Friday, June 1, 2012

በጣም የሚዋሸው ወንድ ነው ሴት ?



በቅርቡ መቼ ነበር የዋሹት ? በብድር ወይም በስራ ማመልከቻ  ጥያቄ ላይ ራስዋትን ከፍ በማድረግ ጥቂት ግነቶችን አቀላቅለው ይሆን ? መኪናዋትን ለማሻሻጥ ጥረት ሲያደርጉ ሁልግዜም ዘይት የማፍሰሱን ሁኔታ በመርሳት ወይም ቸል በማለት ስለመኪናዋ ብቁነት ሳይሰብኩ ይቀራሉ ?  ቢያንስ በሰባት ዓመት ዕድሜ ዝቅ ብሎ ለመታየት ጸጉርዋን ቀለም መቀባትዋ… አሊያም የሳሳውን የጸጉር ክፍልዋ በቀሪው ጸጉር ለመሸፋፈን ጥረት አድርገው መሆንዋንም ያስታውሱ፡፡ ከፍ ያለ ተረከዝ ያለው ጫማን በማድረግ ቅልጥምዋን ረጅምና ያማረ ለማስመሰል ምን ያህል ግዜ ተጨንቀው ይሆን ?  ሰው ሰራሽ ጸጉርና ጥፍር እንዲሁም ሌሎቸን የማስዋቢያ ቁሳቁሶች በመጠቀም እውነተኛው መልኬ ይሄ ነው በማለትስ ምን ያህል ባዝነዋል ?  አሁን የሆነ ከባድ ውሸት ትዝ አለዋት ;…. አይጨነቁ ! ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች እንዋሻለንና - ጥቅም ለማግኘት ወይም ስቃይን ለማስወገድ ፡፡

የውሸት ዓይነቶች፣

አራት የውሸት ዓይነቶች አሉ፡፡ ነጭ ውሸት፣ ጠቃሚ ውሸት፣ ተንኮል አዘል ውሸት እና አሳሳች ውሸቶች ናቸው ፡፡ ነጭ ውሸት እውነታው ሌላ ሆኖ  በተቃራኒ መልኩ የሚነገር ድርጊት ነው፡፡ ጠቃሚ ውሸት አንድ ሰው ሆን ብሎ ሌሎችን ለመርዳት በማሰቡ የሚፈጠር ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የአደጋ ግዜ ሰራተኞች ከሚቃጠል መኪና ውስጥ ጎትተው ያወጡትን ህፃን እናቱና አባቱ በደህና ሁኔታ እንደሚገኙ ሊነግሩት ይችላሉ፡፡ ይህም ህጻኑ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባና ለትንሽ ግዜም ቢሆን በህይወቱ እንዲቆይ ለማድረግ ነው፡፡
አሳሳች ውሸት በጣም አደገኛ የውሸት ዓይነት ነው፡፡ ምክንያቱም የሚዋሸው ሰው ለራሱ ጥቅም ሲል ሌላውን ሊጎዳ ወይም ጥቅሙን ሊጋፋ ስለሚችል፡፡ አሳሳች ውሸት  ሁለት ዓይነት መንገዶች አሉት - መደበቅና ፈጥሮ መናገር ናቸው፡፡
ተንኮል አዘል ውሸት የሚነገረው ለብቀላ ወይም ትርፍ ለማግኘት ነው፡፡ ጥሩ ዝና ያላቸው ሰዋች ለምሳሌ የፊልም አክተር፣ ባለጸጎችና ፓለቲከኞች የሚያገኙትን ጥቅም በማለም ይህን ዓይነቱን ውሸት ይጠቀማሉ፡፡ ተንኮል አዘል ውሸት ሁልግዜም በውድድር ሁኔታ ውስጥ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ተንኮል አዘል ውሸትን የሚያቀነቅኑ ሰዋች ባላንጣቸውን ወይም ማጥቃት የሚፈልጉትን ስምና መልካም ዝና በአስደንጋጭ መልኩ ያፈራርሳሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ኩባንያ በተፎካካሪው ላይ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት የገንዘብ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንዱ የፓለቲካ ፓርቲ በሌላኛው አባላት ላይ መጥፎ የዝሙት ባህሪ፣ ሙሰኝነት፣ ወዘተ እንዳለባቸው በማስመሰል ማስወራቱ የተለመደ ነው፡፡ ይህ የውሸት ዓይነት ውሸት መሆኑ በስተመጨረሻ ሊደረስበት ቢችል እንኳን ጎጂ ገጽታ አለው፡፡ ምክንያቱም አንድ ጭብጥ ጭቃ የሆነ ነገር ላይ ቢወረወር የተወሰነው ተለጥፎ መቅረቱ አይቀርምና፡፡

የውሸታሞች ዓይነት፣

‹‹ የተፈጥሮ ውሸታሞች ›› ህሊና ያላቸው ሲሆን ነገር ግን ውሸቱን ሲጠቀሙ የመጡት ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በመሆኑ በመዋሸት ብቃታቸው በጣም የሚተማመኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዋች ከተለያዩ ቅጣቶች ለማምለጥ ከቤተሰባቸው ውሸቱን የተማሩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ችሎታቸው ሲያድጉም ስለሚጠቀሙ ጠበቃ፣ ነጋዴ፣ አስማሚ፣ ደላላ፣ አክተር፣ ፓለቲከኛና ሰላይ ሆነው ለመስራት ዕድል አላቸው፡፡
‹‹ ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ውሸታሞች ›› የሚባሉት ልክ እንደ ህጻን ፣ ቤተሰቦቻቸው ለእነሱ ውሸት መናገር የማይቻል መሆኑን በማሳመን ያሳደጓቸው ዓይነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሞኝ የሆኑ ሰዋች ህይወታቸውን ያሚያሳልፉት ላገኙት ሁሉ የሁሉንም እውነት በመስበክ ነው፡፡ ለዚህ የማሳመኛ መሳሪያቸው ደግሞ ‹‹ እኔ በፍጹም ውሸት መዋሸት አልችልም ›› የሚለው አባባላቸው በመሆኑ ከሰዋች ጋር ለግጭት ያዳረጋሉ፡፡

በጣም የሚዋሸው ማነው ?

አያሌ ሴቶች በጋለ ስሜት እንደሚያማርሩት ከሆነ ከሴቶች ይልቅ የበለጠ የሚዋሹት ወንዶች ናቸው፡፡ ሳይንሳዊ ጥናቶችና ምርምሮች የሚያሳዩት ግን ሴቶችና ወንዶች የሚዋሹት በእኩል ደረጃ ነው፡፡ የሚለያያቸው ነገር ቢኖር የውሸቶቹ ይዘቶች ናቸው፡፡ የሴቶች ውሸት የሚያዘነብለው ሌሎች ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲሆን ወንዶች የሚዋሹት ራሳቸውን ጥሩ አድርጎ ለማሳየት ነው፡፡ ሴቶች ግንኙነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ለመጠበቅ ሲሉ ሲዋሹ ወንዶች ጭቅጭቆችን ለመከላከሉ ይዋሻሉ፡፡ ሴት ልጅ አንድ ወንድ አዲስ ልብስ ለብሶ ነገር ግን በጆንያ የተሞላ ድንች መስሎ ቢታያት እንኳን በጣም ቆንጆ መሆኑን ከማስረዳት ወደ ኃላ አትልም፡፡

ሴቶችና / በፍጥነት / የመዋሸት ጥበባቸው፣

በርካታ ወንዶች ትንሽዬ ውሸት እንኳን ብትሆን ሴቶች ፊት ለፊት ቆመው ለመዋሸት እንደሚከብዳቸው ያውቃሉ፡፡ ወንዱ የግድ ሴቷን መዋሸት ካለበት የሚመርጠው በስልክ ግንኙነት ይሆናል፡፡ በአንጻሩ አብዛኛዋቹ ሴቶች ከወንድ ጋር ፊት ለፊት ተገኛኝተው ለመዋሸት ያን ያህል ችግር ውስጥ የሚገቡ አይደሉም፡፡ የጭንቅላታችንን  የውስጥ ገጽታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው መሳሪያ እንደሚመሰክረው የሴት ጭንቅላት ፊት ለፊት ለሚደረግ ግንኙነት የሚረዳት ከ14 እስከ 16 የሚደርሱ ቁልፍ የአቀማመጥ ስርዓቶች ይታይበታል፡፡ እነዚህ ክፍሎች የምልክት መልዕክቶችን ለመተርጎም፣ የድምጽ ቃናንና የሰውነት መልዕክትን ለመለወጥ ትልቅ ፋይዳ የሚሰጡ በመሆኑ         ‹‹ የሴቶች ስሜት ›› በሚል መጠሪያ ይገለጻሉ፡፡
ወንድ ፊት ለፊት ለሚደረገው የመረጃ ልውውጥ የሚረዳው የአእምሮው ክፍል ከ 4 አስከ 7 አካባቢዋች ላይ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የወንድ ጭንቅላት የተፈጠረው ወይም ቀስ በቀስ እያደገ የመጣው የርስ በርስ ግንኙነት ከማዳበሩ ይልቅ የጠፈር ስራ በማከናወን ላይ በመሆኑ ነው፡፡

ሴቶች ውሸትን ያስታውሳሉ፣

በምስራቅ ካሮሊና ዩኒቨርስቲ ረዳት የስነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ኤሪክ ኤቨርሀርት እና ጓደኞቻቸው ከ 8 እሰከ 11 ዓመት በሚሞላቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች ላይ ባደረጉት ጥናት ሁለቱም ጾታዋች የሰዋችን መልክና ገጽታ የሚያስታውሱት በተለያ የአእምሮ ክፍሎቻቸው ነው፡፡ በጥናቱ መሰረት ወንዶች ነገሮችን ለማስታወስ የሚጠቀሙት የቀኝ አእምሮአቸውን ሲሆን ሴቶች የግራ ክፍላቸውን ነው፡፡ ሴቶች የግራ አእምሮአቸውን መጠቀማቸው በፊት ገጽታ ላይ የሚታዩ ጥቃቅን ለውጦችን ለይቶ ለማወቅ የረዳቸው ሆኗል፡፡
ሴቶች ራሳቸው የዋሹትንም ሆነ የትኛው ሰው የዋሻቸው መሆኑን የሚያስታውሱ ሲሆን ወንዶች ግን ውሸታቸውን ይረሳሉ፡፡             ‹ ሂፓካምፓስ › የሚባለው የአእምሮ ክፍል ትዝታዋችን የማከማቸትና ፈልጎ የማምጣት ተግባር ያከናውናል፡፡ ይህ ክፍል ኦስትሮጅን በተባለ ንጥረ ነገር የተሞላ ሲሆን ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ቶሎ የማደግ አቅም አለው፡፡ ለዚህም ነው ሴቶች የላቀ አስታዋሽ የሆኑበት ምስጢር፡፡

በውሸት ውስጥ የሚንጸባረቁ ቃላትና ሐረጎች፣

በሰዋች የዘወትር ንግግር ውስጥ አንዱ ሌላውን ለማሳመን የተለያዩ ቃላቶችንና አባባሎችን ሲጠቀም ይታያል፡፡ የማሳመኑ ጉዳይ በእውነት ላይ ተመስርቶ አሊያም እውነታን በተዛባ መልኩ አዛብቶ በማቅረብ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ታዲያ አንዳንድ የተጋነኑ ቃላቶች መረጃው የእውነት መስሎ እንዳይሰማን ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ በእውነቱ ›› ፣ ‹‹ ከልብ ›› እና ‹‹ በግልጽ ሁኔታ ›› እያለ የሚናገር ሰው ለእነዚህ አባባሎች ያለው እውነት ግን በጣም ዝቅ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡
አንዳንድ ተናጋሪዋች ‹‹ ከአክብሮት ጋር ›› … ‹‹ እጅግ የተከበራችሁ ››…. ወዘተ በማለት አድማጩን ቢደልሉም አነስተኛ ክብር የሌላቸው መሆኑ ይታወቃል ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዋች ዋና ዓላማቸው የሚናገሩት ነገር እውነት ተደርጎ እንዲቆጠር ማሳመኑ ላይ በመሆኑ የተለያዩ አገላለጾችን ከመጠቀም ወደ ኃላ አይሉም፡፡ እነሆ ጥቂት አብነቶች፣
‹‹  እመነኝ ››
‹‹ የምዋሽበት ምክንያት የለኝም ››
‹‹ ለምን እዋሻለሁ ››
‹‹ በእውነተኛ አነጋገር ››
‹‹ የምነግራችሁ እውነት ነው ››
‹‹ ለፈጣሪ ታማኝ ነኝ ››
‹‹ በእናቴ መቃብር እምላለሁ ››
‹‹ ፈጣሪን ምስክር አድርጌ … ››
‹‹ ፈጣሪ በሞት ይቅጣኝ ››

ውሸታሞችን በኮምፒውተር መያዝ ፣

በሰለጠነው የኮምፒውተር ሳይንስ ዘመን ኮምፒውተር ሰዋች መዋሸት አለመዋሸታቸውን የሚለይበት ቴክኖሎጂ እውን ማድረግ ችሏል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ፓሊግራፊ የሚባል ሲሆን የሰዋቸን አተነፋፈስ፣ የአተነፋፈስ መጨመር ወይም መቀነስን ያሳያል፡፡ ሰውየው ወይም ሴትየዋ እውነት የሚናገሩ ከሆነ ምንም ዓይነት ለውጥ አይታይም፡፡
እንደ አሜሪካ ፓሊግራፊ ማህበር መረጃ ከሆነ ባለፉት 25 ዓመታት 250 የሚደርሱ ምርምሮች ተደርገው ሁሉም የፓሊግራፊ መሳሪያን ትክክለኛነት አሳይተዋል፡፡ በቅርቡ የተደረገ ሌላ ጥናትም ይህ ዘዴ ለመቶ ፐርሰንት የቀረበ እውነት ማሳየቱ ተመስክሯል፡፡ መሳሪያው በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ቴሌቪዥን ቶክሾው ላይ የሚታይ ሲሆን ተመልካቾች የትኛው እንግዳ ንጹህ ወይም ታማኝ መሆኑን ይለዩበታል፡፡ በርግጥ ፓሊግራፊ ይህን ያህል ውጤታማ ቢሆንም በፍርድ ቤቶች አካባቢ እንደ አንድ ማስረጃ የሚቆጠርበት አሰራር እሰካሁን ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ውሸትን በድምጽ መለየት፣

በድምጽ ውሸትን ለመለየት የሚያስችሉ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች የድምጽ ቃና፣ የድምጽ ፍጥነትና የድምጽ መጠን ናቸው፡፡ አንድ ሰው በውጥረት ውስጥ ካለ የሚንሳጠጥ ድምጽ የሚፈጥር ሲሆን ፍጥነቱና መጠኑም ይጨምራል፡፡ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከሆነ 70 በመቶ የሚደርሱ ሰዋች በሚዋሹበት ግዜ የድምጻቸው ቃና ይጨምራል፡፡ ብዙዋች በድንገት ውሸቱ ሲገለጥባቸው ንግግራቸው እየተቆራረጠና በመሃሉም እያረፉ …እእ..እ…ምምም… የሚል የተንተባተበ ጽምጽ ያወጣሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ስለ መረጃው አስቀድመው ባለመስማታቸውና ባለመለማመዳቸው ነው፡፡ ሁኔታው በአብዛኛው በወንዶች ላይ የሚታይ ሲሆን ሴቶቹ ይህን መሰሉን የመንተባተብ ቋንቋ የሚቆጣጠርላቸው የአእምሮ ክፍል አላቸው፡፡

አካላዊ እንቅስቃሴን ማንበብ፣

እንደሚታወቀው ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በሚዋሹበት፣ በሚጠራጠሩበት፣ ርግጠኛ ባልሆኑበት ወይም ነገሩን ባጋነኑበት ግዜ ከእጅ አንስቶ እስከ ፊታቸው የሚታየው እንቅስቃሴ መጠን ይጨምራል፡፡ በውሸት ወቅት የሚጎላው አካላዊ እንቅስቃሴ አይንና አፍንጫን ማሻሻት፣ ጆሮን መሳብና ኮሌታን መጎተትን ይጨምራል፡፡ ለምሳሌ ያህል የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን የሞኒካ ሊውኒስኪን ክስ ፍርድ ቤት ተገኝተው ለማስተካከል በሞከሩበት ወቅት 26 ግዜ አፍንጫቸውንና ፊታቸውን መነካካታቸው ተመዝግቧል፡፡

የፒኖቺዬ ውጤት፣

ሳይንቲስቶች በሚጠቀሙበት ልዩ ካሜራ አማካይነት አንድ ሰው ሲዋሽ ደም ወደ ሰውነት ክፍሉ ሲፈስና አፍንጫው እያደገ ሲሄድ መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህ ወቅት የደም ግፊት እየጨመረ አፍንጫን እንደሚነፋና ሰውየው አፍንጫውን ደጋግሞ በማከክ እንደሚደሰት ታውቋል፡፡
በቺካጎ የሚገኘው የማሽተትና የመቅመስ ህክምና እና የጥናት ድርጅት ሳይንቲስቶች እንደሚገልጹት አንድ ሰው በሚዋሽበት ግዜ ከሰውነቱ ውስጥ ካቲኮላሚን / catecholamines/ የተባለ ኬሚካል ስለሚለቅ በአፍንጫ ውስጥ የሚገኙ ቲሹዋች አፍንጫ እንዲያብጥ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ይህን እብጠት በተለየ መሳሪያ ካልሆነ በስተቀር በግልጽ አይኖች ማስተዋል አይቻልም፡፡ በጣም የሚያስገርመው ደግሞ ሰውየው ሲዋሽ ብልቱም ማበጡ ነው፡፡ ስለዚህ ሰውየው መዋሸት አለመዋሸቱን ማረጋገጥ ካልተቻለ ሙታንቲውን ወደ ታች ማውረድ ይጠቅማል፡፡

No comments:

Post a Comment