ፈስ ሳይንሳዊ በሆነ አካሄድ ወጥ ትርጉም እንዳለው
ይታወቃል ፡፡ ነገር ግን በወንዶችና ሴቶች ዓይን ነጥለን ካየነው ሁለት የተለያዩ ትርጉሞች መስጠቱ ግድ ነው ፡፡
ከሴት አኳያ -- አሳፋሪ ተረፈ ምርት
ከወንድ አኳያ --- ከወንድ ጋር የተቆራኘ፣ ራስን
መግለጫና መጨረሻ የሌለው የመዝናኛ ምንጭ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
ፈስ ግዜና ቦታ አይመርጥም ፡፡ አንዳንድ ሰዋች
ወንዶች ከሴቶች ይልቅ ብዙ ግዜ ይፈሳሉ ይላሉ ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ወንዶች በስብሰባ ፣ ስራ ቦታ፣ በእምነት ተቋማት፣ በየመንገዱ
ያለርህራሄ ይተኩሱታል ማለት ነው ፡፡ በሌላ በኩል ይህ አባባል እውነት ከሆነ ሴቶች ፈስን በጣም በመቆጠብ መጨረሻ ላይ ግን አስገምጋሚ
ጋስ ያስወነጭፋሉ እንደ ማለት ነው ፡፡
የፈስ ሽታ የሚመጣው አነስተኛ መጠን ካላቸው የሃይድሮጅን
ሰልፋይድ ጋስና መርካፕታን ከተባለው ንጥረ ነገር ድብልቅ ነው ፡፡ እነዚህ ድብልቆች ሰልፈርን ይዘዋል፡፡ ምግብ ውስጥ ብዙ ሰልፈር
ካለ የፈስ ሽታም ጠንካራ እየሆነ ይሄዳል፡፡ አንድ ሰው በቀን በአማካኝ ግማሽ ሊትር የሚደርስ ፈስ ሊያመነጭ ይችላል፡፡ ፈስ ወደ
ፈሺው አፍንጫ ቶሎ ከመድረስ ይልቅ ከ 13 እስከ 20 ሰከንድ ሊቆይ ይችላል፡፡ ፈስ በድምጽ ፍጥነት የሚጓዝ ቢሆን ኖሮ ሽታውንም
ወዲያው ማጣጣም በተቻለ ነበር ፡፡
ልብ ብላችሁ ከሆነ በሴቶች ሽንት ቤት ውስጥ የፈስ
ድምጽ የሚሰማው በእንግዳ ስሜት በጣም አልፎ አልፎ ነው፡፡ ፈስ ከተሰማ ይህን አድራጊዋ ፣ የሰሙ ሰዋች ከአካባቢው እስኪርቁ ድረስ
እዛው ልትደበቅ ትችላለች፡፡ በወንዶች ሽንት ቤት ግን ፈስ የበዓል ማዳመቂያ ወይም የጀግንነት ምልክት ይመስል በከፍተኛ ድምጽ ሲንጓጓ
ነው የሚውለው ፡፡
በነገራችን ላይ በየትኛውም የዓለም ማዕዘን የምትገኝ
ሴት ብዙ የሚያበሳጫትና መታገስ የማትፈልገው ነገር አለ ከተባለ በፈስ ጉዳይ ነው ፡፡ በጥንት ዘመን ወንድ ልጆች አስር አመት ሲሞላቸው
ያላቸውን ብቃትና ጥንካሬ ከሚለኩባቸው መንገዶች አንዱ የሚፈሱት ፈስ ምን ያህል ርቀት ድረስ ይሰማል የሚል ነበር ፡፡ አንዳንድ
አካባቢ ፈስ በአደባባይ ቢፈሳም የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይደለም ፤ አንዳንድ አካባቢ ደግሞ መሸማቀቅ ይስከትላል ፡፡ በአንድ ወቅት ፕሬዝዳንት ኦባማ ንግግር እያደረጉ ‹ ጠ ረ ረ ረ ር ር …. › የሚል
ድምጽ ይሰማሉ ፡፡ ንግግራቸውን ገታ አድርገው ወደ ታች
ካዩ በኃላ ‹‹ sorry for
the gas ! ›› ብለው
ንባባቸውን ቀጠሉ ፡፡ ወደ ታች ዝቅ ብለው ሲመለከቱ የሌላ ነገር ድምጽ ሳይመስላቸው አልቀረም ፡፡ አንድ የኛ
ሀገር መሪም ንግግር እያደረጉ ፈሳቸውን አንጣረሩት፡፡ ደንገጥም ሳይሉ ንግግራቸውን ቀጠሉ ፡፡ ምናልባት በለሆሳስ ነው የፈሳሁት
ብለው አስበውም ይሆናል ፡፡ ግን ማይክራፎኑ ገዳዩን አጋኖ ቁጭ አደረገው ፡፡ ምናልባትም ከጆርጅ ቡሽ ጋ ጓደኝነት ይኖራቸው ይሆናል
፡፡ ቦብ ውድዋርድ የተባለ ጸሀፊም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ በፈስ ነክ ቀልዶች በእጅጉ እንደሚንፈቀፈቁ ጽፏልና ፡፡
ዴይሊ ሜል የተባለው ጋዜጣ ደግሞ የሚላዊ ፕሬዝዳንት
ቢንግዋ ሙታኒካ በየአደባባዩ መፍሳትን ህገ ወጥ ድርጊት በማድረግ ቅጣት እንዲጣል ሀሳብ ማቅረባቸውን ይነግረናል፡፡ እንደ ጋዜጣው
አስተያየት ከሆነ ህጉ የተረቀቀው ህዝቡ ኃላፊነት የሚሰማውና በስነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን ከማሰብ አንጻር ነው ፡፡
ሳቅ አለም አብራህ ትስቃለች፣ ፍሳ ለግዜውም ቢሆን
ሁሉም ሳቃቸውን ያቆማሉ የሚል ቀልዳዊ አባባል አለ ፡፡ ወፍ የምትጮኀው እንዳገሯ ነውና ወደኛ ስንመጣ ፈስ በቀላሉ ‹‹ ፈሳም
! ›› የሚል ስድብ ያሰጣል፡፡ ‹‹ ይሄ ፈሳም ነው ! ›› ከተባለ ለቁም ነገር የማይበቃ፣ ፈሪና የሚናቅ መሆኑን ሊጠቁም ይችላል ፡፡ እናም ለመፍሳት ግራና ቀኝ መመልከት ፣ ከተለቀቀም በኃላ
ምን ያህል ይሸት ይሆን ? ብሎ አፍንጫን እንደ ውሻ ወደፊት መቀሰር ፣ ይታወቅብኝ ይሆን ? ብሎ አይንና ጆሮን ወደ ጎን ማሽሟጠጥ
ይከተላል፡፡
ፈስን ጋስ ነው ብሎ የሚቀበል ትውልድ ገና አልመጣም
፡፡ ህጻናት እንኳን ፈሰኛን የሚያወግዙበት ስነ ግጥም አለቻቸው ፡፡
ፈስ ፈሶ ፈሳራራ
ቆርጦ ቆርጦ ደም ያሳራ
ደሙ ሲረጋ በለው ባለንጋ
አለንጋው ሲበጠስ
ምንቄው ይበጠስ ! / ምንቄ ግን ምንድነው ?
/
ወደ አማራው ክልል ስንጓዝ ደግሞ ፈስ ሃይለኛ
የጦር መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ፡፡ የቆሎ ተማሪዋችና ደብተራዋች ‹ የጎዳቸውን › ሰው ለማጥቃት በወፍ ቋንቋቸው ይደጋግማሉ ፡፡
ይህን ቋንቋ ከአዲስ ኪዳን ማውጫ ተውሰን ‹‹ የደብተራ ወንጌል
›› ወይም ‹‹ የደብተራ ስራ ›› ፤ አሊያም ከብሉይ ኪዳን ተነስተን
‹‹ መጽሀፈ ደብተራ ›› ወይም ‹‹ ትንቢተ ደብተራ ›› ለማለት እንኳን የሚያስቸግር ይመስለኛል ፡፡ ብቻ ከመጽሀፍ ቅዱስ ክልል ውጪ
ቢሆንም የዋሉበት ድግምት አያሳፍራቸውም ነው የሚባለው ፡፡ ያ - በግዕዝ ቋንቋ የተቃመበት ሰው ታዲያ ቀኑን ሙሉ ለዚያውም ቦታ
ሳይመርጥ እንደ አህያ ዘረጥ - ዘረጥ ሲያደርግ ይውላል፡፡ አቤት መሳቀቁ አይታያችሁም ፡፡
‹‹ ወይ ጉድ ያ- የተበላሸ ባቄላ እኮ ነው ?! …
‹‹ አዬ አያ እንትና ያ - የማልወደውን ሻሜታ
ግቶኝ ግቶኝ !…
መጨረሻ ላይ እውነትን መካድ ሁሉ ሊመጣ ይችላል
፡፡ ‹‹ አይ ይህ ሆዴ … ሆዴ እኮ ነው እንዲህ የሚጮኀው ? …
››
አህያ የሚለው ቃል የአለቃ ገብረሃና ቀልዶችን
አስታወሰኝ ፡፡ ሴትየዋ በእንስራ ውሃ ተሸክማ ቁልቁል ትወርዳለች ፡፡ ቁልቁለቱ በጣም ያዘቀዘቀ በመሆኑ ዘጭ - ዘጭ እያለች በፍጥነት
እንድትወርድ ያስገድዳታል ፡፡ በዚህ ግዜ ፈሷ ያመልጣትና ዛጥ ዛጥ ታደርገዋለች ፡፡ ይሄኔ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ‹‹ አንተ ጊዮርጊስ አሁንስ እንደ አህዮቹ ልታደርገኝ ነው ? ›› ትላለች
፡፡
‹‹ እ.ህ.ህ ! … ›› እያለ ጉሮሮውን የሚጠራርግ ሰው ድምጽ ሰምታ ዘወር
ስትል አለቃን አየች ፡፡
‹‹ ውይ አለቃ ! መቼ መጡ ? ›› አለች የምንተፍረቷን
‹‹ ጊዮርጊስ አህዮቹን ይዞ የወረደ ግዜ !
›› ሲሉ ኩም አደረጓት
ለነገሩ በዚህ ረገድ አለቃም ኩም የሚሉበት አጋጣሚ
ጥቂት አይደለም ፡፡ ልዩነቱ ሌሎቹን እንደሚተርቡ ሁሉ በራሳቸው ላይም መቀለድ መቻላቸው ነው ፡፡ አንድ ወቅት እንዲህ ሆነ ፡፡
የቅርብ ዘመዳቸው ስለሞተ አልቅሰው ፣ ቀብረው ቢደክማቸውም ወደ ቤታቸው መሄድ አልቻሉም ፡፡ ማታ ራት ተበልቶ ተጎዝጉዞ ከለቀስተኛ
ጋር በመደዳ ይተኛሉ ፡፡ ትንሽ ቆይተው ግን ፈሳቸው መጣባቸው ፡፡ ይሄኔ ቀስ ብለው ያለ ድምጽ ሊፈሱ አስበው ቂጣቸውን በእጃቸው
ከፍተው ቢለቁት ‹ ጠ ረ ረ ረ ር … ! › ብሎ አጋለጣቸው ፡፡ እናም ምነው አለቃ ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ ?! ወዘተ የሚሉ
አፋጣጭ ጥያቄዋች ከመወርወራቸው በፊት ‹‹ አዬ እድሌ መልግጌ አባስኩት አይደል ? ›› በማለት ለቀስተኛውን አሰፈገጉት
፡፡
በአንድ እጁ የጀግንነት በሌላኛው የፍርሃት ችቦ
ለኩሶ የሚጓዘው ፈስ በተረብ፣ በተረት፣ በአባባል፣ በጥናትም የደለበ ነው ፡፡ የጥናቱን ካዝና ስንከፍተው 96.3 ከመቶ የሚደርሱት
ወንዶች ፈስ እንደሚፈሱ ሲያምኑ የሴቶች ቁጥር 2.1 ከመቶ ብቻ መሆኑን እንረዳለን ፡፡ ወንዶች በአማካኝ በቀን 12 ግዜ በመፍሳታቸው
ከ 1.5 እስከ 2.5 ሊትር ጋስ ያጣሉ ፡፡ ይህ መጠን አንድ አነስተኛ ፊኛን ለመሙላት በቂ ነው ፡፡ በሌላ በኩል ሴቶች በአማካኝ
በቀን ሰባት ግዜ ሲፈሱ ከ 1 እስከ 1.5 ሊትር ጋስ ያስወጣሉ ፡፡
በዓለማችን ታዋቂ ፈሳም ተብሎ የተመዘገበው ጆሴፍ
ፓጁል እ.ኤ.አ በ1892 በፓሪስ ከተማ የፈስ ትዕይንት ያቀርብ ነበር ፡፡ ድርጊቱን የሚጀምረው የሆነ ታሪክ እያወራ ሲሆን ይህንንም
የተለያዩ ድምጾች ባሉት አሰገራሚ ፈሱ ማጀብ ይችላል፡፡ ይህ ሰው በላስቲክ ውስጥ ሲጋራ ካስገባ በኃላ ላስቲኩን በቂጡ ቀዳዳ ውስጥ
በመጨመር ያጨሳል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዋሽንቱን ቂጡ ላይ ከሰካው ላስቲክ ጋር በማያያዝ የሀገሪቱን ብሄራዊ መዝሙር ይጫወታል ፡፡
በዚህ ድርጊቱ ከወንዶች ይልቅ ፈስ የሚጠሉት ሴቶች በጣም እንደሚስቁ ተዘግቧል፡፡ አንዳንዶች እንደውም ሳቅ በማብዛታቸው እየታመሙ
ወደ ሆስፒታል እሰከመወሰድ ደርሰዋል ፡፡
ከፈስ ጋስ ውስጥ ከ 50 እስከ 60 ከመቶው ናይትሮጂን፣
ከ30 እስከ 40 ከመቶው ካርቦን ዳይኦክሳይድ እንዲሁም ከ 5 እሰከ 10 ከመቶው የሚደርሰው ሚቴን ነው ፡፡ ሚቴን ጋስ መሬት ውስጥ
የተቀበረ ፈንጂ እንዲፈነዳ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ አንድ ጥናት ብዙ ለመፍሳት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በምግብ ግዜና
ከምግብ ውጪ ብዙ ማውራት መሆኑ ታውቋል ይለናል፡፡ ፈስን በከፍተኛ ደረጃ በማመንጨት በኩል ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ምግቦች የአበባ
ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ዳቦ፣ ባቄላ፣ ነጭ የወይን ጠጅ እና አትክልትና ፍራፍሬዋች ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ ከከብቶችና ከበጎች ፈስ የሚወጣው
የሚቴን ጋስ በመላው ዓለም 35 ከመቶ ያህል በመሆኑ የመሬት ሙቀት እንዲጨምር፣ የኦዞን ሌዪር ቀዳዳ እንዲሰፋ ትልቅ አስተዋጽኦ
ያደርጋል ፡፡ በመሆኑም ለዓለማችን ትልቁ ስጋት አሸባሪነት ሳይሆን የላሞች ፈስ ሳይሆን አይቀርም ፡፡