Wednesday, December 11, 2013

አሳዛኙ የመንግስት ሰራተኛ




የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው ኢትዮጽያ ውስጥ ከአንድ ሚሊየን በላይ የመንግስት ሰራተኞች ይገኛሉ ፡፡ እነዚህ ሰራተኞች አባቴ ለሚሉት መንግስት አቋርጠው የማያውቁት ጥያቄ ‹ ኑሮ ስለከበደኝ ደመወዝ ጨምርልኝ ! › የሚል ነው ፡፡ በቀደመው አሰራር ሰራተኞች በየሁለት አመቱ ጥቂትም ብትሆን የእርከን ጭማሪ ያገኙ ነበር ፡፡ ይህም ሁልግዜ ከፊታቸው የተንጠለጠለ የተስፋ ዳቦ እንዳለ ስለሚጠቁማቸው ለመጨበጥ ይተጉ ነበር ፡፡  / ርግጥ ነው በአንድ ወቅት 320 ብር የነበረውን ደመወዝ 420 ፤ 3152 የነበረውን የመምሪያ ኃላፊ ደመወዝ 4343  ያስገባ ጭማሪ ተከናውኗል  ፤ ያው በወሩ ጭማሪው ሻጭና አከራይ እጅ ተገኘ እንጂ /

‹‹ በመርህ ደረጃ ኑሮ እየከበደ እንደሚሄድ እገነዘባለሁ ፤ ግና በተወሰነ ርቀት ብር መጨመሩ ሳይንሳዊና አዋጪ አይደለም ! ›› የሚለው ኢህአዴግ ሰራተኛው ማደግ የሚገባው የሚታይና የሚቆጠር ሀገራዊ እድገት ሲያበረክት ነው በሚል የቆየው አሰራር ላይ ‹ ታሽጓል › የሚል ወረቀት ለጥፎ ነበር - በአራት ነጥብና በቃል አጋኖ በመታገዝ  ፡፡
‹‹ ታዲያ እስከዛስ ችግሩን እንዴት እንቋቋም ? ›› አባቴ የሚሉት ሰራተኞች ባገኙት የስብሰባ አጋጣሚ ሁሉ ጥያቄያቸውን ወረወሩ ፡፡

‹‹ በረሃብና በስቃይ ቀቀለን እኮ ?! ›› በየኮሪደሩና በየመሸታው ቤት ይህን ስሜት የተነፈሱት ደግሞ ኢህአዴግን የእንጀራ አባት ብለው የደመደሙት ናቸው ፡፡

የደመወዝ ጥያቄ ከለውጥ መሳሪያዎች አንጻር

መንግስት ለሁሉም ወገኞች በቂ ምላሽ መስጠት የሚቻለው ሳይንሳዊ አሰራርን በመዘርጋት ነው በሚል የጥናት ቁፈሮ ጀመረ ፡፡ ማዕድንን ፈልጎ ለማውጣት አታካች አመታትን አሳልፏል ፡፡ በመጨረሻም ቢፒአር / Business Process Reengineering / የተባለ የከበረ ድንጋይ መገኘቱ ይፋ ሆነ ፡፡ ከወጪ ፣ ግዜ ፣ ጥራትና ደረጃ መመዘኛዎች አንጻር አሰራሩ ቀልጣፋ ፣ ፍትሃዊና አንጀት አርስ መሆኑ ተነገረለት ፡፡ ሰራተኞች የፍልስፍናውን ሀሁ በየተቋማቸው በሶስት ቀን ጥልቅ ጥናት ከአኩዋ አዲስ ጋር አጣጣሙት ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙዋቹ ቀድመው መማር የፈለጉት ስለ ደመወዝ የሚያትተውን ምዕራፍ ነበር ፡፡ ይህ ምዕራፍ ግን እዚህ ጥራዝ ውስጥ አልነበረም ፡፡ እንደውም ትንሽ ቆይቶ ሀሴትን ሳይሆን መርዶን ማዘሉንም አበሰረ ፡፡ ጥቂት የማይባሉትን ከእኔ አሰራር ጋር መጓዝ አትችሉም ፣ የትምህርት ዝግጅታችሁ በቂ አይደለም ፣ አመለካከት ሲቀነስ የተንጠለጠለ ብቃት እኩል ነው  C  ማይነስ በሚል ከስራ ዉጪ አድርጓቸዋልና ፡፡ በአንዳንድ መ/ቤትማ ብቀላና ፖለቲካ ስራቸውን ሰርተዋል ፡፡

ከአውሎ ንፋሱ የተረፉት ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ ማበረታቻና የደመወዝ ጭማሪ የግድ ያስፈልጋል የሚል ዳግማዊ ጥያቄ ከማንሳት አልተቆጠቡም ፡፡ መንግስትም የሰራን ለመሸለምና ለማሳደግ የሚቻለው የዚህን ተከታይ ሳይንስ እውን በማድረግ ነው በሚል ሌላ ቁፋሮ ውስጥ ገባ ፡፡ ከአመታት በኃላም ሚዛናዊ የውጤት ተኮር / Balanced Score Card / ስርዓትን አስተዋወቀ ፡፡ በዘጠኝ ደረጃዎች የተዋቀረው ውጤት ተኮር ከስትራቴጂ ግንባታ ጀምሮ እስከ ክትትልና ግምገማ ድረስ የሚዘረዘር ነው ፡፡ ጥናቱ እንደ አሹ ቤት ስጋ የሚያስጎመዥ ነው ፡፡ በደረጃ ሰባት ላይ የሚገኘው ‹‹ አውቶሜሽን ›› የእያንዳንዱን ፈጻሚ ስራ መመዝገብና መተንተን የሚችል በመሆኑ ሰራተኛውን ከለጋሚው ለመለየት የሚያስችል ነው ተብሏል ፡፡ በሌላ አነጋገር አጭበርባሪው ፊርማ ፈርሞ ሹልክ ማለት ወይም መድረክ ላይ በሚያቀርበው አስመሳይ ተውኔት ብቻ ተላላ ሃላፊዎችን መሸወድ አይቸልም ፡፡ ፋብሪካና ኢንድስትሪ ውስጥ ባይሆንም ከቢሮ የሚታደለውን ስራ ቆጥሮ ይረከባል በኃላ ደግሞ ቆጥሮ ያስረክባል -  ይህ ማለት ግን የሚሰራው ንብረት ክፍል ውስጥ ነው ወይም ከጥበቃ ስራ ጋር በስተደቡብ ይዋሰናል ማለት አይደለም ፡፡ በፍጹም ፡፡ ርግጥ ነው ሳይንሱ አንድ ኃላፊ እንደ ጥበቃም እንደ ንብረት ክፍል ኤክስፐርትም ሁለገብ እንዲሆን ያበረታታል ፡፡ እንግዲህ በዚህ ምክንያት ነው ሳይንሱ ስራና ሰራተኛን ያገናኛል የተባለለት ፡፡

በመሆኑም ምርጥ ፈጻሚዎች ተገቢውን ሽልማትና የደመወዝ እድገት ለማግኘት እንዲችሉ በመነገሩ ስራው ተጧጧፈ ፡፡ በአንዳንድ ተቋማት የምርጥ ፈጻሚዎችና ምርጥ አመራሮች ፎቶግራፍ ሳይቀር መለጠፍ ጀመረ ፡፡ አመቱ መጨረሻ ላይ ሽልማትና ዕድገት የሚጠበቅ ቢሆንም መንግስት እፍርታም ሆነ ፡፡ ለምርጦች እውቅና ከመስጠት ይልቅ በርካታ ምክንያቶችን መደርደርን ‹‹ ደረጃ አስር ›› አደረገው ፡፡ ግምገማው ትክክል አይደለም ፣ በተቋሙ መሰረታዊ ለውጥ ካልመጣ ሰራተኞችም የተለየ አፈጻጸም ሊኖራቸው አይችልም … የሚሉትን እንደ ዋና ዋና ማሳያነት ማነሳሳት እንችላለን ፡፡

ዛሬ አገር ጥለው የሄዱት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ በአንድ ወቅት የመንግስት መ/ቤቶች ቢፒአርን እንዴት እንደሚጠቀሙበት በቂ ትኩረትና ዝግጅት ሳያደርጉበት ወደ እንቅስቃሴ በመግባታቸው መፍትሄ ሊያመጣ አልቻለም በማለት መግለጫ ሰጡ ፡፡ ለነገሩ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ ሆኖ እንጂ ቢፒአርና ቢኤስሲ ስልጠና ሲሰጥ ብዙ ቸግሮች መኖራቸውን መስማት ነበረባቸው ፡፡ አንደኛው ችግር በስልጠናው ወቅት ከሰራተኛው የተነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን አሰልጣኞች በበቂ ሁኔታ መመለስ አለመቻላቸው ነው ፡፡ እናም አሰልጣኞች ወዴት እየሄዳችሁ ነው ? ሲባሉ ‹‹ ያልገባኝን ነገር ላልገባቸው ሰዎች ልነግርን ነው ›› አሉ ተብሎ እስካሁንም ይቀለዳል ፡፡

የመንግስት ሰራተኛው ሁለቱን የለውጥ መሳሪያዋች ለማስፈጸም ዛሬም እየተንገታገተ ቢሆንም ቃል በተገባለት የደመወዝ ጭማሪና በሳይንሳዊ አሰራሮቹ መካከል ያለው ተጨባጭ ቁርኝት ሊገለጽለት አልቻለም ፡፡ ብዙ ተቋማት ውስጥም የለውጡ ስራ መሬት የወረደ ፣ የሚታይና የሚቆጠር ከመሆን ይልቅ አንዳንዶች ‹ ኮስሞቲክ › እያሉ እንደሚጠሩት ሳምንታዊ ቅጽ መሙላት ፣ ደረት ላይ ባጅ ማድረግ ፣ ጠረጼዛ ላይ ስምና የስራ ድርሻን ማስተዋወቅ እየሆነ መጥቷል ፡፡ የአዲሱ አሰራር ግብ ይህ አይደለም ፤ ሰራተኛው አዲሱ አሰራር / ሳይንስ / ህይወቴን ለመቀየር የሚያስችል መሰረት የለውም የሚል ድምዳሜና የጥርጣሬ ዳርቻ ላይ አዳርሶታል ፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ መርፌ ከለገመ ቅቤ መብሳት አይችልም የሚባለውን ብሂል ይኮረኩራል ፡፡

አድጎ ያላደገው የውሎ አበል

ሌላው የመንግስት ሰራተኞች መሰረታዊ ጥያቄ የውሎ አበል ጉዳይ ነው ፡፡ እንደሚታወቀው ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራበት የቆየው የውሎ አበል ክፍያ ዝቅተኛው 35 ከፍተኛው ደግሞ 70 ብር ነበር ፡፡ ይህ ክፍያ በተለይም ከ 2000 ዓም በኃላ አስቂኝ ገጽታ ይዞ ነበር ፡፡ ሰራተኛው እንደነገሩ የቆመ አልቤርጎን በ70 ብር ተከራይቶ ምግብ ሳይበላ ነበር በፈጣሪ ቸርነት ስራውን ሲሰራ የቆየው ፡፡ ይህ ችግር የመስክ ሰራተኞች መኪና ውስጥ እንዲያድሩ ፣ በየሄዱበት ዘመድ ብቻ ሳይሆን ዘመዳቸው ድንገት የተዋወቃቸውን ሰዎች እንዲፈልጉ ፣ አንድ አልጋ ለሁለትና ሶስት ሆነው እንዲከራዩ አድርጓቸዋል ፡፡

ከስንት አቤቱታ በኃላ አዲሱ የውሎ አበል ታህሳስ 27 ቀን 2004 ዓም በሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርቦ ጸደቀ ፡፡ በዚህ ግዜ አልጋ ብቻ ሳይሆን ኑሮ ጣራ ያለፈበት በመሆኑ አበሉ ከፍተኛ እንደሚሆን ተጋኖ ተወርቶለት ነበር ፡፡ መንግስትም ለማስተካከያ 465 ሚሊየን 838 ሺህ ብር ተጨማሪ ማድረጉን ገለጸ ፡፡ ይህ ትልቅ የሚመስል ገንዘብ ሲተነተን ግን የብዙዎቹን አንገት አስደፋ ፡፡ አበሉ ወረዳን ፣ ዞንና ዋና ከተሞችን ብቻ ሳይሆን የደመወዝ እርከንንም ከፋፍሎ የሰራ ሆነ ፡፡ ለምሳሌ ያህል እስከ 2248 ብር ደመወዝ የሚከፈላቸው ሰራተኞች ሃዋሳ ከሄዱ 182 ብር ፣ ከ2249 እስከ 3816 ብር ደመወዝ የሚያገኙ 192 ብር ፣ ከ3817 ብር በላይ ደመወዝ ተከፋዮች ደግሞ 201 ብር ያገኛሉ ፡፡ ይህ በዋና ከተማ ደረጃ በመሆኑ ትልቁ ክፍያ ነው ፡፡ ሰመራ ፣ ባህርዳር ፣ ድሬደዋ ወዘተ ሲጓዙ ደግሞ የገንዘቡ መጠን እየቀነሰ ይመጣል ፡፡ ትንሹ የአበል ክፍያ እንደቅድም ተከተሉ 83 ፣ 92 እና 101 ብር ነው ፡፡

ብዙ የተወራለት የአበል ጭማሪ የወቅቱን የሆቴሎች የአገልግሎት ዋጋ ፍጹም ያላገናዘበ ነው ፡፡ አንድ ተራ አልጋ 90 እና 100 ብር በሚጠራበት በአሁኑ ወቅት 111 ብር ይዞ ከቤተሰብ መራቅን የመሰለ መሳቀቅና ቅጣት ከየት ይገኛል ? ይህ መስተካከልን የሚጠይቅ አንደኛው ችግር ሲሆን ሁለተኛው  ለመስክ የሚወጣን ሰራተኛ በአበል ማበላለጡ ተገቢ ያለመሆኑ ጉዳይ ነው ፡፡ አልጋውና ምግቡ እንደሆነ ለሁሉም እኩል ነው ፤ ታዲያ - የቢሮ ቢሮክራሲ ጫካና በረሃ ድረስ አብሮ እንዲጓዝ መፍቀድን ምን አመጣው ? በስራው ውጤት ከመጠበቅና ከፍትሃዊነት አንጻርም  ፍጹም የማይጠቅምና ትክክል ያልሆነ  አሰራር ነው ፡፡

የተጋነነ የታክስ መጠን

የኑሮ ውድነቱ ጫና በደመወዝ ጭማሪም ሆነ በውሎ አበል ማካካስና ማስተካከል ያልቻለው የመንግስት ሰራተኛ በመንግስት አይን እንቁላል የሚጥል ዶሮ ነው ወይም ሳያንገራግር የሚታለብ ላም ፡፡

የመንግስት ሰራተኛ እንደሌሎች ነጋዴዎች ወይም ባለሀብቶች የስራ ግብርን ለማስቀረት ፣ ለማስቀነስ ፣ ለማጭበርበር የሚያስችል መሰረት የለውም ፡፡ ምክንያቱም ግብሩ የሚቆረጥበት ገና ደመወዙን ከመቁጠሩ በፊት ነውና ፡፡ ዜጎች ግብር የመክፈል ግዴታ ያለባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉም  ዜጋ ግብርን መክፈል ያለበት ፍትሃዊና እኩል በሆነ አግባብ መሆኑ አያጠያይቅም ፡፡ ይሁን እንጂ ትንሹ ደመወዝተኛ ትልቅ ግብር እንዲከፍል መደረጉ ያሳምማል ፡፡ በአመት ብዙ መቶ ሺህና ሚሊየን ብር የሚያስገቡት ነጋዴዎች ግብር በዛብን ብለው በመደራደርና በማስቀነስ ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ገንዘብ እየከፈሉ ጉልበት በሌለውና መድረሻ ቢስ በሆነ  ዜጋ ላይ መጨከን አግባብ አይደለም ፡፡

አንድ ምሳሌ እንውሰድ ፡፡ በህጉ ቀመር መሰረት ከታክስ ነጻ የሚሆኑት እስከ 150 ብር ገቢ ያላቸው ዜጎች ናቸው ፡፡ ከ 151 እስከ 650 ብር የሚያገኝ ሰው 10 ከመቶ ፣ ከ651 እስከ 1400 ብር የሚያገኘው 15 ከመቶ ፣ ከ1401 እስከ 2350 ብር የሚያገኙ 20 ከመቶ ፣ ከ2351 እስከ 3550 ብር የሚያገኙ 25 ከመቶ ፣ ከ3551 እስከ 5000 ብር የሚያገኙ 30 ከመቶ ፣ ከ5000 ብር በላይ የሚያገኙ ደግሞ 35 ከመቶ ይቆረጥባቸዋል ፡፡ ርግጥ ነው በሁሉም ስሌት ላይ ተቀናሽ የሚሆኑ ጥቂት ገንዘቦች አሉ ፡፡

በወር 3817 ብር ደመወዝ የሚያገኙት አቶ ፍርድ ያጣው 30 ከመቶ የግብር እዳ ሲከፍሉ  አንድ ሺህ 145 . 10 ያጣሉ ፡፡ በቀመሩ መሰረት 412 .50 ሳንቲም ሲቀነስላቸው 732 .60 በየወሩ ግብር ይከፍላሉ ማለት ነው ፡፡ ከዚህ ላይ ሰባት ከመቶ የጡረታው ሲወራረድ  267 .19 ይቀነስባቸዋል ፡፡ በአጠቃላይ ግብርና ጡረታው 999 .79 ስለሚያሳጣቸው ለግዜው ኪሳቸው የሚገባው ገንዘብ 2818 ብቻ ነው ፡፡ ለግዜው ያልኩት ድምር ውስጥ ያልገቡ መዋጮችን በማስቀረቴ ነው ፡፡

እዚህ ላይ ሶስተኛው የፖለቲካ አማራጭ ይሁን መንገድ እከተላለሁ የሚሉትን የአቶ ልደቱ አያሌውን ሀሳብ ማድነቅ ግድ ሊል ነው ፡፡ እኚህ ፖለቲከኛ በአንድ ወቅት ለመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ከመጨመር ይልቅ የተጋነነውን ታክስ መቀነስ ይጠቅማል ብለው ነበር ፡፡ እሳቸው ያነሱት ከኢንፍሌሽንና ከነጋዴው ነጣቂ እጆች ለማስቀረት በሚል ቢሆንም እኔ ደግሞ ከፍትሃዊነት አንጻር ጭምር የሚለውን እጨምርበታለሁ ፡፡ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ለመንግስት ሰራተኛው መስራት አይኖርበትም ….

የአቶ ፍርድ ያጣው የበዙ ቃል ኪዳኖች

በ80 ቢሊየን ብር ወጪ 5250 ሜጋዋት እንዲያመነጭ እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የገንዘብ መሰረቱን ሀገር ቤት ነው ያደረገው ፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ የስራው 24 ከመቶ ተጠናቋል ፡፡ ለግንባታው ቃል ከተገባው 10 .2 ቢሊየን ብር ሊሰበሰብ የቻለው ግን 5.2 ቢሊየን ብር ብቻ ነው ፡፡

ቃል የገቡ ሰዋችና ድርጅቶች ሀሳባቸውን ለምን አጠፉ ? ወይም ለመክፈል ለምን መዘግየት ፈለጉ ? ብዙ የመላ ምት ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል ፡፡ በጣም የሚያስገርመው ግን የመንግስት ሰራተኛ እንደሌሎቹ ቃሌን አጥፋለሁ ወይም ‹ ይብራብኝ › ቢል እንኳን አለመቻሉ ነው ፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰራተኛ ሙሉ ደመወዙን በአመት ለመክፈል ቃል ከገባ ልክ እንደ ግብሩ ደመወዙን ከመጨበጡ በፊት በሂሳብ ክፍል ተቆርጦ ስለሚወሰድበት ፡፡ ስለዚህ አሁንም የመንግስትን ሰራተኛ ታማኝ ፣ ማምለጫ የሌለው ፣ ሳያንገራግር የሚታለብ ወዘተ ልንለው እንችላለን ፡፡ የህዳሴ ግድብ ግንባታ 76 ከመቶ ገና የሚቀር በመሆኑ ለቀጣይ አራትና አምስት አመታት አሁንም እንደ መርግ ከተጫነው ኑሮ ጋር የተለመደውን ክፍያ ቃል እየገባ ወይም ቃል እየተገባለት እንደሚከፍል ሳይታለም የተፈታ ነው ፡፡

አሁንም የ3817 ብር ደመወዝተኛውን አቶ ፍርድ ያጣውን እናምጣቸው ፡፡ የወር ደመወዛቸውን በአመት ለመክፈል ቃል ከገቡ በየወሩ የሚያስቆርጡት 318 ብር ይሆናል ፡፡ በግብርና ጡረታ 999 ብር ያጡት እኚህ ሰው ከግድቡ መዋጮ ጋር ሲደመርላቸው 1317 ብር ያስከረክማሉ ፡፡ በኪሳቸው የሚገኘው የተጣራ ገንዘብ ደግሞ ወደ 2500 ያሽቆለቁላል ፡፡

እንደሚታወቀው የሚኒስትሮች ም/ቤት የጤና መድህን ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅን በ2003 አጽድቋል ፡፡ የኤጀንሲው አላማ በየተቋማቱ የጤና መድህን የሚስፋፋበትን መንገድ ማመቻቸት ነው ፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች ከደመወዛቸው ላይ 3 ከመቶ መዋጮ ያደርጋሉ ፡፡ ይህም ስርዓት በቅርቡ እንደሚጀመር በየተቋሙ ኦሪየንቴሽን ተሰጥቷል ፡፡ በመሆኑም የደመወዛቸው ሶስት ከመቶኛ ሲሰላ 114 ብር ነው ፡፡ ከደመዛቸው ላይ የሚያስቆርጡት ገንዘብ 1431 ሲመጣ ኪሳቸው የሚቀረው የተጣራ ብር ደግሞ 2386 ይደርሳል ፡፡ አቶ ፍርድ ያጣው አንገታቸውን አቀርቅረው ስለሚኖሩ ቤት አከራያቸው ለረጅም ግዜ ታሪፍ አልጨመሩባቸውም - በመሆኑም ለሁለት ክፍል ቤት በየወሩ 1200 ብር ይወረውራሉ ፤ ይህም የተጣራ ደመወዛቸውን 1186 ያደርሰዋል ፡፡ ከቤት ኪራይ ጫና ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ አከራዮች ግፍ ለመገላገል ኮንዶሚኒየም የተመዘገቡ ቢሆንም እድላቸውም እንደ ኪሳቸው ‹ ድሃ › ሆኖ አስካሁን ስማቸውን አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ሊመለከቱት አልቻሉም ፡፡

በቅርቡ የአዲስ አበባ መንግስት አዲስ ደንብ በማውጣቱ ለሁለት መኝታ ቤት በየወሩ 561 ብር ባንክ ማስቀመጥ ግዴታ ሆኖባቸዋል - በዚህም ምክንያት የተጣራ ደመወዛቸው 625 ብር ብቻ ነው ፡፡ ‹ ዘመድ አዝማድ  ለ4 ሺህ ጥቂት የጎደለው ብር  ይገሸልጣል እያለ ቢያማኝም እኔን ማቆሚያ የሌለው መዋጮ ደህና አድርጎ እየገሸለጠኝ ነው › የሚሉት  አቶ ፍርድ ያጣው በየቀኑ ለሚጨምረው ወርሃዊ አስቤዛ ፣ ለልጆች ት/ቤት  ፣ ለልብስና ጫማ ፣ ለትራንስፖርት ፣ ለእድር ፣ ለህክምና ፣  የመሳሰሉትን ክፍያዎችን እንዴት እንደሚሸፍኑ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው ፡፡ እንግዲህ ምርኮኛው ፣ የሚታለበውና ምስኪኑ የመንግስት ሰራተኛ በአስማት ነው የሚኖረው የሚባለው ለዚህ ነው ፡፡

ተረት ተረት  ?

መንግስት የመንግስት ሰራተኛውን ድካምና ጥረት ብቻ ሳይሆን የኑሮ ውድነቱንም ጫና ግንዛቤ ወስጥ በማስገባት ሰበቦቹን ከርክሞ በቂ የሚባል የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ይጠበቅበታል ፡፡ ሁለት ዲጂት እያደግን ባለንበት ወቅት ይህ አይቻልም የሚባል ከሆነ ደግሞ አንድ ዲጂትን በተግባር ማዋል ያቃተውን ሰራተኛ ለዚህና ለዚያ አዋጣ የሚለውን ልመናና ግዴታ መገደብ ይኖርበታል ፡፡ ቢያንስ ጥያቄውን ‹ አዋጅ › ከማድረጉ በፊት ገቢና ወጪውን ለአፍታ ያህል ማመዛዘንና ማስላት ይጠበቅበታል ፡፡

የላም በረት ? !



7 comments:

  1. Very nice article. You put the facts with a sense of humour.

    ReplyDelete
  2. Nice article conveying an important message with a sense of humour.

    ReplyDelete
  3. ልጅ አሌክስ ምርጥ ዳሰሳ ነው፤በርታልን




    ReplyDelete
  4. Alexo,it's an interesting article representing the opinions of many civil servants-- '' better to be called: citizens with unheard voices '' !!
    (Alex--EWCA)

    ReplyDelete
  5. Alexo የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩትን ያህል ይስቃል አሉ አበው ሲተርቱ!! ችለነው ነው እንጂ ሁላችንም የእግር እሳት የሆነብንን ርዕሰ ጉዳይ ነው ያነሳኸው፡፡ እጆችህ ይባረኩ ወንድምአለም!!

    ReplyDelete
  6. I'm the living witness of this reality!

    ReplyDelete
  7. After short while,you are coming with the best products

    ReplyDelete