Tuesday, July 11, 2017

የዘመኑ ሥነ-ግጥም ያነሳውና የጣለው



የፌስ ቡክ ግድግዳ ከሚነግረን አንደኛው ጉዳይ በርካታ ገጣሚያን እያፈራን መሆኑን ነው ። ሰነጽሁፍ በማይበረታታበት ሀገር ወፈ - ሰማይ ስንኝ መታሪያዎች እንደምን ፈለቁ የሚለውን ጥያቄ በቀላሉ ማንሳት ቢቻልም ጥናት ላይ ሳይመሰረቱ ቀላልና የዋዛ ምላሽ ማግኘት አይቻልም ።

ግን ደግሞ ለጸሀፊዎች ወይም ለመስኩ ባለሙያዎች ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ የተገኝ ይመስለኛል ። የወጣ መጽሀፍን እያደንኩ በማነብበት ዘመን አታሚዎችም ሆነ አከፋፋዮች ሥነ- ግጥምን ምናምን እንደነካው እቃ አፍንጫቸውን ይዘው ሲያርቁት አውቃለሁ ። ያኔ ብዙዎች እንደ ቀንድ አውጣ ኩምሽሽ ብለው ራሳቸውን ምሽግ ውሰጥ ይከቱ ነበር ።

ዛሬ ተመስገን ነው ። ቀንድ አውጣዎቹ አንገታችውን ስበው እየዳኹ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ በፌስ ቡክ ግድግዳ ላይ ክንፍ አውጥተው እየበረሩ ናቸው ። በህትመት ደረጃ የሚታየውን የብዛት መሰላል ግራፍ ለማድረግ የቅርብ አስተውሎት / በርቀት ምክንያት / ባይኖረኝም አሁንም የፌስ ቡክ ግድግዳ የሚነግረኝ ዜና አለ ። ግጥም ጥቂት በማይባል መልኩ እየተመረቀ መሆኑን ።
ታዲያ እነዚህ የግጥም ስራዎች የሚያበስሩን ብዛታቸውን ብቻ ሳይሆን ያነሱትንም የጣሉትንም ጉዳይ ጭምር ነው ። በርግጥ ምን የተለየ ነገር እያነሱ ናቸው ?

1 . የዘመኑ ግጥሞች በሚያነሱት ሀሳብ በእጅጉ የበለጸጉ ናቸው ። ያልታሰቡና ያልተገመቱ ርዕሰ ጉዳዮችን ፈልፍለው በማውጣት በደማቅ ሲጽፏቸው እንመለከታለን ። ይህ የሚያሳየው ገጣሚው የመጻፊያ ርዕስ ችግር የሌለበት መሆኑን ነው ። ርዕስ ለመምረጥ አምስቱንም የስሜት ህዋሳቶች በደንብ ይጠቀማሉ ።

ከወደቀ ግዙፍ ግንድ ላይ የሚያማመሩ ጉማጆችን ለማውጣት በጭፍኑ አይደለም መጥረቢያቸውን የሚወረውሩት ። በስልትና በተገራ መልኩ ነው ጎኑን የሚኮረኩሩት ። ያኔ ተንሳጣጭ ሳይሆን የሚያስቅ ድምጽ ፈጥረው እኛንም የሳቅ ተጋሪ ያደርጉናል ።

2 . ጥበባዊ አጨራረስ የዘመኑ ግጥም ደማቅ ባህሪ እየሆነም ይመስላል ። ከተነሳው ሀሳብ በተጨማሪ የግጥሙ መዝጊያ አንዳንዴም የግጥሙ አንኳር መልዕክት አንባቢው ከሚጠብቀው በተቃራኒ ሁኔታ ሲያልቅ እንመለከታለን ። በስልቱም እንዝናናለን ። እንስቃለን - በሥስ ፈገግታ ሳይሆን ጮክ ብሎ ባመለጠን ሳቅ ። እንገረማለን - በአርምሞ ብቻ ሳይሆን ነገርና ጥያቄ በሚያመነጭ ትዝብት ። ይህ አይነቱ የፈጠራ አካሄድ ቀደም ባሉት የግጥም ስራዎች ጎልቶ የወጣ ነው ማለት አይቻልም ።

3 . ምጸታዊ ቅርጽም / Satirical poetry / ሌላኛው መለያ እየሆነ መጥቷል ። በዚህ ስልት ትልቅ ልምድ ያላቸው ሮማንስ ናቸው ። ስልቱ በተለይም ነባራዊውን የፖለቲካ መስመር ለመሸንቆጥና ለመተቸት ፣ በገሃድ የሚታየው ፍትህና ሞራል ላይ ለማላገጥ አመቺ  ስልት ነው ።

የዘመኑ ገጣሚ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቦበት በየቤቱ እኽኽ ... የሚለውን ዜጋ ትንፋሽ በቅብብሎሽ አደባባይ ላይ እያሰጣው ይመስላል ። በፖለቲካው ምክንያት በየቤቱ የተወከለው የበገና ድምጽ ነው ። ለስለስ ያለና አንዳች ተአምር የሚለማምን ድምጽ ። ገጣሚዎቹ ይህን በገና አንዴ ትራምፔት ሌላ ግዜ ማሲንቆና ከበሮ እያደረጉት ነው - በደማቁ ።

ከላይ የተገለጹት  የፈጠራ አካሄዶችና ስልቶች ቀደም ባሉት የግጥም ስራዎች ጎልተው የወጡ አልነበሩም ። በሌላ በኩል የዘመኑ ገጣሚ እንዳነሳው ሁሉ ምን አይነት ስልቶችን እየጣለ መጥቷል የሚለውን ጥያቄ መቃኘት መልካም ነው ።

1 . የምሰላ / Imagery / መኮሰስን እንደ አንደኛው ችግር ማንሳት ይቻላል ። ገጣሚ በአንባቢ ጭንቅላት ውስጥ ምስልና ስሜትን መፍጠር ይኖርበታል ። ምሰላ ስንል የፎቶ ጉዳይ ብቻ አይደለም ። ምሰላ የሰእል ፣ የድምጽ ፣ የማሽተት ፣ የመቅመስና የመዳሰስ ህብረ ውጤት ነው ።

ከዚህ አንጻር የዘመኑ ግጥሞችን በአምስቱ ህዋሳታችን ለመረዳት እያስቸገረን ነው ። ለዚህ ትልቁ መንስኤ ደግሞ አንድ አይነትን ይተበሃል መከተላቸው ነው ። አብዛኛው ገጣሚ ግጥም በአራት፣ በስድስት እና ስምንት መስመር የሚያልቅ ጥበብ እንደሆነ የበየነ ይመሰላል ። እናም ጉዳዩን እንደጀመረ ጉዳዩን አሳጥሮ ይጨርሳል ። የግጥም መንገድ አጭርና የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ነው ባይ መስሏል ። አንዳንዴ ግጥም ማንበብ ጀምራችሁ ማለቁን በግድ ታምናላችሁ ። በቃው ... ይሄው ነው ? ... ምን ለማለት ፈልጎ ነው የሚሉ ጥያቄዎች በምናባችሁ ይዥጎደጎዳል ። ያ ማለት ግጥሙ ወይም መልእክቱ አላሳመናችሁም ማለት ነው ። ግጥም እንደ አንባቢው መረዳት ነው ብሎ የቤት ስራውን ለእናንተ የሚቆልል ስንኝ ቋጣሪ ሳይውል ሳያድር ስራውን መፈተሽ ይኖርበታል ።

ውጤቱን በምሳሌ ላስረዳ -  በቡና መታደም ስርአት ። የበፊት ገጣሚዎች ስኒውን ፣ ቡና ቁርሱን ፣ የካዳሚዋን እንቅስቃሴ ኪናዊ በሆን መንገድ ሊያቀርቡት ይችላሉ ። ቡናው ከጀበናው ማማ ቁልቁል ስኒው ላይ እንደ ፏፏቴ ከመፈጥፈጡ በፊት ጢሱን ሊያሳዩንና እንድናሸተው ሊጋብዙን ይችላሉ ። በጢሱ ጠመዝማዛ ሰረገላ አሳፍረው የነገውን መጻኢ ማንነት ሊያመላክቱን ሁሉ ይችላሉ ። የአሁኑ ገጣሚ ዙሪያ ጥምጥሙን በመግደፍ በሞቀ ውሃ ውስጥ ዱቄት ጨምሮ እንደሚጠጣ እያሳየ ነው ።

ለአሁኑ ገጣሚ የሰርገኛ መኪና አደባባዩን ደጋግሞ መዞሩና አናስገባም ሰርገኛ እያሉ መገፋፋት ብዙም ጠቃሚ የሆነ አይመስልም ። ለመጋባት ከማዘጋጃ ፍቃድ ማግኘት ካልሆንም ያለምንም ግርግር ጠልፎ ጉዳዩን መጨረስ በቂ እንደሆነ እያሳየ ይመስላል ። ይህነኑ ብይንና እምነት ሰእላዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ ቢቻልም አንድ ጥሩ መንገድ በሆነ ነበር - ሆኖም ቶሎ ወደ ጉዳዩ የመንደርደር ስልት ግን ምሰላን እያዳከመው ነው ። የዘመኑ ገጣሚ የግድ እንደ ሆሜር ኦሊያድ እና ኦዲሴ ረጅም ተራኪ ስታይል ይጠቀም ለማለት ሳይሆን ቢያንስ ስብጥራዊ መንገዶች ይኑሩት ነው ። ረጅም ሆኖ የሚመስጥ ግጥም መስራት እንደሚቻልም የከበደች ተክለአብ ፣ አበራ ለማ ፣ ክፍሌ አቦቸር እና የመሳሰሉ ስራዎችንም ያገላብጥ ነው ።

በቅርጽ አወራረድም የመመሳሰል በሽታ ይታያል ። ብዙ ግጥሞች እንደ ፋብሪካ ምርቶች ተመሳሳይ ፍሰት ፣ ዜማና ምት የሚጋሩ መስሎ ይሰማናል ። በጣም የወጡ ገጣሚዎች በሌሎች ላይ እያሳደሩ የመጡት ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑ እስኪታወቅ ደረስ ። ገጣሚው ለምሳሌ እንደ በእውቀቱ እንጂ እንደ ጸጋዬ ፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፣ ከበደ ሚካኤል ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ወዘተ የራሱን መስመር ማስመር እንዳለበት አላመነም ።

2 . የቋንቋ ችግር ። የዘመኑ ገጣሚ ግጥም የሚጻፈው በቀላል ቋንቋ ነው የሚባለውን መረዳት በመያዝ ይመስላል የተለየ ትኩረት ሲሰጥ የማይታየው ። የግጥም ቋንቋ ከተራውና ከተለመደው መግባቢያ የላቀ ውበትና ዜማ የተጎናጸፈ ነው ።  የግጥም ቋንቋ የሚፈጥረው ውስጣዊ ወይም ሌላኛው ትርጉምም ማለታችን ነው ። የግጥም ቋንቋ ከሰዋሰውና ከቀበሌኛ ዘዬም በላይ ነው ።
ጠንካራና ውብ ቋንቋ ለመፍጠር ሰርካዝም የሚባሉትን ምጸት ፣ ሽሙጥና ውስጠ ወይራዎችን ማወቅና መጠቀም ይጠቅማል ። ሜታፎር የሚባሉትን ዘይቤያዊ አነጋገር ፣ አሊጎሪና ምሳሌዎችን ማወቅና መጠቀም ግድ ይላል ። ግጥም እነዚህን ዘይቤዎች አይነኬ የሚያደርጋቸው ከሆነ ተራ መደዴ ነው የሚሆነው ። ውበትና ልቀትን ነው የሚያደበዝዘው ።


እናም የሚነሳውን እያጠናከሩ የሚጣለውን ደጋግሞ እየመረመሩ መሄድ የሚያዋጣ ይመስለኛል ።

No comments:

Post a Comment