Thursday, May 29, 2014

ማቋረጥ

                                      

                   . ልቦለድ ቢጤ

መምህር ተሻለ አዲስ አበባ ውስጥ አለ በሚባለው ትምህርት ቤት ውስጥ የአማርኛ መምህር ነው ። ለሁለት ሰዓታት የነበረውን እረፍት ከጓደኞቹ ጋር ቼዝ ሲጫወት ቆይቶ ፔሬዱ ሲደርስ ወደሚያስተምርበት ክፍል እየተጣደፈ ሲጓዝ ነበር ድንገት ከኌላው በዳይሬክተሩ አቶ ዘሩ የተጠራው
<< የት ክፍል እየገባህ ነው ? >>
<< ስድስተኛ ቢ ነኝ - ምነው ፈለጉኝ እንዴ ? >>
<< እንግዶቹ ቤተመጻህፍቱንና ላቦራቶሪ ክፍሉን ጎብኝተው ጨርሰዋል >>
<< እንዴ እስካሁን ከዚህ ግቢ አልወጡም ? >> አለ ተሻለ በግርምት
<< አዎ አኔ ቢሮ ብዙ ስለቆዩ ነው ። ሪፖርቴን ጣፋጭ በሆነ መልኩ አቅርቤያለሁ ። ምቀኞች ደካማ ነው እያሉ የሚያሰወሩትን የትምህርት ጥራት መገምገም ስለፈለጉ ተግባራዊውን ነገርም ማየት ፈልገዋል ። ዛሬ ርዕሰ ጉዳይህ ምንድነው ? >> ዳይሬክተሩ እየተጣደፉ ነው የሚያወሩት ።
<< ቃላት ፣ የቃላት እርባታና የቃላት አረዳድ የሚል ነው ። በተጨማሪም ... >>
<< ኡ ? ... ምነው ተሻለ ? ምንድነው ዲሪቶ አደረከው እኮ ? >>
<< ተማሪዎች አንድን ተመሳሳይ ቃል እንዴት እንደሚተረጉሙትና በምሳሌም እንዴት እንደሚያስደግፉት የሚታይበት በመሆኑ የአረዳድ ማዕዘናቸውን የሚያሰፉበት ነው >>
<< ጥሩ ... ጥሩ ... ዘዴው ምንድነው ? ማለቴ የምታስተምርበት ? >> አሉ ግራና ቀኝ እየተገላመጡ
<< ተማሪዎች ቃሉን ከሶስት ቀናት በፊት ስለወሰዱ ያዩበትን መንገድ ሰምተን ወደ አጠቃላዩ ትምህርት ነው የምንደረደረው >>
<< አደራ እንግዲህ ? ... >> ዳይሬክተሩ ሀሳባቸውን ሳይቋጩ እንግዶቹን ወዳዩበት አቅጣጫ በሩጫ ተፈተለኩ ።
ሃላፊ ሆኖ የመርበትበትና ሃላፊ ሆኖ የመኮፈስ መንታ ገጽታዎች ሽንት ቤት ገብቶ አሜባን ማማጥና ከግልግል በኌላ ፈገግ ብሎ ቀበቶን ከማሰር ጋር እንዴት እንደተመሳሰለበት አላወቀም - ግን ያለቦታው ይህን ምሳሌ ነበር ሲያነጻጽር የነበረው ። ወደመሬት ወድቄ እምቦጭ እላለሁ የሚል የሚመስለውን ቦርጭ በአንድ እጅ ፣ ወዲህና ወዲያ የሚወራጨውን ካራቫት በሌላ እጃቸው ይዘው በዚህን ያህል ፍጥነት መሮጣቸውም በአስገራሚ መልኩ ፈገግታ ጭሮበታል ።
ለመምህር ተሻለ የማስተማር ስልት መሰረት የሆነው ቢቢሲ የተባለው መገናኛ ብዙሃን ነው ። ይህ ጣቢያ በቀጣዩ ሳምንታት የሚያቀርባቸውን አንኳር ጉዳዮች አስቀድሞ ነው የሚያስተዋውቀው ። ተማሪዎችም ቀጣዩን ምዕራፍ አስቀድመው ካወቁ መደናገርን አስወግደው ተሳታፊና እንደ ካራ ስል ይሆናሉ የሚል እምነት አለው ። ይህ ስልት ከፍተኛ ባለስልጣን ፣ ሀብታሞችና ታዋቂ ሰዎች ልጆቻቸውን በሚያስተምሩበት በዚህ ትምህርት ቤት በሁሉም መምህራን እንደ ቋሚ አሰራር ተግባራዊ እንዲሆን በተለያዩ ግዜያት በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ እስከመናገር ደርሷል ። የማስተማሪያ መንገድንና የፈተና አወጣጥ ዘዴን ደብቅ እያደረግን የትምህርት ጥራትን ከፍ ለማድረግ መሞከር ከንቱ ምኞት ነው የሚል ሀሳብም አለው ።
የስድስተኛ ቢ በር ድንገት ተበርግዶ በርካታ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተግተልትለው ወደ ውስጥ ሲገቡ ተማሪዎቹ እንግዶቹን ቆመው ተቀበሏቸው ። እንግዶቹ ክፍት በተደረገው አንደኛው ጠርዝ ከተቀመጡ በኌላ መምህር ተሻለ ሞቅ ያለ ሰላምታ አቅርቦ ማስተማሩን ቀጠለ ።
<< እሺ ተማሪዎች ሁላችሁም እንደምታውቁት የዛሬው ክፍለ ግዜ የቃላት አረዳድ ላይ የተመሰረተ ነው ። እስኪ ዋነኛ ቃሉን የሚያስታውሰኝ ማነው ? >>
<< አቋረጠ >> አለ በላይ የተባለው የክፍሉ አለቃ ተሽቀዳድሞ ፤ እንደስሙ ሁሌም የበላይ መሆን አለብኝ ብሎ ስለሚያስብ ለብዙ ነገሮች ደንታ የለውም ።
<< ልክ ነው አቋረጠ ሲረባ ማቋረጥ ፣ ያቋርጣል ፣ አቋራጭ ፣ ያቆራርጣል ወዘተ እያለ ይቀጥላል ። ለመሆኑ አቋረጠ ምንድነው ? እንዴት ተረዳችሁት የሚል ነበር የቤት ስራው ? >>
<< እሺ መስፍን >> አለ መምህር ተሻለ እጅ ካወጡት ውስጥ ለአንደኛው እድል እየሰጠ
<< አቋረጠ ማለት የቀለበት መንገድ አጥርን ዘለለ ማለት ነው ። ሰዎች ብረቱን የሚያቋርጡት በቅርበት መሸጋገሪያ ድልድይ ስለማይሰራላቸው ነው ። ሆኖም ብዙ ሰዎች ቶሎ እንደርሳለን ብለው ሲዘሉ በመኪና አደጋ እስከመቼውም ሳይደርሱ ቀርተዋል ። የመኪና አደጋ አሰከፊ ነው >> አለ ተማሪው የሀዘን ገጽታ እያሳየ ።
<< የማን ልጅ ነህ መስፍን ? >> አሉ አንደኛው ሚኒስትር በፈገግታ
<< የኢንጂነር ፈቃዱ >> ባለስልጣናቱ በአግርሞት ሳቅ አውካኩ
<< በመንፈስ ደግሞ የሳጅን አሰፋ ... >> አሉ ጥግ ላይ የተቀመጡት የፖሊስ ኮሚሽነሩ ፤ ቤቱ እንደገና በሳቅ ተንጫጫ ።
<< እሺ አያሌው ? >> ሳቁ እየሰከነ ሲመጣ መምህር ተሻለ ሁለተኛውን ተጠያቂ ጋበዘ
<< ማቋረጥ ማለት የቀበሮ ማቋረጥ ነው ። ሰዎች ለውጊያ ሲሄዱ ቀበሮ መንገዱን ካቋረጠቻቸው ይሸነፋሉ ። አጼ ቴዎድሮስም ሆኑ አጼ ሚኒሊክ በዚህ እንደሚያምኑ አያቴ አጫውተውኛል >> አለና ቁጭ አለ ። መምህር ተሻለ ፊት ላይ መደናገጥ ቢታይም ባለስልጣናቱ ከመሳቅ የገደባቸው ነገር አልነበረም ።
<< አያሌው አያትህ ማናቸው ? >> አሉ አሁንም አንደኛው ሚኒስትር እንደዘበት
<< ቀኛዝማች ነቅአጥበብ ....  >>
ወደ መሃል ቁጭ ያለ አንድ ባለስልጣን የተማሪውን ሀሳብ አቋርጦ << እነ ፊታውራሪና ቀኛዝማች አሁንም ሄደው ሄደው አላለቁም እንዴ ? >> ከማለቱ ቤቱ በእንባ ቀረሽ ሳቅ ተበጠበጠ ። መምህር ተሻለ የውሸት ፈገግታ እየታየበት ቀጣዩን ተማሪ ጋበዘ
<< ማቋረጥ ማለት የማራቶን ሩጫን ማቆም ማለት ነው ። ሩጫውን የሚያቆሙት ወንዶች ናቸው ። ወንዶች ሩጫውን የሚያቋርጡት በሴት ሰዓት ላለመግባት ነው ። የአባቴ ስም አሰልጣኝ ቶሎሳ ይባላል >>
የስድስተኛ ቢ ክፍል ኮርኒስ በሳቅ ወላፈን የእሳት ጢስ የፈጠረ መሰለ ። ሳቁን ያባባሰው ተማሪው አይቀርልኝም ብሎ ከወዲሁ  የአባቱን ስም ማስተዋወቁ ነበር ።
<< ማነህ ስምህ ? >> አሉ አንደኛው ሚኒስትር ወደተናጋሪው ተማሪ እየተመለከቱ
<< ዘላለም >>
<< ዘላለም  እኔ እንኳን የአባትህ ስም ቱርቦ ቱሞ ይሆናል ብዬ ጠብቄ ነበር >> አሉ ቀድመው እየሳቁ
<< እንዴ አያውቁም እንዴ ? እሱ እኮ ሞቷል - በጣም ጎበዝ አትሌት ነበር ። የሞተውም ተማሪ መስፍን እንዳለው በመኪና አደጋ ነው ። በመኪና አደጋ ላይ ብዙ መሰራት አለበት >> አለ ተማሪው ፈርጠም ብሎ
<< በእውነት የተማሪዎችህ የአመላለስ ስርዓት ጥሩ ነው ። በተለይ ጥሩ ነው ያልኩት በጣም ግልጽ ከመሆናቸው አንጻር ነው ። ይህ ባህሪ ነው እያደገ መውጣት ያለበት ። አንድን ጉዳይ የሚያዩበት መንገድም እንደሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች የሰፋና የሚያምር ነው ። የመሰላቸውን የመናገር ነጻነትም እንዳላቸው መረዳት ይቻላል ... >> አሉ አንደኛው ሚኒስትር ስሜታቸውን መቆጣጠር እያቃታቸው ።
ተማሪዎች እንደ ማዕበል በሚንጠው የሳቅ ጎርፍ ሳይናጡ እጃቸውን ለተሳትፎ በጉጉት ከማውጣት አልተቆጠቡም ። በምስጋናው የተነቃቃው መምህር ተሻለ ለመጀመሪያ ግዜ የሴት እጅ በማየቱ ተሳትፎውን ለማሰባጠር የመናገር እድሉን ትእግስት ለተባለች ተማሪ ሰጣት
<< አቋረጠ ማለት ንግግር አቋረጠ ማለት ነው ። ንግግር የሚያቋርጠው ደግሞ አበበ ገላው የተባለ ሰው ነው ። አበበ ገላው የጠላውንም ሆነ የወደደውን ሰው ንግግር ያቋርጣል ። አበበ ያቋረጠው ሰው የሀገር ውስጥ ስሪት ከሆነ ሰውየው ይሞታል ። ለምሳሌ ያህል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ። አበበ ያቋረጠው ሰው የውጭ ሀገር ስሪት ከሆነ ሰውየው አይሞትም ። ለምሳሌ ያህል ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ >>
በሳቅ ሲታመስ የነበረው ክፍል በሚያስደነግጥ ጸጥታ ተወጣጠረ ። የባለስልጣናቱ ግንባር እንደ በረሃ መሬት እየተሰነጣጠቀ አስፈሪ የቦይ ምስል ሲፈጥር በግልጽ ይታያል  ። በግልባጭ በመምህር ተሻለና ዳይሬክተሩ ጆሮ ግንድ ስር መነሻውን አናት ያደረገ የላብ ጎርፍ ወደታችኛው የሰውነት ክፍሎች ደለል እየጠራረገ በፍጥነት ያሽቆለቁል ነበር ።
<< ምን እየተካሄደ ነው አቶ ዘሩ ?! ትምህርታዊ ኩዴታ እያደረጋችሁ ነው ! >> ተቀዳሚው ሚኒስትር ከወንበራቸው ተነስተው  ጸጥታውን በረጋገዱት
<< በእውነት አይን ያወጣና የተቀነባበረ የሽብር ተግባር ይመስላል ! >> ቃለ አቀባዩ እንደ ነብር ገሰሉ
<< በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ ። ምሳሌዎቹ በዚህ መልኩ ይቀርባሉ ብዬ አልጠበኩም ። የትምህርት ማቋረጥ ፣ የጽንስ ማቋረጥ ፣ የመንገድ መቋረጥ ፣ የወንዝ ማቋረጥ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ አጉልቶ በማውጣት ... >>
<< ዝም በል አንተ ! ራስህ አቋርጥ ! ... ንግግርህን አቋርጥ ! ... >> የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሌባ ጣታቸውን ቀስረው እየተንቀጠቀጡ የመምህር ተሻለን ቀልብ ገፈፉት ። ተክዘው የቆዩት አንደኛው ሚኒስትር ጣልቃ ገብተው <<  ያሳዝናል ! በተለይ ከዚህ ትምህርት ቤት ይህን የመሰለ ተራ አሉባልታ መስማት ያሳፍራል ... ትዕግስት ለመሆኑ የማን ልጅ ነሽ ? >> ሲሉ ለስለስ ባለ ድምጽ ጠየቋት
<< የአበበ >> አለች ልጅቱ ፈራ ተባ እያለች
<< የአበበ ? >> አንደኛው ሚኒስትር አንዴ ልጅቱን ሌላ ግዜ ባለስልጣናቱን እያፈራረቁ ተመለከቱ
<< የቱ አበበ ?! >> አሉ በመገረምም በመኮሳተርም
<< የአበበ ገላው እኮ አይደለም ! የጄኔራል አበበ ... >> የክፍሉ አለቃ በላይ ነበር ጣልቃ ገብቶ የመለሰላት ፤ ትዕግስት ጭንቅላቷን  አወዛወዘች
አንደኛው ሚኒስትር ተጨማሪ አስተያየት ሳይሰጡ ከክፍሉ ሲወጡ ባለስልጣናቱም እየተጣደፉ አጀቧቸው ። ፖሊስ ኮሚሽነሩና አንድ የደህንነት ባለስልጣን የአቶ ዘሩንና የመምህር ተሻለን ክንድ እንደ ምርኩዝ ተጠቅመው ተከተሉ ። የክፍሉ አለቃ በላይ እየሮጠ በሩን ከፍቶ የእንግዶቹን መራቅ ካረጋገጠ በኌላ ጥቁር ሰሌዳው ላይ << ማቋረጥ >> ሲል በትልቁ ጻፈ ። የክፍሉን ግራና ቀኝ ካሰተዋለ በኌላ
<< ቃሉ ማቋረጥ ቢሆንም እኛ እንቀጥላለን - ተጨማሪ ሃሳብ ያለው አለ  ? >> ሲል እጁን ኪሱ ከቶ ጠየቀ ። ዘላለም እጁን አወጣ
<< እሺ ዘላለም >>
<< ማቋረጥ ማለት የመምህር ተሻለን ትምህርት ማቋረጥ ነው >>
<< ትስማማላችሁ ? >>
<< በጣም ! በጣም ! ሰሌዳው ላይ ጻፈው ! ጻፈው ! >> ሲሉ ተንጫጫቡት ። በላይ የተነገረውን ጹሁፍ በትልቁ ጻፈው ። ቀጥሎ እጅ ያወጣችው ትዕግስት ነበረች
<< እሺ ትዕግስት ተጨማሪ ነው ? >>
<< ዋናው ጥያቄ የስድስተኛ ቢ የእውቀት ጉዞ ለምን በድንገት ተቋረጠ የሚለው ይመስለኛል ? >> ስትል ጥያቄ አዘል አስተያየት ወረወረች ። አለቃው የትዕግስትን ጥያቄ አሁንም ሰሌዳው ላይ አሰፈረው ።
<< እውነት የስድስተኛ ቢ የእውቀት ግጥሚያ ለምን ተቋረጠ ? >> ሲል የክፍሉ አለቃ እየንተጎራደደ ጠየቀ ። አያሌው እጅ በማውጣቱ እንዲናገር ተፈቀደለት ።
<< የእውቀቱ ጉዞ የተቋረጠው  ብዙ ቀበሮዎች ክፍላችንን ስላቋረጡት ነው ! ይህን አያቴ የነገሩኝ ሳይሆን አይኔ የተመለከተው ነው >> ሲል የክፍሉ ተማሪዎች በመልስ አሰጣጡ በሳቅ መንፈራፈር ጀመሩ ። አሳሳቃቸው የባለስልጣናቱን የሳቅ ከፍታ በልጦ መገኘትን ያለመ ይመስል ነበር ።
<< ምንድነው እንዲህ የሚያደርጋችሁ ... ?! >> የሚለው ደንገተኛ ድምጽ ከወደ በሩ ብቅ ብሎ የሳቁን ወላፈን በአንድ ግዜ ጤዛ አለበሰው ።
የነገር ሽታን የሚያነፈንፈው የደህንነቱ ሰው ኮሚሽነሩን አስከትሎ ወደ ክፍል ገባ ። ከዚያም የስድስተኛ ቢን ተማሪዎች ትምህርት ከጥቁር ሰሌዳው ላይ በቅደም ተከተል በጥንቃቄ ማንበብ ጀመረ ።
< ቀበሮዎች > የሚለው ቃል ጋ ሲደርስ ግን ሳቁን መቆጣጠር አልቻለም ። የስድስተኛ ቢ ክፍል ተማሪዎች በባለስልጣኑ ድራማዊ ተግባር  ተገርመው ሳቁን ሊያጅቡት ቢገባም በፍጹም አልሳቁም ። በሚከብድ ጸጥታ የአሳሳቁን አይነት እየመረመሩና ቃሉን በነገር እያራቡ ነበር ። ከልቡ ሳቀ ... ከአንገት በላይ ሳቀ... እንደ ማሽላ ሳቀ...
ሳቀ ...
ይሳቅ ...
ስቆ...
አሳሳቆ ...

No comments:

Post a Comment