Tuesday, April 17, 2012

‎የፌስ ቡክ ወግ‎








ፌስ ቡክ ከነችግሩና ከነሱሱም ቢሆን ብዙ ሚዛን የሚደፉ ጠቀሜታዋች እንዳሉት መከራከር የዋህነት ነው፡፡ የቁምነገረኝነቱን ጎን መመርመር ለእናንተ ትቼ ከፌዛዊ መልኩ/ ጥቅሙ ጥቂቶቹን ልወርውር፡፡

ፌስ ቡክ በደበረዋትና ብቸኛ በሆኑ ግዜ የተረት አባት ሚናን ተክቶ ሊያስቆት ይችላል፡፡ መቼም የአጫጭር ጥቅሶች ባህር በመሆኑ ጥቅስ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆኑ በንግግርዋ መሃል ‹‹ እጠቅሳለሁ ›› የሚል ማዋዣ እንዲጠቀሙ መንገድ ይመራል፡፡ በየመንገዱ ጥቅሶች ካጋጠመዋት ‹‹ ግዛ-ግዛ ›› የሚል ሞጋች መንፈስ እንደበቀለብዋት ይገነዘባሉ፡፡ የፌስ ቡክ ጣሪያና ግድግዳ ፎቶ በፎቶ በመሆኑ በየቤቱ ለእንግድነት ሲሄዱ ‹‹ እስኪ ያቺን አልበም ወዲህ በላት ?›› የሚል ጥያቄ ያመነጫሉ፡፡ አልፎ አልፎ  የስዕል ኤግዚቢሽኖች መከፈታቸውን ሲሰሙ ‹‹ መግዛት ባንችል እንኳን ሄደን ማበረታታት አለብን !! ›› የሚል ደመቅ ያለ ንግግር ወደ ሌሎች ጆሮ እንዲደርስ ሳያደርጉ አይቀርም፡፡ መቼም ግጥም ወይም መጣጥፍ ለሚዲያ ቢልኩ ውበቱ፣ መልዕክቱ፣ ሚዛናዊነቱ፣ ደጋፊነቱ ወዘተ የተባሉ ህጋዊና ህገወጥ ሳንሱሮችን ማለፍ አለበት፡፡ ፌስ ቡክ ገጽ ላይ ታዲያ ሲፈልጉ ሰክረው፣ ወይም በእንቅልፍ ልብዋ አይንዋን  እያጨናበሱ ሁሉ ያለ ከልካይ ይጽፋሉ፡፡ የዚህ እኩያ የሆነ ነጻነት አሜሪካ ወይም ህንድ ያገኛሉ ? በፍጹም !!! 
 
ፌስ ቡክ ብቻ ሳይሆን የፌስ ቡክ ኦንላይን ተጠቃሚዋችም ነገረ ስራ ከተመረመረ በጣም ነው የሚያስቀው፡፡ በጣም ነው የሚያሳዝነው፡፡ ብዙ በጣሞች፡፡ ታዲያ ለወሬ እንዲመቸን ለተጠቃሚዋች ባህሪ ስያሜ እየሰጠን ነው የምናወራው ያው ለመዝናናት ያህል የቀረበ መሆኑንም አስምሩልኝ - በተለይ ለወግ አጥባቂዋች

1 . አድፋጭ ፤  ይህ ቡድን ዘወትር በአውሮፓ በረዶና ጉም የተሸፈነ ነው የሚመስለው፡፡ ብዙ ግዜ ኦንላይን ላይ አይጠፋም ፤ ግን አይታይም፡፡ አልፎ አልፎ ወይ ጥቅሱን ወይ ፎቶውን ወይ ዜናውን ዋናው ሰሌዳ ላይ በተን ያደርጋል፡፡ ጠፋ እንዳትሉት ደግሞ ሰሌዳው ላይ በተለጠፉት መረጃዋች ላይ ወይ ፍቅሩን አሊያም ተቃራኒ ሀሳቡን ሲገልጽ ያዩታል፡፡ ማህበራዊ ተሳትፎውን በጓጉንቸር ቁልፍ የከረቸመ ይመስላል፡፡ አድፍጦ ይሰራል ወይም አድፍጦ ጓደኞቹን ይከታተላል ለማለት ያስቸግራል፡፡ መስኮትና በሩ በተዘጋ ቤት ውስጥ ስንት ቀን ? ስንት ወር ? መቀመጥ ይቻላል፡፡ ‹‹ አይወብቃቸውም ? ›› እላለሁ አንዳንዴ  ‹‹ አይጨንቃቸውም ? ››

2. ጠባቂ ፤  ይህ ቡድን መብራቱን አያጠፋም፡፡ ሰውየው የቅርብም ሆነ የሩቅ ጓደኛዋ ሊሆን ይችላል፡፡ ከተለያያችሁም ረጅም ግዜ አስቆጥራችሁ ይሆናል፡፡ የፈለገ ቢሆን ግን ቅድሚያውን ወስዶ ሰላምታ አያቀርብልዋትም፡፡ የግድ ከእርስዋ የሚለኮሰውን ክብሪት ይጠብቃል፡፡ ዛሬ ቅድሚያውን መውሰድዋን ግምት ውስጥ አስገብቶ እንኳ በሚቀጥለው ግዜ የማያልቀውን ሰላምታ ለማስቀደም ፍላጎት የለውም፡፡ ደግነቱ ሁሌም ቅድሚያውን የሚወስዱ ከሆነ ፈታ ብለው የሚያወሩ ናቸው፡፡ የኩራት ጉዳይ ወይስ የክብር ፍለጋ ?        ‹‹ ወንድ ወደሽ ጺሙን ፈርተሸ ›› እንዴት ይሆናል ነው ነገሩ ???

3. ስልታዊ አፈግፋጊ ፤ ይህ ቡድን መስመር ላይ መኖሩ በመብራቱ ይታወቃል፡፡ አገር ሰላም ነው ብለው ወሬ ሲጀምሩ በጥንቃቄም ቢሆን መልስ ይሰጣል፡፡ ወሬው የፓለቲካ፣ የኑሮ ውድነት፣ የወቅታዊ ሁኔታዋች ላይ ሲያነጣጥር ደህና እደር እንኳን ሳይልዋት መብራቱን ድርግም አድርጎ ያጠፋል፡፡ የርዕዮተ ዓለምና የሌላ አመለካከት ካላችሁ ደግሞ እርሶ ኦን ላይን እንደገቡ የርሱ መስኮት ጨለማ ይውጠዋል፡፡ ወይም ደግሞ ደቃቅ ሰላምታ ያቀርብልዋትና ምላሽዋን ሳይጠብቅ ቤቱን ክርችም ያደርጋል፡፡ ይሄ እንግዲህ አገም - ጠቀም መሆኑ ነው፡፡ ሰላምታ ሲልኩለት ባላየ ማለፍም ስልቱ ነው፡፡ ከዛ የእርሶ መስኮት ሲዘጋ ‹ በጣም ይቅርታ አላየሁትም ነበር › የሚል መልዕክት በጣም ዘግይታ ትደርሶታለች፡፡ እዚህ ቡድን ውስጥ ያሉ ሰዋች በጥርጣሬና በፍርሃት የተዋጡ ነጻነት የራቃቸው ስለሚመስሉኝ ያሳዝኑኛል፡፡ ሁሌም በአንድ ጥቅስ የሚጽናኑም ይመስለኛል     ‹‹ በጎመን በጤና !!! ››

4. ተቸካይ  ፤ ብዙም ባይሆኑ እዚህ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ተጠቃሚዋችም አሉ፡፡ ለጓደኝነት ጠይቀዋታል፣ ወይም ጓደኝነትዋን ተቀብለዋል፡፡ በኦን ላይን ሜዳ ላይ ለሚልኳቸው መልዕክትም ሆነ ሰላምታ ግን ምላሽ አይሰጡም ፡፡ ምን ማለት ነው ? ምን እያሰቡ ነው  ? የሆነ ነገር ሰሌዳው ላይ በመወርወር ይሳተፋሉ ነገር ግን የጓደኞቻቸውን ተሳትፎ በማድነቅም ሆነ በመተቸት አስተያየት አይሰጡም ፡፡ ወይ ጉድ የሆነ ፓርቲ አላያቸውም እንጂ ‹‹ መሃል ሰፋሪ! የያዘውን የማይለቅ ! የድሮን የበግ ዋጋ በመጥራት ግዜውን የሚያሳልፍ ! ›› ወዘተ ወዘተ እያለ ያሸክማቸው ነበር ፡፡

5 . ሰጥቶ ተቀባይ ፤ ይህ ቡድን መልከ ብዙና ነገረ ዓለሙ የገባው ይመስለኛል፡፡ እንደ ነጋዴ ሳየው ወዲህ የሚልከውንም ሆነ ከዚያ የሚመጣለትን መረጃ በአግባቡ ያውቃል፡፡ በዲፕሎማት ጎን ከታየ ለያዘው ነገር በመከራከር ከዛኛው ወገን የሚገኙ ተሞክሮዋችን አንድ ባንድ ይለቅማል፡፡ ውይይት ለመክፈትም ሆነ የውይይት ግብዣ ሲቀርብለት ለመታደም አይቸገርም፡፡ በር ዘግቶ ሲሰራ መልዕክት ብትልኩለት ምላሹ ፈጣን ነው፡፡

6. የሌሊት ወፎች ፤ ፌስ ቡክ ላይ ቀን ዳናቸውን አጥፍተው ሌሊት ደምቀው የሚታዩ ሰዋች አጋጥመውኛል፡፡የለሊት ወፍ ቀን በየዛፉና በየዋሻው ቁልቁል ተዘቅዝቃ ነው የምታሳልፈው፡፡ ለሊት ቀን የጠፋውን ግዜ ለማካካስ በሚመስል መልኩ እንደ ጀት ስትካለብ ትውላለች ፡፡ ማታ ማታ መስኮታቸውን የሚከፍቱ ፌስ ቡከሮች እንደ ለሊት ወፍ ተኝተው ሳይሆን በስራ ወዲህና ወዲያ ሲካለቡ የሚውሉ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ እንደ ለሊት ወፍ ወይም እንደ ‹ አርጋው በዳሶ › በጭንቅላታቸው ቆመው አይደለም የሚሰሩት፡፡ የእንቅልፍ ሰዓታቸውን ስለሚሻሙ ብቻ ሳይሆን ባልነበሩበት ሰዓት ምን እንደተከናወነ ለማወቅ ከአንዱ ሳይት ወደሌላው በፍጥነት የሚሮጡ ይመስለኛል፡፡ ስታዋሯቸው ሁኔታዋችን በአጭሩ ለመቋጨት የሚሞክሩትም ከዚህ አንጻር ሊሆን ይችላል፡፡ ውጪ ያሉትስ ይሁን እዚሁ እያሉ ካለ ለሊት አንታይም የሚሉት ምንድነው ሀሳባቸው ? ፌስ ቡክ ውስጥ የምታማልል ጨረቃ አለች እንዴ  ? በተምስጦ እያነበቡ ቅኔ ለመቀኝትም ሊሆን ያችላል ? የአይን ቆብ ላይ ያረገዘ እንቅልፍን ለመገላገል ያመችም ይሆናል፡፡

7 . የመብራት ሃይል ባልደረባ ፤ በሀገራችን እምነት ካጡ መ/ ቤቶች አንዱ መብራት ሃይል ነው፡፡ የማይታመነው ባልተጠቀሙበት ታሪፍ ላይ ያሰኘውን እጥፍ ጨምሮ ማስከፈሉ አይደለም፡፡ ብርሀን ሆነልኝ ሲሉ ወዲያው በጨካኝ እጁ ወደ ጨለማ ይወረውሮታል፡፡ በቃ ጠፋ! ብለው ተስፋ ሲቆርጡ ብልጭ ብሎ ሊያስደስትዋት ይችላል፡፡ ወዲያው ደግሞ ምስጋናዋትን አስጨርሶ ድራሹ ይጠፋል ‹‹ እረ እልም ያድርግህ እቴ !! ›› የማይደርስ ርግማን ከኋላው ይከተለዋል፡፡ እና አንዴ ይበራል፣ አንዴ ይጠፋል፡፡ ፌስ ቡክም ላይ መስኮታቸውን በኦን ላይን መብራት ብልጭ አድርገው በሆነ ነገር እንደ ደነገጡ ሁሉ ድርግም አድርገው የሚዘጉ ሰዋች አሉ፡፡፡ አንዳንዴ እንደውም ይህ ነገር በር ቢሆን አቤት ጩኀቱ !! ስል አስባለሁ ፡፡ አሁንም አዘናግተው ብቅ ይሉና ወዲያው ጨለማው ውስጥ ይሰወራሉ፡፡ ይህን ጨዋታ ለማራዘም ከፈለጉ የርስዋን መብራት ድርግም አድርገው ቆይተው ድንገት ሲያበሩት ያ የመብራት ሃይል ባልደረባ በብርሃን ተርታ ተሰልፎ ያገኙታል፡፡ ወዲያው ግን ጨለማ ይውጠዋል፡፡ አሁን ለብርሃን ሳይሆን ለጨለማ ይስቃሉ፡፡ ምንድነው እንደዚህ ማብሪያ - ማጥፊያ ማንገጫገጭ !!!  ‹‹ እረ አንፓሉ ያቃጠላል ?? !! ››

ስለደከመኝ ምድቡን እዚህ ጋር አቁሜዋለሁ ፡፡ እርስዋን የት ቅርጫት ውስጥ አገኙት ?? ያልታየ ምድብ ካለም ልምድዋን ይወርውሩ፡፡ 12 ከደረስን በሁለት ተከፍለን አንድ የፌስ ቡክ ፕሪምየር ሊግ እንመሰርታለን ፡፡



1 comment:

  1. Dear Alexo,it is a very intersting outlook about Facebook and its users,,,it is a real out look also i can say,,,,FB is really gonna becomes the whole part of life here in my part of the world,,am expecting the other parts on related issues on FB,,,all the best,,Fasika kebede

    ReplyDelete