ፎቶ ሸገር ብሎግ |
ገና ሀምሌ ሲገባደድ ነው የቡሄ
መነቃቃቶች የሚፈጠሩት ፡፡ ሂሳብ ላይ ከፍ ያለ ክፍያ እንዲደርሰን በማሰብ ቡድኑን በስድስት ቢበዛ በስምንት አባላት
እናዋቅረዋለን ፡፡ ከስብስብ ምስረታ ቀጥሎ የሚመጣው የዱላ ዝግጅት ነው ፡፡ ዱላ ለመቁረጥ የምናመራው ‹‹ ዝንጀሮ ገደል ››
ወደተባለው አካባቢ ነው ፡፡ ዛሬ አካባቢውን መኖሪያ ቤቶችና የድንጋይ ካባ ተቋማት ከበውት አንድም ዛፍ አይገኝም ፡፡
ዱላው ተቆርጦ ከደረቀ በኃላ ቆርኪ እየጠፈጠፍን ‹‹ ክሽክሽ ››
እንሰራለን - ማድመቂያ ፡፡
የማታ ማደሪያ መምረጥም
ዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ የሚካተት ነው ፡፡ ቤቱን ስንመርጥ የቤቱን ስፋትና የወላጆችን ባህሪ ግምት
ውስጥ በማስገባት ነው ፡፡ ምክንያቱም ማታ ከመተኛት ይልቅ መተራረብና መሳሳቅ ስለሚበዛ ‹‹ ቁጫጭ ሁላ ! ዝም ብለህ አተኛም
! ›› ብሎ የሚያስፈራራንን አባወራ እንዲኖር አንፈልግምና ፡፡ ዳቦና ገንዘብ ያዥም ከወዲሁ ይመረጣል ፡፡ ዶቦ ያዥነትን እንደ
ሸክም ፣ ገንዘብ ሰብሳቢነትን እንደ ስልጣን ስለሚመነዘር ምርጫው
ተቃራኒ ገጽታዋችን ማስተናገዱ ግድ ነው ፡፡
ዛሬ ላይ ሆኜ
ጭፈራችንን ስፈትሸው የድራማ ስልት እንደነበረው ይሰማኛል ፡፡ ያልደከመ ጉልበታችንን አስቀድመን የምንጠቀመው
በሀብታሞች ቤቶች ላይ ነበር ፡፡
‹‹ መጣንኖሎት
በዓመቱ እንዴት ሰነበቱ / 2 ግዜ /
ክፈት በለው በሩን - የጌታዬን
/ 2 ግዜ /
በሩ የብረትም ሆነ የቆርቆሮ
እየጨፈርን በዱላችን እንደበድበዋለን - ስሙን ማለታችን ነው ፡፡ አንዳንድ ተንኮለኛ ደግሞ መጥሪያውን ሊያስጮኀው ይችላል ፡፡
አሁን ውሾች ካሉ እንደ ጉድ ይጮሃሉ ፡፡ ክፉ ጥበቃ ካለም እንደ ውሾቹ እየጮኀ መጥቶ ከአቅማችን በላይ የሆነ ስድብ ያሸክመናል
፡፡ ‹‹ መናጢ የድሃ ልጅ ! በር ስበር ተብለህ ነው የተላከው ? መጥሪያው ቢበላሽ አባትህ መክፈል እንደማይችል
አጥተኀው ነው ፡፡ ሂድ ጥፋ ከዚህ ! ሰበበኛ ሁላ ! ›› ቆሌያችን
እንደ ውሻ ጭራ በፍርሃት ይጣበቃል። ደግነቱ የዚህ ተቃራኒ አለመጥፋቱ ፡፡ አዝማሚያው ደህና መሆኑን
ካረጋገጥን አሁን አንደኛ ማርሽ እናስገባለን ፡፡
« … የኔማ ጋሼ
ሆ.. !
የተኮሱበት
ስፍራው ጎድጉዶ
ሆ.. !
ውሃ ሞላበት
እንኳን ሰውና
ሆ.. !
ወፍ አይዞርበት !
እያልን እስከታች እንቀጥላለን ፡፡ ብዙ ካስለፈለፉንና ‹ ተወው ጮሆ ጮሆ ይሄዳል › እያሉ የሚያስቡ
መስሎ ከተሰማን የጭፈራችን መልዕክት ይቀየራል ፡፡ ሁለተኛ ማርሽ እናስገባለን ማለት ነው ፡፡
‹‹ ላስቲክ ተቀብሮ
አይበሰብስም
አንዴ መጥተናል
አንመለስም ::
አባባ ተነሱ ኪስዋትን ዳብሱ !! ›› በማለት በአንድ በኩል ጠንካራ መሆናችንን እያሳየን በሌላ
በኩል ትዕዛዝ ብጤ እናስተላልፋለን ፡፡ መቼም አንዳንድ ሰው ግድ ስለሌለው ወይም ማስለፍለፍ ስለሚወድ ድምጹን ያጠፋል ፡፡ አሁን ገሚሱ እንሂድ ሲል ሌላው በቀላሉ አንለቅም በማለት ይከራከራል ። ብዙ ግዜ እነዚህን አስተያየቶች የሚያስታርቁ ሀሳቦች ያሉት ይመስለኛል - ቡሄ ፡፡ አስታራቂው
ሀሳብ የጨፋሪውን መዳከም የሚጠቁም ይምሰል እንጂ በንዴትና በምሬት ነው የሚገለጸው ፡፡ እናም ንዴታችንን ለማፍጠን
ሶስተኛ ማርሽ እንጠቀማለን ::
‹‹ እረ በቃ በቃ
ጉሮሯችን ነቃ
በዚህ ማርሽ ተፈላጊው ውጤት ካልተገኘ የኃላ ማርሽ በመነጫነጭ ይገባል ፡፡
ንጭንጭ አንድ !
‹ ይራራ ሆድዋ -
እግዜር ይይልዎ ! › ሊል ይችላል አንዱ ቅኝቱን እንደጠበቀ
ንጭንጭ ሁለት !
‹ አለም አንድ ነው
የለም አንድ ነው እኛን ማስለፋት የሚያሳፍር ነው › ማለትም የተለመደ ነው ፡፡ ከብዙ ልፋት በኃላ ስጦታው
ከተፍ ካለ ደስታችን ወደር ያጣል ፡፡ ሳናውቀውም ማርሹ አራተኛ ገብቷል ፡፡
‹‹ አመት አውዳመት
ድገምና
አመት
ድገምና
የጋሽዬን ቤት
ድገምና
አመት
ወርቅ ያፍስስበት
እንዲህ እንዳለን
ሆ …!
አይለየን !!
ክበር በስንዴ
ክበር በጤፍ
ምቀኛ ይርገፍ !! ›› በማለት እየተሳሳቅን ውልቅ ነው ፡፡ ወደሌላኛው ቤት ስንጓዝ በመሃሉ የምንጠቀመው የጭፈራ ስልትም አለ ፡፡ ‹‹ አሲዮ ቤሌማ ›› የሚባል
፡፡ የሬዲዮ ጋዜጠኞች ይህን ዓይነቱን መሸጋገሪያ ‹‹ ብሪጅ ›› ይሉታል ፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ሞራል ማነቃቂያ መሰለኝ
የምንጠቀምበት ፡፡ የምንጨፍረው እየሮጥን ነው ፤ በል ሲለን ዱላችንን ርስ በርስ እናጋጫለን ፡፡ ምናልባት ሳናውቀው ከመስቀል
ጨፋሪዋች ያጋባነው ሊሆንም ይችላል ፡፡ ብቻ ዛሬ ድረስ የማይገቡኝ ቃላቶች አሉበት ፡፡
‹‹ አሲዮ ቤሌማ
ኦ … ኦ
አህ እንበል
አሲዮ ቤሌማ
ቤሌማ ደራጎማ … ›› ለአብነት ያህል ‹ ደራጎማ › ግጥሙ እንዲመታልን
የተጠቀምነው ቃል ነው ወይስ ትርጉም አለው ?
የቡሄ ዕለት ሲርበን ለምሳ ወደ
ቤት መሄድ የማይታሰብ ነው ፡፡ ዳቦ ክፍሉ በጎተራው ያለውን ንብረት ያሳውቅና እንከፋፈላለን ፡፡ ዳቦ እንኳን ባናገኝ ካላቸው
ላይ ገዝተን ነው የምንበላው ፡፡ አንድ ክረምት ላይ ዝናቡ ዳቧችንን አሹቆት ነበር ፡፡ በጣም የራባቸው ዳቦውን እንደ ጨርቅ
ጨምቀው የቀማመሱበት ሁኔታ ነበር ፡፡ ወደ ኃላ እየቀረ ዳቦውን በጥርሱ እየከረከመ የሚያስቸግረን ባልደረባም ነበረን ፡፡
በንዴት ስንጮህበት ‹ እንዲሁ ነው የተረከብኩት ! › ብሎ ይሸመጥጣል ፡፡
ገና ‹‹ የወንዜው ነበረ ›› ስንል ‹‹ ነብር ይብላህ ! ›› በማለት የሚያባርሩን ሰዋች እንደው
ራሳቸው ከነብር ካልተሰሩ በስተቀር በአውዳመት ይህን እኩይ ቃል መጠቀማቸው ይገርመኛል ፡፡ ለረጅም ሰዓት ከኛ ጋር
ግቢው ውስጥ ጨፍሮና አስጨፍሮን ‹‹ በሉ የዓመት ሰው ይበለን ፤ ያኔ ደግሞ ከዚህ በላይ እንጨፍራለን ›› ብሎ በነጻ
የሚሸኘንም ሰው ነበር ፡፡ ያኔ በሳቅ ከመፍረስ ጎን ለጎን ዞር ብለን በተረብ ቀዳደን እንጠለው ነበር
‹‹ ምናባቱ ድሮ ሳይጨፍር ያለፈበትን
ግዜ በኛ ያስታውሳል እንዴ ?! ብሽቅ ! .. ገገማ ! … ጥፍራም ! … ሽውደህ ሞተሃል ?! … ›› በዛሬ ዓይን ሳስበው ግን
‹ ምን ዓይነት ፍቅር ያለው ሰው ነው ? › እላለሁ ፡፡ አደገኛ ውሻ ለቀውብን ስንፈረጥጥ በሳቅ ብዛት
የሚሰክሩትም ጥቂት አይደሉም ፡፡ በጣም የሚገርመው ከመታ የሚገላግለውን ወጠምሻ ዱላ አዝለን ከሩጫና ፍርሃት መገላገል
አለመፈለጋችን ነው ፡፡ ማታ ላይ ጉዳዩ ተነስቶ ስንተራረብ ‹ እኔ የሮጥኩት ወሻውን ሳይሆን ባለቤቱን ፈርቼ ነው › በማለት
እናስተባብላለን - እንዲም አድርጎ ሽውዳ የለም ፡፡ ዞሮ ዞሮ የተፈጸመብንን ግፍ ወደሌላው በማጋባትም እንታወቃለን ፡፡ ሌላ
የጨፋሪ ቡድን መንገድ ላይ ስናገኝ ‹ እዛ ቤት 10 ብር አግኝተናል › በማለት ወደ ውሻው ቤት እንዲሄዱ እንጠቁማቸዋለን ፡፡
ከዛ በተራችን ራቅ ብለን የአዳኝና ታዳኝ ትርዒቱን በሳቅ እያጣቀስን መኮምኮም ነው ፡፡
ማታ ስንተኛ የቀኑን ውሎ እያስታወስን የምንስቅበት፣ የምንተራረብበትና የምንገማገምበት መድረክ ነው
ማለት ይቻላል ፡፡ የሁላችንም ዱላ ስሩ ይታያል ፤ መሬት ሲደበድብ ስለሚውል ተቸርችፎ የተጠቀለለ ሉጫ ጸጉር ይመስላል ፡፡ ይህ
የጸጉር መጠን አነስተኛ የሆነበት መሬቱን በደንብ ስለማይመታ ለጋሚ ነው ተብሎ ይተቻል ፡፡ ድምጽም ሌላው መመዘኛ ነው ፡፡
በደንብ ሲጮህ የዋለ ድምጹ እንደ አለቀ ባትሪ መነፋነፉ ይጠበቃል ፡፡ ብዙም ያልተለወጠ ከተገኘ ‹ በእኛ ላይ ሲያሾፍ ስለነበር
ክፍፍሉ ላይ ዋጋውን ያገኛል ! › ይባላል ፡፡
ታዲያ በማግስቱ ያ - ሰው እኔ ካላወጣሁ እያለ ሲያሸብር ይውላል ፡፡ በደንብ ማውጣት የማይችሉ አባላትም ሌላው የመዝናኛ ገጸ በረከቶች ናቸው ፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ መጣንሎት በዓመቱ እንዴት ሰነበቱ ›› የምትለውን የመግቢያ ስንኝ ከጨረሰ በኃላ በምን ዓይነት ዝላይ እንደሆነ ሳይታወቅ የመጨረሻውን ‹‹ እረ በቃ በቃ ጉሮሯችን ነቃ ! ›› ላይ ፊጢጥ የሚል ያጋጥማል ፡፡ በስንት ህክምናና ስለት ልጅ እምቢ እንዳላቸው እያወቀ ‹‹ ይራራ ሆድዋ እረ በልጅዋ ! ›› የሚል ልመና በማቅረብ እኛን ለመጥፎ ሳቅ ሰዋቹን ለማሳቀቅ የሚዳርግም አይጠፋም ፡፡ አንዳንዴ ወደማናውቀው ሰፈር ጥሩ ብር ለመስራት ሄደን በሰፈሩ ጉልቤዋች የ ‹ ኮቴ › ተብሎ የምንቀማበት ሁኔታ ያጋጥማል ፡፡ ይህ ጉዳይ ከተፈጸመ ማታ ብዙውን የክርክር ጊዜ ሊወስድብን ይችላል ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሚወቀሰው ግን ራሱ ገንዘብ ያዡ ነው ፡፡
ታዲያ በማግስቱ ያ - ሰው እኔ ካላወጣሁ እያለ ሲያሸብር ይውላል ፡፡ በደንብ ማውጣት የማይችሉ አባላትም ሌላው የመዝናኛ ገጸ በረከቶች ናቸው ፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ መጣንሎት በዓመቱ እንዴት ሰነበቱ ›› የምትለውን የመግቢያ ስንኝ ከጨረሰ በኃላ በምን ዓይነት ዝላይ እንደሆነ ሳይታወቅ የመጨረሻውን ‹‹ እረ በቃ በቃ ጉሮሯችን ነቃ ! ›› ላይ ፊጢጥ የሚል ያጋጥማል ፡፡ በስንት ህክምናና ስለት ልጅ እምቢ እንዳላቸው እያወቀ ‹‹ ይራራ ሆድዋ እረ በልጅዋ ! ›› የሚል ልመና በማቅረብ እኛን ለመጥፎ ሳቅ ሰዋቹን ለማሳቀቅ የሚዳርግም አይጠፋም ፡፡ አንዳንዴ ወደማናውቀው ሰፈር ጥሩ ብር ለመስራት ሄደን በሰፈሩ ጉልቤዋች የ ‹ ኮቴ › ተብሎ የምንቀማበት ሁኔታ ያጋጥማል ፡፡ ይህ ጉዳይ ከተፈጸመ ማታ ብዙውን የክርክር ጊዜ ሊወስድብን ይችላል ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሚወቀሰው ግን ራሱ ገንዘብ ያዡ ነው ፡፡
‹ ከርፋፋ ! ገንዘቡን ዝም ብለህ ሜዳ ላይ ታስቀምጠዋለህ ?! › ሊባል ይችላል ፡፡ አንድ
ሰው ገንዘብ ያዥ ሆኖ ሲመረጥ የራሱን ጥበብ መዘየድ ይኖርበታል ፡፡ ገንዘቡ በጉልቤዋች ሊበረበር ይቻላል በሚል ስጋት የሱሪው
እግር አካባቢ፣ ኮሌታ ስር፣ በቀበቶው ማድረጊያ የውስጥ ክፍል ወይም በሌላ አሳቻ ቦታ ሰፍቶ በመደበቅ የማምለጫ ፋይዳዋችን
ማስፋት አለበት እንጂ በድንጋጤ ንብረቱን ማስረከብ የለበትም ፡፡ ሌላው ቢቀር የተወሰኑ ወፍራም ቡጢዋችን ቢቀምስ እንኳን ‹
እረ ገና አልሰራንም ! › ብሎ መሸምጠጥ ይጠበቅበታል ፡፡
በማታው ክፍለ ግዜ አባላቱ እየተንጫጩ ራሱን ዜሮ ማርሽ ላይ አቁሞ በጸጥታ የሚሰምጥም አይጠፋም ፡፡
ለመሆኑ የዝምታው ምንጭ ምን ሊሆን ይችላል ? በአብዛኛው ሶስቱ ናቸው ። እዳ ፣ ነጠቃ እና ግርፊያ ::
እዳ … የሚፈጠረው በብይ ወይም በጠጠር ጨዋታ ነው ፡፡ በክረምት ገንዘብ ከሌለን ጨዋታው ሞቅ እንዲል በሚል በዱቤ እንጫወታለን - ለቡሄ ለመክፈል በመስማማት ፡፡ ብዙ የማይችሉት ታዲያ ከአሁን አሁን እናስመልሳለን እያሉ እዳው ጣራ ይነካባቸዋል ፡፡ እናም ያስባል ፤ ብሩን አስረክቤ ቤት ምን ይሉኛል ? ድጋሚ አቤቱታ ልጠይቅ ? ልካድ ? ብክድ ምን ይመጣብኛል ? ….
እዳ … የሚፈጠረው በብይ ወይም በጠጠር ጨዋታ ነው ፡፡ በክረምት ገንዘብ ከሌለን ጨዋታው ሞቅ እንዲል በሚል በዱቤ እንጫወታለን - ለቡሄ ለመክፈል በመስማማት ፡፡ ብዙ የማይችሉት ታዲያ ከአሁን አሁን እናስመልሳለን እያሉ እዳው ጣራ ይነካባቸዋል ፡፡ እናም ያስባል ፤ ብሩን አስረክቤ ቤት ምን ይሉኛል ? ድጋሚ አቤቱታ ልጠይቅ ? ልካድ ? ብክድ ምን ይመጣብኛል ? ….
ነጠቃ … የምንለው ደግሞ በጉልቤ ቤተሰቦች የሚከናወን ነው ፡፡ ለስለስ ባለ አነጋገርና የጭንቅላት
ዳበሳ ሁለት ቀን ጨፍሮ ያገኘውን ብር ይቀመጥልህ አይደል ? ይባላል … ኮስተር ባለ ግንባር ልጅ ገንዘብ ከለመደ ዱሩዬ ይሆናል
! ይባላል … ዲፕሎማት በሆነ መንገድ አበድረኝ ሊባል ይችላል … ብቻ በብሩ እንደሌሎች የፈለገውን ማድረግ ስለማይችል
የማምለጫ መንገድ ፍለጋ በሃሳብ ይኳትናል ፡፡
ግርፊያ … የሚመነጨው ከሃርደኛ አባቶች ነው ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹ መጨፈር አንሶህ በዓመት በዓል ሰው
ቤት ምናባህ ያሳድረሃል ?! › የሚል ነው ፡፡ በጨፈረበት ዱላ የሚወቀጥ … ባገኘው ገንዘብ በርበሬ ገዝቶ የሚታጠን …
ያጋጥማል ብሎ መውሰድ ይቻላል ፡፡
ብቻ ምንም ሆነ ምን ባለ ማርሹ ቡሄ ደስታው የላቀ ነው ፡፡ በቡሄ ገንዘብ ከማግስቱ
ጀምሮ እንቁጣጣሽን አንቨስት ማድረግ እንጀምራለን ፡፡ ወረቀት ፣ ንድፍ ፣ ቀለም ይገዛል ፡፡
የወቅቱ የእግር ኳስ ኮኮቦችና ሁሌም ቋሚ ተሰላፊ የሆኑትን መላዕክቶች በመኳል እንደሰታለን ፡፡ እናም ቡሄ ባይኖር ኖሮ
እንቁጣጣሽ ይከብደን ነበር ፡፡ ኢንቨስት የምናደርግበትን ገንዘብ ማን ይሰጠናል ?
No comments:
Post a Comment