Sunday, January 13, 2013

‎የ ‹‹ ዋሊያዎቹ ›› ስያሜ ምን ያህል ፍትሃዊ ነው ?‎







የእግር ኳስ መጠሪያ በአፍሪካ
ሁሉም የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ልዩ መጠሪያ አላቸው ፡፡ ሀገሮች የቡድናቸውን መጠሪያ ከባንዲራ ፣ ከጥንካሬ ፣ ከማሊያ ፣ ሀገራቸው ጎልታ ከምትታወቅበት ጉዳይ ፣ ቡድኑ እንዲሆን ከሚፈለገው አንጻርና ከመሳሰሉ ጉዳዮች ተነስተው ይሰይማሉ፡፡
ይህ ማለት ግን ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ስም የለጠፉ የሉም ማለት አይደለም ፡፡ ለምሳሌ የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን Red Devils ነው የሚባለው ፡፡ ይህን ስያሜ የቤልጂየም ብሄራዊ ቡድንና ማንችስተር ዩናይትድ ይጋሩታል ፡፡ ሰይጣን ጥቁር ነው በሚባልበት ዓለም ቀያዮቹ ማንቸስተሮች ተምሳሌቱን የተጠቀሙበት ለምን እንደሆነ ይገባናል ፡፡ በመልክ ከሆነ ለሰይጣን የቀረቡት ኮንጎዎች ራሳቸውን ቀይ ሰይጣን የሚሉበት አግባብ አለ ቢባል እንኳን በአሳማኝነቱ ዙሪያ ዕድሜ ልክ ሊያከራክር የሚችል ነው ፡፡

የስያሜ እጥረት ያለ ይመስል የሌላውን ሀገር የደገሙም አሉ ፡፡ የኮትዲቭዋር ‹ the elephant › በጊኒ < the national elephant > ሆኖ ይገኛል ፡፡ ለአብዛኛው አፍሪካዊያን ቡድን መጠሪያ የሆኑት ግን የዱር እንስሳት ናቸው ፡፡ ርግጥ ነው አፍሪካ በዱር እንስሳት ሃብት አትታማም ፡፡ ይህ በራሱ መነሻ ሆኖ ሊሆን ይችላል ፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካዊያንና የዱር እንስሳት ትስስር ስናጤን ግን መነሻው ተግባር ላይ መዋል እንዳቃተው ህግ ሽባ ሆኖ ይታየናል ፡፡  አፍሪካዊያን የዱር እንስሳትን ቢወዱም ለስጋቸው ፣ ለጀብዱ ፍለጋ ፣ ኪሳቸውን ለማደለብ ሲሉ ያለ ርህራሄ ይገድሏቸዋል ፡፡ አፍሪካዊያንና የዱር እንስሳት እንደ ኦቴሎና ዴዝዲሞና የሚመሳሰሉ ናቸው ፡፡ እየወደዱ የሚገድሉ ፡፡

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ከሀገራችን ዋሊያ ጋር የሚደረገውን ግብግብ እናንሳ ፡፡ ዋሊያ ለመጀመሪያ ግዜ የታየው በ1835 ነበር ፡፡ በ1960ዋቹ ለስሊ ብራውን በተባለ ሰው በተደረገው ጥናት ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ በላይ ነበር ፡፡ ይሁን እንጂ ጣሊያን ሀገራችንን ሲወር እጅ አንሰጥም ያሉ አርበኞች ተራራው ላይ መሽገው ይዋጉ ነበር ፡፡ በአካባቢው የታየው ዋሊያም ‹‹ ምን እንበላለን ? ›› ለሚለው ወቅታዊ ጥያቄያቸው ሁነኛ አማራጭ ሆነ ቀረበ ፡፡ በዚህም ሳቢያ ቁጥሩ አሽቆለቆለ ፡፡

ጣሊያን ሀገሪቱን ለቆ ከወጣ በኃላም ዋሊያ በአካባቢው ነዋሪዋች ለስጋውና ለቀንዱ ይታደን ነበር ፡፡ ደገኛው ስጋውን እያጣጣመ በቀንዱ ኩባያ ሰርቶ ጠላ ይጠጣበታል ፡፡ ይህ ገደላ ጋብ ያለው በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚሰራው The International union for conservation of nature / IUCN / ቀጭን ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኃላ የኢትዮጽያ መንግስት ብሄራዊ ፓርኩን በ1966 በማቋቋሙ ነው ፡፡ ዋሊያ ዛሬም ድረስ በመጥፋት ላይ የሚገኝ እንስሳት ዝርዝር ውስጥ ቢገኝም ቁጥሩ ከ 500 በላይ መድረስ ችሏል ፡፡

አንበሳ አፍቃሪዎች
 የዚህን ድንቅ እንስሳ ለብሄራዊ ቡድናቸው መጠሪያ ያደረጉት ግን ካሜሮን ፣ ሞሮኮና ሴኔጋል ናቸው ፡፡

ዘንድሮ ማጣሪያውን ማለፍ ያቃታቸው ካሜሮን Indomitable lions ይባላሉ ፡፡ የማይሸነፉ አንበሶች እንደማለት ፡፡ ርግጥ ነው የኛ ሀገር የስፖርት ጋዜጠኞች የማይበገሩ አንበሶች እያሉ ነው የሚጠሯቸው ፡፡ ካሜሮን በ1972 ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ማለፍ አለመቻሉ የሀገሪቱን ፖለቲከኞች አነጋግሮ ነበር ፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አህመዱ አሂዶ የሀገሪቱ የስፖርት መዋቅር በአዲስ መልክ እንዲገነባ ትዕዛዝ አስተላለፉ ፡፡ የስፖርት ሚኒስትሩ በጉዳዩ ዙሪያ ሲሰሩ ከተነሱት አጀንዳዋች መካከል የቡድኑ ስያሜ ነገር ይገኝበታል ፡፡ ቡድኑ ጥንካሬን እንዲላበስ ‹ አንበሳ › ማለት እንደሚገባ ቢያስቡም ይህ አንበሳ ከሌሎቹ ሀገሮች በምን ይለያል የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈልጎ ነበር ፡፡ እናም ‹ Indomitable › የሚል ቃል ከፊቱ እንዲገባ ስምምነት ተደረገ ፡፡ ዘንድሮ ግን አንበሶቹ የሉም ፡፡ ይህ ያስቆጫቸው የቀድሞዎቹ እነ ሮጀር ሚላ ባለጌ ወንበር ላይ ተሰይመው ‹‹ አንበሳ ሲያረጅ የዝምብ መጫዎቻ  ይሆናል ! ›› እያሉ ነው አሉ ፡፡

የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን ስያሜ ‹ The lion of Terenga › የሚል ነው ፡፡ በሀገሪቱ ቋንቋ ‹ Terenga › እንግዳ ተቀባይ ማለት ነው ፡፡ ጥሬ ትርጉሙ እንግዳ ተቀባዩ አንበሳ ሊሆን ነው ፡፡ ስምን አንበሳ ብሎ ተግባሩን ለማዳና የዋህ ማድረግ ሊጋጭ ይችላል ፡፡ ግን ደግሞ ሴኔጋሎች ስፖርት ዝምድናን ማጠናከሪያ መሆኑን በመረዳት ከአስፈሪ ይልቅ ሰላማዊ ስያሜ የመስጠታቸው ሀሳብ ከዚህ የመነጨ ሊሆን ይችላል ፡፡

የሞሮኮዎቹ ‹ The lion of the Atlas › የሚለው ስያሜ ደግሞ ከሴኔጋሉ በተቃራኒ የሚተነተን ነው ፡፡ ሞሮኮዎቹ የሚያምኑት አንበሳ በጫካ ውስጥ ሃይለኛና ጠንካራ መሆኑን ነው ፡፡ ይህ አንበሳ ደግሞ በሀገራቸው ጎልቶና ደምቆ በሚገኘው የአትላስ ተራራ ውስጥ እንደ ድምጻዊው አሸብር በላይ ‹ ይሰለፍና ፈረስ ከእግረኛ
                             እኔ ነኝ ያለ ይሞክረኛ ! › እያለ የሚፈነጭ ነው ፡፡ እናም ቡድናቸውም የማይደፈር እንዲሆን ከመፈለግ አንጻር የተነሱ ይመስላል ፡፡ ከአፍሪካ ዉጪም ቡልጋሪያ ‹ the lions › ፣ ኢራቅ ‹ the Babylon lions › ፣ ሉክሰምበርግም ‹ the lions › የሚል መጠሪያ ያላቸው መሆኑን ስንረዳ ልንገረም እንችላለን ፡፡

አዳኝ አእዋፋት


ማሊ / The eagles / ፣ ናይጄሪያ / The super eagles / ፣ ሱዳን / Desert Hawks / ፣ እና ቱኒዚያ / The eagles of Carthage /               ንስር አሞራና ፋልኮን ከረጅም ርቀት መሬት ላይ ያለ እንቅስቃሴን አጥርተው ይመለከታሉ ፡፡ አይናቸው ለአጉሊ መነጽር መፈብረክ መንስኤ ሆኖ ቢገኝ እንኳ አይበዛበትም ፡፡ በሚገርም ፍጥነት ወደ ታች ተምዘግዝገው የሚበሉትን ነገር ገቢ ማድረጋቸው ሲታይ ለሚሳይል መፈጠር ለምን መነሻ አልሆኑም ብሎ እስከ መከራከር ያደርሳል ፡፡

ንስር አሞራ ረጅም እድሜ ከሚኖሩ አእዋፋት መካከል አንደኛው ነው ፡፡ 70 ዓመት ይኖራል ፡፡ እዚህ እድሜ ላይ የሚደርሰው ግን ጠንካራ ውሳኔዋችን በማሳለፍ ነው ፡፡ በተለይም 40 ዓመት ሲሞላው እንስሳትን ሰቅስቆ የሚይዝበት ረጅም ጥፍሩ መያዝ ያቅተዋል ፡፡ ስጋን ቦጭቆ የሚያነሳው የአፉ መንቆር ይጣመማል ፡፡ ትልቁ ክንፉ ለመብረር ያስቸግረዋል ፡፡ ስለዚህ መሞት ወይም በአስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ማለፍ ከተባሉ አማራጮች ጋር ይፋጠጣል ፡፡ ቀጣይ ዕድሜ ያስፈልገኛል ካለ የአፉን መንቆር ከድንጋይ ጋር እያጋጨ ማስወገድ ይኖርበታል ፡፡ ክንፎቹንም ነቅሎ መጣል ፡፡ ይህንን ተግባር በከባድ ስቃይ ውስጥ አልፎ ከከወነ ከአምስት ወራት አስቸጋሪ ጉዞ በኃላ አዲስ ክንፍና መንቆር ያወጣል ፡፡ እናም ቀጣዩን ሰላሳ ዓመታት በአስተማማኝ ሁኔታ ይኖራል ፡፡

ይህን አስቸጋሪ የህይወት ጉዞና ጥንካሬ በማሰብ ለቡድናቸው ስያሜ የሰጡ ሀገሮች መነሻቸው ለክፉ አይሰጥም ፡፡ ችግሩ ዉጤት ላይ ነው፡፡ ቱኒዝያ አንድ ግዜ ፣ ናይጄሪያ ደግሞ ሁለት ግዜ ብቻ ነው የአፍሪካን ዋንጫን ያነሱት ፡፡ ከዚህ አንጻር ባለ ስያሜዋቹ ሀገሮች ዛሬም መንቁራቸውንና ጥፍራቸውን ከድንጋይ ጋር በመጋጨት ላይ የሚገኙ ይመስላል ፡፡

የሀገራችን ‹‹ ዋሊያዋች ›› የስያሜ መነሻ

የኢትዮጽያ ብሄራዊ ቡድን ‹‹ ዋሊያዋቹ ›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ከምን አንጻርና መመዘኛ እንደሆነ የሚያብራራ መረጃ ማግኘት አልቻልኩም ፡፡ ይሁን እንጂ ለእውነት በጣም የቀረበ ግምት መሰንዘር ይቻላል ፡፡ ስም አውጪዎቹ ለመረጣ መነሻ የሆናቸው ሀገራችንን የሚያስጠራ ነገር የመፈለጋቸው ጉዳይ ነው ፡፡ ከዚህ አንጻር ኢትዮጽያ ሲባል ምንድነው ገዝፎ ሊነሳ ወይም ሊታይ የሚችለው መገለጫ የሚለው ሀሳብ - ሀሳባቸውን እንዳፋፋመው አይጠረጠርም ፡፡
በወቅቱ ባንኖርም የወደቁና የተወሰኑ ነገሮችን እንገምት ፡፡

. ኢትዮጽያ ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች ብቸኛ አፍሪካዊ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን በጦርነት በማሸነፍ የምትታወቅ ብቸኛ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ የሰው ልጅ መገኛ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ የቡና መገኛ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ 13 ወራት ጸሃይ የምታበራ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ የራሷ የሆነ ፊደል ያላት ብቸኛ አፍሪካዊ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ በሌላው ዓለም የማይገኙ ብርቅዬ እንስሳት ባለቤት ናት
እናም አንዱን ካንዱ  የግድ አበላለጡና ብርቅዬ የዱር እንስሳቱ ነገር ቀልባቸውን አሸነፈው ፡፡ በሀገራችን ብርቅዬ የሚባሉት አጥቢ እንስሳት ደግሞ ዋሊያ ፣ ቀይ ቀበሮ ፣ የስዋይን ቆርኬ ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ ፣ የሚኒሊክ ድኩላ እና የደጋ አጋዘን ናቸው ፡፡ እነዚህን ሲያወዳድሩ ደግሞ ምርጫቸው ዋሊያ አይቤክስ ላይ አረፈ ፡፡ እናም የብሄራዊ ቡድኑን መጠሪያ ‹‹ ዋሊያዎቹ ! ›› አሉት ፡፡

ዋሊያ ምኑ ይስባል ?

ወንዱ ዋሊያ ክብደቱ በአማካኝ 120 ኪሎግራም ነው ፡፡ በጣም ከሚስበው ሰውነቱ አንደኛው ጠመዝማዛውና ጉጣሙ ቀንዱ ነው ፡፡ የቀንዱ ርዝመት 110 ሴ.ሜ ያህል ሲሆን በቀንዱ ላይ ያሉ ጉጦች የእድሜ ክቦች ናቸው ፡፡ ዋሊያ ትልቁ ዕድሜው ከ 12- 15 ነው ፡፡ ቀንዱ ላይ አስር ጉጦች ከታዩ አስር አመት አካባቢ እንደሆነ ይገመታል ፡፡ ይህ ስሌት የፈረንጆቹ እንጂ በሀገራችን የተደገፈ ማስረጃ አላየሁም ፡፡ ቸኮሌት የመሰለው መልኩና ጺሙም አይን ወጣሪዋች ናቸው ፡፡ የሚኖረው ከ2500 እስከ 4000 ሜትር በሚደርስ ተራራ ላይ ነው ፡፡ ብዙ ውሃ ባያገኝ ግድየለውም ፡፡ ሳሩ ላይ የማይጠፋውን ጤዛ ከላሰ ‹‹ ተመስገን ! ›› ለማለት ይበቃል ፡፡ 

አካባቢው በብርድ ወራት በረዶ የሚሰራ መሆኑ ለዋሊያ አይስክሬም እንደ መላስ ሳይጠቅመው አይቀርም ፡፡ ዋሊያ ልክ እንደ ጭላዳ ዝንጀሮ ገደል ለገደል ሲሮጥ እወድቃለሁ ብሉ አይሰጋም ፡፡ ይህም ጠላቶቹ እንዳይደርሱበት ሁነኛ ምሽግ ሆኖታል ፡፡

የዋሊያ ውክልና ነገር ?
ዋሊያ በስሪያ ወቅት ካልሆነ በስተቀር ብቸኛ ነው ፡፡ ሲበላና ሲንቀሳቀስ የሚታየው በማለዳና ሲመሻሽ ነው ፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ ግዜያትን የሚያሳልፈው ጥሻና ገደላ ገደሉ ውስጥ በመደበቅ ነው ፡፡ ማህበራዊ ህይወቱ እጅግ የተቆጠበ ፣ በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ነው ፡፡ ከሰሜን ትላልቅ ተራራዋች ወደ ታች ወርዶ ለመኖር ፣ አካባቢውን ለመጎብኘትና የሌሎችን ህይወት በአንክሮ ለማጤን ፍቃደኛ አይደለም ፡፡ ‹‹ አትድረሱብኝ- አልደርስባችሁም ! ›› የሚል ሎጎ አሰርቶ ዘወትር የሚያውለበልባት ይመስላል ፡፡ 

የዚህ ብሂል መነሻን ለመፈተሸ ስብሰባ ቢጤ ቢዘጋጅ የዋሊያ ምላሽ የአካባቢዋቹን ሰዋች መሰረት ያደረገ ሊሆን ይችላል ‹‹ የራሷን የማትሰጥ የሰው የማትነካ ኢትዮጽያ መሆኗን አልተረዱም ለካ ! ›› ስለሚሉ ፡፡ መሬትም ዳገትም ላይ የሚኖረው ጭላዳ ዝንጀሮ ግን ለዚህ የዋሊያ መፈክር ‹‹ አይሰማም ! ›› የሚል ምላሽ ሰጥቶ ተጎራብቶታል ፡፡ ዋሊያ ማህበራዊ መስተጋብሩ ቁጥብና ገለልተኛ ከሆነ እንዴት ለምሳሌነት ሊበቃ ቻለ የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርበታል ፡፡ በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኙትን ሌሎች ብርቅዬ እንስሳት ትተን ከቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮ አንጻር ልናነጻጽረውና ልናወዳድረው እንችላለን ፡፡

እንደሚታወቀው ቀይ ቀበሮ አይጥ እየተመገበ የሚኖር እንስሳ ነው ፡፡ ማህበራዊ ህይወታቸው ጠንካራ ነው ፡፡ ለማህበራዊ ሰላምታና ድንበራቸውን ለመቃኘት ማለዳ ፣ ከሰዓትና ሊመሻሽ ሲል ይሰባሰባሉ ፡፡ ሌሊቱንም አብረው ያሳልፋሉ ፡፡ የጋራ ምግባራቸውም የሚገርም ነው ፡፡ ምግብ መካፈል ፣ ወዳጅነትን የሚያሳይ መተሻሸትና በጥርስ መነካካት ፣ መባረርና የቀልድ ጸብ በዝቶ ይታይባቸዋል ፡፡ ድንበራቸውን የሚከልሉት በሽንታቸው ፣ በዓይነምድራቸውና መሬቱን በመቧጨር ነው ፡፡ የበሉትንም በማስመለስ ቡችሎቻቸውን ይቀልባሉ ፡፡

የቀይ ቀበሮ ልዩ ባህሪ በእጅጉ አዳኝ መሆኑ ነው ፡፡ አይጥ ለማደን በትዕግስት ያደፍጣል ፡፡ ታዳኙ ቀለበት ውስጥ ገብቷል ብሎ ሲያስብ ሁለት እግሮቹን ወደ ላይ አንስቶ ወደ መሬት በመወርወር በአፍንጫው ሰርስሮ በመግባት አይጡን አንጠልጥሎ ያወጣል ፡፡ ይህን ተግባር 90 ዲግሪ ላይ ያረፈ ምርጥ የቅጣት ምት ፣ ከማዕዘን የተሻማ ኳስን ነቅንቆ በጭንቅላት እንደማስገባት አሊያም ወደ ጎል የተመታች አደገኛ ኳስን ተወርውሮ እንደመያዝ ሊመሰል ወይም ሊቆጠር ይችላል ፡፡ ታዲያ ቀይ ቀበሮ በጥሩ ምሳሌነቱ ለምን ቀዳሚ የብሄራዊ ቡድናችን ስያሜ አልሆነም ብንል እንደመሳሳት አያስቆጥርም ፡፡

ጭላዳ ዝንጀሮም ለቡድናችን ስያሜ ተመራጭ የሚሆንበት አግባብ አለ ፡፡ አንደኛው ልክ እንደ ዋሊያ የመልኩና የአቋሙ ጉዳይ ነው ፡፡ ጸጉር የሌለው ቀይ ደረቱ በእጅጉ ይስባል ፡፡ ወንዱ አንበሳን ያስታውሳል ፡፡ በጎፈሬው ማለት ነው ፡፡ የጅራቱ ጫፍም ልክ እንደ አንበሳ ጎፈሬያም ነው ፡፡ አፉን እየከፈተ ሲራመድ ያስደነግጣል ፡፡ የጭላዳ ልዩ ባህሪ በጋራና በመንጋ መኖራቸው ነው ፡፡ ቀኑን የሚያሳልፉት እንደ ዋሊያ በመተኛት ሳይሆን በእጃቸው ሳር በመጫር ነው ፡፡ በጣም ‹ ቢዚ › ናቸው ፡፡ አንዳንዴ ርስ በርስ ለመፈታተሸና ሚስት ለመጥለፍ የሚያደርጉት ሩጫና ትግል ምን ያህል ጠንካራ አትሌትና ቡጠኛ መሆናቸውን ያስረዳል ፡፡ ነገረ ስራቸው ሁሉ ስፖርታዊ ነው ፡፡ ታዲያ ለምን ከስፖርቱ ጋር አልተያያዙም ቢባል ከላይ የቀረበው ማስረጃ ያዋጣል ፡፡

በርግጥ ጭምቱ ዋሊያ ፣ ሜዳ ሳይሆን ተራራ ይመቸኛል የሚለው ዋሊያ ፣ ከሌሎች እንስሳት ጋር በሰንበቴና ዕቁብ መገናኘት ያልፈለገው ዋሊያ እንዴት ከኳስ ጋር ተያያዘ ? ከብርቅዬዋቹ እንስሳት ጋርስ በአግባቡ ተወዳድሮ ነው ያሸነፈው ? ይህ ውክልናስ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት አንጻር ሲታይ ምን ያህል የሰመረ ነው ?  ምክንያቱም አዳኝ አይደለም ! ራሱንና ጓደኞቹን አስተባብሮ የሆነ ተዓምር ወይም ለውጥ ለማምጣት ተነሳሽነት የሚታይበት አይደለም ! እንቅልፋም እንጂ ሰራተኛ አይደለም ! ግልጸኝነት ይጎድለዋል ! በቡድን ለመኖርም ሆነ ለመተጋገል የፈጠነ አይደለም ፡፡ ውድ የኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ‹ ፈሪ ለእናቱ › ብሎ የተደበቀን እንስሳ ፣ በዘመኑ ሂስና ግለ ሂስ ግምገማ ሂሳብ ቢታይ C- ሊያገኝ የሚችልን እንስሳ እንዴት ለብሄራዊ ቡድን መጠሪያነት አበቃችሁት ?  በቀለሙ ? በቀንዱ ? በጺሙ ? በተራራ አፍቃሪነቱ ? ነው ዋሊያም በእውቀት ሳይሆን በእምነት የመስራት ሳይንስ ልዩ ዋጋ እንዳላት ተረድቷል ፡፡

የተዘነጉ አማራጮች
‹‹ ዋሊያዋቹ ›› የተባለው ብሄራዊ ቡድናችን ልክ እንደ ዋሊያ ለ 31 ዓመታት ወደ አፍሪካ ውድድር አልወጣም በማለት ተደብቆ ነበር ፡፡ የእንስሳው ተግባር ተጋብቶባቸው ይሆን ; ደቡብ አፍሪካ ላይስ በ ‹ ዋሊያ › ተግባር ነው ፍልሚያውን እንዲያካሂዱ የሚጠበቀው ? ህብረትና ወረራ ፈጥረው ዝሆን ፣ ነብር ፣ ንስር አሞራ ፣ የበረሃ ተኩላንና የመሳሰሉትን ለማጥቃት የተለየ ስነ ልቦና ሰንቀው ይሆን ? አይታወቅም ፡፡

ኢትዮጽያ ለብሄራዊ ቡድንዋ ልዩ ስያሜ ለማውጣት እንደ ባህር የሰፋ አማራጭ ውስጥ የተቀመጠች ሀገር መሆኗም መጠቀስ ይኖርበታል ፡፡ ብቸኛ ባለ ቋንቋ ሀገር በመሆኗ ‹‹ ፊደል ›› ፣ የቡና መፈጠሪያ በመሆኗ ‹‹ ቡና ›› ፣ ተራራማ ሀገር በመሆኗ ‹‹ ራስ ዳሽን ›› ፣ ጀግና የበቀለባት በመሆኗ ‹‹ አድዋ ›› የሚል ስያሜ ለማውጣት ማን ይከለክላታል ፡፡
ቀደምት የስልጣኔ ባለሟል በመሆኗ ‹‹ አክሱም ›› ፣ የትልቅ ወንዝ ባለሃብት በመሆኗ ‹‹ አባይ ›› ፣ በተአምረኛ ሃውልቷ ‹‹ ላሊበላ ›› ፣ ብሎ ለመጥራትም አማራጭ አለ ፡፡

ተአምር ከሚያሳዩና በቱሪስት በብዛት ከሚጎበኙ ብሄር ብሄረሰቦች ተግባር ውስጥ የጎላውን ማውጣትም ይቻላል ፡፡ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ዘጠኝ ቅርሶቻችንም እኛን ለማስተዋወቅ ዓለማቀፍ መታወቂያ ያላቸው መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል ፡፡

ኢትዮጽያ በተፈጥሮ ድሃ ሳትሆን ድሃ ሆና ቆይታለች ፡፡ በርካታ ወንዞች እያሏት በውሃ ጥም ፣ በኤሌትሪክ ሃይልና በድርቅ ቅጥል ብላለች ፡፡ በዚህ የተለመደ አባባል መሰረት ቆይታችንን ብንገመግመው ከሚከተለው አባባል ጋር ያላትመናል ‹‹ በርካታ ድንቅና ውብ መወኪያ ስም ቢኖራትም ስም ማውጣት አልቻለችም ! ››

ስምን መልዓክ ያወጣዋል የሚባለው አባባላችንና ‹‹ ዋሊያዋቹ ›› ምንና ምን ናቸው ?

ለማንኛውም መልካም ጥቅስ ሳይሆን መልካም ዕድል - ለዋሊያዋች !!!

ይህ ጽሁፍ በቁም ነገር መጽሄት የጥር ወር ዕትም ላይ የወጣ ነው

No comments:

Post a Comment