ታሪኩ የተገነባው ብዙዎቻችን በምናውቀው እውነት ላይ ነው ። ጠላትህ ጠላቴ ነው ተባብለው የተማማሉ ሁለት ብሄርተኛ ቡድኖች ለረጅም አመታት ታግለው እንደ ሀገር የሚያስበውን ቡድን አሸንፈው ስልጣን ያዙ ።
በስልጣን ማግስት ሀገር የፈለገውን ይበል ብለው መስመር ባለፈ ፍቅር ከነፉ ። እንደ
ደራሲ ከበደ ሚካኤል ግጥም ‹ ሁለት አፍ ያለው ወፍ › ሆኑ ። በፍቅር ተጎራረሱ ። ተቃቅፈው በረሩ ፣ አለም ጠበባቸው ... ተጣብቀው
ዘመሩ ‹ አይበላንዶ ... › እያሉ ።ተያይዘው ፈከሩ ! ‹ ነፍጠኛ ሰመጠ ፣ ተራራ ተንቀጠቀጠ › በማለት
... አብረው ተዛበቱ ‹ ትግል ያጣመረውን ህዝብ አይለየውም › በሚል ስልቂያ ... ኪስህ ኪሴ ነው ፤ ሚስትህ ሚስቴ ናት ፤ ግዛትህ
ግዛቴ ... ምን ያልተባባሉት አለ ?
ከአይን ያውጣችሁ ያላቸው
ግን አልነበረም ።
እየቆየ አይንና ናጫ ሆኑ ... በአጎራረስህ እየተጎዳው ነው በሚል አንደኛው አፍ
የጫካ ውንድሙን ካደ ። የእህል ምርቱንም ሆነ የሚያጌጥበትን ማእድን ደበቀ ። የብር ኖቶችን ቀየረ ፣ የድንበር ንግድ ግብይት በዶላር
እንዲሆን ድንገተኛ ህግ አረቀቀ ። ይህ ተግባር ለሁለተኛው አፍ የማይታመን ክህደት ነበር ። ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ አለ ። ጠፍጥፎ
በሰራው ልጅ ተናቀ ... ሹካ አያያዝ አስተምሬው ? በኔ ደም ለወንበር በቅቶ እንዴት ክብሬን ያራክሳል በማለት ለጦርነት ተዘጋጀ
።
‹ አውሮራ › ይህን የምናውቀውን ታሪክ ይዞ ነው መዋቅሩን የገነባው ። የኢትዮ ኤርትራ
ጦርነት እንዴት ተጀምሮ እንደምን እንዳለቀ እናውቃለን ፣ ምን እንዳስከተለም የብዙ ወገኖች መረጃ አለን ። የመንግስት ሚዲያዎችን
ጨምሮ የድርጅቶቹ ልሳኖች የአውደ ውጊያውን ታሪክና የታሪክ ሰሪ ሰዎችን ህይወት በመዳሰስ አታካች በሆነ መልኩ በተከታታይ አቅርበውልናል
። ታዲያ አውሮራ ምን የተለየ ነገር ሊነግረን ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ሆነ ? ቢባል ትክክል ነው ።
ደራሲው ሀብታሙ አለባቸው ግን ብልህ ነው ፣ ገና በጠዋቱ ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ያስተዋወቀንን የታሪክ
በከራ እንዴት ሳይሰለች እያጠነጠነ እስከ ምዕራፍ 43 መዝለቅ እንዳለበት በሚገባ ተረድቷል ። ስለተረዳም ሳቢና ተነባቢ አደረገው
።
ይህን ለማከናወን ከረዳው ስልት አንደኛው የትረካውን ኳስ ለመለጋት በመረጠው የመቼት
አንግል የተወሰነ ይመስለኛል ። ደራሲው 80 ከመቶ የሚሆነውን ታሪክ የሚያቀብለን ከኤርትራ አንጻር ሆኖ ነው ። በትረካው የአስመራን
ውበት ፣ የወታደራዊ ካምፖችን ሚስጢር ፣ የደህንነት ተቋማት ፕሮፓጋንዳ ፣ ሳዋ ስለተባለው የሰው ቄራ ፣ የፕሬዝዳንቱን ጽ/ቤት
ከነተግባርና ግዴታቸው እንመለከታለን ። የህዝቡን አበሻዊ ጥላቻ ፣ ፖለቲካዊ ሹክሹክታ እና ስነልቦና እንመረምራለን ። የባለስልጣናቱን
በተለይም የፕሬዝዳንቱን እምነት ፣ አስተሳሰብ እና ፍላጎት እንታዘባለን ። በአጠቃላይ ከአስመራ የምናገኘው አዲስ መረጃ ታሪኩ ሰቃይና
አጓጊ እንዲሆን ትልቅ ሚና ተጫውቷል ። የታሪኩ ልጊያ ከአስመራ እየተነሳ ወደ ኢትዮጽያ ፣ ጅቡቲና ሌሎች አካባቢዎች ሲያመራ ደግሞ
ተዝናኖት ብቻ ሳይሆን አማራጭ እሳቤ ይፈጥርልናል ። በመሆኑም የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት አዲስ ሆኖ እንዲሰማን አድርጓል ።
ሌላም አለ ። ታሪኩን የሚደግፉት የሴራ ቅንብሮች ባለሁለት አፍ ወፎቹ ይፋ በሆነ
መልኩ በመድፍ እንዲቆራቆሱ ብቻ አይደለም የሚያደርገው - ወፎቹ በየሰፈራቸው በተዳፈነው ረመጥ እንዲለበለቡም ጭምር እንጂ ።
የአስመራው ወፍ / ኢሳያስ / ክብሩንና ጥቅሙን ለማስጠበቅ መጠነ ሰፊ ፣ የተደራጀና
ህቡዕ ተኮር እንቅስቃሴ ያደርጋል ። ኢትዮጽያዊው ወፍ / መለስ / አንድም አናት አናቱን ከሚጠቀጥቁት ወንድም ግንደ ቆርቁሮች በሌላ
በኩል ከሩቅ አጎቱ የሚወረወርበትን ሞርታር ለመከላከል መከራውን ሲበላ እንመለከታለን ።
በነገራችን ላይ ከአስመራ ወደ ኢትዮጽያ የሚጋልበው የታሪክ ጅረት ሁለት መቆጣጠሪያ
ቤተመንግስቶች አሉት ። የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እና የአቶ ሃይላይ ሃለፎም ። በፍትህ ሚ/ሩ አቶ ሃይላይ ቤት አራት የታሪኩ ቁልፍ
ሰዎች ይገኛሉ ። ቤተሰቦች ናቸው ። ሳህል በረሃ የተወለደችው ፍልይቲ ፣ ወንድሟ ሰለሞን እና ባለስልጣን እናታቸው አኅበረት ።
ሃይላይ በርግጥም ለሰላምና ፍትህ የቆመ ብቸኛ ሚኒስትር ነው ። ከኢትዮጽያ ጋር የሚደረገው ጦርነት መሰረት የሌለው የዜሮ ድምር
ፖለቲካ በመሆኑ መቆም አለበት በሚለው አቋሙ ከዋናው ቤተመንግስት ሰውዪ ጋር ይጋጫል ።
በሌላ በኩል ኢሳያስ የሃይላን ልጅ ፍልይቲን እንደ ጆከር ሲጠቀምባት እናያለን ።
ኢ/ያ ውስጥ የሚከናወነውን የዶላር ዘረፋ ፣ የስለላ ስራና ህቡዕ ግድያ ትመራለች ። በጅቡቲ ወደብ ወደ ኢ/ያ የሚገባውን ስትራቴጂካዊ
ንብረት ለማውደም ተመራጭዋ ሰው እሷ ናት ። ባድመ በመዝመት ለሌሎች ያስቸገሩ የመረጃና የተመሰጠሩ መልእክቶችን የመፍታት ስራ ትሰራለች
። ፍልይቲ የፕሬዝዳንቱ ቀኝ እጅ ፣ ብሩህ አእምሮ ያላት ፣ ደፋር ፣ አፍቃሪ እና ጨካኝ ገጸባህሪ ናት ።
ከኤርትራ ህዝብ አንጻር / አማራ ጠላት ነው የሚል ቆሻሻ ሀሳብ / ግን አንድ ይቅር
የማይባል ክህደት ትፈጽማለች ። ክህደቱ ለኤርትራ የቴሌ እና ኤሌክትሮኒክስ ግንባታ ትልቅ ድርሻ ያከናወነውን ኢትዮጽያዊ ሰው በማፍቀሯ
ነው ። አስራደ ሙሉጌታ ይባላል ። ሻእቢያ ጉልበቱንና እውቀቱን እንደ ሽንኮራ ከመጠጠው በኋላ ሊያስወግደው ቀነ ቀጠሮ ይዞለታል
። ለአስመራ ፖለቲካ ትልቅ አይን የሆነችው ፍልይቲ ከመንግስታዊው ተልዕኮ ጎን ለጎን ፍቅረኛዋን ለማዳን ህቡዕ ትግል ስታከናውን
እንመለከታለን ። የሃይላይ ወንድ ልጅ ሰለሞን ‹ ናጽነት › በሚለው ነጠላ ዜማው በከተማው የታወቀ ዘፋኝ ሆኗል ። ሙዚቃው ማዝናኛ
ብቻ ሳይሆን የዘመቻ መቀስቀሻም ነው ። ናጽነት ብሎ የዘፈነው ግን በኢሳያስና በአባቱ ለተመራው ትግል ማስታወሻ ለመስራት ብቻ አይደለም
። እንደውም በዋናነት የዘፈነው ነጻነት የተባለች ቆንጆ ወጣት በማፍቀሩ ነው ። ነጻነት ለኤርትራ ወጣት የእግር እሳት ወደሆነበት
ሳዋ ስትገባ እሱም እንዳላጣት ብሎ ፈለግዋን ይከተላል ። እሷን ፍለጋ ላይ ታች ሲል ነጻነት በሁለት የባደመ ጦር ጄነራሎች አይን
ውስጥ ትወድቃለች ። ልክ እንደ ባድመ መሬት ሊቆጣጠሯት ሌት ተቀን ስትራቴጂክ ይነድፋሉ ።
እናም የአንደኛው ቤተመንግስት ሰውዪ ከኢ/ያ ድል ለማግኘት ሲራራጥ ፣ የሁለተኛው
ቤተመንግስት አባላት ደግሞ ከራሱ ከኢሳያስ ጭቆና ለመላቀቅ እንዲሁም ፍቅረኛዎቻቸውን ለመታደግ ላይ ታች ሲሉ በታሪኩ ተወጥረን እንያዛለን
።
መጽሐፉ ጥቃቅን ቴክኒካል ችግሮች የሉበትም ማለት አይቻልም ፣ ለአቅመ ግነት የሚበቁ
ስላልመሰለኝ ዘልያቸዋለሁ ። ይልቁንስ ደራሲው የራሱ እምነት የሚመስል ጉዳይ መጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ቆስቁሶ እንዲረሳ ወይም እንዲጨነግፍ
ማድረጉ የሚቆጭ ይመስለኛል ። ያነሳቸው ጥያቄዎች የአንባቢም መሰረታዊ ጥያቄዎች ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው ። የባርካ ማተሚያ ቤት ባለቤት
የሆኑ ግለሰብ አቶ ሃይላይ ሊጽፉ ባሰቡት መጽሐፍ ውስጥ አራት መሰረታዊ ጥያቄዎችን አዳብረው አንዲሰሩ ሀሳብ ያቀርባሉ ። ከቀረቡት
ሃሳብ ውስጥ ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው ፣
1 . የኤርትራ ነጻነት ትግል ለምን በ 1885 ምጽዋ በኢጣሊያ መያዝን በመቃወም
አልተጀመረም ?
2 . ከኤርትራ ልዩ ማንነት የተፀነሰ ትግል ከሆነ ለምን 30 አመታት ፈጀ ?
ደራሲው ስራውን ከሰሩት 285 ሺህ ናቅፋ እንደሚያገኙም ውል ታስሮ ነበር ። ሆኖም
የማተሚያ ቤቱ ባለቤት ሲያዙ ፣ አቶ ሃይላይም ሲገደሉ ሃሳቡ ይመክናል ። እንደ ስነጽሁፍ ሃያሲ የሁለቱ ሰዋች መጥፋትን በአስመራ
ወስጥ የመጻፍ ፣ የመናገር ፣ የማሰብ እና የዴሞክራሲ መሞትን ለመተርጎም ያስረዳን ይሆናል ። ከዚህ በላይ ግን ታሪኩ ባይጨነግፍ
የበለጠ ጠቃሚ ያደርገን ነበር ብሎ መከራከር ያስኬዳል ። አቶ ሃይላይ ለእውነት የቆሙ ገጸባህሪ በመሆናቸው እየመረራቸውም ቢሆን
ከኤርትራ ጀርባ የተደበቁ ጉዳዮችን ያነሱ ነበር ። ይሄን አንስተው ቢሞቱ ደግሞ ሞታቸውንም ይመጥን ነበር ። የበለጠ ጀግና መስዎዕት
እናደርጋቸው ነበር ።
‹ አውሮራ › ጦርነት ላይ መሰረት አድርገው እንደተሰሩት ልቦለዶቻችን ማለትም ኦሮማይ
እና ጣምራጦር የተሳካ ስራ ነው ። ድንበር ያቆራርጣል ፤ እዚህና አዚያ እንደ ቴኒስ ኳስ ሲያንቀረቅበን ጨዋታው ሰለቸኝ ብለን ከሜዳው
ዞር ማለት አንችልም ። ፈጣን ነው ፤ በድርጊት የተሞላና በመረጃ የደነደነ ። መንቶ ነው ፤ ፍቅርና ጦርነትን በእኩል ጥፍጥና ከሽኖ
ማቅረብ የቻለ ። ሰባኪ ነው - ፍቅር ያሸንፋል የሚል አይነት ፤ ተዛምዶ ተጋብቶ ተዋልዶ የተካደ ትውልደን የሚያባብል ። የሆነውን
ብቻ ሳይሆን የሚሆነውን ቁልጭ አድርጎ የሚናገር ። በተለይም የአንድነት
አሳቢዎችን ገድለን ቀብረናል ብለው ለሚመጻደቁ ጠባቦች « ውሸት ነው ! » ብሎ ጥበባዊ ምስክርነት የሚሰጥ ።
በታሪኩ ውስጥ ማንነቱን ደብቆ ስሙን አቦይ ግርማ አስብሎ ቀን ከለሊት በባድመ የልመና
ተግባር የሚያከናውነው እንኮዶ /የደርግ ኮማንዶ የነበረ / አንድ እጁ ስለተቆረጠና አይኑ ስለተጎዳ ማንም ግምት ውስጥ ያሰገባው
አልነበረም ። ሆኖም መጀመሪያ የባድመን መሬት ፈልፍለው የገቡ የሻእቢያ ወታደሮችን ፣ በመጨረሻም እጁን በመጋዝ ቆርጦ የጣለውን
ጄኔራል ግዜ እየጠበቀ መበቀል ችሏል « ለገንጣይና ጡት ነካሽ ዋጋው ይሄ ነው » እያለ ። ይህ ትርክት በስነጽሁፍ ቋንቋ ፎርሻዶው
ወይም ንግር የሚባለው ቴክኒክ ነው - ነገ እንዲህ መሆኑ አይቀርም ለማለት ።
No comments:
Post a Comment