ፊንፊኔ ስላሽ አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ
ፊንፊኔ እና አዲስ አበባ
አዲ ሃይፈን ፊን
ፊን ነጥብ አዲ
አ ወይም ፊ
የቱ ነው እየመጣ ያለው የከተማችን መጠሪያ ? የቱ ነው እውነቱ ? የሚያስከትለው
ውጤትስ ? ታዋቂው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ራልፍ ኤድዋርድ Truth
and Consequences እንዲል ። ይህን Truth and Consequences የተባለውን የNBC ቴሌቪዥን ፕሮግራም የመመልከት እድል ያጋጠመው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ይገነዘባል ። እውነትን
ማወቅ ስጋት ማራገፊያ መሆኑንና እውነታን መሳት ካልታሰበ ችግር ጋ የሚያላትም መሆኑን ።
የፕሮግራሙ
ፈጣሪ ራልፍ ኤድዋርድ
ከተመልካች ውስጥ የተወሰኑትን መድረክ ላይ በማቅረብ ነው ጥያቄውን
የሚያቀርበው ። የጥያቄውን ምላሽ ያገኘ ነጻ ይወጣል ። እውነታውን የሳተ ግን በቀጣይ የሚቀርብለትን አስደናቂ ወይም አስቸጋሪ ወይም አሳፋሪ ትርዒት የማቅረብ ግዴታ አለበት ። ትርዒቱ ከአቅሙ በላይ ሊሆንይችላል ፣ ቢሆንም ከድርጊቱ
ጋር መጋፈጥ አለበት ። ለምሳሌ ያህል አንድ ወቅት ያየሁት ተጠያቂው ባለ አንድ ጎማ ብስክሊት እንዲያሽከረክር ታዞ ነበር ። ሰውየውን
እንደምንም ብለው የሳይክሉ ረጅም ወንበር ላይ ሰቀሉት ። ታዲያ ምን ያደርጋል ላይ ተንጠልጥሎ ራሱን ባላንስ ማድረግ አልቻለም ።
እናም ፔዳሉን ወደፊትና ወደኋላ ከማባበል ይልቅ በሃይልና በድንጋጤ ሲንጠው ቀጥታ ወደ ተመልካቹ ተፈተለከ - ህዝቡ መሃል እንደ
ቲማቲም ፈርጦ ክፉ የሽብር ተግባር ይፈጽማል ብዬ ስጠብቅ አምላክ ረድቶት አንድ ጥግ ምናምን ይዞ ዳነ ። በሰውየው ድንጋጤና ያልተገራ ጥበብ ብዙ ሰአት እንደሳቅኩ አስታውሳለሁ ።
የዚህ ፕሮግራም አዘጋጅ ከመድረክ ኩምኩና በተጨማሪም ለአለማችን አስቂኝ የከተማ ስም
በመፍጠርም ይታወቃል ። ነገሩ እንዲህ ነው ። በ1940 የተጀመረውን
Truth and Consequences አስረኛ አመት ለማክበር በአዘጋጁ በኩል አንድ ጥሪ ይተላለፋል ። የከተማውን ስያሜ በፕሮግራሙ
መጠሪያ ለሚቀይር ዝግጅቱ በቀጥታ ከከተማው እንዲተላለፍ ይደረጋል የሚል ። ይሄኔ የ < Hot Spring > ነዋሪዎች ፍቃደኝነታቸውን ይገልጻሉ ።
ከተማዋ የበርካታ የተፈጥሮ ሙቅ ውሃ ባለቤት ናት ። እናም በመጋቢት 1 ቀን 1950 ዓም ህዝበ ውሳኔ ያከናውናሉ ። 295 ሰዎች ይህን እብደት አንደማይቀበሉ ሲገልጹ 1294 ያህሉ ግን ስማችን እንዲቀየር እንፈልጋለን አሉ ። በቀጣዩ ቀን ማለትም
ሚያዚያ 1 ፣ 1950 ፕሮግራሙ ከከተማዋ ተላለፈ - የከተማዋ አዲሱ
መጠሪያም Truth or Consequences ሆነ ።
ይህ ስም በአለማችን ካሉት ረጅም እና ቀፋፊ ስሞች መካከል እንደ አንደኛው ሊቆጠር
የሚችል ነው ። የTruth or Consequences ከተማ ነዋሪዎች ይህ ቀፋፊ ስም እንዴት ከእናንተ ተግባር ጋር ይገናኛል ሲባሉ የሚከተለውን
ሽፍንፍን ያለ ምላሽ ይሰጣሉ « እውነታው / Truth / በከተማችን ጤና ሰጪ ፍልውሃዎች ያለን መሆኑ ነው ፣ ይህ ያስከተለው ውጤት/
Consequences / ከተባለ ደግሞ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ነው
» የሚል ። ነዋሪዎቹ ዛሬ ዛሬ በረጅሙ ስያሜ በመዳከማቸው
ቲ ኦር ሲ ወደሚል ምህፃረ ቃል ወርደዋል ።
ምናልባትም ሁለተኛው ረጅም እና ቀፋፊ ስም የአዲስ አበባው ፊንፊኔ ጥምረት ሊሆን
ይችላል ። በህግ ፊት እኩል የመቆም መብት የተሰጣቸው አዲስ አበባና ፊንፊኔ በሚያስከትለው ውጤት / Consequences
/ ብዙ
ሊፋተጉ ይችላሉ ተብሎ የተሰላ ይመስላል ። አዲስ አበባ ይቅደም ፊንፊኔ ? አቀማመጡ እና ጥምረቱስ ? በወይም ይቆለፍ ወይስ በ እና ሰረገላ ? በስላሽ ድንበር ያብጁ ወይስ የዶት ታኮ ይሰራላቸው ?
ምፀታዊ ዋጋው የአዲስ አበባ ህዝብ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣው በዚሁ ጉዳይ ሀሳብህ
ምንድነው ተብሎ አለመጠየቁ ነው ። ስሙን በማስረዘሙ ልዩ ጥቅም ያገኛል ? የውሃ ፣ መብራት ፣ ስልክ ፣ ስራ እና የዋጋ ንረት
ሰቆቃው በፊንፊኔ ስላሽ አዲስ አበባ ገመድ ይጠፈነጋል ? ከአንድ ወደ ሁለት ቃላት ያደረገውን ድንገተኛ ሽግግር ተመችቶት ይቀበለዋል
፣ ህጋዊና ስነልቦናዊ ግዴታስ አለበት ? ነው መንግስት ካለ አለ ነው- ተከተል አለቃህን አክብር አርማህን እንዲሉ ። ከቅርብ ግዜያት
የፖለቲካ ተሞክሯችን ስንነሳ ግን በንግግርና መግባባት ላይ ያልተመሰረተ ውሳኔ ያልታሰበ ውጤት ለማስከተል ምንም የሚያግደው ነገር
የለም ። በመሆኑም የኦሮሞ ተወላጆች ፊንፊኔ ሲሉ የተቀሩት ደግሞ
በአዲስ አበባ እንዲፀኑ መንገድ ይከፍታል ። በአንድ ከተማ ሶስት
ስያሜ መሆኑ ነው ።
ይህም ወደ ሌላ አላስፈላጊ ውጤት ይመራል ። ወደ ይዞታ ጉዳይ ። ከተማዋ ለእኛ ነው
የምትገባው ወደሚለው የኦሮሞ - አማራ ጭቅጭቅ ። በርግጥ ማነው ቀደምቱ
? ከአዲስ አበባ በፊት ፊንፊኔ ነበር ... ስለዚህ ከተማዋ የኛ ናት ፣ እናንተ እንግዶቹ በኛ ስር ልታድሩ ግድ ነው ይልሃል አንደኛው
ጠርዝ ... ከፊንፊኔ በፊትስ እነማን በምን ስም ነበሩ ?... ኦሮሞዎቹስ ከየትና እንዴት መጥተው በሀገሪቱ ተስፋፉ ይልሃል ሌላኛው
ጠርዝ ። ጭቅጭቁና እንካሰላንቲያው በተዋረድ በሰፈርና አደባባይ ስሞች ግዘፍ ነስቶ
ይመጣል ። ለመንገድ ስያሜ ከተሜው ግድ ላይኖረው ይችላል ። ግድ የሚሰጠው ግን እንደ ማተቡ ውስጡ የቆየውን የሰፈር ስያሜ ቀይር
አትቀይር የሚል ሙግት ከተከተለ ነው ። መንግስት በቀጭን ትዕዛዝ አስራለሁ ቢል እንኳን ጥቁር ገበያው አይሎ ኢ- መደበኛው ኮሙኑኬሽን
እንደሚልቅ አያጠራጠም ።
የአዲስ
አበባን ደም መርምሮ ሁነኛ ብይን ማግኘት አይቻልም ። የደም ምርመራው ኦ ኔጌቲቭ ፣ ኦ ፖዘቲቭ ፣ ኤ ኔጌቲቭ ፣ ኤ ፖዘቲቭ
፣ ቢ ኔጌቲቭ ፣ ቢ ፖዘቲቭ ፣ ኤቢ ኔጌቲቭ እና ኤቢ ፖዘቲቭ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አዲስ አበባ
ከኦሮሞም ከአማራም በላይ መሆኗ ነው ። ከተማዋ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ሃብት ናት ። የኢትዮጽያዊነት አሻራ ወይም ቅጂ ናት ።
የአፍሪካዊነት መሰረት የዝማሬያቸውም ሰንደቅ ናት ።
ከመቶ አመታት በላይ የዘመናዊ አስተዳደር ጽንሰ ሃሳብን ስትገነባ የመጣችን ከተማ በምን ተአምር የብሄር ካፖርት
ማልበስ ይቻላል ? የዘመናዊነት ትርፉ እኮ ትላልቅ ፎቆችንና ዘመናዊ ባቡሮችን ማስገኘት ብቻ አይደለም ። ዘመናዊነት ከሁሉም በላይ
አስተሳሰባዊ ዝመናን ይመለከታል ። የከተማው ህዝብ ኑሮ አጉብጦት ይሆናል እንጂ በአስተሳሰቡ ሸንቃጣ ነው ። ብዙ ትርፍና ተቀማጭም
ሀብት አለው - የገንዝብ ሳይሆን የማመዛዘን ፣ የመቻቻልና የፈሪሃ
እግዚአብሄርነት ። በዚህ መሰል ችግር ወቅት እየመነዘረ የሚያካፍለው ። የማይናድ ልዩ ጥቅም አለው ከተባለ ይኸው ነው ።
ግራም ነፈስ ቀኝ የአዲስ
አበባን እውነታ አብጠርጥሮ ማወቅ ካልተቻለ የሚያስከትለው ውጤት ከባድ ሊሆን ይችላል ።
No comments:
Post a Comment