Sunday, April 15, 2012

‎የእኛ የእያሱና የመንግስት ‹‹ ቲፕ ››‎






ቲፕ ይሰጣሉ ? ከሰጡ ውስጥዋ የሚቀር አሳማኝ ምክንያት አለ ? ወይስ ስለዚህ ጉዳይ በአንክሮ አስበው አያውቁም ፡፡ ምናልባት አንዳንድ ምክንያቶቸን ላስታውስዋ….

1 . አስተናጋጆች አነስተኛ ደመወዝ ስለሚከፈላቸው
2 . አስተናጋጆች መልሱን በዕቃ ስለሚያቀርብልዋትና የዕቃው ራቁትነት ስለሚያሳፍርዋት
3 . ለሚያገኙት ሸጋ መስተንገዶ ክብር መግለጫነት
4 . ለትውውቅ ወይም ለጠበሳ
5 . ሌሉች ሰዋች ስለሚያደርጉት
6 . ክፉ አይደለሁም የሚል ማስታወቂያ ለማሰራት
7 . ሃይማኖታዊ መርህን ለማስከበር

በርግጥ ከዚህ የተለየም  ምክንያት ሊኖርዋት ይችላል፡፡ ቲፕ ቅርጽና ይዘቱን ሳናወዳድር ጥንትም እንደነበር አንዳንድ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ የእቴጌ ምንትዋብ ልጅ የሆነው ዳግማዊ እያሱ በስልጣን ዘመኑ ትምህርትን የተመለከተ ቲፕ ነበረው፡፡
ዳግማዊ እያሱ በአንድ ወቅት ‹‹ መማር የሚፈልግ ሁሉ በነጻ ከቤተመንግስት መመገብ ይችላል ›› የሚል አዋጅ አስነገረ ፡፡

ለመሆኑ እያሱ ቲፕ ለመስጠት ምን አሳሰበው?
መመዘኛው ምንድነው?
ቲፑን ለነማን ሰጠው?
እነሆ እያሱ እንደሚከተለው ተናገረ ፤

 ማንም ሰው በትምህርቱ ወደፊት ገፍቶ ከተወሰነ ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ ይበልጥ በተሟላ ገበታ ላይ በክብር ተቀምጦ  መመገብ ይፈቀድለታል !!!

 ተራ ምግብ የሚሰጣቸው ማንበብና መጻፍ ብቻ የሚችሉ ናቸው !!!


በሳይንሳዊ ጥናቱ  ቀጥሎ ወዳለው ደረጃ የተሸጋገረ ሁሉ ከመደበኛው ማዕድ ጋር ጠላ ይሰጠዋል !!!

ነገር ግን በእውቀቱ ከላቀ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው፣ ለምሳሌ ቅኔ ከተቀኝ፣ ከምግብ ጋር ጠጅ ይቀርብለታል !!!

የቅኔን ሳይንስ ጨርሶ ወደ መጻህፍት ጥናት የተሸጋገረ ሁሉ የመጨረሻው ምርጥ ማዕድ ይቀርብለታል !!!

እንደሚታወቀው በቀድሞው  የኢትዬጽያ ባህል መሰረት ጠጅ ለመጠጣት የሚፈቀድላቸው በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍ ካለ የታዋቂነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ብቻ ናቸው፡፡

ባለንበት ዘመንም ጥሩ የሰራ ይሸለማል የሚል መፈክርን የያዙ ቲፕ መሰል ጥናቶች ብዙ ጊዜ ይፋ ሆነዋል፡፡ በጣም ጥቂቶቹ ይጠቀሱ ቢባል እንኳን ወንድማማቾቹን ቢፒአርና ቢኤስሲን እማኝ ማድረግ ይቻላል፡፡
እነሆ መንግስት እንደሚከተለው ተናገረ፤

የውጤት ተኮር ስርዓትን ያለምንም ማበረታቻ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር የሰራተኛውን ተነሳሽነት የሚያዳክምና የተቋሙን አፈጻጸም የሚጎዳ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ከአማካኝ አፈጻጸምና በላይ የሚገኙ ሰራተኞች የተለያዩ መጠን ያለው ማበረታቻ ክፍያ ያገኛሉ፡፡ ቢኤስሲ መ/ቤቶችን ያጥለቀለቀ ቢሆንም ትጉሃን ግን እስካሁን አልተሸለሙም ፡፡

ለመሆኑ መንግስት ቲፕ ይውቃል ?
ካወቀ ቲፕ ይሰጣል ?
ከሰጠ መቼ ይሰጣል ?
እረ ለመሆኑ እንዴት ይሰጣል ?
እኮ ለነማን ይሰጣል ?
ውስጡ ያለው አሳማኝ ምክንያት ምንድነው ?
ልክ ከላይ በዝርዝር እንደገለጽነው ‹‹ እንደ እኛ ›› እያነጻጸራችሁ የምትመልሱ ከሆነ ብዙ ፈገግታ አጫሪ ምላሾች ብቅ ጥልቅ እንደሚሉባችሁ አሰብኩ፡፡

ለምሳሌ በተራ ቁጥር 4 ዓይን ካሰባችሁ ‹‹ ሰዋች እሱን መስለው ሲተዋወቁት ወይም ሲጠብሱት ›› የሚል ምላሽ ታገኛላችሁ፡፡ ከፈለጋችሁ በዚሁ ስሌት ቀጥሉ…….

እረ የቲፕ ያለህ !!!!
እረ የጠላ ያለህ !!!!
እረ የጠጅ ያለህ !!!!
እረ የማዕድ ያለህ !!!!
ለመሆኑ ቲፕ ምንድነው ???????????????????????

No comments:

Post a Comment