Tuesday, May 1, 2012

ሸረሪት ለማድራት… እኛ ለመሰለፍ ማን ብሎን ?!





ሰሞኑን ያየሁትን ሰልፍ ማመን አልቻልኩም…

ከግርምቱ አውድ ከወጣሁ በኃላ አይኔን ጨፍኜ ማንሰላሰልኩ ጀመርኩ፡፡ እስከዛሬ ለስንት ነገር ተሰልፈናል ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነበር ትግል የያዝኩት፡፡ በእውነት ብዙ ምላሾች ተደራረቡብኝ፡፡ መቁጠር ጀመርኩ፡፡ እነሱን ቆጥሮ ለመጨረስ ራሱ ረጅም የትዕግስት ሰልፍ ያሰፈልጋል ?  ህይወታችን በሙሉ ሰልፍ ነበር እንዴ  ? በምናቤ ዚግዛግ የሰሩትን ትናንሸና ትላልቅ ሰልፎች እያበላለጥኩ delete ማድረግ ጀመርኩ፡፡ እውነት ለስንት ነገር ተሰልፈናል ??

ልጅ ሆነን ቤተመጻህፍት ለመግባት / ብሪትሽ፣ ማዘጋጃ፣ ወመዘክር፣ጉድሸበር ወዘተ / ረጅም ሰልፍ ውስጥ እንሰምጥ ነበር፡፡ ጸሃይ ካንቃቃን በኃላ ‹ ለዛሬ ስለሞላ ቦታ ልቀቁ! ነገ በጠዋት ዳይ ! › የሚል ወፍራም ደምጽ መርዶ ሲያረዳን እየተነጫነጭን  እንበተን ነበር፡፡ ከቀበሌ ዳቦ ለመግዛት በለሊት ተነስተናል፡፡ ዘወትር ጥፊ በመቅመስ ለሚዝናናው ብሄራዊ ቡድን ስታዲየምን በሰልፍ ድር አወታትበናል ፡፡ ዋና ዋና ሰልፎችን ብቻ ካላስታወስኳችሁ ይህ አጭር አርቲክል ረጅም ልቦለድ እንዳይሆን ሰጋሁ፡፡ አዋ ! አንድ አራቱን አስወግጄ ልቀጥል፡፡

አንድ ኪሎ ስኳር ለማግኝት በኢትፍሩት ደጆች ለስንት ሰዓታት ቆመናል ? አንድ ሊትር ዘይት ለመግዛት ይደረግ የነበረው ጉዞስ ? መሳለሚያ  አለቀ ! ሲባል በየአቅጣጫው መሮጥ ይጀመራል፡፡
       ‹ ፒያሳ ሳይኖር አይቀርም ?  ›
       ‹ ካሳንችስ ወረፋው ነው እንጂ አለ ሲባል ሰምቼያለሁ ! ›
       ‹ እንደው መራቁ ነው እንጂ ሳሪስማ መኖሩ ተረጋግጧል ! ›
       ‹ ታዲያ ምን አማራጭ አለ እንሄድ እንጂ ?! .
ሀገሬው በአራቱ ማዕዘን ተሰልፎ ይተማል  - ሌላ ሰልፍ ኃላ ለመሰካት ፡፡

በቅርቡ ሜክሲኮ ያየሁት ሰልፍ ግን አዲስ ሆኖብኛል …..

ጄሪካኖች ትዝ አሏችሁ ;… ቢጫ ጄሪካኖች ፡፡ አብዛኛው ሰፈር በውሃ ድርቅ ሲመታ የሆኑ ጥቂት ሰፈሮች ላይ በሆነ ተዓምር በወፍራሙ የሚፈሱ የውሃ ባንቧዋች አይጠፉም ፡፡ ከተሜው እነዚህን ቧንቧዋች እንደ ፈለቀ ጸበል ነበር የሚቆጥራቸው ፡፡ እናም በሰሚ ሰሚ መረጃውን ጨብጦ ከጀሪካኑ ጋ  ይሮጣል ፡፡ ቦታው ታቦት አይወጣበትም እንጂ ህዝቡስ ጥምቀተ ባህርን ይተካከል ነበር ፡፡

እናም ጀሪካኖች ሰውን ተክተው ረጅሙን ሰልፍ ይቀላቀላሉ፡፡ ፈረንጆች  < virtual queue >  የሚሉት አይነት መሆኑ ነው፡፡ ሰው ከጀርባ ሆኖ ተራውን በናፍቆት ይጠባበቃል፡፡ እዚህ ጋ ለግዜው  < physical queue > አይኖርም ፡፡ ግን ጀሪካኖች በሙሉ መልካቸው አንድ ዓይነት ስለነበር በይገባኛል ጥያቄዋች ስድድቦሽና ግብግቦችን ማስተናገድ የተለመደ ነበር ፡፡ ውሃው በአንድ ብር ተለክቶ  ለተሸካሚ  አስር እጥፍ ይለካለታል፡፡

ቢጫ ጀሪካን ከተነሳ አይቀር ጠቆርቆር ያለውንም ማንሳት ይኖርብናል፡፡ ጥቁሩ ጀሪካን ዋና ዓላማው ጋዝ መሸከም ቢሆንም ብዙውን ግዜ አይሳካለትም ፡፡ ባለቤቱ ለረጅም ሰዓታት ጸሃይ እየበላው ተሰልፎ አለ ..ቀ ?  ይባላል፡፡ ያኔ ይመስለኛል ከተማው ውስጥ ያሉ ማደያዋች በህዝቡ ዘንድ በአግባቡ የታወቁት፡፡
         ‹ ሞቪል እንሞክራ ?! ›
         ‹ ሽየል አይቀርበንም  ? ›
         ‹ እዚያ አጂፕ ደግሞ ይደብቃሉ ይባላል ›
         ‹ እነሱ ደግሞ እንደ ምልክታቸው አውሬ ናቸው ! ›
         ‹ እረ የቶታል ብሷል ! ህዝቡንም መኪናውንም ማሰለፍ ሰልችቶኛል እያለ ነው አሉ ! ›
         ‹ ምን ያቃናጣዋል እቴ ?! ቶታል ማለት አጠቃላይ ማለት አይደል ? ታዲያ አጠቃሎ ቢያሰልፍ ምን አለበት ?  ባፋንኩሎ !!! ›

ሰልፉ በራሱ ራስ ምታት መሆኑ ሳይቀር ሰልፉ ሲበተን የሚታየው የህይወት ሩጫ ያሳምማል ፡፡ ዛሬ ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባው እንጂ ‹ ዲቪ በአንድ ብር አሜሪካ ! › እየተባለ ፎርም በሚሸጥበት ግዜ በፓስታ ቤትና በአንዳንድ ቦታዋች የነበረው ሰልፍም  ‹ ሰው ብርቱ ድመት ጠንካራ ! › የሚባለውን አባባል ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ነበር ፡፡ ሰው ስራ ሊመዘገብ ሄዶ ረጅም ሰልፍ ካየ ቢያንስ     ‹ ነገ › ብሎ ይመለሳል ፡፡ የዲቪው ሰልፍ የአንድ ቀበሌን ርዝመት አካልሎ እያየ ፣ የቢሮ መዝጊያ ሰዓት ተኩል ሰዓት ብቻ የቀረው መሆኑን እየተነገረው እንኳን ቀልድ አይውቅም ነበር ፡፡ ፈገግ እያለ ከኃላ ይለጠፋል ፡፡

በቅርቡ በሜክሲኮ የተጀመረው ሰልፍ የቀድሞውን የዲቪ ዘመን የሚያስታውስ ነው…

መቼም fair እና unfair ሊባሉ የሚችሉ ሰልፎችንም አካሂደናል፡፡ የምርጫ 97 ግዜ ያች በእልህና በደም ቀለም የተጻፈችውን ካርድ ሳጥን ውስጥ ለመወርወር አብዛኛው ሰው ለሊት ላይ ነበር መሰለፍ የጀመረው ፡፡ ግን ገጹ ሀሴት እንጂ ምሬትን ሲረጭ አልታየም ፡፡ የቴሌቪዥን ግብርና ውዝፍ ለመክፈልም የሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ በሰልፍ የተጥለቀለቀበትን ግዜ አስታውሳለሁ፡፡ ህዝቡ በሰልፉ ብዛት ብቻ ሳይሆን በሚከፍለው ነገር ተገቢነት ላይ ደስተኛ አልነበረም፡፡ ‹‹ የረባ ነገር ሳልመለከት እንዴት  እንድከፍል  እገደዳለሁ ፤ በማየው ነገር ጨጓራዬ እየተላጠ አሁን ደግሞ በሰልፍ ለምን እቃጠላለሁ ? ›› ይል ነበር ፡፡ በዓመት የሚከፈለው 50 ብር ለየወሩ ቢካፈል ከአምስት ብር የሚያንስ ነው ፡፡ ሰው የሚያጉረመርመው ለዚህ ብር አንሶ አይደለም ፤ ለምን ይቀለድብኛል በማለት እንጂ፡፡

ኢትዮጽያ ውስጥ ሞባይል የሀብታሞች መለኪያ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ በ20 ቤት ተጀምሮ 25 ላይ አቆመ፡፡ ባለ 20 - ባለሀብት፤ ባለ 21 - ባለስልጣን ፤ ባለ 22 ደላላ ፤ ወዘተ እየተባለ የዳቦ ስም አወጣ - የኔ ዓይነቱ ተመልካች፡፡ ርግጥ ነው መሃል ላይ በምን ዘዴ እንደሚሰጥ ባይታወቅም በ40 የሚጀምሩ ሞባይሎች አንዳንድ ሰዋች እጅ ላይ ይታዩ ነበር ፡፡ ታዲያ ብዙ አመታትን ካሰቆጠረ በኃላ የካርድ ክፍያ ዘዴ ተግባራዊ በመሆኑ ሞባይል መነሻዋን 60 አድርጋ ብቅ አለች ፡፡ አቤት ያኔ የነበረ ሰልፍ !! ‹ ሰልፍ › ጉዳዩን ቀላል ስለሚያደርገው ‹ ግድያ › ብለው ይሻላል፡፡ ከአራትና አምስት ቀናት መራር ትግል በኃላ ሲም ካርዷን የሚይዝ ተገልጋይ አቤት የፊቱ ጸዳል !! አቤት አረማመድ !! ኩራቱስ ብትሉ !! ስኮላርሺፕ ያገኘ ወይም ኮካ ጠጥቶ ቲኮ መኪና የተሸለመ ነበር የሚመስለው ፡፡ ዛሬ ነገር ዓለሙ ተቀያይሮ ሁላችንም በር ላይ እየተሰለፈ ያለው ራሱ ቴሌ ሆኗል ፡፡ በቀን የአንድ ሰው የሞባይል በርን ከ4 እስከ 8 ግዜ ያንኳኳል፡፡ በርግጥ አንኳክቶ ገና ፍቃድ ሳያገኝ ነው ጓዳ ወደሆነው << Inbox >> ውስጥ ዘሎ ዘው የሚለው ፡፡ ተኳሾቹ ተኩሰው ከገደሉ በኃላ ‹‹ ቁም !! ›› እንደሚሉት ዓይነት መሆኑ ነው ፡፡

 እናም ሳጥናችሁን ከፈት ስታደርጉ ‹‹ እባካችሁ የሲም ቅናሽ አድርጌያለሁ ይላችኃል ›› መልከ ብዙው ቴሌ፡፡ 
ከአፍታ በኃላም ‹‹ ስለ ቀፎም አታስቡ! በአነስተኛ ዋጋ አቅርቤያለሁ ›› ትባላላችሁ ከማይታይ ፈገግታ ጋር ፡፡ 
‹‹ የዳይቨርት አገልግሎት መጀመሬን ሳበስር በእናንተ ደስታ ከወዲሁ እየሰከርኩ ነው ›› ይላችኃል ጡንቸኛው ቴሌ፡፡
 ቴሌ ከስራው ጋር በማይመጣጠን መልኩ በወሬ እያደነቆረን ስለሆነ በርግጠኝነት አንድ ቀን የሚከተለውን መልዕክት ያደርሰናል ብዬ እየተጠባበቅኩ ነው ‹‹ ጥራት ያለውን አገልግሎት በርካሽ ዋጋ መስጠት አለመቻሌን ስገልጽ በታላቅ ፌሽታ ነው !! … ከሚታይ ሰላምታ ጋር >>

በቅርቡ ሜክሲኮ እየታየ ያለው ሰልፍ ….

አዋ ! በግራና በቀኝ ረዝሞ የሚታየው ሰልፍ እንደ አውሮፓዋቹ ለስራ ምዝገባ አይደለም ፡፡ ይህ ሰልፍ የታክሲ ጥበቃ ነው፡፡ ልብ በሉ የአንበሳ ወይም የባቡር አይደለም፡፡ እንዴት ነው በአንዴ ወደታች ያሽቆለቆልነው  ? ነው የዘመናዊ አሰራር መግለጫ ሆኖ እመርታ እያሳየን ነው  ? እንቆቅልሽ ፡፡  አንድ ታክሲ ጥጉን ታኮ ሲቆም ከግራ 6 ፣ ከቀኝ 6 እየተሰፈረ ወደ ውስጥ ይላካል፡፡ ሌላ ታክሲ እስኪመጣ ደግሞ ጥበቃ ይከናወናል፡፡ መቼም ባቡር ወይም እንደ ባቡር የረዘመው አዲሱ አውቶብስ ቢሆን አንዴ ሁሉንም ሰብስቦ ስለሚጓዝ መታከትን ያሰቀራል ፤ የስራ ሰዓትን ያስከብራል፡፡ ይሄ ነገር የሚያዋጣ ነው ?  ‹ ከግፊያው ይሻላል ! - አይሻልም  ? › የሚል እንደ ጋዜጠኛ ጠይቆ እንደ ባለስልጣን የሚመልስ አካላትንም  እያጠራቀመ ይመስላል ፡፡

ሰልፉ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ወደቦሌ ለሚጓዙ መንገደኞች ብቻ ነው ፡፡ ለምን  ? የቦሌ አንደኛው መስመር እየተሰራ ስለሆነ  ? ታዲያ ቢሰራስ  ? ወደ ቦሌ የሚሄዱ ታክሲዋች እንደሆነ ድሮም ሆነ አሁን ኮታቸው ይታወቃል፡፡ ታዲያ እጥረቱ የባሰ እንዴት ተባባሰ  ? ታክሲዋቹ ወደዛ አንሄድም በማለታቸው ይሆን ?  በአዲሱ አሰራር መሰረት መንግስትን ‹ የራስህ ጉዳይ አንሄድም ! › ማለት ይችላሉ  ? በሚሰራ ህግ ካሰብን መልሱ ‹ ውልፍት ማለት አይችሉም ! › የሚል ይሆናል፡፡

ይህኛው መላምት ካልሰራልን አንድ  እየተሞከረ ያለ ጉዳይ ሳይኖር አይቀርም ብለን እንነሳ፡፡ የ If – Then ሎጂክን በሰበቡ እያስታወስን ፡፡ ስለሁኔታው ጋዜጣዊ መግለጫ አልተሰጠበትም እንጂ ፣

ስያሜው              -              የታክሲ ሰልፍ ፓይለት ፕሮጄክት
ፕሮጄክቱ የሚሸፍንበት ቦታ -      ከሜክሲኮ እስከ ቦሌ ድልድይ
የስራው ተቋራጭ             -     ተራ አስከባሪዋች
ጥናትና ምክር                 -     ቻይናዋች
የስራው ዕድሜ                -     ሩብ ዓመት
አሰሪ                           -     ውጤቱ ካላማረ መንገድ ትራንስፓርት ፤ ውጤቱ ካማረ የአ/አ መስተዳድር የሚሆን ይመስለኛል፡፡

አላማው ግልጽ ነው፡፡ መንግስት የከተማውን የታክሲ አሰራር መስመር አስይዤ ነዋሪውን ከግፊያና ከብዝበዛ እፎይ አደርጋለሁ ብሎ ቢፎክርም፣ አፎካከሩ ሪትም ያልጠበቀና ከለር የሌለው በመሆኑ ከራሱ ዕቅድም ሆነ ከውድድሩ ዙር ተሰናብቷል፡፡ አሁን ራሱን አጠናክሮ የመጣው በቻይናዋች አለሁ ባይነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እናም ብዝበዛውን መቆጣጠር ቢያቅተው እንኳን ግፊያውን ማስቆም የሚያስችል ንዑስ አላማ ይዞ  በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ የሙከራ ፕሮጄክት ከተሳካ ተሞክሮው በሌሎች አካባቢዋች እንዲስፋፋ ይደረጋል፡፡ ተሳፋሪው የግፊያ ግርግር ከቀረለት አፉን ለእንካ ሰላንትያ ከማዘጋጀት ፤ እዚህ ግባ የማይባለውን ክንዱን ለቦክስ ከመሰብሰብ ይድናል፡፡ ለዚህ የሚያወጣውን ከፍተኛ  መዋዕለ  ንዋይ ቢያንስ ለተወሰኑ ቀናት ኪሱ ውስጥ በማስቀመጥ በራስ የመተማመን ባህሉን እንዲያሳድግ ይረዳዋል፡፡
የፕሮጄክቱ ጠቀሜታ በዚህ ብቻ የሚገደብ አይደለም፡፡ ተራ አስከባሪዋች ከባለታክሲው ብቻ ሳይሆን በስምምነትና በድርድርም ከተሳፋሪው ደቃቅ መልሶችን የሚቀበሉበት አሰራር ሊዘረጉ ይችላሉ፡፡ በርግጥ የዚህ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ወደፊት በህግ የሚወሰን ይሆናል፡፡ በዚህ የማስፋት ስትራተጂም በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ወደ ዘርፉ የሚሳቡበት መንገድ እያደገ ይመጣል፡፡

የፕሮጄክቱ መሪ ቃል ‹‹ ከመጋፋት ሰልፍ ላይ መዝመት ›› የሚል እንደሆነ ይገመታል ፡፡ የስድስት ኪሎ ምሁራን ‹‹ ከመጠምጠም መማር ይቅደም ›› የሚሉት ነገር ነበራቸው፡፡ የዚህ ፕሮጄክት አንድ አካል የሆነው ፓሊስ ታዲያ የጥቅሷን ጆሮ እንደምንም ጠምዝዞ በተገለጸው መልኩ ቤት እንድትመታ አድርጎታል ነው የሚባለው፡፡ ለፕሮጄክቱ ባቀረበው መነሻ ሀሳብ ላይም ነዋሪው የሰልፍ ስርዓት እንዲይዝ መደረጉ ጸጥታን ከማስፈን አኳያ አይነተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ፡፡ ሰው በሰልፍ ላይ እያለ ታክሲ እስኪመጣ ማለት ነው የሰልፍ ትምህርት ብቻ ሳይሆን የኮሚኒቲ ፓሊሲንግ ጽንሰ ሃሳብን ማስረጽ ይቻላል፡፡ ሌላኛው አጋር የሆነው የወረዳ መዋቅር ፍንድቅድቅ ብሎ ገለጸ የተባለው ቅዳሜና እሁድ ለስብሰባም ሆነ ለልማት ሲጠራ ድርሽ የማይለውን ነዋሪ ለመለየት፣ ለመታዘብ፣ አስፈላጊ ከሆነም ለመወቃቀስ የግድ ከሆነም በቀጣዩ እንዳይቀር የማግባባት ስራ ለማከናወን ምቹ ዕድል ይፈጠራል፡፡

‹‹ ፕሮጄክቱ አይሳካም ! በውጭ ሀገር ጫማ እንራመድ ማለት ተጠላልፎ መውደቅ ነው ! ፕሮጄክቱ ከበስተጀርባው ድብቅ ዓላማ ሳይኖረው አይቀርም ! ›› ወዘተ የሚሉ ስጋቶችና ጥያቄዋች ሲበራከቱ የሚመለከተው ክፍል ይፋ የሆነ ጋዜጣዊ መገለጫ ለመስጠት የሚገደድ ያመስለኛል፡፡

                                                                                                                                                                        መግለጫውን ጨምቄ ላቅርብላቸሁ ……

‹‹ ያው… እንደሚታወቀው በሀገራችን አዲስ ነገር ሲመጣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ Resistance የተለመደ ነው፡፡ ብዙ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የመንገድ ግንባታ… የኮንዶ ግንባታ … የቢፒአር ማሻሻያ … የሰፈራ ፕሮግራም …የግብር ስርዓት ወዘተ በተጀመሩ ግዜ ሁሉ ይህን መሰሉ ጥርጣሬዋች ነበሩ፡፡ ከውጤት በኃላ ግን ጥያቄ ሳይሆን የድጋፍ ሀሳብ ነው የሚነሳው፡፡ ዛሬ ከሰፈራችን ተነስተን ቤት ይሰራልን የሚለው ብዙ ሆኗል፡፡ የተናቀውን ድንጋይ ዳቦ ማድረግ ስለምንፈልግ አደራጁን የሚለው ጥያቄ በዝቷል፡፡ እናም በሜክሲኮ - ቦሌ የሰልፍ ፕሮጀክት የለገሃሩ፣ የሳሪሱ፣ የካራቆሬው፣ የኮተቤው፣ የመርካቶው ዛሬ ቢስቅና ቢያሽሟጥጥ ነገ ላደፈው ሀሳቤ ይቅርታ አድርጉልኝ እንደሚል እናውቃለን ››

ጋዜጠኞች በተሰጠው ምላሽ ስለረኩ ተጨማሪ ጥያቄዋችን አልሰነዘሩም፡፡ ዜናውን ለማድረስ መቻኮል ላይ ናቸው ፡፡ ግን እንደ አንድ ታዛቢ ለሚከተሉት ጥያቄዋች ሊሰጥ የሚችለውን ምላሽ  አሰልፌ ማየት አማረኝ ?

1 . ‹‹ ሰልፍ ሲረዝም ጣልቃ ገቢው ይበዛል፡፡ ቦታን በመሸጥ ሰፊ ልምድ ያላት አዲስ አበባ ወረፋ ቸርቻሪዋችን አታበቅልም ማለት አይቻልም፡፡ ይህን እንዴት መከላከል ይቻላል  ? ››
2 . ‹‹ ለሰልፍ በሚደረገው የዘወትር ሩጫ የሚዳከመውን የነዋሪውን የፈጠራ አቅም እንዴት ለማሳደግ ታስቧል  ?  ››
3 . ‹‹ በየሰፈሩ ከሚታየው የትየለሌ ሰልፍ የገቢ ምንጭ መፍጠር አይቻልም  ?  ለምሳሌ ለውጭ ባለሀብት ርካሽ የሰው ጉልበት        መኖሩን በማሳየት፣ ከመዝናኛ አንጻርም እዚህና እዚያ  የሚታየው ሰልፍ አክሮባት አይሰራም እንጂ እንደ አንፊ ሰርከስ ሊቆጠር ይችላል ፡፡ ከዚህ አንጻር የሆነ ነገር ማግኘት አይቻልም … ?
4 . ‹‹ ለታክሲ የቆመው ህብረተሰብ እግረ መንገዱን ለጋዝ፣ ለዘይት፣ ለስንዴ  ወይም ለስኳር ሰልፍ ሊያውለው ይችላል ? ነው ለእያንዳንዱ ኩፓን ለማዘጋጀት ነው የታሰበው ?  … ›

አመሰግናለሁ !!!
ሰልፋችን ከተባለው ሰፈር …
የማይታይ ፊርማ አለው

No comments:

Post a Comment