Monday, April 16, 2012

‎ መለስ ዜናዊና የህወሃት የትግል ጉዞ‎



‹‹ መለስ ዜናዊና የህወሃት የትግል ጉዞ ›› በኮ/ል ኢያሱ መንገሻ የተጻፈ መጽሀፍ ነው፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም ‹‹ ሰርዶ ›› እና ‹‹ ካብ ማህደር ፈንቅል ›› የተሰኙ ስራዋችን ለንባብ አብቅተዋል፡፡  ለደራሲው ምስጋና ይድረሰውና አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዋችን ላካፍላችሁ፡፡……..
 
የአቶ ዜናዊ ልጆች 
 
 አቶ ዜናዊ በአጠቃላይ 13 ልጆች አሏቸው፡፡ ሰሰን ዜናዊ በአድዋ ከተማ ጠላ ጠምቃ እየሸጠች የምትተዳደር ነች፡፡ ገርግስ ዜናዊ እንግሊዝ አገር የምትገኝ ስትሆን፣ ቢንያም ዜናዊም በተመሳሳይ እንግሊዝ ሀገር ይገኛል፡፡ በመምህርነት ስራ በአድዋ ከተማ የሚገኝው ፍሰሃ ዜናዊ የመለስ ታላቅ ወንድም ሲሆን፣ ጸጋዬ ዜናዊ ደግሞ ራማ በተባለች አነስተኛና አድዋ አጠገብ በምትገኝ ትንሽ ከተማ ቡቁልት እየሸጠ ኑሮውን ይመራል፡፡
 
   ማሚት ዜናዊ ቀደም ብሎ ታጋይ የነበረች ሥትሆን አሁን ባለትዳርና አስተማሪ ሆና ባድዋ ከተማ ትገኛለች፡፡ ካሁሱ ዜናዊ ታጋይና አሁን በሽሬ ከተማ በመንግስት ስራ ላይ ተሰማርታ እየሰራች ያለች ስትሆን፣ ግዛቸው ዜናዊ ደግሞ በስደተኞች ጉዳይ መ/ቤት እየሰራ ይገኛል፡፡ ሀይሌ ዜናዊ በአዲስ አበባ ቤተክህነት ውስጥ፣ ዘውዲ ዜናዊ በት/ሚኒስትር ውስጥ በጸሃፊነት፣ ኒቆዲሞስ ዜናዊ ደግሞ በባንክ ሰራተኝነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
 
መለስ በልጅነት
 በህጻንነት እድሜው ጠብና ድብድብ የመሳሰሉት ባህርይዋች የማይታይበት ሰላማዊና ትእግስተኛ ነበር፡፡ በአብዛኛው በልጅነት ዕድሜው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተለያዩ ጥፋቶችን መፈጸም ያለና የተለመደ ክስተት ቢሆንም፣ መለስ ግን ከፍ ሲል ከተገለጸው  ባህሪው የተነሳ ቤተስብ ልጆቻቸው እንዲፈጽሟቸው የማይፈልጉ ተግባራትን አይፈጽምም ነበር፡፡ ጥሩ ስነምግባርም ነበረው፡፡
 
የአቶ ዜናዊ ምስክርነት
 
መለስ አንድ ቀንም አጥፍቶ አያውቅም ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳም ገስጨው አላውቅም፡፡

ሰይጣን ፍለጋ
 
በአድዋ በሚገኝ አንድ የመዋኛ ኩሬ ሰይጣን ይዋኝበታል የሚል አመለከከት ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መለስና ጓደኞቹ ይመክሩና እውነታውን ለማረጋገጥ አንድ ለሊት ወደቦታው ያመራሉ፡፡ ደፈጣ ይዘው ሰይጣኑን ሲዋኝ እናየዋለን በማለት ጠበቁ፡፡ ጸጥታ ብቻ ሆነ፡፡ጥበቃው ያሰለቸው መለስ ካደፈጠበት ይነሳና ለምን ገብተን አናረጋግጥም ? በማለት ጓደኞቹን ይጠይቃቸዋል፡፡ አዋንታዊ ምላሽ ያገኛል፡፡ ፈጥኖና ቀድሞ ልብሱን በማውለቅ ወደ ቀዝቃዛው ኩሬ ዘሎ በመግባት በጨለማ ውስጥ ዋና ቀጠለ፡፡ ጓደኞቹም ተከተሉት፡፡ ሰይጣን ፍለጋውንም ተያያዙት፡፡ ተፈላጊው ሰይጣን ግን አልተገኝም፡፡

መለስና ትምህርት

በየዓመቱ ከፍተኛ ውጤትን እያስመዘገበ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ከማጠናቀቁ በተጨማሪ በ64 ዓም የ12ኛ ከፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተናን በከፍተኛ ውጤት ማለፍ ችሏል፡፡ በወቅቱ ከተጠቀሰው ት/ቤት ተፈታኝ ከነበሩት ተማሪዋችና በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ማምጣታቸው ተረጋግጦ ለቀዳማዊ ሀይለስላሴ ሽልማት ከበቁ አስር ወጣት ተማሪዋች መካከል አንዱ ነበር፡፡

የዶ/ር ዳንኤል ፈቀደ ምስክርነት
ዶ/ር ዳንኤል የመለስ የት/ቤት ጓደኛና አብሮ ተሸላሚ ከነበሩት ተማሪዋች አንዱ ነበሩ፡፡ አሁን በአ/አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ፋከልቲ መምህር ናቸው፡፡ ‹‹ መለስ ትጉህ ጥንቁቅና ጎበዝ ተማሪ ነበር፡… በትርፍ ሰዓት የቅርጫት ኳስንና የጠረጼዛ ቴኒስ ጨዋታ መጫወትን ይወድ ነበር፡፡መለስ ጥቃትን አይወድም ነበር፡፡ በዕድሜ ሆነ በጉልበት ተለቅ ብለውና በልጠው ይታዩ የነበሩ ተማሪዋች በእሱ ላይ የሚፈጽሙትን ማናቸውም የማስፈራራትና ተጽዕኖ የመፍጠር ሁኔታን አጥብቆ የመቃወምና ያለመቀበል ባህሪና ሁኔታ ይታይበት ነበር፡፡ … ለዩኒቨርስቲው ተማሪዋች ህብረት አመራርነት ተወዳድሮም የሳይንስ ፋኩልቲ ተማሪዋች ህብረትን እንዲወክል ተመርጦም ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር የነበረውን ዕምቅ የአመራር ችሎታ ባህሪያትንና በተስብሳቢ ፊት በመድረክ ላይ አሳማኝ ማራኪ ንግግርን የማድረግ ተሰጥኦውንና ብቃቱን ማሳየት የጀመረው፡፡›› ብለዋል፡፡

ማገብት
 
የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል ከ11 ባልበለጡ ታጋይች የካቲት 11/1967 ዓም ደደቢት በተባለ ቦታ እንደተጀመረ ይፋ ከመደረጉ በፊት ለህዝባዊ ትጥቅ ትግሉ መጀመርና ለህወሃት መመስረት መሰረትና ጥንስስ የነበረ አንድ አደረጃጀት ነበር- እሱም ማህበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ ነበር፡፡
 
የማገብት መስራቾች

ማገብት ዩኒቨርስቲ በነበሩ ተማሪዋች የትግራይ ተወላጆች ተመሰረተ፡፡ መስራቾቹ አግአዚ ገሰሰ፣ ስዩም መስፍን፣ አባይ ጸሀዬ፣ በሪሁ በርሀ/ አረጋዊ/ ፣ አይሉ መንገሻ/ ነጠበ/፣ ግደይ ዘርአጽዮን፣ አስፍሃ ሐጎስ/ ሙሉጌታ/ ነበሩ፡፡ በሂደት ስበሰሃት ነጋ፣ ሙሴ ተህለና ገሰሰው አየለ በምስረታው ተቀላቅለዋል፡፡
 
መለስ ተሕለና መለሰ ዜናዊ
 
መለስ ተሕለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዋች ንቅናቄ ታሪክም ሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትግራይ ተወላጆች ተማሪዋች ማህበር ንቅናቄ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠሩ ታዋቂ ታጋይ ተማሪዋች አንዱ ነበር፡፡ በዋቢሸበሌ ሆቴል ላይ ተፈጸመ በተባለ የቦንብ ፍንዳታ እጁ አለበት በሚል የሐሰት ውንጀላ በመጋቢት 67 ዓም በደርግ መንግስት በግፍ የተገደለ ወጣት ተማሪና ታጋይም ነበር፡፡ ይህን ታጋይ ለመዘከር ለገሰ ስሙን በመታሰቢያነት ምርጫውና መጠሪያው አደረገው፡፡

ደደቢት

የካቲት 11/1967 የትጥቅ ትግል የተጀመረበት ቦታ ነው፡፡ ደደቢት የእጣን ዛፍ ጨምሮ የተለያዩ የበርሃ ዛፎች የተሞላበት በርሃ ነው፡፡ የመሬቱ ገጽታ ሰበርባራ መሬት የበዛበትና ለአይን የሚገባ ትልቅ ተራራ የማይታይበት ቆላ መሬት ነው፡፡ ከየካቲት እስከ ሰኔ ያሉት ወራቶች የእሳትን ያህል የሚፋጅ የሀሩር ንዳድ ከሰማይ የሚዘንብባቸው ጊዚያቶች ናቸው፡፡መንደር የሚባል እምብዛም አይታይበትም፡፡ ዛፎችን እንደ መኖሪያ ጎጆ፣ አለቶችን ደግሞ እንደ መኝታ መደብ አድርገው የሚገለገሉበት ቦታ ነበር፡፡

ተሓህት
ተሓህት የተመሰረተውና ህልውና ያገኝው በሰኔ 1967 ዓም ሕርሚ ላይ በተካሄደው አጠቃላይ ስብሰባ ነው፡፡

የወይን መፈጠር
በስዩም መስፍን የሚመራ ስምንት አባላት የነበሩበት ሃይል ወደ አዲግራት ከተማ በመግባት በከተማው ውስጥ በሚገኝው አግአዚ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ላይ ኦፕሬሽን በማካሄድ የሚፈለጉ ቁሳቁሶችን እንዲያመጣ ተሰማራ፡፡ ግዳጁም የተሳካ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታም ይፈለጉ የነበሩት ቁሳቁሶች ማለትም ወረቀትን ጨምሮ ቀለም፣ ታይፕራይተሮችና ማባዣዋች ተገኙ፡፡ ይህን በመጠቀምም የተሓት የመጀመሪያው ልሳን ወይን ቁ. 1 በጥር 1968 ዓም ተጽፎ ወጣ፡፡/ ይዘቱም ማስተባበያ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ተህሃትና ግንባር ገድሊ ሃርነት ትግራይ ለመዋሃድ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው ግንባሩ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ተግባር በመፈጸሙ በተህሃት ተመቶ ነበር፡፡ እናም ‹‹ ይድረስ ስህተት እየፈጸሙ ላሉ ወገኖቻችን›› በሚል ርዕስ ለትግራይ ህዝብ እውነታውን የማሳወቅ ስራ ነበር/

ሬሽን
 
ሕወሓት ከጨቅላነቱ ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገው የነበረና፣ በዚህ የተነሳም የተወሰኑ አባላቱን ያስለመዳቸው አንድ ነገር ነበር፡፡ እሱም የሲጋራ ሬሽን ነበር፡፡ ሲጃራ ለሚያጨሱና ሱስ ለነበራቸው አባላቱ በድርጅቱ አሰራር መሰረት በየቀኑ አምስት ፍሬ ሲጃራ በሬሽን መልክ ይታደላቸው ነበር፡፡ 5   ‹‹ ግስላ ›› እየተባለ ይታወቅ የነበረ ሲጃራ በዚያን ሰዓት ለድርጅቱ የሲጃራ ሬሽን ዕደላና ለአጫሾቹ ብቸኛ አማራጭ ነበር፡፡ በወቅቱም ምርት ሲጃራው ተወዳጅም ነበር፡፡

የአህዴን አመሰራረት
 
በህወሃትና በኢህዴን መካከል ተከራረዋ በተባለ ቦታ 142 ቀናትን ያስቆጠረ ውይይት ተካሂዷል፡፡ … በተካሄደው አብይ ስብሰባ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ለመመስረትና ትግሉን ለመቀጠል የወሰኑ 51 አባላት የተሳተፉበት ነበር፡፡መጀመሪያ አብረዋቸው የመጡ 64 የሚሆኑት የተቃውሞ ንቅናቄ አባላት የነበሩት ግን ትግል መቀጠል አይቻልም በማለት ቀደም ብለው ራሳቸውን በማግለላቸው እንዲሸኙ ተደርገዋል፡፡… ኢህዴን እንደተመሰረተ ይፋ የተደረገበት ጉባኤ የተጠናቀቀው ታምራት ላይኔ፣ አዲሱ ለገሰ፣ ጌታቸው ጀቤሳ፣ ተፈራ ዋልዋ፣ በረከት ስምኦን፣ ሃይሌ ጥላሁን፣. ታደሰ ካሳ፣ ህላዌ ዮሴፍ እና ዘለቀን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አድርጎ በመምረጥ ነበር፡፡ ሚያዚያ 11/1973 ዓም ኢህዴን ረጅሙን የትጥቅ ትግል መጀመሩን በይፋ አወጀ፡፡

ዝነኛው ሳህል
እግዜር አለምን ሲፈጥር ተናዶ በክርን እየደቆሰ የተማታበት መሬት ይመስላል፡፡ ንዴቱ ከመሬቱ ገጽታ ላይ ተጽፏል፡፡ ተደራርበው የተቀመጡ ያገጠጡት ድንጋዮች ተፈጥሮ በዘመናት የቆለላቸው አይመስሉም፡፡ አንድ ሃይል ለምጽአት ቀን በጥበብ ጠርቦ ያስቀመጣቸው የመቃብር ድንጋዮች እንጂ፡፡ ተራሮቹ መረማመጃ ቀርቶ ለእግር መቆናጠጫ የሚሆን ቦታ የላቸውም፡፡ ለሰው ቀርቶ ለዝንጀሮዋችም ቢሆን አይመቹም፡፡ አንዳንዶቹ ተራሮች እስከ ትከሻቸው ድረስ ጉም ለብሰው ሲታዩ ዓለምን በመናቅ የአመጽ ጋቢ ተከናንቦ በእብሪት ተወጥሮ የቆመን ወንበዴን ይመስላሉ፡፡/ ጸሀፊው የበዓሉ ግርማን አባባል ሲጠቀም/

No comments:

Post a Comment