Friday, April 20, 2012

‎ያልተደራጁ ውሾች‎



በደ/ዘይት እየተወራለት የመጣውን  የኩሪፍቱ ሪሶርት ለመመልከት አንድ ከሰዓት ከአንድ ቡድን ጋር አቅንቼ ነበር፡፡ ወደ መዝናኛው ያመራሁት በሳምንት አንድ ቀን ለ30 ደቂቃ በነጻ መጎብኘት ይቻላል በሚባልበት ቀን ነበር፡፡ ከዚህ ቀን ውጪ  ለመግቢያ የሚጠየቀው ወጪ / በርግጥ ምሳ ይጨምራል / የሀገሬን ድሃ ማዕከል ያደረገ አይደለም፡፡

ወደዚህ መዝናኛ ሳመራ በርካታ ውሾች አራትና አምስት ሆነው በትናንሽ ዛፎች ጥላ ስር ተለሽልሸዋል፡፡ በዱር እንስሳት ባህሪያዊ እሳቤ ቢሆን የቡድን ምስረታው በራሱ መልእክት ነበረው፡፡ የጎረምሳ ቡድን…ብዙ ሚስቶችን የሚያስገብር የአባወራ ቡድን…አንድ ቤተሰብን ያቀፈ ቡድን… ወዘተ በማለት ፡፡ እነዚህ ግን የቤት እንስሳት ናቸው፡፡ በወንድማቸው ቀበሮና በአጎታቸው ተኩላ አይን ለአፍታም ቢሆን ካየናቸው ዱር ተኮር ትንተና አናጣም ፡፡ አዲስ ውሻ ወደ ጥላው መንደር ሲመጣ የራሱን መሬት በራሱ ግዜ ከተመራ በኋላ በተቻለ መጠን ድንጋዩንና አሸዋውን በእግሮቹ ይጠራርጋል፡፡ ስራው የሚያበቃው ርጥብ መሬት ከታየ በኋለ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የዛፎቹ ጥላ ብቻ በራሱ በቂ አለመሆኑን ነው ፡፡

ሙቀቱ ድብን ስላደረጋቸው ነው መሰለኝ የርስ በርስ ግጭቶች አይታይባቸውም፡፡ ውሾች በሙቀት ወቅት ያሳዝናሉ፡፡ ሁመራና ጎዴ ያየኋቸው ውሻዋች ትዝ አሉኝ ፡፡ በስህተት ቢረገጡ እንኳን ቀልጥፈው በመነሳት ‹‹ ው…ው… ›› የሚባለውን ውሻዊ ወግ ለማሰማት አቅም ያንሳቸዋል፡፡ ጎበዝ ከሆኑ እንደምንም የአንድ አይናቸውን ቆብ ከፈት አድርገው ብዥ ያለን ምልከታ ይጠቀሙ ይሆናል፡፡

አወዳደቃቸውና ፍርግጥግጥ ማለታቸው ከጎዳና ተዳዳሪዋች ጋር ቅርበት ያላቸው ያስመስላል፡፡ድንገት ደግሞ የአሜሪካው ኬኒል ክለብ ፍረጃ ወይም ጥናት ትዝ አለኝ ፡፡ ይህ ቡድን የአለማችን ውሾች በሙሉ ዝርያቸው 150 ያህል ነው ብሎ ይነሳል ፡፡ እነዚህን ዝርያዋች ደግሞ በሰባት መሰረታዊ ቡድን ከፍሏቸዋል ፡፡ የስራ፣ የስፓርት፣ የአደን፣ የከብት ጠባቂ፣ የጌጥ /አሻንጉሊገቶች/ እና ስፓርታዊ ያልሆኑ  በሚል፡፡

ውሻ በዚህ መልኩ ይፈረጅ እንጂ ከሰው ልጆች ጋር ብዙ ታሪክ ስርቷል፡፡ በነገራችን ላይ ከኛ ጋር ሲኖር 25ሺ አመታትን አስቆጥሯል ፡፡ ትስስራችንም ‹‹ የፍቅር እስከ መቃብር ›› ያህል መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዋች ሞልተዋል ፡፡ ለአብነት ያህል በዴንማርክ፣ አየርላንድ፣ ጀርመንና ቻይና የተቆፈሩ የጥንት መቃብር ቦታዋች ውሻና ሰዋች አንድ ላይ ተቀብረው ተገኝተዋል ፡፡ ‹‹ እኔ ስሞት ከተከበረው ውሻዬ አጠገብ ቅበሩኝ ›› የሚል ኑዛዜ ነበር ማለት ነው!

ውሻ ቀደም ባሉት ጦርነቶች መልእክት አቀባይ ሆኖ ስርቷል፡፡ ዛሬ ደግሞ በወንጀል ምርመራ፣ መስማት ለተሳናቸው ጆሮ እና እጅ ሆኖ፣ ማየት ለተሳናቸው ዓይንና እግር ሆኖ አጋርነቱን አጠናክሯል፡፡ ከሌላው አለም ሱፍን አስበልጣ ወደ ውጭ የምትልከው አውስትራሊያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በጎችን አደራ ሰጥታ ወደ መስክ የምታሰማራው ለውሾች ነው፡፡ ውሻ ዳርና ዳር ሆኖ ምናልባትም ጥርሱን እየፋቀ ‹‹ ና ተመለስ ብዬሃለሁ ! …›› ይለዋል በጸባይ ፡፡ 

‹‹ ይሄ ነጫጭባ ዛሬ ምን ቀምሷል ?!.... መስመሩን ይዞ አይጓዝም እንዴ ?! ›› ይለዋል አብሻቂ በግ ሲያጋጥመው ደግሞ ::
ታዲያ ይህን መሰሉ ውሻ ያለው ክብር፣ ፍቅርና እንክብካቤ ቀላል እንዳይመስላቸሁ፡፡ ቢያጠፉ እንኳን ‹ ጥፋ ከዚህ! ልክስክስ ! › ተብሎ አይዋረድም፡፡ ወይም ድንገት ሳያስብ ጀርባው በወፍራም ዘነዘና አይወቀጥም ፡፡ መጀመሪያ ልክ እንደ በኩር ልጅ ምቾት የሚሰጥ እቅፍ ውስጥ ይገባል ፡፡ ከዚያም ጀርባው፣ አንገቱና ጆሮው ላይ ለስላሳ ጣቶች ስልት ባለው መልኩ እንዲደንሱ ይደረጋል፡፡ ከዚያ ነው የሚከተለው ንግግር የሚደመጠው  ‹‹ ምነው ቦቢ?! What’s wrong with you ? are you alright any way? Ohhh! My hero! I hope you will not repeat such a silly mistake! ›› በመጨረሻም ምርቃት ጣል ይደረግለታል - ማለትም የሆነ ቦታ ይሳማል፡፡

መቼም የጓደኛችንን ውሻ ተግባር እንዘርዝረው ብንል ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ ታዲያ ምነው የደ/ዘይት ውሾች ያለስራ ተቀመጡ?!       ‹ አደገኛ ቦዘኔዋች ›  ብለን ለመጥራት የሚቀረን አላፊ አግዳሚውን ባለመተናኮላቸው ብቻ ነው ፡፡ በየቦታው እንደ ችቦ ተሰባስበዋል፡፡ ግን አልተደራጁም፡፡ ሳይንሳዊ መስመር እንከተል ካልን  ከሰባቱ ዝርያዋች የት ውስጥ እንደሚወድቁ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ የመደራጀት ጥያቄ አቅርበው ‹ ፍትሃዊ  አይደለም › የሚል ምላሽ አግኝተው ከሆነስ ? ደግሞ ለውሻ እንዲሉ….. 

ግራም ነፈሰ ቀኝ የአካባቢው ነዋሪዋች፣ ባለሀብቶችም ሆነ ባለስልጣናት ውሻን የልማት ምንጭ አድርገው ማየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመደራጀት ለመጠቀም ሲሉ ግን ውሾች ራሳቸው መራራውን ሃላፊነት ቀድመው መውሰድ አለባቸው፡፡
እነሆ የደ/ዘይት አርሶአደሮች በባህላዊ መንገድ ቢሆንም አጭር ስልጠና እንዲያዘጋጁ ጥያቄ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ ስልጠና መሬት ላይ የሚያስቸግራቸውን አይጥና አይጠ መጎጥ በመቀነስ ረገድ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ካስፈለገ የባሌን ወይም የሰሜን ቀበሮን የአደን ስልት በተሞክሮ መውሰድ ይቻላል፡፡  ተሞክሮው ይቀመራል፣ የተቀመረው ይስፋፋል ፡፡ የሀገራችን ውሻ ጥርሱን እየፋቀ ባይሆንም ኮቴ እየነከሰ ከብት መጠበቅ ይችላል፡፡ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ መሪ ለሆነቸው ሀገር ጠንከር ያለ ተሞክሮ አስፈላጊ በመሆኑ ለልምድ ልውውጥ አሜሪካ ወይም አውስትራሊያ መጓዝም የግድ ነው፡፡ ርግጥ ነው ባሁኑ ግዜ አፋጣኝ ምላሽ ሊያገኝ የሚችለው የቻይና ጉዞ ነው፡፡ ቻይናዋች ግን ውሻዋቻችንን በሰላም ይመልሳሉ ማለት ዘበት በመሆኑ ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

የደ/ዘይት ውሾች ቀጣዩ ጥያቄዋቻቸው ባለሀብቶችን ይመለከታል፡፡ ባለሀይቋ ከተማ የሚዝናናባትን እያረካች ያለቸው በዋናነት በራሱ በሀይቁ ተፈጥሮ ሲሆን አልፎ አልፎ ጥቂት ጀልባዋች ዊን ዊን እንዲሉ ታደርጋለች፡፡ እነዚህ ውሾች ጥቂት ስልጠና ቢያገኙ ሀይቁ ባፍዛዥ የሰርከስ ትርዒት ሊደምቅ ይችላል፡፡ የውሾች የዋና ውድድር ቢካሄድስ? ለአብነት ባለሀብት የተረዳቸው 14ሺህ የሚደርሱ የአሜሪካ ውሾች በየአመቱ የውሻ ትዕይንት ያቀርባሉ፡፡ በእንግሊዝ፣ ሜክሲኮና ስፔን የውሻ የሩጫ ውድድር የተለመደ ነው፡፡

ማን ቀረ ? መንግስት ? … መንግስት ያው በተፈጥሮው በኮምፕሌይን ማሸን complex ውሳኔዋችን አዋጪ በሆነ መንገድ የሚያመርት ተቋም ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ጥያቄው ህገመንግስታዊ መብት መሆኑን ተናግሮ ወቅታዊ አለመሆኑን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ጥያቄው አንገብጋቢ መሆኑን ጠቅሶ ለምላሹ ዘርፈ ብዙ ምርምር እንደሚያከናውን ቆምጫጫ መልስ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ጥያቄው አንድ ቀን እንደሚነሳ እንደሚያውቅ ገልጾ ነገር ግን የበጀት አመቱ ዝርዝር ጉዳዩን address እንደማያደርገው ሊያሰምርበት ይችላል፡፡

መቼ እንደሚያደርገው ባይታወቅም አንዳንዴ ደግሞ እንደ ግሩም አጭር ልቦለድ ነገሩን ባልተጠበቀ መልኩ ሊጨርሰው ይችላል፡፡ ‹ የውሾችን ችግር መፍታት › በማለት ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ ሊያወጣ ይችላል፡፡ የውሾች ችግርን መፍታት…..

. በኮንዶሚንየም ሰፈሮች የሚታየውን ዘረፋ ለመቀነስ
. በሞተው ስፓርት ላይ ቅመም ለመጨመር
. የቀበሮን እብሪት ለማስተንፈስ
. መርሃ ግብሩን ለማሳካት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡



No comments:

Post a Comment