Monday, September 25, 2017

ደራሲው ጋዳፊ ለምን ሀሳቡን አልሆነም ?




የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ ፖለቲከኛ ፣ ሃሳብ አመንጪ እና ደራሲ ነው ። በረጅም የስልጣን ዘመን ቆይታው Escape to hell and others , My vision እና The Green Book የተሰኙ ሶስት ተጠቃሽ መጻህፍትን ለዓለም አበርክቷል ።

አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍናውን በመጽሐፍ መልክ ማሳተም የጀመረው በ1975 ነበር ። የዴሞክራሲ ችግር መፍትሄ ፣ የኢኮኖሚ ችግር መፍትሄ እና የሶስተኛው ዓለማቀፍ ቲዎሪ ማህበራዊ መሰረቶች የሚሉ ሶስት ጥራዞችን በተለያዩ ግዜ ጽፏል ። ኋላ ላይ እነዚህን ጥራዞች አንድ ላይ በመሰብሰብ አረንጓዴው መጽሐፍ በሚል ለንባብ አብቅቷቸዋል ።

አረንጓዴው መጽሐፍ ዓለምን ብዙ ያነጋገረና ያከራከረ ስራ ነው ። ይህን መጽሐፍ የተማሩበት የሊቢያ ወጣቶች ብቻ አልነበሩም ። በፈረንሳይ ፣ ምስራቅ አውሮፓ፣ ኮሎምቢያ እና ቬንዚውላ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ተወያይተውበታል ፤ አውደጥናት ተካፍለውበታል ።

ጋዳፊ የፍልስፍና ውሃ ልኩን በአረንጓዴው መጽሐፍ ለማሳየት ሞክሯል ። በተለይ የምእራቡ ዓለም የዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ አስተምህሮ ጠማማ መሆኑን መነሻ በማድረግ የችግሮቹን መፍትሄ በአማራጭ አተያይ / ሶስተኛው አለማቀፍ ቲዎሪ / ለመተንተን ሞክሯል ።

ጋዳፊ በዚህ ጥራዝ ብዙ ርእሰ ጉዳዮችን ነው የመዘዘው ። በመጀመሪያ ክፍል ምርጫን ፣ የተወካዮች ም/ቤትንና ህዝበ ውሳኔን በእጅጉ ይኮንናል ። እንደርሱ እምነት ዴሞክራሲ የህዝቦች ስልጣን እንጂ የጥቂት እንደራሴዎች ሃብት አይደለም ። ህዝብን እንወክላለን ብለው በፓርላማ በሚሰበሰቡ አባላት ዴሞክራሲ እውን ሊሆን አይችልም ምክንያቱም እነሱ ከተመረጡ በኋላ ለራሳቸው ጥቅም ነው የሚንቀሳቀሱት ። በተለይ ፓርላማው በአንድ ፓርቲ የተዋቀረ ከሆነ የአሸናፊ ፓርቲ ፓርላማ እንጂ የህዝብ ፓርላማ መባሉ አግባብ አይደለም ። ጋዳፊ የወቅቱን የእኛ ሀገርን ፓርላማ ቀድሞ ነው የተቸው ማለት ነው ። እውነተኛው ዴሞክራሲ የሚገኘው በቀጥተኛው የህብረተሰብ ተሳትፎ ነው ። እውነተኛ ዴሞክራሲ ተግባራዊ የሚሆነው ብዙሃኑ በህብረት ወጥቶ ህዝባዊ ኮሚቴ እና ታላቅ የመማክርት ጉባኤ ሲዋቀሩ ነው ። ህዝበ ውሳኔም ቢሆን / Referendum / ዴሞክራሲን የማጭበርበሪያ ዘዴ እንደሆነ ጽፎታል ። ‹ አዎ › ወይም ‹ አይ › ብለው እንዲመርጡ የሚገደዱ ዜጎች ነጻ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ አይደረግም ። በመሆኑም ይህ አይነቱ አሰራር ጨቋኝና አምባገነናዊ ነው ሊባል የሚገባው ።

ፕሬስንና ሃሳብን በነጻነት መግለጽን አስመልክቶም የግለሰቦችና የቡድኖች ያልተገደበ መብት እንደሆነ ይዘረዝራል « ፕሬስ ማለት ማንኛውም ሰው ራሱንና አስተሳሰቡን የሚገልጽበት ነው ፣ ሌላው ቀርቶ እብደቱን ጭምር ። የዚህ ሰውየ እብደት የሌላ ሰው ወይም ሰዎች እብደት ነው ተብሎ መቆጠር የለበትም ። በመሆኑም በጋዜጦች የሚወጡ አስተያየቶችን የህዝብን ሃሳብ አደርጎ ጥያቄ ማንሳት መሰረተ ቢስ ነው ፣ ምክንያቱም ጋዜጦች ያተሙት የዚያን ሰውየ አስተያየት ነውና »

በሁለተኛው ክፍል ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተዳሰዋል ። እንደ ጋዳፊ ሃሳብ ደመወዝተኞች ለቀጠራቸው ግለሰብ ግዜያዊ ባሪያዎች ናቸው ። መሰረታዊ ፍላጎቶች/ ቤት ፣ ትራንስፖርት ወዘተ / በግለሰቦች ቁጥጥር ስር መዋል የለባቸውም ምክንያቱም ብዝበዛንና ባርነትን ያመጣሉና ። በሶሻሊስት ማህበረሰብ ውስጥ ሰዎች የሚሰሩት በሽርካነት እንጂ ለደመወዝ ብለው አይደለም ። በሌላ ሠው ቤት የሚኖሩ ሰዎች ማለትም ኪራይ የሚከፍሉም ሆነ የማይከፍሉት ነጻነት አላቸው ማለት አይቻልም ። መሬት የማንም ሃብት አይደለም ነገር ግን ማንኛውም ሰው በመሬት ላይ ማንንም ሳይቀጥር የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን ይችላል ። የቤት ሰራተኝነት የዘመናዊው ዓለም ባርነት ነው ። እናም የቤት ስራ መከናወን ያለበት በነዋሪዎቹ ነው ።

ሶስተኛው ክፍል ማለትም የሶስተኛው ዓለማቀፍ ቲዎሪ ቤተሰብን ፣ ጎሳን ፣ ብሄርን ፣ ሃገርን ፣ አናሳ ብሄርን ፣ ሙዚቃን ፣ ስፖርትና ሴቶችን ይዳስሣል ። ሌላው ቀርቶ ጥቁር ህዝቦች ወደፊት አለምን / ቀደም ብሎ ቢጫዎች ፣ አሁን ደግሞ ነጮቹ እየገዙ ነው / ይመራሉ ይላል ። ስፖርት ልክ እንደ ጸሎት ግላዊ ጉዳይ መሆኑን ይገነዘባል ። ቦክስ እና ነጻ ትግል ግን የሰው ልጅ ገና ከአረመኔነቱ አለመላቀቁን የሚያሳዩ ድርጊቶች ናቸው ።

ጋዳፊ ቤተሰብ ከመንግስት የበለጠ አስፈላጊ ተቋም እንደሆነ በሚከተለው መልኩ ያምናል  « ቤተሰብ እንደ እጽዋት ነው ። ቅርንጫፍ ፣ ግንድ ፣ ፍሬና ቅጠል ያለው ። እጽዋት የመነቀል ፣ የመድረቅ እና የእሳት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ሁሉ ቤተሰብም ህልውናው በብዙ ነገሮች ይፈተናል ። ያበበ ማህበረሰብ ማለት ግለሰቦች በቤተሰብ ውስጥ ቤተሰቦች ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ ማደግ ሲችሉ ነው ። ቅጠል ለቅርንጫፍ ፣ ቅርንጫፍ ለዛፍ እንዲሉ ግለሰብም በቤተሰብ ውስጥ የጠነከረ ትስሥር አለው ። ግለሰብ ያለ ቤተሰብ ትርጉም የለውም ። የሰው ልጅ እንደዚህ አይነቱን ትስስር ከጣለ ስር የሌለው ሰው ሰራሽ አበባ ነው የሚሆነው »

ጋዳፊ ለጎሳ መራሹ የአፍሪካ ህዝብም ጠቃሚ ስንቅ ያቀበለ ይመስላል ። ማህበራዊ ትስስር ፣ አንድነት ፣ ቅርበትና ፍቅር ከጎሳ ይልቅ በቤተሰብ ይጠነክራል ፤ ከሀገር ይልቅ በጎሳ ይጠነክራል ። ከዓለማቀፍነት ይልቅ በሀገር ይጠነክራል ። ጎሳ ትልቅ ቤተሰብ ነው ... ለጎሳ ትልቁ መሰረት ደም ነው ... ጎሳ አባላቱን የሚከላከለው በመበቀል ነው ። ጎሰኝነት ናሽናሊዝምን ያጠፋል ፤ ምክንያቱም የጎሳ ታማኝነት ከሀገር ታማኝነት የላቀ ነው ። በሀገር ውሰጥ የሚገኙ ጎሳዎች የሚጋጩ ከሆነ ሀገር ችግር ውሰጥ ይወድቃል ። ብሄርተኞች ፍላጎታቸውን በሃይል የሚገልጹ ከሆነና የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሰቀድሙ ከሆነ ሰብዓዊነት ላይ አደጋ ይፈጠራል በማለት ስጋቱን ክፍላጎቱ ጋር አዛምዶ መርሁ ላይ አስፍሮታል ።

የአንድ ሀገር ህዝቦች የሚበየኑት በቦታው ላይ በመፈጠራቸው ብቻ አይደለም ። ይህ መሰረታዊ ነገር ሊሆን ይችላል ። ከዚህ በተጨማሪ ግን ለረጅም ግዜ በአንድ ላይ በመኖር የጋራ ታሪክ ፣ ቅርስ እና ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ሲኖራቸው ነው ። ህዝቦች ከደም ትስስር ይልቅ ሀገራዊ አንድነትና የኔነትን በጋራ ይዛመዳሉ ።

ሴቶች ከወንዶች እኩል አይደሉም በሚባለው ብሂል ጋዳፊ አይስማማም ። ሴቶች እኩል መስለው የማይታዩበትንም ሳይንሳዊ ምክንያት በዝርዝር አስቀምጧል ። ሴቶች አንስታይ ወንዶች ተባእታይ ናቸው ። ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት ሴቶች በየወሩ ደም ሲያዩ ወንዶች አይኖራቸውም ። ሴት ደም ካላየች ነፍሰጡር ናት ። ነፍሰ ጡር ስትሆን ለአመት ያህል ንቁ ተሳታፊ አትሆንም ። ልጅ ስትወልድ ወይም ሲያስወርዳት ደግሞ በ ፒዩፐሪየም / Puerperium / ትሰቃያለች ። ወንድ ይህ ሁሉ ስቃይ አይደርስበትም ። ከወለደችም በኋላ ለሁለት አመታት ታጠባለች ። ጡት ማጥባት ማለት ሴት ከልጅዋ የማትለያይበት በመሆኑ አሁንም ሌሎች እንቅስቃሴዎቿ ይቀንሳል ። በመሆኑም ሌላን ሰው ለመርዳት ቀጥተኛ ሃላፊነት መውሰድ በእሷ ላይ ይወድቃል። ያለ እርሷ ብርቱ ድጋፍ ያ ፍጡር ይሞታል ። ወንድ በሌላ በኩል አያረግዝም ፣ አያጠባም ::

ጋዳፊ በአረንጓዴው መጽሐፍ ታላላቅ ሀሳቦችን አንስቷል ። በክፍል አንድ ስልጣን የህዝብ መሆኑን እንመለከታለን ። ግለሰቦች ሊያብዱ ይችላሉ ይህ ማለት ግን ማህበረሰቡ አብዷል ማለት አይደለም በሚለው ነጥብ ዙሪያ ፕሬስ ሃሳብን መግለጫ ነጻ መሳሪያ መሆኑ ተሰምሮበታል ። በሁለተኛው ክፍል ለኢኮኖሚው ችግር መፍትሄው ሶሻሊዝም መሆኑ ተቀምጧል - በእያንዳንዱ ቤት ወስጥ የሚኖር ዜጋ የቤቱ ባለቤት እንጂ ጭሰኛ መሆን የለበትም የሚል የሚደላ አቋም ይታያል ። የአስቂኝም አስደናቂም ስብስብ በሆነው ሶስተኛ ክፍልም ሴት ከወንድ ታንሳለች ማለት የተፈጥሮ ህግን መካድ ነው የሚል ጠንካራ አቋም ይገኛል ።

ደራሲው ጋዳፊ ከፖለቲከኛው ጋዳፊ ጋር ተጣጥሞ ቢዘልቅ መልካም ነበር ። በተለይ በዙሪያህ የተኮለኮሉ ሰዎች / የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው / የስብእና አምልኮ እየገነቡልህ ሲሄዱ ዝም ካልክ መቀበሪያህ እየተማሰ መሆኑ ማወቅ ይገባል ። ። ጋዳፊ መርሁ እንዲዘመር እንጂ እንዲሰራበት ለማድረግ ያልቻለበት አንደኛው ምክንያትም ይሄው ነው ። ጹሑፍህን ደጋግመህ በፍቅር ታነበዋለህ እንጂ ደፍረህ አርትኦት አታደርገውም ። በዚያ ላይ ፍልስፍናን ለማሰብና ለመራቀቅ እንጂ ሆኖ ለመኖር ይከብዳል ።




Wednesday, September 13, 2017

« በፍቅር ሥም » ከጥቅል አደረጃጀት አንጻር



የአለማየሁ ገላጋይን « በፍቅር ስም » ለመተቸት የሚነሳ ሀያሲ በምን ርዕሰ ጉዳይ ስር ልጻፍ ብሎ የሚጨነቅ አይመስለኝም ። መጽሐፉ በዘርፈ ብዙ የሃሳብና የትርክት ሃዲዶች ላይ ስለሚጋልብ አንዱን የታሪክ ሰበዝ መዞ ምልከታንና ሙያዊ ትንተናን ማዋሃድ ይቻላል ።

እኔ እንግዳ በመሰለኝ የመዋቅር አደረጃጀት እና ፍሰት ላይ አተኩራለሁ ። ደራሲው እኔ በተሰኘው የአተራረክ ስልቱ ጽሁፉን የሚጀምረው « በሴት የመከበብን ጥቅም የምናውቀው እኔና ጠቢቡ ሰለሞን ብቻ ነን » በማለት ነው ። የታሪኩ አባት ትንሹ ‹ ታለ  › ነው ። ታለ ይህን የሚነግረን በጥቅሙ በረከት ፈግጎ ነው ። ወጣቱ ታለ በመጽሐፉ መዝጊያ ላይ በተመሳሳይ ዜማ የሚከተለውን ይናገራል « የኛ አስር ደቂቃ በእርሱ / ቹቹ / ስንት እንደሆነ የማውቀው እኔ ነኝ » ታለ ይህን የሚነግረን በህመምና ፀፀት ውስጥ ሰምጦ ነው ።

ታለ የፍቅርና ፀፀት ጥለትን እየለበሰና እያወለቀ የሚዘልቅ ገጸባህሪ ነው ። ደራሲው ይህን የታሪክ ጉዞ የሚያሳየንና የሚነግረን በተለመደው የገጸባህሪ የበቀል/አሸናፊነት ፍትጊያ አይደለም ። የታሪኩ መረማመጃዎች ጥቅል ሰብዕናዋች/ ማንነቶች ናቸው ። አንዱ ጥቅል ቢዘንና አንጓቼ / ባልና ሚስት / ናቸው ። ይህ ጥቅል አውቶብስ በመሰለው ቤተሰባዊ ጎጆ / በነገራችን ላይ የቤተሰቡ መኖሪያ በገጽ 22-23 በአስቂኝ መልኩ ተገልዿል / ውስጥ እንደ ሹፌርና አውታንቲ ሊቆጠር የሚችል ነው ። ሹፌርና ረዳት በሳንቲም መጋጨታቸው አይደንቅም ። አንድ ቤት የሚኖሩ ባልና ሚስት ግን ወንድን ልጅ / ታለን / የግላቸው ለማድረግ የማያባራ ጦርነት መከፈታቸው ያልተለመደ / bizarre / ነው ።

« እግዚአብሄር የሰጠኝን ወንድ ልጅ የገዛ ሚስቴና ልጆቼ ነጠቁኝ » ይላል አባወራው
« ከመላእክት እስከ አጋንንት ደጅ የረገጥኩበትን ልጄንማ አልተውም » ትላለች እማወራ

በዚህ መነሻነት ጥቅሉ እየተፈታ ሌላ ግዜ እየተተረተረ ታሪኩንና የታሪኩን ማህበረሰብ ያናጋዋል ። በስድብና ሽሙጥ አረር ይጠዛጠዛሉ ። የቅናትና ጥርጣሬ ዳመራ በየግዜው ይለኮሳል ። ሰባት ሴት ልጅ መውለዳቸው ያልተዋጠላቸው አባወራ ሰባት ስድቦችን ነው የወለድኩት እስከማለት ይደርሳሉ ። በመልክ ለየት ያሉ ልጆችን ሳይቀር በተጠየቅ ይሞግቷቸዋል ። ጥቁሯን አበባ « ለመሆኑ የአፍሪካ ህብረት ሲቋቋም ተረግዛለች ? » ቀይዋ ስምረትን « መልኳ ሁሉ የእንግሊዝ ነው ፣ እኔ የምለው እንግሊዝ ሲመጣ ነው የተወለደችው ? » ረቂቅን ደግሞ « ይሄ ባኒያንኮ ያልደረሰበት ቦታ የለም » በማለት የነገር ጅራፋቸውን ይተኩሳሉ ። ባልና ሚስቱ በሚታክት መልኩ ይናቆሩ እንጂ ችግር በመጣ ግዜ እንደ ማግኔት ይፈላለጋሉ ፣ ጥቅሉ ማንነት ውስጥ ለአደባባይ አይናፋር የሆነ መተሳሰብ አለ ።

ሁለተኛው ጥቅል ሰባቱ ሴቶች ልጆች ናቸው ። አውቶቡስ በመሰለው ቤት ውስጥ ተሳፋሪ ይምሰሉ እንጂ መኪናው እንዳይገለበጥ ወይም ተበላሽቶ እንዳይቆም ምሶሶ ሆነው የቆሙ ናቸው ። ለምሳሌ የአቶ ቢዘን ጡረታ ስለማያወላዳ እናታቸውን በጉሊት ስራ ይረዳሉ ። በተቃራኒው አባታቸው ጠጅ ቤት ከሰው ጋ ሲጣላ ተሰብስበው ሄደው ወግረው በድል ይመለሳሉ ። ይህም የቢዘን ፍርጎ የሚል ስያሜ ቢያሰጣቸውም አባታቸው በሰፈሩና በየካቲካላው ቤት እንዲፈራ አድርጓል - ከሴት ልጅ ባህሪ አኳያ ግን ያልተለመደ ነው ።

ይህ ጥቅል ገጸባህሪ ለየት የሚልበት ሌላም ጉዳይ አለው ። ቤተሰባቸውን ያፍቅሩ እንጂ ለሌላው እምብዛም ፍቅር የላቸውም ። በተለይ ወንድን በማባረር ተመሳሳይ አቋም ነው ያላቸው ። የርስ በርሳቸው ምክር « እንግባ ቢልሽ አትግቢ ! እንውጣ ቢልሽ አትውጪ ! » ብቻ ነው ። ፍቅር ተፈጥሯዊ ጸጋ ስለመሆኑ ፊት አይሰጡም ። ድንገት ከመካከላቸው አንዷ ፍቅር ሽው ያለባት ግዜ እንኳ መቀመጫ ሲያሳጧት ይታያል ። ወንዳወንዴዋ ቹቹ እንኳ ሰለወደዳት ልጅ እንዲወራ አትፈቅድም ። ይህ ከሴት ልጅ ስስ ልቦናና ተቃርኗዊ ትስስር አንጻር ያልተለመደ ይመስላል ።

ሶስተኛው ጥቅል አራቱ ስፖርተኞች ናቸው ። ደራሲው በዚህ ሃዲድ እንድንጓዝ የፈለገው የልጅነትን ሌላኛው ገጽታ እንድንመለከት ብቻ አይደለም ። እንደ ሽክና አይነት ቀልደኞች ቆምጫጫውን የታሪክ ጉዞ እንዲያለሳልሱት ብቻ አይደለም ። እግርህን ከፍተህ የምትሄደው ጭገርህን ስላላበጠርክ ነው እያለ በግድ መጣላት የሚፈልገውን የ ‹ ቲኔጀር › ሞት አይፈሬነት ለመጠቆም ብቻ አይደለም ። የወንድነት ክትባት የሚፈልገውን ታለን ለማከምም ጭምር ነው ። ስፖርተኞቹ ሰፈር የምታደርሰው ወንዳወንዴዋ ቹቹ መሆኗን ስናስብ ግን በቤተሰቡ ውስጥ ያለውን ሁለተኛ ‹ ቢዛሪ ›ጉዳይ እናጤናለን ።

በሌላኛው ጥቅል አደረጃጀት ውስጥ የተቀረጹት ሶስቱ ወታደሮች ናቸው ። ወታደሮቹ በአፋዊ ገጽታቸው ይለያዩ እንጂ በሀገር ፍቅር ጽናታቸው አንድ ናቸው ። ብዙ ግዜ ለመዝመትና ለመሞት የቆረጡ ናቸው ። ተሸንፈው እንኳን አንዲት ህገር በሚለው መንግስቱ ስም ለመለመን አይሳቀቁም ። መንግስቱን ሳይሆን ታሪካዊ መርሁን አሻግረው ያያሉ ።

የወታደሮቹ ሌላኛው ውክልና ሀገር የገባችበትን ውጥንቅጥ ፈተና ማሳየት ነው ። በማህበረሰቡ ውስጥ አፈሳ ያስከተለውን የፍርሃት ቆፈንና የአስተዳደር መናጋት እንመለከታለን ። ፍርሃት ምንያህል ሀገራዊ ኩይሳ እንደሰራ ለማውቅ የአእምሮ ዝግምተኛው ቹቹ እንኳ መደበቂያ ሲፈልግ መታየቱ ነው ። ሻምበል ጠናጋሻውን ስናስብ ደግሞ ደራሲው ጦር ሰራዊቱ ውስጥ ያነበቡ ፣ የተማሩና ህዝባዊ ፍቅር የተላበሱ ግለሰቦች መኖራቸውን ለመጠቆም ብቻ እንዳልቀረጸው እንረዳለን ። ሻምበሉ ለታሪኩ እንድርድሮሽ መረማመጃነት አገልጋይ ነው ። ሻምበሉ ለታለ ያበረከተው የማይታመን ነገር ግን ጠቃሚ ስጦታ ቀጣዩ ጥቅል ስብእና የደረጀ እንዲሆን አግዟል ።

በዚህ መሰረት ለጥቆ የምናገኛቸው ታለን እና ሲፈንን ነው ። ርግጥ ነው በታለ ውስጥ ቹቹ ፣ በሲፈን ውስጥም ቹቹ አለ ። ቹቹ ‹ ኮመን ዶሚነተር › ነው ። የታለና ሲፈን ፍቅር አይኑን ገልጾ ከፍተኛ ደረጃ / Climax / የደረሰው ሻምበሉ ከከፈለው ጥሎሽ በኋላ ነው ። ጥሎሹ ሲፈን እንድትዝናና ታለ በአዲሱ አለም ላይ አይኑን እንዲከፍት አስችሎታል ።

ሲፈን በርግጥም የአውሊያ ፈረስ ትመስላለች ። ጋልባ ጋልባ ስድስተኛው ጥቅል ገጸባህሪያት ሰፈር የምታደርሰው እሷ ናት ። ደራሲው ይህን በ ‹ ጃክሰኖች › መስሎታል ። አምስቱ ጃክሰኖች የተለያዩ የሙያ ባለቤት ሲሆኑ በሚገናኙበት ጫት ቤት ውስጥ የማያነሱትና የማይጥሉት ርዕሰ ጉዳይ የለም ። እውቀት ጠገብ / ለምሳሌ ከታሪኩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው የአውሊያ ጉዳይ ተነስቶ አጥጋቢ ምላሽ ሲሰጡ ይታያል / ሆነው በሚፈልጉበት የስራ መስክ መሰማራት ያልቻሉትን የሀገራችንን ምሁራን ይወክላሉ ። ተጠየቃዊ ሙግቶች የክብርና የአደባባይ አጅንዳ ከመሆን ይልቅ በየስርቻው የሚጣሉ የጋን ውስጥ መብራት መሆናቸውንም ያሳያል ።

« በፍቅር ስም » በጥቅል ገጸባህሪያት አደረጃጀት ውስጥ ነው የሚያልፈው ። ጥቅሉ እየተፈታ የሚሰበሰብ ፣ እየተሰብሰብ የሚፈታ ነው ። ጥቅሉ ለታሪኩ መጓጓዣ ምንጣፍ ነው ። የጎሉ ተናጥላዊ ባህሪያት ቢኖሩ እንኳ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ጥቅል ውስጥ እንደቀንዳውጣ ወጣ ገባ ማለታቸው አይቀሬ ነው ። ደራሲው ተናጥላዊ ባህሪያትን አጉልቶ ለመለየት የማይረሳ ምልክት ለጥፎባቸዋል ። ለምሳሌ አቶ ቢዘን ባወሩ ቁጥር ‹ ጣ › ይላሉ ። ቹቹ ‹ ቲሽ ! › ማለት ይቀናታል ። የታለ እናት ‹ ኦሆሆይ › በማለት ግርምታቸውን ይተነፍሳሉ ። ሻምበል ሲጠይቅም ሲመልስም ‹ ጥሩ › ን ያስቀድማል ።

እንደ ጥቅልም እንደተናጠልም የሚታየው ታለ ማነው ? ምን ይፈልጋል ? ስንል ወደ ጭብጡ መንደር እንደርሳለን ። በዚህም ረገድ ጥቅል ጉዳዮች ይገኛሉ ። ወንዳወንድነትን ማግኘት በዋናነት ደግሞ አውሊያና ጥንቆላን መዋጋት ። ታለ ህብረተሰቡ « ሴታሴት » ነህ ብሎ ስለፈረደበት ከዚህ የጅምላ ንቀትና ተጽእኖ ለመላቀቅ ያላሰለሰ ትግል ያከናውናል ። ህበረተሰቡ ተፈጥሮውን ተቀብሎ እንኳ እንዲኖር አልፈቀደለትም ። ወንዳወንድ እንዲሆን የተመረጡ ወንዶች ጋር ይውላል ። ወታደር በመሆንና በመሞት ወንድነት የሚገኝ ከሆነ እዘምታለሁ እስከማለት የደረሰ ነው ። የህብረተሰቡን ጥያቄ የተቀበለው ግን ራሱ ህብረተሰቡን በመንቀፍ ነው ። ነቀፌታው ገደብ የለውም እናቱን ፣ አባቱን ፣ ጃክሰኖችን ፣ ሲፈንን ፣ እህቶቹን ፣ ቹቹን ሳይቀር ይተቻል - ያሽሟጥጣል ። ድንኳን መትከልና መንቀል የወንድ ንፍሮ መቀቅልን የሴት ስራ ያደረገው ማነው ? ይላል ። የእንስሣት ሴታ ሴት ይኖር ይሆን እያለ ደግሞ ፈጣሪውን ይሞግታል ።

በሌላ ፊቱ በጥንቆላና ድግምት የእኔን በሽታ ወደ ቹቹ አዙራ ለጥፋተኝነትና ለጸጸት የዳረገችኝ እናቴ ናት በማለት ከእናቱ ጋር የስነልቦና ጦርነት ያካሄዳል ። ሲፈንም ፍቅረኛዬ ሳትሆን በእናቴ እኔን ታገልግል ዘንድ የተመረጠች አውሊያ ናት ብሎ ያምናል ። ሻምበል ይህን ቤተሰባዊ እምነት በማስቀየር የቹቹ በሽታ የአእምሮ ዝግመት ችግር መሆኑን ቢነግረውም አይቀበልም ። ስንት የታገለችለትን እናቱን ፊት ይነሳል ። በርግጥ አውሊያ ልክ እንደ አፈሳው ምን ያህል በሰፈርተኛው እንደሚፈራ እንገነዘባለን ።

ደራሲው በፍቅር ስም ፍቅር አልባ መሆን አለ የሚል ይመስላል ።

Wednesday, August 16, 2017

የኛ ሰፈር ቡሄ ባለ ማርሽ ነበር

ፎቶ ሸገር ብሎግ
ገና ሀምሌ ሲገባደድ ነው የቡሄ መነቃቃቶች የሚፈጠሩት ፡፡ ሂሳብ ላይ ከፍ ያለ ክፍያ እንዲደርሰን በማሰብ ቡድኑን በስድስት ቢበዛ በስምንት አባላት እናዋቅረዋለን ፡፡ ከስብስብ ምስረታ ቀጥሎ የሚመጣው የዱላ ዝግጅት ነው ፡፡ ዱላ ለመቁረጥ የምናመራው ‹‹ ዝንጀሮ ገደል ›› ወደተባለው አካባቢ ነው ፡፡ ዛሬ አካባቢውን  መኖሪያ ቤቶችና የድንጋይ ካባ ተቋማት ከበውት አንድም ዛፍ አይገኝም ፡፡  ዱላው ተቆርጦ ከደረቀ በኃላ ቆርኪ እየጠፈጠፍን ‹‹ ክሽክሽ ›› እንሰራለን - ማድመቂያ ፡፡

የማታ ማደሪያ መምረጥም  ዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ የሚካተት ነው ፡፡ ቤቱን ስንመርጥ የቤቱን  ስፋትና የወላጆችን  ባህሪ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ፡፡ ምክንያቱም ማታ ከመተኛት ይልቅ መተራረብና መሳሳቅ ስለሚበዛ ‹‹ ቁጫጭ ሁላ ! ዝም ብለህ አተኛም ! ›› ብሎ የሚያስፈራራንን አባወራ እንዲኖር አንፈልግምና ፡፡ ዳቦና ገንዘብ ያዥም ከወዲሁ ይመረጣል ፡፡ ዶቦ ያዥነትን እንደ ሸክም ፣ ገንዘብ ሰብሳቢነትን  እንደ ስልጣን ስለሚመነዘር ምርጫው ተቃራኒ ገጽታዋችን ማስተናገዱ ግድ ነው  ፡፡

ዛሬ ላይ ሆኜ  ጭፈራችንን ስፈትሸው የድራማ ስልት እንደነበረው ይሰማኛል ፡፡ ያልደከመ ጉልበታችንን  አስቀድመን የምንጠቀመው በሀብታሞች ቤቶች ላይ ነበር ፡፡

‹‹ መጣንኖሎት በዓመቱ  እንዴት ሰነበቱ / 2 ግዜ /
ክፈት በለው በሩን - የጌታዬን / 2 ግዜ /

በሩ የብረትም ሆነ የቆርቆሮ እየጨፈርን በዱላችን እንደበድበዋለን - ስሙን ማለታችን ነው ፡፡ አንዳንድ ተንኮለኛ ደግሞ መጥሪያውን ሊያስጮኀው ይችላል ፡፡ አሁን ውሾች ካሉ እንደ ጉድ ይጮሃሉ ፡፡ ክፉ ጥበቃ ካለም እንደ ውሾቹ እየጮኀ መጥቶ ከአቅማችን በላይ የሆነ ስድብ ያሸክመናል ፡፡ ‹‹ መናጢ የድሃ ልጅ ! በር ስበር ተብለህ ነው የተላከው ?  መጥሪያው ቢበላሽ አባትህ መክፈል እንደማይችል አጥተኀው ነው ፡፡ ሂድ ጥፋ ከዚህ ! ሰበበኛ ሁላ ! ››  ቆሌያችን እንደ ውሻ ጭራ በፍርሃት ይጣበቃል። ደግነቱ የዚህ ተቃራኒ አለመጥፋቱ  ፡፡ አዝማሚያው ደህና መሆኑን ካረጋገጥን  አሁን አንደኛ ማርሽ እናስገባለን ፡፡
 « … የኔማ ጋሼ
  ሆ.. !
  የተኮሱበት
  ስፍራው ጎድጉዶ
  ሆ.. !
  ውሃ ሞላበት
  እንኳን ሰውና
  ሆ.. !
  ወፍ አይዞርበት !
 እያልን እስከታች እንቀጥላለን ፡፡ ብዙ ካስለፈለፉንና ‹ ተወው ጮሆ ጮሆ ይሄዳል › እያሉ የሚያስቡ መስሎ ከተሰማን የጭፈራችን መልዕክት ይቀየራል ፡፡ ሁለተኛ ማርሽ እናስገባለን ማለት ነው ፡፡

‹‹ ላስቲክ ተቀብሮ አይበሰብስም
 አንዴ መጥተናል አንመለስም ::
 አባባ ተነሱ ኪስዋትን ዳብሱ !! ›› በማለት  በአንድ በኩል ጠንካራ መሆናችንን እያሳየን በሌላ በኩል ትዕዛዝ ብጤ እናስተላልፋለን ፡፡ መቼም አንዳንድ ሰው ግድ ስለሌለው ወይም ማስለፍለፍ ስለሚወድ ድምጹን ያጠፋል ፡፡ አሁን ገሚሱ እንሂድ ሲል ሌላው በቀላሉ አንለቅም በማለት ይከራከራል ። ብዙ ግዜ እነዚህን አስተያየቶች የሚያስታርቁ ሀሳቦች ያሉት ይመስለኛል  - ቡሄ ፡፡ አስታራቂው ሀሳብ የጨፋሪውን መዳከም የሚጠቁም ይምሰል እንጂ በንዴትና በምሬት ነው የሚገለጸው ፡፡ እናም  ንዴታችንን ለማፍጠን ሶስተኛ ማርሽ  እንጠቀማለን ::

‹‹ እረ በቃ በቃ
  ጉሮሯችን ነቃ
 በዚህ ማርሽ ተፈላጊው ውጤት ካልተገኘ የኃላ ማርሽ በመነጫነጭ ይገባል ፡፡

 ንጭንጭ አንድ !
 ‹ ይራራ ሆድዋ - እግዜር ይይልዎ ! › ሊል ይችላል አንዱ ቅኝቱን እንደጠበቀ

 ንጭንጭ ሁለት !
 ‹ አለም አንድ ነው የለም አንድ ነው  እኛን ማስለፋት የሚያሳፍር ነው › ማለትም የተለመደ ነው ፡፡ ከብዙ ልፋት በኃላ ስጦታው ከተፍ ካለ ደስታችን ወደር ያጣል ፡፡ ሳናውቀውም ማርሹ አራተኛ ገብቷል ፡፡

‹‹ አመት አውዳመት
  ድገምና
  አመት
  ድገምና
  የጋሽዬን ቤት
  ድገምና
  አመት
  ወርቅ ያፍስስበት
  እንዲህ እንዳለን
  ሆ …!
  አይለየን !!
  ክበር በስንዴ
  ክበር በጤፍ
  ምቀኛ ይርገፍ !! ›› በማለት እየተሳሳቅን ውልቅ ነው ፡፡ ወደሌላኛው ቤት ስንጓዝ በመሃሉ የምንጠቀመው የጭፈራ ስልትም አለ ፡፡ ‹‹ አሲዮ ቤሌማ ›› የሚባል ፡፡ የሬዲዮ ጋዜጠኞች ይህን ዓይነቱን መሸጋገሪያ ‹‹ ብሪጅ ›› ይሉታል ፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ሞራል ማነቃቂያ መሰለኝ የምንጠቀምበት ፡፡ የምንጨፍረው እየሮጥን ነው ፤ በል ሲለን ዱላችንን ርስ በርስ እናጋጫለን ፡፡ ምናልባት ሳናውቀው ከመስቀል ጨፋሪዋች ያጋባነው ሊሆንም ይችላል ፡፡ ብቻ ዛሬ ድረስ የማይገቡኝ ቃላቶች አሉበት ፡፡

‹‹ አሲዮ ቤሌማ
  ኦ … ኦ
  አህ እንበል
  አሲዮ ቤሌማ
  ቤሌማ ደራጎማ … ›› ለአብነት ያህል ‹ ደራጎማ › ግጥሙ እንዲመታልን የተጠቀምነው ቃል ነው ወይስ ትርጉም አለው ? 

የቡሄ ዕለት ሲርበን ለምሳ ወደ ቤት መሄድ የማይታሰብ ነው ፡፡ ዳቦ ክፍሉ በጎተራው ያለውን ንብረት ያሳውቅና እንከፋፈላለን ፡፡ ዳቦ እንኳን ባናገኝ ካላቸው ላይ ገዝተን ነው የምንበላው ፡፡ አንድ ክረምት ላይ ዝናቡ ዳቧችንን አሹቆት ነበር ፡፡ በጣም የራባቸው ዳቦውን እንደ ጨርቅ ጨምቀው የቀማመሱበት ሁኔታ ነበር ፡፡ ወደ ኃላ እየቀረ ዳቦውን በጥርሱ እየከረከመ የሚያስቸግረን ባልደረባም ነበረን ፡፡ በንዴት ስንጮህበት ‹ እንዲሁ ነው የተረከብኩት ! › ብሎ ይሸመጥጣል ፡፡

 ገና ‹‹ የወንዜው ነበረ ›› ስንል ‹‹ ነብር ይብላህ ! ›› በማለት የሚያባርሩን ሰዋች እንደው ራሳቸው ከነብር ካልተሰሩ በስተቀር በአውዳመት ይህን እኩይ  ቃል መጠቀማቸው ይገርመኛል ፡፡ ለረጅም ሰዓት ከኛ ጋር ግቢው ውስጥ ጨፍሮና አስጨፍሮን  ‹‹ በሉ የዓመት ሰው ይበለን ፤ ያኔ ደግሞ ከዚህ በላይ እንጨፍራለን ›› ብሎ በነጻ የሚሸኘንም ሰው ነበር ፡፡ ያኔ በሳቅ ከመፍረስ ጎን ለጎን ዞር ብለን በተረብ ቀዳደን እንጠለው ነበር

 ‹‹ ምናባቱ ድሮ ሳይጨፍር ያለፈበትን ግዜ በኛ ያስታውሳል እንዴ ?! ብሽቅ ! .. ገገማ ! … ጥፍራም ! … ሽውደህ ሞተሃል ?! … ›› በዛሬ ዓይን ሳስበው ግን ‹ ምን ዓይነት ፍቅር ያለው ሰው ነው ?  › እላለሁ ፡፡ አደገኛ ውሻ ለቀውብን  ስንፈረጥጥ በሳቅ ብዛት የሚሰክሩትም ጥቂት አይደሉም ፡፡ በጣም የሚገርመው ከመታ የሚገላግለውን ወጠምሻ ዱላ አዝለን ከሩጫና ፍርሃት መገላገል አለመፈለጋችን ነው ፡፡ ማታ ላይ ጉዳዩ ተነስቶ ስንተራረብ ‹ እኔ የሮጥኩት ወሻውን ሳይሆን ባለቤቱን ፈርቼ ነው › በማለት እናስተባብላለን - እንዲም አድርጎ ሽውዳ የለም ፡፡ ዞሮ ዞሮ የተፈጸመብንን ግፍ ወደሌላው በማጋባትም እንታወቃለን ፡፡ ሌላ የጨፋሪ ቡድን መንገድ ላይ ስናገኝ ‹ እዛ ቤት 10 ብር አግኝተናል › በማለት ወደ ውሻው ቤት እንዲሄዱ እንጠቁማቸዋለን ፡፡ ከዛ በተራችን ራቅ ብለን የአዳኝና ታዳኝ ትርዒቱን በሳቅ እያጣቀስን መኮምኮም ነው ፡፡

 ማታ ስንተኛ የቀኑን ውሎ እያስታወስን የምንስቅበት፣ የምንተራረብበትና የምንገማገምበት መድረክ ነው ማለት ይቻላል ፡፡ የሁላችንም ዱላ ስሩ ይታያል ፤ መሬት ሲደበድብ ስለሚውል ተቸርችፎ የተጠቀለለ ሉጫ ጸጉር ይመስላል ፡፡ ይህ የጸጉር መጠን አነስተኛ የሆነበት መሬቱን በደንብ ስለማይመታ ለጋሚ ነው ተብሎ ይተቻል ፡፡ ድምጽም ሌላው መመዘኛ ነው ፡፡ በደንብ ሲጮህ የዋለ ድምጹ እንደ አለቀ ባትሪ መነፋነፉ ይጠበቃል ፡፡ ብዙም ያልተለወጠ ከተገኘ ‹ በእኛ ላይ ሲያሾፍ ስለነበር ክፍፍሉ ላይ ዋጋውን ያገኛል ! › ይባላል ፡፡ 

ታዲያ በማግስቱ ያ - ሰው እኔ ካላወጣሁ እያለ ሲያሸብር ይውላል ፡፡ በደንብ ማውጣት የማይችሉ አባላትም ሌላው የመዝናኛ ገጸ በረከቶች ናቸው ፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ መጣንሎት በዓመቱ እንዴት ሰነበቱ ›› የምትለውን የመግቢያ ስንኝ ከጨረሰ በኃላ በምን ዓይነት ዝላይ እንደሆነ ሳይታወቅ የመጨረሻውን ‹‹ እረ በቃ በቃ ጉሮሯችን ነቃ ! ›› ላይ ፊጢጥ የሚል ያጋጥማል ፡፡ በስንት ህክምናና ስለት ልጅ እምቢ እንዳላቸው እያወቀ ‹‹ ይራራ ሆድዋ እረ በልጅዋ ! ›› የሚል ልመና በማቅረብ እኛን ለመጥፎ ሳቅ ሰዋቹን ለማሳቀቅ የሚዳርግም  አይጠፋም ፡፡ አንዳንዴ ወደማናውቀው ሰፈር ጥሩ ብር ለመስራት ሄደን በሰፈሩ ጉልቤዋች የ ‹ ኮቴ › ተብሎ የምንቀማበት ሁኔታ ያጋጥማል ፡፡ ይህ ጉዳይ ከተፈጸመ  ማታ ብዙውን የክርክር ጊዜ ሊወስድብን ይችላል ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሚወቀሰው ግን ራሱ ገንዘብ ያዡ ነው ፡፡

 ‹ ከርፋፋ ! ገንዘቡን ዝም ብለህ  ሜዳ ላይ ታስቀምጠዋለህ ?! › ሊባል ይችላል ፡፡ አንድ ሰው ገንዘብ ያዥ ሆኖ ሲመረጥ የራሱን ጥበብ መዘየድ ይኖርበታል ፡፡ ገንዘቡ በጉልቤዋች ሊበረበር ይቻላል በሚል ስጋት የሱሪው እግር አካባቢ፣ ኮሌታ ስር፣ በቀበቶው ማድረጊያ የውስጥ ክፍል ወይም በሌላ አሳቻ ቦታ ሰፍቶ በመደበቅ የማምለጫ ፋይዳዋችን ማስፋት አለበት እንጂ በድንጋጤ ንብረቱን ማስረከብ የለበትም ፡፡ ሌላው ቢቀር የተወሰኑ ወፍራም ቡጢዋችን ቢቀምስ እንኳን ‹ እረ ገና አልሰራንም ! › ብሎ መሸምጠጥ ይጠበቅበታል ፡፡

 በማታው ክፍለ ግዜ አባላቱ እየተንጫጩ ራሱን ዜሮ ማርሽ ላይ አቁሞ በጸጥታ የሚሰምጥም አይጠፋም ፡፡ ለመሆኑ የዝምታው ምንጭ ምን ሊሆን ይችላል ?  በአብዛኛው ሶስቱ ናቸው ። እዳ ፣ ነጠቃ እና ግርፊያ ::

እዳ … የሚፈጠረው በብይ ወይም በጠጠር ጨዋታ ነው ፡፡ በክረምት ገንዘብ ከሌለን ጨዋታው ሞቅ እንዲል በሚል በዱቤ እንጫወታለን - ለቡሄ ለመክፈል በመስማማት ፡፡ ብዙ የማይችሉት ታዲያ ከአሁን አሁን እናስመልሳለን እያሉ እዳው ጣራ ይነካባቸዋል  ፡፡ እናም ያስባል ፤  ብሩን አስረክቤ ቤት ምን ይሉኛል ? ድጋሚ አቤቱታ ልጠይቅ ? ልካድ ? ብክድ ምን ይመጣብኛል ? ….

 ነጠቃ … የምንለው ደግሞ በጉልቤ ቤተሰቦች የሚከናወን ነው ፡፡ ለስለስ ባለ አነጋገርና የጭንቅላት ዳበሳ ሁለት ቀን ጨፍሮ ያገኘውን ብር ይቀመጥልህ አይደል ? ይባላል … ኮስተር ባለ ግንባር ልጅ ገንዘብ ከለመደ ዱሩዬ ይሆናል ! ይባላል …  ዲፕሎማት በሆነ መንገድ አበድረኝ ሊባል ይችላል … ብቻ በብሩ እንደሌሎች የፈለገውን ማድረግ ስለማይችል የማምለጫ መንገድ ፍለጋ በሃሳብ ይኳትናል ፡፡

 ግርፊያ … የሚመነጨው ከሃርደኛ አባቶች ነው ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹ መጨፈር አንሶህ በዓመት በዓል ሰው ቤት ምናባህ ያሳድረሃል ?! › የሚል ነው ፡፡ በጨፈረበት ዱላ የሚወቀጥ … ባገኘው ገንዘብ በርበሬ ገዝቶ የሚታጠን … ያጋጥማል ብሎ መውሰድ ይቻላል ፡፡

 ብቻ ምንም ሆነ ምን  ባለ ማርሹ ቡሄ ደስታው የላቀ ነው ፡፡ በቡሄ  ገንዘብ ከማግስቱ  ጀምሮ እንቁጣጣሽን አንቨስት ማድረግ እንጀምራለን  ፡፡ ወረቀት ፣ ንድፍ ፣ ቀለም  ይገዛል ፡፡ የወቅቱ የእግር ኳስ ኮኮቦችና ሁሌም ቋሚ ተሰላፊ የሆኑትን መላዕክቶች በመኳል እንደሰታለን ፡፡ እናም ቡሄ ባይኖር ኖሮ እንቁጣጣሽ ይከብደን ነበር ፡፡ ኢንቨስት የምናደርግበትን ገንዘብ ማን ይሰጠናል ?


Monday, August 14, 2017

ከለንደኑ ውድድር ያተረፍናቸው ሽሙጥ እና ግጥሞች


የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዝናንቶን አለቀ ። ኢትዮጽያን የወከለው ቡድን ሁለት ወርቅና ሶስት ብር አጥልቆ በሰባተኛ ደረጃ ውድድሩን ጨርሷል ። ከለንደን ያገኘነው ግን ሜዳሊያ ብቻ አይደለም - ሽሙጥና ቅኔዎችም ጭምር እንጂ ። በመንፈስ አብሮ ሲሮጥ የነበረው ኢትዮጽያዊም ሲበሳጭ በሃይለቃል ፣ ሲደሰት በግጥም ግራ ሲጋባም በጥያቄ ሀሳቡን በማካፈል የማይናቅ ሚና ተጫውቷል ።

ሀገራዊ ሽሙጥ

ንዴቱ የጀመረው ገንዘቤ ዲባባ ያልተጠበቀ ውጤት ባስመዘገበችበት ወቅት ነበር ። ይቺ ብርቅ አትሌት የባለብዙ ሪክርድ ባለቤት መሆኗ ይታወቃል ። በየግዜው ሪከርድን እንደ ፋሽን ከመቀያየሯ አንጻር በለንደን ያጋጠማትን ሽንፈት ለመቀበል አስቸጋሪ ነበር -ለብዙዎች ። ከገንዘብና ከሀገር ፍቅር ስሜት ጋር በማያያዝ ሽሙጡ ፣ ስላቁ እና ዝርጠጣው ተወረወረ ። ቀስቱን ሊመክቱላት የተጉ ሰዋች ቢኖሩም ስሜቷን ከመሰበር አላዳነውም ።

ስምን መልአክ ያወጣዋል የሚል ስነቃል ወርውሮ ገንዘቤን ከገንዘብ ... አልማዝን  ከእንቁነት ጋር ብቻ ማዛመድ ኢትዮጽያዊ ፍርድ ቤትን መምሰል ነው የሚሆነው ። ፍርደ ገምድልነት ግዜያዊ ቁጣና እብሪትን ያበርድ ከሆነ እንጂ ከኋላ የተቆለለውን እውነት አይሸፍነውም ። ወርቅ የመራብ ጉጉት ታላቁን በረከት መሸፈን አልነበረበትም ። ዓለምን በተደጋጋሚ ድል ጉድ ያሰኘው እግሯ ቢሆንም እጆቿም ባንዲራን በማውለብለብ የገጽታ ግንባታን ያለ ገደብ ገንብተዋል ። አለም በብቃቷ ተማርኮ ንግስትና ጀግና ያደረጋትን አትሌት በምንም ሃይል ከከፍታዋ ላይ ማውረድ አይቻልም ። አጉል ግራ መጋባት እንጂ ።

ይልቅ በአደጋገፋችን ላይ የሚሰነዘረውን ሽሙጥ መመርመር ብንችል ማለፊያ ነበር ። አንድ አትሌት ኢትዮጽያን ወክሎ ከሀገር ይወጣል ፣ መንገድ ላይ ግን በብዙ ባንዲራዎች ይደገፋል ። የውጭ ሀገር ሰዎች የተለያየውን ባንዲራ እያዩ አንተ ከየት ነህ ? ለማነው የምትደግፈው እያሉ ይጠይቃሉ ። ባንዲራ ለባሹ በኩራት ይመልሳል ። ታዛቢው ኢትዮጽያ ስንት ባንዲራ ነው ያላት ? ስንት ስያሜ ነው ያላት ? መጀመሪያ እየተደናበረ ቆይቶ ደግሞ እያሽሟጠጠ ይጠይቃል ። መላሹ እየተቆጣ ይመልሳል ። ይኅው አዙሪት እንደቀጠለ ነው ።
ግራ የገባው ሰው ምንኛ ታደለ
ቀኝም ሆነ ግራ ያልገባው ስንት አለ - ይልሃል አሽሟጣጩ ስንኝ ...

ግጥም
‹ የማይሸነፈው › ሞ ፋራ በዮሚፍ ቀጀልቻ በር አስከፋችነት ለሙክታር እድሪስ እጅ የሰጠ ግዜ ደግሞ አሽሙረኛው ሁላ ገጣሚ ሆኖ ቁጭ አለ ። ግጥም እንደ ጉድ ዘነበ ። ስድ ንባብ በደስታ ወቅት ዋጋ ቢስ ነው ለካ ? የህዝቡ እምቅ ችሎታ አፍጥጦ ወጣ ። ማን ያልገጠመ ማን ጥቅስ ያላመነጨ አለ ? የፌስ ቡክ ግድግዳዋች ከአጫጭር ግጥሞች ጎን ለጎን በፉከራዎችና ሽለላዎች ደመቁ ። እናት ሀገርም በግልባጭ ሞገስና ውዳሴ አገኘች ። ነባር የፌስ ቡክ ገጣሚዋችም ቅኔ ዘረፉ

ጥረትና ድካም
ካልታየ በስራ
ለአራዳም አልሆነ
እንኳንስ ለፋራ አሉት ።

በርግጥ በሌላኛው ጠርዝ የሚገኘው ህዝብም ለሞ ፋራ ብልጥ የሆኑ ስንኞችን ከመጠር ቦዝኖ አያውቅም ።

Born in Somalia
Trains in California
Arsenal fan, a Gooner
Running in Londinium
A superstar, a Muslim
Cheered by the Whole stadium

አለማቀፋዊ  ሽሙጥ
አልማዝ አያና አንድ ወርቅና አንድ ብር በማሸነፍ በሰሌዳ ደረጃችን ላይ ትልቅ ሚና ተጫውታለች ። አልማዝ ፣ ወርቅ ፣ ብር ደስታዊ ትስስሮሽ በመፍጠሯ ህዝቡ ወስጥ እንቁነት ፈጥራለች ። በበጎ ያዩዋት ሁሉ የአስር ኪሎ ሜትሩን ሩጫ ተአምር ነው ብለዋል ። ለ 11 ወራት ከሩጫ ርቃ ከሶስት አትሌቶች በስተቀር ሁሉንም ደርባ ማሸነፍዋ አጀብ የሚያሰኝ ነው ። የብዙዎቹን አትሌቶች የግል ሰአት እንዲሻሻል ምክንያት መፍጠሯ እና በ 46 ሰከንድ ርቃ ማሸነፏ የውድድሩ ክስተት ነበር ።

የአልማዝ ውጤት ያልተዋጠላቸው ግን ጥቂቶች አልነበሩም ። ለምሳሌ የአውስትራሊያ የሶስት ግዜ ሻምፒዮናና አሰልጣኝ ሊ ትሩፕ አለማቀፉን ፌዴሬሽን በመውቀስ ውድድሩ ቀልድ እንደሆነ ጽፏል ። የስኮትላንድ ረጅም ርቀትና የጎዳና ተወዳዳሪ የነበረችው ኤልሳቤጥ ማኮልገን ውጤቱን እንደማትቀበለው ገልጻለች ። ሌሎችም በድረ ገጻቸው የአልማዝን ተአምረኛ እግሮች እንደሚጠራጠሩት ጽፈዋል ። በሪዮ አኦሎምፒክ ለቀረበላት ተመሳሳይ ጥያቄ የኔ ዶፒንግ ስልጠና እና ፈጣሪ ነው ብትልም ዘንድሮም ሆያሆዬው አልቀረላትም ።








LIZ mccolgan @Lizmccolgan

So from 3k to 8 k Ayana 5 k split 14:30. Until Ethiopia follow proper doping procedures i for one do not accept these athletes performances


Well they might. But I would suggest the issue is broader than simply a country. It's who trains there & how often they're tested OOC? 

Won't she be tested tonight? Why pin the blame on a country then international testing is in place? Does the UK test Mo?
 But you cheer on Farah, who has hidden with Jama Aden several years?

የዚህ ሽሙጥ ፍላጻም ወገንተኛውን ሚዲያ ያጥበረበረው ይመሰለኛል ። በሚዲያ ሽፋን ቦልት እንጂ ጀስቲን ጋትሊን አዲስ ጀግና አልሆነም ። ጀግናውን ሞ ፋራ ላቆመው መሃመድ በቂ ነገር አልተሰራም ።

ሌንሱን ሞ ፋራህና ቦልት ላይ ብቻ አነጣጥሮ ብዙ ሊመረመርና ሊባልበት የሚገባውን የአልማዝ ልዩ ስትራተጂ በዝርዝር መቃኘት አልፈለገም ። ለአዲስና ልዩ ለሆነ ዘዴ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚያከራክረውና የሚያመራምረው አለማቀፍ ሚዲያ እሱም አሽሟጣጭ ካልሆነ በስተቀር ጉዳዩን ችላ የሚልበት መንገድ ግልጽ አይደለም ።

የአልማዝ የ 10ሺህ ሜትር ስልት የእሷ ብቻ ምልክት ነው ወይም ስልታዊ ሪከርድ ነው ። ይህን ልዩ ስልት ሌሎች አትሌቶች እንዴት እውን ማድረግ ይችላሉ ? ነው ይህን ስልት መከተል አዋጭ አይደለም ? በተወዳዳሪነትና ልብ አንጠልጣይንት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ እንዴት ይታያል ? ምክንያቱም አንድ ሰው ገና ከጠዋቱ ቀድሞ ወጥቶ ማሸነፍ ከቻለ ተመጣጣኝ ውድድር እና አጓጊንት ይኖራል ለማለት ያስቸግራል ። ብዙ ሊጠናበት ግድ ቢልም ሚዲያው ሸውራራነትን መርጧል ። አሰልጣኞች የጉዳዩ ባለቤት ከመሆን ይልቅ ቅንድባቸውን መስቀል ፈልገዋል ።


ድንቄም ... ?! አለ አሽሟጣጭ

Thursday, August 3, 2017

የድርሰት ሰማይን ያደመቁ ብዕረኛ

ደራሲ አማረ ማሞ ብዙ አልተባለላቸውም ። ግን ለስነጽሁፍ ብዙ ሰርተዋል ፤ በእጅጉ ደክመዋል ። እጣ ፈንታ ሊሆን ይችላል ። አንዳንድ ያደለው በአንድ ጥሩ ስራ ስማይ ላይ ሊወጣ ይችላል ። የዚህ አይነቱ እድለኛ ባለቲፎዞም ስለሚሆን ክበባቱ ፣ ሚዲያውና ማስታወቂያው እንኮኮ ያደርገዋል ።

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ደራሲ፣ አርታኢና ተርጓሚ አማረ ማሞ ማናቸው ተብሎ አልተመረመሩም ። እኚህ ሰው ስነጸሁፍ ፍቅራቸው ብቻ ሳይሆን ህይወታቸው በመሆኑ ኖረውብታል ማለት ይቻላል ። የኢትዮጽያ መጻህፍት ድርጅት ስነጽሁፍንና ደራሲዎችን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ተጫውቷል ። እሳቸው ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ ም/ስራ አስኪያጅ ነበሩ ።

በድርጅቱ አሳታሚነት ለንባብ ይበቁ የነበሩ መጻህፍትን የሚያስታውስ አንባቢ የአቶ አማረን ድርሻ በአግባቡ ለመረዳት አያዳግተውም ። የነባርና እጩ ደራሲዋችን የአሳትሙልኝ ረቂቅ ጽሁፎችን በመለየት ፣ የተለየውን ደግሞ የአርትኦት ስራ በማከናወን በድርሰት ላይ የማዋለድና ጥሩ ቁመና የመፍጠር ህክምና አበርክተዋል ።

እንዴት ላሳትም ወይም በምን መልኩ ልጻፍ ወይም የመሳሰሉ ጥያቄዋችን አንግቦ ቢሯቸው ጎራ የሚሉትን ጥበብ አፍቃሪዋች ውሃ የሚያነሳ ምላሽ ለመስጠት አያነቅፋቸውም ። የኢትዮጽያ መጻህፍት ድርጅት ከስራ ውጪ ከሆነ በኋላ እንኳ አቶ አማረን ኪነጥበባዊ እድሞሽ ላይ ማግኘት ቀላል ነበር ። በስነጽሁፋዊ ውይይቶችም ሆነ ህትመት ምርቃቶች ላይ ከፊት በመገኘት ልምዳቸውንና ሃሳባቸውን ሳይሰላቹ አጋርተዋል ።

አቶ አማረ የበርካታ መጻህፍት ደራሲና ተርጓሚ ናቸው ። ዶን ኪሆቴ ፣ አሳረኛው ፣ እሪ በይ ሃገሬ ፣ የእውነት ብልጭታ ፣ የቀለም ጠብታ እና የልብ ወለድ ድርሰት አጻጻፍ የተስኙ ስራዋችን በጥቂቱ መጠቃቀስ ይቻላል ።

እውነቱን ለመናገር የልብ ወለድ ድርሰት አጻጻፍ የተሰኘው ስራቸው ብቻ ሽልማት የሚገባው ነው ። በ1960ዎቹ የታተመው ይህ ስራ የብዙ ድርሰት አፍቃሪያንን አይኖች የገለጠ ነው ። እንደሚታወቀው ኮሌጅ/ዩኒቨስቲ የመግባት እድል ያላጋጠማቸው የሀገራችን ደራሲዎች ጥቂቶች አይደሉም ። ብዙዎቹ ታዲያ መጽሀፉን እንደ አንድ ተቋም ክብር በመስጠት የልቦለድ ባህሪና ምንነትን እንዲሁም እንዴት መቀሸር እንደሚገባው የተረዱት ይህን መጽሀፍ በማንበብ ነው ። ለመጽሀፉ ምስጋና ይግባውና ጠንካራ ምናብና ብእር ያላቸው ደራሲዎች መፈጠር ችለዋል ።

ይህ መጽሀፍ ድንበር ያጠረው አልነበረም ። ሌላው ቀርቶ በኮሌጆችና/ዩኒቨስቲዎች ለስነጽሁፍ ትምህርት አጋዥ በመሆን ለመምህራኑም ሆነ ለተማሪዎች ትልቅ ግብዓት ፈጥሯል ። በነገራችን ላይ የራሳቸውን ማንዋል አዘጋጅተው ወይም አጋዥ ስራ አሳትመው የሚያስተምሩ ውለተኛ መምህራን ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው ። የቲያትር ኮርስ ሲሰጥ የፋንታሁን እንግዳ የተውኔት መጽሀፍ ነው ትልቅ ድርሻ የሚወስደው ። ተማሪ እየተናጠቀ ኮፒ ለማድረግ ይራወጣል ። በዚህ ረገድ ደበበ ሰይፉና ዘሪሁን አስፋው የሚታሙ አይመስለኝም ። ርግጥ ነው ብርሃኑ ገበየሁም ኋላ ላይ ተቀላቅሏል ። መሰረታዊ ስነጽሁፍ ለኮሌጅ ተማሪዋች በተለይ የአፍሪካ ስነጽሁፍን አስመልክቶ ግን ብዙ ያልተዘመረለት መምህር አለ ። መክነህ መንግስቱ የሚባል ። ርግጠኛ ባልሆንም ከኮተቤ ወደ ዩኒቨርስቲ የተዘዋወረ ይመስለኛል ። በርካታ ድርስት ነክ ስራዎችን በእንግሊዘኛ ቋንቋ አሳትሟል ። ተማሪዎችም የእሱን ስራዎች መነሻ በማድረግ የአፍሪካን ስነጽሁፍን ለማወቅና ለመመርመር አግዟቸዋል ።

የአቶ አማረ ስራ ግን ኮሌጅ ለረገጠውም ላልገባውም ፣ ለጀማሪውም ለመምህራንም ፣ ለስነጽሁፍ አድናቂም ለተመራማሪውም ዛሬም ድረስ የውለታ ሃውልት ሆኖ ቆሟል ። እንግዲህ እዚህ ሃውልት ላይ ነው ሰሞኑን የክብር ካባ እና የወርቅ ብእር የተሰቀለው ። በሸላሚው ድርጅት ማለትም በንባብ ለህይወት የፌስ ቡክ ገፅ ላይ « አይናቸውን ያልጨፈኑ የድርሰት ሰማያችንን ያደመቁ ኮኮብ ሆነው ሆነው በመገኘታቸው የዓመቱ የወርቅ ብዕር ተበርክቶላቸዋል » የሚል ጽሁፍ ይነበባል ።

ግሩም ምስክርነት ሆኖ ስላገኘሁት ደስ ብሎኛል ። በርግጥም የድርሰት ሰማያችንን ለማድነቅ የተጉ በርካታ ጸሐፊያን አሉን ። አቶ አማረ ግን ኮኮቦቹ ከመታየታቸውም በፊት ጧፍ ሆነው ተገኝተዋል ። ብዙዎችን አርመዋል ... ኮትኩተዋል ... በርካቶችም የጧፉን ብርሃን ተከትለው  መንገድ አግኝተዋል ።


ንባብ ለህይወት በአጭር እድሜው አምባሳደር ዘውዴ ረታ ፣ አዳም ረታንና አማረ ማሞን የወርቅ ብዕር ተሸላሚ አድርጓል ። መልካም ጅምር ስለሆነ ለረጅምና ላልተቆራረጠ ጉዞ ብርታቱን እንዲሰጣችሁ እመኛለሁ ። ብርታቱ ግን እንደ አማረ ማሞ ብዙ ሰርተው ያልተነገረላቸውን ብዕረኞችን  ለማፈላለግ ጭምር እንዲሆን ማድረግ ይገባል ።

Wednesday, July 26, 2017

የጣና ነጋሪት መቼ ይጎሰማል ?


የህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 የውጭ ወረራ ሲያጋጥም  ፣ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት ፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የክልል መስተዳድሮች የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሊያውጁ እንደሚችሉ ይደነግጋል ።

ከላይ በተገለጸው አንቀጽ ውስጥ አራት መሰረታዊ ሀረጎች ጎልተው ይታያሉ ። የውጭ ወረራ ፣ የስርአት አደጋ ፣ የተፈጥሮ አደጋ እና የጤንነት አደጋ ።

መንግስት እስካሁን የተመቸው ሀረግ የ ‹ ስርአት አደጋ › ነው ። በዚህ ለመጣበት አይደራደርም ። በዚህ የመጣበትን በብዙ ጆሮዎች የመስማትና በብዙ አይኖች የመመልከት ችሎታ አለው ። ይህን አደጋ በወንበር የመማለል አደጋ ይለዋል ። እረ ጥሩ ጥሩ ዘይቤያዊ አነጋገሮችንም ይጠቀማል ። መንግስት እንደ ኢያሪኮ ግንብ በጩኅት አይፈርስም የሚላት ነገር አንደኛዋ ናት ... መንግስት እንደ ሾላ ፍሬ በድንጋይ አይወርድምም ይልሃል ... ሌላም ሌላ ጥብቅ ማሳሰቢያዎች አሉት ። የስርዓቱን አደጋ ለማነቃነቅና ለመጣል የተሞከረን ሀገራዊ ‹ ብጥብጥና ሁከት › ጸጥ ለማድረግ ይቻል ዘንድ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከታወጀ አያሌ ወራት ተቆጥረዋል ። ይህም የጥብቅ ማሳሰቢያው የመጨረሻ ደረጃ ነው ። ከዛሬ ነገ አዋጁ ይነሳል ሲባል የሰርዓቱ አደጋዎች ቅርጽ እና ይዘታቸውን እየቀየየሩ መፈልፈላቸው አሳሳቢ ነው ። አንዱ በአንዱ ቀለበት ውስጥ እየገባ ዛሬ የግብር አደጋ ተረኛ ጥያቄ ፈጣሪ ሆኗል ። እናም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ታፍሮና ተፈርቶ ለማይታወቅ ዘመናት ሊውለበለብ ይችላል ።

የአዋጅ ነገር ከተነሳ በተፈጥሮ አደጋም ተጨማሪ ክተት ያስፈልገን ነበር ። መንግስት የሚመቸውን ብቻ አዳማጭ ስለሆነ እንጂ የጣና በእምቦጭ አረም የመወረር አደጋ ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት የሚታዘዝበት ነበር ።

የመንግስትን ዳተኝነት የገነቡት ብዙ ምከንያቶች ሊሆኑ ቢችሉም ሁለቱን የጎሉ አስተሳሰቦች እንመልከት ። አንደኛው ችግሩን መፍታት ያለበት የክልሉ መንግስት ሲሆን ጉዳዩም ከክልሉ አቅም በላይ የሚዘል አይደለም የሚል ነው ። የክልሉ መንግስት ለበርካታ አመታት ሳይንሳዊ ውጤት ለማምጣት ባዝኗል ። ችግሩን መፍታት ቢኖርበት ይህን ሁሉ አመታት ያለ ተጨባጭ ነገር መራወጥ ባልተገባው ነበር ። እውነታው ግን የምርምርም ሆነ የገንዘብ አቅሙ ተፈላጊውን መፍትሄ ያስገኘለት አለመሆኑ ነው ።

ሁለተኛው መንግስታዊ አመለካከት የጣና ሃይቅ በአረም መወረር በውጭ ወራሪ መወረር አይደለም ወይም የተፈጥሮ አደጋ ነው ብሎ ለመቀበል የሚያስችል መደላድል የለም ከሚል ይመነጫል ። ሲጀመር ህገ መንግስቱ የተፈጥሮ አደጋ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አላሰፈረም ። ሌላው ቀሮቶ ‹ የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት › የሚለው ሀረግ አሻሚና ግልጽነት የሌለው ነው ። በሽታ የሚለው ተላላፊዎችን ነው ... በሽታ የሚለው ግዜ የማይሰጡትን ነው ... በሽታው ኮሌራ ነው ? ኢቦላ ነው ? ማጅራት ገትር ነው ? ... አይታወቅም

በመሆኑም የ « ተፈጥሮ አደጋዋችም » ሆኑ « ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ በሽታዋች» ን እውነተኛ ብይን መረዳት ያስፈልጋል ። የተፈጥሮ አደጋዋች ሰፊ ናቸው ። በአጭሩ ግን ስነ ምድራዊ ፣ ሰነ ውሃዊ ፣ ስነ አየራዊ ፣ ሰደድ እሳት እና የህዋ ጥፋት ብሎ ማሰቀመጥ ይቻላል ። ለአብነት መሬት መንቀጥቀጥን፣ የበረዶ ናዳ እና እሳተ ጎመራን ስነ ምድራዊ ውስጥ እናገኛቸዋለን ። ድርቅና የተለያዩ የአውሎ ንፋስ አደጋዋችን ሰነ አየራዊ ውስጥ ይመደባሉ ። በዚህ ሳይንሳዊ አካሄድ መሰረት የጣና ሃይቅ ችግር ስነ ውሃዊ / Hydrological Disasters / ውስጥ የሚገኝ ይሆናል ።

ሳይንቲስቶች ስነ ውሃዊ አደጋን A Violent , Sudden and destructive change either in the quality of earth’s Water or in the distribution or movement of water on land below the surface or in the atmosphere በማለት ይበይኑታል ።

ህገ መንግስቱ ዝርዝር መግለጫ ስለሌለው ከዚህ በመነሳት ሀሳብ መስጠት ግድ ይላል ። በመሆኑም በጣና ሃይቅ የደረሰው አደጋ የውሃውን መጠን ፣ ጥራትና ፍሰት የሚጎዳ ነው ። በውሃውና በአካባቢው የሚገኙ ስነህይወታዊ ስርአትን ያፋልሳል ። ከሃይቁ ቀጥተኛ የህልውና ትርጉምን እውን በሚያደርገው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ይፈጥራል ።

ከዚህ ሁሉ በላይ ጣና የኢትዮጽያ ታላቅ ቅርስ ነው - በባህላዊ ፣ ታሪካዊ ፣ ሰነውበታዊ እና ስነ ምድራዊ ሃብቶች የበለጸገ ። በእኛም ብቻ ሳይሆን በዩኔስኮ ዳኝነት የተመሰከረለት ። እንግዲህ ይህ የሀገርና የአለም ሀብት ነው አደጋ ውስጥ ስለሆነ ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ያስፈልገዋል እየተባለ የሚገኘው ።

በቅርቡም ባለሙያዋች እንደገለጹት ሃይቁን ተረባርቦ ማከም ካልተቻለ በአደገኛው አረም ሊጠፋ ይችላል ። ከዚህ የላቀ ምስክርነት ታዲያ ከየት ሊመጣ ይችላል? ይህን አደጋ የተፈጥሮ አደጋ አይደለም ማለት ፣ ይህ አደጋ በህዝብ ሃብትና ማንነት ላይ የተጋረጠ ቀውስ አይደለም ማለት ራስን ከማታለል የሚቆጠር ነው ። እናም አደጋውን ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት መንግስት የዋና ገጸባህሪ ብቻ ሳይሆን የአዘጋጅነቱንም ሚና መጫወት ይኖርበታል ። መንግስት ልግመኛ ካልሆነ በስተቀር ‹ ኩራትም እራትም › ነው የሚለውን በርካታ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በቦታው ቢያሰማራ የማይናቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ። በነገራችን ላይ መከላከያ ሰራዊት ህዝባዊነቱን እያሳየ ነው  ተብሎ ብዙ ግዜ አረም ሲነቅልና እህል ሲያጭድ በቲቪ ተመልክተናል እኮ ? ታዲያ ምነው እንቦጭን ለመንቀል አልከሰት አለ ?

መንግስት ጣና የሀገር ጉዳይ ነው ብሎ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ከሰራ ሀገራዊ መፍትሄ የሚጠፋ አይመስለኝም ። ከአቅም በላይ ከሆነም ወደ ውጭ ለማየት አሁንም የመንግስት አይን ጥቅም አለው ።  ቢያንስ A+ ባለው የእርዳታ ክህሎቱ ‹ ጎበዝ ተባበሩኝ ›  ቢል አውሮፓዋቹ የሚጨክኑ አይመስለኝም - ሌላው ቢቀር ቻይናዊ መፍትሄ አይጠፋም ። ለስርአት አደጋ ብቻ ሳይሆን ቀስ እያለ በተፈጥሮ ሊደርስ የሚችል ጥፋትን ለመከላከል ሳይቃጠል በቅጠል የተሰኘ ፖሊሲ መከተል ብልህነት ነው ።

ጣና የሁላችንም ጉዳይ ነው !

ቢረፍድ እንኳን ለጣና ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ያስፈልጋል !

Saturday, July 15, 2017

የአማረ አረጋዊ ልዩ ዋንጫ


አቶ አማረ አረጋዊ የኢትዮጽያ ፕሬስ ባለውለታ መሆናቸውን በማገናዘብ ሰሞኑን የእውቅና ሽልማት አግኝተዋል ። አንዳንዶች አቶ አማረ ከኢትዮጽያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሽልማት ማግኘታቸውን አልወደዱትም ። ለምን ሲባሉ ሁለት ምክንያቶችን ያቀርባሉ ። የመጀመሪያው ምከር ቤቱ የማይገባውን ስራ በመስራቱ የሚል ነው ። የምክር ቤቱ ቀዳሚ ስራ የፕሬስ ነጻነት እንዲረጋግጥ ብሎም በስርጭት ወቅት ክህዝብ የሚቀርብ አቤቱታ ካጋጠመ እንዲታረም ማድረግ ነው  ። ከዚህ አንጻር አባላትን ለመሸለም የሚያስችል ህጋዊ ማእቀፍ እንደሌለው ይገልጻሉ ።

ሁለተኛው ምክንያት የአመራር አባል የሆነን ግለሰብ መሸለም በሽልማቱ አካሄድ ላይ ተጽእኖ እንዲፈጠር እድሉን ያሰፋል የሚል ነው ። የአቶ አማረ አመራር አባልነት በሽልማቱ አካሄድ ላይ ችግር ይፈጥራል የሚለው ህሳብ እንኳን በቀላሉ ቅቡልና የሚያገኝ አይመስለኝም ። ምክንያቱም የምክር ቤቱ አባላት በበርካታ እውቀት ጠገብ ድርጅቶች የታቀፈ ነው ።  ፎርቹን ፣ አዲስ አድማስ ፣ ሸገር ፣ ኢቢሲ ፣ ዛሚ ፣ ካፒታል ፣ ኢትዮጽያ ፕሬስ ኤጀንሲ ፣ ኢጋማ ፣ ኢትዮ ቻናል ፣ ቁም ነገር እና ሌሎች ማህበራት ይገኙበታል ። ሲጀመር እነዚህ ቡድኖች ጥራት ያለው ማንዋል አይኖራቸውም ማለት ይከብዳል ። ሲለጥቅ በግልጽ ፣ በማያሻማና ዴሞክራት በሆነ መልኩ የፈልጉትን የሚመርጡበት ስነ ሰርዓት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል ።

የሆኖ ሆኖ አቶ አማረና ድርጅታቸው ከዚህ በፊትም አንድ ሀገራዊ ምርጫ አሸንፈው መጭበርበራቸውን ለሚያውቅ ለእኔ አይነቱ ሰው የአሁኑ ምርጫ አሸናፊነት ብዙም ላያስገርመው ይችላል ።

እንዴት ተጭበረበሩ ?

የቀዳማዊ ሃይለስላሴ የሽልማት ድርጅት ከተረሳ በርካታ አመታት በኋላ በሀገራችን አንድ የሽልማት ድርጅት ተቋቁሞ ነበር ። የኢትዮጽያ ስነጥበባትና መገናኛ ብዙሃን ድርጅት የሚባል ። ይህ ድርጅት በ 1994 ዓም ላካሄደው የሽልማት ተግባር አስቀድሞ ነበር በየዘርፉ ሊዳኙ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን ግለሰቦች የመረጠው ። እናም የመጀመሪያው ትውውቅ ቀን በስብሰባ ማዕከል ተጠርተን በአቶ እቁባይ በርሄ የአሰራር መግለጫና ወፍራም አደራ ተሰጥቶን በየቡድናችን ስራውን ማሳለጥ ጀመርን ።

ጋዜጠኞችን ለመምረጥ ታሪካዊውን እድል ያገኘነው አምስት አባላት ነበርን ። ስብጥሩ ደግሞ ሁለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንጋፋ መምህራን ፣ አንድ የኢቲቪ አንጋፋ ጋዜጠኛ / ከእንግሊዘኛው ክፍል / ፣ አንድ የአትዮጽያ ሬዲዮ አንጋፋ ጋዜጠኛ እና እኔ ነበርን ።

ቢሮአችን ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሆኖ ደከመን ሰለቸን ሳንል ተጋን ። ሊቀ መንበራችን ልምድ ያለው ሰው በመሆኑ እንዴት መሄድ እንዳለብንና ምን የተሻለ ስራ ማከናወን እንደሚኖርብን መንገድ አመላካች ነበር ማለት ይቻላል ። መጠይቆች ተሰርተው በመንግስትና በግልሚዲያ ተቋማት ተበተኑ ። የዚህ መጠይቅ ውጤት ተሰብስቦ እስኪቀመር ድረስ ደግሞ በየዘርፉ ያሉ ጋዜጠኞችን መዘርዘር ጀመርን ። የዳኞች ስብጥር ሁሉንም አካባቢ የሚወክል በመሆኑ ብዙም አልተቸገርንም ነበር ። ከዚያም በእያንዳንዱ ጋዜጠኛ ላይ ውይይትና ክርክር ይደረጋል ። ብዙ መቶዎችን ወደ መቶ ፣ መቶዎቹን ወደ ሃምሳ ፣ ሃምሳውን ወደ ቀጣዩ ግማሽ በመውሰድ ለፍጻሜ መድረስ ቻልን ። በመሃሉ ግን ‹ የስነጥበብ ዘርፍ ዳኞች እየጨረሱ ናቸው እናንተ ምን እያደርጋችሁ ነው ? › የሚለው የነ አቶ እቁባይ ጭቅጭቅ እረፍት ነሺ ሆነብን ። የኛ ጥያቄ ታዲያ ‹ በአጭር ግዜ የሚጨርሱት ምን አይነት ስልት ቢከተሉ ነው ? › የሚል ነበር ። በጥራት እሰራለሁ ብሎ ለሚነሳ ቡድን እያንዳንዱን እጩ በተጨባጭ አቅሙን መፈተሽ ግድ ይለዋል ። የራሱን ግምት ብቻ ሳይሆን የባለሙያውን አስተያየት ምርኩዝ ማድረግ ይኖርበታል ። ይህ ደግሞ ግዜ ይፈልጋል ።

በእውነት ከባድና አታካች ስራ ነበር ። ብዙ ግዜም የተሻሉትን ለመምረጥና ለማበላለጥ ስንቸገር ድምጽ መስጠቱ ነበር የሚገላግለን ። እናም በርካታ ወራት ከደከምን በኋላ የተሸላሚዎችን ስም ዝርዝር ከነ ምክንያቱና ማብራሪያው ጽፈን አስረከብን ።

ተጠባቂው ቀን ደረሰ ።

ሸራተን ሆቴል ልዩው ስነ ስርአት ሲካሄድ የመረጥናቸው ሁለት ሰዋች ተሰርዘው የማናውቃቸው ሁለት ጋዜጠኞች ክብሩንና 20ሺ ብሩን በእጃቸው ወሰዱት ፣ በአንገታቸው አጠለቁት ። የእኛ እንገት ግን በሃፍረት፣ በቁጭትና በህዘን አቀረቀረ ። ሁለት ዳኞችን አግኝቼ ስለ ሁኒታው አነጋገርኳቸው - እንደኔ ድንጋጤ አስክሯቸው ነበር ። ያ ሁሉ ልፋታችን ገደል ገባ ። « የዳኞች የመጨረሻ ውሳኔ የመጨረሻ ነው » በተባልነው ዲስኩር ላይ ለማላጋጥ ሞከርኩ - ይህን ማድረግ ግን አልቻልኩም ፤ ምክንያቱም በግልጽ ያላገጠብኝ እሱ መሆኑን ሰለተረዳሁ ።

ለዳኞች የተሳትፎ ወረቀት በሚሰጥበት ቀንም በነበረው አሰራር ላይ ውይይት ስለነበር በአጭበርባሪው ምርጫ ላይ የማላገጥ እድል አገኘሁ ። የተሰማኝን ሁሉ ተነፈስኩ ። ነገር ግን በእኔ ሀሳብ ላይ ምላሽ ወይም አስተያየት የሰጠ አልነበርም ። አንዱ በአንዱ ሲስቅ... እንደማለት ።

በእነ እቁባይ በርሄ ከተሰረዙት ተሸላሚዎች መካከል ብዙ ወንድማገኝ እና ሪፖርተር ጋዜጣ ይገኙበታል ። የተተኩት ደግሞ በኢትዮጽያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የነበሩት ሳሙኤል ፍቅሬ እና የሃይለራጉኤል ታደሰ ባለቤት የሆነችው ሂሩት ናቸው ።

ያኔ ታዲያ ሪፖርተርን እንደ ጋዜጣ እንዲሸለም ያጨነው ህትመት ላይ ካሉ ጋዜጦች ጋር በማወዳደር ነበር ። ለማወዳደሪያነትም ተነባቢ ፣ አሳታፊ ፣ ወቅታዊ ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ የሚሉና ሌሎች የጋዜጠኝነት መርህና መመሪያዎችን መሰረት እድርገናል ። ይህ ማለት የስታፉ ሁለገብ ተሳትፎን ጨምሮ የዋና አዘጋጁ አማረ አረጋዊ ሚና ትልቅ እንደነበር የሚያመላክት ነው ። አቶ አማረ ከ 97 በፊትና በኋላ አንድ አይደለም የሚሉ ሰፊ ሃሳቦች ቢኖሩም ፈተና ለበዛበት የሀገራችን ፕሬስ ያደረገው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። ትናንት ያጣውን ሽልማት አሁን ማግኝቱ ማስደሰቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ልዩ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።

Tuesday, July 11, 2017

የዘመኑ ሥነ-ግጥም ያነሳውና የጣለው



የፌስ ቡክ ግድግዳ ከሚነግረን አንደኛው ጉዳይ በርካታ ገጣሚያን እያፈራን መሆኑን ነው ። ሰነጽሁፍ በማይበረታታበት ሀገር ወፈ - ሰማይ ስንኝ መታሪያዎች እንደምን ፈለቁ የሚለውን ጥያቄ በቀላሉ ማንሳት ቢቻልም ጥናት ላይ ሳይመሰረቱ ቀላልና የዋዛ ምላሽ ማግኘት አይቻልም ።

ግን ደግሞ ለጸሀፊዎች ወይም ለመስኩ ባለሙያዎች ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ የተገኝ ይመስለኛል ። የወጣ መጽሀፍን እያደንኩ በማነብበት ዘመን አታሚዎችም ሆነ አከፋፋዮች ሥነ- ግጥምን ምናምን እንደነካው እቃ አፍንጫቸውን ይዘው ሲያርቁት አውቃለሁ ። ያኔ ብዙዎች እንደ ቀንድ አውጣ ኩምሽሽ ብለው ራሳቸውን ምሽግ ውሰጥ ይከቱ ነበር ።

ዛሬ ተመስገን ነው ። ቀንድ አውጣዎቹ አንገታችውን ስበው እየዳኹ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ በፌስ ቡክ ግድግዳ ላይ ክንፍ አውጥተው እየበረሩ ናቸው ። በህትመት ደረጃ የሚታየውን የብዛት መሰላል ግራፍ ለማድረግ የቅርብ አስተውሎት / በርቀት ምክንያት / ባይኖረኝም አሁንም የፌስ ቡክ ግድግዳ የሚነግረኝ ዜና አለ ። ግጥም ጥቂት በማይባል መልኩ እየተመረቀ መሆኑን ።
ታዲያ እነዚህ የግጥም ስራዎች የሚያበስሩን ብዛታቸውን ብቻ ሳይሆን ያነሱትንም የጣሉትንም ጉዳይ ጭምር ነው ። በርግጥ ምን የተለየ ነገር እያነሱ ናቸው ?

1 . የዘመኑ ግጥሞች በሚያነሱት ሀሳብ በእጅጉ የበለጸጉ ናቸው ። ያልታሰቡና ያልተገመቱ ርዕሰ ጉዳዮችን ፈልፍለው በማውጣት በደማቅ ሲጽፏቸው እንመለከታለን ። ይህ የሚያሳየው ገጣሚው የመጻፊያ ርዕስ ችግር የሌለበት መሆኑን ነው ። ርዕስ ለመምረጥ አምስቱንም የስሜት ህዋሳቶች በደንብ ይጠቀማሉ ።

ከወደቀ ግዙፍ ግንድ ላይ የሚያማመሩ ጉማጆችን ለማውጣት በጭፍኑ አይደለም መጥረቢያቸውን የሚወረውሩት ። በስልትና በተገራ መልኩ ነው ጎኑን የሚኮረኩሩት ። ያኔ ተንሳጣጭ ሳይሆን የሚያስቅ ድምጽ ፈጥረው እኛንም የሳቅ ተጋሪ ያደርጉናል ።

2 . ጥበባዊ አጨራረስ የዘመኑ ግጥም ደማቅ ባህሪ እየሆነም ይመስላል ። ከተነሳው ሀሳብ በተጨማሪ የግጥሙ መዝጊያ አንዳንዴም የግጥሙ አንኳር መልዕክት አንባቢው ከሚጠብቀው በተቃራኒ ሁኔታ ሲያልቅ እንመለከታለን ። በስልቱም እንዝናናለን ። እንስቃለን - በሥስ ፈገግታ ሳይሆን ጮክ ብሎ ባመለጠን ሳቅ ። እንገረማለን - በአርምሞ ብቻ ሳይሆን ነገርና ጥያቄ በሚያመነጭ ትዝብት ። ይህ አይነቱ የፈጠራ አካሄድ ቀደም ባሉት የግጥም ስራዎች ጎልቶ የወጣ ነው ማለት አይቻልም ።

3 . ምጸታዊ ቅርጽም / Satirical poetry / ሌላኛው መለያ እየሆነ መጥቷል ። በዚህ ስልት ትልቅ ልምድ ያላቸው ሮማንስ ናቸው ። ስልቱ በተለይም ነባራዊውን የፖለቲካ መስመር ለመሸንቆጥና ለመተቸት ፣ በገሃድ የሚታየው ፍትህና ሞራል ላይ ለማላገጥ አመቺ  ስልት ነው ።

የዘመኑ ገጣሚ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቦበት በየቤቱ እኽኽ ... የሚለውን ዜጋ ትንፋሽ በቅብብሎሽ አደባባይ ላይ እያሰጣው ይመስላል ። በፖለቲካው ምክንያት በየቤቱ የተወከለው የበገና ድምጽ ነው ። ለስለስ ያለና አንዳች ተአምር የሚለማምን ድምጽ ። ገጣሚዎቹ ይህን በገና አንዴ ትራምፔት ሌላ ግዜ ማሲንቆና ከበሮ እያደረጉት ነው - በደማቁ ።

ከላይ የተገለጹት  የፈጠራ አካሄዶችና ስልቶች ቀደም ባሉት የግጥም ስራዎች ጎልተው የወጡ አልነበሩም ። በሌላ በኩል የዘመኑ ገጣሚ እንዳነሳው ሁሉ ምን አይነት ስልቶችን እየጣለ መጥቷል የሚለውን ጥያቄ መቃኘት መልካም ነው ።

1 . የምሰላ / Imagery / መኮሰስን እንደ አንደኛው ችግር ማንሳት ይቻላል ። ገጣሚ በአንባቢ ጭንቅላት ውስጥ ምስልና ስሜትን መፍጠር ይኖርበታል ። ምሰላ ስንል የፎቶ ጉዳይ ብቻ አይደለም ። ምሰላ የሰእል ፣ የድምጽ ፣ የማሽተት ፣ የመቅመስና የመዳሰስ ህብረ ውጤት ነው ።

ከዚህ አንጻር የዘመኑ ግጥሞችን በአምስቱ ህዋሳታችን ለመረዳት እያስቸገረን ነው ። ለዚህ ትልቁ መንስኤ ደግሞ አንድ አይነትን ይተበሃል መከተላቸው ነው ። አብዛኛው ገጣሚ ግጥም በአራት፣ በስድስት እና ስምንት መስመር የሚያልቅ ጥበብ እንደሆነ የበየነ ይመሰላል ። እናም ጉዳዩን እንደጀመረ ጉዳዩን አሳጥሮ ይጨርሳል ። የግጥም መንገድ አጭርና የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ነው ባይ መስሏል ። አንዳንዴ ግጥም ማንበብ ጀምራችሁ ማለቁን በግድ ታምናላችሁ ። በቃው ... ይሄው ነው ? ... ምን ለማለት ፈልጎ ነው የሚሉ ጥያቄዎች በምናባችሁ ይዥጎደጎዳል ። ያ ማለት ግጥሙ ወይም መልእክቱ አላሳመናችሁም ማለት ነው ። ግጥም እንደ አንባቢው መረዳት ነው ብሎ የቤት ስራውን ለእናንተ የሚቆልል ስንኝ ቋጣሪ ሳይውል ሳያድር ስራውን መፈተሽ ይኖርበታል ።

ውጤቱን በምሳሌ ላስረዳ -  በቡና መታደም ስርአት ። የበፊት ገጣሚዎች ስኒውን ፣ ቡና ቁርሱን ፣ የካዳሚዋን እንቅስቃሴ ኪናዊ በሆን መንገድ ሊያቀርቡት ይችላሉ ። ቡናው ከጀበናው ማማ ቁልቁል ስኒው ላይ እንደ ፏፏቴ ከመፈጥፈጡ በፊት ጢሱን ሊያሳዩንና እንድናሸተው ሊጋብዙን ይችላሉ ። በጢሱ ጠመዝማዛ ሰረገላ አሳፍረው የነገውን መጻኢ ማንነት ሊያመላክቱን ሁሉ ይችላሉ ። የአሁኑ ገጣሚ ዙሪያ ጥምጥሙን በመግደፍ በሞቀ ውሃ ውስጥ ዱቄት ጨምሮ እንደሚጠጣ እያሳየ ነው ።

ለአሁኑ ገጣሚ የሰርገኛ መኪና አደባባዩን ደጋግሞ መዞሩና አናስገባም ሰርገኛ እያሉ መገፋፋት ብዙም ጠቃሚ የሆነ አይመስልም ። ለመጋባት ከማዘጋጃ ፍቃድ ማግኘት ካልሆንም ያለምንም ግርግር ጠልፎ ጉዳዩን መጨረስ በቂ እንደሆነ እያሳየ ይመስላል ። ይህነኑ ብይንና እምነት ሰእላዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ ቢቻልም አንድ ጥሩ መንገድ በሆነ ነበር - ሆኖም ቶሎ ወደ ጉዳዩ የመንደርደር ስልት ግን ምሰላን እያዳከመው ነው ። የዘመኑ ገጣሚ የግድ እንደ ሆሜር ኦሊያድ እና ኦዲሴ ረጅም ተራኪ ስታይል ይጠቀም ለማለት ሳይሆን ቢያንስ ስብጥራዊ መንገዶች ይኑሩት ነው ። ረጅም ሆኖ የሚመስጥ ግጥም መስራት እንደሚቻልም የከበደች ተክለአብ ፣ አበራ ለማ ፣ ክፍሌ አቦቸር እና የመሳሰሉ ስራዎችንም ያገላብጥ ነው ።

በቅርጽ አወራረድም የመመሳሰል በሽታ ይታያል ። ብዙ ግጥሞች እንደ ፋብሪካ ምርቶች ተመሳሳይ ፍሰት ፣ ዜማና ምት የሚጋሩ መስሎ ይሰማናል ። በጣም የወጡ ገጣሚዎች በሌሎች ላይ እያሳደሩ የመጡት ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑ እስኪታወቅ ደረስ ። ገጣሚው ለምሳሌ እንደ በእውቀቱ እንጂ እንደ ጸጋዬ ፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፣ ከበደ ሚካኤል ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ወዘተ የራሱን መስመር ማስመር እንዳለበት አላመነም ።

2 . የቋንቋ ችግር ። የዘመኑ ገጣሚ ግጥም የሚጻፈው በቀላል ቋንቋ ነው የሚባለውን መረዳት በመያዝ ይመስላል የተለየ ትኩረት ሲሰጥ የማይታየው ። የግጥም ቋንቋ ከተራውና ከተለመደው መግባቢያ የላቀ ውበትና ዜማ የተጎናጸፈ ነው ።  የግጥም ቋንቋ የሚፈጥረው ውስጣዊ ወይም ሌላኛው ትርጉምም ማለታችን ነው ። የግጥም ቋንቋ ከሰዋሰውና ከቀበሌኛ ዘዬም በላይ ነው ።
ጠንካራና ውብ ቋንቋ ለመፍጠር ሰርካዝም የሚባሉትን ምጸት ፣ ሽሙጥና ውስጠ ወይራዎችን ማወቅና መጠቀም ይጠቅማል ። ሜታፎር የሚባሉትን ዘይቤያዊ አነጋገር ፣ አሊጎሪና ምሳሌዎችን ማወቅና መጠቀም ግድ ይላል ። ግጥም እነዚህን ዘይቤዎች አይነኬ የሚያደርጋቸው ከሆነ ተራ መደዴ ነው የሚሆነው ። ውበትና ልቀትን ነው የሚያደበዝዘው ።


እናም የሚነሳውን እያጠናከሩ የሚጣለውን ደጋግሞ እየመረመሩ መሄድ የሚያዋጣ ይመስለኛል ።

Tuesday, July 4, 2017

እየመጣ ያለው አስቀያሚ ስያሜ



ፊንፊኔ ስላሽ አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ
ፊንፊኔ እና አዲስ አበባ 
አዲ ሃይፈን ፊን
ፊን ነጥብ አዲ
አ ወይም ፊ

የቱ ነው እየመጣ ያለው የከተማችን መጠሪያ ? የቱ ነው እውነቱ ? የሚያስከትለው ውጤትስ ? ታዋቂው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ራልፍ ኤድዋርድ Truth and Consequences እንዲል ። ይህን Truth and Consequences የተባለውን የNBC ቴሌቪዥን ፕሮግራም የመመልከት እድል ያጋጠመው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ይገነዘባል ። እውነትን ማወቅ ስጋት ማራገፊያ መሆኑንና እውነታን መሳት ካልታሰበ ችግር ጋ የሚያላትም መሆኑን ።

የፕሮግራሙ ፈጣሪ ራልፍ ኤድዋርድ ከተመልካች ውስጥ የተወሰኑትን መድረክ ላይ በማቅረብ ነው ጥያቄውን የሚያቀርበው ። የጥያቄውን ምላሽ ያገኘ ነጻ ይወጣል ። እውነታውን የሳተ ግን በቀጣይ የሚቀርብለትን አስደናቂ ወይም አስቸጋሪ ወይም አሳፋሪ ትርዒት የማቅረብ ግዴታ አለበት ። ትርዒቱ ከአቅሙ በላይ ሊሆንይችላል ፣ ቢሆንም ከድርጊቱ ጋር መጋፈጥ አለበት ። ለምሳሌ ያህል አንድ ወቅት ያየሁት ተጠያቂው ባለ አንድ ጎማ ብስክሊት እንዲያሽከረክር ታዞ ነበር ። ሰውየውን እንደምንም ብለው የሳይክሉ ረጅም ወንበር ላይ ሰቀሉት ። ታዲያ ምን ያደርጋል ላይ ተንጠልጥሎ ራሱን ባላንስ ማድረግ አልቻለም ። እናም ፔዳሉን ወደፊትና ወደኋላ ከማባበል ይልቅ በሃይልና በድንጋጤ ሲንጠው ቀጥታ ወደ ተመልካቹ ተፈተለከ - ህዝቡ መሃል እንደ ቲማቲም ፈርጦ ክፉ የሽብር ተግባር ይፈጽማል ብዬ ስጠብቅ አምላክ ረድቶት አንድ ጥግ ምናምን ይዞ ዳነ ።  በሰውየው ድንጋጤና ያልተገራ ጥበብ ብዙ ሰአት እንደሳቅኩ አስታውሳለሁ ።

የዚህ ፕሮግራም አዘጋጅ ከመድረክ ኩምኩና በተጨማሪም ለአለማችን አስቂኝ የከተማ ስም በመፍጠርም ይታወቃል ። ነገሩ እንዲህ ነው ። በ1940 የተጀመረውን Truth and Consequences አስረኛ አመት ለማክበር በአዘጋጁ በኩል አንድ ጥሪ ይተላለፋል ። የከተማውን ስያሜ በፕሮግራሙ መጠሪያ ለሚቀይር ዝግጅቱ በቀጥታ ከከተማው እንዲተላለፍ ይደረጋል የሚል ። ይሄኔ የ < Hot Spring > ነዋሪዎች ፍቃደኝነታቸውን ይገልጻሉ ። ከተማዋ የበርካታ የተፈጥሮ ሙቅ ውሃ ባለቤት ናት ። እናም በመጋቢት 1 ቀን 1950 ዓም ህዝበ ውሳኔ ያከናውናሉ ።  295 ሰዎች ይህን እብደት አንደማይቀበሉ ሲገልጹ  1294 ያህሉ ግን ስማችን እንዲቀየር እንፈልጋለን አሉ ። በቀጣዩ ቀን ማለትም ሚያዚያ 1 1950 ፕሮግራሙ ከከተማዋ ተላለፈ - የከተማዋ አዲሱ መጠሪያም Truth or Consequences ሆነ ።

ይህ ስም በአለማችን ካሉት ረጅም እና ቀፋፊ ስሞች መካከል እንደ አንደኛው ሊቆጠር  የሚችል ነው ። የTruth or Consequences ከተማ ነዋሪዎች ይህ ቀፋፊ ስም እንዴት ከእናንተ ተግባር ጋር ይገናኛል ሲባሉ የሚከተለውን ሽፍንፍን ያለ ምላሽ ይሰጣሉ  « እውነታው / Truth /  በከተማችን ጤና ሰጪ ፍልውሃዎች ያለን መሆኑ ነው ፣ ይህ ያስከተለው ውጤት/ Consequences /  ከተባለ ደግሞ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ነው » የሚል ነዋሪዎቹ ዛሬ ዛሬ በረጅሙ ስያሜ በመዳከማቸው  ቲ ኦር ሲ ወደሚል ምህፃረ ቃል ወርደዋል ።

ምናልባትም ሁለተኛው ረጅም እና ቀፋፊ ስም የአዲስ አበባው ፊንፊኔ ጥምረት ሊሆን ይችላል ። በህግ ፊት እኩል የመቆም መብት የተሰጣቸው አዲስ አበባና ፊንፊኔ በሚያስከትለው ውጤት / Consequences / ብዙ ሊፋተጉ ይችላሉ ተብሎ የተሰላ ይመስላል ። አዲስ አበባ ይቅደም ፊንፊኔ ? አቀማመጡ እና ጥምረቱስ ? በወይም ይቆለፍ ወይስ በ እና ሰረገላ ? በስላሽ ድንበር ያብጁ ወይስ  የዶት ታኮ ይሰራላቸው ?

ምፀታዊ ዋጋው የአዲስ አበባ ህዝብ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣው በዚሁ ጉዳይ ሀሳብህ ምንድነው ተብሎ አለመጠየቁ ነው ። ስሙን በማስረዘሙ ልዩ ጥቅም ያገኛል ? የውሃ ፣ መብራት ፣ ስልክ ፣ ስራ እና የዋጋ ንረት ሰቆቃው በፊንፊኔ ስላሽ አዲስ አበባ ገመድ ይጠፈነጋል ? ከአንድ ወደ ሁለት ቃላት ያደረገውን ድንገተኛ ሽግግር ተመችቶት ይቀበለዋል ፣ ህጋዊና ስነልቦናዊ ግዴታስ አለበት ? ነው መንግስት ካለ አለ ነው- ተከተል አለቃህን አክብር አርማህን እንዲሉ ። ከቅርብ ግዜያት የፖለቲካ ተሞክሯችን ስንነሳ ግን በንግግርና መግባባት ላይ ያልተመሰረተ ውሳኔ ያልታሰበ ውጤት ለማስከተል ምንም የሚያግደው ነገር የለም ። በመሆኑም  የኦሮሞ ተወላጆች ፊንፊኔ ሲሉ የተቀሩት ደግሞ በአዲስ አበባ እንዲፀኑ መንገድ ይከፍታል  ። በአንድ ከተማ ሶስት ስያሜ መሆኑ ነው ።

ይህም ወደ ሌላ አላስፈላጊ ውጤት ይመራል ። ወደ ይዞታ ጉዳይ ። ከተማዋ ለእኛ ነው የምትገባው ወደሚለው  የኦሮሞ - አማራ ጭቅጭቅ ። በርግጥ ማነው ቀደምቱ ? ከአዲስ አበባ በፊት ፊንፊኔ ነበር ... ስለዚህ ከተማዋ የኛ ናት ፣ እናንተ እንግዶቹ በኛ ስር ልታድሩ ግድ ነው ይልሃል አንደኛው ጠርዝ ... ከፊንፊኔ በፊትስ እነማን በምን ስም ነበሩ ?... ኦሮሞዎቹስ ከየትና እንዴት መጥተው በሀገሪቱ ተስፋፉ ይልሃል ሌላኛው ጠርዝ   ። ጭቅጭቁና እንካሰላንቲያው በተዋረድ በሰፈርና አደባባይ ስሞች ግዘፍ ነስቶ ይመጣል ። ለመንገድ ስያሜ ከተሜው ግድ ላይኖረው ይችላል ። ግድ የሚሰጠው ግን እንደ ማተቡ ውስጡ የቆየውን የሰፈር ስያሜ ቀይር አትቀይር የሚል ሙግት ከተከተለ ነው ። መንግስት በቀጭን ትዕዛዝ አስራለሁ ቢል እንኳን ጥቁር ገበያው አይሎ ኢ- መደበኛው ኮሙኑኬሽን እንደሚልቅ አያጠራጠም ።

የአዲስ አበባን ደም መርምሮ ሁነኛ ብይን ማግኘት አይቻልም ። የደም ምርመራው ኦ ኔጌቲቭ ፣ ኦ ፖዘቲቭ ፣ ኤ ኔጌቲቭ ፣ ኤ ፖዘቲቭ ፣ ቢ ኔጌቲቭ ፣ ቢ ፖዘቲቭ ፣ ኤቢ ኔጌቲቭ እና ኤቢ ፖዘቲቭ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አዲስ አበባ ከኦሮሞም ከአማራም በላይ መሆኗ ነው ። ከተማዋ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ሃብት ናት ። የኢትዮጽያዊነት አሻራ ወይም ቅጂ ናት ። የአፍሪካዊነት መሰረት የዝማሬያቸውም  ሰንደቅ ናት ።

ከመቶ አመታት በላይ የዘመናዊ  አስተዳደር ጽንሰ ሃሳብን ስትገነባ የመጣችን ከተማ በምን ተአምር የብሄር ካፖርት ማልበስ ይቻላል ? የዘመናዊነት ትርፉ እኮ ትላልቅ ፎቆችንና ዘመናዊ ባቡሮችን ማስገኘት ብቻ አይደለም ። ዘመናዊነት ከሁሉም በላይ አስተሳሰባዊ ዝመናን ይመለከታል ። የከተማው ህዝብ ኑሮ አጉብጦት ይሆናል እንጂ በአስተሳሰቡ ሸንቃጣ ነው ። ብዙ ትርፍና ተቀማጭም ሀብት አለው - የገንዝብ ሳይሆን  የማመዛዘን ፣ የመቻቻልና የፈሪሃ እግዚአብሄርነት ። በዚህ መሰል ችግር ወቅት እየመነዘረ የሚያካፍለው ። የማይናድ ልዩ ጥቅም አለው ከተባለ ይኸው  ነው ።

 ግራም ነፈስ ቀኝ የአዲስ አበባን እውነታ አብጠርጥሮ ማወቅ ካልተቻለ የሚያስከትለው ውጤት ከባድ ሊሆን ይችላል ።