ከዓለማችን ፈጣጣ ህግ አንዱ አፓርታይድ ነበር
፡፡ የዘር ልዩነትን የሚያራምድ ፓሊሲ በመደንገጉ ፡፡ በህጉ መሰረት ደቡብ አፍሪካዊያን ነጭ፣ ባንቱ፣ ጥቁር አፍሪካና ኤሽያ/ ህንዶች
ተብሎ በተከፈለው መሰረት ብቻ ይማራሉ…ይሰራሉ.. ይኖራሉ…
ይህ ጨቋኝ ህግ ማንዴላንና ጓደኞቻቸውን ለ ‹
እረ ጥራኝ ደኑ ! › አነሳሳ፡፡ ክፉው ዘመን ከ 1948 እስከ 1994 አካባቢ ሲቆይ 21 ሺህ ዜጎችን ጨፍጭፏል ፡፡ ሁሉም የጥቁር
ት/ቤቶች እንግሊዝኛንና የአፍሪካን ቋንቋ በእኩል መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለው ተቃውሞ ለማሰማት ከወጡ 20ሺህ ተማሪዋች መካከል
700 ያህሉ የጥይት ራት ሆነዋል ፡፡ በሶዌቶ ህጻናት በጥይት ሲፈነገሉ የተመለከተ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ የደም እንባ አፍስሷል ፡፡
ነጭ የደቡብ አፍሪካ ፓሊሶች ወጣቶችን በመርዘኛ ውሾች እያስነከሱ ሲዝናኑም ዓለም አልቅሷል ፡፡
የጸረ አፓርታይድን እንቅስቃሴ የሚመሩት ማንዴላና
ጓደኞቻቸውም ለረጅም ዓመታት በሮበን ደሴት በእስር ማቀዋል ፡፡ በህዝቡ
ከፍተኛ መስዋዕትነትና በውጩም ዓለም ግፊት ክሌርክ በፓርቲው ላይ የጣሉትን ዕገዳ ጨምሮ ማንዴላን ለመፍታት ተገደዱ ፡፡
አዲሱ ህገ መንግስትም በፊርማ ጸደቀ ፡፡ በኃላም ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ስልጣኑ ለተገቢው ህዝብ ደረሰ ፡፡
ዓለምና ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን በቀል ቢፈሩም
ማንዴላ ‹‹ ይልቅ ይቅር ተባብለን ብሄራዊ እርቅን እናንግስ ››
አሉ ፡፡ ያልተጠበቀና የማይታመን የጀግንነት ውሳኔ ነበር ፡፡ በዚሁ መልኩ አፓርታይድ በርህራሄ ተሸንፎ ራሱን ገደለ ፡፡ በጣም
ተጸጽቶም ‹ ጉድጓዴን በጣም አርቃችሁ ቆፍሩ ! › ብሎ በተወው የኑዛዜ ወረቀት መሰረት ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል ፡፡
ሰሞኑን የሞተው አፓርታይድ ተነስቶ ይሁን ወይም
እሱ ሲሞት አስረግዞት የነበረው ክፋት በውል ባይታወቅም ሀገሪቱ አስደንጋጭ ጭፍጨፋ አስተናግዳለች ፡፡ በማሪካና በሎንሚን ፕላቲኒየም
ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ዘወትር ጥልቅ ግድጓድ ውስጥ ከፍተኛ ስራ ብንሰራም የምናገኘው አነስተኛ በመሆኑ ደመወዝ ይጨመርልን
የሚል ጥያቄ ያነሳሉ ፡፡ የሰራተኞቹ ደመወዝ ከ 4 እስከ 5 ሺህ ራንድ የሚደርስ ሲሆን ለጉልበታቸው የሚመጣጠነው ዋጋ 12 ሺህ
500 ራንድ መሆኑን ገልጸው ነበር ፡፡
ታዲያ ምን ዋጋ አለው ? ፓሊሶቹ ቀጥታ ወደ ሰራተኞቹ በመተኮስ የ 34 ሰዋችን ህይወት አጠፉ ፡፡
78 ቱ ሲቆስሉ 259 ያህሉ እስር ቤት ተወረወሩ ፡፡ አማረብኝ ብለው ደግሞ ‹‹ የተኮስነው ራሳችንን ለመከላከል ነው ›› የሚል
ምላሽ ሰጡ ፡፡ መከላከል እንዲህ ነው እንዴ ? ሲባሉ ‹‹ መጀመሪያ
ውሃ፣ አስለቃሽ ጋዝና የመሳሰሉትን ተጠቅመን ነበር ›› ብለው እርፍ፡፡ እንደው መቼ ይሆን አፍሪካ ከእንደዚህ ዓይነቶቹ
ማፈሪያ ፓሊሶች ተግባር የምትጸዳው ? የአፍሪካ ፖሊሶች ዘወትር ስልጠና
ወሰደን ይላሉ - ግን መቼ ይሆን ስልጠናው ህዝብን የማክበር ምዕራፍ ላይ የሚያደርሳቸው ? የሰው ልጅ በተለመደው አልሰር፣ ስኳር ወይም ሌላ በሽታ ይጠቃል እንጂ
እንዴት የማመዛዘን ክፍተት ሰለባ ይሆናል ፡፡ ለሀገር ክብር ሲፋለሙ ስለወደቁ የዓለማችን ጀግኖች ከመስማትና ከማንበብ ይልቅ እንዴት
Made in ራሳችን በሚሉት የዱላና ጥይት ተረቶች ይበልጥ ይነቃቃሉ ?
በእውነት ተስፋ ያስቆርጣል ፡፡ አንዳንድ ሰልፈኞች
ዱላ፣ ቆንጨራና ጦር ይዘው ቢታዩም እነዚህን የሚመክተውና ጸጥ የሚያደርገው
ጥይት ነው ብሎ ተመጣጣኝ ትርጉም መስጠት በእውነት ያሳፍራል ፡፡ ለነገሩ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ ፖሊሶች
አትኩሮ ላያቸው - ወፍራም ስድብ
ሰው አገኘው ብሎ ለሚያስረዳው - ወፍራም ኩርኩም
የመንግስት ያለህ ብሎ ለሚጮኀው - ጥይት የሚያቅሙ
ናቸው ፡፡
አሷፊ ፓርላማ፣ አጣሪ ኮሚቴ ወይም የእንባ ጠባቂ
ድርጅት ድንገት ከጠየቃቸው ‹ በህጉ መሰረት ነው የሰራነው › ይላሉ ፡፡ ይህ መልስ እንግዲህ ሳያስፈቅድ የጮኀ ሌላ ትርጉም እስካልተሰጠው
ድረስ ሞቱን በራሱ ግዜ የጠራ ፍጡር ነው ወደሚለው የቃላት መፍቻቸው የሚያደርሰን ይሆናል ፡፡ ይህን ዝነኛ ወታደራዊ መፍቻ መጨረሻውን
አያለው ብላችሁ ከተጓዛችሁ ፖሊሶች ልክ እንደ ማዕረግ ሁሉ በአስተሳሰብም እንደሚከፋፈሉ ትረዳላችሁ ፡፡ በመሆኑም ይላል ቃላት መፍቻው ‹ አንዳንድ ፖሊሶች ማለት ከጥይት የተሰሩ ጥቁር ድንጋዮች ናቸው
› ፡፡ ይህ ነጻ ትርጉምማ መጨረሻው ሊሆን አይችልም በሚል ሌላ
‹ እንዴትን ? › ያነሳ ደግሞ በመጽሀፉ ማገባደጃ ገጽ ላይ ‹ ህልምና ቋንቋ እንደፈቺው ነው የሚባለው አባባል የዋዛ አይደለም › ከሚል ማጣቀሻ ጋር ይላተማል ፡፡
እና ተስፋ መቁረጥ ብቻ ሳይሆን አሳምረው መፍራት
ይጀምራሉ ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች እየጮኀ እንጀራ የጠየቀውን ድሃ ሰራተኛ በላስቲክ ጥይት ቀጥ ማድረግ ይሳናቸው ነበር ? ወደ ሰማይ መተኮስ ነው የሚቀድመው ወደ ሰው ? ጥይቱን ወደ ሰማይ በመተኮስ ብቻ መበተን እንደሚቻል አያውቁም ወይስ አልፈለጉም
?
የደቡብ አፍሪካው የሩምታ ጭፍጨፋ የሀገራችንን
አነጣጥሮ ገዳዮች አስታወሰኝ ፡፡ ምርጫ 97ትን ተከትሎ በኢትዮጽያ 193 ሰዋች በጥይት ሲሞቱ 763 ያህል ቆስለው ነበር ፡፡ በወቅቱ
ጉዳዩን እንዲያጣራ የተሾመውና በአቶ ፍሬህይወት ሳሙኤል የሚመራው ቡድን
‹ መንግስት ያልተመጣጠነ ርምጃ ወስዷል ! › በማለት
ሪፖርቱን አቀረበ ፡፡ ቀደም ብሎም ሪፖርቱን እንዲያለሳልሱ በመንግስት ቢነገራቸውም ሰብዓዊና ፍትሃዊነት የሚሰማቸው ሰዋች ያባ ቢላዋ
ልጅ ነን አሉ ፡፡ በርግጥ በሪፖርቱ አንስማማም ብለው ሸርተት ያሉ አባላትም ነበሩ ፡፡ ዞሮ ዞሮ ሪፖርቱ ‹ ተቃውሞ የሚበተንበት
ቀላል አማራጭ የለም እንዴ ? የፖሊስ አመለካከትስ ለምንድነው የማይቀየረው
? › የሚል አሽሟጣጭ አስተያት አቅርቦ ነበር ፡፡
የኛን ሪፖርት ለደቡብ አፍሪካዊያን አስቀድመን
በግልባጭ ብናሳውቅ ኖሮ ምን ያህል በጠቀማቸው ፡፡ ለነገሩ አርቃችሁ ቅበሩኝ ያለ ስርዓት እንደ እባብ አፈር ልሶ ይነሳል ብሎ የገመተ
ማን አለ ? በጅምላው የእኛን ጨምሮ የአፍሪካ ፖሊሶች የአመለካከት ችግር ካልተቀየረ ነገና ከነገ ወዲያም የሌሶቶውን ጭፍጨፋ ሃትሪክ ለማድረስ
የሚሯሯጡ ጭፍኖች ይፈጠራሉ ለማለት ያስደፍራል ፡፡ ጭንቅላታቸው ውስጥ
የተጠራቀመውን አለቃ ! ታዘዝ ! ጥይት ! ተኩስ ! ግደል ! አቁስል
! ወዘተ የተሰኙ መራራና የታሸጉ ቃላቶችን ገላልጠው መፈተሸ ይኖርባቸዋል ፡፡ ህዝብ ! ሰብዓዊ ክብር ! ርህራሄ ! ወገን ! ድሃ
! ለምን ! የሚሉ ሃሳቦችን ከመራራዋቹ ጋር ማዋሃድ ባይችሉ እንኳን እንደ ኮዳ ወይም ጥይት ማስቀመጫቸው ከቻሉ ጭንቅላታቸው ውስጥ ካልቻሉ ወገባቸው ላይ አንጠልጥለው መዞር
ይጠበቅባቸዋል ፡፡ ‹ በለው ! ግደል ! › የሚል አረመኔ አለቃ ቢያጋጥም እንኳ ሀሳቦቹ ‹ ለምን ! ወገንህን ! › ብሎ ያስታውሳቸዋልና
፡፡
ለማንዴላና ለእውነተኛ ታጋዮቹ በንጹሀን ላይ የደረሰው
ፍጅት ሰቆቃ ይፈጥራል ፡፡ እርጅና ተጫጭኗቸው በገጠር ሰፈራቸው የሚኖሩት ማንዴላ ስልጣናቸውን ሲያስረክቡ የመጨረሻ ንግግራቸውን
በም/ቤቱ ውስጥ እንደሚከተለው ተናግረው ነበር ‹‹ የህገ መንግስታችን የመርሁ ምንጭ የሰው ልጆች ክብር ላይ የተመሰረተ ነው ፡፡
የሰው ልጅ ክብር መልካምነት ላይ መስማማት ይኖርብናል ፡፡ ታሪካዊ ባላንጣችን ከነበረው አፓርታይድ ወደ ዴሞክራሲ ያደረግነውን ሰላማዊ
ሽግግር የተቀበልነው ለሰው ልጆች ካለን መልካምነትና ይህንኑ ማግኘት ከሚገባው ተገቢነት አኳያ ነው ፡፡ ዴሞክራሲያችን ለሁሉም በጎ
ፍሬ ማምጣት ይኖርበታል ፡፡ በተለይም ለድሆችና ትኩረት አጥተው ለቆዩት ››
ይህ አደራ ለዚያውም ሰላማዊ በተባለው ዘመን በአይጠ
መጎጦች ተበልቷል ፡፡ የፍቅር፣ ርህራሄና ነጻነት ካባ የደረቡት ማንዴላ በድርጊቱ ምን ያህል እንደሚጎዱ ማሰብ ከባድ አይሆንም ፡፡
Long Walk to Freedom በተባለው መጽሀፋቸው ‹‹ ረጅም ጎዳና የተጓዝኩት ነጻነትን ለማግኘት ነው ፡፡ ብዙ ተጨባጭ ውጤቶችን
አግኝተናል ፤ አሁን ያረፍኩት ለግዜው ነው ፡፡ ረጅም ጉዞዬ ግን ገና አልተጠናቀቀም ›› ብለው ነበር ፡፡
የሚገርም ትንቢት ተናግረዋል ፡፡ በፍቅር፣ በፍትህና
በአድልዋ ላይ የሚደረገው ጉዞ ገና የተጠናቀቀ አይመስልም ፡፡ አዝኛለሁ በማለት ምርመራ እንዲደረግ ያዘዙት ጃኮብ ዙማ አዲስ ትንሳኤ
ያስገኛሉ ወይስ አፈሩን አርግፎ ራቁትን በከተማው ዳር ለቆመው አፓርታይድ ጂንስና ካፖርት ያቀብላሉ ?
No comments:
Post a Comment