Monday, May 12, 2014

የተመጣጣኝ ርምጃ ልኩ የት ድረስ ነው ?




ፖሊስ ረብሻንና ብጥብጥን ለማረጋጋት መጀመሪያ መጠቀም ያለበት ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ በማይችሉ ነገሮች ነው ። ምክንያቱም ሰው የመኖር ፣ ከግርፋትና ሰብዓዊነት ከጎደለው አያያዝ የመጠበቅ መብት አለውና ። ለዚያም ነው ቆመጥ ፣ ውሃ ፣ አስለቃሽ ጋዝ ፣ የፕላስቲክ ጥይትና የመሳሰሉት በመጀመሪያ ረድፍ የግድ መታየት የሚኖርባቸው ።
በርግጥ እነዚህ ድርጊቶች በራሳቸው ጉዳት ሊያመጡ ስለሚችሉ ተግባራዊ ሲደረጉም ጥንቃቄና ሰብዓዊነት የተላበሰ መርህን ይፈልጋሉ ። ለምሳሌ ያህል ፖሊስ ዱላ ሲጠቀም በፍጹም ጭንቅላት ፣ አንገት ፣ አከርካሪ አጥንት ፣ ልብና ኩላሊት ላይ ማነጣጠር የለበትም ። የፕላስቲክ ጥይትም ቢሆን ከደረት በታች ባሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ ነው ተግባራዊ መሆን ያለበት ። አስለቃሽ ጋዝም መጠኑና ደረጃው ከፍ እንዳይል ጥንቃቄ ይፈልጋል ።
የሀገራችን እውነታዎች ግን ለዚህ መርህ ጀርባቸውን የሰጡ መሆኑ ይታያል ። ፌዴራል ፖሊስ በአንድ ምት ጭጭ የሚያደርገውን ዱላውን በቀጥታ የሚሰነዝረው ለጭንቅላት ነው ። አጋጣሚ ሆኖ በሁለት ምክንያቶች ኢላማዎች ግባቸውን ይስታሉ ። አንዱ እንደ አይን ሁሉ የጭንቅላት አምላክ አትርፎህ ዱላው ጀርባህን እንደ ሙሴ ዘመን ባህር ይሰነጥቀዋል ። ሁለተኛው ራስህን ለመከላከል ወደላይ የሰነዘርከው እጅህ ተሰብሮም ቢሆን አንጎልህን ከመፈጥፈጥ ይታደገዋል ። በጣም የሚያሳቅቀው ግን አንዱ ፖሊስ መምታት ሲጀምር ሌላውም ሰልፍ ጠብቆ የጭካኔውን ደርሻ ማዋጣቱ ነው ። በሰብዓዊ ስሜት ተገፋፍቶ < እረ ይበቃዋል ? > ብሎ የሚከላከል አለመገኘቱ ሌላኛው አሳዛኝ ክስተት ነው ። ሰው ሬሳ እስኪሆን ድረስ እንደ እባብ መቀጥቀጥ ምን የሚባል ትምህርት እንደሆነ ግልጽ አይደለም ። ሰብዓዊው ህግ ብዙ ደም ለፈሰሰው የመጀመሪያ እርዳታ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ሁሉ ያዛል ። በመሰረቱ እንደዚህ አይነት ክስተቶች የመሰረታዊ መብት ጥያቄዎች ግብግብ እንጂ ድንበር የመቁረስ ወይም ሀገር የማስገበር ጦርነት አይደለም ። በለየለት የሁለት ሀገር ጦርነት ላይ እንኳን የተማረከ ወታደር በቁጥጥር ስር ይውላል እንጂ ሰብዓዊና ሞራላዊ ህግን በመተላለፍ አይጨፈጨፍም ። ጀግኖች የሚቀጡህም ሆነ ጠማማ ካለብህ የሚያስተካክሉህ በማስተማር ነው ።
ለህይወት አስጊ የሆነው ተኩስ በአስገዳጅ ሁኔታ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው በተለያዩ አጥጋቢ ምክንያቶች ነው ። ፖሊሱ ሁሉንም ስልቶች ውጤት አጥቶበት በተለይም ሁከቱ በህይወቱ ላይ አደጋ የሚያስከትልበት ከሆነ ራሱን ለመከላከል ፣ ሁከቱ የሌሎች ሰዎችን ህይወት ሊያጠፋ የሚችል ከሆነ ተመጣጣኝ ርምጃ ሊወስድ ይችላል ። ከረብሻና ተቃውሞ ዉጪም አንድ ወንጀለኛ ካመለጠ ሌሎችን ይጎዳል ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ መሳሪያ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ።
ይህ ማለት ግን ከላይ የተቀመጡትን ምክንያቶች ሰበብ በማድረግ ፖሊስ ወይም የተደራጀው ሃይል ፍጹም ሊተካ የማይችለውን የሰው ልጅ ህይወት ይቀጥፋል ማለት አይደለም ። በተመድ ለፖሊስ የተዘጋጁ ደረጃቸውን የጠበቁ የስልጠና ማንዋሎች እንደሚያስረዱት እያንዳንዱ ፖሊስ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት በስልጠና ወቅት ራስን ስለመከላከል ፣ ስለ ሰብዓዊ አያያዝ ፣ ስለመጀመሪያ ርዳታ ፣ ስለተሰበሰበ ህዝብ ባህሪ ፣ ስለግጭት አፈታት ፣ ስለውጥረት አስተዳደር ወዘተ በቂ ትምህርት የሚያገኝ ቢሆን በችግር ግዜ አንድና አንድ ወደሆነው ግድያ ወይም የፈሪ ዱላ በፍጥነት አያመራም ። በስልጠና የበለጸገ እንዲሁም የሃላፊነቱ ሚና ከህዝባዊነት የመነጨ መሆኑን የሚገነዘብ ፖሊስ ቢያንስ በመጨረሻው ሰዓት ሲተኩስ እንኳ ወንጀለኛን ለመቆጣጠር እንጂ ነፍስን ለማቋረጥ አያልምም ። ጭንቅላት መምታት ነጥብ የሚያሰጠው በስልጠና ወቅት የተኩስ ሰሌዳ ላይ እንጂ የራስህ ቤተሰብና ወገንህ ተቸግሮ ተቃውሞ በሚያሰማበት ወይም ሁከት በሚፈጥርበት አንድ ቀን አይደለም ። ዞሮ ዞሮ ህዝብ ጠላት ሆኖ ስለማያውቅና ሊሆንም ስለማይችል እግሩን መምታትም ሲበዛበት ነው ።
አዲስ አበባንና በዙሪያዋ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞችን በማካተት የተዘጋጀውን የጋራ ማስተር ፕላን በመቃወም በየቦታው የተቀሰቀሰው ቁጣ የብዙ ሰላማዊ ዜጎችን ህይወት በልቷል ። መንግስት የሟቾቹን ቁጥር 11 ቢልም ተቃዋሚ ድርጅቶች እስከ 45 ያደርሱታል - የውጭ መገናኛ ብዙሃን ደግሞ አስከ ሰላሳ ። የቁጥር ዝቅታና ከፍታ የሚመነጨው ኌላ የሚቀርበውን ዓለማቀፍ ስሞታና ክስ ታሳቢ ከማድረግ አንጻር ነው ። አነስተኛ ሰው ከሞተ ተመጣጣኝ ርምጃ ነው የወሰድኩት በማለት ቁጣን ለማርገብ ይቻላል ። የኢትዮጽያ መንግስት በዛ ያሉ መብት ጠያቂዎችን በአደባባይ የመግደል ልምድ ከግዜ ወደ ግዜ እያደበረ የመጣ ይመስላል ።
በምርጫ 97 ማግስት በተቀሰቀሰ ቀውስ የሰው ልጅ ክብር ህይወት በጥይት ሲረግፍ አቶ መለስ ዜናዊ ተመጣጣኝ ርምጃ ነው የወሰድነው በማለት መጠነኛ አሃዝ በመጥቀስ መግለጫ ሰጥተው ነበር ። ሆኖም ጉዳዩን እንዲያጣራ የተሰየመውና በአቶ ፍሬህይወት ሳሙኤል የሚመራው ቡድን << መንግስት ያልተመጣጠነ/ ከመጠን ያለፈ /  ርምጃ ወስዷል >> የሚል ያልተጠበቀ ሪፖርት አቀረበ ። በሪፖርቱ መሰረት 193 ሰዎች በጥይት ሲሞቱ 763 ያህል ቆስለው ነበር ። ሪፖርቱ ጓዳ የነበረን ራቁት ገላ ድንገት ለአደባባይ ያጋለጠ አውሎ ንፋስ ነበር ።
ተቃውሞ የሚበርደው ሰዎች ሲሞቱ ነው የሚለው ፍልስፍና ያልተለወጠ መሆኑም የዛሬው እውነታ እያሳበቀ ነው ።  በ1997 ግርግር አንዳንድ የአዲስ አበባና ፌዴራል ፖሊስ አባላት አጋዚ የተባለው ልዩ ጦር እንጂ እኛ ሰላማዊ ህዝብን አልገደለንም እያሉ ራሳቸውን ነጻ ሲያወጡ ነበር ። መጸጸቱ በራሱ ጥሩ ይመስለኛል - ግን ይህ አይነቱ ደመ ንጹህነት መሰዎዕትነት ለሚከፈልለው ሲቪል ማህበረሰብ ትርጉም አልባ ነው ። መደበኛው ፖሊስ የመግደል አማራጭን በመርህ ደረጀ የማይቀበል ከሆነ የገዳዩንም ጣልቃ ገብነት ማለዘብ የሚከብደው አይሆንም ። ምናልባት መቋቋም የማይችለው የአስገዳዩን ቀጭን ትዕዛዝ ከሆነ አላውቅም ። ዞሮ ዞሮ በኛ ሀገር ፖሊሲያዊም እንበለው አጋዚያዊ ቀመር የተመጣጣኝ ርምጃ ልኩ የት ድረስ ነው ? ስንት ሰው ሲሞትና ስንት ሰው ሲቆስል ? ይህ ወለል ካልታወቀ እንዴት ነው < የወሰድኩት ርምጃ ተመጣጣኝ ነው > ማለት የሚደፈረው ? ግድያን ለማስቀረት መጣሩ ነው የሚሻለው ወይስ እየገደሉ በቁጥር ጅዋጅዌ መጫወት ?
የዛሬ የገደላ ዜና በሁላችንም የባንክ ደብተር ውስጥ የሚቀመጥ የቁጠባ ቦንድ ነው ። ይህን ኖት ነገ እያወጣን ስንመዝረው ውስጣችንን የሚሞላው ፍርሃት አፋችንን የሚሞላው ደም ነው ።
 እናም ነገ ያስፈራል ።
ውሃ ጠማኝ ፣ ደመወዝ አነሰኝ ፣ መሬቴን በህገወጥ መንገድ ተቀማሁ ፣ አስተዳደሩ ገለማኝ ብሎ ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጣ ሰው ባልጠበቀው መልኩ ስሙ አሸብር ፣ ነውጤ ፣ ነፍጤ ተብሎ ቢቀየር እስር ቤት ሊያደርሰው ይችላል ።
ያስፈራል ።
የተቃውሞ ሰልፍ ድንገት ተደናቅፎ ግርግር ከፈጠረ ወይም ነፍሰጡሩ ተቃውሞ ድንገት ሜዳ ላይ ብሶታዊ ልጅ ቢገላገል ሊያስገድል ይችላል ።
በ2001 በወጣው የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 21 << ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ >> ላይ ተጠርጣሪው ለምርመራ ፍቃደኛ ካልሆነ ፖሊስ አስፈላጊ የሆነ ተመጣጣኝ ሃይል ተጠቅሞ ከተጠርጣሪው ናሙና ሊወስድ ይችላል ይላል ። ተመጣጣኝ ሃይል  እዚህም ጋ አለች ።  እንግዲህ ሰውየው መረጃ አልሰጥም ብሎ ግግም ካለ ፖሊስ ገድሎትም ቢሆን ናሙና ይወስዳል ማለት ነው ? -  አያስቅም - ያስፈራል ።

           

No comments:

Post a Comment