Tuesday, August 28, 2012

ሞትና ንግድ





ታዋቂ ሰዋች ሲሞቱ የብዙዋች ትኩረት ወደ ሟቾቹ ይሳባል  ፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ በብዙ ምክንያቶች ነው ፡፡ ሰዋቹ በሰሯቸው ታላላቅ ስራዋች ክብርና ሞገስ ስለሚያገኙ እንዲሁም ከብዙዋቹ ታላላቅ ሰዋች ጀርባ አከራካሪና አወዛጋቢ ጉዳዮች በመኖራቸው  ብሎ መጥቅለል ይቻላል ፡፡

አንዳንድ ሰዋች ታዋቂዋቹ በህይወት እያሉ ግልብ በሆነ አድናቆትና ፍቅር ውስጥ ነው የሚያስቧቸው ፡፡ ለአድናቆታቸውና ለፍቅራቸው መሰረት የጣለላቸውን አብይ ጉዳይ ካወቁ በቂ ነው ፡፡ ታዋቂዋቹ በሞት ሲለዩ ግን ከመደናገጥና ከመሸበር ባሻገር የመጸጸትና የጥፋተኝነት ስሜት ያበቅላሉ ፡፡ ስለ ሰውዬው ማንነት የሚገልጹ ስራዋችን ከዛሬ ነገ አያለሁ፣ አነባለሁ፣ ለማወቅ ጥረት አደርጋለሁ እያሉ የቆዩበትን መንገድ ይተቻሉ ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የታዋቂ ሰዋች ህይወት ባለ ሁለት መስተዋት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ህዝቡም ሆነ አድናቂው የሚያውቀው የፊት ለፊት ገጽታቸውን ነው ፡፡ የጀርባ ህይወታቸው ከባህል፣ ፓለቲካ፣ ስነ ልቦናና ማህበራዊ ህይወት አንጻር ያፈነገጠና በግጭቶች ውጤት ያበጠ በመሆኑ በብዙ መልኩ ደብቀውት ይጓዛሉ ፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ አንድም ይህን የተደበቀ ማንነታቸውን በሌላ በኩልም አጉድሎ ያቆየውን ፕሮፋይል ለማወቅ በብርቱ ይፈልጋል ፡፡ ከሞቱ በኃላ የሚያገኛቸው ልዩ ልዩ መረጃዋች ስሎ የቆያቸውን ጀግኖች ይበልጥ ለማክበርና ለመዘከር ይረዳዋል ፡፡ ተቃራኒ በሆነው ስብዕናቸውም ለመደመም፣ ሚዛናዊ ምስክርነቱን ለመስጠት ብቻ ሳይሆን እይታውን በማስፋት ትምህርትና ልምድ ለመውሰድ ይጠቀምበታል ፡፡

ይህ የሰው ልጆች የጋለ ባህሪ ነው ፡፡ እንግዲህ ይህን  ተዝቆ የማያልቅ ፍላጎት በማንበብ ነው ‹ አቅርቦት › ፈጣሪዋች ምናባቸውን የሚያሰሩት ፡፡ ለምሳሌ ያህል የማይክል ጃክሰን ልጆች ምግብ ማዘጋጃ ክፍል ውስጥ ባለ ጥቁር ሰሌዳ ላይ ‹ I Love Daddy › ብለው የጻፉት የተለመደ ስሜትን መግለጫ ሃሳብ  ከሞተ በኃላ በ 5 ሺህ ዶላር ተሸጧል ፡፡ አርቲስቱ ጠዋትና ማታ ፊቱን የሚያይበት የቁም ሳጥን ደግሞ 25 ሺህ 750 ዶላር አውጥቷል ፡፡ የሙዚቃ ስራው  ተለቆ 170 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል ፡፡ 

ስፔናዊውን ስመ ጥር ሰዓሊ ፓብሎ ፒካሶን ብዙዋች ያውቁታል ፡፡ ግንቦት 2010  Nude, Greeen Leaves and Bust የተሰኘው ስራው ለጨረታ ቀርቦ በ105 ሚሊዮን ዶላር ተሸጧል ፡፡ ይህ ስራ በ1951 የተሸጠው በ19 ሺህ 800 ዶላር ብቻ ነበር ፡፡ የዊትኒ ሀውስተን ቀሚስ 20ሺህ 480 ዶላር፣ የኤልቪስ ፕርስሊ የሞተር ሳይክል ጃኬት 41 ሺህ 600 ዶላር አውጥቷል ፡፡ በወቅቱ ብዙም ልብ ያልተባሉ ንግግሮች፣ መሸጥ ያቆሙ ካሴቶች ወይም የፎቶ አልበሞች ተጠርዘው ለህትመት ሲበቁ ሚሊዮኖች ያለ ጥያቄ ይገዟቸዋል ፡፡ አንድም ድሮ የዘለልኩትን መረጃ አገኛለሁ በሚል አንድም ለማፍቀርና ለመዘከር ፡፡

የአገራችን የሙዚቃ ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ ሲሞት ያልደነገጠና ያላዘነ ሰው አልነበረም ፡፡ ጥላሁን እጅግ የሚከበር የመሆኑን ያህል አነጋጋሪ ማንነቶች እየተከተሉት የቆየ አርቲስት ነበር ፡፡ በተለይም በራሱ አንደበት የተገለጸው ‹‹ የሆድ ይፍጀው ! ››ን እውነተኛ ታሪክ ብዙዋች ማወቅ ይፈልጉ ነበር ፡፡ ከደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር፣ ማሞ ውድነህና አፈወርቅ ተክሌ በበለጠ መልኩ በጥላሁን ላይ የንግድ ስራዋች በስፋት ተከናውነዋል ማለት ይቻላል ፡፡ ልዩ ልዩ ፎቶዋቹ  ‹የዝነኛው…የአንደኛው …የንጉሱ .. › በሚል ማስታወቂያ ታጅበው እንደ ጉድ ተሽጠዋል ፡፡ ፎቶውን የያዙ የቁልፍ መያዣዋች፣ የማይጠገቡ ድምጾቹን ያቀፉ ዘፈኖች ፣ ማንነቱን የሚተርኩ የህትመት ውጤቶች ገበያ ላይ ውለው ብዙ አልቆዩም ፡፡ የስብሃት ገ/ እግዚአብሄር የተወሰኑ መጻህፍት ጀትን መወዳደር በቻለ ፍጥነት ታትመው አንባቢው ያለበትን ክፍተት ብቻ ሳይሆን የነጋዴዋችንም ኪስ መሙላት ችለዋል ፡፡

በቅርቡ አቡነ ጻውሎስና ጠ/ሚ/ር መለስ በሞት ተለይተዋል ፡፡ የአቶ መለስ እልፈት አቡኑን በመሸፈኑ ማየት የሚገባንን ንግዳዊ ትርዒት ገድቦብናል የሚል እምነት አለኝ ፡፡ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ እየታየ ያለው ንግዳዊ ስርዓት ግን የሚገርም ሆኗል ፡፡ በከተማችን በሁሉም ማዕዘን ሌላ ነገር ሲሰሩ የነበሩ ወይም ስራ ያልነበራቸው ወጣቶች የመለስን ፎቶ በተለያዩ መጠን በማሳተም ከሁለት እሰከ አስር ብር ይሸጣሉ ፡፡ በተለይም የቀብር ስነ ስርዓቱ እንደ ሀገራችን ፍርድ ቤቶች ረጅም ቀጠሮ የተያዘለት መሆኑን መሰረት በማድረግ አቀራረባቸውን አሳድገዋል ፡፡ የመጀመሪያዋቹ ቀናት ሲሸጡ የነበሩ ፎቶዋች ልሙጦች ነበሩ ፡፡ በሂደት ግን ፎቶዋቹ ላይ ሳቢ ጥቅሶች እንዲጨመሩበት አድርገዋል ፡፡ በአንድ ወረቀት ላይ ሁለትና ሶስት ፎቶዋችን በማካተትም የገዢውን ትኩረት ለመሳብ ጥረዋል ፤ አነጋገራቸውስ ብትሉ !! በፊት ‹ የጀግናው መሪ ማስታወሻ አያምልጣቸሁ ! › የሚል ነበር ፡፡ አሁን ደግሞ ‹ ሞቶም ስራ የፈጠረውን መለስ ዜናዊን በእጅዋ ያስገቡ ! › ወደሚለው ማዕረግ ተሸጋግሯል  ፡፡

እንደ ፎቶው አይብዙ እንጂ ሰው የበዛበት ቦታ ላይ ጥቅስ እያነበቡ በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰዋች እንዳሉ ይታወቃል ፡፡ የነዚህ ሰዋች ስነ ልቦና የማንበብ ትጋት በጣም የሚያስገርም ነው  ፡፡ ድሃ የበዛበት አካባቢ

‹‹ ድሃና አክተር ይንገላታል እንጂ አይሞትም ! ››

‹‹ ምንም ድሃ ቢሆን ባይኖረው ሀብት
ከደጃፍ ሲቀመጥ ደስ ይላል አባት ›› የሚሉ ዓይነት ጥቅሶችን ለገበያ ያቀርባሉ ፡፡ መርካቶ መንገድ ላይ የሚነግዱ እናቶች ጋ ጠጋ ብለው ደግሞ     

‹‹ እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ
   ቅማል ታገኛለች በጨለማ ዳብሳ ›› ካሉ መሃረብና መቀነቶች የግድ መላላታቸው አይቀርም ፡፡
ቤተክርስትያን አካባቢ ‹ እግዚአብሄርን ፈልጉት ትጸናላችሁም !! › የሚል ዓይነት ጥቅሶችን ከነመገኛ ቁጥራቸው ሲያንበለብሉ መልስና ብርታት የሚሹ ልቦች በፈገግታ ይቀበሏቸዋል ፡፡  ዐስርቱ ትዕዛዛትን ከሚያምር ስዕል ጋር አስደግፈው ያቀርባሉ ፡፡ በሰሙነ ህመማት ግዜ ከሰኞ እስከ እሁድ ያሉ ቀናቶች ያላቸውን ሚና በመጻፍ ጮክ ብለው ያስተዋውቃሉ ፡፡ ታዲያ ለዚህ መሰሉ አስታዋሽ ጥቅስን መግዛት አይደለም ‹ ይባርክህ ! › የተሰኘውን ብሩክ ምርቃት መጨመርስ ምን ይጎዳል ? ምንም ነው መልሱ ፤ ሰዋቹ ድንገት እንኳን አፈንግጠው

‹‹ በማያልቀው እቃ እየተነገደ
  ሴቱ በማርቼዲስ ወንዱ በእግሩ ሄደ ››  ቢሉ አንዴ በበጎ ያወጡትን ‹ ይባርክህ - ይድፋህ ! › በሚለው ለመለወጥ አቅም አይኖሮትም ፣ ባይሆን በስሱ ፈገግ ይላሉ እንጂ ፡፡ የነሱም ዓላማ ሳቅና ትኩረትን በጅምላ ማጋባት ነው - ቻይናዋች ፈገግ የማይል ሱቅ አይክፈት እንደሚሉት ፡፡ ጥቅሰኞቹ በትዕዛዝም ሊሰሩ ይችላሉ ፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ሃይገር ባስ ላይ ያየነው ‹‹ ጎበዝ የአባይ ቃል ስላለብን ጠጋ ጠጋ በሉ ! ›› የሚለው ልመናዊ ትዕዛዝ ነው ፡፡ የሰሞኑ ወቅታዊ ጥቅሳቸው ደግሞ መልኩ ተቀይሮ

‹‹ አባይ ይገደባል ፤ መለስ ይታወሳል ! ››
‹‹ የሞተው ታጋይ እንጂ ትግል አይደለም ! ››
‹‹ ቆራጡ መሪ እናከብርሃለን ! ›› የሚሉና የመሳሰሉ ሆነዋል ፡፡ ጥቅሱ ብቻ ሳይሆን አነባበባቸው ረጋ ያለና ሀዘንን አቀጣጣይ በመሆኑ ደንበኞች አላጡም ፡፡

የጠ/ሚ/ር መለስን ሞት ምክንያት በማድረግ የልብስ ነጋዴዋችም የአቅጣጫና የቀለም ለውጥ ያደረጉ ይመስላሉ ፡፡ ጥቁር ልብስ ለክፉ ቀን እንደሚፈለግ ቢታወቅም  ጥቁር መዘዝን ሊጠራ ይችላል በሚል ልማዳዊ መመሪያ ድንበር ከልለው እንደሁኔታው ብቻ የሚወዳጁት ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ ዛሬ ግን ገለልተኛ ፖሊሲያቸው እንደተጠበቀ መሆኑን በማሳየት የአሰቸኳይ ግዜ አዋጁን ዕውን ለማድረግ ተነስተዋል ፡፡ ጥቁር ሻሽ፣ ቢትልስ፣ ነጠላ፣ ሸሚዝ፣ ኮፍያ፣ ቀሚስ፣ ሱሪ ወዘተ ተፈላጊነታቸው በመጨመሩ ደፋ ቀናውን በእጥፍ አሳድገዋል  ፡፡ ፎቶ ቤቶች ቢታዘዙም ባይታዘዙም በትልቁ አጥበው መስቀል ከያዙ ቀናት አስቆጥረዋል ፡፡ በአነስተኛና ጥቃቅን በህትመት ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ቲሸርት ፣ ኮፍያ፣ የደረት ባጅ ፣ ፓስተር ወዘተ በብዛት እያመረቱ ይገኛሉ ፡፡

በየግዜው ዋጋ በመጨመር የሚታወቁት ስጋቤቶች ራሳቸውን ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር ለማዛመድ እያሶመሰሙ ይመስላል ፡፡ የት አካባቢ እንደሆነ ባይታወቅም አንድ ስጋ ቤት መጠሪያውን ‹‹ ጀግናው አይሞትም ስጋ ቤት ›› ብሎታል ፡፡ ከስያሜው አጠገብም        ‹‹ ለሀዘን የሚሆን ጥሬና ጥብስ አለ ›› በማለት ያስረዳል ፡፡  ነገና ከነገወዲያም የኢህአዴግን ስትራቴጂዋችንና የትኩረት አቅጣጫዋች እየመዘዙ ለንግድ ስራቸው ስያሜ የሚሰጡ ሰዋች እንደሚኖሩ መገመት ትክክል ነው ፡፡ ጥያቄው ግን ስያሜዋቹ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምን ያህል በአግባቡ ተቀናጅቷል የሚለው ነው ፡፡

አንድ ለአምስት የተባለውን አደረጃጀት አንስቶ ‹‹ አንድ ለአምስት ዳቦ ቤት ›› ብሎ መጥራት አሻሚነትን በአዋጅ እንደማስነገር ይቆጠራል ፡፡ የኔ አንድ ዳቦ የአምስት ሰዋችን ጉሮሮ ያረካል ለማለት ከሆነ ጠዋት ጠዋት ከውሃ ጋር የምንውጠውን ኪኒን ዳቦ እያስታወስን በአላጋጭ ፈገግታ ልንደምቅ ነው ፡፡ በርግጥ በተቃራኒው ማሰብ የሚቻል ከሆነ አምስቱ ዳቦ ለአንድ ሰው ረሃቡን ተንፈስ ሊያደርግለት ይችላል ፡፡ በየቀኑ ይህን እንዳናደርግ ግን የተቀደደው ኪሳችን እስካሁን አልተሰፋልንም ፡፡

አንድ ሌላ ነጋዴ ንግድ ቤቴ ጨዋታ በጣም የሚዳመቅበት ስለሆነ ከዛሬ ጀምሮ ‹‹ ሂስና ግለሂስ ጠጅ ቤት ›› ብየዋለሁ ሊል ይችላል ፡፡ አንባቢው ሲተረጉመው ደግሞ ‹ ይህ ሂስና ግለሂስ በጠጅ የደነበዡ ሰዋች የሚንጫጩበት መድረክ ነው ለካ ? › በማለት ቢያፍታታው ትርጉሙ አውዱን ስቷል ብሎ ለመከራከር አያስችልም ፡፡ እንዲህና እንዲህ የመሳሰሉ ነገሮች ተጠባቂ ይመስላሉ ፡፡ ነጋዴዋች በሃሳብ    ‹ በቅርብ ቀን  › የሚል ማስታወቂያ እያዘጋጁ ይመስለኛል ፡፡ ምን ሊሉ  ? ከተባለ

‹ ውሃ ማቆር ግሮሰሪ ›
‹ ድሃ ተኮር ጋዜጣ ›
‹ ቢፒአር ሁለገብ መናፈሻ ›
‹ ትራንስፎርሜሽን ጫማ ቤት › የመሳሰሉትን ፡፡

ጋዜጦችና መጽሄቶች መረጃ ከማድረስ አንጻር ወቅታዊ ሁኔታን መዘገብ ኃላፊነትና ግዴታቸው መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ሆኖም የፓለቲካውና የሃይማኖቱ  መሪዋች ማለፍ አቅጣጫዋችንና ገቢያቸውን አለወጠውም  ብሎ መናገር ያስቸግራል ፡፡ አዳዲስ ጉዳዮችን ለመጠቆም የሚጥረውን መረጃ ከላይ በመግቢያዬ እንደገለጽኩት ህብረተሰቡ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይፈልገዋል ፡፡ ይህም የህትመቶቹ ኮፒ እንዲያድግ አይነተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ፡፡ በሌላ በኩል ድርጅቶችና ግለሰቦች ከወትሮው በተለየ ምልከታ የሀዘን መግለጫቸው ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ ይፈልጋሉ ፡፡ ይህም ለጋዜጦች ያልታሰበ በረከት ነው ፡፡ እነሆ በግማሽ ዓመት ስራቸውን ሲገመግሙ ‹‹ ከዕቅድ በላይ አትርፈናል ! ›› የሚል የደስ ደስ ያለው ንግግር ይጠቀማሉ ፡፡

የባንዲራ፣ የአበባ፣ የጧፍና ሻማ ገበያም በቀላሉ የሚታይ አይደለም ፡፡ ወቅታዊውን ሞት አዘል ንግድ መዘርዘር ስለሰለቸኝ ወደፊት የሚጠበቁትን አንዳንድ ሁኔታዋች ላመላክት ፡፡ ድርጅቶች ለአዲሱ ዓመት አጀንዳ፣ ፓስት ካርድ፣ የቀን መቁጠሪያ ወዘተ ያሳትማሉ ፡፡ መረጃውን አስቀድመው ወደ ማተሚያ ቤት የላኩ ካሉ መከለሳቸው አይቀሬ ነው ፡፡ መንገድ ላይ ያሉት የፈጀው ግዜ ፈጀቶም ቢሆን ስለ መሪዋቹ ብዙ እንደሚዘክሩ ይጠበቃል ፡፡ ደብተር አሳትመው የሚያከፋፍሉ ድርጅቶች ከከባድ ይቅርታ ጋር በእቅድ የያዟቸውን ታዋቂ ስፖርተኞችና ምርጥ እጆች የተጨነቁባቸውን ስዕሎች ላልተወሰኑ ግዜ ያስተላልፋሉ ፡፡ እነሆ በግማሽ ዓመት ስራቸውን ሲገመግሙ ‹‹ ማቀድ ብቻ ሳይሆን ደራሽ ስራዋችም ያበለጽጋሉ ! ›› የሚል አባባል ያንጸባርቃሉ ፡፡

 ፊልም፣ ቲያትር፣ የቴሌቪዥን ድራማ፣ ሙዚቃ፣ የሙዚቃ ኮንሰርት መነሻውና መድረሻው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጠ/ሚ/ር መለስ ተጽዕኖ እንደሚያርፍበት ይገመታል ፡፡ በእንቁጣጣሽ ክብረ በዓል ስፖርተኛ፣ አክተርና መላዕክትን ማዕከል አድርገው ሲጓዙ የቆዩ ወጣቶች በአቡነ ጻውሎስና በአቶ መለስ ህይወት ዙሪያ ያነጣጠሩ ስዕሎች ላይ ቢያተኩሩ ምንም አይገርምም ፡፡

እንደሚታወቀው ሙዚቃ ቤቶች ከበሮው ወፈር ያለ ሙዚቃ ማሰማት አቁመዋል ፡፡ በምትኩ በድምጽ መሳሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ሙዚቃዋች እየተሰሙ ናቸው ፡፡ ለዚህ የጥበብ ስራ በርካታ ሰዋች ያን ያህል በቂ ትኩረት ይሰጣሉ ማለት ያስቸግራል ፡፡ እኔ ሳነብም ሆነ ስጽፍ በአብዛኛው የምጠቀመው በክላሲካል በመሆኑ ሊሆን ይችላል  ይህ የጥበብ ስራ ሳይታሰብ በከተማው ገኖ መውጣቱ አስደስቶኛል ፡፡ ይህ ስልት ለዘመናት አላፈናፍን ያሉትን የነሮክ፣ ሬጌ፣ ራፕ፣ ጃዝ ወዘተ የጭቆና ቀንበር የሰበረ ሁሉ መስሎኛል ፡፡ ድሮንስ አንድ ዓይነት ነገር ሲበዛ ይጎመዝዝ የለ ! ጥበቡ ልክ እንደ ቋንቋ በራሱ ሙሉ በኩልሄ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለጥሞና ፣ ለፍቅርና ራስን ለመመርመር ምን ያህል ፍቱን መድሃኒት መሆኑን እያሳየ ነው ፡፡

 ክላሲካል ህይወት ከጫጫታና ግርግር ወጪ ያላትን የማይፋጅና የማይበርድ ገጽታን በሚያስደምም መልኩ የሚያንጸባርቅ ጥበብ ነው ፡፡ የሙዚቃ የዓለም ቋንቋነት ይበልጥ ደምቆ የሚታየው በክላሲካል ነው ማለት ይቻላል ፡፡ እስኪ ለአብነት የቻይና፣ የጃፓን ፣ የሱዳንና የግብጽን ክላሲካሎች ያዳምጡ ፡፡ የሰሟቸውን ሀገሮች ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅን ረቂቅ ማንነት እንደ ቴሌቪዥን ይመለከታሉ፣ እንደ ሬዲዮ ያዳምጣሉ፣ እንደ መጸሀፍ ያነቡታል ፡፡ ፓለቲከኞች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራን የሚሰብኳቸውንና የሚመኟቸውን ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነት በረቂቅ ድምጾቹ ውስጥ ገዝፈው ያገኟቸዋል ፡፡

ነፍስ ይማር !!

Thursday, August 23, 2012

‹‹ አለሁ !! ›› ማለት






የሰው ህያውነት ተቋርኗዊ ግብሩ
ምንድነው ተብሎ ቢጠየቅ ተዓምሩ
መዛኝ... ምጡቅ ... ማህበራዊ
ጨቋኝ ... አጥፊ ... አድሏዊ
በሚል ይበየናል በቁም ሰውነቱ
በዛሬ ምህዋር ነገን በማስላቱ ፡፡
ግና የነገን ጆንያ የውስጡን ቋጠሮ
ማን ያውቃል ? ጭነቱን ድርጊቱን መንዝሮ ፡፡
ፊት ያለችው ጸሃይ የተምሳሌቷ ግርማ
ወበቅ ትደብቅ መብረቅ ፤ ብርሃን ትቀፍ ጨለማ
ማን ያውቃል ? የውሎዋን መዘርዝር
የርግማንዋንና ምርቃቷን ሚስጢር ፡፡
ልምድ ሆኖ ብቻ ‹‹ ፍጡሩ ›› አርበኛ
ነገን ይማርካል ‹‹ ፈጣሪ ›› ሆኖ ዳኛ
አለሁ ይላል ‹‹ ያደገው ›› እንስሳ
እንደዛሬው ሁሉ ነገንም ሳይረሳ
ግና ‹‹ አለሁ ! ›› ማለት
ታላቅ ዘበት ! የዘመኑ እብደት !!!

Monday, August 20, 2012

አፓርታይድ በጓሮ በር መጣ




ከዓለማችን ፈጣጣ ህግ አንዱ አፓርታይድ ነበር ፡፡ የዘር ልዩነትን የሚያራምድ ፓሊሲ በመደንገጉ ፡፡ በህጉ መሰረት ደቡብ አፍሪካዊያን ነጭ፣ ባንቱ፣ ጥቁር አፍሪካና ኤሽያ/ ህንዶች ተብሎ በተከፈለው መሰረት ብቻ ይማራሉ…ይሰራሉ.. ይኖራሉ…

ይህ ጨቋኝ ህግ ማንዴላንና ጓደኞቻቸውን ለ ‹ እረ ጥራኝ ደኑ ! › አነሳሳ፡፡ ክፉው ዘመን ከ 1948 እስከ 1994 አካባቢ ሲቆይ 21 ሺህ ዜጎችን ጨፍጭፏል ፡፡ ሁሉም የጥቁር ት/ቤቶች እንግሊዝኛንና የአፍሪካን ቋንቋ በእኩል መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለው ተቃውሞ ለማሰማት ከወጡ 20ሺህ ተማሪዋች መካከል 700 ያህሉ የጥይት ራት ሆነዋል ፡፡ በሶዌቶ ህጻናት በጥይት ሲፈነገሉ የተመለከተ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ የደም እንባ አፍስሷል ፡፡ ነጭ የደቡብ አፍሪካ ፓሊሶች ወጣቶችን በመርዘኛ ውሾች እያስነከሱ ሲዝናኑም ዓለም አልቅሷል ፡፡

የጸረ አፓርታይድን እንቅስቃሴ የሚመሩት ማንዴላና ጓደኞቻቸውም ለረጅም ዓመታት በሮበን ደሴት በእስር ማቀዋል ፡፡ በህዝቡ  ከፍተኛ መስዋዕትነትና በውጩም ዓለም ግፊት ክሌርክ በፓርቲው ላይ የጣሉትን ዕገዳ ጨምሮ ማንዴላን ለመፍታት ተገደዱ ፡፡ አዲሱ ህገ መንግስትም በፊርማ ጸደቀ ፡፡ በኃላም ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ስልጣኑ ለተገቢው ህዝብ ደረሰ ፡፡

ዓለምና ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን በቀል ቢፈሩም ማንዴላ ‹‹ ይልቅ ይቅር ተባብለን ብሄራዊ እርቅን እናንግስ  ›› አሉ ፡፡ ያልተጠበቀና የማይታመን የጀግንነት ውሳኔ ነበር ፡፡ በዚሁ መልኩ አፓርታይድ በርህራሄ ተሸንፎ ራሱን ገደለ ፡፡ በጣም ተጸጽቶም ‹ ጉድጓዴን በጣም አርቃችሁ ቆፍሩ ! › ብሎ በተወው የኑዛዜ ወረቀት መሰረት ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል ፡፡

ሰሞኑን የሞተው አፓርታይድ ተነስቶ ይሁን ወይም እሱ ሲሞት አስረግዞት የነበረው ክፋት በውል ባይታወቅም ሀገሪቱ አስደንጋጭ ጭፍጨፋ አስተናግዳለች ፡፡ በማሪካና በሎንሚን ፕላቲኒየም ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ዘወትር ጥልቅ ግድጓድ ውስጥ ከፍተኛ ስራ ብንሰራም የምናገኘው አነስተኛ በመሆኑ ደመወዝ ይጨመርልን የሚል ጥያቄ ያነሳሉ ፡፡ የሰራተኞቹ ደመወዝ ከ 4 እስከ 5 ሺህ ራንድ የሚደርስ ሲሆን ለጉልበታቸው የሚመጣጠነው ዋጋ 12 ሺህ 500 ራንድ መሆኑን ገልጸው ነበር ፡፡

ታዲያ ምን ዋጋ አለው  ? ፓሊሶቹ ቀጥታ ወደ ሰራተኞቹ በመተኮስ የ 34 ሰዋችን ህይወት አጠፉ ፡፡ 78 ቱ ሲቆስሉ 259 ያህሉ እስር ቤት ተወረወሩ ፡፡ አማረብኝ ብለው ደግሞ ‹‹ የተኮስነው ራሳችንን ለመከላከል ነው ›› የሚል ምላሽ ሰጡ ፡፡ መከላከል እንዲህ ነው እንዴ ? ሲባሉ ‹‹ መጀመሪያ ውሃ፣ አስለቃሽ ጋዝና የመሳሰሉትን ተጠቅመን ነበር ›› ብለው እርፍ፡፡ እንደው መቼ ይሆን አፍሪካ ከእንደዚህ ዓይነቶቹ ማፈሪያ ፓሊሶች ተግባር የምትጸዳው  ? የአፍሪካ ፖሊሶች ዘወትር ስልጠና ወሰደን ይላሉ - ግን መቼ ይሆን ስልጠናው ህዝብን የማክበር ምዕራፍ ላይ የሚያደርሳቸው  ? የሰው ልጅ በተለመደው አልሰር፣ ስኳር ወይም ሌላ በሽታ ይጠቃል እንጂ እንዴት የማመዛዘን ክፍተት ሰለባ ይሆናል ፡፡ ለሀገር ክብር ሲፋለሙ ስለወደቁ የዓለማችን ጀግኖች ከመስማትና ከማንበብ ይልቅ እንዴት Made in ራሳችን በሚሉት የዱላና ጥይት ተረቶች ይበልጥ ይነቃቃሉ ?

በእውነት ተስፋ ያስቆርጣል ፡፡ አንዳንድ ሰልፈኞች ዱላ፣ ቆንጨራና ጦር ይዘው ቢታዩም እነዚህን የሚመክተውና  ጸጥ የሚያደርገው ጥይት ነው ብሎ ተመጣጣኝ ትርጉም መስጠት በእውነት ያሳፍራል ፡፡ ለነገሩ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ ፖሊሶች
አትኩሮ ላያቸው - ወፍራም ስድብ
ሰው አገኘው ብሎ ለሚያስረዳው - ወፍራም ኩርኩም
የመንግስት ያለህ ብሎ ለሚጮኀው - ጥይት የሚያቅሙ ናቸው ፡፡

አሷፊ ፓርላማ፣ አጣሪ ኮሚቴ ወይም የእንባ ጠባቂ ድርጅት ድንገት ከጠየቃቸው ‹ በህጉ መሰረት ነው የሰራነው › ይላሉ ፡፡ ይህ መልስ እንግዲህ ሳያስፈቅድ የጮኀ ሌላ ትርጉም እስካልተሰጠው ድረስ ሞቱን በራሱ ግዜ የጠራ ፍጡር ነው ወደሚለው የቃላት መፍቻቸው የሚያደርሰን ይሆናል ፡፡ ይህን ዝነኛ ወታደራዊ መፍቻ መጨረሻውን አያለው ብላችሁ ከተጓዛችሁ ፖሊሶች ልክ እንደ ማዕረግ ሁሉ በአስተሳሰብም እንደሚከፋፈሉ ትረዳላችሁ ፡፡ በመሆኑም ይላል ቃላት መፍቻው  ‹ አንዳንድ ፖሊሶች ማለት ከጥይት የተሰሩ ጥቁር ድንጋዮች ናቸው ›  ፡፡ ይህ ነጻ ትርጉምማ መጨረሻው ሊሆን አይችልም በሚል ሌላ ‹ እንዴትን ? › ያነሳ ደግሞ በመጽሀፉ ማገባደጃ  ገጽ ላይ  ‹ ህልምና ቋንቋ እንደፈቺው ነው የሚባለው አባባል የዋዛ አይደለም ›  ከሚል ማጣቀሻ ጋር ይላተማል ፡፡

እና ተስፋ መቁረጥ ብቻ ሳይሆን አሳምረው መፍራት ይጀምራሉ ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች እየጮኀ እንጀራ የጠየቀውን ድሃ ሰራተኛ በላስቲክ ጥይት ቀጥ ማድረግ ይሳናቸው ነበር ?  ወደ ሰማይ መተኮስ ነው የሚቀድመው ወደ ሰው ?  ጥይቱን ወደ ሰማይ በመተኮስ ብቻ መበተን እንደሚቻል አያውቁም ወይስ አልፈለጉም ?

የደቡብ አፍሪካው የሩምታ ጭፍጨፋ የሀገራችንን አነጣጥሮ ገዳዮች አስታወሰኝ ፡፡ ምርጫ 97ትን ተከትሎ በኢትዮጽያ 193 ሰዋች በጥይት ሲሞቱ 763 ያህል ቆስለው ነበር ፡፡ በወቅቱ ጉዳዩን እንዲያጣራ የተሾመውና በአቶ ፍሬህይወት ሳሙኤል የሚመራው ቡድን   ‹ መንግስት ያልተመጣጠነ ርምጃ ወስዷል ! › በማለት ሪፖርቱን አቀረበ ፡፡ ቀደም ብሎም ሪፖርቱን እንዲያለሳልሱ በመንግስት ቢነገራቸውም ሰብዓዊና ፍትሃዊነት የሚሰማቸው ሰዋች ያባ ቢላዋ ልጅ ነን አሉ ፡፡ በርግጥ በሪፖርቱ አንስማማም ብለው ሸርተት ያሉ አባላትም ነበሩ ፡፡ ዞሮ ዞሮ ሪፖርቱ ‹ ተቃውሞ የሚበተንበት ቀላል አማራጭ የለም እንዴ ?  የፖሊስ አመለካከትስ ለምንድነው የማይቀየረው ? › የሚል አሽሟጣጭ አስተያት አቅርቦ ነበር ፡፡

የኛን ሪፖርት ለደቡብ አፍሪካዊያን አስቀድመን በግልባጭ ብናሳውቅ ኖሮ ምን ያህል በጠቀማቸው ፡፡ ለነገሩ አርቃችሁ ቅበሩኝ ያለ ስርዓት እንደ እባብ አፈር ልሶ ይነሳል ብሎ የገመተ ማን አለ ? በጅምላው የእኛን ጨምሮ የአፍሪካ ፖሊሶች የአመለካከት ችግር ካልተቀየረ ነገና ከነገ ወዲያም የሌሶቶውን ጭፍጨፋ ሃትሪክ ለማድረስ የሚሯሯጡ ጭፍኖች ይፈጠራሉ  ለማለት ያስደፍራል ፡፡ ጭንቅላታቸው ውስጥ የተጠራቀመውን  አለቃ ! ታዘዝ ! ጥይት ! ተኩስ ! ግደል ! አቁስል ! ወዘተ የተሰኙ መራራና የታሸጉ ቃላቶችን ገላልጠው መፈተሸ ይኖርባቸዋል ፡፡ ህዝብ ! ሰብዓዊ ክብር ! ርህራሄ ! ወገን ! ድሃ ! ለምን ! የሚሉ ሃሳቦችን ከመራራዋቹ ጋር ማዋሃድ ባይችሉ እንኳን እንደ ኮዳ ወይም ጥይት ማስቀመጫቸው ከቻሉ ጭንቅላታቸው ውስጥ ካልቻሉ ወገባቸው ላይ አንጠልጥለው መዞር ይጠበቅባቸዋል ፡፡ ‹ በለው ! ግደል ! › የሚል አረመኔ አለቃ ቢያጋጥም እንኳ ሀሳቦቹ ‹ ለምን ! ወገንህን ! › ብሎ ያስታውሳቸዋልና ፡፡

ለማንዴላና ለእውነተኛ ታጋዮቹ በንጹሀን ላይ የደረሰው ፍጅት ሰቆቃ ይፈጥራል ፡፡ እርጅና ተጫጭኗቸው በገጠር ሰፈራቸው የሚኖሩት ማንዴላ ስልጣናቸውን ሲያስረክቡ የመጨረሻ ንግግራቸውን በም/ቤቱ ውስጥ እንደሚከተለው ተናግረው ነበር ‹‹ የህገ መንግስታችን የመርሁ ምንጭ የሰው ልጆች ክብር ላይ የተመሰረተ ነው ፡፡ የሰው ልጅ ክብር መልካምነት ላይ መስማማት ይኖርብናል ፡፡ ታሪካዊ ባላንጣችን ከነበረው አፓርታይድ ወደ ዴሞክራሲ ያደረግነውን ሰላማዊ ሽግግር የተቀበልነው ለሰው ልጆች ካለን መልካምነትና ይህንኑ ማግኘት ከሚገባው ተገቢነት አኳያ ነው ፡፡ ዴሞክራሲያችን ለሁሉም በጎ ፍሬ ማምጣት ይኖርበታል ፡፡ በተለይም ለድሆችና ትኩረት አጥተው ለቆዩት ››

ይህ አደራ ለዚያውም ሰላማዊ በተባለው ዘመን በአይጠ መጎጦች ተበልቷል ፡፡ የፍቅር፣ ርህራሄና ነጻነት ካባ የደረቡት ማንዴላ በድርጊቱ ምን ያህል እንደሚጎዱ ማሰብ ከባድ አይሆንም ፡፡ Long Walk to Freedom በተባለው መጽሀፋቸው ‹‹ ረጅም ጎዳና የተጓዝኩት ነጻነትን ለማግኘት ነው ፡፡ ብዙ ተጨባጭ ውጤቶችን አግኝተናል ፤ አሁን ያረፍኩት ለግዜው ነው ፡፡ ረጅም ጉዞዬ ግን ገና አልተጠናቀቀም ›› ብለው ነበር ፡፡
 

የሚገርም ትንቢት ተናግረዋል ፡፡ በፍቅር፣ በፍትህና በአድልዋ ላይ የሚደረገው ጉዞ ገና የተጠናቀቀ አይመስልም ፡፡ አዝኛለሁ በማለት ምርመራ እንዲደረግ ያዘዙት ጃኮብ ዙማ አዲስ ትንሳኤ ያስገኛሉ ወይስ አፈሩን አርግፎ ራቁትን በከተማው ዳር ለቆመው አፓርታይድ ጂንስና ካፖርት ያቀብላሉ ?

Friday, August 10, 2012

‎የጀግና መንገድ‎



ኒክ ከባለቤቱ ጋር


--- እጅም እግርም የለውም ፤ ግን የዓለማችን ደስተኛ ሰው ነው ፡፡
--- እጅና እግር አለን ፤ ግን የዓለማችን ሀዘንተኛ ህዝቦች ነን ፡፡
--- < life is greater purpose > በሚል ርዕስ መጽሀፍ አሳትሟል ፡፡
--- < life is knife ! > የሚል ሰፊ ሀሳብ ውስጣችን ቢከማችም ‹ ሆድ ይፍጀው ›  ብለን ለህትመት አላበቃነውም ፡፡

ተቃርኗችን ቢዘረዘር ሰፊ ነው ፡፡ በርግጥ እሱ በአንድ ወቅት እጅግ ተከፍቶና ተስፋ ቆርጦ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል ፡፡ ጥያቄውና ጸሎቱ አንድ ነበር ፡፡ ‹ እጅና እግር ስጠኝ › የሚል ፡፡ ሰሚ ባለማግኝቱ በጣም ተከፋ ፡፡ እናም በዚህ የሚደርስበትን ሙከራ መቋቋምና መታገስ ባለመቻሉ ድርጊቱን ፈጸመ ፡፡

ለኛ ተስፋ መቁረጥና መከፋት ብርቅ አይደለም ፡፡ አንዱ ጥያቄ ሳያድግ በላዩ ላይ ሌላ ጥያቄ ስለሚረገዝ የጥያቄዋቻችን ብዛት እንደ ህዝብ ብዛታችን አስጊ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው ፡፡ ጥያቄዋቻችን ብዙ ህጻናት እንደሚያሳድጉ ቤተሰቦች አእምሯችን ውስጥ ያለ ስርዓት ይንጫጫሉ ፡፡ አእምሯችን ሰላም፣ ፍቅር፣ ፍትህ፣ ነጻነት፣ እንጀራ ወዘተ እያለ ዘወትር ይጠይቃል ፡፡ ከጥያቄዋቻችን መላመድ የተነሳ ነው መሰለኝ ጥያቄዋቹን እንደ ቤት ቁጥር ወይም ታርጋ ከማንነታችን ጋር ለጥፈናቸዋል ፡፡ እንጀራ የሚል ስም አልሰማሁም እንጂ ሰላም ፣ ፍቅር፣ ፍትህና ነጻነት የተባሉ ሰዋች በሺዋች የሚቆጠሩ ናቸው ፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ ? በተጨባጭ ያጣናቸውን ጉዳዮች በምኞት ወይም በመምሰል ለማካካስ ይሆን ? ላይሆንም ይችላል ፡፡

ለማንኛውም ስማቸውን ሳይሆን ከጀርባ ያለውን ማንነት ጠይቀው ምላሽ ያላገኙ ሰዋች መከፋታቸው ይጠበቃል ፡፡ መታገስ ያልቻሉት ውድ ህይወታቸውን በበረኪና፣ በገመድ፣ በጥይትና በመሳሰሉት ለማጥፋት ፈትነውታል ፡፡ ብዙዋች የጥያቄዋቻቸውን ግልባጭ ጆሮ ላለው ለማድረስ ከኬንያ እስከ አሜሪካ ድረስ ተበትነዋል ፡፡ በርግጥ በስደት ህይወት በቂ ምላሽ ያገኙ የታደሉና የተቀደሱ መሆን አለባቸው ፡፡ እስራኤላዊያን ግብጽ ውስጥ ለአያሌ አመታት ኖረው በተፈቀደው ግዜ መመለሳቸውን ያስታውሷልና ፡፡ ጥያቄውን ለሚመለከተው ሁሉ ያላለው የኔ ቤጤ ደግሞ ይሐው በርካታ የእህህ … ክላሲካሎችን እየደረሰ ይገኛል ፡፡ ድምጽ ሳይሆን በቂ ድፍረት ያላቸው ቢያንስ የአይዶል ውድድር ላይ
        ‹‹ እህህ ጠዋት ማታ ዋውዬ
           እህህ ሌሊት ዋውዬ  …. ›› እያሉ ይገኛሉ ፡፡ ‹ ተመስገን › የተሰኘውን ልማዳዊ መዝሙር ጠዋትና ማታ በማቀንቀን የሚታወቁት ቡድኖች ደግሞ  ‹ እነ ፍቅርና ነጻነት › በተሰኙት ስሞች እየተጽናኑ ይመስላል ፡፡

ግን ከባድ ነው ፡፡

በጦርነት ታምሶ የቆየ ቀጠናን እንጂ በጥያቄ የተወጣጠረ አእምሮን በ ‹ ማረጋጋት › መስመር ማስያዝ ይከብዳል ፡፡ በርግጥ ብርቅዬውን ‹ ደስታ › አሁንም በስም መልክ ካልሆነ በተግባር እንዴት መገብየት ይቻላል ? ተስፋ መቁረጥን እንዴት ማከም ይቻላል ?

አዋ ከባድ ነው ፤ በመሆኑም የፈጣሪ ብቻ ሳይሆን የኒክ መንገድም ሳያስፈልገን አይቀርም ፡፡
ቢቻል በአካል ልንጨብጠው ካልሆነ መንፈሱን ልንሞቀው ሳይገባ አይቀርም ፡፡   

እሱ ነው እንደ አማዞን ደን የረዘመውንና የገዘፈውን ተስፋ መቁረጥ ከርክሞ የበረንዳ አበባ ያደረገው ፡፡ እሱ ነው በክፋትና በፌዝ ያበጡ ቦርጮችን አስተንፍሶ የቅርጽ ተወዳዳሪ ያደረጋቸው ፡፡ እሱ ነው የጨካኞችን የደነደነ ልብ ሞርዶ ከውስጣቸው ከርሰ ምድር የሩህሩህነትን እንባ ማፍለቅ እንደሚችሉ እያለቀሱ እንዲያረጋግጡ ያደረገው ፡፡

እሱ ማነው ?

ሙሉ ስሙ ኒኮላስ ጀምስ ቩጂክ ሲሆን ብዙዋቹ የሚጠሩት ኒክ እያሉ ነው ፡፡ ታፍሳስ 4 ቀን 1982 በአውስትራሊያ ሆስፒታል ውስጥ ሲወለድ እጆችና እግሮች እንደሌሉት ታወቀ ፡፡ ወላጆቹ ጤነኛ በመሆናቸው ይህን ክስተት መቀበል አልቻሉም ፡፡ እንዴት ይበላል ? እንዴት ይራመዳል ? እንዴት ይሮጣል ? እንዴት ይማራል ? እንዴት ይጫወታል ? እረ እንዴት ሆኖ እንዴት ይሆናል ?  እናትና አባት ጥያቄዋቹን እያነሱ ምላሽ ሲያጡ ይንሰቀሰቃሉ ፡፡ ሰማይ ምድር ተደፋባቸው ፡፡

ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ከትልቅ ችግር ጋር መጋጨት ጀመሩ ፡፡ በአውስትራሊያ ህግ አካል ጉዳተኛ መደበኛው ት/ቤት ውስጥ ገብቶ መማር አይችልም  ፡፡ ቤተሰቦቹ ሳያቋርጡ ‹ የመብት ያለህ ! › እያሉ በመጮሃቸው ግን ህጉ ሊሻሻል ቻለ ፡፡ ኒክም የመጀመሪያው አካል ጉዳተኛ ተማሪ ሆኖ ተመዘገበ ፡፡ እንደ ልጆቹ ወንበር ላይ ሳይሆን ከፍ ያለ ጠረጼዛ ላይ ቁጭ ብሎ ልጥፍ ግራ እግሩ ላይ ባሉት ጣቶች እየታገዘ መጻፍ ለመደ ፡፡

ትንሽ ከፍ እያለ ሲመጣ ግን ከውጪውና ከውስጡ የሚደርስቡትን ጥያቄዋችና ተጽዕኖዋች መቋቋም አልቻለም ፡፡ እኔ እንዴት ከሌሎቹ ልጆች በተለየ መልኩ ተፈጠርኩ ? ለምን የሰዋች መጠቋቋሚያና መሳለቂያ ሆንኩ ? ማለት ጀመረ ፡፡ በብቸኝነትና በመገለል ቆሰለ ፡፡ ስምንት ዓመት ሲሞላው ራሱን ስለማጥፋት ማንሰላሰል የጀመረበት ግዜ ነበር ፡፡ ቢቸግረው በልጅነት ልቡ ‹‹ አምላኬ ለኔም እጅና እግር ስጠኝ ?  ›› በማለት ዘወትር በማልቀስ ይለምን ጀመር ፡፡ ሰሚ አልነበረውም ፡፡ አስር አመት ሲሞላው ራሱን ውሃ ውስጥ አስምጦ  ለመግደል ሙከራ አደረገ ፡፡ ይሁንና በቤተሰቦቹ ጥረት ከሸፈ ፡፡ በአንድ ወቅት እናቱ አንድ አካል ጉዳተኛ እንዴት ህይወቱን እየመራ እንደሚገኝ የሚተርክ ጋዜጣ በማሳየት ታሪኩን አነበበችለት ፡፡ ይህ ታሪክ በዓለም ላይ ያለው አካለ ጉዳተኛ እሱ ብቻ አለመሆኑን አስገነዘበው ፡፡ ቀስ በቀስም እጅና እግር ያላቸው ልጆች የሚያደርጉትን ነገሮች በሙሉ ያለማንም አጋዥነት ማከናወን እንዳለበት በማመን ልምምዶችንና ጥረቶችን ቀጠለ ፡፡

ውጤቱ አስገራሚ ሆነ ፡፡ ጥርሶቹን ማጽዳት፣ ጸጉሮቹን ማበጠር፣ በኮምፒውተር መጻፍ ፣ መዋኘት ፣ ቴኒስ መጫወት፣ ሰልክ ማናገርና ሌሎችንም ያለ እጆችና እግሮች ማከናወን ቻለ ፡፡ ይህም እንደ ተረገመ ፍጥረት ሲመለከቱት የነበሩ ተማሪዋች አሁን እንደ መልዓክ እንዲመለከቱት አስቻለው ፡፡

 
ኒክ በአካውንቲንግና በፋይናንሻል ፕላኒንግ ሁለት ዲግሪዋችን ከያዘ በኃላ በ19 ዓመቱ የህይወቱን ውጣውረድ ለሌሎች የሚያካፍልበት የንግግር መድረኮችን ማዘጋጀት ጀመረ ፡፡ ለዚህ ይረዳው ዘንድም  life with out limbs  የተባለ አትራፊ ያልሆነ ድርጅት አቋቋመ ፡፡ ዛሬ በት/ቤቶች፣ በእምነት ተቋማት ፣ በድርጅቶች፣ በወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያዋች፣ በእስር ቤቶች፣ በሆስፒታሎችና በስታዲየሞች እየተገኘ ህይወቱንና ልምዱን በመሳጭ የንግግር ችሎታው ያካፍላል ፡፡ በአፍሪካ፣ ኤሽያ፣ ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ሃያ ሀገራት እየተዟዟረ አስተምሯል ፡፡

ኒክ የህይወትን ቀፋፊ ጎኖች በማሸነፍ የላቁ ሜዳሊያዋችን በየግዜው አጥልቋል ፡፡ በ2005 የአውስትራሊያን የዓመቱ ወጣቶች ሽልማት ያገኘ ሲሆን የራሱን ህይወትና እንቅስቃሴ የሚያሳይ የዲቪዲ ፊልም life is greater purpose በሚል ርዕስ ሰርቶ አሰራጭቷል ፡፡ በ2009   < No arms , No legs , No worries > የሚል መጽሀፍ ከማሳተሙ በተጨማሪ < The Butterfly Circus > በሚል ርዕስ በሰራው ፊልም በአጭር ፊልም የምርጥ አክተር ሽልማት ተቀብሎበታል ፡፡ < Some thing more > የሚል ሙዚቃም  ለቋል ፡፡ የካቲት 12 ቀን 2012 ካኔ ሚያራን የተባለች ቆንጆ አግብቶ ህይወቱን በመምራት ላይ ይገኛል ፡፡

‹‹  ፈጣሪን እጅና እግር በተዓምር ስጠኝ እያልኩ እንደዛ ስለምነው ቢሰጠኝ ኖሮ እንደማንኛውም ሰው የተለመደ ህይወት ነበር የምኖረው ፡፡  በወቅቱ ተዓምር ላገኝ አልቻልኩም ፤ አሁን ስረዳው ግን ለካስ ራሴ ተዓምር ነበርኩ ››  በማለት አድማጮቹን በሳቅ ያፈርሳል ፡፡

እንግዲህ የሰው ፍቅርን፣ ፍትህን፣ የህሊና ነጻነትና ሰላምን ሲመኝ የነበረው ኒክ ማለት ይህ ነው ፡፡
ሰው በስድቡ፣ ንቀቱና ማግለሉ ‹ ንክ › ይሆናል ብሎ ሲጠብቀው ‹ ልባቸው እንዲነካ › ያደረገው ኒክ ይህ ነው ፡፡
ያጣውን ሰላም ፣ ፍቅርና ነጻነት በራሱ የጀግና መንገድ የፈታው ኒክ ይህ ነው ፡፡
እንግዲህ ፍቅር፣ ሰላም፣ ነጻነት፣ ፍትህና እንጀራ የምንለምነው ‹‹ እኛም ›› ይኀው አለን ፡፡

ተቆጥረው የማያልቁት ችግሮቻችን እንደ ኩይሳ አድገው ጫፉ ላይ የታሰረው ሰንደቅ ከኩራት ይልቅ ተስፋ መቁረጥን እያውለበለበ ነው ፡፡ ይህ የኩይሳ ምሶሶ እየደነደነ ይሄድ ወይስ ይገርሰስ ? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ የመኖር ወይም ያለመኖር ምርጫ መሆኑ አያከራከርም ፡፡ እንዴት ?  ለሚለው ጥያቄ ነው እንግዲህ የጀግና መንገድ ያስፈልገናል የሚባለው ፡፡




Sunday, July 22, 2012

‎ጠ/ሚ/ር መለስ ሲመለሱ ….‎



መቼም ዓለም የተቃርኖ ሙሌት ናት፡፡ ብርሃን ስንል ጨለማ፣ ሰማይ ስንል ምድር፣ ጎፈር ስንል ዘውድ፣ ደስታ ስንል ሀዘን፣ ህይወት ስንል ሞት የሚባሉት የቁርጥ ቀን አዛማጆች በአእምሮአችን ሳይጠሩ ከተፍ ይላሉ ፡፡

ከዚህ እውነት አንወጣም ፡፡

እንደሚታወቀው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ታመው ህክምና በመከታተል ላይ ናቸው ፡፡ እሳቸው ባይናገሩም ሌሎች ግን ስለሳቸው ከላይ በተገለጸው እውነት መሰረት ሀሳባቸውን ይሰነዝራሉ ፡፡ የመንግስት ኃላፊዋች ድነው ይመለሳሉ ሲሉ ሌላው ህመሙ አስጊ ስለሆነ አይተርፉም ይላል፡፡ ክርክሩ ይጡዝ እንጂ ነባራዊውን እውነት የሚዳኘው ፈጣሪ ነው፡፡ አሁንም አንዳንዶች ወሳኙ ሀኪሞች ናቸው ሊሉ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ጫፎች መሳሳብ ስላለባቸው ፡፡ ሁለቱ ጫፎች ለስነፍጥረትም ሆነ ለቴክኖሎጂው መሰረት መሆናቸውም ይታወቃል ፡፡

እኔም ሁለቱን ጫፍ ተንተርሼ በአቶ መለስ ዙሪያ ወግ ለመሰለቅ አሰብኩ ፡፡ አቶ መለስ ድነው ቢመለሱና አያድርግባቸውና አቶ መለስ ቢያርፉ በሚሉት ሀሳቦች ላይ ፡፡ ቆይቼ ሳስበው ‹ ቢያርፉ › የሚለው ሀሳብ ከይሲ ሆኖ ተሰማኝ ፡፡ ደግሞስ እኔ ማነኝና ይህን ለማወቅም ሆነ ለመገመት ስልጣን የተሰጠኝ ፡፡ ደግሞስ ግዜው ነው ወይ ? ሲል ውስጤ ሞገተኝ ፡፡ ስለዚህ ቀናውን ሞፈር ጨብጬ የወግ ማሳዬን መተርተር እንደሚሻል ወሰንኩ ፡፡

እነሆ ከጎፈር ዘውድን መረጥኩ / ስልጣን ስለሆነ / ፤ እነሆ ከሰማይ ምድርን ሻትኩ / መቼትን ስላስታወስኩ / ፤ እነሆ ከሞት ህይወትን ጠራሁ ፡፡ እናም አቶ መለስ በህይወት ሲመለሱ ምን ያደርጋሉ ? ምን እንሰማለን ? የሚሉ ምናባዊ ትንታኔዋችን እያነሳሁ እጥላለሁ ፡፡

ምዕራፍ አንድ የሚጀምረው አውሮፕላን ውስጥ ነውና አቶ መለስ በኢትዮጽያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ ነው፡፡ ሻምፓኝ ተከፍቶ እየተጠጣ ነው ፡፡ ጎምቱ ባለስልጣናት መለስን ከበው በማያስቀው ሁሉ ይስቃሉ ፡፡ አራት ቦታ የተቆረጠው ኬክ ገና አልታደለም ፡፡ በእያንዳንዱ ቁራጭ ላይ የሰፈሩት ጽሁፎች ሲገጣጠሙ ‹‹ ረጅም ዕድሜ ለመለስ ›› የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ ፡፡

ሲፈራ ሲቸር የቆየው የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ማይኩን ይዞ ወደ አቶ መለስ ጠጋ ሲል የሚያውካኩ ድምጾች መጥፋት ጀመሩ ፡፡
‹‹ እንኳን ለዚህ አበቃዋት ጠ/ሚ/ር ››
‹‹ አመሰግናለሁ ! ››

የጋዜጠኛው ድምጽ ባይሰማም  የሆነ ጥያቄ ወረወረ፡፡ ያው ከመልሱ እናገኘው የለ ?! መልሱም ተከተለ ፡፡

1 . እንደሚገባኝ የመታከሙ ተልዕኮ የተሳካ ነበር ማለት ይቻለል፡፡ ይህን አባባል በሶስት መልኩ መንዝሮ ማብራራት የተሻለ ሳይሆን አይቀርም ፡፡ ቁልፉና ማጠንጠኛው አንድ ሰው በተለይም አንድ የሀገር መሪ ታሞ መዳን መቻሉ ነው ፡፡ ይህን የመዳን ጥያቄ ደግሞ ጠንካራ የሚያደርገው የታማሚው መሪ ግለኛ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የታማሚውን መጨረሻ የሚጠብቁ ብዙ ሚሊዮን አይኖች መኖራቸው ነው ፡፡ ርግጥ ነው 90 ከመቶ ያህሉ ይህ በሽተኛ መሪ እንዲድን ለሚቀርበው ፈጣሪም ሆነ ጣዖት መለማመኑ ይጠበቃል ፡፡ አስር ከመቶው ግን ከቁጥሩ በላይ ያበጠ ፍላጎት እንደነበረው አምናለሁ ፡፡ በጣም የሚገርመው በዚሁ አሃዝ ውስጥ የሚካተተው ጥቂት ማህበረሰብ የሚናገረው ርግጠኛ የመሆኑ ጉዳይ ላይ ነው  ፡፡

ለምሳሌ ያህል  ‹ መለስ ከዳነ ከምላሴ ጸጉር ይነቀል › ብሎ ይነሳል ፡፡ በርግጠኝነት የሚያወራው ሞቱን ብቻ ሳይሆን የሕመሙንም መንስኤ ነው ፡፡ የያዘው የጭንቅላት ዕጢ የሚያፈነዳው እንጂ ለቀዶ ጥገና የሚመች አይደለም ብሎ ይደመድማል ፡፡ ወይ በሌላ ገጹ በድብቅ ያበሉት መርዝ ለጥቂት ግዜ ብቻ ነው የሚያላውሰው እንደሚል አይጠረጠርም ፡፡ ስለሆነም ጥቂቶች ካወሩት ሚሊዮን አሉባልታና ሚሊዮን ክፉ ምኞት አንጻር ህክምናው የተሳካ ነበር ለማለት ያስደፍራል ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ መታየት ያለበት እኔን ሲያክሙና ሲንከባከቡ ከነበሩ ዶክተሮች አንጻር የሚተነተን ነው ፡፡ እንደምታውቀው መሪዋች ሲታከሙ ለማዳን የሚኖረውን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያህል ከውስጥ በጣም ያረገዘ ነገር ግን የማይታይ ስጋት ይኖራል ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የተጠራቀመው ስጋት የሚጫነው ደግሞ ሀኪሞች ላይ ነው ፡፡ ሀኪሞች ሌላ ዓላማ ላነገቡ ሰዋች፣ ቡድኖች ወይም መንግስታት ማለት ይቻላል ተገዢ ወይም ተንበርካኪ ባይሆኑ እንኳን ኃላፊነታቸው በራሱ ስጋት ላይ ሊጥላቸው ይችላል፡፡ ከስጋትም አልፎ በጥቂት ነገር ሊሳሳቱ ይችላሉ ፡፡ ከተሳሳቱ ደግሞ ተበላሸህ ነው ፡፡ አለቀ ፡፡ ዛሬ ኤሪያል ሻሮን፣ ሙባረክና ሌሎች መሪዋች ምን ያህል ኮማ ውስጥ እንወደቁ ማየት ይቻላል ፡፡ እና ህክምናው ውስጥ ያለውን ጦርነት በድል ከመወጣት አንፃር ተልዕኮው የተሳካ ነበር ማለት እችላለሁ ፡፡

በሶስተኛ ደረጃ መቀመጥ ያለበት የተሞክሮ ቅመራ ወይም የቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደት ነው ፡፡ የታከምኩበት ሀገር የምታራምደው ርዕዮት ምንም ይሁን ምን በህክምና ዘርፍ የደረሰችበት ደረጃ ከፍተኛ ነው ፡፡ ይህን ቴክኖሎጂ ወደ ሀገራችን እንዲገባ በማድረግ ተሞክሮውን በማጥናትና በመቀመር ማስፋፋት ይኖርብናል ፡፡ ይህን በማድረጋችን ለህክምና የምናወጣውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ማዳን ይቻላል ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የያዝነውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ተጨማሪ ምርኩዝ ይሆንልናል ፡፡

2. ጠ/ሚ/ር መለስ ቤተመንግስት ከገቡ በኃላ ከእንደገና በነገሮችና በሁኔታዋች ሊወጠሩ እንደሚችሉ ይገመታል ፡፡ የመጀመሪያ ተግባራቸው በየደረጃው መግለጫዋችን መስጠት ይሆናል ፡፡

ሀ . ለህዝብ ፤

አቶ መለስ ህዝቡ በሃሳብም ሆነ በጸሎት ላደረገላቸው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባሉ የሚለውን እንደ አርእስተ ዜና እንውሰደው ፡፡ ድርጅቱ መራራውን የትጥቅ ትግል ሲያደርግ ከጎን እንደነበር ፣ ሰላም ሰፍኖ የልማት ግንባታው ከቀጠለ በኃላም አለኝታነቱን እንዳረጋገጠ ወደፊትም የኩሩውንና የቀናኢውን ህዝብ ድጋፍ እንደማይለያቸው አስረግጠው መናገራቸውን ደግሞ ርዕሱን የሚያፍታታው ዝርዝር ሃሳብ ይሆናል ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጅምሮች አሉና፡፡ ቢያንስ የአባይ ግድብ ማለቅ አለበት ፡፡ ቢያንስ ህዝቡ በቀን ሶስት ግዜ መብላት አለበት ፡፡ ስለዚህ ህዝቡ መሪውን  አሳፍሮ እንደማያውቅ የታሪክን ሰበዝ በማውጣት ንግግራቸውን ሊያጠናክሩት ይችላሉ ፡፡ ይህ ደግሞ የኃላ ታሪክ / Background / መሆኑ ነው ፡፡ ማለትም የአጼ ዮሀንስ  ‹ ሀገርህ እናትህ፣ ዘውድህ፣ ሚስትህ…  › የሚለው ገዳይ ጥቅስ የተዘጉ ልቦች ዳር እንዲንኳኳ ይደረጋል ፡፡ በሌላ በኩል የአጼ ሚኒሊክ ‹ ጉልበት ያለህ በጉልበት ርዳኝ … › የምትለው ትሁት ስንኝ ይጨመርበታል ፡፡ በላዩ ላይ ወርቅ የመሳሰሉ አዳዲስ መፈክሮች ጣል ይደረግበታል ‹‹ ጸረ ህዝብም ሆኑ ጸረ ጤንነቶች ከመንገዳችን አያደናቅፉንም ! ››

ለ . ለፓርቲ አባላት ፤

ጠንካራ ሀሳቦችና ጉዳዮች የሚመዘዙት በዚህ ክፍለ ግዜ እንደሚሆን ይጠበቃል ፡፡ ስብሰባውን ፈታ ለማድረግ በ ‹‹ ሞት ›› ላይ አንድ ሁለት ቀልዶችን ወርወር ማድረግ ማን ይከለክላቸዋል ፡፡ አሁን የታየው ውጥረት ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት፣ ከህወኃት ክፍፍልና ከ97ቱ ምርጫ ቀጥሎ ሊቀመጥ የሚችል የፈተና ምዕራፍ በመሆኑ ትልቅ የጠቆረ ቦታ ይኖረዋል ፡፡ በመሆኑም በህወኃት ክፍፍል ግዜ የተባለውን ቁም ነገር በማስታወስ ‹‹ ሞት ለምሳ ሲያስበን ለቁርስ አድርገነዋል ›› ሊሉ ይችላሉ ፡፡ ካስፈለገ ደግሞ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የትዝታ ኮሮጆ ውስጥ የጄኔራል ሳሞራን ብሂል በማውጣት

 ‹‹ በሽታ አካልን ማገርጣትና ማሰቃየት ይችልበታል ፤
እኛ ደግሞ ሰንኮፉን በጽናት አስነቅለን ቆመን መሄድ እንችላለን ›› ቢሉ ወፈ ሰማይ ካድሬ እስከ ሻይ እረፍት አይስቅም ብሎ መከራከር አያዋጣም ፡፡ በርግጥ ሁሌም የሚጠራጠሩ አንዳንድ ሰዋች ከቀልዱ ጀርባ ምን ተደግሷል በሚል በመተርጎምና በመተንተን ቀኑን ሊያሳልፉት ይችላሉ ፡፡  ‹ በርግጥ ለምሳ ያሰቡ እነማን ናቸው ? …. ሰንኮፎቹስ ?  .. ›

አቶ መለስ በነካ እጃቸው ሰምና ወርቅ ያለው ምስጋና በማቅረብ የቤቱን ሙቀት ሊያግሉት ይችላሉ ፡፡ ‹‹ እዛ ድረስ መጥተው የጠየቁኝ የቁርጥ ቀን ወዳጆቼ አሉ ፡፡ ይህ ማለት ግን በስራ መብዛት ወይም የአውሮፕላን ወጪ በማጣት ያልመጡ ጓዶች ሁሉ እኔን አልጠየቁኝም ወይም ለእኔ አያስቡም ማለት አይደለም ! ››

‹ እዛ ድረስ ሄደው የጠየቁት በርግጥ አባካኝ ናቸው ወይስ የቁርጥ ቀን ልጆች ? አሁን ማን ይሙት የአውሮፕላን ወጪ የሚከብደው ኃላፊ የቱ ነው ? ጉድ ነው ይሄ ነገር ! … › ሌላ ምናባዊ ሀሳቦች ይፈለፈላሉ ፡፡ ይህን መሰል ፍም በራሱ ፓለቲካ ሰፈር ውስጥ መለኮስና እንዳይጠፋም በአባላቱ ምላስ እንዲርገበገብ ማድረግ ጠቃሚ ነው ፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ተርከክ ያለው ፍም ላይ ‹ በቆሎ › ይጠበስበታል ፡፡ በቆሎ ከጠፋ እንኳን ሰብሰብ ብለው ወይ ተረት ወይ ትዝታን እያወሩ ይሞቁታል ፡፡

3 . የወ/ሮ አዜብ መስፍን ሹፌር ቤተመንግስት አካባቢ በተነሳው የስልጣን ሹክቻ በመስጋት በቱርክ አድርጎ ግሪክ መግባቱን አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል ፡፡ ይህ ወሬ እውነት ከሆነ አቶ መለስ በቀጣይነት ለሚንደረደሩበት ርዕሰ ሀሳብ ጥሩ መረጃ ይሆናል ፡፡ ዜናው እውነት ካልሆነ ወደ ርዕሰ ጉዳዩ የሚያሰገባው መንገድ የተለየ መሆኑን ልብ ይሏል ፡፡ እናም አቶ መለስ የሾፌሩን ስም ጠርተው  ‹ ምን መሆኑ ነው ግን ? የኛ የስልጣን ሹክቻ የሚያሰጋው እሱ ባለስልጣን ነው እንዴ ? › የሚል ጥያቄ ወርወር ያደርጋሉ ፡፡ ወዲያው ደግሞ  ‹‹ የዚያች የጥንቸሏ ብጤ መሆኑ ነው ?!  ነብር ነው ዝሆን እየታደነ ይያዝ ሲባል እሷ እግሬ አውጪኝ ትላለች ፡፡ እንስሳትም ምን ሆነሽ ነው የምትፈረጥጪው ?  አዋጁ እንደሆነ አንቺን አይመለከትም ሲሏት ዝሆን አለመሆኔ እስኪረጋገጥ ለምን ፍዳዬን አያለሁ ነበር ያለችው ! ›› በማለት ላነሱት ጥያቄ ማብራሪያ ይሰጣሉ ፡፡ አቶ መለስ ፊታቸውን ከስከስ አድርገው ይቀጥላሉ ፡፡

‹‹ በርግጥ ሰው ወጣ ሲል የሰው በር ለማንኳኳት የቋመጡ ሰዋች እንደነበሩ ተሰምቷል ፡፡ የዉጪዋቹስ መቼም ግርግር ለሌባ ይመቻል ! የሚባለውን ብሂል አሁን ነው መጠቀም ያለብን ለማለት ነው ፡፡ በጣም የሚገርመው የቤታችን ጉድ ነው ! አንዳንዱ የተሰጠውን ስራ አድምቶ ሳይሰራ ነው ወደ ላይ መንጠልጠል የፈለገው ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ተገፍቶና ባዶ ተስፋ ተሸክሞ ነው ››

ከዚህ በኃላ የደፈረሰው ይጠራ ዘንድ፣ ለአቅመ ጠላ ያልደረሰው መጠጥ መቼ፣ እንዴትና በነማን እንደተጠነሰሰ ይታወቅ ዘንድ ተከታታይ ሂስና ግለሂሶች ይካሄዳሉ ፡፡ በመሃሉ የሚፈረጥጡ ጥንቸሎችም አይጠፉም ፡፡ ነገሩ ሀገሪቱ ውስጥ እንደሚወራው ጠንካራ ከሆነ ድርጅቱ ለፓለቲካ ጸበል ሁለት -  ሰባት  ‹ ሸንኮራ › መውረዱ አይቀርም ፡፡

እንግዲህ ይህ ሲያልቅ ነው አዳዲስ ነገሮች የሚፈልቁት ፡፡  በመጀመሪያ መግለጫው ፤

. ‹ ከናፋቂነት ተፈወስን ! › የሚል ሀሳብ ላይ ይሽከረከር ይሆናል ፡፡ ከዚህ በፊት ጠባቂነት፣ ተሃድሶ፣ መበስበስ ወዘተ የሚሉ ምጡቅ መግለጫዋች ስለነበሩ እንዳይደገሙ ጥንቃቄ ስለሚደረግ ማለት ነው ፡፡

. ውስጥ ለውስጥም ሆነ ይፋ በሆነ መግለጫ ሹም ሽሮች ሊከናወኑ ይችላሉ ፡፡ በሹም ሽሩ ከዚህ ቀደም በአቅም ማነስና በእጅ አመል ቀንዳቸውን የተመቱ ሁሉ አሁን የኤሊን ገጸ ባህሪ ወክለው ይጫወታሉ ፡፡

. የከፋ ነገር የተገኘባቸው / ለአብዮቱ ያልተመቹ / ደግሞ ፈጽሞ አልመው ወደማያውቁት የቃሊቲ ዓለም ይወረወራሉ ፡፡ ጎበዝ ከሆኑ ‹ ህይወት ከቪላ  በኃላ › ወይም  ‹ የአብዮታችን  ያልተገረዘ መጋዝ › በሚል አንድ አስደናቂ መጽሀፍ ሊደርሱ ይችላሉ ፡፡

4 . ከምስጋና ፣ መወቃቀስና ሹም ሽር በኃላ አዳዲስ ቃላቶችና አባባሎች የሚፈጠሩ ይመስለኛል ፡፡ እነ ተንበርካኪነት፣ 
ተስፋፊነት፣ ጠባቂነት፣ ተቸካይነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የልማት ሰራዊት እና የመሳሰሉት ተመሳሳያቸውን ወይም ተቃራኒያቸውን የሚያፈሩበት ሁኔታ ይኖራል ፡፡ ከዛም እንደ አካሄድ … እንደ አሰራር… ስብሰባ እንደ ስብሰባ … እያሉ ሃሎ ሃሎ መንፋት ነው ፡፡ በአነጋገር አንድ ዓይነት ልብስ የለበሰ  …

እስኪ  ያወራሁትን ምን ያህል እንደማውቀው ለማረጋገጥ የሆነ መልመጃ ልሞክር ፡፡ < ከላይ በተገለጹት ቃላቶችና የአሰራር ይትበሃሎች ቢያንስ ሁለት ቃላቶችን መስርት ? >

. በቃላት ራስን መቻል !
. የቃላት ሰራዊት ማፍራት !


Sunday, July 15, 2012

‎ፈሳዊ ጉዳያችን‎



ፈስ ሳይንሳዊ በሆነ አካሄድ ወጥ ትርጉም እንዳለው ይታወቃል ፡፡ ነገር ግን በወንዶችና ሴቶች ዓይን ነጥለን ካየነው ሁለት የተለያዩ ትርጉሞች መስጠቱ ግድ ነው ፡፡

ከሴት አኳያ --   አሳፋሪ ተረፈ ምርት
ከወንድ አኳያ --- ከወንድ ጋር የተቆራኘ፣ ራስን መግለጫና መጨረሻ የሌለው የመዝናኛ ምንጭ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡

ፈስ ግዜና ቦታ አይመርጥም ፡፡ አንዳንድ ሰዋች ወንዶች ከሴቶች ይልቅ ብዙ ግዜ ይፈሳሉ ይላሉ ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ወንዶች በስብሰባ ፣ ስራ ቦታ፣ በእምነት ተቋማት፣ በየመንገዱ ያለርህራሄ ይተኩሱታል ማለት ነው ፡፡ በሌላ በኩል ይህ አባባል እውነት ከሆነ ሴቶች ፈስን በጣም በመቆጠብ መጨረሻ ላይ ግን አስገምጋሚ ጋስ ያስወነጭፋሉ እንደ ማለት ነው ፡፡

የፈስ ሽታ የሚመጣው አነስተኛ መጠን ካላቸው የሃይድሮጅን ሰልፋይድ ጋስና መርካፕታን ከተባለው ንጥረ ነገር ድብልቅ ነው ፡፡ እነዚህ ድብልቆች ሰልፈርን ይዘዋል፡፡ ምግብ ውስጥ ብዙ ሰልፈር ካለ የፈስ ሽታም ጠንካራ እየሆነ ይሄዳል፡፡ አንድ ሰው በቀን በአማካኝ ግማሽ ሊትር የሚደርስ ፈስ ሊያመነጭ ይችላል፡፡ ፈስ ወደ ፈሺው አፍንጫ ቶሎ ከመድረስ ይልቅ ከ 13 እስከ 20 ሰከንድ ሊቆይ ይችላል፡፡ ፈስ በድምጽ ፍጥነት የሚጓዝ ቢሆን ኖሮ ሽታውንም ወዲያው ማጣጣም በተቻለ ነበር ፡፡

ልብ ብላችሁ ከሆነ በሴቶች ሽንት ቤት ውስጥ የፈስ ድምጽ የሚሰማው በእንግዳ ስሜት በጣም አልፎ አልፎ ነው፡፡ ፈስ ከተሰማ ይህን አድራጊዋ ፣ የሰሙ ሰዋች ከአካባቢው እስኪርቁ ድረስ እዛው ልትደበቅ ትችላለች፡፡ በወንዶች ሽንት ቤት ግን ፈስ የበዓል ማዳመቂያ ወይም የጀግንነት ምልክት ይመስል በከፍተኛ ድምጽ ሲንጓጓ ነው የሚውለው ፡፡

በነገራችን ላይ በየትኛውም የዓለም ማዕዘን የምትገኝ ሴት ብዙ የሚያበሳጫትና መታገስ የማትፈልገው ነገር አለ ከተባለ በፈስ ጉዳይ ነው ፡፡ በጥንት ዘመን ወንድ ልጆች አስር አመት ሲሞላቸው ያላቸውን ብቃትና ጥንካሬ ከሚለኩባቸው መንገዶች አንዱ የሚፈሱት ፈስ ምን ያህል ርቀት ድረስ ይሰማል የሚል ነበር ፡፡ አንዳንድ አካባቢ ፈስ በአደባባይ ቢፈሳም የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይደለም ፤ አንዳንድ አካባቢ ደግሞ መሸማቀቅ ይስከትላል ፡፡ በአንድ ወቅት ፕሬዝዳንት ኦባማ ንግግር እያደረጉ ‹ ጠ ረ ረ ረ ር ር …. › የሚል ድምጽ ይሰማሉ ፡፡ ንግግራቸውን ገታ አድርገው ወደ ታች ካዩ በኃላ ‹‹ sorry for the gas ! ›› ብለው ንባባቸውን ቀጠሉ ፡፡ ወደ ታች ዝቅ ብለው ሲመለከቱ የሌላ ነገር ድምጽ ሳይመስላቸው  አልቀረም ፡፡ አንድ የኛ ሀገር መሪም ንግግር እያደረጉ ፈሳቸውን አንጣረሩት፡፡ ደንገጥም ሳይሉ ንግግራቸውን ቀጠሉ ፡፡ ምናልባት በለሆሳስ ነው የፈሳሁት ብለው አስበውም ይሆናል ፡፡ ግን ማይክራፎኑ ገዳዩን አጋኖ ቁጭ አደረገው ፡፡ ምናልባትም ከጆርጅ ቡሽ ጋ ጓደኝነት ይኖራቸው ይሆናል ፡፡ ቦብ ውድዋርድ የተባለ ጸሀፊም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ በፈስ ነክ ቀልዶች በእጅጉ እንደሚንፈቀፈቁ ጽፏልና ፡፡

 
ዴይሊ ሜል የተባለው ጋዜጣ ደግሞ የሚላዊ ፕሬዝዳንት ቢንግዋ ሙታኒካ በየአደባባዩ መፍሳትን ህገ ወጥ ድርጊት በማድረግ ቅጣት እንዲጣል ሀሳብ ማቅረባቸውን ይነግረናል፡፡ እንደ ጋዜጣው አስተያየት ከሆነ ህጉ የተረቀቀው ህዝቡ ኃላፊነት የሚሰማውና በስነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን ከማሰብ አንጻር ነው ፡፡

ሳቅ አለም አብራህ ትስቃለች፣ ፍሳ ለግዜውም ቢሆን ሁሉም ሳቃቸውን ያቆማሉ የሚል ቀልዳዊ አባባል አለ ፡፡ ወፍ የምትጮኀው እንዳገሯ ነውና ወደኛ ስንመጣ ፈስ በቀላሉ ‹‹ ፈሳም ! ›› የሚል ስድብ ያሰጣል፡፡ ‹‹ ይሄ ፈሳም ነው ! ›› ከተባለ ለቁም ነገር የማይበቃ፣ ፈሪና የሚናቅ መሆኑን  ሊጠቁም ይችላል ፡፡ እናም ለመፍሳት ግራና ቀኝ መመልከት ፣ ከተለቀቀም በኃላ ምን ያህል ይሸት ይሆን ? ብሎ አፍንጫን እንደ ውሻ ወደፊት መቀሰር ፣ ይታወቅብኝ ይሆን ? ብሎ አይንና ጆሮን ወደ ጎን ማሽሟጠጥ ይከተላል፡፡

ፈስን ጋስ ነው ብሎ የሚቀበል ትውልድ ገና አልመጣም ፡፡ ህጻናት እንኳን ፈሰኛን የሚያወግዙበት ስነ ግጥም አለቻቸው ፡፡
ፈስ ፈሶ ፈሳራራ
ቆርጦ ቆርጦ ደም ያሳራ
ደሙ ሲረጋ በለው ባለንጋ
አለንጋው ሲበጠስ
ምንቄው ይበጠስ ! / ምንቄ ግን ምንድነው ? /

ወደ አማራው ክልል ስንጓዝ ደግሞ ፈስ ሃይለኛ የጦር መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ፡፡ የቆሎ ተማሪዋችና ደብተራዋች ‹ የጎዳቸውን › ሰው ለማጥቃት በወፍ ቋንቋቸው ይደጋግማሉ ፡፡ ይህን ቋንቋ ከአዲስ ኪዳን ማውጫ ተውሰን  ‹‹ የደብተራ ወንጌል ›› ወይም  ‹‹ የደብተራ ስራ ›› ፤ አሊያም ከብሉይ ኪዳን ተነስተን  ‹‹ መጽሀፈ ደብተራ ›› ወይም  ‹‹ ትንቢተ ደብተራ ››  ለማለት እንኳን የሚያስቸግር ይመስለኛል ፡፡ ብቻ ከመጽሀፍ ቅዱስ ክልል ውጪ ቢሆንም የዋሉበት ድግምት አያሳፍራቸውም ነው የሚባለው ፡፡ ያ - በግዕዝ ቋንቋ የተቃመበት ሰው ታዲያ ቀኑን ሙሉ ለዚያውም ቦታ ሳይመርጥ እንደ አህያ ዘረጥ - ዘረጥ ሲያደርግ ይውላል፡፡ አቤት መሳቀቁ አይታያችሁም ፡፡

‹‹ ወይ ጉድ  ያ- የተበላሸ ባቄላ እኮ ነው ?! …
‹‹ አዬ አያ እንትና ያ - የማልወደውን ሻሜታ ግቶኝ ግቶኝ  !…
መጨረሻ ላይ እውነትን መካድ ሁሉ ሊመጣ ይችላል ፡፡ ‹‹ አይ ይህ ሆዴ … ሆዴ እኮ ነው እንዲህ የሚጮኀው ?  … ››
አህያ የሚለው ቃል የአለቃ ገብረሃና ቀልዶችን አስታወሰኝ ፡፡ ሴትየዋ በእንስራ ውሃ ተሸክማ ቁልቁል ትወርዳለች ፡፡ ቁልቁለቱ በጣም ያዘቀዘቀ በመሆኑ ዘጭ - ዘጭ እያለች በፍጥነት እንድትወርድ ያስገድዳታል ፡፡ በዚህ ግዜ ፈሷ ያመልጣትና ዛጥ ዛጥ ታደርገዋለች ፡፡ ይሄኔ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ  ‹‹ አንተ ጊዮርጊስ አሁንስ እንደ አህዮቹ ልታደርገኝ ነው ? ›› ትላለች ፡፡
 ‹‹ እ.ህ.ህ ! … ›› እያለ ጉሮሮውን የሚጠራርግ ሰው ድምጽ ሰምታ ዘወር ስትል አለቃን አየች ፡፡
 ‹‹ ውይ አለቃ ! መቼ መጡ ? ›› አለች የምንተፍረቷን
‹‹ ጊዮርጊስ አህዮቹን ይዞ የወረደ ግዜ ! ›› ሲሉ ኩም አደረጓት

ለነገሩ በዚህ ረገድ አለቃም ኩም የሚሉበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም ፡፡ ልዩነቱ ሌሎቹን እንደሚተርቡ ሁሉ በራሳቸው ላይም መቀለድ መቻላቸው ነው ፡፡ አንድ ወቅት እንዲህ ሆነ ፡፡ የቅርብ ዘመዳቸው ስለሞተ አልቅሰው ፣ ቀብረው ቢደክማቸውም ወደ ቤታቸው መሄድ አልቻሉም ፡፡ ማታ ራት ተበልቶ ተጎዝጉዞ ከለቀስተኛ ጋር በመደዳ ይተኛሉ ፡፡ ትንሽ ቆይተው ግን ፈሳቸው መጣባቸው ፡፡ ይሄኔ ቀስ ብለው ያለ ድምጽ ሊፈሱ አስበው ቂጣቸውን በእጃቸው ከፍተው ቢለቁት ‹ ጠ ረ ረ ረ ር … ! › ብሎ አጋለጣቸው ፡፡ እናም ምነው አለቃ ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ ?! ወዘተ የሚሉ አፋጣጭ ጥያቄዋች ከመወርወራቸው በፊት            ‹‹ አዬ እድሌ መልግጌ አባስኩት አይደል ? ›› በማለት ለቀስተኛውን አሰፈገጉት ፡፡

 
በአንድ እጁ የጀግንነት በሌላኛው የፍርሃት ችቦ ለኩሶ የሚጓዘው ፈስ በተረብ፣ በተረት፣ በአባባል፣ በጥናትም የደለበ ነው ፡፡ የጥናቱን ካዝና ስንከፍተው 96.3 ከመቶ የሚደርሱት ወንዶች ፈስ እንደሚፈሱ ሲያምኑ የሴቶች ቁጥር 2.1 ከመቶ ብቻ መሆኑን እንረዳለን ፡፡ ወንዶች በአማካኝ በቀን 12 ግዜ በመፍሳታቸው ከ 1.5 እስከ 2.5 ሊትር ጋስ ያጣሉ ፡፡ ይህ መጠን አንድ አነስተኛ ፊኛን ለመሙላት በቂ ነው ፡፡ በሌላ በኩል ሴቶች በአማካኝ በቀን ሰባት ግዜ ሲፈሱ ከ 1 እስከ 1.5 ሊትር ጋስ ያስወጣሉ ፡፡

በዓለማችን ታዋቂ ፈሳም ተብሎ የተመዘገበው ጆሴፍ ፓጁል እ.ኤ.አ በ1892 በፓሪስ ከተማ የፈስ ትዕይንት ያቀርብ ነበር ፡፡ ድርጊቱን የሚጀምረው የሆነ ታሪክ እያወራ ሲሆን ይህንንም የተለያዩ ድምጾች ባሉት አሰገራሚ ፈሱ ማጀብ ይችላል፡፡ ይህ ሰው በላስቲክ ውስጥ ሲጋራ ካስገባ በኃላ ላስቲኩን በቂጡ ቀዳዳ ውስጥ በመጨመር ያጨሳል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዋሽንቱን ቂጡ ላይ ከሰካው ላስቲክ ጋር በማያያዝ የሀገሪቱን ብሄራዊ መዝሙር ይጫወታል ፡፡ በዚህ ድርጊቱ ከወንዶች ይልቅ ፈስ የሚጠሉት ሴቶች በጣም እንደሚስቁ ተዘግቧል፡፡ አንዳንዶች እንደውም ሳቅ በማብዛታቸው እየታመሙ ወደ ሆስፒታል እሰከመወሰድ ደርሰዋል ፡፡

ከፈስ ጋስ ውስጥ ከ 50 እስከ 60 ከመቶው ናይትሮጂን፣ ከ30 እስከ 40 ከመቶው ካርቦን ዳይኦክሳይድ እንዲሁም ከ 5 እሰከ 10 ከመቶው የሚደርሰው ሚቴን ነው ፡፡ ሚቴን ጋስ መሬት ውስጥ የተቀበረ ፈንጂ እንዲፈነዳ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ አንድ ጥናት ብዙ ለመፍሳት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በምግብ ግዜና ከምግብ ውጪ ብዙ ማውራት መሆኑ ታውቋል ይለናል፡፡ ፈስን በከፍተኛ ደረጃ በማመንጨት በኩል ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ምግቦች የአበባ ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ዳቦ፣ ባቄላ፣ ነጭ የወይን ጠጅ እና አትክልትና ፍራፍሬዋች ናቸው፡፡

በነገራችን ላይ ከከብቶችና ከበጎች ፈስ የሚወጣው የሚቴን ጋስ በመላው ዓለም 35 ከመቶ ያህል በመሆኑ የመሬት ሙቀት እንዲጨምር፣ የኦዞን ሌዪር ቀዳዳ እንዲሰፋ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ፡፡ በመሆኑም ለዓለማችን ትልቁ ስጋት አሸባሪነት ሳይሆን የላሞች ፈስ ሳይሆን አይቀርም ፡፡


                                                                

Wednesday, July 11, 2012

‎አልጀዚራ ነፍስ ፍለጋ የለኮሰው ሻማ ይዳፈን ይሆን ?‎





እድሜ ለአልጀዚራ አንድ የሞተ ታሪክ ነፍስ ዘራ፡፡ ታዋቂው የኖቤል ተሸላሚና የፍልስጤም መሪ ያሲር አራፋት ህዳር 11 ቀን 2004 በፓሪስ በሚገኝ አንድ ወታደራዊ ሆስፒታል ውስጥ ነበር የሞቱት፡፡ በወቅቱ የሞታቸው መንስኤ ተደፋፍኖ ስለነበር ‹  ይሄ በሽታ ነው የገደላቸው ›  ለማለት አልተቻለም፡፡ ይህም በርካታ መላምቶች እንዲወለዱ አደረገ፡፡  ጉበት፣ ካንሰር፣ የደም መታወክና ኤድስ የሚሉት በጣም ጎልተው ይሰሙ ነበር ፡፡ እነሆ ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኃላ አራፋት የሞቱት ፓሎኒየም በተባለ ሬዲዮ አክቲቭ ንጥረ ነገር ተመርዘው መሆኑ ተደረሰበት፡፡ ምርምራው የተካሄደው ስዊዘርላንድ በሚገኘው የሬዲዮ ፊዚክስ ተቋም በመሆኑ ዜናው አጠራጣሪ የሚሆንበት መንገድ ዝግ ነው፡፡ በምርመራው የአራፋት ልብሶች፣ ደም፣ ሽንት፣ ምራቅና ላብ ሳይቀሩ ተካተዋል፡፡ የተቋሙ ኃላፊ ዶ/ር ፍራንኮይስ ቦችድ ውጤቱን በይፋ ያረጋገጡ ሲሆን ምርምሩን ይበልጥ ማጠናከር ካስፈለገ የአራፋትን ሬሳ ሊመረመር ይችላል ብለዋል፡፡  እናም አራፋት የሞቱት በተፈጥሮ በሽታ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ በተቀነባበረ የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ አራፋትን ማን ገደላቸው ? ፍልስጤም፣ ፈረንሳይ፣ እስራኤል፣ አሜሪካ ወይስ ሌሎች ?

ሲታከሙበት የነበረው የፈረንሳይ ወታደራዊ ሆስፒታል አሟሟታቸውን ለምን ደበቀ ?  እውነት የፍልስጤማዊያን ኃላፊዋችስ ምስጢሩን አያውቁም ነበር ?  በቀጣይ የሚደረገው ዓለማቀፍ ምርመራ  የተጠያቂ ግለሰቦችንና ሀገሮች ዱካ ላይ ይደርስ ይሆን ?  ይህ ወንጀልስ በቀጣዩ የሰላም ድርድሮች ላይ ምን ተጽዕኖ ያስከትላል ?  እንግዲህ ተቀብሮ የነበረው ጉዳይ ሳጥን ፈንቅሎ በመውጣት ሌላ የቀዝቃዛ ጦርነት ሊያስከትል አሞጥሙጧል፡፡

አልጀዚራና ሱሃ አራፋት
 
የስዊዘርላንዱን የሬዲዮ ፊዚክስ ተቋም ጨምሮ አልጀዚራና የያሴር አራፋት ባለቤት ሱሃ አራፋት ይህን ፈታኝ የምርመራ ስራ ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የምርመራው ስራ አሰልቺና ከባድ ዘጠኝ ወራትን ጠይቋል፡፡ የአራፋት የአሟሟት መንስኤ ከአሉባልታዋች ባለፈ ተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተደገፈ አለመሆኑ ሲቆጨው የነበረው አልጀዚራ ኃላፊነቱን ወስዶ ጉዳዩ እንደ አዲስ እንዲነሳ ማድረጉ የሚገርም ነው፡፡ ግዜው በራቀ ቁጥር ተጨባጭ ማስረጃ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እየሳሳ እንደሚሔድ ይታወቃል፡፡ ግን እስካሁን ግልጽ ያላደረጉትን አስተማማኝ የምርመራ ፍንጭ በማግኘታቸው ሊሆን ይችላል ሀ ብለው የጀመሩት፡፡ በርግጥም የጋዜጠኝነት ፈታኝ ተግባር የሆነውን የምርመራ ዘገባ ለመስራት እውቀት፣ ብልሃት፣ ትዕግስት፣ ድፍረትና መስዋትነት ይጠይቃል፡፡

 ‹‹ የምርመራ ዘገባ  ሰዋች ወይም ድርጅቶች በምስጢር ሊይዙት የሚሽቱን ዓይነተኛ ጉዳይ በግል የስራ ውጤትንና ተነሳሽነት መዘገብ ነው ፡፡ እያንዳንዷን ዝርዝር ጉዳይ በጥልቀት የመፈተሸ፣ እውነታን የማፈላለግና ስነልቦናዊ ብቃትን ይጠይቃል፡፡ ጋዜጠኛውን የሚጠረጥረውን ወይም ዋጋ ይኖረዋል ብሎ ያሰበውን ጉዳይ ቀርቦ የመመርመር ብቻ ሳይሆን ከቀጣዩ ውጤት አንጻር የመተንተን ስራም ያከናውናል፡፡ ጉዳዩ ከጽሁፍ ማስረጃዋች ጋር ብቻ ሳይሆን እወቅና ከገኘ የህክምና ውጤት፣ ሳይንሳዊ ውጤቶች፣ ማህበራዊና ህጋዊ ድንጋጌዋች ወዘተ ጋር ሁሉ ሊተሳሰር ይችላል ›› / የጋዜጠኝነት ፈታኝ አጀንዳዋች ፤ አለማየሁ ገበየሁ ፤ ገጽ 16 /

በርግጥ የምርመራው ዘገባ ዋናውን ምዕራፍ ገለጸ እንጂ የመጨረሻው ውጤት ላይ አልደረሰም ፡፡ ይህ ምዕራፍ ግን ልክ  ለአንድ  የህንጻ  ግንባታ ትልቁን ሚና እንደሚጫውተው ‹‹ መሰረት ›› ግዙፍ መደላድል መፍጠሩ የማይታበል ነው፡፡ ቀጣዩን ስራ ለማከናወን የተዘረጋው አስፋልት ወደ መጨረሻው ፌርማታ ለማድረስ ፈጥነትንም ምቾትንም ታሳቢ ሊያደርግ ይችላል ፡፡ 

ለመሆኑ የምርመራው ስራ እንዴት ተጠንስሶ ወደ ውጤት ተቀየረ ?  ሱሃ አራፋት ሁኔታውን እንደሚከተለው ትገልጸዋለች
‹‹ በመጀመሪያ እኔ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ የሄድኩበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኃላ ለምን አስፈለገ  ? ብለህ መጠየቅህ አይቀርም፡፡ ሆኖም የአልጀዚራ ጣቢያ ወደኔ መጥተው ምርመራ ማከናወን እንደሚፈልጉ ገለጹልኝ ፡፡ እናም አልጀዚራ ሌሎች ያልወሰዱትን ኃላፊነት ሊወስድ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ብሄራዊ ስራ ነው፡፡ በዓለም ላይ ከፍተኛ ዝናና አቅም ያለው የምርመራ ተቋም ሊያስሱ ነው፡፡ በመሆኑም የፈረንሳይ ሆስፒታል የሰጠኝን ልብሶችና ቁሳቁሶች በሙሉ ሰጠዋቸው፡፡ የሴት ልጄንም ዘረመል ወሰዱ፡፡ ዘረመሉን ከባለቤቴ ልብስና ጸጉር ያገኙትን ነገር የማነጻጸር ስራ አከናወኑ፡፡ ውጤቱም ተመሳሳይ ሆነ፡፡

‹‹ ይህን ስራ የጀመርነው ከዘጠኝ ወራት በፊት ነበር፡፡የባለቤቴን ንብረቶቸ፣ የህክምና መድሃኒቶች፣ ሰዓቱን፣ የአንገት ሀብሉን በሙሉ ፈትሸዋል፡፡ በመጨረሻም ከፍተኛ መጠን ያለው ፓሎኒየም በደሙ፣ በልብሶቹ፣ በባርኔጣው፣ በውስጥ ልብሱ ሳይቀር ንጥረ ነገሩ ተገኝቷል፡፡ ይህ ደግሞ የሚገኘው በበለጸጉ ሃገሮቸ ብቻ ነው፡፡ አሁን አራፋት የሞተው በተፈጥሮ ህመም ሳይሆን በወንጀል መሆኑን መግለጽ እንችላለን፡፡ ከዚህ በኃላ የፍልስጤምን መንግስት እኔንም ሆነ ህዝቡን እንዲረዳ የምጠይቀው የባለቤቴ ሬሳ እንዲመረመር ፍቃድ እንዲሰጠኝ ነው፡፡ ሀኪሞች ትክክለኛውን አጥንት ካመጣሁ ንጥረ ነገሩ እንደሚገኝ ገልጸውልኛል፡፡ ሌላው ቢቀር ሬሳውን የከበበው አፈር ላይ እንኳ ሊገኝ ይችላል ፡፡ ሆኖም በፍጥነት መከናውን አለበት ››

ፓሎኒየም ምንድነው ?
ፓሎኒየም 210 በዓለማችን በቀላሉ ከማይገኙ ማዕድናት ውስጥ ይመደባል፡፡ በመጀመሪያ የተገኘው እኤአ በ1898 ሜሪ እና ፔሪ ኩሪ በተባሉ ሳይንቲስቶች ነበር፡፡ እነሱም ለሀገራቸው ክብር ሲሉ የማዕድኑን የመጀመሪያ ስም ከሀገራቸው Poland ጋር ለማስተሳሰር ሞክረዋል፡፡ በተፈጥሮ ከመሬት የላይኛው ክፍል ላይ በጥቂቱ የሚገኝበት ሁኔታ ያለ ሲሆን ለኒውኩለር ማብላሊያነትም በሰው ሰራሽ ዘዴ ሊመረት ይችላል፡፡ የፖሎኒየም አነስተኛ ንጥረ ነገር ማለትም 0.04 ኦውንስ ሰውን ለመግደል በቂ ነው፡፡ በተለይም ጉበት፣ ኩላሊትና የአጥንት ውስጥ ፈሳሽን በከባዱ የሚያጠቃ ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ የማስታወክ፣ የጸጉር መሳሳት፣ የጉሮሮ ማበጥና መገርጣትን ያስከትላል፡፡

በነገራችን ላይ በዚህ ንጥረ ነገር የሚሞቱ ሰዋች በጣም አነስተኛ ሲሆኑ የቀድሞው የሶቭየት ህብረት መኮንና ሰላይ የነበረው አሌክሳንደር ሊቲቬንኮ በጉዳዩ የመጀመሪያው ሟች መሆኑ ተመዝግቧል፡፡ ለስለላ ተቋማት ይሰራ የነበረው ይህ ሰው ከሀገሩ ተሰዶ በእንግሊዝ ጥገኝነት አግኝቶ ይኖር ነበር፡፡ ከዚያም ጋዜጠኛ ሆኖ ከቼቼኒያ ጎን በመቆም ሩሲያን የሚቃወሙ ሁለት መጻህፍትን አሳትሟል፡፡ በሞስኮ ትያትር ቤት የተከናወነውን የጠለፋ ድራማና ለሌሉች የሽብር ተግባራት ተጠያቂው ፑቲን መሆናቸውንም ይገልጽ ነበር፡፡ ህዳር 2006 ታሞ ከሶስት ሳምንታት በኃላ ሞተ፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በፖሎኒየም የሞተ ተብሎ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ እንደውም ሳይንቲስቶች የኒውክለር ሽብር ተጀመረ በማለት ስጋታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ሰላዩ የሞተው የሚጠጣው ሻይ ውስጥ ንጥረ ነገሩ ተጨምሮበት ሲሆን የሞተውም በሚታወቁ የቀድሞው ጓደኞቹ አማካኝነት ነው፡፡ የእንግሊዝ መንግስት ኃላ ላይ የሩሲያን ዲፕሎማሲ ላለማበላሸት በሚል ክሱን አዳፍኖታል፡፡

ሱሃ አራፋትን በጨረፍታ



 
ሱሃ በዌስት ባንክ ከሚኖሩ ሀብታም የክርስትያን ቤተሰቦች የተገኘች ናት፡፡ አባቷ ዳውድ አል ታዊል የባንክ ባለሙያ ሲሆን፣ እናቷ ሪሞንዳ አልታዊል ፓለቲከኛና የሚዲያ ሰው ነበሩ ፡፡ ትምህርቷን በፍልስጤም ግዛት ውስጥ ከተከታተለች በኃላ ለተጨማሪ ትምህርት ፓሪስ ወደሚገኘው ስርቦኔ ዩኒቨርስቲ አቅንታለች፡፡

አራፋት ሱሃን ያገኟት ጆርዳን በሚገኘው የአል ውህዳት ስደተኞች ካምፕ ውስጥ እኤአ በ1985 ነበር፡፡ ያኔ ዕድሜዋ በሃያዋቹ መጀመሪያ ሲሆን አራፋት 58 ሻማ ለኩሰዋል፡፡ የስራ ግንኙነታቸው ቀስ በቀስ ዳበረ፡፡ ሱሃ አራፋት ከፈረንሳይ ባለስልጣናትና ፓለቲከኞች ጋር ሲገናኙ ረዳትና አስተርጓሚ ሆና ትሰራ ነበር፡፡ በ1989 ተጋቡ ፤ ግንኙነቱ ግን ምስጢራዊ ነበር፡፡

አራፋትን ካገባች በኃላ ክርስትናን ወደ እስልምና በመቀየር ወደ ፒኤልኦ ጠቅላይ መምሪያ ቱኒዝያ አመራች፡፡ የሁለቱ ጋብቻ ህዝብ ያወቀው በ1992 አራፋት በሊቢያ በረሃ ከአውሮፕላን ተከስክሰው ሱሃ ልትጠይቃቸው ባቀናችበት ግዜ ነበር፡፡ ሀምሌ 24 ቀን 1995 ሴት ልጅ ወለደች፡፡ አራፋት በ1993 የሞቱትን እናታቸውን ለማስታወስ በሳቸው ስም ዛህዋ ሲሉ ሰየሟት፡፡ ሱሃ አራፋት ከሞቱ በኃላ በቱኒዚያ ለትንሽ ግዜ ተቀምጣለች፡፡ ይሁን እንጂ ከቱኒዝያው መሪ ሚስት ለይላ ቢን አሊ ጋር በመጣላቷ ወደ ማልታ ሄዳ ለመኖር ተገዳለች፡፡ በአሁኑ ግዜም ከፍልስጤም መንግስት ድጎማ ትቀበላለች፡፡

በቀድሞው ታሪክ ውስጥ ፈረንሳይና ፍልስጤም ምን ብለው ነበር ?
 
የፈረንሳይ ባለስልጣናት በሀገራቸን ህግ መሰረት የግለሰቦችን ምስጢር ማውጣት አንችልም በሚል መንስኤው እንዲደበቅ አድርገዋል፡፡ ትንሽ ቆይተውም የአራፋትን የህክምና ፋይል መስጠት የሚቻለው ለቅርብ ዘመዶች ብቻ ነው በሚል ለአጎታቸው ለናስር አል ኪድዋ ሰጥተውት ነበር፡፡ በወቅቱ ሚስታቸው ሱሃ ፍቃደኝነቷ አልተጠየቀም፡፡ ከዚያ ደግሞ የፍልስጤም የካቢኔ ጸሀፊ ሀሰን አቡ ሊድህ የአራፋትን ሙሉ የህክምና መረጃ ማግኘታቸውንና ታሪካዊ መረጃ መሆኑን በመግለጽ በዚሁ መሰረት መንግስታቸው አሰፈላጊ ርምጃዋችን እንደሚወስድ ተናግረው ነበር፡፡ ይህ ንግግር ለህዝቡ ዝርዝር መረጃ መስጠትን ያካትታል፡፡
ይሁን እንጂ መረጃው ለህዝቡ ስላልተገለጸ አራፋት የሞቱት እስራኤል መርዛቸው ነው የሚል ወሬ በሀገሪቱ ውስጥ ተሰራጨ፡፡ አስቀድሞ አራፋትን ሲከታተሉ የነበሩት ሀኪም አሽራፍ አል ኩርዲም ምናልባት ለአራፋት ሞት የተሻለው ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል በማለት ግምታቸውን ሰነዘሩ፡፡ የአራፋት አጎት አል ኪድዋ እስራኤል መርዛ ለመግደልዋ ምንም አይነት መረጃ የለም በማለት ተከራከሩ፡፡ በወቅቱ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን የአራፋት ሞት ኤድስ ነው በማለት ይዘግቡ ነበር፡፡ ምናልባት አራፋት ከመሞታቸው በፊት የፈረንሳይ  ሀኪሞች አራፋት አነስተኛ የቀይ ደም ሴልና ከፍተኛ ነጭ ደም ሴል እንደታየባቸው መግለጻቸውን መሰረት በማድረግ ‹‹ ይሄ ይሆናል ›› የሚለውን ግምት እንዲያሰፋው አድርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ሆን ተብሎ ፡፡

ለአራፋት ሞት የእስራኤል እጅ አለበት ?
አልጀዚራ የቀድሞውን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ሽሎም ቤንአሚንን አነጋግሮ ነበር፡፡
‹‹ አራፋትን በደንብ አውቀዋለሁ ለማለት ርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የተደረጉት የሰላም ሂደቶች በሙሉ ለእኔ ውስብስብ የሆነ ሰውን የመፈለግ ሂደት አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ ሎይድ ጆርጅ ከአይሪሽ መሪ ዲቫለራ ጋር መደራደር ሜርኩሪን በሹካ እንደማንሳት ያህል ነው ብሎ ነበር ፤ በቃ አራፋት ማለት ይህ ነው፡፡ የማይጨበጥ ነው ፡፡ በፍፁም በሩን አይዘጋም - በፍጹም በሩን አይከፍትም፡፡ ሁልግዜ የሚናገረው ለፍቺ የሚያስቸግርና አሻሚ ነው፡፡ ስምምነት እንደሚፈልግ ግልጽ ነው ፡፡ ነገር ግን ለስምምነቶቹ የሚያስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዋች ምን እንደሆኑ በፍጹም ግልጽ አይደለም፡፡

‹‹ ጤንነቱን በተመለከተ ገና ወጣት እያለ ታማሚ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ እስራኤል ለአራፋት ሞት ማንኛውንም ነገር ታደርጋለች የሚል እምነት ውስጤ የለም፡፡ በሌላ በኩል የአራፋት መኖር ከፓለቲካ አኳያ ለኤሪያል ሻሮን እንደ ትልቅ ንብረት ነው የሚቆጠረው፡፡ ››

ብዙዋች አራፋት የካምፕ ዴቪድን ስምምነት ባለመቀበላቸው ጥርስ ውስጥ መግባታቸውን ይስማማሉ፡፡ የረጅም ግዜ የአራፋት አማካሪ የነበሩት ሞሀመድ ራሺድ በተለይም ኢሁድ ባራክ በምርጫ ከተሸነፉና የክሊንተን ቡድን ከቢሮው ከለቀቀ በኃላ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚወድቅ ገልጬላቸው ነበር ይላሉ፡፡ ኤርያል ሻሮንን ባናገርኩበት ግዜ አንተን አልፈልግህም ለአለቃህ ግን ቀጣዩ ግዜ ከባድ እንደሚሆን ንገራቸው ብለውኝ ነበር የሚሉት አማካሪው ስለዚህ በመርዝ ይገደላሉ የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡ ጉብኝት በሚያደርግበት ግዜ ፕሮቶኮልም ሆነ ምግብ ቀማሽ የለውም የሚሉት  አማካሪው ለ32 ዓመታት ሳውቀው ብቻውን አይበላም ሲሉ አስተያየታቸውን አጠናክረዋል፡፡

ለሱሃ ጥሪ የተሰጠው ምላሽ
 
የሱሃን ጥሪ ተከትሎ የፍልስጤም መንግስት ሁለት መሰረታዊ ምላሾችን አሰምቷል፡፡ የመጀመሪያው ምርመራውን ያጠናክረው ዘንድ የያሲን አራፋት ሬሳ / ቤተሰቦቹ ፍቃደኛ ከሆኑ / እንዲመረመር ፍቃደኛ መሆኑን ማረጋገጥ ሲሆን ሁለተኛው በጉዳዩ ላይ ዓለማቀፍ ምርመራ እንዲደረግ ለዓለማቀፉ ማህበረስብ ጥያቄ ማቅረቡ ነው ፡፡ የፍልስጤምን ጥያቄ ተከትሎ ቱኒዝያ ፣የአረብ ሊግና ሀማስ ምርመራው ሳይውል ሳይድር እንዲጀመር እየጠየቁ ይገኛሉ ፡፡  ሌላው ዓለም ግን ልክ እንደተፈራራ ወይም የሁኔታውን አደገኛነት በመገንዘብ ሊሆን ይችላል እስካሁን ዝምታው ላይ እንደተኛ ነው፡፡

ምን ይጠበቃል ?
 
እናስ መጨረሻው ምን ሊሆን ይችላል ? ልክ እንደ ሩሲያው ሰላይ የአራፋትም ነገር ተዳፍኖ ይቀር ይሆን ? አለሁ አለሁ የሚሉት የአለማቀፉ ፍርድ ቤትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችስ ኃላፊነታቸውን በምን መልኩ ለመወጣት ይዘጋጃሉ ? ሱሃ አራፋት ላይ እየተነሱ የሚገኙት ጥያቄዋች አቅጣጫውን ይለውጡት ይሆን ?  ቱኒዚያ የተባረሩትን መሪዋን በሙስና ስለምትከስ ሱሃንም ለጥያቄ እንፈልጋታለን እያለች ነው ፡፡ የፈረንሳይ ጋዜጦች አራፋት በባንክ ያሰቀመጡትን ገንዘብና የዝውውር ሁኔታን በተመለከተ  የሱሃ እጅ ይጣራ እያሉ ይመስላል ፡፡ እነዚህ ነገሮች ዓላማቸው ምን ይሆን ?  

የአራፋት ነፍስ ግን ትጣራለች  - ቢያንስ  ለኛም ሀገር  የምርመራ ጋዜጠኛነት ተሞክሮ እያስተማረ የሚገኘው አልጀዚራ የለኮሰውን ሻማ ያጠፋዋል ማለት ያስቸግራል፡፡

Saturday, July 7, 2012

‎እውነት ድንጋዩ ማነው ?‎


አመክንዮ ተኮር ዳሰሳ


‹‹ ድንጋይ ራስ ! ›› ያስባል ተብሎ ለሚታሰበው ፍጡር ክፉ ስድብ ነው ፡፡ ለነገሩ ህይወት ካላቸውም ሆነ ከሌላቸው መካከል የማያስቡ በርካታ ቢሆኑም የድንጋይ ክፉ ተምሳሌትነት ግራ ያጋባል፡፡ በግ ራስ ! … ዛፍ ራስ ! … ለምን አልተባለ ይሆን ? በድንጋዮች ወገን ሆነን ብናስብ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው የሚሆንብን ፡፡

ከድንጋይ ስር የማይለየው ሰው ድንጋይን ማንቋሸሹ ለድንጋዮች አይዋጥም፡፡ ድንጋይ በመሬት፣ በጨረቃ፣ በባህር፣ ሌላው ቢቀር በሰው ሆድ ዕቃ ውስጥ አለ፡፡ መኖሩ ብቻ ሳይሆን መገለጫው በርካታ ነው፡፡ ድንጋይ ! እያለ የሚያንቋሽሸው ዘመናዊው ሰው የድንጋይ ቤት ውስጥ ለመቀመጥ ዕድሜ ልኩን ይለፋል፡፡ የአንድ መኪና ድንጋይ ዋጋ ጣራ ነካ እያለ እዬዬውን ያቀልጠዋል፡፡ የከበረ ድንጋይ በመሻት እርስ በርሱ ይጨራረሳል፡፡ ካባ ውስጥ ወዛም ድንጋይ ለመፈለግ አካባቢውን በፈንጂ ያሸብራል፡፡ በኮብል ስቶን ስራ ሲሰማራ ድንጋይ ዳቦ ሆነ በማለት ይፈላሰፋል ፡፡ ለአጥር፣ ለመንገድ፣ ለመጸዳጃ ቤት ወዘተ ውበት መፍጠሪያ ያለ ድንጋይ አይታሰብም ፡፡ ሲሞት ድንጋይ መሃል መቀበሩ አላረካው ብሎት የድንጋይ ህንጻ ይገነባል፡፡ ድንጋዩም ላይ እነሆ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ሲል በድንጋይ ፊውቸር ቴንስ ጥቅሶችን ይጠቃቅሳል ፡፡

ይህን ሁሉ ድርጊት አርቀው የሚያስቡ ድንጋዮች በሰው አላዋቂነት …. ትንሽ ዕውቀት አደገኛ ነው እያሉ ማሽሟጠጣቸው ይጠበቃል፡፡ በተለይ እሱ ራሱ አፈር ከሆነ በኃላ ወደ ድንጋይ የመለወጥ ዕድሉ የሰፋ መሆኑን አለመገንዘቡ ያበሽቃቸዋል፡፡ እናም የመሰዳደቢያ ፈሊጣቸው ሰው ነው፡፡ ‹‹ ሰው ራስ ! ››… የተባለ ድንጋይ ራሱን ከመፈረካከስ ወደ ኃላ እንደማይል አይታያችሁም ?

በርግጥ ለድንጋይ ክብር የነሳው ዘመናዊው ሰው እንጂ የጥንቱ አይደለም፡፡ የጥንቱማ ቤቱ፣ ጠመንጃው፣ ክብሪቱ፣ ምጣዱ፣ ወረቀቱ… ድንጋይ ነበር ፡፡ ለድንጋይ ክብር የማይፋቅ ተዓምራትን አበርክቷል፡፡ የግብጹ ፒራሚድ፣ የሮሙ ላተርንና የአክሱሙ ሀውልቶች ሌሎችም ዛሬም ድረስ የሰውና የድንጋይ ጥምረትን ያሳብቃሉ፡፡ ድንጋይ ራስ ! እያለ የሚሳደበው ዘመናዊው ሰው በጥንቶቹ ሰዋች ተአምር ዛሬም እየተደመመ ነው፡፡ ተዓምራቶቹን ፈልቅቆ መነሻቸውንና ውበታቸውን ለማወቅ ቢፍጨረጨርም እንቆቅልሹ ባሰበው መልኩ አልተፈታለትም፡፡ ታዲያ ሰው ድንጋይን በቅጡ ሳያውቅ እንዴት የስድብ መጠሪያ አደረገው ? እስኪ እስካሁን አጥንቶ ምላሽ ያላገኘባቸውን ጥቂት የድንጋይ ጉዳዮች እያነሳን እንጫወት፡፡

ኮስታሪካ

በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን በደቡብ ምዕራብ ኮስታሪካ ልዩ ልዩ መጠን ያላቸው ድንጋዮች ነበሩ፡፡ ድንጋዮቹ ትሪያንግል፣ ሬክታንግልና ክብ ቅርጽ ያላቸው ነበሩ፡፡ አብዛኛዋቹ ድንጋዮች የተገኙት በድኩዊስ ወንዝ አካባቢ ሲሆን የተፈጠሩት በ400 CE እንደሚሆን አርኪዋሎጂስቶች ገምተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኮስታሪካ ሙዚየም እስካሁን በሀብትነት የመዘገባቸው 130 ያህሉን ነው፡፡ ሌሎችማ በዘመናዊው ሰው ግልብ ፍላጎት ተፈረካክሰዋል -  ድንጋዮቹ መሃል ጌጣጌጥ ይገኛል በሚል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ለጌጥነት በመኖሪያ ቤት፣ በአትክልት ቦታዋችና በየቤተክርስትያናት ተበታትነዋል፡፡

የዛሬውን ሰው እያነጋገረ ያለው ጉዳይ ድንጋዮቹ እንዴት ተፈጠሩ ? የሚለው ነው ፡፡ የአንዱ ድንጋይ ክብደት 16 ቶን ሲደርስ ፍጹማዊ ክብነቱ ጂኦሜትሪን ያሳጣል፡፡ ያኔ ደግሞ ስርዓት ያለው የሂሳብ ትምህርት አይታሰብም፡፡ አንዳንድ ተመራማሪዋች ቀራጺዋች ለዝናና ለጌጥ የሰሯቸው ናቸው በማለት ገምተዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በወቅቱ የነበሩ ሰዋች በከፍተኛ ደረጃ የማቅለጥ ግንዛቤ ነበራቸው ? የሚል ጥያቄ ያስከትላል፡፡ ምናልባት ድንጋዩን በአሸዋና በቆዳ አቅልጠው በማለስለስ ከበረደ በኃላ ክብ ገጽታ ለፈጥር ይችላል ይላሉ፡፡ የግራናይቱ ድንጋይ ከዲኪዋስ ወንዝ 40 እና 50 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ተራራ ላይ እንደነበር ታውቋል፡፡ እና ቀራጮቹ ድንጋዩን ሰርተው እንዴት ወደሌላ ቦታ አዘዋወሯቸው ? የሚለውም ጥያቄ ምላሽ አላገኘም፡፡ ምክንያቱም አንዱ ድንጋ|ይ ከ16 ቶን በላይ ስለሚከብድና በወቅቱ ዘመናዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ስለማይታሰብ ነው፡፡

ኢትዮጽያ

ከ7 እሰከ 9 የሚገመቱት የአክሱም ሀውልቶችም ከጥበባቸው በላይ ርዝመታቸውና ግዝፈታቸው እስካሁንም እያጠያየቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንዴት ተጓጓዙ ? እንዴትና በየትኛው መሳሪያ ደጋፊነት እንዲቆሙ ተደረገ ? በአበሾች ወይስ በሌሎች ? ለሚሉት ጥያቄዋች የሚሰጠው ምላሽ ያው አንጀት የማያርስና የግምት ትራስን የተደገፈ ነው፡፡ የጢያ ትክል ድንጋይ በቅርስነት የተመዘገበ ሃብት ነው፡፡ አካባቢው የመቃብር ቦታ እንደነበር ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ በሀውልቱ ላይ የተቀረጹት ምስሎች ግን ያው በፈረደበት ግምት እየተመተሩ ነው፡፡ የሳርና የዘንባባ ምልክቶች ልምላሜና ሀብትን… በወንድ ብልት መሰል የተቀረጹት ሀውልቶች የጀግንነትና የዘር መራባትን ሊጠቁሙ ይችላሉ በሚል፡፡ 

ኔዘርላንድ

በደች ግዛት በሆነቸው ድሬንዝ በፐ ቅርጽ የተሰሩ ድንጋዮች በብዛት ይታያሉ - ዶሊሚን ይሏቸዋል፡፡ ድንጋዮቹ ቀብር አካባቢ የሚገኙ ሲሆን ቱሪስቶች በብዛት ይጎበኙዋቸዋል፡፡ 53 ዶሊሚን የተመዘገቡ ሲሆን 52ቱ በድሬንዝ ይገኛሉ፡፡ ትልቁ ድንጋይ 22 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን የ47 ድንጋዮች ቅንጅት ነው፡፡ አንዱ ድንጋይ 3 ሜትር ቁመትና 20 ቶን ክብደት አለው፡፡ ይህ ሁሉ ሁኔታ እነዚህን ድንጋዮች ማን ሰራ ? መቼ ? ለምንና እንዴት ? የሚሉ ጥያቄዋችን ያጭራል፡፡ ሳይንቲስቶች ዶሊሚን የተገነቡት በበረዶ እየተንሸራተቱ ነው ብለው ያስባሉ - በበረዶ ዘመን፡፡ የሚገነቡትም ገበሬዋች ሲሆኑ የባህላቸው አካል ስለሆኑ ነው፡፡ ሌላው ወገን በእንጨት እየተንከባለለ እንደሚጓዝ ይናገራል፡፡ ነገር ግን የሞቱ ሰዋች ለምን በተለመደው መልኩ ሊቀበሩ አልተፈለገም የሚለውን ጥያቄ መመለስ አልተቻለም፡፡

ዘመናዊው ሰው ስለ ድንጋዮች በቂ መረጃ ባያገኝም የጥንቱ ሰው በተግባር ተኮር እንቅስቃሴ የተከበበ ይመስላል፡፡ ጥናት፣ ምርምር ፣ኮንፈረንስ በሚሉ መሰረተ ሃሳቦች ግዜውን ከመግደል ይልቅ ያሰበውን ለመስራት ይተጋል፡፡ የበጀት፣ የአቅም፣ የግዜ ፣ የተነሳሽነት ጥያቄዋችን አካብዶ ሳያነሳ ድርሻውን ተወጥቷል፡፡ በዚህ እውነታ ስር የፈበረካቸው ምርጥ ተግባራት ለዘመናዊው ሰው ፈተና ፈጥረዋል፡፡ ዳናውን ለማግኘት ሌት ተቀን ቢያጠና ተጨባጭ እውነት አልያዘም፡፡ ጠብ ያለው ውጤት የግምት መልሱ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ… ለዚህ ጥቅም… ለዚህ ተልዕኮ በዚህ ዓይነት ሰዋች ተሰርተው ይሆናል ይለናል፡፡ ከዚሁ ጎን የጥንት ሰዋችን የአሰራርና የእምነት ፍልስፍና በእሱ መነጽር ብቻ እየተመለከተ ኃላቀርነታቸውን ይነግረናል፡፡ ስለ ድንጋይ ክብር ሳይገነዘብ ወይም ምኞቱን ከሟላ በኃላ እየረሳ ድንጋይ ራስ ! እያለ ይሳደባል፡፡ ይህ ደግሞ ድንጋይ ራስ ! የሚለው ስድብም ግምታዊ ሊሆን እንደሚችል ጠቋሚ ነው፡፡

ዘመናዊው ሰው ትልቁ ድንጋይ  ውስጥ ወርቅ ይገኛል እያለ መፈረካከሱ ግለኝነቱንና አላዋቂነቱን ያቃጥራል፡፡ የቱሪስት መስህብ እያለ ገንዘብ ይሰበስብባቸዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ የሃብት፣ የሞራልና የታሪክ ፍላጎቶች መሰረቱ የጥንት ሰው ነው፡፡ የጥንት ሰው ደግሞ ለድንጋይ ታላቅ ክብር አለው፡፡ በዚህ እሳቤ ድንጋይ ራስ ! የሚል ስድብ አይጠቀምም፡፡ ይህን ሁሉ ሃሳብ / logic / ብናገጣጥመው አንድ ስዕል እናገኛለን፡፡ ሊሳደብ የሚችለው አፍ ያለው ሰው ወይስ አንደበቱ የማይታየው ድንጋይ ? የትኛውስ ነው ትክክል ?…. ድንጋይ ራስ ! የሚለው ሰው ወይስ ሰው ራስ ! የሚለው ድንጋይ ?….

Tuesday, July 3, 2012

እየተወገዘ የሚለመልም …




‹‹ የት ተፈጠረ ? ›› የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ብዙዋች ይጣሉበታል፡፡ ገሚሱ ትውልድ ሃገሩ ኢትዮጽያ ነው ሲል ሌላው የመን መሆኑን ያስረዳል፡፡ ኢትዮጽያ እና የመን ‹‹ የኔ ነው ›› እያሉ የሚከራከሩበት በስንት ነገር ነው ጃል ?! ላለፉት 3ሺ ዓመታት በታላቋ ንግስት ሳባ የታሪክ ጉተታ ውስጥ ገብተው የሃሳብ ልብሳቸውን ሲቦጫጭቁ ነበር፡፡ በርግጥ ትግሉ በአዳፍኔና በጨበጣ መጠዛጠዝን ያለመ አልነበረም፡፡ ስልቱ ዞር ያለ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል

የደረጀ ጥናታዊ ጽሁፍን - እንደ ጦር ማምረቻ ሰፈር
የቁፋሮ ምርምርን - እንደ ፈንጂ
ነባራዊ ማስረጃ የሆኑትን ማለትም ቤተ መንግስትን - እንደ ዘመቻ መምሪያ
መዋኛ ገንዳን - እንደ  መርከብ
ሳባዊ ጽሁፍን - እንደ ፕሮፓጋንዳ ክፍል
የሚነገሩ ትውፊቶችን - እንደ ሚዲያ ተቋም ሳይጠቀሙ አይቀርም፡፡ ደግነቱ ሁለቱም ወገኖች ወደ ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ሳይሄዱ ወይም የመሄድ ፍላጎት ሳያሳዩ ሳይንቲስቶች የአሸናፊነቱን ካባ ለኢትዮጽያ አልብሰዋል፡፡ አሁንም በነካ እጃቸው የዚህን ተክል መፈጠሪያ ቢወስኑ ጥሩ ነው፡፡ ለነገሩ የመጀመሪያ መባል ታሪካዊ ትርፍ ካለው እንጂ ይሄኛው ተክልስ አጨቃጫቂ ባህሪ አለው፡፡

ይህ ተክል የት ተፈጠረ ብቻ ሳይሆን መቼ ተገኘ ? የሚለውም ሀሳብ ላይ ስምምነት አልተገኘም፡፡ ገሚሱ በ13ኛው ሌላው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚል ሀሳብ አለውና፡፡ ተክሉ ኢትዮጽያም ይፈጠር የመን ከዚያ ወዴት አቀና ለሚለው ጥያቄ ግን ተመራማሪዋቹ ተመሳሳይ ምላሽ አላቸው፡፡ ወደ ሶማሊያ፣ ማላዊ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ አረብ፣ ኮንጎ፣ ዚምባብዌ፣ ዛምቢያና ደቡብ አፍሪካ የሚል፡፡

ለረጅም ዓመታት የሳይንቲስቶችን ቀልብ የገዛው ተክል መጠን ሰፊ ጥናት ሲደረገረበት ቆይቷል፡፡ አንዳንዶቹ አደገኛ ሌሎች ለስላሳ ወይም የማይጎዳ የሚል ፍረጃ ቢሰጡትም የአፍቃሪዋቹ ቁጥር በእጅጉ ከመበራከት ያገዳቸው ሁኔታ የለም፡፡ መልከ መልካሙ  ቅጠል በየሀገሩ የተለያየ ስያሜ ቢሰጠውም ከቤት መድፊያ አንጻር ተመሳስሎ ይንጸባረቅበታል፡፡ በኢትዮጽያ ጫት፣ በአረብ ጃት፣ በየመን ካት ወይም ጋት፣  በሶማሊያ ጃድ፣ በኬንያና ታንዛንያ ሚራ ይባላል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በኢትዮጽያ ወይም በየመን በቀለ የሚባልለት ‹ ካት . በብዙ ሀገሮች ዘንድ እንደ እርኩስ መንፈስ ተቆጥሮ / በርግጥ ቀደም ባሉት ግብጻዊያን የሰማይ ቤት ምግብ እንደሆነ እምነት አላቸው / የህግ አጥር ቢበጅለትም እንደ ጀት በፈጠነ ሩጫው ገብኝቱን ከማጠናከር ወደ ኃላ አላለም፡፡  የቅርብ ግዜ መረጃዋች እንደጠቆሙት ከሆነ ‹ ጃድ › በእንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ አምስተርዳም፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ኒውዚላንድና አሜሪካ ታይቷል፡፡

ጫት እንደ ክፉው ሰይጣን በቀን ሺህ ግዜ ይወገዛል ፡፡ አደንዛዥነቱ፣ የሱስ ተገዢ ማድረጉና የስራ ባህልን መጉዳቱ፣ ከጥርስ ጀምሮ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ፣ አልፎ አልፎም የአእምሮ ስርዓትን በማፋለስ ለቀውስነት እንደሚዳርግ ሳይንሳዊ እውነታዋችን ዋቢ በማድረግ የማስጠንቀቂያ አታሞ ይደለቅለታል፡፡ በተቃራኒው ጎን ደግሞ ሺ ግዜ ይሞገሳል ፣ ይገጠምለታል ፣ ይጠቀስለታል ‹ የቃመ ተጠቀመ ፣ ያልቃመ ተለቀመ › ዓይነት ...

ዛሬ የከተማን ህጻን ጅብ ይበላሃል ብለው ቢያስፈራሩት ባማረ መልኩ ይስቅቦታል፡፡ ምክንያቱም ከተሞች ጅብን የሚያሳድር ጫካቸውን በሚያስፈራሩ ሰዋች መነጠቃቸውን ያውቃልና፡፡ እንደ ህጻናቱ ሁሉ ወጣቱም ሆነ አዛውንት የቂማ ስራዊት በጫት ላይ የተመሰረቱ አስጊ ዜናዋችን የሚያዳምጠው ጫት እየቃመ ነው፡፡ ከመደንገጥ ይልቅ ፈገግ ይላል፡፡ ፈገግታው መቼም ለምጸት እንጂ ለኮረኮረው እውነታ ቅርብ ሆኖ አይመስልም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምጸቶች ደግሞ ኅልቆ መሳፍርት የሆነ ፍቺ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እንደው ሲያቀብጠኝ እንደሚከተለው እያሰበ ይሆን እላለሁ ?

እሳቤ አንድ፣

ደራሲው በመጣጥፉም ሆነ በግጥሙ ጫት እንዴት ትውልድን እያደነዘዘና እየገዘገዘ መሆኑን በሚያስጨበጭብ መልኩ ይገልጸዋል፡፡ የተጨበጨበለትን ስነጽሁፍ የደረሰው ግን ኮባውን ትራስ፣ እንጨቱን መፋቂያ፣ ቅጠሉን መስተፋቅር አድርጎ ነው፡፡

እሳቤ ሁለት፣

ጋዜጠኞች በአንደኛው መታወቂያቸው ሀሳቡን ደጋግመው ወቅጠውታል፡፡ ምናልባት የቀራቸው ‹‹ በርጫ ›› የሚል ቋሚ አምድ ወይም ፕሮግራም ማስጀመር አለመቻላቸው ነው፡፡ በሁለተኛው መታወቂያቸው ላይ ‹‹ ለዚች ዓለም ዱካክና ድብርት ሳትበገር ሀቃራህን ፍታ ! ›› የሚል ጽሁፍ በትልቁ ይታያል፡፡ ይህ ጽሁፍ የሚገኘው ‹ ብሄር › የሚለው ሰረዝ ላይ ነው፡፡

እሳቤ ሶስት፣

ሙዚቀኛው ምርጥ ግጥምና ዜማን ለማፍለቅም ሆነ ለመምረጥ ተመስጦ ፍቱን መሳሪያ መሆኑን ያምናል፡፡ ተመስጦውን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ዮጋን ሳይሆን በለጬን አስበልጧል ፡፡ በህንድ የተመሰረተው ዮጋ ሂንዱዚም፣ ቡዲሂዝም፣ ጄይኒዝም፣ ሲኪዝም በተባሉ የእምነት እቅፍ ውስጥ ያደገ ነው፡፡ ታዲያ በዮጋ ለሰዓታት ተቆራምዶ የማይታወቅ የ< ኢዝም > ባህር ውስጥ ሰምጦ ማን ይንቦጫረቃል ? ከማያውቁት መልዓክ የሚያውቁት ሰይጣን እንዲሉ ይልቅ ሳቅ፣ ደመቅና ቦርቀቅን አስቀድሞ ጨመቅና ደንዘዝን ለሚያስከትለው ቅጠል የአውሊያን መንገድ ማሳየት ይበልጣል ፡፡

እሳቤ አራት፣

መንግስት በአደባባይ ያወግዘዋል ፤ ከበስተኃላ በጫት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እንዴት የሆነ እጥፍ መጨመር እንደሚገባው ከብጤዋቹ ጋር እየገመገመ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡

አስደሳች ማስተካከያ ፤ ደራሲ፣ ጋዜጠኛና ሙዚቀኛ የሚለው ሀሳብ ፊት ‹‹ አንዳንድ ›› የምትል ሚዛናዊ ማድረጊያ ቃል እንዳለች በውስጠ ዘ ይታወቅልኝ !!

ታዲያ እንዲህ እየተወገዘ የሚለመልም ተክል እንዴት የአጋሮቹ ቁጥር ሊቀንስ ይችላል ?  ‹ ሚራ ›  የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻርም በእርሻ ክፍለ ዘርፍ ውስጥ ግዛቱ ሰፊ እየሆነ ነው ፡፡ ለምሳሌ በየመን 40 ከመቶ የሚሆነው የውሃ አቅርቦት በመስኖ የሚጓዘው የጫት ተክልን ሊያለማ ነው፡፡ በ2001 በተደረገ ጥናት የየመን አርሶአደር ከአንድ ሄክታር ፍራፍሬ 0.57 ሚሊዮን ሪያል ሲያገኝ የጫቱ ገቢ ግን 2.5 ሚሊዮን ሪያል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ጫት የሚበቅልበት 8ሺህ ሄክታር በ2000 ዓ.ም 103 ሺህ ሄክታር ደርሷል፡፡ ኢትዮጽያ በምትልከው ጫት በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እያገኘች በመሆኑ እንደ ቃሚው ሁሉ የእርሻ መሬቱም ግዛቱን እያሰፋ መጥቷል፡፡
 

የጫት አርሶ አደሮቹም በየግዜው ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው ፤ ከፍተኛ ገቢ አግኝተንበታል … አነስተኛ ውሃ ነው የሚፈልገው… የማይበጠስ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቁርኝት አለው / በሰርግ፣ በለቅሶ፣ በጸሎት ወዘተ ወቅት ይቃማል / … እንደ ሌሎች ሰብሎች ጉልበታችንን አይበላም… እንደ ምግብም ያገለግላል… ወዘተን የሚገልጹት በታላቅ መተማመን ነው ፡፡ 
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ  አንድ ተጠቃሽ ቀልድ ትዝ አለኝ ፡፡ አንዳንዶች እውነት ነው ቢሉትም እኔ አስተማማኝ መረጃ ባለማግኘቴ ጉዳዩን ብቻ አነሰዋለሁ ፡፡ ሀረር ውስጥ በቀረበ አንድ የ ‹ ልጅ ቀለብ ይቆረጥልኝ › ክስ ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን ወርሃዊ የደመወዝ ገቢ መሰረት በማድረግ ቀለብ እንዲቆረጥ ውሳኔ ይሰጣል ፡፡ ሆኖም ተከሳሽ በፍርድ ቤት የተቆረጠበት የገንዘብ መጠን ፈጽሞ አልዋጽልህ ይለዋል ፡፡ ስለሆነም የይግባኝ አቤቱታ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ያቀርባል ፡፡ ተከሳሹ በይግባኝ አቤቱታው ላይ ቅሬታውን ሲያሰማ ‹‹ የተከበረው ፍርድ ቤት በዚህ የኑሮ ውድነት ደመወዝ ከምግብና ከበርጫ እንደማታልፍ እየታወቀ …. ›› ብሎ በመናገሩ ፍርድ ቤቱ  የቀለብ መጠኑን ሲወስን  ‹‹ በርጫን ›› ግምት ውስጥ ማስገባት እንደነበረበት በአጽንኦት ተከራክሯል ፡፡  
ታዲያ ጫትንና እንደ አንዳንዶች አገላለጽ ‹  ጫታም ትውልድን › እንዴት ነው ማረቅ  የሚቻለው ?  ሲሰድቡትም ደስ የሚል ፣ ሲቅሙትም ደስ የሚል ነገር እንደምን ማጥፋት ይቻላል ? ለምሳሌ ጫትን ሳንቲም አድርገን ብንወስደው በሁለቱም ፊቱ አንድ አይነት ምስል ነው ያለው ፡፡ ወይ ጎፈር ወይ ዘውድ፡፡ ሁለቱንም ምስሎች በግድ እንኳን ብናጠፋ ሳንቲሙ ሳንቲም የመባሉ ጉዳይ ያበቃለታል፡፡  ጫት የማይነገር ከፍተኛ ክብር እንዳለውም ማወቅ ይገባል፡፡ የውጭ ምንዛሪ በማምጣት የቡና ተከታይ በመሆኑ እስካሁንም የብር ሜዳሊያ አጥላቂነቱን የነጠቀው ምርት የለም፡፡ ወደፊት የኢኮኖሚ ዋልታ በርጫ በርጫ… ተብሎ አይዘፈንለትም ብሎ መከራከር ጠባብ ዕድል እንደመያዝ ያስቆጥራል፡፡

‹ ለሁሉም ግዜ አለው ! › የተሰኘውን የጠቢቡ ሰለሞንን ምሳሌ የተዋሰው የሚመስለው ‹ ጫት › በኢትዮጽያ ሌላ ታሪክ መፍጠር ችሎ እንደነበር ስንቶቻችን እናውቃለን ?  ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ ነውና አጭር ትረካ ላስከትል …

 በአንድ ወቅት ዶ/ር እያሱ ኃ/ስላሴን ለማነጋገር ካሳንችስ ወደሚገኘው ክሊኒካቸው አምርቼ ነበር ፡፡ ሀኪሙ በመደበኛ ከሚሰጡት የህክምና አገልግሎት ውጪ በስነ ተዋልዶና በኤችአይቪ ዙሪያ ምሽት አካባቢ ለህብረተሰቡ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ በተጨማሪም የምርምር ስራዋችን ያከናውናሉ፡፡ በወቅቱ እኔን የሳበኝ በጫት ቅጠል ላይ ያደረጉት ምርምር ነበር ፡፡ መጀመሪያ በኢትዮጽያ ጫት በሚበቅልባቸው አካባቢዋች በመዘዋወር የጫትን አጠቃላይ ባህሪ አጠኑ፡፡ በተለይም የአደንዛዥነቱና የምርቃና ደረጃው ምን ያህል ነው ?  አንዱ ከሌላው እንዴት ይለያል ?  የሚለውን ማለት ነው፡፡ እሳቸው እንደነገሩኝ ጫት ከተቆረጠ ከ48 ሰዓታት በኃላ የማነቃቃት ኃይሉን ያጣል ፡፡ ከዚህ አንጻር ጫት ከነማሪዋናና ኮኬይን ጋር ተጨፍልቆ የሚሰደበውና የሚወገዘው አለኃጢያቱ ነው እንዴ ?  የሚል ጥያቄ ማንሳት ነውር የለውም ፡፡

እናም በአንጻራዊነት ለስላሳ ከሚባለው ዕጽ የምርምር ውጤታቸውን ይፋ አደረጉ ፡፡ የጫት ቪኖ ተሰራ !! የቪኖው የአልኮልነት መጠን ከአስካሪ መጠጦች ደረጃ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ነበር ፡፡ ይህንንም ደረጃ መዳቢዋች በመሄድ እንዲረጋገጥ አድርገዋል፡፡ እኔም ታሽገው ከተቀመጡት ቪኖዋች ለሙከራ ስለተሰጠኝ ማጣጣም ችያለሁ ፡፡ ወደ ጫት የተጠጋው መዓዛ በስሱ ነው የሚታይበት ፡፡ እንደ መደበኛው ቪኖ ጉሮሮ ላይ የሚያግደው ነገር ሳይኖር ቁልቁል ከብለል ይላል ፡፡ የዶክተሩ እቅድ ሰፊ ነበር ፡፡ ምርቱን በስፋት ወደ ውጭ በመላክ ለራሳቸውም ሆነ ለሀገር የገቢ ምንጭነት ማሳደግ ፡፡ ሆኖም ከመድሃኒትና ቁጥጥር መ/ቤት ጋር በግዜው መግባባት ላይ መድረስ አልቻሉም ፡፡ ዛሬ ባለሙያው ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ አላውቅም ፡፡ በመሆኑም በኢትዮጽያ የተፈጠረው የጫት ቪኖ እውቅና ሳያገኝ ተድበስብሶ ቀርቷል ፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ እነ የመን ኮፒ ፔስት ከተጠቀሙ ሌላ የጭቅጭቅ ምዕራፍ ሊከፈት አይደል ? ይልቅ ዛሬ- ዛሬ በጣም የምታስፈራው ቻይና ናት ፡፡  ሀገራችን ብቅ ጥልቅ የሚሉት ዜጎቿ አሳምረው መቃምና መጨበስ ጀምረዋል ፡፡ ታዲያ ተከታዩ ጉዳይ ቪኖ አይደለም የድሃ ውስኪ መስራት ላይ አያነጣጥርም ማለት አይቻልም ፡፡ 

ዞሮ ዞሮ የቪኖው ሀሳብ  በራሱ ገራሚ ነው ፡፡ ምነው ቢሉ ቪኖው በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ቅቡልና ካገኘ  ‹ አደገኛ › ፣ ‹ እርኩስ › ፣ ‹ የጥፋት ቀለሃ ›  ወዘተ የሚሉ ቅጥያዋችን አራግፎ ለውዳሴ ይበቃል ፡፡ ቪኖው አሪፍ ጣዕም ስላለው እንደ ‹ ወይን ሃረጊቱ › እና የ ‹ ሾላ ፍሬነሽ › ሊገጠምለት ወይም ሊዘፈንለት ላለመቻሉስ ርግጠኛ የሚሆን ማን አለ ?

የጫት ብይን ምን ይሁን ታዲያ ?
.  እየተወገዘ የሚለመልም
.  እየተነቀፈ አጋር ያደመቀው
.  ሳይዋጋ የሚማርክ  ፡፡

Saturday, June 23, 2012

አስገራሚው የ ‹ ከቤ እና የእሙሙ › ፌስቲቫል !‎!‎




ጃፓኖች ትሁትና አይናፋር ናቸው፡፡ ወግ አጥባቂዋች ስለሆኑ በግልጽ ደፍረው ስለ ወሲብ ለመወያየት የሚያስቸግራቸው ይመስላል፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች እንዲህ ብናስብ አልተሳሳትን ይሆናል፡፡ ግን ስለ ብልት የሚዘፍኑበት፣ የሚለምኑበት፣ የሚቀልዱበት፣ አካፋን አካፋ የሚሉበት ግዜ መኖሩን ለሚያስብ ሊገረም ይችላል፡፡ አላውቃቸውም እንዴ በማለት ?!

የዓለማችን ሀገሮች የራሳቸው የሆነ ልዩ ክብረ በዓል እንዳላቸው ይታወቃል ፡፡

ሳምባ - የብራዚል ፌስቲቫል ሲሆን የሳምባ ዳንስ ውድድር ይከናወንበታል፡፡

ኤል ኮላቻ - የስፔን ፌስቲቫል ሲሆን ገና የተወለዱ ህጻናት ተደርድረው ይዘለላሉ፡፡ ዓላማው ህጻናትን ከኃጢያት ማንጻት ነው፡፡

የጦጣ ቡፌ - በታላይንድ ፌስቲቫል 600 ጦጣዋች 3ሺህ ኪ.ግራም የሚደርስ ፍራፍሬና ቅጠላ ቅጠል እንዲበሉ የሚጋበዙበት ነው፡፡ ዓላማው የራማን ጀግና መምረጥ ነው፡፡

ሆሊ ፌስቲቫል - በህንድ የሚከበር የቀለማት በዓል ነው፡፡ ሰዋች ከኒምና ከተለያዩ ቅጠሎች የቀመሙትን ቀለሞች ይወረውራሉ፡፡ ቀለሙና ፓውደሩ ገንፋንና ትኩሳትን ያድናል ብለው ያምናሉ፡፡

ማስላንታስ - በሩሲያ የሚከበር ነጻ የሆነ የቦክስ በዓል ነው፡፡ ህግ ስለሌለው ግብግቡ የሚያበቃው ተፋላሚው በደም ሲሸፈን ነው፡፡
ላ ቶማቲና - በስፔን በሺ የሚቆጠሩ ሰዋች በቲማቲም ርስ በርስ የሚደባደቡበት ፌስቲቫል ነው፡፡ ይህን ትርዒት 3 መቶ ሺህ ቱሪስቶች ይከታተሉታል፡፡

ሮስዌል - በአሜሪካ ይህ በዓል የሚከበረው ዩፎዋች በሮስዌል ያደረሱትን ጥቃት ለማሰብ ነው፡፡ በዓሉ ሰዋች ልዩ ፍጥረት የሚያስመስላቸውን ማስክ አድርገው በልዩ ልዩ ስፓርታዊ እንቅስቃሴዋች በመወዳደር ነው፡፡

ሃይማኖታዊ መሰረት ቢኖራቸውም በሀገራችንም ጥምቀትና መስቀልን የመሳሰሉ በርካታ ቱሪስት ጠሪ ፌስቲቫሎችን መጠቃቀስ ይቻላል፡፡

ሌላም የትየለሌ ፌስቲቫሎች ሊደረደሩ ይችላሉ፡፡

እነዚህና ሌሎችም ግን ከጃፓን ክብረ በዓሎች ጋር መወዳደራቸው ያጠራጥራል፡፡ በዓሉ የሚያተኩረው በሰው ልጆች አቢይ ብልቶች ላይ ነውና ፡፡ ይህን ክብረ በዓል ድንገት የሚቀላቀል በድንጋጤ ግር ቢለውም እየቆየ ሲሄድ ግን በሳቅ መፈንዳቱና መደሰቱ አይቀርም፡፡ ነገሩ የማይደፈር በመሆኑ በተለይም የጃፓን ቀጣይ ትውልድ ልዩ ሃሳቦችን እንዲያመነጩ ያግዛችዋል ነው የሚባለው፡፡

ቀኑ መጋቢት 15 ነው፡፡

በዕለቱ የወንድንም ሆነ የሴት ብልትን በስሙ ነው የሚጠሩት - አይናፋሮቹ ጃፓኖች፡፡ ለዚህም ነው የፌስቲቫሉ ስያሜም ምንም ሽፍንፍን ሳይደረግ ‹ የወንድ ብልት ፌስቲቫል! ›… ‹ የሴት ብልት ፌስቲቫል ! › እየተባለ የሚጠራው፡፡  ለጽሁፉ አስገራሚነት ፣ ለአውዱ ጥያቄና ማማር ሲባል እኔም ለዛሬ አካፋን አካፋ እያልኩ መጥራት ነበረብኝ፡፡ ግን ከጻፍኩት በኃላ ሸከከኝ ፡፡ የሞራል ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ እናም የወንዱን ‹‹ ከቤ ! ›› የሴትን ‹‹ እሙሙ! ›› እያልኩ የቅጽል ካፓርት ማልበስ አስፈለገኝ፡፡ 
·          
መጋቢት 15 ቀን የከቤ ቀን በተለይ በኮማኪ ከተማ በደማቅ መልኩ ይከበራል፡፡ ከዚህ ክብረ በዓል አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ደግሞ የእሙሙ ፌስቲቫል አለ ፡፡ እነዚህ በዓሎች የ1500 ዓመታት ዕድሜ አላቸው፡፡ የበዓላቱ መነሻዋች ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በአንድ በኩል መሬታቸው ጥሩ ሰብል እንዲሰጣቸው በሌላ በኩል ምርት ብቻ ሳይሆን ልጅ እንዲያገኙ ብልቶችን ወይም የብልት አምልኮዋችን የሚለማምኑበት ስርዓት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ጃፓን በዓለማችን አነስተኛ የወሊድ መጠን የተመዘገበባት ሀገር ናት፡፡ በመረጃው መሰረት 1.37 ህጻናት ናቸው ለአንዲት ሴት የሚደርሱት፡፡ ባለፈው ዓመት ስልጣን የያዘው ገዢ መደብ ሴቶች ተጨማሪ ህጻናትን እንዲወልዱ የሚያበረታታ ስጦታ አበርክቷል፡፡ መመሪያውን ተግባራዊ የሚያደርጉ እናቶች ለህጻናቱ ማሳደጊያ በየወሩ 280 ዶላር ይቆረጥላቸዋል፡፡

በእሙሙ ፌስቲቫል ቀን እናቶች ልጆቻቸውን አዘንጠው በፕላስቲክ፣ በእንጨት ወይም በተለያዩ ቁሳቁሶች የተሰሩ ትናንሽ የእሙሙ ምስሎችን ይዘው በዋናው አደባባይ እንዲገኙ ያደርጋሉ፡፡ 40 የሚደርሱ ሰዋች በትልቅ ቅርጽ የተሰራውን እሙሙ  በቃሬዛ መልክ ይዘው ይዞራሉ፡፡ በዕለቱ እናቶች ለልጆቻቸው ጤንነት ይጸልያሉ፡፡ በዓሉ ላይ የተለያዩ ምግቦችና ቢራዋች ይዘጋጃሉ፡፡ በበዓሉ ማብቂያ ላይ ነጭና ሀምራዊ ጣፋጭ ሩዝ ሰዋች ላይ ይረጫል፡፡

በከቤ ፌስቲቫል ቀን ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ጃፓናዊያንና የውጪ ቱሪስቶች በቦታው ይታደማሉ፡፡ በኛ ሀገር በክብረ በዓል ቀን በየመንገዱ፣ ድልድይ፣ ቆርቆሮ፣ የስልክ እንጨት ወዘተ ላይ የሚንጠለጠለው ባንዲራ ነው፡፡ ጃፓኖች በዚሁ ዕለት ከላይ በተገለጹት ቦታዋች ላይ የሚያንጠለጥሉት ሌላው ቀርቶ በአፍንጫቸው ላይ የሚያስሩት የወንድን ብልት ነው ፡፡

ይህ በዓል የሚከበረው እኛ ሀገር ቢሆን ከባንዲራው ጎን ጥቅሶችና መፈክሮች መኖራቸው ግድ ይላል፡፡ እንደው ሳስበው
 ‹‹ ከቤ ለዘላለም ይኑር ! ›› የሚል ጥቅስ ብዙ ሰው የሚይዘው ይመስለኛል፡፡
‹‹ ያለ እሙሙ ተሳትፎ
እንኳን አብዮቱ
አይነጋም ሌሊቱ ›› የሚል ሞጋች ስነ ቃልም ከወግ አጥባቂ ሴቶች ክንድ ላይ ይጠበቃል፡፡
‹‹ አርሜ ኮትኩቼ ያሳደኩት ከቤ
  አምላክ ይመስገነው ደረሰ ከሃሳቤ ›› የሚል መፈክር ደግሞ በአንዳንድ ፍንዳታዋች እጅ ቢጠፋ እንኳን እንደ መዝሙር ሲደጋግሙት ሊሰማ ይችላል፡፡
‹‹ የከቤና የእሙሙን  አቅም አሟጦ በመጠቀም የልማታችንን ቀጣይነት እናረጋግጣለን ! ›› የሚል ካድሬያዊ መልዕክት ይጠፋል ማለትማ የሰማይ ስባሪ የሚያህል ውሸት እንደ መናገር ያስቆጥራል፡፡
ተረቶቻችን፣ አባባሎቻችን፣ ዘፈኖቻችን፣ የወሬ ማጣፈጫዋቻችን፣ ቀረርቶዋችን ሁሉ ከነ ከቤ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተጋመዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሌላው ቢቀር
ራሰ በረሃ አንገተ ክርክር
ሁለት ልጆች ይዞ በጫካ የሚኖር !
የተባለችውን እንቆቅልሽ ከልጅነቱ ሳይሰማት ያደገ ማን አለ ?  ከፍ እያልን ስንሄድ ተረትና እንቆቅልሾቻችንን በሰምና ወርቅ አጠናክረናቸዋል፡፡ ካስፈለገም የአግቦና አሽሙር ብቃታችንን ከኃላ ኪሳችን እናወጣለን፡፡ ምናለፋችሁ ፌስቲቫሉ ቀውጢ የሚሆን ይመስለኛል፡፡
·          
እናላችሁ በትልቅ ቅርጽ የተሰራው ከቤ ርዝመቱ 25 ሜትር ሲሆን ክብደቱ 280 ኪ.ግራም ይመዝናል፡፡ ቪንሚንሻ ይሉታል ጃፓኖች ይህን ጣዖት፡፡ ይህን ቅርጽ በመሸከም ታዋቂውን አደባባይ መዞር፣ ማጨብጨብ፣ መዘፋፈን ፣ መጸለይ፣ በቅርጹ የተሰራ ሻማ ማብራት የተለመደ ነው፡፡ ድርጊቱ ለአንድ ወይም ለአንድ ተኩል ሰዓታት ይፈጃል፡፡ የጥንት ጃፓኖች የከቤው አደባባይ የዕድገትና የልማት ሁሉ መሰረት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በሌላ አነጋገር እናት የሆነቸው መሬት፣ አባት በሆነው ሰማይ ታረግዛለች፡፡ ይህን ተምሳሌት የሚያቀነቅን ፈላስፋ ማን ነበር ?

በመሆኑም ልጅ የሌላቸውም ሆኑ ተጨማሪ ልጅ የሚፈልጉ ሁሉ በክብረ በዓሉ ላይ በለመለመ ተስፋና ፍቅር ይገኛሉ፡፡ ክብረ በዓሉ በርካታ ቱሪስቶችን እየሳበ በመሆኑ ሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ታገኛለች፡፡ ነጋዴዋችም በእሙሙና  በከቤ ቅርጽ የተሰራ ከረሜላና ቸኮላታ ይቸበችባሉ፡፡ በእንጨትና በፕላስቲክ ቅርጻ ቅርጾች የተሰሩ ብልቶች፣ የጆሮ ጌጦች፣ የሲጋራ መተርኮሻዋች ይሸጣሉ፡፡ በተለይም ወጣት ሴቶች በወንድ ብልት የተሰራን ከረሜላ በመምጠጥ ራሳቸውን ያዝናናሉ፡፡ የሚገርመው የሁለቱም ጾታዋች ብልቶች ዋጋ እኩል 600 የን ያህል  መሆኑ ነው፡፡ በርካታ ቱሪስቶች ፌስቲቫሉ በተለይም ልጅን ይሰጣል የሚለውን ሀሳብ ባይቀበሉትም ቢራ በመጠጣትም ሆነ ቅርጹን በመምጠጥ፣ በሃገሬው ደስታና እምነት በመደሰት እንዲሁም ከከቤ ጋር የተያያዙ ቀልዶችን በማውራት ይዝናናሉ፡፡

በማይደፈር ነገር መዝናናት ብልግና ነው ሀሴት ?

መቼም የነከቤ ፌስቲቫል ይኑረን  ባይባልም ፣ ጀግንነት ነው እየተባለ የሰው ከቤ የሚቆረጥበትና  የልጃገረዶችን እሙሙ  የሚሰፋበት ሀገር ውስጥ ከመኖራችን አንጻር ለዚህ ወሬ ቢያንስ አክብሮት ሊኖረን ሳይገባ አይቀርም፡፡

ወጣቶች በከቤ የተሰራ ከረሜላ ሲመጡ



ረጅም ዕድሜ ለከቤና ለእሙሙ !!