Sunday, April 7, 2013

‎የወላጅ አልባ አንበሶች ያልተነገረ ታሪክ‎


ስለ ወላጅ አልባ ህጻናት እንጂ ስለ ወላጅ አልባ እንስሳት ብዙዎች ብዙ እንዳልሰሙ ግልጽ ነው ፡፡ ብይኑ እነዚህን እንስሳት ወላጅ የሌላቸው እንስሳት ሆነው ራሳቸውን ማስተዳደር የማይችሉ ይላቸዋል ፡፡ ለሀገራችን ወላጅ አልባ ህጻናት መፈረጃ ትልቁ ምክንያት ድህነትና ኤችአይቪውን ጥቂት ከጎናቸው በማራቅ በምትኩ በሽታን ይወስዳሉ ፡፡ በመኪናና በተፈጥሮ አደጋ በተለይም ደግሞ በአዳኞች ርጉም ጥይት መሞት አብይ መንስኤያቸው ሆኗል ፡፡

ትልቅ ሆነው ፍርሃት ከሚያነግሱ እንስሳት አንበሳን በዋናነት መጥቀስ እንችላለን ፡፡ ይህ የስልጣን ፣ የኃይል ፣ የድፍረትና የዝና ምልክት የሆነው እንስሳም ክፉ ቀን ከመጣበት ወላጅ አልባ መጠለያ ውስጥ ፊቱን ጥሎ ሊታይ ይችላል ፡፡ መቼም እነ ጎሽ ፣ የሜዳ አህያ ፣ ሚዳቆ ፣ አጋዘን የመሳሰሉት በአጋጣሚ በሽቦ አጥር የተከለለ መጠለያ ውስጥ ቢያዩት መቶ ፐርሰንት ተስማምቶም ሆነ ተገዶ እዚህ መገኘቱን አያምኑም ፡፡

‹ ወይ ጋሽ አንበሶ ? እንዲህ ዓይነት ማዘናጊያ ጀመረ ደግሞ ! › ልትል ትችላለች ሚዳቆ
‹ ቆይ ግን ምን ለማለት ነው ? በመላመድ ከሌሎች ጋ በሰላም መኖርም እችላለሁ እያለን ነው ? › አጋዘን እየበሸቀ መናገሩ ይጠበቃል ፡፡
‹ ሌባ በለው አጭበርባሪ ! › ከጎሽ ኃይለ ቃል አይጠፋም ፡፡

ሌሎቹም ቢሆኑ በጣም እየፈሩና እይተጠነቀቁም ቢሆን የበዛ ስልቂያ እንደሚያሰሙ አያጠራጥርም ፡፡ ምክንያቱም የደኑ ንጉስ ከፈለገ አጥሩን በጣጥሶ አሊያም ብዙም ሳይንደረደር ከለላውን እንደሚዘላት ይገባቸዋልና ፡፡ እንኳን እነሱ ‹ ከኔ በላይ ላሳር › የሚለው የሰው ልጅ ከእሱ በላይ መኖሩን የሚያስመሰክር ዘፈን ዘወትር እንደሚከተለው እንደሚያሰማ የወሬ ወሬ ሰምተዋል ፡፡

          ‹‹ አንበሳው አንበሳው አንበሳው ልጅሽ
                              ይኅው መጣልሽ !!! ››

ይህን የሚዘምረው በጣባብ የጎል ልዩነት ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ ብሄራዊ ቡድን ብቻ አይደለም ፡፡ ይህን የሚዘምረው ወገቡ በዝናር ጥይትና በእጅ ቦንብ ፤ እጁ አውቶማቲክ ጠመንጃና ጸረ ታንክ የተሸከመ ስልጡን ወታደር ጭምር እንጂ ፡፡ ዓለምን የሚያደባይ መሳሪያ የጨበጠ ሰው እንኳ ከመሳሪያው ይልቅ ለአንበሳ ትልቅ ክብር እንደሚሰጥ ይረዳሉ ፡፡
ታዲያ የነጎሽና አጋዘን መላምት እንዴት ትክክል ላይሆን ይችላል ? እረ ለቁጥር የሚታክቱ ማሳያዋችና ማስረጃዋችንም አንድ ሁለት እያሉ መዘርዘር አይከብድም ፡፡ ምን ዘፈን ፣ ሙገሳና ቀረርቶ ብቻ ?

ማነው የአንበሳው ክፍለጦር እያለ ስያሜ የሚሰጠው ?
አንበሳ ግቢ ?
አንበሳ አውቶብስ ?
አንበሳ ጫማ ?
አንበሳ ባንክ ?
አንበሳ ኢንሹራንስ ?
ጥቁር አንበሳ ?
አቶ አንበሴ ?

የአውጉስታ ሸሚዝ ፋብሪካ ምልክት የሆነው የሜዳ አህያም ሆነ የፈጣንና ዘመናዊ መኪናዋች ምስል የሆነው አቦሸማኔ አንበሳ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጽያ የብዙ ነገሮች ምልክት መሆኑን የሚያውቁት ገና ጥርስ ከማውጣታቸው በፊት ነው ፡፡
አንበሳ በቀድሞዎቹ የኢትዮጽያ ባንዲራ ላይ
በአሁኑ ፍራንክ ላይ
በቀድሞ ጽሁፎች ላይ
በኢትዮጽያ ንግድ መርከብ
በቀድሞው አየር መንገድ
በኢትዮጽያ መንገዶች ባለስልጣን
በቴሌኮሙኒኬሽን

ባልጠቀስናቸው መ/ቤቶች እንደ ሎጎ አገልግሏል ፤ ዛሬም በገሃድ እያገለገለ ይገኛል ፡፡ በሚንሊክ ዘመነ መንግስት መስቀል በእግሩ የያዘና ዘውድ የደፋ አንበሳ ባንዲራ ላይ ይታይ ነበር ፡፡ ይህ ምልክት በንጉስ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስትም ሰርቷል ፡፡ የይሁዳ አንበሳ ይሉታል ፡፡ ደርግ ስልጣን ሲይዝ አናቱ ላይ የደፋውን ዘውድ በሞርታር ጥይት አሽቀንጥሮ በዚያው ይቀጥላል ቢባልም አንበሳው የያዘው መስቀልና እሱ የሚከተለው ርዕዮት ሊዛመድለት አልቻለም ፡፡ በአጠቃላይ ‹ አንበሳ አያስፈልገኝም › በማለት ገፈተረው ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን አንበሳው ክፍለጦርን አቋቁሞ አንበሳውን ደጋግሞ ማሞገስ ተያያዘ ፡፡

አንበሳ ከዚህም በላይ ሊወራለት እንደሚችል ይታወቃል ፡፡ ከዚህ አንጻር አንበሳ በወላጅ አልባ እንስሳት ስም መጠለያ ገባ የሚለው ዜና የማይመስል ሊመስል ቢችል አያስገርምም ፡፡ ወይም የማይታወቅ ፡፡

ከአዲስ አበባ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ማለትም ሆለታ አካባቢ የሚገኘው የእንስሳት መጠለያ ግን የስድስት አንበሶች ልዩ ታሪክ ይዟል ፡፡ ቦርን ፍሪ በሰዎች ተይዘው የሚሰቃዩ እንስሳትን ተግባር በማስቀደም ከችግር የሚላቀቁበትንና እንክብካቤ የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች አለማቀፍ ድርጅት ነው ፡፡ የዚህ ድርጅት የኢትዮጽያ ተጠሪ ሆለታ አካባቢ የሚገኘውን መጠለያ ‹‹ የእንስሳት ኮቴ ›› የሚል ስያሜ በመስጠት በሀገራችን የመጀመሪያውን የዱር እንስሳት ጥበቃ ፣ ልማትና ትምህርት ማዕከል በመሆን እየሰራ ይገኛል ፡፡

ግቢው 77 ሄክታር መሬት የሚያካልል ሲሆን በደን የተሸፈነ ነው ፡፡ በቀጣዮቹ አንቀጾች ከምንገልጻቸው ጥንድ - ጥንድ አንበሶች በተጨማሪ አቦሸማኔ ፣ ጉጉት ፣ ጦጣ ፣ ኤሊ ፣ ተራውና በሀገራችን ብቻ የሚገኘው ዝንጀሮዋችም ይገኙበታል ፡፡

ዶሎና ሶፍያ

ዶሎና ሶፍያ

ዶሎ የተባለው አንበሳ አንድ ሜትር ርዝመት ባለው ሰንሰለት በደቡብ ኢትዮጽያ በሶማሌ ድንበር አካባቢ በአንድ ሰው እጅ ነበር ፡፡ ይህ ሰው ለአራት ዓመታት ያህል በፍልጥ እንጨት በተሰራ ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲኖር አስገድዶታል ፡፡ የአካባቢው ሰዎች እንዳስረዱት አንበሳው ብቸኛ በመሆኑና አያያዙም ጥሩ ስላልነበር ዘወትር ጠዋት የሚያሰማው የሰቆቃ ጩኀት በከተማው ሙሉ  ይሰማ ነበር፡፡

ሰቆቃወ ወ ዶሎ ከአዛማጅ ትርጉም አንጻር እንደሚከተለው የሚገለጽ መስሎኛል . . .

‹ እረ የአንበሳ ያለህ ?! እረ የእንስሳት ያለህ ?! ዛሬስ ጠረናችሁ ናፈቀኝ !! ›
‹ አይ እናቴ ! ነጻ በሆነው ጫካ ተወልደሃል የምትይው መዝሙር እንዴት ተቀይሮ ከባርነት ጫማ ስር ተገኘሁ ?! ›
‹ እረ የነጻነት ያለህ ?! እረ የፍትህ ያለህ ?! በምን ጥፋቴ ነው ሰንሰለት የሚበላኝ ?! በምን ተፈጥሮ ነው በሰው ልጅ የምዳኝ ?! ›
ይህ ሁኔታ ብዙዎችን ስላሳሰበ ጉዳዩን ለሚመለከተው ክፍል አሳወቁ ፡፡

ዶሎ በዱር እንስሳትና በቦርን ፍሪ ትብብር መጀመሪያ የተወሰደው ወደ አዋሽ ብሄራዊ ፓርክ ነበር ፡፡ እዚያ የተሻለ እንክብካቤ አግኝቷል ፡፡ አንበሳ ያልነበረው የእንስሳት ኮቴ ዶሎን የመጀመሪያ እንግዳ አድርጎ ለመቀበል ብዙ ጥረት አድርጓል ፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ግቢ ለመስራት ፣ የተሻለ ምግብ በቀጣይነት ለማቅረብና  ህክምናውን ለመከታተል የሚያስችሉ ዝግጅቶች ከተከናወኑ በኃላ ጉዞ ወደ ሆለታ ሆነ ፡፡ ዶሎን ለማጓጓዝ ሰባት ሰዓታትን ማሳለፍም ግድ ብሏል ፡፡

ዶሎ አሳድገዋለሁ ባለው ሰው እጅ እያለ ምን እንደሆነ ባይታወቅም አይኖቹ ተጎድተዋል ፡፡ ሩቅ የማየት ችግር እንዳለበትም ተረጋግጧል ፡፡ ሀኪሞች በልጅነቱ በምግብ እጥረት በመጎዳቱ ለአይን በሽታ ሳይጋለጥ አይቀርም የሚል ሀሳብ አላቸው ፡፡ በሰንሰለቱ ምክንያትም ግርማ ሞገስ ሊፈጥርለት የሚገባው የጋማው ጸጉር ሊረግፍ ችሏል ፡፡

ዶሎ በሰፊው ግቢ፣ በምግቡና በተፈጠረለት አንጻራዊ ነጻነት ቢረካም ‹  አንድ ውሃ አጣጪ ባገኝ ምን አለበት ? › እያለ እንደሚያስብ ይገመታል ፡፡ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ኡደት በተባለ ቦታ የሚገኙ ልጆች ሴት አንበሳ ይዘው በአነስተኛ እንጨት ውስጥ መቀመጧ ሪፓርት ይደረጋል ፡፡ አንበሳዋ ስትገኝ እድሜዋ ገና ሰባት ወር ብቻ ነበር ፡፡ እናትየው ልጆቿ ወንዶች ከሆኑ ትልቁ አንበሳ በመቅናትና የነገ ባላንጣዬ ነው በማለት እንደሚገድላቸው ስለምታውቅ ከአጠገቧ እንዲርቁ አታደርግም ፡፡ አንበሶች ልጃቸውን ለመንከባከብ ግድ የማይኖራቸው የምግብ ችግር ባለበት ግዜ ነው ፡፡ ምናልባትም በኃላ ላይ ‹‹ ሶፍያ ›› የሚል ስም የተሰጣት አንበሳ በህጻናቱ እጅ የወደቀችው ይህን በመሰለ ችግር ሊሆን ይችላል ፡፡

ዞሮ ዞሮ ዶሎ ከሶፍያ ጋር መጣመር መቻሉን እንደ ሁለተኛ ዕድልም ድልም ነው የሚመለከተው ፡፡ የመጀመሪያው ሰንሰለቱን የማስቆረጡ ተግባር ነው ፡፡ ሰንሰለት በውሻ እንጂ በአንበሳ አንገት ላይ ቦታው አይደለምና ፡፡ ሁለተኛው ዕድል / ድል በረዶ የሰራበትን ብቸኝነት ብቻ ሳይሆን እንደ አለት የጠጠረውን የፍቅር ጥያቄ ቀስ በቀስ እያቀለጠች ምላሽ ልትሰጥ የምትችል ተቃራኒ ጾታ የማግኘቱ ሚስጢር ነው ፡፡ በርግጥ ጾታዊ ግንኙነቱ ‹ ብዙ ተባዙ ! › እስከማለት የሚያደርስ አይደለም ፡፡ ምክንያቱም የግቢው ህግ የተጎዱ እንስሳትን ለመንከባከብ እንጂ ለማራባት የሚፈቅድ አይደለምና ፡፡ ለምን ከተባለ የዱር እንስሳትን በተወሰነ አጥር ውስጥ ከልሎ ማራባት ከተፈጥሯዊ የኑሮ ዘይቤያቸው አንጻር ስለማይቻል ፡፡ አደኑ ፣ መሯሯጡ ፣ ምግብ ፍለጋው ፣ መደበቂያው ፣ መራቢያው እና ሌላውንም ጉዳይ የሽቦው ቤታቸው አይመልስምና ፡፡ በዚያ ላይ የተራቡትን ሁሉ ለማሳደግ የኢኮኖሚ አቅም አይፈቅድም ፡፡ ይህን ሳይንሳዊ የተባለ የሰው ልጅ ምክንያት እነ አንበሶ አይቀበሉትም ፡፡ አንዳንዶች ስለ ሙሉ ነጻነት ነው የሚያስቡት ፤ ሰዎች ደግሞ እነዚህ አንበሶች ወደ ጫካው ቢለቀቁ የመገለልና የመጠቃት ዕጣ ስለሚያጋጥማቸው ጉዳቱ ይብስባቸዋል ነው የሚሉት ፡፡ አንበሶቹ ግን የፈለገ ቢሆን ማን እንደ ቤት … ማን እንደ ዘር ባይ ናቸው ፡፡ አንዳንዶቹ ተቃውሟቸውን በጩኃት ይገልጻሉ ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የማንዴላን መጽሀፍ ያነበቡ ይመስል ‹‹ LONG ROAR TO FREEDOM ›› የሚል ድርሰት ለመጻፍ በዝምታ ያደፈጡ ይመስላል ፡፡

ሜጀርና ጄኔራል


ሜጀርና ጄኔራል

በወታደራዊ አጠራር ሜጀር ጄኔራል ትልቅ ስልጣን ነው ፡፡ በሀረር የሚገኝ አንድ የጦር ካምፕ ለ13 አመታት ሲያሳድጋቸው ለቆየው ሁለት አንበሶች ወታደራዊ መጠሪያ ለመስጠት ባያመነታም ትልቁን ወታደራዊ ማዕረግ ለሁለት መሰንጠቁ ግን ግራ አጋቢ መስሏል ፡፡ አንዱን ሜጀር ሌላውን ጄኔራል በማለት ፡፡

እነዚህን ጀርባ ጥቁር አንበሶች የተመለከተ በግርማ ሞገሳቸው ይማረካል ፡፡ ከነዶሎና ሶፍያ ግቢ በተወሰነ ርቀት ላይ በሌላ የሽቦ አፓርታማ ውስጥ ነው የሚኖሩት ፡፡ በርግጥም እንደ ወንድማማችነታቸው ተሳስበው በሰላም የሚኖሩ ይመስላሉ ፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላው እየተንጎማለሉ የሚያሰሙት ልዩና አሳዛኝ ድምጽ አላቸው ፡፡ ባለሙያዎቹ የተለመደና ተፈጥሯዊ ጉዳይ ነው ቢሉም እኔ ግን ምናልባትም ስለ ሶፍያ የሚያሰሙት የፍቅር መወድስ ሊሆን ይችላል ባይ ነኝ ፡፡ የአንበሳ የፍቅር ዘለቄታነት እስከመጨረሻው ቢሆንም ሴት እጅግ ብርቅ በሆነበት በዚህ ጫካ መንግስት እንደሚለው ወጪን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ነገር ተጋርቶ መኖር እንደ ስርዓት አልበኝነት አያስቆጥርም ፡፡ እናም ዶሎ ቢከፋው እንኳ … ሜጀርና ጄኔራል እንደሚከተለው  እያሉ መስሎኛል …

                  ኦ ! ሶፍያ . . .
                  መች ይሆን የፍቅርሽ ገበያ
                  የሚውለው ከጠረንሽ አልፎ
                  ልፍያና ጉንተላን አሰልፎ
                  ከኛም ግቢ … ከኛ መንደር
                  የሚወደስ  … የሚከበር
                  ኦ ! ሶፍያ . . .
                  ከለለን አጥሩ
                  አነቀን ድንበሩ
                  እንዲህ ነበር እንዴ ወጉ ?!
                  የባህል ልምዳችን ማእረጉ
                  ታዲያ መች ይጸድቃል ቀኑ ?
                  ‹ ፓሪ › መጨፈሪያችን ‹ ዩኒየኑ ›
                   ኦ ! ሶፍያ . . .                           

የዛሬን አያድርገው እንጂ ወንድማማቾቹ የተፈጠሩት ሶስት ሆነው ነበር ፡፡ በአንድ ክፉ ቀን ሶስት የአንበሳ ግልገሎች በባሌ አካባቢ በወታደሮች ተገኙ ፡፡ ወይም በወታደራዊ ቋንቋ ተማረኩ ፡፡ የግልገሎቹ ወላጆች የት ጥለዋቸው እንደሄዱ ፣ ወይም ምን እንደሆኑ አይታወቅም ፡፡ አንደኛዋ ግልገል ሴት ነበረች ፡፡ ይሁን እንጂ ማራኪዎቹ ወደ ካምፓቸው ባደረጉት ጉዞ ሴቷ በፋቲክ ለባሾች እጅ ከመውደቅ በሚል ነው መሰለኝ ከመኪና በመዝለሏ ወዲያው ሞተች ፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች ከመሞት መሰንበትን መርጠው ካምፕ ውስጥ በአነስተኛ መጠለያ ለመቀመጥ በቁ ፡፡

ግልገሎቹ እያደጉ ሲመጡ ማራኪዋቻቸው የየዕለት ተግባራቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ፡፡ በመሆኑም የዱር እንስሳት ባለስልጣን እንዲታደጋቸው ጥሪ አቀረቡ ፡፡  ቦርን ፍሪ በበኩሉ የአንበሶቹን መኖሪያ በመገንባት የሶስት ወራት ግዜ ወሰደ ፡፡ ትላልቆችን አንበሶች በትልቅ የጭነት መኪና የእንስሳት ኮቴ ግቢ ለማድረስ 16 ሰዓታት መንዳት አስፈልጓል ፡፡ ዛሬ የሜጀርና ጄኔራልነት ተክለ ሰውነት ብቻ ሳይሆን ስለ ፍቅር ፣ ወንድማማችነትና ስለ ህይወት የሚያቀነቅኑትን ፉከራዎችንና አርምሞዎችን መስማት የሆነ ስሜት ይፈጥራል ፡፡

አንድሪያና ጃኑ


አንድሪያና ጃኑ

ስማቸው እንደሚጠቁመው እነዚህ ሁለት አንበሶች ዜግነታቸው ከጣሊያን ነው ፡፡ አስተዳደጋቸው ደግሞ ኢትዮጽያ ፡፡ አንበሶቹ በሆነ ወቅት አነጋጋሪ ጉዳይ መፍጠር ችለው ነበር ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው ፡፡

እአአ በ2006 ሁለቱ ቤተሰብ አልባ ግልገል አንበሶች ጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ተገኙ ፡፡ የመጡት የአንድ ልዑክ ቡድን ምክትል ኃላፊ በሆኑ ሰውና ሚስታቸው አማካኝነት ነበር ፡፡

ሁለቱ ወንድማማች አንበሶች እያደጉ ሲመጡ ጣሊያኖቹ አንበሶቹ ማግኘት ስለሚገባቸው ትክክለኛ ቤትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ቦርን ፍሪን ማነጋገር ጀመሩ ፡፡ አንደኛው ሀሳብ አንበሶቹ ወደተወለዱበት ጣሊያን መመለስ ይኖርባቸዋል የሚል ነበር ፡፡ጣሊያን መቼም የራሷን ንብረት አይደለም የወረረችውንም ሀገር ሃውልት ሳይቀር ተሸክማ ሄዳለች ፡፡ በነገራችን ላይ ወራሪዎች የከበሩ ማዕድናትንና ውድ ቅርሶችን በመዝረፍ አልሆን ካላቸውም አውድመው በመሄድ ይታወቃሉ ፡፡ ጣሊያን ግን ያን ትልቅ ሃውልት ስንት ባህር አቋርጣ ተሸክማ መሄድዋ ይገርመኛል ፡፡ እንደውም አንዳንዴ እኛ በተረት የምናውቀው አህያ ተሸክሞ የሚሄደውን ማሞ ቂሎ ሁሉ የሆነች ይመስለኛል ፡፡ እያደር ግን ድንጋይና ኃውልት ላይ ሃይለኛ ፍቅር እንዳላቸው ተገንዝቤያለሁ ፡፡

መቼም ፍትሃዊ ህዝብና መንግስት ሀገር ላወገዘው ወንጀለኛ / ግራዚያኒ / የጀግና ሃውልት ያቆማል ተብሎ አይታሰብም - ልክ ብልጥ መንግስት የሰማይ ስባሪ የሚያህል ሃውልት ተሸክሞ እንደማይሄደው ሁሉ ፡፡ ጣሊያን ግን ከነዚህ እውነት ጀርባ በኩራት ቆማለች ፡፡ እናም አንበሶቻችን ይመለሱ ብለው መጠየቃቸው የኃላ ታሪካቸውን ለሚያውቅ አያስገርምም ፡፡

የኢትዮጽያ መንግስት ግን ከብዙ ሁኔታዎች አንጻር ይህን ሀሳብ ለመቀበል ተቸገረ ፡፡ ይሄኔ ቦርን ፍሪ ከፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገር ጀመረ ፡፡ ይህ ውይይትም ትውልደ ጣሊያን አንበሶቹ ለግዜው በፕሬዝዳንቱ ቤ/መንግስት ይቀመጡ የሚል ውሳኔ ሀሳብ እንዲመነጭ አስቻለ ፡፡

ቤተ መንግስቱ ግን የተሻለና የመጨረሻ አማራጭ ባለመሆኑ ዘለቄታዊ ማረፊያ ወደሆነው የእንስሳት ኮቴ በህዳር 2011 እንዲጓዙ ተደረገ ፡፡

አንድርያና ጃኑ እንደ ሜጀርና ጄኔራል የመቅበጥበጥም ሆነ እረ ጎራው የማለት ባህሪ አይታይባቸውም ፡፡ ምናልባት እንደ ጌቶቻቸው አድፋጭነት ተጋብቶባቸው ይሆናል ፡፡ ምናልባት ጸብ አጫሪነት ፋይዳ ቢስ መሆኑን በመረዳት በነጭ ባንዲራ ስር ለመኖር ቆርጠው ይሆናል ፡፡ ምናልባትም መወለድ ቋንቋ ነው እንዲሉ ላደጉበት ሀገር ሰላምና ፍቅር በመመኘት ቋሚ ‹ አርምሞ › ውስጥ ገብተው ይሆናል ፡፡ ምናልባትም በቅርቡ  ይፋ የሆነውን ሰበር ዜና አስቀድመው ስለሚያውቁት በራስ የመተማመን ስሜታቸው ተሰብሮ ይሆናል ፡፡

የቅርቡ ዜና  የኢትዮጽያ አንበሶች ዝርያ ከመላው አፍሪካ አንበሶች ይለያል የሚል ነው ፡፡ ከ 20 አንበሶች ውስጥ የዲ ኤን ኤ ምርመራ የተደረገላቸው 15ቱ ልዩነት ማሳየታቸው ታውቋል ፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ አንበሳ ‹ አንበሳ › ከሚለው አስፈሪና ሞገሳም ዝናው በተጨማሪ ‹‹ በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኝ ! ›› የሚለው ማዕረግ በሰዎች ክብር ሊጨመርለት ነው ማለት ነው ፡፡ ለነገሩ ነገሩ ቀድሞ የተገለጠላቸው የሚመስሉት አንዳንድ የሀገራችን መሪዎች ለአንበሳ የሚገርም ፍቅርና አክብሮት ነበራቸው ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ተራራ ላይ በአንበሳ ተከበው ይውሉ ነበር ፡፡ ንጉስ ሃይለስላሴ አንበሳ እያረቡ መሳጭ ወዳጅነት መፍጠር ችለዋል ፡፡ የሀገራችን አርበኞች በህቡዕ ሲደራጁ ስማቸውን  ‹ የጥቁር አንበሳ አርበኞች እንቅስቃሴ › ማለት ነው የወደዱት ፡፡ አንበሳ ብቻ አይደለም - ጥቁር አንበሳ ፡፡  አንበሳ ወደ ዳለቻና ቡኒ ቀለም መጠጋቱ እየታወቀ በሀገራችን ብዙ ነገሮች ‹ ጥቁር አንበሳ › የሚል ስያሜ እንዴት ሊያገኙ ቻሉ ? የሚሉትን ጥያቄዎች ጆሮውን መጠምዘዝ ከተፈቀደ ቀደም ያሉትን አባቶቻችንን ምናባዊ ዕውቀት ልናድቅ ግድ ይለናል ፡፡ የመገለጥ ብቃት ፡፡

ርዕሰ ዜናውን አንድ ግዜ ላስታውስና ልቀጥል ፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ አንበሳ ‹ አንበሳ › ከሚለው አስፈሪና ሞገሳም ዝናው በተጨማሪ ‹‹ በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኝ ! ›› የሚለው ማዕረግ በሰዎች ክብር ሊጨመርለት ነው ማለት ነው ፡፡ በሌላ አነጋገር ዶሎ ፣ ሶፍያ ፣ ሜጀርና ጄኔራል እንደ ሳሞራ የኑስ ብቸኛውን ማዕረግ ትከሻቸው ላይ ሊጭኑ ነው  - ሙሉ ጄኔራል ወይም ልዩና ብርቅዬ አንበሳ ፡፡ አንድርያና ጃኑ ደግሞ ባለ ሌላ ማዕረግተኛ  - ወይም ተራው አንበሳ ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጽያዊ ደም ስለሌላቸው ሳይንሳዊው እርከን አይመለከታቸውም ፡፡ ይህ ኮምፕሌክስ በጫካው ሰፈር አይኖርም ለማለት ማረጋገጫ አይኖርም ፡፡ 
ተመራማሪዋቹ በነካ እጃቸው ይህ ኮምፕሌክስ እየቆየ ሲሄድ ‹ አንበሳዊ ፍርሃት › ይፈጥራል የሚል ጥናት ያሰሙን ይሆናል ፡፡

ለማንኛውም  ተሷሚዎቹንም ሆነ ባለ ሌላ ማዕረግተኞቹን  ወላጅ አልባ አንበሶች በእንሰሳት ኮቴ ተገኝቶ መጎብኘት ስለሚቻል አንድ እሁድ ጎራ ብለው ይዝናኑ ፡፡

ማስታወሻ፡ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 149 ላይ የወጣ ፅሑፍ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡ 

No comments:

Post a Comment