Sunday, May 27, 2012

‎በኢፋግ ያረጉት ሶስት ህጻናት‎





በነሄለን ቤት- ሄለንን ጥበቃ



ወደ ሰሜን የሚገኙትን ብሄራዊ ፓርኮች ለማየት ባቀናሁበት ወቅት አንድ አስገራሚ ዜና ሰማሁ፡፡
‹‹ በኢፋግ ሶስት ህጻናት አረጉ !! ›› የሚል
‹‹ ምን ?! ›› -  ድንጋጤ !
‹‹ በኢፋግ ከተማ ሶስት ህጻናት አረጉ !! ››
‹‹ እንዴት ?! ›› - ጥርጣሬ !
‹‹ መንፈስ ቅዱስ ቀረባቸው ፡፡ ወደ ሰማይ መጠቁ ፡፡ ተልዕኳቸውን ተቀብለው ወረዱ ››
‹‹ ህጻናት ? ለዛውም ሴቶች ?! ከዛስ ? ›› - ብዥታ !
በርግጥም ይህ ዓይነት ያልተለመደ ዜና የሰማ ሁሉ መደንገጡ፣ መፍራቱ፣ መደሰቱ፣ መጠራጠሩና በቅጽበት የተምታታ ሀሳብን እንደ አሸን ማራባቱ የሚጠበቅ ነው ፡፡ የዚህን ወሬ ጫፍ ለመጨበጥ በጣም ጓጉቼያለሁ፡፡ ሁኔታው በመጽሀፍ ቅዱስ የተገለጹትን የፈጣሪ ተአምራትና የቅዱሳን ገድሎችን ለማስታወስ ብሎም ለማነጻጸር ይጋብዛል ፡፡

v                           
መኪናችን አዲስ ዘመን ከተማ ለመድረስ የተወሰነ ርቀት ሲቀራት ዳር ያዘች፡፡ ወደ ውስጥ ከመዝለቃችን በፊት ከአርሶ አደሩ መረጃ ለመሰብስብ ሞከርን ፡፡ ተመሳሳይ ሀሳብ ነበር ያዳመጥነው ፡፡ ድርጊቱ እውነት መሆኑን ነገር ግን ህጻናቱን ማየት የሚቻለው በዕለተ ሰንበት ቤተክርስትያን መሆኑን ፡፡ እናም በማግስቱ ለመመለስ ወስነን ፊታችንን ወደ ጎንደር አቀናን ፡፡

v          

ሰው ያስባል እግዚአብሄር ይፈጽማል እንዲሉ ቀድሞ ይዘነው የነበረውን ቀጠሮ በስራ ጫና ምክንያት ለማክበር አልቻልንም ፡፡ ቢሆንም ከ14 ቀናት በኃላ በዕለተ አርብ በኢፋግ ከተማ ተገኝተናል ፡፡ ኢፋግ ከአ/አበባ በ625 ኪሜ አካባቢ የምትገኝ የፎገራ ወረዳ አካል ናት ፡፡ በከተማው ዳገታማ ቦታ ላይ የሚገኘው የስላሴ ቤ/ክርስትያን ከተለያዩ አካባቢ በመጡ ምእመናን ተጨናንቋል፡፡ ወደ ግቢው ጫማ አድርጎ መግባት በፍጹም የተከለከለ በመሆኑ ጥቁር እንግዳውን ከነዋሪው፣ ከተሜውን ከአርሶአደሩ ለመለየት ቀላል መንገድ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ ጥቁር እንግዳውና ከተሜው በጠጠሩ ላይ እንደ ልብ መራመድ ስለማይችሉ እንደ አካል ጉዳተኛ ሸብረክ፣ እንደ ብሬክ ዳንሰኛ እጥፍጥፍ እያሉ ነው የሚጓዙት ፡፡

ግቢውን አንድ ግዜ በዝግታ ዞርኩት፡፡ ብዙዋች ጸበል ለማግኝት ይሻማሉ፡፡ የብዙዋች ፊት በእምነት ስለተዥጎረጎረ ፊታቸው ላይ የሆነ ስዕል ማግኝት ይቻላል፡፡ አንዳንዶች ግን አይናቸውን ብቻ ስላስቀሩት ድንገት ሲታዩ ያስደነግጣሉ፡፡ በስተጀርባ የሚጓግሩ፣ የሚጮሁና የሚለማምኑ ሰዋች አሉ፡፡ ግቢው ውስጥ ከሚታየው ምዕመናን የአይነስውራንና የአካል ጉዳተኛ ድርሻ ቀላል አለመሆኑ በራሱ የሆነ ነገር መኖሩን ያመላክታል፡፡

የግራ ፊቱ በጣም ያበጠ ወጣትና አይነስውር የሆኑ እናት ጋ ቀረብ ብዬ ጥያቄዬን ቀጠልኩ፡፡ ሁለቱም ከሩቅ ቦታ የመጡት መንፈስ ቅዱስ ባደረባቸው ሶስት ህጻናት ለመፈወስ መሆኑን ገለጹልኝ ፡፡ ሌሎቹም ተናገሩ ‹‹ አይናቸው የበራ፣ እግራቸው የተቃና፣ ከውስጥ ህመማቸው የዳኑ ሰዋች ጥቂቶች አይደሉም ››

መረጃው ሚዛናዊ እንዲሆን ወይም ማረጋገጫ ይገኝ ዘንድ ዲያቆኖችና ቄሶችን ማነጋገር አስፈላጊ ነበር ፡፡ ‹‹ በዚህ ጉዳይ መረጃ መስጠት አልችልም ›› አለኝ አንድ ዲያቆን

‹‹ እኔ መናገር አልችልም ፤ ሃላፊውን አስፈቅድ ›› ብሎ ወደ አንድ ሰው ጠቆመኝ - አንድ ቄስ ፡፡ ትልቅ ማስታወሻ ላይ የሆነ ነገር የሚጽፉት ቄስ ሊያናግሩኝ እንደማይችሉ ገለጹልኝ ፡፡ ስራ ስለበዛባቸው ይሁን ወይም በጉዳዩ ዙሪያ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ግን መለየት አልቻልኩም፡፡ በአንድ እጄ ጫማዬን በሌላኛው ማስታወሻ ደብተሬን ይዤ ሸብረክ ላለማለት አፈር እየመረጥኩ ከቅጥር ግቢው ወጣሁ ፡፡
     
v          

የሶስቱን ህጻናት ተአምራት ለመመልከት ከተቻለም ለመፈወስ በሺህ የሚቆጠር ህዝብ በየቀኑ ወደ ስላሴ እየጎረፈ ቢሆንም ህጻናቱ በተለያዩ  ምክንያት ወደ ቤ/ክርስትያን እንዳይመጡ መከልከሉ ይነገራል፡፡ ህዝቡ ግን ጠንካራ እምነትን ይዞ ወደ ግቢው ይጎርፋል ፡፡ ህጻናቱ ካረጉ በኃላ የተመለሱት ብሎም ከክልከላው በፊት ተዓምር ያሳዩት በዚሁ ቦታ በመሆኑ በራሱ ውጤት እንደሚኖረው ያስባልና፡፡ የተሻለ መረጃ የሚገኘው ከህጻናቱ ወይም ከቤተሰባቸው ወይም ፈውስ ካገኙ ሰዋች እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ፡፡ ተፈወሱ ስለተባሉ ሰዋች ብዙዋች ተመሳሳይ አስተያየት ቢሰጡንም ሰዋቹን በአካል ማግኝት እንደማንድችል ተረድተናል፡፡ እናም የህጻናቱን ቤት ማፈላለግ ጀመርን፡፡

v     

እነሆ በአንደኛዋ ቤት ተሰይመናል፡፡
የዚህችኛዋ ቤት ከሁለቱ ይለያል፡፡ ቤቱ ሻይ - ዳቦ የሚሸጥበት በመሆኑ ከቤ/ክርስትያን የተመለሰው ህዝብ በሙሉ ሻይ እጠጣለሁ በሚል ሰበብ ቤቱን ያጣብባል፡፡ ከውጭ ደግሞ ቦታ ያጣበቡ አያሌ  ሰዋች ተኮልኩለው ይታያሉ፡፡ ጠባብዋ ቤት በመፋጠጥና በሹክሹክታ ግላለች ፡፡ ውጭ ያለው ህዝብ ደግሞ ቤቱ እንዲለቀቅለት ይንጫጫል፡፡ ልጅ እግሩ አስተናጋጅ ሻይ ጠጥተው የጨረሱትን ‹ እባካችሁ ልቀቁልን ! › ለማለት የደፈረ አይመስልም ፡፡ ግራ በመጋባት ወደ ጓዳና ሳሎን ገባ ወጣ ይላል፡፡ ህዝቡ ይህን አነስተኛ ቤት ለምን እንዳጣበበው አሳምሮ ያውቃል፡፡ ሞባይሌ ውስጥ የሚገኝውን ካሜራ ከፍቼ ጆሮዋቼን ግራና ቀኝ ቀስሬያለሁ፡፡

v       

አርገው ተዓምራትን ፈጽመዋል የተባሉት  ሶስት ሴት ልጆች ከ 7 እሰከ 10 ዓመት ዕድሜ የሚገመቱ እንቦቃቅላዋች ናቸው፡፡ ሻይ እየጠጣን የምንጠባበቅበት ቤት የምትገኘው ሄለን ትባላለች፡፡ የአምላክና ሰርጌ ደግሞ ጓደኞቿ ናቸው፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው ከወር በፊት ነበር፡፡ ሰዓቱ ደግሞ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት፡፡ ሶስቱ ልጆች ወደ ሰንበት ት/ቤት እየሄዱ ሳለ ወደ ኃላ ቀረት ብለው ተሰወሩ፡፡ አብሮአቸው የነበረው መምህር ዞሮ ቢፈልግ፣ ግራና ቀኝ ቢሮጥ ሊያገኛቸው አልቻለም፡፡ ምን ዋጣቸው በሚል ተደናገጠ፡፡ ከብዙ ፍለጋ በኃላ ወደ ቤታቸው ሄዶ ቢጠይቅም ሁሉም አልተገኙም፡፡ 12 ሰዓት አካባቢ ሁለቱ ህጻናት በነጭ  ፣ አንዷ በጥቁር ፈረስ መንፈስ ቅዱስ ተላብሰው ስላሴ አካባቢ ወደ ምድር ወረዱ፡፡ ከዚያም የሆነውን ሁሉ በመናገር መምህራቸውን አንድ ተአምር ሊያሳዩት ወደ ስላሴ ይዘውት ተመለሱ ፡፡

‹‹ ይታይሃል ቤ/ክርስትያናችን በብርሃን ደምቃ ? ››
‹‹ ምንም አዩታየኝም ›› መምህሩ የሚናገሩትን ነገር ማየት ብቻ ሳይሆን መገንዘብ አልቻለም
እንግዲህ ከዚህ በኃላ ነበር ስላሴ ተገኝተው መስበክና ማስተማር ፣ የተፈቀደላቸውን አይነስውራንን ማብራት፣ አካለስንኩላንን ማዳን፣ በውስጥ ደዌ የሚሰቃዩትን በመዳበስ ፈውስ መፍጠር የቻሉት፡፡ ተአምሩና ዜናው ርቆ ሲናኝ የኢፋግ ከተማና የስላሴ ቤ/ክርስትያን በሰው ማዕበል መጥለቅለቅ ጀመረ፡፡

አንድ ዕለት ወሬውን የሰሙ አንድ ጻጻስ ወደ ቤ/ክርስትያኑ መጥተው ‹‹ እስኪ እኔንም ዳብሽኝ  ?›› በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ልጅቷ ወደ ኃላ እያፈገፈገች ‹‹ እርስዋ ብዙ ኃጢአት የተሸከሙ በመሆንዋ በቅድሚያ ንስሐ መግባት ይኖርቦታል ! ›› በማለት ህዝብ ፊት ተናገረች ፡፡ የተከበሩት ቄስ ሽምቅቅ አሉ፡፡ ‹ እነዚህን መሰል ሀሰተኛ መሲህ በየግዜው የሚመጣ በመሆኑ ማንም ይህን ጉዳይ ማመን የለበትም ! › በማለት ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ ከማግስቱ ጀምሮም ህጻናቱ ወደ ቤ/ክርስትያን እንዳይገቡ ተከለከለ፡፡ የአካባቢው ሰዋች እኚህ ትልቅ የሃይማኖት ሰው ተግባራቸው የረከሰና የቀለሉ መሆናቸውን እናውቃለን ባይ ናቸው፡፡ በተለይም የሄለን አባት አቶ ታደሰ ሰዋችን በሻይ ስም ወደ ቤትህ እያስገባህ ገንዘብ በመቀበል ህጻኗን ታሳያለህ በሚል ታሰረው በማስጠንቀቂያ ተለቀዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ልጅቱን ጓዳ ውስጥ ለመደበቅ ተገደዋል፡፡

በነጭ ፈረስ የመጡት ሁለቱ ህጻናት የደግነትና የገነት ተምሳሌት፣ በጥቁር ፈረስ የመጣችው ደግሞ የክፋትና የገሃነም ተምሳሌት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያነበበውም ሆነ ተራው ህዝብ ፍች ሰጥቶታል፡፡ በነጭ ፈረስ የመጡት ሁለት ህጻናት ተአምር ሲሰሩ ሶስተኛዋ ህጻን እነሱን ከማጀብ ውጪ ሌላ ተግባር እንዳልነበራትም ያስረዳሉ፡፡ የኃላ ኃላ ግን ሶስተኛዋም ህጻን ኃይል ተጎናጽፋ ጓደኞቿን ለመምሰል በቅታለች፡፡

ህጻናቱ ወደ ት/ቤት ለመሄድ በሞከሩበት አንድ ቀንም ‹‹ ተቃጠልን ! ›› እያሉ በመጮኃቸው ቤተሰቦቻቸው ተሸክመው ወደ ቤት እንደመለሷቸው ይነገራል፡፡ ህጻናቱ ምሽት ላይ ሰውነታቸው በጣም ቀዝቃዛ የሚሆንበት ግዜ በመኖሩ ቤተሰቦቻቸው ሞተዋል ብለው ያለቀሱበት አጋጣሚ እንደነበርም ተገልጾልኛል፡፡ የህጻናቱን ምስክርነት የሚያሳይ ቪዲዮ በአንድ ሰው ተቀርጾ እየተሸጠ እንደነበር ስንሰማ ደግሞ ቪዲዮውን ለማግኘት ከተማዋን አሰስን፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ሌላው ጋ እየጠቆምን በእጃችን ማስገባት አልቻልንም፡፡ በዚሁ ጉዳይም የተወሰኑ ሰዋች በመታሰራቸው ሰዋቹ እንደሚፈሩም የኃላ ኃላ ተነግሮናል፡፡

v     

ቤቱ ውስጥ ለብዙ ሰዓት ተቀምጠው የታከታቸው ሰዋች እያጉረመረሙ ወደ ውጭ ሲወጡ ሌሉች በሩጫ አግዳሚውን አጣበቡት፡፡ አስተናጋጁ ‹‹ ምን ልታዘዝ  ? ›› ሲል ግን ደፍሮ ‹‹ ሄለንን ለማየት ነው ! ›› የሚል ምላሽ የሰጠ አልነበረም፡፡ ተረኛውም አንባሻውን ከሻዩ ጋር እያጣጣመ አንዴ ሰውን ሌላ ግዜ ግድግዳውን ይቃኛል፡፡

ግድግዳው ላይ የቡና ፖስተሮች ፈንጠር ፈንጠር ብለው ተሰቅለዋል፡፡ ግድግዳውን ብቻ ሳይሆን የኮመዲኖውን ውስጥና አናት በአይኔ በረበርኩት፡፡ ብዙ ቤት ውስጥ የቤተሰብ ፎቶ ቢሰቀልም ይህ ቤት ፍንጭ ለማሳየት የፈለገ አይመስልም፡፡ ከአንድ ጥግ ሆኜ ሻይ ጠጥተው የጨረሱ እንግዶችን በሞባይሌ አነሳው፡፡ አስተኛጋጁ ሳይመለከተኝ አይቀርም ፡፡አንዳንዶች ሲጨንቃቸው በልጁ ጆሮ ስር ጥያቄያቸውን ያቀርባሉ፡፡

‹‹ አይቻልም ! ተከልክለናል ! በሰው እየነገዳችሁ ነው እየተባልን ነው ›› ይላል ፡፡ ቆይቶ ሲጠየቅ ደግሞ ‹‹ ተኝታለች ›› የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ እኛም ታክቶን ከመነሳታችን በፊት ለልጁ ከሩቅ መምጣታችንን በመግለጽ በማስተዛዘን ጥያቄ አቀረብን፡፡ ምላሽ ሳይሰጠን ሻይ መቅዳትና አንባሻ ማቀራረቡን ቀጠለ፡፡

ድንገት ከጓዳ ወጥቶ ግን ተከታዩን የምስራች ለታዳሚው ተናገረ ‹‹ እሺ ልጅቱ አሁን ተኝታለች ፤ ከተወሰነ ደቂቃ በኃላ እናሳያችኃላን፡፡ በፍጹም ድምጽ መቅረጽም ሆነ ፎቶ ማንሳት አይቻልም ! ››  ወዲያው የሰውን ፊት ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ብዙ ፊቶች ላይ የጠበቅኩትን ፈገግታ ማየት አልቻልኩም - ቅጭም ያሉ ፊቶች እንጂ፡፡ ሰው መቀመጫው ላይ መቁነጥነጥ፣ ሴቶች ነጠላቸውን አናታቸው ላይ ማስተካከል፣ ገኖ የነበረው ሹክሹክታ ረጭ ወደማለት ተቃረበ፡፡

ከዚያም በእናቷና በአስተናጋጁ የተያዘች ቆንጆ ህጻን የጓዳው በር ላይ ስትደርስ ‹‹ ልጅቱ እቺ ናት ! ›› አለ አስተናጋጁ፡፡ አይኖች ተወረወሩባት፡፡ በርግጥም ከእንቅልፍዋ የተቀሰቀሰች መሆኑ የተረበሸ ፊቷ ይመሰክራል፡፡ ጸጉሯ ላይ ጨርቅ ሸብ አድርጋለች፡፡ ነጭ ቀሚሷን እንደያዘች በሰያፍ ነበር ሰውን የምትመለከተው፡፡ ለሶስት ደቂቃ ያህል የቆየ ገራሚ ትዕይንት ፡፡

‹ ደህና ዋልሽ ? ›
‹ እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን ! ›
‹ እ.ል.ል.ል.. ተባረኪ እቴ ! ›
‹ ስለ ተዓምሩ የሆነ ነገር ብትነግሪን ? ›
እነዚህና ሌሎች ጥያቄዋች ይነሳሉ ብዬ ብጠብቅም የሁላችንም አፍ ዱዳ ነበር የሆነው፡፡ አስተናጋጁ አስቀድሞ ድምጽ መቅረጽ አይቻልም ብሎ ስላስጠነቀቀን ነው ወይስ ስለተገረምንና ሰለፈራን ???  እናቷ ወደ ውስጥ ሲያስገቧት ብዙዋች የነቁ መሰለኝ ፡፡ እኛም  ‹‹ ይገርማል ?! ›› እያልን ቤተሰቦቿን አመስግነን ውልቅ አልን ፡፡ ውጭ ያለው ሰው ቀላል አይደለም ፡፡ ተፋጠጡ እስከመቼ ይሆን የሚቀጥለው ???

v     
 
የአካባቢው ነዋሪና ጉዳዩን ለማየት የመጣው ህዝብ ተዓምራቱ እውነት ስለመሆኑ ቅንጣት ያህል አይጠራጠርም፡፡ ፈውስ አገኝ ዘንድ በሚል ተስፋ አካባቢው በበሽተኞች ቁጥር መጨናነቁም ጉዳዩ በቀላሉ መታየት እንደማይገባው የሆነ ነገር ያጭራል፡፡ በሌላ በኩል ዲያቆናትና ቄሶች ስለጉዳዩ እንዲጠየቁ አይፈልጉም ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ጉዳዩ ትክክለኛ አለመሆኑን ይናገራሉ ፡፡
በርግጥ ራዕይ ተገለጸልን፣ መንፈስ ቅዱስ ቀረበን በሚል አንዳንድ ሀሰተኛ ሰዋች ህዝቡን ያሳሳቱበት ግዜ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ተልዕኳቸውም የግል ጥቅማቸውን ለማበልጸግ መሆኑ ግልጽ ነው ፡፡ ኢፋግ ላይ የታዩት ህጻናት ግን ገና የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ያልጠገቡ የዋሆች ናቸው፡፡ እነዚህ ህጻናት ለምን ዓላማ የተሳሳተ ድርጊት ያከናውናሉ ? ለኔ ያልተመለሰልኝ ጥያቄ ይህ ነው ፡፡ በቤተሰቦቻቸው ተገፋፍተው እንዳይባል ህጻናቱ ብዙ ግዜ ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ በሚል እስርና የተለያዩ ተጽዕኖዋች ተደርጎባቸዋል ፡፡

እንግዲህ እኔ የምነግራችሁ እዚህ ድረስ ብቻ ነው ፡፡


ስላሴ ቤ/ክርስትያን

 
የኢፋግ ከተማ

ውጭ  በር ላይ የተኮለኮለው ህዝብ


 





1 comment:

  1. አሌክስ በጣም እናመሰግናለን። ለምን ካልህ በዚህ ዘመን ወሬ ካንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ለመድረስ የሚፈጅበት ጊዜ እጅግ አጭር ነው፣ እናም ስለ ሄለን፣የአምላክና ሰርጌ በወሬ ደረጃ ሰምተናል እናም ይህ ነገር ወሬ ነው ወይስ የሚል ነበር በብሎግ ላይ ምንም መረጃ ላገኝ አልቻልሁም ነበር ባጋጣሚ ያንተን ዌብሳይት ላይ ሳገኝ በጣም ተደስቻለሁ የተረጋገጠ መረጃ በማንበቤ።
    ዘርያዐቆብ ይሁን
    ከደብረ ማርቆስ

    ReplyDelete