Wednesday, July 26, 2017

የጣና ነጋሪት መቼ ይጎሰማል ?


የህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 የውጭ ወረራ ሲያጋጥም  ፣ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት ፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የክልል መስተዳድሮች የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሊያውጁ እንደሚችሉ ይደነግጋል ።

ከላይ በተገለጸው አንቀጽ ውስጥ አራት መሰረታዊ ሀረጎች ጎልተው ይታያሉ ። የውጭ ወረራ ፣ የስርአት አደጋ ፣ የተፈጥሮ አደጋ እና የጤንነት አደጋ ።

መንግስት እስካሁን የተመቸው ሀረግ የ ‹ ስርአት አደጋ › ነው ። በዚህ ለመጣበት አይደራደርም ። በዚህ የመጣበትን በብዙ ጆሮዎች የመስማትና በብዙ አይኖች የመመልከት ችሎታ አለው ። ይህን አደጋ በወንበር የመማለል አደጋ ይለዋል ። እረ ጥሩ ጥሩ ዘይቤያዊ አነጋገሮችንም ይጠቀማል ። መንግስት እንደ ኢያሪኮ ግንብ በጩኅት አይፈርስም የሚላት ነገር አንደኛዋ ናት ... መንግስት እንደ ሾላ ፍሬ በድንጋይ አይወርድምም ይልሃል ... ሌላም ሌላ ጥብቅ ማሳሰቢያዎች አሉት ። የስርዓቱን አደጋ ለማነቃነቅና ለመጣል የተሞከረን ሀገራዊ ‹ ብጥብጥና ሁከት › ጸጥ ለማድረግ ይቻል ዘንድ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከታወጀ አያሌ ወራት ተቆጥረዋል ። ይህም የጥብቅ ማሳሰቢያው የመጨረሻ ደረጃ ነው ። ከዛሬ ነገ አዋጁ ይነሳል ሲባል የሰርዓቱ አደጋዎች ቅርጽ እና ይዘታቸውን እየቀየየሩ መፈልፈላቸው አሳሳቢ ነው ። አንዱ በአንዱ ቀለበት ውስጥ እየገባ ዛሬ የግብር አደጋ ተረኛ ጥያቄ ፈጣሪ ሆኗል ። እናም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ታፍሮና ተፈርቶ ለማይታወቅ ዘመናት ሊውለበለብ ይችላል ።

የአዋጅ ነገር ከተነሳ በተፈጥሮ አደጋም ተጨማሪ ክተት ያስፈልገን ነበር ። መንግስት የሚመቸውን ብቻ አዳማጭ ስለሆነ እንጂ የጣና በእምቦጭ አረም የመወረር አደጋ ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት የሚታዘዝበት ነበር ።

የመንግስትን ዳተኝነት የገነቡት ብዙ ምከንያቶች ሊሆኑ ቢችሉም ሁለቱን የጎሉ አስተሳሰቦች እንመልከት ። አንደኛው ችግሩን መፍታት ያለበት የክልሉ መንግስት ሲሆን ጉዳዩም ከክልሉ አቅም በላይ የሚዘል አይደለም የሚል ነው ። የክልሉ መንግስት ለበርካታ አመታት ሳይንሳዊ ውጤት ለማምጣት ባዝኗል ። ችግሩን መፍታት ቢኖርበት ይህን ሁሉ አመታት ያለ ተጨባጭ ነገር መራወጥ ባልተገባው ነበር ። እውነታው ግን የምርምርም ሆነ የገንዘብ አቅሙ ተፈላጊውን መፍትሄ ያስገኘለት አለመሆኑ ነው ።

ሁለተኛው መንግስታዊ አመለካከት የጣና ሃይቅ በአረም መወረር በውጭ ወራሪ መወረር አይደለም ወይም የተፈጥሮ አደጋ ነው ብሎ ለመቀበል የሚያስችል መደላድል የለም ከሚል ይመነጫል ። ሲጀመር ህገ መንግስቱ የተፈጥሮ አደጋ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አላሰፈረም ። ሌላው ቀሮቶ ‹ የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት › የሚለው ሀረግ አሻሚና ግልጽነት የሌለው ነው ። በሽታ የሚለው ተላላፊዎችን ነው ... በሽታ የሚለው ግዜ የማይሰጡትን ነው ... በሽታው ኮሌራ ነው ? ኢቦላ ነው ? ማጅራት ገትር ነው ? ... አይታወቅም

በመሆኑም የ « ተፈጥሮ አደጋዋችም » ሆኑ « ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ በሽታዋች» ን እውነተኛ ብይን መረዳት ያስፈልጋል ። የተፈጥሮ አደጋዋች ሰፊ ናቸው ። በአጭሩ ግን ስነ ምድራዊ ፣ ሰነ ውሃዊ ፣ ስነ አየራዊ ፣ ሰደድ እሳት እና የህዋ ጥፋት ብሎ ማሰቀመጥ ይቻላል ። ለአብነት መሬት መንቀጥቀጥን፣ የበረዶ ናዳ እና እሳተ ጎመራን ስነ ምድራዊ ውስጥ እናገኛቸዋለን ። ድርቅና የተለያዩ የአውሎ ንፋስ አደጋዋችን ሰነ አየራዊ ውስጥ ይመደባሉ ። በዚህ ሳይንሳዊ አካሄድ መሰረት የጣና ሃይቅ ችግር ስነ ውሃዊ / Hydrological Disasters / ውስጥ የሚገኝ ይሆናል ።

ሳይንቲስቶች ስነ ውሃዊ አደጋን A Violent , Sudden and destructive change either in the quality of earth’s Water or in the distribution or movement of water on land below the surface or in the atmosphere በማለት ይበይኑታል ።

ህገ መንግስቱ ዝርዝር መግለጫ ስለሌለው ከዚህ በመነሳት ሀሳብ መስጠት ግድ ይላል ። በመሆኑም በጣና ሃይቅ የደረሰው አደጋ የውሃውን መጠን ፣ ጥራትና ፍሰት የሚጎዳ ነው ። በውሃውና በአካባቢው የሚገኙ ስነህይወታዊ ስርአትን ያፋልሳል ። ከሃይቁ ቀጥተኛ የህልውና ትርጉምን እውን በሚያደርገው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ይፈጥራል ።

ከዚህ ሁሉ በላይ ጣና የኢትዮጽያ ታላቅ ቅርስ ነው - በባህላዊ ፣ ታሪካዊ ፣ ሰነውበታዊ እና ስነ ምድራዊ ሃብቶች የበለጸገ ። በእኛም ብቻ ሳይሆን በዩኔስኮ ዳኝነት የተመሰከረለት ። እንግዲህ ይህ የሀገርና የአለም ሀብት ነው አደጋ ውስጥ ስለሆነ ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ያስፈልገዋል እየተባለ የሚገኘው ።

በቅርቡም ባለሙያዋች እንደገለጹት ሃይቁን ተረባርቦ ማከም ካልተቻለ በአደገኛው አረም ሊጠፋ ይችላል ። ከዚህ የላቀ ምስክርነት ታዲያ ከየት ሊመጣ ይችላል? ይህን አደጋ የተፈጥሮ አደጋ አይደለም ማለት ፣ ይህ አደጋ በህዝብ ሃብትና ማንነት ላይ የተጋረጠ ቀውስ አይደለም ማለት ራስን ከማታለል የሚቆጠር ነው ። እናም አደጋውን ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት መንግስት የዋና ገጸባህሪ ብቻ ሳይሆን የአዘጋጅነቱንም ሚና መጫወት ይኖርበታል ። መንግስት ልግመኛ ካልሆነ በስተቀር ‹ ኩራትም እራትም › ነው የሚለውን በርካታ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በቦታው ቢያሰማራ የማይናቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ። በነገራችን ላይ መከላከያ ሰራዊት ህዝባዊነቱን እያሳየ ነው  ተብሎ ብዙ ግዜ አረም ሲነቅልና እህል ሲያጭድ በቲቪ ተመልክተናል እኮ ? ታዲያ ምነው እንቦጭን ለመንቀል አልከሰት አለ ?

መንግስት ጣና የሀገር ጉዳይ ነው ብሎ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ከሰራ ሀገራዊ መፍትሄ የሚጠፋ አይመስለኝም ። ከአቅም በላይ ከሆነም ወደ ውጭ ለማየት አሁንም የመንግስት አይን ጥቅም አለው ።  ቢያንስ A+ ባለው የእርዳታ ክህሎቱ ‹ ጎበዝ ተባበሩኝ ›  ቢል አውሮፓዋቹ የሚጨክኑ አይመስለኝም - ሌላው ቢቀር ቻይናዊ መፍትሄ አይጠፋም ። ለስርአት አደጋ ብቻ ሳይሆን ቀስ እያለ በተፈጥሮ ሊደርስ የሚችል ጥፋትን ለመከላከል ሳይቃጠል በቅጠል የተሰኘ ፖሊሲ መከተል ብልህነት ነው ።

ጣና የሁላችንም ጉዳይ ነው !

ቢረፍድ እንኳን ለጣና ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ያስፈልጋል !

No comments:

Post a Comment