Friday, March 30, 2018

የደበበ ሰይፉ የ ‹ ብርሃን ፍቅር › ምስጢር ምንድነው ?



የታላቁ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ የግጥም መጽሐፍ ‹ የብርሃን ፍቅር › ይሰኛል ። በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት በ1980 ዓ.ም ለህትመት የበቃ ቢሆንም ዛሬም እንደ አዲስ ቢነበብ የማይጎረብጥ ይልቁንም በተክለቁመናው የሚመስጥ ስራ ነው ። ማለትም የዜማው ፣ የቃላት አጠቃቀሙ ፣ መልእክቱ ፣ የቤት አመታቱ እና የስንኝ አወራረዱ የአንባቢን ቀልብ ይስባል ።

አንባቢያንና የዘርፉ ባለሙያዎችም ተክለቁመናውን መሰረት በማድረግ ያሳደረባቸውን ስሜት በአስተያየትና በሂስ መልክ ሲጽፉ ኖረዋል ። የማያረጅ ወይም ዘመን ተሻጋሪ ስራ ነውና ነገም ብዙ እንደሚባልለት አያጠራጥርም ።

ደበበ የመጽሐፉን ስያሜ ለምን « የብርሃን ፍቅር » እንዳለው ግን ምንም የተባለ ነገር የለም ። ምንም ያልተባለው ሚዛን የሚደፋ ቁም ነገር ስለጠፋ አይደለም ። እንደሚመስለኝ ትችቶቹ ከተክለቁመናው ባሻገር ያለውን ገጽታ ማየት ባለመቻላቸው ነው ። ደበበ እንደ ብዙ ገጣሚዎች አንደኛውን ትልቅ ወይም ገዢ ሃሳብ ያለው ግጥም አንስቶ ለመጽሐፍ ርዕስነት አላደረገም ፤ በውስጡ ‹ የብርሃን ፍቅር › የሚል ግጥም የለምና ። የመጽሐፉን አጠቃላይ አንድምታ በመለካትም መዞ ያወጣው ነው ለማለት በቂ አይደለም ። ይልቁንም ብርሃናዊ ሚስጢራትን በመስቀለኛ ሃሳቦች እንድንመረምራቸው የፈለገ ነው የሚመስለው ፤ ማለትም ርዕሰ ጉዳዩን ከቀጥታ እይታ ፣ ከተምሳሌት ፣ ከአሊጎሪ አውድና ከመሳሰሉት ፈትሸን እንድናይ ከተቻለም የተገለጸውን ብርሃን እንድንሞቅ ።

ደበበ በስሜት ብቻ ሳይሆን በእውቀትም የሚጽፍ ባለቅኔ በመሆኑ ይህንን አያስብም ብሎ መከራከር አይቻልም ። ጸሐፊ ተውኔትነቱና ተመራማሪነቱም ይህን ሃሳብ ለመደገፍ እገዛ ያደርጋሉ ። ለምሳሌ ያህል ገጸባህሪ ፣ ሴራ ፣ መቼት እና ቃለ - ተውኔት የተባሉ ስነጽሑፋዊ ቃላትን በመፍጠር ሙያዊ እገዛ አድርጓል ።

አጋጣሚ ሆኖ እነዚህ የአማርኛ ፍቺ ያገኙ ሙያዊ ቃላት ይጠቀሱለታል እንጂ በግጥሞቹ ውስጥም በርካታ ያልተባለላቸው ስልቶች የሚገኙ ይመስለኛል ። አንደኛው ቃላትን በሚያዝናና መልኩ ደቅሎ መልእክትን የማስተላለፍ ጥበቡ ነው ።

ለምሳሌ ያህል ‹ ልጀቱ የዘመነችቱ › በተሰኘው ግጥሙ ውስጥ ዘማኒዋ ሱሪዋን - ሱርት ፣ ጫማዋን - ጭምት ፣ ቀበቶዋን - ቅብትት ፣ ጃኬቷን - ጅክት ነው የምታደርገው ። እነዚህ ከስም ውስጥ የተደቀሉ መገለጫዋች የገጣሚውን ምናበ ሰፊነት ያስረዳሉ - አንድም ቋንቋን ከመፍጠር አንድም ምስል አከሳሰትን ከማጉላት ።

እንደ እኔ እምነት የደበበ ሰይፉን ስራዎች በጥልቀት የመረመረ ባለሙያ አንድ ተጨማሪ የግጥም አይነት መታዘቡ አይቀርም ። ከወል ፣ ሰንጎ መገን ፣ ቡሄ በሉ ፣ ሆያሆዬ እና ከመሳሰሉት ውጪ ማለቴ ነው ። ደበበ ልክ እንደ ፀጋዬ ገ/መድህን የራሱ ቀለማት ፣ አወቃቀርና ምት የሚጠቀም ባለቅኔ ይመስለኛል ። በተለይ ከግጥም አወራረዱ አንጻር የአንድ ቃል ዜማ / ሽግግር / ወይም የአንድ ቃል መድፊያን በሚጥም መልኩ በብቸኝነት ተጠቃሚ ነው ።

ሰማይና ምድር ፣ ልጅነት ፣ በትን ያሻራህን ዘር ፣ ያቺን ሟች ቀን የተሰኙ ግጥሞች የዚህ አባባል ማሳያ ናቸው ። በ ‹ ሰማይና ምድር › ውስጥ

በጀርባዪ ተንጋልዬ
አውዬ
በቅጽበት የፈተልኩትን ለብሼ
ሞቆኝ
በእኔው አለም ነግሼ
ደልቶኝ
ከፅድቁ ገበታ ቀምሼ
ጣፍጦኝ
እያለ ይወርዳል ።
አውዬ
ሞቆኝ
ደልቶኝ
ጣፍጦኝ ... የሚሉ ነጠላ ቃላት ያነከሱ ይመስላሉ እንጂ ያለክራንች ነው የቆሙት - ለዛውም ጠብቀው ። በ ‹ ያቺን ሟች ቀን › ውስጥም እንዲሁ ብቻቸውን ቁጭ ያሉት ትብነን ! ... ትምከን ! ... የሚሉ ቃላት ርግማናዊ ግዝፈታቸው ከምላሰ ጥቁር የሰፈር ሽማግሌዎች ወይም መጋረጃ ካገዘፋቸው ታዋቂ ጠንቋዮች የላቀ ነው ።

ይህ ሃይለኛ የአወራረድ ስልት በ ‹ ደበበ ቤት › ተይዞ መጠናት ያለበት ይመስለኛል ። ደበበ እንግዲህ እንዲህ ከምናውቀው በላይ ብዙ ነው ። የብርሃን ፍቅር ሚስጢርነትም ሰፊ ፍቺ የሰነቀ ነው ። በመድብሉ ውስጥ 49 ግጥሞች ተካተዋል ። ከእነዚህ ውስጥ 24 ግጥሞች ብርሃንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያነሳሉ ። 15 የሚደርሱ ግጥሞቹ ብርሃንን የሚያወሱት ፀሃይንና ጨረቃን መሳሪያ በማድረግ ነው ። ማለትም ፀሃይና ጨረቃ በተፈላጊው ቦታና አውድ በግልጽ ተጠቅሰዋል ። ዳኢቴ ፣ አዴላንቃሞ ፣ እቴቴ ፣ ዛሬ እንኳን ፣ ብቻ መገኘትሽ ፣ ሀዘንሽ አመመኝ ፣ ይርጋለም እና የመሳሰሉትን ለአብነት መጠቃቀስ ይቻላል ።

ዘጠኝ በሚደርሱ ግጥሞች ደግሞ ‹ ብርሃን › የተወከለው ራሱን ችሎ ወይም ተምሳሌታዊ ሻማ በማብራት ነው ። ሰማይና ምድር ፣ ያቺ ቆንጂት ፣ ወለምታ ፣ ስንብት ፣ መንታ ነው ፍጥረትሽ እና የመሳሰሉት እዚህ ምድብ ወስጥ የሚወድቁ ናቸው ። ለአብነት ያህል ‹ ያቺ ቆንጂት › በሚለው ግጥም

ጋሼ ላጫውትህ ትለኛለች
ያይኔን ብርሃን እየሞቀች  › የሚል ተደጋጋሚ ስንኝ አለ ። እዚህ ላይ ብርሃን የተወከለው ፍቅርና መልካምነትን ለመግለጽ ነው ።
በግጥም መድብሎች ላይ በተለይም አንድን ጉዳይ በስፋትና በጥልቀት መወቀር የተለመደ አይደለም ። ምክንያቱ የተለያየ ቢሆንም በዋናነት ግን ገጣሚው ራሱ ሊያመነጫቸው በሚችለው ውስን ሀሳቦች ባለመርካቱ ሲሆን አልፎም ተርፎም አንባቢን አሰለቻለው ብሎ መፍራቱ ነው ።

የብርሃን ፍቅር ብርሃናዊ ጨረሮቹን በተለያየ መልክ ሳይሰስት ነው የሚያደርሰን ። በርግጥ ለደበበ ሰይፉ ብርሃን ምንድነው ? ብርሃንን የሚያስረዳን የጨለማ ተቃርኗዊ ውጤት መሆኑን ነው ? ወይስ ከሳይንሳዊ ፣ አፈታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ዳራዎች ጋር የተያያዙ ሃሳቦች አሉት ?

በ ‹ እሱ ነው - እሱ › ግጥሙ ላይ
እሱ ነው - እሱ
አይን ሳይኖረው
      ለምን ብርሃን ኖረ የሚለው
እግር ሳይኖረው
      ለምን መንገድ ኖረ የሚለው
እሱ ነው - እሱ
ከቀናቴ
      ፀሃይቱን የሰረቀ
በመንገዴ
      አሜከላ ያፀደቀ
እያለ የሚበሳጨው ለምንድነው ? ይህ ግጥም የምናወራበትን የ ‹ ብርሃን › ጉዳይ በሚገባ የሚገልጽ ነው ። ምክንያቱም የገጣሚውን ያገባኛል ባይነት ደምቆ እንመለከታለን ። በተጠየቅ የሚሞግትባቸው ቃላዊ - ሃሳቦች ብርሃን ፣ መንገድ እና ፀሃይ ናቸው ። ሃሳቦቹን በቤተዘመድ ጉባኤ አይን ካየናቸው አንድም ሶስትም ናቸው ። ገጣሚው በእውቀት ፣ እድገት እና እውነት ላይ የማይደራደር መሆኑ ይሰማናል ።

የደበበ ሰይፉ የብርሃን ትኩረት አንደኛው ምንጭነት ከህይወት ተምሳሌትነት የመቀዳቱ ጉዳይ ይመስላል ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ከፈጠረ በኋላ የምድር ጨለማ የተሸነፈው በብርሃን ውልደት አማካኝነት ነው ። ፈጣሪ ብርሃንን የፈጠረው ለድምቀት ብቻ አይደለም ። በብርሃን አማካኝነት ሃይል ተሞልቶ ለፕላኔታችን መቀጠል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ። የመሬት ሰርዓተ ምህዳር የተመሰረተው በፀሃይ ከሚገኘው ብርሃን ነው ። ምክንያቱም አጽዋት የፀሃይ ብርሃንን ምግባቸውን ለማዘጋጀት ይጠቀሙበታል ። በሌላ በኩል ሰውና እንስሣት ምግባቸውን ከእጽዋት ስለሚያገኙ ሰንሰለቱ የጠነከረ ነው ።

ደበበ ሰይፉ የብርሃን ሰረገላ የማይታየውን ወይም የማይደፈረውን ነገር ሁሉ እውነት ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ መሆኑን የመረዳቱ ጉዳይም ርዕሰ ጉዳዩን አጥብቆ እንዲይዝ አግዞታል ።

ምነዋ ባየሁኝ › በሚለው ግጥም
ምነው ባየሁኝ
መሬቷን ሰቅስቄ
ዛፉን ተራራውን ቤቷን ሰዋን ሁሉ
አንድ ላይ ጠቅልዬ
በብርሃን ፍጥነት በሚምዘገዘግ ዘንግ
ወዲያ አንጠልጥዬ
እያለ ቀስተ ዳመናንና ጨረቃን ሁሉ ቀላል መጫወቻ እንዲሆኑለት ይመኛል ። ይህ ምኞት መለኮታዊ መሻትም ጭምር ነው ። ምክንያቱም መላዕክት የሚታዩት ብርሃን ባለበት ነው ። ብርሃንን ከመሬት ወደ ሰማይ ለመጓጓዝ እንደ ኤሌክትሮማግኔቲክ ሃይል ይጠቀሙበታል ። ሰዋች ጸሎትና ምሰጣ ሲያከናውኑ እንደ ሻማ አይነት ብርሃናዊ ነገሮችን የሚጠቀሙትም መለኮታዊ ግንኙነት ለመፍጠር በማሰብ ነው ።

ሌላው የደበበ ግጥሞች መሰረታዊ መለያ ፀሃይንና ጨረቃን የብርሃን ምሶሶ ወይም ኪናዊ ምርኩዝ የማድረጋቸው ጉዳይ ነው ። ከላይ እንደገለጽኩት 15 የሚደርሱ ግጥሞች ላይ ምርኩዝ ሆነው ቆመዋል ። አንባቢም በገባው መልኩ በዛቢያቸው እንዲሽከረከሩ ያደርጋቸዋል ። ገጣሚውም አልፎ አልፎ ለብቻ አንዳንዴ ደግሞ አንድ ላይ ያቀርባቸዋል ።

የጥንት ሰዋች የሁለቱን አብሮነት Duality በማለት ይገልጹታል ። ምክንያቱም እንደ ብዙ ሀገሮች አፈታሪክ ከሆነ ፀሃይና ጨረቃ ባልና ሚስት ፣ ወንድምና እህት ወይም ወንድማማቾች ሆነው ይወከላሉ ። የስው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ የሁለትዮሽ ውጤት ነው ። ሁለት እጅ ፣ ሁለት እግር ፣ ሁለት አይን ፣ ሁለት ጆሮ ወዘተ ያለው ። ይህ ጥምረት የፀሃይን ግማሽ እና የጨረቃ ግማሽ ውህደትንም ይወስዳል ። ፀሃይ የቀኝ ጎን ስትሆን ጨረቃ የግራ ናት ፤ የቀኝ ጎን ወንድ የግራ ደግሞ ሴትነትን ወካይ ነው ይላሉ ።

ደበበ ‹ አዴ ላንቃሞ › በተሰኘው ግጥም / አንድ የሲዳሞ ወንድ ነው / ተጠቃሹ ሰው ባሉት ሶስት ሚስቶችና ወንድ ሆኖ በመፈጠሩ ሲደሰት እናያለን ። በደማቅ የጨረቃ ብርሃን ታጅቦ ለሶስቱም ሚስቶች ለአዳር እንደሚመጣ ትእዛዝ ሰጥቶ እንዴት ሽር ጉድ እንደሚሉ በማሰብ ነው የሚስቀው ። ሊያድር የሚችለው ግን አንዷ ጋ ብቻ ነው ።

ብርማይቱ ጨረቃ
የብርሃን ጠበል አፍልቃ
ተፈጥሮን ስታጠምቃት
እንደገና ስትወልዳት
እያለ ነው ግጥሙ የሚዘልቀው ። እንደ ጨረቃዋ ልዩ ድምቀት ሶስቱ ሚስቶቹ ጋ በነበረው ሃያል ሙቀት እየረካ ነበር ። ምክንያቱም ሶስቱም ‹ እኔ ጋ ነው የሚያደረው › በሚል ያሻቀበ ጉጉት ጎጆውን በፍላጎት ፍላት እንደሚያነዱት ስለማይጠረጠር ። ጨረቃዋና ሴቶቹ በፈጠሩት ግለትም ሆነ ጾታዊ አንድነት የተመሳሰሉ ይመስላል ። በግጥሙ መሰረትም አዴ ላንቃሞ የወንድነቱን ፅድቅ አድናቂ ነውና ከጨረቃ በትይዩ የቆመ የፀሃይ ወገን ሊሆን ይችላል ።

ደበበ በተለይም ‹ ገና በልጅነት › እና ‹ ዛሬ እንኳን › በተሰኙ ግጥሞቹ ውስጥ ፀሃይና ጨረቃን በጋራ እየገለጸ ተጠቅሞባቸዋል ። ፀሃይን ሲያነሳ ሃይልን ፣ ህይወትን ፣ ጤናን ፣ ጥልቅ የፍቅር ስሜት መገለጫነትን በመወከል ሲሆን ጨረቃን ሲገልጻት ሚስጢርን ፣ ብቸኝነትን ፣ ውበትን የመሳሰሉትን እንድናስብ በማመላከት ነው ። የደበበ ሰይፉ የብርሃን ፍቅር ብርሃን አስሶ ፣ በብርሃን ተማርኮ ብርሃን የሚሰብክ ኪናዊ ዳመራ ነው ። ‹ የብርሃን ፍቅር › አንድ አይኑን ፀሃይ ሌላውን ጨረቃ አድርጎ ብርሃናማ መሃልየ የሚሰብክ ኪናዊ ካህን ነው ።

No comments:

Post a Comment