የአፍሪካ ማሊያ በጦርነት ፣ አምባገነንነትና ድርቅ
ቀለማት የተሰራ ነው ፡፡ ቁምጣው ላይ የስደት … ጋምባሌው ላይ የመፈንቅለ መንግስት… ታኬታው ላይ የበሽታ መንፈሶችን መመልከት
የሚቻል ይመስለኛል ፡፡ አፍሪካዊያን ነጻ በወጡ ማግስት ለዚህ ሁሉ የዳረገን መሰረታዊ ነቀርሳ የቅኝ አገዛዝ እባጭ ነው የሚል መከራከሪያ
አቅርበው ነበር ፡፡ አሳማኝ ይመስላል ፤ እረ መሰሏልም ፡፡
ከነጻነት በኃላስ የአህጉሪቷ እድሜ ስንት ቆጠረ ? ሃምሳ !... ይኅው ሰሞኑን አዲስ አበባ
ውስጥ ያካሄዱት 20ኛ መደበኛ ጉባኤያቸው የህብረቱን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤሊዩ ለማክበር በተነሳሳ መንፈስ አይደል ? ግን እኮ
አህጉራችን ዛሬም በኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች ውጤታማ
አክሊሎችን አልደፋችም ፡፡ ታዲያ ለዛሬው ተጨባጭ ችግር የበፊቱን የምክንያት ኩታ ማልበስ ይቻላል ? ማለት ቅኝ አገዛዝ የሚል
? መቼም ለፈገግታ ካልሆነ በስተቀር አያዋጣም ፡፡ ታዲያ ችግሩ ምንድነው ብለን በአንክሮ ከጠየቅን ነገር አለሙ ሁሉ መሪዋቹ ትከሻ
ላይ ወድቆ ቁጭ ይላል ፡፡
በርግጥ መሪዎቹ እንዲህ አያስቡም ፡፡ ያስባሉ
ብሎ መጠበቅም ከስጋ ለበስ ሰብዓዊነት አንጻር እንጂ ፖለቲካዊ መላ ሆኖ አይደለም ፡፡ የስብሰባቸው ውሎም የሚነግረን አፍሪካ ተስፋ
ያላት አህጉር የመሆኗን ጉዳይ ነው ፡፡ ምክንያቱም ጥቂት ቢሆኑም
ዓመታዊ እድገታቸው በሁለት ዲጂት የሚራመድ ሀገሮች ባለቤት መሆን ጀምራለች ፡፡ ይህን ውጤት ቀምሮ ለማስፋፋትም ይቻል ዘንድ በኢኮኖሚና
ንግድ ዙሪያ ተነጋግረዋል ፡፡ የስትራቴጂ ዕቅድም ነድፈዋል ፡፡ በላዩ ላይም የአዲሱ የአፍሪካ ልማት አጋርነት / NEPAD / እንቅስቃሴ
ምን እንደሚመስል የሪፖርት ካፖርትን ጣል አድርገዋል ፡፡ ማሊያው ላይ ከሚገኙት ቀለማት በተለይም ‹‹ ድርቅ ›› ቋሚ ተሰላፊ መሆኑን
ግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል እንዴት በአሰቸኳይ ግዜ እርዳታ ሊፈታ እንደሚችል መክረዋል ፡፡ በአፍሪካ በአራቱም ማዕዘናት የባሩድ
ሽታ ተለይቶ ባያውቅም በዚህ ስብሰባቸው ይበልጥ ያስነጠሳቸው የሚሊ የጸጥታ ችግር ሆኗል ፡፡ እና ጉዳዩን ለመፍታት 50 ሚሊዮን
ዶላር ከካዝናቸው መዥረጥ እስከማድረግ ደርሰዋል ፡፡
ታዲያ ወሬ ብቻ ሳይሆን መፍትሄም እየሰጠ የሚጓዝ
የመሪዎች ስብስብ የምስጋና ሰርተፍኬት እንጂ እንዴት የማስጠንቀቂያ ካርድ ይመዘዝበታል ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ አይደለም ሊባል አይችልም
፡፡ በዚህ ላይ የሰሞኑ ስብሰባ የሃምሳ አመት አፍሪካዊ ትግልን የሚዘክር ነው ፡፡ የውይይቱ ማጠንጠኛ ‹‹ ፓን አፍሪካኒዝም እና
የአፍሪካ ህዳሴ ›› በሚል ወርቃማ ሰንሰለት የተሞሸረውም ለዋዛ አይደለም ፡፡ እንዴት ካልክ ሰንሰለቱን ቀስ በቀስ ስትፈታ ነው
የትግሉን ውጣ ውረድና የውጤቱን ግዙፍነት ልትረዳ የምትችለው ፡፡ እነዚህ በተደጋጋሚ የተወቀጡ ሁለት ጽንሰ ሀሳቦች እውነት መሪዎቹ
ያለባቸውን ክፍተት የመሸፈን አቅም አላቸው ? በፍጹም የላቸውም ፡፡ ለማንኛውም ከመፍረዳችን በፊት ጥቅልሎችን እንፍታ ፡፡
‹‹ ፓን አፍሪካኒዝም ››
አፍሪካን በቅኝ ግዛት የተቆራመቷት የውጭ ሃይሎች
እምቅ ሀብቷን ከመበዝበዝ በተጨማሪ የህዝቡን ነጻነት በማፈን ሲሸጡና ሲለውጡት ቆይተዋል ፡፡ በተለያዩ ሀገራት ተበትነው የሚገኙ
አፍሪካዊያን የቅኝ ግዛት እና የባሪያ ንግድ እንቅስቃሴን መነሻነት በመቃወም በአህጉሪቱ ነጻነት ፣ ብሄራዊ ስሜት፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ
ትብብር ፣ የታሪክና ባህል ግንዛቤ እንዲሁም አንድነት እንዲፈጠር ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገዋል ፡፡ ይህ እንቅስቃሴም ፓን አፍሪካኒዝም
ይባላል ፡፡ በ1900 አካባቢ የተመሰረተው ይህ ርዕዮተ አለም መላው አፍሪካን አንድ ማድረግ ላይ ያተኩራል ፡፡ የፓን አፍሪካ መሪ
የሚባሉት እነ ኩዋሜ ንክሩማህ ፣ ጆሞ ኬንያታ ፣ አጼ ሃይለስላሴ ፣ ሙአመር ጋዳፊና ሌሎችም የአፍሪካ አንድ መሆን አህጉሪቷ በራሷ
እንድትተማመንና የራሷን እምቅ ሀብት በነጻነት በራሷ በማልማት የህዝቦቿን የዘመናት ጥያቄ እንድትመልስ ያደርጋል ባይ ናቸው ፡፡
‹‹ የአፍሪካ ህዳሴ ››
የአፍሪካ ሀገራትና ህዝቦች በወቅቱ እያጋጠማቸው
የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ችግር ተቋቁመው የባህል ፣ ሳይንስና ኢኮኖሚያዊ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ማድረግ ነው ፡፡ ይህ ጽንሰ ሃሳብ
በ1946 ብቅ ያለው በቼክ አንታ ዲውፕ ‹‹ Towards The
African renaissance ›› በተሰኘው መጽሀፍ ውስጥ ነው
፡፡ ይህ የተዳፈነ ሀሳብ ይበልጥ ቦግ ያለው ታቦ ምቤኪ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በተሾሙበት ወቅት ነበር ፡፡ ‹‹ I
am an African ›› በተሰኘው ታዋቂ ንግግራቸው ውስጥ የአፍሪካ
ህዳሴ መጀመር ከድህረ አፓርታይድ ዘመን በኃላ ትልቅ የአፍሪካ አጀንዳ እንደሚሆን ገልጸው ነበር ፡፡
እኤአ በጥር 11 ፣ 1999 የአፍሪካ ህዳሴ ተቋም
በፕሪቶሪያ ተመስርቷል ፡፡ የተቋሙ ጽ/ቤት የሚገኘው ቦትስዋና ጋቦሬኒ ነው ፡፡ ይህ ተቋም እንዲፈጽም የተሰጠው ተግባር ሰፊና ከአቅሙ
በላይ ይመስላል ፡፡ የቅድሚያ ተግባሩ ምርጥ የአፍሪካ ሳይንቲስቶችን ማፍራት ነው ፡፡ ምሁራኑ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን
በመፍታት የኢንዱስትሪ ውጤቶች የሚጎመሩበትን ሁኔታ ያመቻቻል ፡፡ የሰው ኃይል ልማት ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፣ ግብርና ፣ ምግብና
ጤና ፣ ባህል ፣ ንግድ ፣ ሰላም እና መልካም አስተዳደርም የትኩረት አቅጣጫዎቹ ናቸው ፡፡ ይህ ተቋም የፖለቲካና የፍልስፍና ማራመጃ
በመሆኑ ከአፍሪካ ግጭት ፣ ሙስና ፣ ድህነትና ጥቅማጥቅም ለባለግዜዎች ይገባል / Elitism
/ ብሎ ማመን እንዲጠፋ ሌት ተቀን ይሰራል ፡፡
በጀ ! በማለት… ጥቅልሎቹ እንደተከፈቱ አንዳንድ ሀሳቦችን እንወርውር ፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም
በዛ በራቀ ዘመን መወለዱ ድንቅ ነው ፡፡ የቅኝ አገዛዝና የባሪያ ንግድን ካቴና አውልቆ ማሽቀንጠሩ አሪፍ ነው ፡፡ የዛሬን የግሎባላይዜሽን ሁኔታ ተንብዮ ስለ አንዲትና የተባበረች አፍሪካ ማሰቡም
ማለፊያ ነው ፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደርና የነጻነት ብርሃን እንዲወጣም አዎንታዊ ሚና ነበረው ፡፡ ጽንሰ ሃሳቡ ውስጥ ያሉ አንዳንድ
ሀሳቦች ግን በአፍሪካዊያን ጥርስ የሚቆረጠሙ አይደሉም ፡፡ ለምሳሌ ስለ እኩል መብትና አንድነት በዛሬይቱ አፍሪካ ማለም እንጂ ማረጋገጥ
እንዴት ይቻላል - አይቻልም ፡፡ ይቻላል የሚሉትም እነዛው መሪዎች ብቻ ናቸው - በመክፈቻ ዲስኩር ወቅት ፡፡
በነገራችን ላይ የአፍሪካ ህዳሴ የሚባለው ጽንሰ
ሃሳብና የሀገራችን አንዳንድ ህጎች ሳይመሳሰሉ አይቀርም ፡፡ በወረቀት ደረጃ እንከን የለሾች ሲሆኑ በተግባር ግን የማይተገበሩ ናቸው ፡፡ ህዳሴው የአፍሪካን ግጭትና ሙስናን የሚከላከል ፤
መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የሚያሰፍን ነው - ነኝ
ስለሚል ማለት ነው ፡፡ ይህ ታፍረውና ተከብረው በቆዩ የአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ቃል በቃል ነው ወይስ ተገልብጦ የሚነበበው ? እረ ለመሆኑ
1.
የትኛው መሪ ነው እጁን ከካዝና
የሚያርቀው ?
2.
የትኛው መሪ ነው ግጭቶችን
ለፓለቲካ መጠቀሚያ የማያውለው ?
3.
የትኛው መሪ ነው ስልጣኑን
በግዜው ለመልቀቅ ፍቃደኛ የሚሆነው ?
እንግዲህ ፓን አፍሪካኒዝምም ሆነ የአፍሪካ ህዳሴን
የሚፈታተኑ መሰረታዊ ጉዳዮች እነዚህ ናቸው ፡፡ ሃምሳኛው ዕድሜው ላይ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ስለ መሪዎች የከፋ ሙሰኝነት ፣
ስለ ስልጣን ገደብ ፣ ስለ ዴሞክራሲና ነጻነት ፣ ስለ ግጭቶች መንስኤ በድፍረት መወያየት ያልቻለው ለምንድነው ? በሌላ አገላለጽ
እነዚህ ጥያቄዎች ሃምሳ ዓመት ያስቆጠረው የህብረቱ ህንጻ ስር የሚገኙ የመሰረት ድንጋዮች ናቸው ፡፡ ድንጋዩን መሳብ ደግሞ ቤቱን
ያፈርሳል ፡፡ እና ማነው ተቀብሮ ለመሞት ዝግጁ የሚሆን ? ለዚህም ነው የአፍሪካ መሪዎች ቀይ በሚያበሩ መስመሮች / ፈንጂ ወረዳዎች
/ ዙሪያ መወያያት የማይደፍሩት ፡፡
አይነኬ አጀንዳ ቁጥር አንድ
‹‹ ለረጅም ዓመታት ሀገሪቱን ገዙ ፡፡ መቼ ነው
ስልጣንዎትን የሚለቁት ? ››
‹‹ በህይወት እስካለሁ ድረስ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት
እኔ ነኝ ! ››
ይህ ምላሽ በባለቤትነት የተመዘገበው በዙምባብዌው
ሮበርቱ ሙጋቤ ነው ፡፡ ይህን የመሰለ አስገራሚ ምላሽ የሚሰጡ የአፍሪካ መሪዎች የትየለሌ ናቸው ፡፡ ከ42 ዓመት በላይ ስልጣን
ላይ የቆዩት ሙአመር ጋዳፊ በህዝብ ማዕበል ተጠራርገው ቢወሰዱም እሳቸውን የመሰለ መሪ ለመፍጠር የመለዋወጫ ዕቃ ችግር በአፍሪካ
ምድር አይታሰብም ፡፡ ምርቱን በጥራት የሚያቀርበው የአፍሪካ ህብረት በርካታ አማራጮችን ከበርካታ ዓመታት ዋስትና ጋር ያቀርብሎታል
፡፡
30 ዓመታት የተፈተኑት ፓውል ቢያ ይሻሎታል ወይስ
22 ዓመታት ጋራዥ የማያውቁት ኦማር አልበሽር ? ሊባሉ ይችላሉ ፡፡ እና አማራጩ ሰፊ ነው ፡፡ የአፍሪካ መሪዎች የሚደርስባቸውን
የስግብግበነት ትችት ለመቅረፍ ይመስላል በ19990 ዎቹ አካባቢ የስልጣን ዘመናቸውን በሚገድብ እንቅስቃሴ ውስጥ ሰምጠው ነበር ፡፡
30 የሚደርሱ መሪዎች አንድ መሪ ከሁለት ግዜ በላይ መመረጥ አይችልም የሚል ሀሳብ በህገ መንግስታቸው ውስጥ አሰፈሩ ፡፡ ጉድ
! አፍሪካ በዴሞክራሲ እጦት ከሚከሰተው የልምሻ በሽታ ልትፈወስ ነው ተባለ ፡፡ ተጨበጨበ ፡፡
አንዳንዶቹ ግን በዚህ ህጋዊና ሰላማዊ የዴሞክራሲ
መረብ ውስጥ መጠመድ አልፈለጉም ፡፡ በፈር ቀዳጅ አጋሮቻቸው ላይም ‹‹ አይነጋ መስሏት… ›› የሚል ተረት ብጤ ወረወሩ ፡፡ እውነትም
የመምራት ሳይሆን የመፍለጥ - መቁረጥ ክፍለ ግዜው ማለቅ ሲጀምር ብዙዎቹ ምላሳቸው ሬት ሬት ይላቸው ጀመር ፡፡ በጠባቡ ጭንቅላታቸው
የስኳር ተገቢነትን በማረጋገጣቸው ለገቡት ቃልና ለህገመንግስቱ ተገዢ መሆን ከበዳቸው ፡፡ አያይዘውም ለተከበረው ህዝባቸው ሳይሆን
እንደ ማስታወሻ ደብተራቸው ለሚቆጥሩት ህገ መንግስት አጭርና ጓዳዊ ደብዳቤ በመጻፍ ማሻሻያውን በፊት ወይም በኃላ ገጹ እንዲሸከም
አደረጉት ፡፡ የአፍሪካ ህገ መንግስቶች ‹‹ ለህዝብ ጥቅም ሲባል … የተጀመሩ የልማት ውጥኖች ዳር እንዲደርሱ ሲባል … የጎመራው
ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዳይጨናገፍ… የህዝብን ይሁንታ ለማክበር ሲባል … እንደሳቸው በሳልና ታላቅ መሪ እስኪፈራ ድረስ … ››
በሚሉ ጅላጅል ሀረጎች መሳቅ እየፈለጉ እንኳ ይፈራሉ ይባላል ፡፡ የህጎች ሁሉ የበላይ እየተባሉ መፍራት ካለ - በርግጥም ራሱ ፍርሃት
ያስፈራል ፡፡
ቃላቸውን ቅርጥፍ አድርገው ከበሉ መሪዎች መካከል
የቡርኪናፋሶው ብሌስ ካምፓወሬ ፣ የኡጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቬኒ ፣ የካሜሮኑ ፓወል ቢያና የጋቦኑን ኦማር ቦንጎን ለአብነት ማንሳት ይቻላል
፡፡ እናም ዛሬ በውጊያ ፣ በኩዴታና ካርድ በማጭበርበር ወንበሩን የያዙ መሪዎች እስከመቼ እገዛለሁ የሚለው ጥያቄ አያስጨንቃቸውም
፡፡ የአባቶቻቸውን ፈለግ ይከተሉ ዘንድ በውስጥ ታዋቂነት ተፈቅዷልና ፡፡ የስዋዚላንዱ ምስዋቲ 25 ፣ የቻዱ ኢድሪስ ዲባይ 22
፣ የኢትዮጽያው መለስ ዜናዊ 21 .... የኤርትራው ኢሳያስ 21 ፣ የጋምቢያው ያህያ ጃማ 18 ፣ ሌሎቹም ኢኮኖሚው ቢያቅታቸው አገዛዛቸውን በሁለት ዲጂት ማሳደግ ችለዋል
፡፡ ታዲያ እነዚህን የመሳሰሉ መሪዎችን ያሰባሰበው የአፍሪካ ህብረት ‹‹ ስልጣናችሁን ገድቡ !! ›› እያለ በየግዜው አጀንዳ ቢይዝ
ከምጸታዊው ፈገግታ የሚወጣውን ጨረር በሙሉ ዓይን ማየት ይችላል ?
አይነኬ አጀንዳ ቁጥር ሁለት
በአንድ ወቅት የአልጄሪያው ፕሬዝዳንት አብዱልአዚዝ
ቡተፍሊካ ለዋሽንግተን ታይምስ እንደገለጹት በ1991 የተጀመረው የርስ በርስ ጦርነት ለመቶ ሺህ ህዝብ እልቂትና ለ20 ቢሊዮን የኢኮኖሚ
ኪሳራ ዳርጓል ፡፡
አፍሪካ ነጻ ከወጣች / 1960 / በኃላ 19
ሚሊዮን ዜጎቿን በጦርነት አጥታለች ፡፡ ይህ ህዝብ ያለቀው በቅኝ ገዢዎች አረር ቢሆን ለማሳበብ በተመቸ ነበር ፡፡ ግን አይደለም
- በራሱ ዜጎች ነው ፡፡ አንዳንድ ማሳያዎችን እንሰንዝር ፡፡
በናይጄሪያ የቢያፍራ ጦርነት - 1 ሚሊዮን
በሞዛምቢክ የሲቪል ጦርነት - 1 ሚሊዮን
በአንጎላ ›› ››
- 1.5 ሚሊየን
በሱዳን ›› ››
- 4 ሚሊየን
በኮንጎ ጦርነት - 6 ሚሊየን
በላይቤሪያ፣ ሴራሊየንና አይቮሪኮስት - 2 ሚሊየን
በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ - 800 ሺህ
በኢዲያሚን ዳዳ ጭፍጨፋ - 200 ሺህ
በሲያድባሬ - 500 ሺህ
በመንግስቱ - 400 ሺህ
በመለስ ዜናዊ - በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት
ብቻ 125 ሺ ሰዋች አልቀዋል ።
ጦርነት ከሚያስከትለው ሰብዓዊ ቀውስ በተጨማሪ
ኢኮኖሚውን ሽባ ያደርጋል ፡፡ ህዝቦች ጦርነት ሲጀመር ስለሚሰደዱ የምርታማነት መጠን ይቀንሳል ፡፡ የአህጉሪቱ ምርታማነት መጠን
በ1960ዎች በ 7 ከመቶ ፣ በ1970ዎቹ በ 15 ከመቶ ፣ በ1980 ዋቹ በ 8 ከመቶ ቀንሷል ፡፡ በዚህም ምክንያት አፍሪካ ሁሌም
ትፎክራለች እንጂ በምግብ እህል ራሷን መመገብ አልቻለችም ፡፡
ለዚህ አሰቃቂ ግድያና ለሚያስከትለው ክስረት በዋናነት
ተጠያቂ የሚሆኑት ስልጣን ላይ የሚገኙት አምባገነን መሪዋች ናቸው ፡፡
የአፍሪካ ህብረት ዘወትር ግጭትና ጦርነት የማይለያት አህጉር
ይዞ በጦርነቶቹ መሰረታዊ መንስኤዎች ላይ ደፍሮ ለመወያየት አጀንዳ መያዝ አይፈልግም ፡፡ የጦርነት መንስኤዎች የዴሞክራሲ ፣ የመልካም
አስተዳደር ፣ የዘረኝነት ፣ የልማት ፣ የስልጣን ክፍፍልና የመሳሰሉ ጥያቄዎች መሆናቸው ይታወቃል ፡፡ ይሁን እንጂ ስልጣን ላይ
የሚገኙ መሪዎች በአምባገነንነትና ሙስና ጡንቻ የፈረጠሙ በመሆናቸው የሌላኛውን ወገን ሀሳብ ጤናማ አድርጎ ለመመልከትና ለማስተናገድ
ፍቃደኛ አይሆኑም ፡፡ ሃያና ሰላሳ አመት ስልጣን ላይ ቢቆዩም ወንበራቸውን ለማካፈል በሚነሳ የሂሳብ ጨዋታ ላይ በራቸውን የሚዘጉት
በቢኤም ጥይቶች ነው ፡፡ እናም ጦርነትን የስልጣን መመከቻ ጋሻ የሚደረገውን ስልት ለማቆም አይፈልጉም ፡፡
በአሁኑ ሰዓትም በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ግጭት ውስጥ በመሆናቸው አሰቃቂው
የእልቂት ሰንሰለት አልተበጠሰም ፡፡ ተተኪዎቹም በዚህ ሻምፒዮን ውስጥ ሳይሳቀቁ መሳተፍ ጀምረዋል ፡፡ አንጋፋው የአፍሪካ ህብረት
ግን ለዓመታዊው ሪፖርቱ የሚሆን መረጃ ማሰባሰብ እንጂ በመሰረታዊው ምክንያት ዙሪያ ውይይት እንዲካሄድ መንገድ አያመቻችም ፡፡ ይህን
ለማድረግ የሚያስችል መሰረትም የለውም ፡፡
አይነኬ አጀንዳ ቁጥር ሶስት
ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ከገዳይነትና አምባገነንነት
በተጨማሪም በዘራፊነትም ፒ ኤችዲአቸውን ሰርተዋል ፡፡ በአስደናቂ የሌብነት ስልቶች ዙሪያ ጥናታዊ ወረቀቶችን አቅርበው የቲፍ -
ፌሰር ማዕረግ ያገኙም በርካታ ናቸው ፡፡ 40 ቢሊየን ዶላር የዘረፈው
ሙባረክ ፣ 14 ቢሊየን ያስደነገጠው ቤን አሊ፣ 10 ቢሊየን ያስመዘገበው ሞቡቱ ፣ 9 ቢሊየን ያስቆጠረው ባባጊንዳ ፣ የ 7 ቢሊየን
ባለቤቱ ኦማር አልበሽር ፣ የ3 ቢሊየኑ ጌታ የቶጎው ኢያዴማን ፣ የበርካታ ሚሊየኑ ባለሀብት የኢትየጽያው መለስ
በዋናነት መጠቃቀስ ይቻላል ፡፡
በዋናነት መጠቃቀስ ይቻላል ፡፡
አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ለዚህ ዓይነቱ አስነዋሪ
ስነምግባር ግድ ያላቸው አይደሉም ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሞቡቱ ሴሴኮ ለኮንግረስ ማን ማርቬን ዳይማሊ ‹‹ በዚህ ትልቅ ሀገር ለ
22 ዓመታት መሪ ሆኖ ለቆየ ሰው ያለኝ ገንዘብ / 10 ቢሊየን ዶላር / ምንም ማለት አይደለም ›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡
ዛሬም ስልጣን ላይ ያሉ መሪዎች በአንድ በኩል ሀገር ውስጥ ስለ ህዳሴ እየሰበኩ በሌላ በኩል በውጭ ሀገራት አያሌ ንብረታቸውን እያደሱ
መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም የራሳቸው አልበቃ ብሏቸው ቤተሰብና ቤተዘመድ ሁሉ በሀገሪቱ የሀብት ገንዳ ውስጥ እንዲዋኙ ፍቃድ ሰጥተዋል
፡፡
የኢኳቶሪያሉ ጊኒ ፕሬዝዳንት ልጅ ቱዎዶር ጉማ
ኦቢያንግ የሀገሪቱን የነዳጅ ገቢ የራሱ በማድረግ ወሲባዊ ህይወቱን ይመራል ፡፡ ይህ ማፈሪያ 38.5 ሚሊየን ዶላር የወጣበት የግል
ጀት፣ 30 ሚሊን ዶላር የፈሰሰበት ትልቅ ህንጻ ፣ 4 ሚሊየን ዩሮ የተቆረጠለት ተሸከርካሪ ፣ 18 ሚሊየን ዩሮ ያወጣ የስዕል ስብስቦች
ባለቤት ነው ፡፡
የአለማቀፉ ሪፓርቶች እንደሚጠቁሙት ለኮንጎ ብራዛቪል
ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሶ ንጌሶ ወንድ ልጅ ክሪስትል የሚወጣው ወርሃዊ ወጪ በኩፍኝ በሽታ ለሚሰቃዩ 80 ሺህ ህጻናት መድሃኒት መግዣ
አሳምሮ ይበቃል ፡፡ የአንጎላው ፕሬዝዳንት ጆሴ ኤድዋርድ ዶስሳንቶስ ሴት ልጅ ኢሳቤል የአባቷን ስልጣን ጋሻ በማድረግ በምታከናውነው
የአልማዝና ሌሎች ንግድ ስራዎች 550 ሚሊየን ዶላር ሃብት በማስመዝገቧ በአፍሪካ ሀብታም ሴት ተብላለች ፡፡ ሀብታም ሌባ ለማለት
የደፈረ ግን የለም ፡፡
አፍሪካዊያን በቀን ከአንድ ዶላር በታች በማግኘት
በድህነት ፣ በሽታ ፣ ድንቁርና ማቅ ውስጥ እየሰመጡ ቢሆንም እናስተዳድርሃለን የሚሉት መዥገር መሪዎች ሀብቱን የመመዝበሩን ዕቅድ አጠናክረው ቀጥለዋል ፡፡ ሙስና የሀገርና እድገት ጸር
መሆኑን የሚለፍፈው የአፍሪካ ህብረት ሚሊኒየርና ቢሊኒየር መሪዎች ፊት ስለ አስጸያፊ ተግባራቸው በጥልቀት ለመወያየት ደፍሮ አያውቅም
፡፡ ይህም ለአፍሪካ ህብረት አይነኬ አጀንዳ ሆኖ ተከብሯል ፡፡
እነዚህን አይነኬዎች በደንብ ነካክቶ ህገ ወጥ
አሰራሮችን ከአናት ማስተካከል ካልተቻለ ፓን አፍሪካኒዝምንና ህዳሴን እውን ማድረግ ያስቸግራል ፡፡ ለአፍሪካ የሚያስጎመዡ ህልም
የሆኑት እነ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርም እንቁልልጬያቸውን ይቀጥላሉ ፡፡ ውጤት ይገኛል ቢባል እንኳ ኮስሞቲካዊ እንጂ ስር ነቀል
አይሆንም ፡፡
No comments:
Post a Comment