡፡ ይህ ውድድር ህይወት እስከመቅጠፍ የሚያደርስ ከሆነ ላይቀር ሙርሲንም ሆነ ሀገሪቷን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የላቀ የኢንቨስትመንት ሀሳብ ማመንጨትይገባል ፡፡ ከዚህ አንጻር እኔ አንድ ሃሰብ አለኝ ፡፡ መጀመሪያ የዓለማችንን ምርጥ - ምርጥ ውግሪያዎች እየለቀሙ ማጥናት ፡፡ ዶንጋ ባህሉን ጠብቆ እንዴት ዓለማቀፍ ውድድር መሆን ይችላል የሚለውን ደግሞ ለጥቆ ማሰብ - መቀመር ፡፡

ለምሳሌ ያህል ብዙ ተመልካች ያለው የነጻ ትግል ስፖርት የሚከናወነው በፕሮሞተሮች ነው ፡፡ እነዚህ ፕሮሞተሮች ድርጊቱን በቴሌቪዥን ፣ በማስታወቂያ ፣ መጽሄትና ኢንተርኔት ያስተዋውቃሉ ፡፡ ታዋቂ ቡጢኞች በመዝናኛው ቻናል ብቅ እያሉ ቡራ ከረዩ እንዲሉ ያደርጋሉ ፡፡ እንግዲህ ይህ አሰራር በዚህ መልኩ ነው ቀስ በቀስ የአሜሪካ ታዋቂ ባህል እንዲሆን የተደረገው ፡፡

የታይላንድ ኪክ ቦክስንም ብንመለከት ከነጠላ መነሻነት ነው ዛሬ አድጎ ትልቅ ካፒታል መፍጠሪያ የሆነው ፡፡ የሀገሪቱ ወታደሮች ጠመንጃ በሌለበት ወቅት እንደ አጋር ተጠቅመውበታል ፡፡ ንጉሶች ለመዝናናት የጦር እስረኞች ደግሞ ለነጻነታቸው በዚህ ፍልሚያ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ቆይተዋል ፡፡ ዛሬ ስፖርቱ ኤሽያን አልፎ አውሮፓ ደርሷል ፡፡

ካራቴንም ብንመለከት ከተፈጠረ ከ 1 ሺህ ዓመት በላይ አስቆጥሯል ፡፡ ሲጀመር በገዳም ተዘውትሮ የሚሰራ ጥበብ ቢሆንም ኃላ ላይ የቻይና ገበሬዎች ከታጠቁ ሽፍቶች ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ጋሻ አድርገውታል ፡፡ ቀስ በቀስ በመላው ዓለም በመዳረስ ለፊልምና ለተለያዩ ውድድሮች የማይነጥፍ ማዕድን ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ፡፡

በመሆኑም ዶንጋን እንደ ነጻ ትግል ፣ ኪክ ቦክስና ካራቴ የላቀ ደረጃ ለማድረስ የማይቻልበት ሁኔታ ስለማይኖር ጉዳዩን በጥሞና ማሰብ ይገባል ፡፡

የብርቅዬነት መገለጫ ሶስት - የገላ ላይ ስዕል
የሙግቴ መዳረሻ - ተንቀሳቃሽ ሸራ
በአንድ ከተማ ውስጥ 10 ሺህ ህዝብ ይኖራል እንበል ፡፡ ይህ ሁሉ ህዝብ ነጋዴ ወይም መሃንዲስ ወይም አንባቢ ሊሆን አይችልም ፡፡ ገሚሱ አተረፍኩ የማይል ነጋዴ ፣ ገሚሱ ከባታ እስከ ባለእግዚአብሄር ሳያዛንፍ ቀን መቁጠር የሚችል የመንግስት ሰራተኛ ፣ ሌላው በሀገርና ህዝብ ስም የነገር ሰበዝ ሲመዝ የሚመሽለት ፖለቲከኛ  ወዘተ ነው የሚሆነው ። የሙርሲ አስር ሺህ ህዝብ በሙሉ ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሰዓሊ ነው ፡፡ እንዴት ከተባለ ቢያንስ በየሳምንቱ የራሱንና የሌሎች ገላ ላይ በነጭ ኖራ ቅርጻ ቅርጽ ያቀልማልና ፡፡ አንዱ የአንዱን ጀርባና ፊት በአንክሮ እየተመለከተ ቅቡን ያደንቃል ወይም እንዲህ መሆን ነበረበት እያለ ልማታዊ  አሰተያየቱን ይሰነዝራል ። አይነቱና ስልቱ ይለያይ እንጂ ሙርሲ የሰዓሊዎች ሀገር ነው ፡፡

የሀገራችን ሰዓሊዎች ስራዎቻቸውን ለተደራሲው የሚያቀርቡት ለተወሰነ ግዜ በጋለሪ ወይም በሚከራዩት ሆቴል ውስጥ ነው ፡፡ ለማየት እድል የሚያጋጥመውም በዛው መጠን በጣም ውስን ነው ፡፡ የሙርሲዎች የስዕል ሸራ ግን ሰውነታቸው በመሆኑ ጋለሪ ውስጥ የታጠረ አይደለም ፡፡ በየሜዳው ፣ በየተራራውና በየመንገዱ ይዘውት ይንቀሳቀሳሉ ፡፡ አላፊ አግዳሚውም ይመለከታቸዋል ፡፡ ሲፈልግ አብሮአቸው ፎቶ ይነሳል ፡፡ የሙርሲ ሰዓሊ ከከተማው የተማረ ሰዓሊ የሚቀርበት ጉዳይ ‹ ፈርምልኝ ? › የሚል ጥያቄ የሚያቀርብለት አለመኖሩ ነው ፡፡ ‹ ተንቀሳቃሽ ሸራ › መምሰሉን ግን ከተሜዎች በተሞክሮነት ሊያጤኗት የምትገባ ጉዳይ ናት ፡፡

ለሙርሲዎች የቀለም አባቱ ነጭ ነው ፡፡ አንዳንዶች ነጭ ቀለም ከብትን ከማርባት ጋር ይያያዛል ይላሉ ፡፡ የስዕሎቹ መሰረት ክብ ፣ መስመር ፣ ነጥብ እና ግማሽ ክብ ናቸው ፡፡ የእነዚህ መገጣጠም ፣ መለያየት ፣ መደራረብ በአጠቃላይ መወሳሰብ ነው አይን በቀላሉ የማይፈታውን አብስትራክት የሚፈጥረው ። ዞሮ ዞሮ ቅርጽና ቀለሞቹ ትርጉም ባዘለ መልኩ እንደሚቀመጡ ይገመታል ፡፡ ምክንያቱም ስዕሎቹ ውስጥ የሂሳብ ፣ አስትሮኖሚ ፣ የእንስሳት፣ የተፈጥሮና የመሳሰሉ ብልጭታዎችን መመልከት ስለሚቻል ፡፡

በርግጥ ስዕሎቹን ለማወቅ ሰዓሊዎቹን ቀድሞ መረዳት ይጠቅማል ፡፡ አስተሳሰባቸው ፣ ፍልስፍናቸው ፣ የኑሮ ዘይቤያቸውና የእምነቶቻቸው ጸጋዎችን እየገለጹ ማንበብ የማንነታቸው መዳረሻ ላይ ያደርሳል ፡፡ ስዕል የውበታቸው መገለጫ ብቻ ሳይሆን የህልውናቸው ህገ ደንብ ወይም ህገ መንግስት ሆኖ ሊገኝ ይችላል ፡፡ ይህ ካልሆነ ታዲያ እንዴት የአንድ ሀገር ሙሉ ህዝብ ሰዓሊ ሆኖ ይገኛል ? ሁሉም ለራሱ ህገ መንግስት ታማኝና ተገዢ ቢሆን እንጂ ፡፡

በመሆኑም ነው የሚመለከታቸው ክፍሎች ሙርሲን ብርቅዬ የሰው ዘር ወይም ኢንደሚክ ብለው መመዝገብ የሚኖርባቸው ።