Sunday, September 23, 2012

‎‹‹ የስልጣን ዘመን ገደብ ›› - ህግና ህዝብ አክባሪ መሪ ይፈልጋል‎



መሪነት የቀደመ መስዋዕትነትን ይጠይቃል

ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ወጥታ ራሷን በራሷ የምታስተዳድረው አፍሪካ ተስፋና ህልሟን ለማሳካት በ1990 ዋቹ አካባቢ ይበል የሚያሰኝ ፓለቲካዊ ርምጃዋችን መውሰድ ጀምራ ነበር ፡፡ ይህ ርምጃ ‹ አፍሪካ ያለ እኛ ድጋፍ ማየትም ሆነ መራመድ አትችልም › ይሉ ለነበሩት ምዕራባዊያን የጠነከረ ምላሽ ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል ፡፡

ህገ መንግስታቸው ውስጥ በደማቅ ቀለም እንዲጻፍ ያደረጉት ‹‹ የስልጣን ዘመን ገደብ ›› የተረጋጋች አህጉር ብቻ ሳይሆን በአጭር ርቀት እከኳን አራግፋ የልማትና የዴሞክራሲ ተቋዳሽ ልትሆን እንደምትችልም ምልክት የፈነጠቀ ዘመናዊ አሰራር ነበር፡፡ 33 የሚደርሱ የአፍሪካ ሀገሮች የህዝብ እንጂ የጥቂት ብልጣ ብልጥ ሰዋች ርስት አይደለም በማለት ገደቡን ከሁለት ግዜ በላይ እንዳይበልጥ አድርገዋል ፡፡ ሶስት ዙር ከምትፈቅደው ሲሸልስ በስተቀር ፡፡ በርግጥ ብዙዋቹ በገደቡ ወሰን ቢመሳሰሉም አንዱ የስልጣን ዘመን ምን ያህል ዓመት ይይዛል በሚለው ልዩነት ነበራቸው ፡፡ አንዳንድ ሀገሮች ትንሹን አራት ሲያስቀምጡ አንዳንዶች ደግሞ ትልቁን ሰባት ዓመት ህገ መንግስታቸው ላይ አስፍረዋል ፡፡

ብዙዋች አንዱን የስራ ዘመን አምስት ዓመት በማድረግ ለሁለት ግዜ ያህል የፈቀዱ ናቸው ፡፡ ቤኒን፣ ቦትስዋና፣ ቡሩንዲ፣ ኬፕቨርድ፣ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐፕሊክ፣ ዴሞክራቶክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ማሊ፣ ሞሪታንያ፣ ሞሪሺየስ፣ ሞዛምቢክ፣ ናምቢያ፣ ኒጀር፣ ሳኦቶሚፕሪንስፔ፣ሴራሊዮንና ዛምቢያ እዚህ ምድብ ውስጥ ይካተታሉ ፡፡

ጋናና ናይጄሪያ አራት ኣመት ፤ የኮንጎ ሪፐፕሊክና ሩዋንዳ ሰባት ዓመት ፤  ኮሞሮስ ፣ ኤርትራና የመሳሰሉት ደግሞ ገደብ ካልጣሉ ሀገሮች ውስጥ ይመደባሉ ፡፡ ግራ የሚያጋባ ምድብ ውስጥ ለረጅም ግዜ ቆይተው ከነበሩ ሀገሮች ውስጥ ኢትዮጽያ ‹‹ የቡድን አባት ›› ሆና ቆይታለች ማለት ይቻላል ፡፡ ልክ እንደኛ በኢትዮጽያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺንም ግራ ተጋብተው እንደነበር በብሎጋቸው ላይ የሰፈረው የሚከተለው ጽሁፍ ያስረዳል ‹‹ የኢትዮጽያ ህገ መንግስት ትልቁን የፓለቲካ ስልጣን ለያዘው ጠ/ሚ/ር ገደብ ማስቀመጥ ቢኖርበትም ያደረገው ለፕሬዝዳንቱ ነው ›› አንዳንዶች ጉዳዩን የሃያው ዓመት ምርጥ ፓለቲካዊ ስላቅ በማለት ሲጠሩት ተሰምቷል ፡፡

እናም ሀገራችን ለረጅም ዓመታት የግራ እግር ጫማ በቀኝ ተጫምታ ስትወላከፍ ቆይታለች ፡፡ ሰሞኑን ታዲያ የቀኝ እግር ጫማ- ለቀኝ እግር ብቻ መዋል አለበት የሚል የሚመስል መግለጫ ይፋ ተደርጓል ፡፡ በኢትዮጽያም የመንግስት ኃላፊዋች የስልጣን ዘመን በአስር ዓመት ተገድቧልና  ፡፡ እልልታ ያስፈልገው ነበር - ግና ከአፍሪካ በሃያ አመታት ወደ ኃላ ቀርቶ ዛሬ የተነገረው ዜና በህዝቡ አንደበት ቀድሞ በመነገሩ  ‹‹ ሰበር ›› ለመባል አልቻለም ፡፡ ምናልባት ለሰበር ጥቂት ቀረብ የሚለው ‹‹ ከ65 ዓመት በላይ የሆነው ሰው በስልጣን ላይ መቀጠል አይችልም ›› የሚለው ገደብ ነው ፡፡ በዚህ ያልወጣ ህግ መሰረት የ66 ዓመት አዛውንት ስለጃጃ ሀገር ለመምራት ብቃት የለውም ማለት በራሱ የጃጀ ሀሳብ ሊያስብል የሚችል ይመስለኛል ፡፡ በሌላ አነጋገር በ80 ዓመታቸው ምርጥ ስራ የሰሩትን የዓለማችንን መሪዋች ታሪክ አለማወቅን ያቃጥራል ፡፡ በመሰረቱ የብዙዋች / አንደኛው / ጥያቄ አንድ መሪ ረጅም ግዜ አይቆይ እንጂ በ66 ዓመቱ አይስራ የሚል አይደለም ፡፡ ለመሆኑ ይህ እድሜ ብቁ አለመሆኑ በምንድነው የተረጋገጠው ? ጥሩ ስም ባላቸው ሰው የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ግኝት ካለ ሊግረን ይገባል ፡፡ ነው የሀገሪቱን Life expectancy በመሾፍ ብቻ ነው ከአራት ነጥብ የተደረሰው ፡፡  አሁን ደግሞ የቀኝ እግር ጫማ በግራ እግር እንዲደረግ ማዘዣ የተጻፈ አስመስሎታል ፡፡

አሁን የወጣው ‹‹ የስልጣን ዘመን ገደብ ›› ተነገረ እንጂ ገና በተግባር ያልተፈተሸ በመሆኑ  ‹‹ ጥሩ ነው ›› የሚል የሞራል ታርጋ ለመለጠፍ የሚያስችል መነሻ የለም ፡፡ ይህን ለማለት የሚያስችለው  ደግሞ አፍሪካ ባለፉት ሃያ አመታት የመጣችበት መንገድ አስተማማኝ አለመሆኑ ነው ፡፡ ብዙዋቹ የአፍሪካ መሪዋች ለወሬ እንጂ ለተግባር ቅርብ አይደሉም ፡፡ ለቁጥር የሚታክት ሚሊዮን ዶላር ወደ ውጭ አግዘው እንኳ ሙስናው ውስጥ ከመልከስከስ አይታቀቡም ፡፡ ሃያና ሰላሳ ዓመታት በፈላጭ ቆራጭነት መንገድ ወንበር ይዘው በመጨረሻ እንኳ የተሻለ ስርዓት ለመፍጠር ፍቃደኛ አይሆኑም ፡፡ ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ለአንድ ጋዜጠኛ ‹‹ በህይወት እስካለሁ ድረስ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ነኝ ›› ማለታቸውን እናስታውሳለን ፡፡ የጋዳፊና የሙባረክ ዓይነቱ ደግሞ እስከመጨረሻው ሰዓት ‹ ህዝባችን ይወደናል፣ ህዝባችን ለኛ ይሞታል ! › ይሉ ነበር ፡፡

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ወደ ስልጣን የመጡት በ1986 ነበር ፡፡ እስከ 2004 ድረስ ሀገሪቷን መሯት ወይም መጠመጧት ፡፡ በዚህ ግዜ ትዝ ሲላቸው ለካ የስልጣን ዘመን ገደብ አስቀምጠዋል ፡፡ በ2005 ለሀገሪቱና ለህዝቡ ጥቅም በሚል ህገ መንግስቱን ፐውዘው የገደቡን ግዜ አሻሻሉት ፡፡ በ2006 በተደረገው ሶስተኛ ምርጫ ደረታቸውን ነፍተው አሸነፉ ፡፡ አሁንም አሉ ፡፡ የገደቡም ቁጥር ከፍ እንዳለ ነው ፡፡

ይህን ምርጥ የዴሞክራሲ ጎዳና የናሚቢያው ፕሬዝዳንት ሳምኒዮማ በ1999 በይፋ ከጣሱት በኃላ ስንት ፈሪ - ጅግኖች ተከተሏቸው ? የሴኔጋሉ ዲዩፍ፣ የጊኒው ላንሳና ኮንቴ፣ የቶጎው ጋንሴቤ ኢያዴማ፣ የጋቦኑ ኦማር ቦንጎ፣ የቡርኪናፋሶው ካምፓወሬ፣ የቻዱ ኢድሪስ ዳቤ፣ የቱንዝያው ቤን አሊ፣ የካሜሮኑ ቢያ፣ የአልጄሪያው ቡተፍሊካ … ማን ቀረ ታዲያ ?  እያንዳንዱ መሪ ራሱ ያወጣውን ህግ ለመሻር ያደረገውን ብልጠትም ሆነ የጭካኔ መንገድ ስናነብ ወይም ስንሰማ የሚያሳፍር ሆኖ ነው የሚገኘው ፡፡

በርግጥ የወጣውን ህግ ጠንክረው በመጠበቃቸው መፈንቅለ ህግ ሊያደርጉ የሞከሩ መሪዋቻቸውን አሳፍረው የመለሱ ህዝቦችም አሉ ፡፡ በዋናነት የዛምቢያ፣ ማላዊና ናይጄሪያ መሪዋች ህገ መንግስቱን የመቀየር ሙከራ ሲከሽፍባቸው የእነሱን እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ አሻንጉሊት መሪዋችን ለመተካት ጥረት አድርገዋል ፡፡

የዛምቢያው ፍሬዲሪክ ቹሉባ ለሶስተኛ ዘመን ምርጫ ሲሯሯጡ የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዋች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ፣ የሰራተኛ ማህበራት፣ የተማሪዋች ህብረት፣ የሴት አደረጃጀቶች፣ ቤተክርስትያናት፣ የህግ ባለሙያዋች እንዲሁም ህዝቡ አረንጓዴ መቀነት በመልበስ፣ የመኪና ጡሩንባ በማሰጮህና በመዘመር አስደንጋጭ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል ፡፡ ተቃውሞው ያሰቡትን እንዳይፈጽሙ ያደረጋቸው ቹሉባ ሌላ ዘዴ ቀየሱ ፡፡ በቀላሉ እቆጣጠረዋለሁ፣ የእኔንም ሃሳብ እንዲፈጽም አደርገዋለሁ ብለው ያሰቡትን  ሌቪ ምዋናዋሳን ለፕ/ት ምርጫ ዕጩ አድርገው መረጡ ፡፡ ምዋናዋሳም ምርጫውን አሸነፉ ፡፡ ነገር ግን ከድሉ በኃላ አዲሱ መሪ የቀድሞውን ጓደኛቸውን ሀሳብና ተጽዕኖ አሽቀንጥሮ በመጣል በራሳቸው መንገድ ተጓዙ ፡፡ የቹሉባን ያለመከሰስ መብት በመግፈፍ በሙስና እንዲጠየቅ አስደረጉ፡፡

የማሊውም  ታሪክ ከዛምቢያው የሚርቅ አይደለም ፡፡ ፕሬዝዳንት ባኪሊ ሙሉዚም ከህዝቡ የደረሰባቸውን ተቃውሞ መቋቋም ባለመቻላቸው አንድ አሻንጉሊት ወራሽ ፈለጉ ፡፡ ቀልባቸውም ቢንጉዋ ሙታሪካ ላይ አረፈ ፡፡ ብዙዋች እኚህ ሰው ታማኝ ጩሎ እንደሚሆኑ እምነት አሳድረው ነበር ፡፡ በርግጥም ከምርጫው ድል በኃላ / ያው በአፍሪካ ፕሬዝዳንቱ የወከለው ሰው በተዓምር አይሸነፍም / ሙሉዚ እና ሙታሪካ በተመሳሳይ መንገድ የሚጓዙ መሰሉ ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኃላ ሙሉዚ ሙታሪካ የቀረጹትን የጸረ ሙስና ፓሊሲ መቃወም ጀመሩ ፡፡ ያኔ ጨዋታው ፈረሰ… ዳቦው ተቆረሰ…

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት አባሳንጆ ህገ መንግስቱን ለመቀየር ያደረጉት ጥረት ከህዝብና ተቃዋሚዋች ብቻ ሳይሆን ከራሳቸውም ፓርቲ ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል ፡፡ በመሆኑም የራሴ ሰው ነው የሚሉትን ኡማሩ ሙሳ ያርአዱም ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ አድርገው አቀረቡ ፡፡ ሚያዚያ 2007 በተደረገው ምርጫ በአጨቃጫቂ ሁኔታ አሸነፉ ፡፡ እኚህ ሰው ግን ከህዳር 2009 ጀምሮ በጠና ታመው ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለህክምና በማቅናታቸው የስልጣን ክፍተት በሀገሪቱ ሊፈጠር ችሏል ፡፡ የካቲት 2010 ሴኔቱ የፕሬዝዳንቱን ስልጣን ለምክትላቸው ጉድላክ ጆናታን አስተላለፈ፡፡ ፕሬዝዳንቱ መጋቢት 5 ቀን 2010 በመሞታቸው የስልጣናቸውን ግዜ እንኳን መጨረስ አልቻሉም ፡፡

ርግጥ ነው አፍሪካ ጥቂት ሞዴል መሪዋችም አሏት ፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ከአንድ የስልጣን ዘመን ቆይታ በኃላ ብቻ ነበር ወንበራቸውን ያስረከቡት ፡፡ የቤኒኑ ማቲሁ ኬሬኩ ፣ የኬፕቨርድ ማስካሪንሃስ ሞንቲሮ ፣ የማሊው አልፋ ኮናሬ ፣ የሞዛምቢኩ ጃኪም ቺሳኖ ፣ የሳኦቶሚፕሪንስፒ ማገል ትሮቫዳ ፣ የታንዛኒያው ቤንጃሚን ማካፓ፣ የቦትስዋናው ፌስተስ ጎንተባይ ሞይ የሁለት ግዜ የስልጣን ዘመናቸውን እንደጨረሱ በህገመንግስቱ ላይ ግፍ ወይም ዘረፋ ሳያካሂዱ ቦታቸውን ለተተኪው አስረክበዋል ፡፡ አፍሪካ እኒህን መሰል ህግና ህዝብ አክባሪ መሪዋች በብዛት ያስፈልጋታል ፡፡ እነዚህ ጥቂት ምርጥ ዘሮች ግን የአረምና የእንክርዳድን ሚና የሚጫወቱት በርካታ መሪዋች እያጠወለጓቸው በመሆኑ የስጋቱ በረዶ ዛሬም ህሊናችን ወስጥ እንደተጋገረ ይገኛል ፡፡

ስልጣን መገደብ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጠናከር ፣ ውድድርን ለማላቅ ፣ አዲስ አስተሳሰብን ለማመንጨት ፣ የገነገነ ቢሮክራሲንና  ሙስናን ለመሞረድ ከፍተኛ ጥቅም አለው ፡፡ ሀገራችን ዛሬ ወደዚህ ስርዓት እቀላቀላለሁ ብትልም አባባሉ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታነት ይሁን ለእውነት የተተኮሰ መሆኑ አይታወቅም  ፡፡ ትክክለኛ ቢሆን ይመረጣል ፡፡  አጠራጣሪ የሚያደርገው  ደግሞ ከላይ ለማሳየት የተሞከረው የአፍሪካ መሪዋች ልምድ ነው ፡፡ ኢትዮጽያም ከዚህ የተሻለ የልምድ ሪከርድ አላስመዘገበችም ፡፡  ግራም ነፈሰ ቀኝ መሪዋቻችን በቺሳኖና በማንዴላ ወይስ በሙሴቬኒና በፓውል ቢያ መንገድ ይጓዛሉ  የሚለውን ጥያቄ  በአግባቡ ለመፍታት ገና ረጅም ርቀት ይቀረናል ፡፡

No comments:

Post a Comment