Monday, September 24, 2012

የጉራጌ ቁጥሮች



እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ፣ አይሁድ በቅናት ተነሣሥተው ለ300 ዓመታት ያህል በቆሻሻ መጣያ ጥለውት ነበር። ይሁንና በ326ዓ/ የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒ ኪራቆስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት፣ መስቀሉ የተጣለበትን አካባቢ ወቀች ። ከዚያም በኋላ ደመራ ደምራ በእሳት አቀጣጥላ ዕጣን ባጨሰች ጊዜ ፣ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አወጣች።
ንግሥተ እሌኒ በጭሱ ምልክትነት፣ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ማስቆፈሯን ማለትም መስከረም 17 ቀን አስጀምራ መጋቢት 10 ቀን እንዳስወጣቸው ይነገራል። ዛሬ በኦርቶዶክስ ምዕመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንን ታሪክ ተከትሎ እንደሆነ ሊቃውንቶች ይናገራሉ ፡፡
መስቀል ብዙ ነገር ነው ፡፡ ክርስትያኖች በግጥም ሲገልጹት እንደሚከተሉት ይደረደራል ፡፡

ዕፀ መስቀሉን ያዙ ጋሻ
ሰይጣን እንዲጠፋ እንዲያጣ መድረሻ ፡፡
ዕፀ መስቀለን ተሳለሙ
የአምላክ ቃል አለበት ደመ ማህተሙ ፡፡
መስቀል ኃይል ነው ለክርስቲያን
እሱን የያዘ ሰው አይደፍረውም ሰይጣን ፡፡
መመኪያችን ነው መስቀል
ተቀድሷልና በመለኮት ኃይል ፡፡

መሰቀል በዓል ብዙ ገራሚ ትውፊቶችን በየክልሉ አቅፎ የያዘ ነው ፡፡ የአዲስ አበባው በከተሜው፣ በመዘምራን፣ በሃይማኖት አባቶችና በቱሪስቶች ድብልቅ መንፈስ ተዋህዶ ልዩ ለዛና መስህብ ይፈጥራል ፡፡ በተለይም በደቡብ ክልሎች ያለው የመስቀል ስርዓት ባህላዊ ትውፊቱ እንደ ተራራ የገዘፈ ሀሴትን የሚያጭር ነው ፡፡ ይህ ባህላዊ እሴት በዓመት አንዴ የሚነገርለት እንጂ ሰፊ ምርምር ተካሂዶበት እንደሚታይ ድንቅ ቅርስ በውስጣችን የምንተክለው አልሆነም ፡፡ ዞሮ ዞሮ የጉራጌ ብሄረሰብ የበዓል አከባበርም ዩኔስኮ  እንዲመረምረውና ዕውቅና እንዲሰጠው ከወዲሁ መጠየቅ አስፈላጊ ሳይሆን አይቀርም ፡፡
አነዚህ በመስቀል ሰሞን የሚደምቁት የጉራጌ 13 ቁጥሮች ማለትም 12፣ 13 ፣ 14.፣ ……. 23፣ 24 …. የማይዳሰሱ ሃብቶች እየመሰሉኝ ነው ፡፡  በበዓል አይን ስናያቸው እያንዳንዳቸው የሚያምር የተግባር ዝናር  ታጥቀዋል ፤ ይህን ወረድ ብለን እናየዋለን ፡፡ በሌላ በኩል ግን በዓላዊ  ምሳሌያቸውን በማስፋት ለሌላ የትግል ግዳጅ ማዝመት ይቻላል ፡፡ ለምሳሌ ነው - የብሄራዊ ቡድናችን ተጫዋቾች አነዚህን ቁጥሮች ለምን ለጀርባቸው መጠሪያ አያደርጓቸውም ? ቀንደኛ ግብ አዳኝ ካለን የማሊያ ቁጥሩ ዳመራው በሚቀጣጠልበት ቀን ይሆናል ፡፡ የራቀንን ውጤት በዚህ መልክ ማምጣት ይቻላል ወይስ ለምን ጥቅም አትበሉኝ ፡፡ ለምሳሌ ነው - መስከረምን 12ኛ ወር ብለነው ጻጉሜን 24ኛ ማድረግ ይቻላል ፡፡ እንደ ጻጉሜ ሁሉንም ልዩ ለማድረግ ወይስ ለምን ጥቅም አትበሉኝ ፡፡ ለምሳሌ ነው - ....
መስቀል ለጉራጌ ብሄረሰብም ብዙ ነገር ነው ፡፡
መስቀል ደስታ ነው
መስቀል ትዳር ነው
መስቀል ምርቃት ነው
መስቀል መዝናኛ ነው
መስቀል የቁጥሮች ውበት ነው ፡፡
መስቀል በጉራጌ ሲታሰብ ከ12 እስከ 24 ያሉ ቁጥሮች ምን ያህል የተለቀ ሚና እንደሚጫወቱ ማሰብ ይቻላል ፡፡  ለመሆኑ በነዚህ ሁሉ እንደ ባቡር ፉርጎ የተቀጣጠሉ ቀናት ምን ይደረጋል መባሉ አይቀርም፡፡ እያንዳንዱ ቀን በራሱ በዓል ወይም የበዓል ድጋፍ ሰጪ ነው ፡፡ እስኪ ቀናቱን እየተረጎምን እንውረድ፡፡
መስከረም 12 ፤  የጃፎር መስቀል ይባላል ፡፡
ይህ በዓል በቡድን በመሆን በዛፍ ስር ይከበራል ፡፡ የቡድኑ አባላት መስዋዕት የሚያደርጉትን ከብት ይዘው ዛፉ ስር  የሚገናኙት ከቀኑ አስር ሰአት ላይ ነው ፡፡ የተዘጋጀው በሬ ታርዶ ደሙ ዛፍ ላይ ሲረጭ ሞራውም በእሳት ይቃጠላል ፡፡ የዚህም ምክንያት የሞራው ሽታ አካባቢውን ከበሽታ ነጻ ያደርገዋል የሚል ነው ፡፡ አባላቱ የቻሉትን ያህል ጥሬ ስጋ በልተው ቀሪውን ተከፋፍለው ወደ ቤት ሲያመሩ ዞረው እንዲያዩ አይፈቀድም፡፡ ቦታውን ከለቀቁ በኃላ ይተካል ተብሎ በሚገመተው ኃይል ችግር እንዳይደርስባቸው በመስጋት ፡፡

መስከረም 13 ፤  ወሬት ያህና ወይም እንቅልፍ ነሺ ቀን ይሉታል ፡፡
 በዚህ ቀን እንቅልፍ የሚታጣው ሁሉም ቤተሰብ መስቀልን ‹‹ እንዴት አሳልፈው ይሆን ; ›› ብሎ ስለሚያስብ ነው ፡፡ አንዳንድ     ሰዋች ቀኑን የበዓሉ መክፈቻ ይሉታል ፡፡
መስከረም 14 ፤ ይፍት ወይም የዕርድ ዋዜማ የሚል መጠሪያ አለው ፡፡
ቀን ሴቶቹ የቤቱን ጣራና ግድግዳ ካጸዱ በኃላ መሸት ሲል ለቤቱ ወለል የተሰሩት ምንጣፎች ይነጠፋሉ ፡፡ የቤት ዕቃዋችና        ጌጣጌጦች ግድግዳ ላይ ይሰቀላሉ ፡፡ ቆጮው በተለየ መልኩ በእንፋሎት ብቻ እንዲበስል ይደረጋል ፡፡ ይህም ‹‹ ዳቡዬ ›› በሚል ይታወቃል ፡፡ ይህ አይነት የቆጮ ጋገራ የተመረጠው አማልክት በምግብ ስነ ስርዓት ላይ የሚሳተፉ ባለመሆናቸው ቢያንስ ሽታው እንዲደርሳቸው በማሰብ ነው ፡፡

መስከረም 15 ፤  ወኀምያ ወይም የእርድ በዓል ተብሎ ይጠራል ፡፡
ወኀምያ ደስታና ሰላም ማለት ነው ፡፡ እለቱ በአንዳንድ አካባቢዋች ‹‹ የጨርቆስ ማይ ›› በመባል ይታወቃል ፡፡ ይህ እለት ጨርቆስን ያመለክታል ፡፡ በዚህ ቀን ለእርድ የተዘጋጁ ከብቶች በየቤቱ በራፍ ይታረዳሉ ፡፡ ከበሬው የሚፈሰው ደም በቃጫ ተነክሮ የቤቱ ደጃፍ መቃንና ምሶሶ ይቀባል ፡፡ ከበሬው የተገፈፈው ሞራም እስከ መጪው ዓመት ድረስ የቤት ምሶሶ ላይ ይሰቀላል ፡፡ የማረድ ግዴታ ያለባቸውና የሌለባቸው ሰዋች እንዳሉም መታወቅ አለበት ፡፡  የማረድ ልምድ ያለባቸው ሰዋች የወሸምያ ዕለት ካላረዱ ወሸምያ ይገድላቸዋል ተብሎ ይታመናል ፡፡ በየዓመቱ ከሚያርዱበት የተወሰነ ቦታ ፈቀቅ ለማለት እንኳን አይሞክሩም ፡፡ ልማድ የሌላቸው ሰዋች ግን ስጋም ገዝተው በዓሉን ማክበር ይችላሉ ፡፡

የማረድ ልማድ ያለባቸው ልምዱን ለመሰረዝ ከፈለጉ የሚከተለውን ህግጋት ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ፡፡ በየአመቱ በሬ የሚያርድ ሰው በቀጣዩ ዓመት ጥጃ ያርዳል፡፡ በሁለተኛው ዓመት ፍየል ያርዳል ፡፡ በሶስተኛው ዓመትም ፍየል ያርዳል ፡፡ በአራተኛው ዓመት ዶሮ አርዶ በአምስተኛው ዓመት ምንም ባያርድ ወሽምያ ስለሚረሳ ችግር አይመጣበትም ፡፡ አሪፍ የማካካሻ ስልት ናት ፡፡

መስከረም 16፤   ምግይር ወይም ደመራ ነው ፡፡
ደመራው በየቤቱ ደጃፍ የሚተከለው የልጆች ደመራና የአባቶች ደመራ ተብሎ ይታወቃል ፡፡ በየበራፉ የሚተከለውን ደመራ ጠዋት ወይም ማታ ማቀጣጠል ይቻላል ፡፡ የአባቶች ደመራ የሚለኮሰው ግን ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው ፡፡ በዚሁ ግዜ አባ ተዘር / ክረምትና በጋ / የተባለውን ጨዋታ ልጆች ይጫወታሉ ፡፡ በደመራ እለትም ሆነ በሌሎች የመስቀል ቀናት ከብቶች ውጪ አይወጡም ፡፡ የተዘጋጀላቸውን ምግብ ከቤት ይበላሉ ፤ አይታለቡም ፡፡

መስከረም 17፤    ንቅባር ወይም ትልቁ በዓል ይባላል ፡፡
በዚህ ቀን ቤተዘመዶች ፣ በቡና የሚገናኙ ጎረቤቶች ተሰብስበው ደስታቸውን ይገልጻሉ ፡፡ አዛውንቶች አናታቸው ላይ ቅቤ ይደረግላቸዋል ፡፡  የከብቱ ሻኛም የሚበላው በዚህ ቀን ነው ፡፡ አንድ ሰው እናት ፣ አባት፣ ታላቅ ወንድም ወይም አያቱ እያለ የመስቀል ሻኛን ለብቻ አይበላም ፡፡ ዘመድ ከሌለው እንኳን በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ጋ ይዞ በመሄድ ማስመረቅ ይኖርበታል ፡፡ ይሄ ሁሉ ለሻኛ  ; ካላችሁ ሻኛ በሰባት ቤት ጉራጌ የበስር ንጉስ ወይም የስጋ ንጉስ መባሉን ማወቅ ያስፈልጋል ፡፡

መስከረም 19- 23 ፤   የጀወጀ ወይም የመተያያ ቀን ይባላል ፡፡ ከመስከረም 18 በኃላ ያሉትን ቀናት የሚያመለክት ሲሆን ለአንድ
ሳምንት ያህል ባሉት ቀናት ባልና ሚስት ወገኖቻቸውን በተለይም እናት አባቶቻቸውን ስጦታ በመያዝ የሚጠይቁበት ነው ፡፡    የሙየቶቸም ጭፈራ ይከናወናል ፡፡ ሙየት ማለት በእናቶችና ሴቶች የሚዘፈን ባህላዊ ጨዋታ ነው ፡፡
ዘመዳሞች ይጠያየቃሉ፣ ይመራረቃሉ ፡፡

መስከረም 24 ፤   አዳብና ወይም መሰነባበቻ በሚል መጠሪያ ይታወቃል ፡፡ በአንዳንድ በተ ጉራጌዋች ዘንድ ከጀወጀ በተለየ መልኩ አሁንም
                   ድረስ በድምቀቱ  የሚታወቅ ሲሆን ለወጣቶችና ልጃገረዶች የተለየ የጭፈራ አጋጣሚ ነው ፡፡ ጭፈራው ከመስከረም
                    አጋማሽ ጀምሮ  ጥቅምት ድረስ ይዘልቃል ፡፡ የአዳብና ጭፈራ በገበያዋች ላይ የሚከወን ሲሆን ድንቅ ባህላዊ አልባሳትና
                   የውዝዋዜ  ትዕይንቶች ይታዩበታል ፡፡ በነገራችን ላይ ‹ መንጠየ › የቋንጣ ክትፎ የሚበላበት የመጨረሻ ስነ ስርዓት ማሳረጊያ
                    ነው ፡፡ ይህ በዓል በአንዳንድ አካባቢዋች እስከ ጥቅምት 5 ሊቆይ ይችላል ፡፡




Sunday, September 23, 2012

‎‹‹ የስልጣን ዘመን ገደብ ›› - ህግና ህዝብ አክባሪ መሪ ይፈልጋል‎



መሪነት የቀደመ መስዋዕትነትን ይጠይቃል

ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ወጥታ ራሷን በራሷ የምታስተዳድረው አፍሪካ ተስፋና ህልሟን ለማሳካት በ1990 ዋቹ አካባቢ ይበል የሚያሰኝ ፓለቲካዊ ርምጃዋችን መውሰድ ጀምራ ነበር ፡፡ ይህ ርምጃ ‹ አፍሪካ ያለ እኛ ድጋፍ ማየትም ሆነ መራመድ አትችልም › ይሉ ለነበሩት ምዕራባዊያን የጠነከረ ምላሽ ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል ፡፡

ህገ መንግስታቸው ውስጥ በደማቅ ቀለም እንዲጻፍ ያደረጉት ‹‹ የስልጣን ዘመን ገደብ ›› የተረጋጋች አህጉር ብቻ ሳይሆን በአጭር ርቀት እከኳን አራግፋ የልማትና የዴሞክራሲ ተቋዳሽ ልትሆን እንደምትችልም ምልክት የፈነጠቀ ዘመናዊ አሰራር ነበር፡፡ 33 የሚደርሱ የአፍሪካ ሀገሮች የህዝብ እንጂ የጥቂት ብልጣ ብልጥ ሰዋች ርስት አይደለም በማለት ገደቡን ከሁለት ግዜ በላይ እንዳይበልጥ አድርገዋል ፡፡ ሶስት ዙር ከምትፈቅደው ሲሸልስ በስተቀር ፡፡ በርግጥ ብዙዋቹ በገደቡ ወሰን ቢመሳሰሉም አንዱ የስልጣን ዘመን ምን ያህል ዓመት ይይዛል በሚለው ልዩነት ነበራቸው ፡፡ አንዳንድ ሀገሮች ትንሹን አራት ሲያስቀምጡ አንዳንዶች ደግሞ ትልቁን ሰባት ዓመት ህገ መንግስታቸው ላይ አስፍረዋል ፡፡

ብዙዋች አንዱን የስራ ዘመን አምስት ዓመት በማድረግ ለሁለት ግዜ ያህል የፈቀዱ ናቸው ፡፡ ቤኒን፣ ቦትስዋና፣ ቡሩንዲ፣ ኬፕቨርድ፣ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐፕሊክ፣ ዴሞክራቶክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ማሊ፣ ሞሪታንያ፣ ሞሪሺየስ፣ ሞዛምቢክ፣ ናምቢያ፣ ኒጀር፣ ሳኦቶሚፕሪንስፔ፣ሴራሊዮንና ዛምቢያ እዚህ ምድብ ውስጥ ይካተታሉ ፡፡

ጋናና ናይጄሪያ አራት ኣመት ፤ የኮንጎ ሪፐፕሊክና ሩዋንዳ ሰባት ዓመት ፤  ኮሞሮስ ፣ ኤርትራና የመሳሰሉት ደግሞ ገደብ ካልጣሉ ሀገሮች ውስጥ ይመደባሉ ፡፡ ግራ የሚያጋባ ምድብ ውስጥ ለረጅም ግዜ ቆይተው ከነበሩ ሀገሮች ውስጥ ኢትዮጽያ ‹‹ የቡድን አባት ›› ሆና ቆይታለች ማለት ይቻላል ፡፡ ልክ እንደኛ በኢትዮጽያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺንም ግራ ተጋብተው እንደነበር በብሎጋቸው ላይ የሰፈረው የሚከተለው ጽሁፍ ያስረዳል ‹‹ የኢትዮጽያ ህገ መንግስት ትልቁን የፓለቲካ ስልጣን ለያዘው ጠ/ሚ/ር ገደብ ማስቀመጥ ቢኖርበትም ያደረገው ለፕሬዝዳንቱ ነው ›› አንዳንዶች ጉዳዩን የሃያው ዓመት ምርጥ ፓለቲካዊ ስላቅ በማለት ሲጠሩት ተሰምቷል ፡፡

እናም ሀገራችን ለረጅም ዓመታት የግራ እግር ጫማ በቀኝ ተጫምታ ስትወላከፍ ቆይታለች ፡፡ ሰሞኑን ታዲያ የቀኝ እግር ጫማ- ለቀኝ እግር ብቻ መዋል አለበት የሚል የሚመስል መግለጫ ይፋ ተደርጓል ፡፡ በኢትዮጽያም የመንግስት ኃላፊዋች የስልጣን ዘመን በአስር ዓመት ተገድቧልና  ፡፡ እልልታ ያስፈልገው ነበር - ግና ከአፍሪካ በሃያ አመታት ወደ ኃላ ቀርቶ ዛሬ የተነገረው ዜና በህዝቡ አንደበት ቀድሞ በመነገሩ  ‹‹ ሰበር ›› ለመባል አልቻለም ፡፡ ምናልባት ለሰበር ጥቂት ቀረብ የሚለው ‹‹ ከ65 ዓመት በላይ የሆነው ሰው በስልጣን ላይ መቀጠል አይችልም ›› የሚለው ገደብ ነው ፡፡ በዚህ ያልወጣ ህግ መሰረት የ66 ዓመት አዛውንት ስለጃጃ ሀገር ለመምራት ብቃት የለውም ማለት በራሱ የጃጀ ሀሳብ ሊያስብል የሚችል ይመስለኛል ፡፡ በሌላ አነጋገር በ80 ዓመታቸው ምርጥ ስራ የሰሩትን የዓለማችንን መሪዋች ታሪክ አለማወቅን ያቃጥራል ፡፡ በመሰረቱ የብዙዋች / አንደኛው / ጥያቄ አንድ መሪ ረጅም ግዜ አይቆይ እንጂ በ66 ዓመቱ አይስራ የሚል አይደለም ፡፡ ለመሆኑ ይህ እድሜ ብቁ አለመሆኑ በምንድነው የተረጋገጠው ? ጥሩ ስም ባላቸው ሰው የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ግኝት ካለ ሊግረን ይገባል ፡፡ ነው የሀገሪቱን Life expectancy በመሾፍ ብቻ ነው ከአራት ነጥብ የተደረሰው ፡፡  አሁን ደግሞ የቀኝ እግር ጫማ በግራ እግር እንዲደረግ ማዘዣ የተጻፈ አስመስሎታል ፡፡

አሁን የወጣው ‹‹ የስልጣን ዘመን ገደብ ›› ተነገረ እንጂ ገና በተግባር ያልተፈተሸ በመሆኑ  ‹‹ ጥሩ ነው ›› የሚል የሞራል ታርጋ ለመለጠፍ የሚያስችል መነሻ የለም ፡፡ ይህን ለማለት የሚያስችለው  ደግሞ አፍሪካ ባለፉት ሃያ አመታት የመጣችበት መንገድ አስተማማኝ አለመሆኑ ነው ፡፡ ብዙዋቹ የአፍሪካ መሪዋች ለወሬ እንጂ ለተግባር ቅርብ አይደሉም ፡፡ ለቁጥር የሚታክት ሚሊዮን ዶላር ወደ ውጭ አግዘው እንኳ ሙስናው ውስጥ ከመልከስከስ አይታቀቡም ፡፡ ሃያና ሰላሳ ዓመታት በፈላጭ ቆራጭነት መንገድ ወንበር ይዘው በመጨረሻ እንኳ የተሻለ ስርዓት ለመፍጠር ፍቃደኛ አይሆኑም ፡፡ ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ለአንድ ጋዜጠኛ ‹‹ በህይወት እስካለሁ ድረስ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ነኝ ›› ማለታቸውን እናስታውሳለን ፡፡ የጋዳፊና የሙባረክ ዓይነቱ ደግሞ እስከመጨረሻው ሰዓት ‹ ህዝባችን ይወደናል፣ ህዝባችን ለኛ ይሞታል ! › ይሉ ነበር ፡፡

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ወደ ስልጣን የመጡት በ1986 ነበር ፡፡ እስከ 2004 ድረስ ሀገሪቷን መሯት ወይም መጠመጧት ፡፡ በዚህ ግዜ ትዝ ሲላቸው ለካ የስልጣን ዘመን ገደብ አስቀምጠዋል ፡፡ በ2005 ለሀገሪቱና ለህዝቡ ጥቅም በሚል ህገ መንግስቱን ፐውዘው የገደቡን ግዜ አሻሻሉት ፡፡ በ2006 በተደረገው ሶስተኛ ምርጫ ደረታቸውን ነፍተው አሸነፉ ፡፡ አሁንም አሉ ፡፡ የገደቡም ቁጥር ከፍ እንዳለ ነው ፡፡

ይህን ምርጥ የዴሞክራሲ ጎዳና የናሚቢያው ፕሬዝዳንት ሳምኒዮማ በ1999 በይፋ ከጣሱት በኃላ ስንት ፈሪ - ጅግኖች ተከተሏቸው ? የሴኔጋሉ ዲዩፍ፣ የጊኒው ላንሳና ኮንቴ፣ የቶጎው ጋንሴቤ ኢያዴማ፣ የጋቦኑ ኦማር ቦንጎ፣ የቡርኪናፋሶው ካምፓወሬ፣ የቻዱ ኢድሪስ ዳቤ፣ የቱንዝያው ቤን አሊ፣ የካሜሮኑ ቢያ፣ የአልጄሪያው ቡተፍሊካ … ማን ቀረ ታዲያ ?  እያንዳንዱ መሪ ራሱ ያወጣውን ህግ ለመሻር ያደረገውን ብልጠትም ሆነ የጭካኔ መንገድ ስናነብ ወይም ስንሰማ የሚያሳፍር ሆኖ ነው የሚገኘው ፡፡

በርግጥ የወጣውን ህግ ጠንክረው በመጠበቃቸው መፈንቅለ ህግ ሊያደርጉ የሞከሩ መሪዋቻቸውን አሳፍረው የመለሱ ህዝቦችም አሉ ፡፡ በዋናነት የዛምቢያ፣ ማላዊና ናይጄሪያ መሪዋች ህገ መንግስቱን የመቀየር ሙከራ ሲከሽፍባቸው የእነሱን እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ አሻንጉሊት መሪዋችን ለመተካት ጥረት አድርገዋል ፡፡

የዛምቢያው ፍሬዲሪክ ቹሉባ ለሶስተኛ ዘመን ምርጫ ሲሯሯጡ የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዋች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ፣ የሰራተኛ ማህበራት፣ የተማሪዋች ህብረት፣ የሴት አደረጃጀቶች፣ ቤተክርስትያናት፣ የህግ ባለሙያዋች እንዲሁም ህዝቡ አረንጓዴ መቀነት በመልበስ፣ የመኪና ጡሩንባ በማሰጮህና በመዘመር አስደንጋጭ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል ፡፡ ተቃውሞው ያሰቡትን እንዳይፈጽሙ ያደረጋቸው ቹሉባ ሌላ ዘዴ ቀየሱ ፡፡ በቀላሉ እቆጣጠረዋለሁ፣ የእኔንም ሃሳብ እንዲፈጽም አደርገዋለሁ ብለው ያሰቡትን  ሌቪ ምዋናዋሳን ለፕ/ት ምርጫ ዕጩ አድርገው መረጡ ፡፡ ምዋናዋሳም ምርጫውን አሸነፉ ፡፡ ነገር ግን ከድሉ በኃላ አዲሱ መሪ የቀድሞውን ጓደኛቸውን ሀሳብና ተጽዕኖ አሽቀንጥሮ በመጣል በራሳቸው መንገድ ተጓዙ ፡፡ የቹሉባን ያለመከሰስ መብት በመግፈፍ በሙስና እንዲጠየቅ አስደረጉ፡፡

የማሊውም  ታሪክ ከዛምቢያው የሚርቅ አይደለም ፡፡ ፕሬዝዳንት ባኪሊ ሙሉዚም ከህዝቡ የደረሰባቸውን ተቃውሞ መቋቋም ባለመቻላቸው አንድ አሻንጉሊት ወራሽ ፈለጉ ፡፡ ቀልባቸውም ቢንጉዋ ሙታሪካ ላይ አረፈ ፡፡ ብዙዋች እኚህ ሰው ታማኝ ጩሎ እንደሚሆኑ እምነት አሳድረው ነበር ፡፡ በርግጥም ከምርጫው ድል በኃላ / ያው በአፍሪካ ፕሬዝዳንቱ የወከለው ሰው በተዓምር አይሸነፍም / ሙሉዚ እና ሙታሪካ በተመሳሳይ መንገድ የሚጓዙ መሰሉ ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኃላ ሙሉዚ ሙታሪካ የቀረጹትን የጸረ ሙስና ፓሊሲ መቃወም ጀመሩ ፡፡ ያኔ ጨዋታው ፈረሰ… ዳቦው ተቆረሰ…

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት አባሳንጆ ህገ መንግስቱን ለመቀየር ያደረጉት ጥረት ከህዝብና ተቃዋሚዋች ብቻ ሳይሆን ከራሳቸውም ፓርቲ ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል ፡፡ በመሆኑም የራሴ ሰው ነው የሚሉትን ኡማሩ ሙሳ ያርአዱም ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ አድርገው አቀረቡ ፡፡ ሚያዚያ 2007 በተደረገው ምርጫ በአጨቃጫቂ ሁኔታ አሸነፉ ፡፡ እኚህ ሰው ግን ከህዳር 2009 ጀምሮ በጠና ታመው ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለህክምና በማቅናታቸው የስልጣን ክፍተት በሀገሪቱ ሊፈጠር ችሏል ፡፡ የካቲት 2010 ሴኔቱ የፕሬዝዳንቱን ስልጣን ለምክትላቸው ጉድላክ ጆናታን አስተላለፈ፡፡ ፕሬዝዳንቱ መጋቢት 5 ቀን 2010 በመሞታቸው የስልጣናቸውን ግዜ እንኳን መጨረስ አልቻሉም ፡፡

ርግጥ ነው አፍሪካ ጥቂት ሞዴል መሪዋችም አሏት ፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ከአንድ የስልጣን ዘመን ቆይታ በኃላ ብቻ ነበር ወንበራቸውን ያስረከቡት ፡፡ የቤኒኑ ማቲሁ ኬሬኩ ፣ የኬፕቨርድ ማስካሪንሃስ ሞንቲሮ ፣ የማሊው አልፋ ኮናሬ ፣ የሞዛምቢኩ ጃኪም ቺሳኖ ፣ የሳኦቶሚፕሪንስፒ ማገል ትሮቫዳ ፣ የታንዛኒያው ቤንጃሚን ማካፓ፣ የቦትስዋናው ፌስተስ ጎንተባይ ሞይ የሁለት ግዜ የስልጣን ዘመናቸውን እንደጨረሱ በህገመንግስቱ ላይ ግፍ ወይም ዘረፋ ሳያካሂዱ ቦታቸውን ለተተኪው አስረክበዋል ፡፡ አፍሪካ እኒህን መሰል ህግና ህዝብ አክባሪ መሪዋች በብዛት ያስፈልጋታል ፡፡ እነዚህ ጥቂት ምርጥ ዘሮች ግን የአረምና የእንክርዳድን ሚና የሚጫወቱት በርካታ መሪዋች እያጠወለጓቸው በመሆኑ የስጋቱ በረዶ ዛሬም ህሊናችን ወስጥ እንደተጋገረ ይገኛል ፡፡

ስልጣን መገደብ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጠናከር ፣ ውድድርን ለማላቅ ፣ አዲስ አስተሳሰብን ለማመንጨት ፣ የገነገነ ቢሮክራሲንና  ሙስናን ለመሞረድ ከፍተኛ ጥቅም አለው ፡፡ ሀገራችን ዛሬ ወደዚህ ስርዓት እቀላቀላለሁ ብትልም አባባሉ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታነት ይሁን ለእውነት የተተኮሰ መሆኑ አይታወቅም  ፡፡ ትክክለኛ ቢሆን ይመረጣል ፡፡  አጠራጣሪ የሚያደርገው  ደግሞ ከላይ ለማሳየት የተሞከረው የአፍሪካ መሪዋች ልምድ ነው ፡፡ ኢትዮጽያም ከዚህ የተሻለ የልምድ ሪከርድ አላስመዘገበችም ፡፡  ግራም ነፈሰ ቀኝ መሪዋቻችን በቺሳኖና በማንዴላ ወይስ በሙሴቬኒና በፓውል ቢያ መንገድ ይጓዛሉ  የሚለውን ጥያቄ  በአግባቡ ለመፍታት ገና ረጅም ርቀት ይቀረናል ፡፡

Saturday, September 15, 2012

ነገን ማየት



ይህ ስዕልና ግጥሙ ምንና ምን ናቸው ? የስዕሉስ ውክልና ምን ይሆን ? ቀዛፊው አሞራ … ዳመና ያነቃት ጸሃይ …ወርቅ የመሰለው ሰማይ …በዳመናው የተሰሩ ጅምር የስዕል ንድፎች … ጥግና ጨለማ ውስጥ መልህቋን የጣለችው መርከብ … በሰማዩ ቅላትና በባህሩ ጥቁረት መካከል ያለው ልዩነት …


ሰላም ፍቅር ሽቶ - ያሰቡት ሲጠፋ
ህብረት ተስፋ ቋጥሮ - የእኩይ ሽል ሲፋፋ
ፍርሃት ያለ ድንበር - ፍጥረታት ሲደቁስ
ጭፍሮቹን አንግሶ - ሰቆቃ ቢለኩስ
በእሳቱ ወላፈን - በወበቁ ጨረር
ርግጥ ባይታወቅ - ነገን ማየት አይቀር
የውስጥ ግብ አንካሴ - ከአድማስ ጫፍ መወርወር
ፍጹም አይገታም - ለድል ቀን መዘመር ፡፡
ምድር በዶፍ ትዕቢት - ዘወትር ብትወቃ !
ምኞት የደም ዕጢ - ሮጦ አያበቃ ፡፡

Saturday, September 8, 2012

‎በቀጣዩ መንግስት የሚወራረዱ ሂሳቦች … ?!?‎






አቶ መለስ በሞት ምክንያት ዱላቸውን ለተተኪው መሪ አላቀበሉም፡፡ ዱላው አንዳንዴም እንደ አራት አንዳንዴም እንደ አንድ በሚያስበው ድርጅት እጅ ነው ያለው ፡፡ ከብዙ ፍትጊያም እንበለው የሰከነ ውይይት በኃላ በአንድ ሰው እጅ ውስጥ መውደቁ የግድ ነው ፡፡ ድርጅቱ ለግዜው ባለዱላውን አይወቀው እንጂ እንዴት መሮጥ እንደሚገባው አስቀድሞ ወስኗል፡፡ ይህን መስመርም ለህዝቡ   ‹‹ የመለስ ፖሊሲና ስትራቴጂን ያለ አንዳች ማዛነፍ እናስቀጥላለን ›› በማለት አውጇል ፡፡

በሌላ አነጋገር አየለም መጣ አየለች ፖሊሲው ትክክለኛ በመሆኑ ሃዲዱን ይዘው እንዲጓዙ ይጠበቃል ማለት ነው ፡፡ እንግዲህ አከራካሪው ጉዳይ የሚጀምረው ከዚህ ምዕራፍ ላይ ነው ፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ወገኖች፣ የፖለቲካ ምሁራኖች፣ ጋዜጠኞች፣ ለሚዛናዊ ብይን የቀረቡ ሰዋች የሚሉት አቶ መለስ እንደ ጥንካሬያቸው ሁሉ ደካማ ጎንም ነበራቸው ፡፡ ህዝቡን አንድ አድርጎ ልማቱን በአስተማማኝ መልኩ ለማስቀጠል ከተፈለገ ዱላውን የያዘው ድርጅት ስለ ደካማ ጎናቸውም መስማት ይኖርበታል ፡፡ መስማትም ብቻ ሳይሆን እውነተኛና ተቋማዊ ለውጥ ለመፍጠርም መዘጋጀት ይገባዋል ፡፡

ዱላውን የሚረከበው መንግስት በመስመሩ ወይም በሃዲዱ ላይ የተለመዱትን አሰራሮች ይዤ እሮጣለሁሁ ከሚል ግራና ቀኛ በማየት አማራጮችን መፈተሸ አለበት ፡፡ የድርጅቱ አጋር የሆኑት ሱዛን ራይስ በቀብር ወቅት በዴሞክራሲ ግንባታ ፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝና በሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴ ዙሪያ መንግስታቸው ሰፊ ስራ መስራት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል ፡፡ ይህን ሃሳብ ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊና መፈታት ያለባቸው ጥያቄዋች በብዙሃኑ ህዝብ አእምሮ ውስጥ እየተመላለሱ መሆኑን መረዳት ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም ፡፡

ኢህአዴግ ዘግይቶም ቢሆን / የ97 ምርጫ ደውል / በልማት ዘርፍ ላይ አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ መምጣቱ ይታወቃል ፡፡ ይህን ውጤትም በተሻለ ደረጃ ማሳደግ ይጠበቅበታል ፡፡ አንድ ምሁር የተናገሩትን መሰረታዊ ንግግር ላስከትል ‹‹ ማንኛውም ሀገር በመጀመሪያ መሰረታዊ የሰው ልጆችን መብት በተጻፈ ህግ መደንገግ ይኖርባታል ፡፡ ህጉና ህገመንግስቱ ደግሞ በየዕለቱ በፖለቲከኞችና በባለስልጣናቱ መጠበቅ ይፈልጋል ›› ምሁሩ እንደሚሉት ለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ዕውቅና በመስጠት ረገድ የሀገራችን ህገ መንግስትም ሆነ ሌሎች ህጎች የተጋነነ ችግር የለባቸውም ፡፡ ችግሩ እነዚህን እንደ ውሃና እንጀራ የሚያሰፈልጉንን መብቶች እንደ ቤት ጌጦች አስቀምጠን ማየታችን ነው ፡፡ የሚያምር ህግ ነው ከማለት ውጪ ከጥቅማቸው እንድንጋራ በተግባር አልተተረጎመም ፤ ሶስቱ ጉልበተኞች / ስራ አስፈጻሚ፣ ህግ አውጪውና  ተርጓሚው / አስፈላጊ በሆነ ግዜ ሁሉ ሺሸራርፏቸው የማስፈጸም ችግር አለ በሚል ይታለፋል ፡፡

ከሲቪል መብቶች ውስጥ የመናገር ፣ የመጻፍ ፣ የመቃወም ፣ ነጻ የፍርድ ቤት አሰራርና የመልካም አስተዳደር አሰራሮችን ለአብነት ብናነሳ ሰፊ ችግሮች የሚታይባቸው ናቸው ፡፡

መረጃ የሚገኝባቸውና ነጻ ሃሰብ የሚተላለፍባቸው ጋዜጦች በተለይም ከ1997 ምርጫ ወዲህ አደጋ ውሰጥ መውደቃቸውን ጥናቶቸ አረጋግጠዋል ፡፡ ጋዜጠኞች በትልቅ በትንሹ ከመከሰስና ከመዋከብ አልፈው ህትመቶች ስርዓት በሌለው መንገድ እንዲዘጉ ይደረጋል ፡፡ ማተሚያ ቤቶች የፈለጉትን ማተም የማይፈልጉትን ቀይ ማሳየት ጀምረዋል ፡፡ መቼም በራሱ የሚተማመን ፣ ለልማትና ፈጠራ የተጋ ፣ በሀገሩ ተግባር የማይሸማቀቅና ነጻነት የሚሰማው ፣ የሰለጠነ አመለካከት ያለው ህብረተሰብ ለመፍጠር ንባብና ከወቅታዊ መረጃ ጋር የተገኛኙ ዜናዋች ሁሉ አስፈላጊ ግብዓቶቹ ናቸው ፡፡ እነዚህን ግብዓቶች ከመንግስታዊ ሚዲያዋችና ጋዜጦች ማግኘት ይቻላል የሚል የውስጥ አቅጣጫ ካለ የታመመ አሰራር በመሆኑ ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል ፡፡ የታመመው ደግሞ ከህገ መንግስቱ መብቶች ጋር በመቃረኑ ነው ፡፡ መቼም ይህ ህገ መንግስት እያለ ‹  ቻይናም ያደገችው ዴሞክራት ሳትሆን በመሆኑ እንቀጥልበታለን ›  ማለት ወደ ለየለት ህመም መድረስን ያሳብቃል ፤ ምክንያቱም የቻይናን የፕሬስ ፈለግ ለመከተል መጀመሪያ ህገ መንግስቱን በወፍራም ቀለም መደለዝ  ስለሚያስፈልግ ፡፡ በመሰረቱ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ሁሉ አጥፊ ተልዕኮ አላቸው ከሚለው ጭፍን አመለካከትም መጽዳት ያስፈልጋል ፡፡ የግል ፕሬሱ የተዛነፉና አድሏዊ አሰራሮችን ነቅሶ በማሳየት ረገድ አይነተኛ ሚና እንዳለውም መቀበል ያስፈልጋል ፡፡ ከዚያ በመለስ የሚታይባቸውን የእውቀትና የአሰራር ችግር ማስተማር ይቻላል ፡፡ ማስተማር ብቻ ሳይሆን መንግስት ንፉግ ሆኖ የቆየበትን መረጃ የመስጠት ግዴታና ኃላፊነት ማሰተከከል ይኖርበታል ፡፡ መንግስትን መተቸት የሚያስፈራና አሳሳሪ መሆን የለበትም ፡፡

ለነገሩ ብዙም አይወራላቸውም እንጂ የመንግስት ጋዜጠኞችም የኤዲቶሪያል ነጻነት የላቸውም ፡፡የሙያው ስነምግባር በሚፈቅደው መልኩ ስራቸውን እንዳይሰሩ ያደረገው የአቅም ችግር ብቻ ሳይሆን የመንግስት የበዛ ጣልቃ ገብነት ነው ፡፡ በዕውቀትና በልምድ የላቁ ጋዜጠኞች የድርጅት አባል እንዲሆኑ ይገደዳሉ ፡፡ ቦታቸውንና የዕለት እንጀራቸውን ላለማጣት ሲሉ ስነ ምግባሩ በማያዘው ጎዳና ውስጥ ገብተው ይዳክራሉ ፡፡ የድርጅት አባል ሆኖ ደግሞ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን እዘግባለሁ ማለት አይቻልም ፡፡ እረ የድርጅት አባል ሆኖ ህዝባዊ ጋዜጠኛ ነኝ ለማለት ሞራል ይተናነቃል ፡፡ 

ከትንሷ ሀገር ኬፕ ቨርድ እንኳ ብዙ መማር ይኖርብናል ፡፡ ይች ሀገር ከ 2006 ጀምሮ እያሳየች በመጣችው የፕሬስ ነጻነት ከአፍሪካዊው ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የዘንድሮው ተሸላሚ ሆናለች ፡፡ እንደሚታወቀው የዓለማችን ሶስት የፕሬስ አፋኝ ሀገሮች ኤርትራ ፣ ሰሜን ኮሪያና ሶርያ ናቸው ፡፡ ቀም ነገሩ እኛስ ? የሚለውን ጥያቄ ጠይቆ በአግባቡ መመለሱ ላይ ነው ፡፡ ፍሪደም ሀውስ ፕሬስ በያዝነው ዓመት የዓለም ሀገራትን ከዲሞክራሲና ከፕሬስ ነጻነት አንጻር በይኗቸው ነበር ፡፡ በዚሁ መሰረት ኢትዮጽያ ከ194 ሀገሮች 176ተኛ ላይ ተቀምጣለች ፡፡ ነጻ ያልሆነች ዞንም ብሏታል ፡፡ ሀገራችን ከአፍሪካ አንጻር እንኳ ደረጃዋ ሲታይ የሚያሳፍር ነው ፡፡ 43ተኛ ናትና ፡፡ ይህች ያልተገዛች ፣ ስለ ነጻነት የምታውቅ ለጎረቤቶቻም ድጋፍ ስትሰጥ የነበረች ሀገር መጨረሻ አፋፍ ላይ መታየት ነበረባት ? 

ባንዲራና መፈክር ያነገቡ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ማየት አልናፈቃችሁም  ? ይህ መሰረታዊ መብት ለምን ኮሰሰ  ?  መቼም የመቃወሚያ ርዕሰ ጉዳይ ጠፍቶ አይደለም ፡፡ በነገራችን ላይ የተቃውሞ ተቃራኒ ወንድም የሆነው ‹ ድጋፍ ወይም ድጋፌ › ግን አልፎ አልፎ ብቅ ከማለት አልተቆጠበም ፡፡ ታዲያ ይህ ድጋፍ መልኩ ወደ ሁለት መቀየሩን ልብ ይሏል ፡፡ መንግስት በደስታ ሲገለፍጥ  አደባባይ ወጥቶ ይጨፍራል ፡፡ መንግስት በሆነ ጉዳይ ሲናደድ አደባባይ ወጥቶ ያስከፋውን ነገር ያወግዝለታል ፡፡ ዞሮ ዞሮ ድጋፍና ተቃውሞ ለዴሞክራሲ ስርዓት ጠቃሚ በመሆናቸው እንደ አቤል እና ቃየን የተለየ ትርጉም አይሰጣቸው ነው ጥያቄው ፡፡

በየመ/ቤቱ በሚካሄድ ስብሰባ ላይ ሰራተኞች ጭብጥ ብለው እንደገቡ ለምን ጭብጥ ብለው ይወጣሉ ? እንዲጠይቁና አስተያየት እንዲሰጡ ሲነገር አንገታቸው ወደ መሬት ያዘቀዝቃል ፡፡ የሚናገሩት ችግር ሳይኖር ቀርቶ ነው ? አንዳንዴ ከሰብሳቢው የተሻለ እውቀት ሳይኖራቸው ቀርቶ ነው ? አይደለም ፡፡ ጠንከር ያለ ሃሳብ ከሰነዘሩ ጀርባቸው ይጠና … የሆነ አመለካከት ተሸካሚ ሳይሆኑ አይቀርም … የእገሌ ደጋፊ ናቸው … የሚለውን ማሰፈራሪያ ወይ በግምገማ ወይ በሌላ አጋጣሚ ስለሚሰሙ እንጂ ፡፡ እናም ቢያውቁም ባያውቁም ይሐው ‹‹ ጎመናን በጤናን ›› በሆዳቸው አሳምረው መዘመር ከያዙ ስንት ዘመን አለፈ ፡፡ እንግዲህ የዴሞክራሲ ስርዓት ከሚፈልገው ግብዓት አንዱ  የሆነው  ‹ ተሳትፎ › ዛሬ ስግግ ያለ ስዕል ያገኘ መስሏል  ፡፡

ፍርድ ቤቶቻችን ፍትሃዊ አሰራርን ማስፈን ግን አልቻሉም  ፡፡ ቀጠሮውና መመላለሱ ወገብ ያነክታል ፡፡  ህገ መንግስቱ የሰጣቸው ነጻ አሰራር ተግባራዊ አልሆነም  ፡፡ አቶ ስዬን የለቀቀው /ቤት በሆነ የፖሊስ ተቋም መንገድ ላይ ሲጠለፍ ተቋሙን ለመክሰስና  የህግ የበላይነትን ለማሳየት አቅም የለውም ፡፡ ፖሊሶች ለበርካታ ግዜያት ስለሰብዓዊ መብት አያያዝ ስልጠና ቢወስዱም ዛሬም አይናችን እያየ  ግለሰቦችን በየአደባባዩ ይወግራሉ  ፡፡እረ በህጉ መሰረት… › ብሎ አስተያየት ለመስጠት የከጀለ ጀርባው ላይ ወፍራም ዱላ ሊያርፍበት ወይም የአይጥ ምስክር ዲንቢጥ ተብሎ  ወደ ጣቢያ ሊጎተት ይችላል ፡፡ ለአንዳንዶቹ  እስረኞችን  አለማክበር ፣ ማንጓጠጥ ፣ መሳደብ የተፈቀደላቸው ይመስላል ፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት እንደሚገልጸው ዜጎች ዛሬም በማያውቁት ሁኔታ ይታሰራሉ፣ ይገረፋሉ ፡፡

ኢህአዴግ ብሄር ብሄረሰቦችን የሚገልጸው ‹ ልዩነታችን ውበታችን ነው › በሚል አሪፍ አገላለጽ ነው ፡፡ ይህ ውበት ለባህልና አኗኗር ብቻ ሳይሆን ለአመለካከትና አስተሳሰብም መዋል ይኖርበታል ፡፡ እሱን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ የሚቃወሙና የሚተቹ  መኖራቸውንም ከልብ መቀበል ያስፈልጋል ፡፡ የዴሞክራሲም ውበት እዚህ ላይ ነው ፡፡ እኔን ብቻ አዳምጡኝ ወይም ተከተሉኝ ካልሆነ ግን መጥፎ ስምና ታርጋ እለጥፍባችኃለሁ ማለት የዴሞክራቶች ፍልስፍና አይደለም ፡፡ በራስ ድምጽና ዘፈን ብቻ ከመደሰት ይልቅ የሌሎችንም ዜማ ማጣጣም ‹ ልዩነት ውበት ነው › የሚባለው ብሂል አካል መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል ፡፡ በአጠቃላይ የዴሞክራሲውን ግንባታ የሚያኮሰምኑ ተግዳሮቶችን አዲሱ መንግስት መቃኝት ይጠበቅበታል ፡፡
ልዩ ልዩ የሲቪክና የሙያ ማህበራት እንዲደራጁና በልማትና በዴሞክራሲ ግንባታው ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲጨወቱ እገዛ ማድረግ ቢቀድምም አምሳያቸውን ፈጥሮ እንዲኮሰምኑ የማድረግ አሰራርን ስንከተል ቆይተናል ፡፡ አዲሱ መንግስት ይህን አካሄድ በድፍረት ተችቶ የተሻለ አቅጣጫ ማሰቀመጥ ይኖርበታል ፡፡


Monday, September 3, 2012

ጥቁርና ነጭ ንግግሮች




የጠ/ሚ/ር መለስ ስርዓተ ቀብር ከመርዘሙና በተፈጥሮ ዝናብ ከመታወኩ በስተቀር የተዋጣለት ነበር ፡፡ በርግጥ ወደ መጨረሻ አካባቢ የጣለው ዝናብ ከሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኢል  ቀብር አንጻር ከታየ ‹ ጥቂት ነው  › የሚባል ዓይነት ነው ፡፡ የያኔው ቀብር ሶስት ሰዓታት ሲፈጅ ኃይለኛ በረዶ አልተለየውም ነበር ፡፡ እንዲያም ሆኖ ትንሽ ትልቁ፣ ሲቪል ሰራዊቱ መንገድ ላይ ወጥቶ አንብቷል ፡፡ የሀገሪቱ ጋዜጣም ኃይለኛውን ዝናብ ‹‹ የገነት ዝናብ ›› ሲል ጠርቶታል፡፡ በሀገራችን ባህል ቀብርን ዝናብ እንዲያውክ ባይፈለግም አንድ እናት  ‹‹ ለመለስ ፈጣሪም አለቀሰለት! ›› በማለት አዛማጅ ትርጉም ሰጥተውታል ፡፡
የመሸኛ ስነስርዓቱ የአቶ መለስን የተሳካ የመሪነት ተግባር በታዋቂ ሰዋች ማስመስከር ላይ ያነጣጠረ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሁሉም ተናጋሪዋች የአቶ መለስን ተክለ ሰውነት በተመቻቸው መንገድ ገልጸውታል ፡፡ ሳቢ ንግግሮችንም አድምጠናል ፡፡አልፎ አልፎ ግን የመስካሪዋቹን ውብ ቋንቋና ከቋንቋው ጀርባ ያለውን ጉዳይ ያለቦታው እያነጻጸርኩ ከጥቁርና ነጭ ምስሎች ጋር ተላትሜያለሁ፡፡
 
ለምሳሌ ዩዎሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ምስክርነታቸውን ሲገልጹ የነበሩት ወረቀት ሳያነቡ ነው ፡፡ ጣፋጭ ንግግራቸው ብቻ ሳይሆን ተክለ ቁመናቸውም ፊልም ከሚሰራ ካው ቦይ ጋር ይመሳሰላል ፡፡ ታዲያ እንዲህ እንዳፈዘዙኝ ስልጣን ወደያዙበት 1986 በሀሳብ አፈናጠሩኝ፡፡ ያኔ ‹‹ ማንኛውም የአፍሪካ መሪ በስልጣን ከ10 ዓመት በላይ መቆየት የለበትም ›› በማለት በይፋ ተናግረው ነበር ፡፡ ዛሬ ረስተውት ይሆን ? ይኀው እሳው በስልጣን ላይ 26 ዓመታቸው ፣ ለነገሩ ይሄ የአፍሪካ መረዎ በሽታ ነው ። 
 
አቶ ኩማ ደመቅሳ ኦማር ሀሰን አህመድ አልበሽርን ‹‹ ፊልድ ማርሻል ›› እያሉ ሲያስተዋውቁ ሰማው ልበል ?  ‹‹ ፊልድ ማርሻል ›› መድረሳቸውን መቼ ሰማሁና ?! እኚህ መሪ ከ2003- 2009 ባሉት ግዜያት ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ሰዋች ማስገደላቸውንና በተመድ ከሚፈልጉ  መሪዋች አንዱ መሆናቸውን ግን አውቃለሁ ፡፡ አፍሪካዊያን መሪዋች ግን ይህን ክስ አልተቀበሉትም ፡፡ ‹  በሰው ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የሚፈተፍቱ ነጮ ›  በኛ ጉዳይ አያገባውም ይላሉ - ከሳሾቹን ፡፡ እርዳታ በሚፈልጉ ግዜ ደግሞ ነጫጭባ የሚቸውን ነጮጭ ወደ መላዕክትነት ይቀይራሉ ፡፡ እናም አልበሽር መኪና ፈርቶ ዳር ዳሩን እንደሚጓዝ ገጠሬ ጥግ ጥጉን ሲጓዙ ዘመናት አስቆጥረዋል  ፡፡ ግን ነጻነትን እንዴት ይሆን የሚተረጉሙት ?
አሜሪካዊቷ አምባሳደር ሱዛን ራይስ ጥቁርና ነጭ ብቻ ሳይሆን ቀይ ቀለምንም ጨምረው የተናገሩ ብልህ ዲፕሎማት ናቸው ፡፡ ልብ በሚነካው ሀዘናዊ ቋንቋ የወ/ሮ አዜብ መስፍንን ልብ ኮርኩረዋል ፡፡ አሜሪካና አቶ መለስ የነበራቸውን ጥብቅ ቁርኝት መግለጻቸው ብቻ ሳይሆን ታላቋ ሀገር ዛሬም ለኢህአዴግ ቀኝ እጅ ሆና እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸው ሁለተኛው ቀለም ነው ፡፡ ኢህአዴጎች ዲፕሎማሲያዊ ግባችንን እንደ ምርጫችን 99 ከመቶ አሳካን ብለው የሚያስቡትም ይህንኑ ይመስለኛል ፡፡
 
እኚህ ብልህ ዲፕሎማት የመጡት የሀዘን ተካፋይ ለመሆንና የሽብርተኞችን ጉሮሮ አንቃ የቆየችውን ምስራቃዊ ሀገር ‹ አይዞሽ › ለማለት ብቻ አይደለም ፡፡ ለሀገሪቱ አባታዊ ቡራኬ ለመስጠትም ጭምር እንጂ ፡፡ ቡራኬው በፓለቲካዊው ጎዳና ላይ ምን እንደሚጓዝና እንዴት እንደሚንቀሳቀስም አቅጣጫ ያስቀምጣል ፡፡ ይህን አቅጣጫ በንግግራቸው መጨረሻ አካባቢ በገደምዳሜ ጠቁመውታል ፡፡ ሀገራችን ዴሞክራሲን፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝና የሲቪክ ማህበራትን እንቅስቃሴ አጠናክራ እንድትቀጥል በመናገር ፡፡
ትንሽ ደቂቃ የቆየው የወ/ሮ አዜብ መስፍን ንግግርም ብዙ ሰዓታት ሊያወያይ የሚችል ፍቺ ያቀፈ ይመስላል ፡፡ ‹‹ የመለስ ፓሊሲና ስትራቴጂ እስካልተበረዙ ድረስ ዓላማው እውን ይሆናል ›› የሚል ሀሳብ ፈንጥቀዋል ፡፡  ‹ ድርጅቱ ያለምንም ለውጥ ያለውን አሰራር ይዞ ይቀጥላል ›  ከሚለው የሃላፊዋቹ አስተሳሰብ ጋር የእሳው ንግግር ለምን ተቃረነ ? ወይም ስጋት ያደረበት መሰለ ብሎ መጠየቅ በርካታ ሚስጢሮን ሊያስገኝ ይላል ።
 
ይበልጥ ትኩረቴን የሳበው ግን በአቶ መለስ ምንነት ላይ የተነገረው ንግግር ነው ፡፡ ‹‹ መለስ ቢል ቦርድ እንዲለጠፍለት ፣ ሃውልት እንዲቆምለት አይፈልግም ! ›› የሚለው ፡፡ ቀደም ብሎም መለስ ስለ ራሱ ማውራትም ሆነ እንዲወራለት አይፈልግም የሚል ሀሳብ ከትግል አጋሮቹ ተንጸባርቋል ፡፡ ታዲያ በእለቱ አቶ መለስ እንዴት ሲገለጹ ነበር ? ለተገላጩ ይሰጡት የነበሩት ቅጽሎች ከላይ የተጠቀሰውን ሀሳብ ያከበሩ አይመስልም ፤ ገደል የከተቱ እንጂ ፡፡ ካድሬዋቹ የማንነት ብቻ ሳይሆን የድርጅት ገጽታ ግንባታ እየሰሩ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም ጥንቃቄን  ‹ ዞር በል ባክህ ! › ያሉት ያስመስላል ፡፡ በዕለቱ ንግግሮች ውስጥ አቶ መለስ በርካታ መለዮና ካፖርት አጥልቀው ነበር :: ብዙዎቹ ግን በልካቸው የተሰፉ አልነበረም ። ተንቦርቅቀው ያስጠላሉ ። አንዳንዶን እንጥቀሳው ።
 
የህዳሴ መሃንዲስ
የለውጥ ጠንሳሽ
የተስፋ አባት
የድሃ አባት
ታላቁና በሳሉ
ገናና መሪ
ተወርዋሪ ኮኮብ
ብልሁና አስተማሪው
የቁርጥ ቀን ታጋይ
ብርቅዬ የአፍሪካ ልጅ
ባለ ራዕይ
የህግ ምሁር
የወታደራዊ ሳይንስ ቁንጮ
ሳይንቲስት
ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ያከበረ መሪ
ሆደ ሰፊ መሪ
ለዓለም አቀፍ ህግ ራሱን ያስገዛ መሪ
አፍሪካዊ መሪ
ህዝባዊ መሪ
የጸረ ደህንነት አርበኛ መሪ
የአፍሪካ ቃል አቀባይ
ህዝባዊ ፍቅር የተላበሰ መሪ
የማይናወጥ የዓላማ ጽናት ያለው መሪ በሚሉ ሀሳቦች ተገልጸዋል ፡፡ በርግጥ አንድ ሰው ይህን ሁሉ ሊሆን አይችልም ፣ ከሆነ ደግሞ የዓለም አስደናቂው መጽሀፍ ላይ መስፈር ነበረበት :: ፖለቲከኞቹ ጊነስ ቡክ ላይ ማስመዝገብ ትተው ሰው ሲሞት ይህን ሁሉ ካፖርት ማሽከም ማዕረግ መሆኑ ነው ?
 
እንደዚህ ዓይነት ምስል መፍጠርም ለማንነታቸው ሌላ ትርጉም የሚያሰጥ ነው የሚሆነው ፡፡ ለምሳሌ ያህል የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኢል  50 የሚደርሱ ልዩ ልዩ መጠሪያዋች ነበሩት ፡፡ ጓድ ሊ /መንበር ፣ የላቀው ሊ/መንበር ፣ የኛ አባት ፣ የተለየው ጄነራል ፣ የሀገሪቱ ጭንቅላት ፣ ጀግናው ፣ የሁሌም ባለድል ፣ የ21ኛው ክ/ዘመን መሪ ኮኮብ ፣ አስገራሚው ፓለቲከኛ የሚሉት ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው ፡፡ ይህ መሪ ግን በተግባር ከነሂትለርና ስታሊን ጋር የሚነጻጸር አምባገነን እንደነበር የፓለቲካ ምሁራን አረጋግጠዋል ፡፡
 
ኢዲያምን ዳዳንም ማስታወስ ይቻላል ፡፡ ይህ መሪ ራሱን የሚጠራው ‹‹ የተከበረው የእድሜ ልክ ፕሬዝዳንት ፣ ፊልድ ማርሻል አልሀጂ ዶክተር ኤዲያሚን ፣ በምድር ላይ የሚገኙ እንስሳትና በባህር ውስጥ የሚገኙ አሳዋች ሁሉ ጌታ ፣ የእንግሊዝን መንግስት በመላው አፍሪካ በተለይም በኡጋንዳ ያሸነፈ ›› በሚል ነበር ፡፡ ታዲያ የአቶ መለስስ ከዚህ በምን ይለያል ? 
 
እናም ጎበዝ ግራና ቀኝ ማየት የሚገባው መስቀለኛ የትራፊክ መንገድ ላይ ሲቆም ብቻ አለመሆኑን ደጋግሞ ማሰብ ያስፈልጋል ፡፡