አቶ ግርማ ካሳ ሰሞኑን በዘ ሀበሻ
ድረ ገጽ ላይ « ግልጽ ደብዳቤ ለፕሮፌሰር
መስፍን ወልደማርያም » የሚል ጦማር ጽፈው አንብበናል ። የደብዳቤው ዋና አላማ በ 2007 ዓ.ም ለሚደረገው ብሄራዊ ምርጫ አንድነት
የተባለው ድርጅት በተለይም ከመድረክ ፣ መኢአድ ፣ አረና ፣ ኢዴፓና ሰማያዊ ፓርቲዎች ጋር ውህደት ፈጥሮ ስልጣን በቃኝ የማያውቀውን
ድርጅት መታገልን ይመለከታል ።
በርግጥ ግልጹ ደብዳቤ ያስፈለገው የተቃዋሚዎችን
ዳግማዊ የአንድነት ትንሳኤ አስረግጦ ለማሳየት ነው ወይስ ለምልጃነት የሚል ገራገር ጥያቄ በእግረ መንገድ ካነሳን ምላሹ የኃለኛው
ሃሳብ ሆኖ እናገኘዋለን ። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ « ግልጽነት የሚሻው ግልጽ ደብዳቤ » የሚል የመጻፊያ ርእስ ድንገት ብቅ የሚለው
። ፕሮፌሰር መስፍን በኢህአዴግ ዘንድ እጅግ የሚፈራውና የተገለለውን የይቅርታ መንፈስ በሀገሪቱ ዳመና ላይ ለማርበብ ወይም በፖለቲካው
አጠራር የብሄራዊ እርቅን አጀንዳ ደጋግሞ ርእሰ ጉዳይ በማድረግ ወደ ተጨባጭ ምዕራፍ ለመለወጥ የተጉ ምሁር መሆናቸው ይታወቃል ።
ይህንንም በሚያደርጉት ንግግር ብቻ ሳይሆን ያሳተሟቸውን በርካታ መጽሀፍት በማንበብም መረዳት ቀላል ነው ።
አጠያያቂው ጥያቄ ፣ አቶ ግርማም እንደነገሩን
፣ ፕሮፌሰር መስፍን ሰማያዊ ፓርቲን ከመሰረቱት አንደኛው በመሆናቸውና የመጀመሪያውም መሪ ስለነበሩ « ግልጹ ደብዳቤ » ሌላው ቢቀር
ያለ ግልባጭ ቀጥታ ለእሳቸው የመጻፉ ነገር ነው ። በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት መሆናቸው
ይታወቃል ። ይህ ደብዳቤ መጻፍ የነበረበት ቀጥታ ለወቅታዊው የፓርቲው አመራር ወይስ ወደጎን ለቀድሞው ቁልፍ ሰው ?
ይህም ጥያቄ ሌላ ጥያቄ ይወልዳል ። አቶ ግርማ
ፓርቲውን አነጋግረው ጥሩ ምላሽ አላገኙም ማለት ነው ? ከሆነ የጻፉት ግልጽ ደብዳቤ እስከሆነ ድረስ ለአንባቢው ይኀው የኃላ ታሪክ
መገለጽ ነበረበት ። ርግጥ ነው አቶ ግርማ ውስጥ ያለውን ነገር ሊነግሩን ባይፈልጉም የግልጹ ደብዳቤ አንዳንድ ሀረጎች በራሳቸው
ችግር መኖሩን እየጮሑ የሚያሳብቁ ናቸው ።
አቶ ግርማ ፈገግ ብለው አሉ ።
1 . « የሰማያዊውን ነገር በርስዎ ጥዬዋለሁ
። ያሳምኗቸውና ያግባቧቸው ዘንድ እጠይቃለሁ »
አቶ ግርማ ኮስተር ብለው አሉ ።
2 . « ምክርዎትን አልሰማ ብለው የተናጥል ጉዞ
ከቀጠሉ ምርጫው የእነርሱ ይሆናል » ጥርሳጨውን እያንቀጫቀጩና ሳይታወቃቸው
ጠረጤዛ እየደለቁ ... « ጉዳዩ የፌዝና የቀልድ ወይንም የግለሰቦች ተክለሰውነት የመገንባት ሳይሆን የአገር ህልውናና ደህንነት
ነው ... » በማለት ቀጠሉ ።
ልብ በሉ አምስት ሳንቲም አላጋነንኩም ። ያደረኩት የአቶ ግርማ ቃላቶች ደምና ስጋ እንዲለብሱ ማድረግ ነው ወይም ቃላቶቹ የሚወክሉትን አካላዊ እንቅስቃሴ አስደግፎ ማቅረብ ብቻ ነው
። ታዲያ እንዴት ነው ጎበዝ ማነው እያፌዘና እየቀለደ ያለው ? እረ ማነው ፖለቲካን ለተክለ ሰውነት መገንቢያ ጥቅም እያዋለ የሚገኘው
? የሚሉ ጥያቄዎች ውስጣችን እየተንጫጫ እንዴት ነው ሆዳችንን የማይቆርጠን ... ለዚህም ነው ግልጹ ደብዳቤ ሊነግረን ያልፈለገው
ወይም የደበቀን ነገር በመኖሩ የግልጽነቱን አላማ ስቷል የሚያስብለው ።
አንባቢ « ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ » ብሎ ይመረምርና ይታዘብ ዘንድ በቂ
የመረጃ ትጥቅ ሊኖረው ይገባል ። አቶ ግርማ እንዳሉት የማስታረቅና የመሸምገል ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር መስፍን በተቃዋሚ ፓርቲዎች
መካከል ያለውን ጠባብም ሆነ ቦርቃቃ ልዩነት ከምን ተነስተው ምን ደረጃ ላይ አደረሱት ? የሚል ምናባዊ ቢጋር አዘጋጅቶ እንዲንቀሳቀስም
ይረዳው ነበር - አንባቢው ። ግና ቢጋሩ እንዳይነደፍ ግልጹ ደብዳቤ ውስጥ unግልጽ የሆኑ እንክርዳዶች መንገድ ዘግተዋል ።
ነገር ሰነጠቅክ አትበሉኝ እንጂ ደብዳቤው ውስጥ
የኢህአዴግን የመሰለ « ረጅም ሪሞት ኮንትሮል » የተመለከትኩ መስሎኛል ። በመጀመሪያ ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ የተዘጋጀውን « ሪሞት
ኮንትሮል » ብያኔ እንስጠው ።
ሀ . የተለየ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር በዚህ
ጽሁፍ ውስጥ « ሪሞት ኮንትሮል » ማለት ገባ ወጣ የማይል የህንድ ፊልም አክተር ማለት ነው ። የህንድ ዋና አክተር በገጀራ አንገቱ
ቢከተከት ፣ በላውንቸር ጥይት ደረቱ ቢቦደስ ለግዜው ቢደማ ፣ ለግዜው ቢሰቃይ እንጂ በፍጹም አይሞትም ። የህንድ አክተር እንደ
ፈጣሪ በሶስተኛው ቀን ባይሆንም እንደ እባብ ከሞተ በኃላ አፈር ልሶ በመነሳት ተመልካቹን ጉድ የማሰኘት አቅም አለው ።
የኢህአዴግ ህንዳዊ አክተር የሆነት አቶ መለስ
ይኀው ሞተውም ቢሆን ሀገር እየገዙ ፣ ሰራዊት እያዘዙ ፣ ቦንዳዊ መልዕክታቸውን ከሚያማምሩ ጥቅሶች ጋር እያስተላለፉና « ሌጋሲ
» የተባለ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማቸውን እያዘጋጁና እየተወኑ ናቸው ። በሪሞት ኮንትሮል ። ብዙ ግዜ ታዲያ የህንድ ፊልም ተመልካች
የአክተሩን ልዩ ተግባር እያደነቀ መመሰጥና ማጨብጨብ እንጂ ለምንና እንዴት በሚሉ ገሪባ ጥያቄዎች መጨናነቅ አይፈልግም ። እናም
ኢህአዴግ ማለት በአራት ጎሳዎች ውህደት የተሰራ ድርጅት ነው የሚለው ትምህርት እንዴት እንደተደለዘ ሳይታወቅ ኢህአዴግ ማለት መለስ
መሆኑ ከተረጋገጠ ቆየ ።
ታዲያ በአቶ ግርማ ደብዳቤ ውስጥ የታየው ሪሞት
ኮንትሮል ምንድነው ? ከተባለ ነገሩን ከኢዴፓ ለመጀመር ይቻላል ። ኢዴፓን ለረጅም ግዜ የመሩት አቶ ልደቱ አያሌው ፖለቲካ ርስት
አይደለም በማለት ከሳርና ስፖንጅ የተሰራውን ወንበራቸውን ለምክትላቸው ለአቶ ሙሼ ሰሙ ማስተላለፋቸው ይታወሳል ። በሶስተኛ ፖሊስ
ጣቢያ ሳይሆን በሶስተኛ የፍልስፍና መንገድ የሚታወቁት አቶ ልደቱ ከፖለቲካ ርቀው በቅርቡ ወደ መዶለቻው ሰፈር /ፖለቲካ / መቀላቀላቸውን
በዜና ሰምተናል ። አቶ ግርማ ለግልጽ ደብዳቤያቸው ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ « አቶ ልደቱ አያሌው ለአድማስ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት
ኢዴፓ ከአንድነት ጋር አብሮ ለመሆን የመፈለግ አዝማሚያ ሳይኖረው እንደማይቀር አስባለሁ » ብለው ጽፈዋል ። ልብ አድርጉ ባለሙሉ
ስልጣኑን አቶ ሙሼን አይደለም የገለጹት - ከጨዋታው የራቁ የመሰሉትን አምባሰደር ልደቱን እንጂ። እዚህ ሀሳብ ውስጥ የህንድ አክተርም
በሉት ሪሞት ኮንትሮልን እንደ ቀጭኔ አንገቱን አስግጎ አልታያችሁም ?
ሁለተኛው ሪሞት ኮንትሮል ራሱ ሰማያዊ ፓርቲ አካባቢ
የሚሸት ነው ። አቶ ግርማ « የርስዋ ድርጅት ሰማያዊ ፓርቲ ሀገር ቤት ጥሩ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ድርጅቶች ከጥቂቶቹ መካከል አንዱ
ሆኗል » በማለት ነበር ለፕሮፌሰሩ የሚገልጹት ።
ኃይለ ቃል ፣ የርስዎ
ድርጅት
ምዕራፍ አንድ ፣
አሁን የአመራር አባል ላልሆነ ሰው እንዲህ እንዲገለጽ የቌንቌ / ሰዋሰው / ስርዓታችን ይፈቅዳል ?
መካከለኛ ምዕራፍ
፣ የርስዎ ደርጅት የሚለው አነጋገር በጣም ለማጠጋጋት እንደሚያስቸግር ቁጥር ከመሃል ዝቅ ብሎ የወረደ ቢሆንም ድሮ የመሰረቱት ለማለት
ተፈልጎ ነው ብለን ብናፏቅቀው ምን ያህል ያስኬደናል ?
መደምደሚያ ፣ የርስዋ
ድርጅት ማለት ሳናጠጋጋው እረ እንደውም ከሩቅ በሪሞት ኮንትሮል ብንነካካው ትርጉሙ አሁንም ከጀርባ ሆነው የሚመሩት ማለት ይሆን
?
የገምጋሚው ማስታወሻ
፣ ግልጽነት ሳይቀድም ይቅር ለእግዚአብሄር መባባል ትርጉም ያጣል ። የግልጽነትን ድልድይ ሳይረግጡ ከአንድነት ቅጥር ግቢ መድረስ
ያስቸግራል ። ደብዳቤውም ግልጽነት ያንሰዋል ። በደብዳቤው እንድንግባባ ተጨማሪ የማፍታታት ስራ እንዲሰሩ ይነገራቸው ። በቂ ነው
ብለው ካሰቡ ግን ላጺስ ከኢህአዴግ ተውሰው ርዕሱን በአስቸኴይ ይደልዙት ። ለባለይዞታው ይመለስ ብለናል ።
No comments:
Post a Comment