Saturday, January 12, 2013

የኮንዶ ጨበጣ



‹‹ ግንባታቸው የተጠናቀቀ ይህን ያህል ሺህ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ተከናወነ ››
ዕጣው ፍትሃዊና ግልጽ መሆኑን እናምን ዘንድ ድርጊቱ በአውራው ቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት ተላለፈ፡፡

ሀ . ከንቲባው የዕድላችንን ሶፍትዌር ሲጫኑት ይጨበጨባል፡፡
ለ . በኮምፒውተር የተመረተው ዕድል ምርቱን በወረቀት አትሞ የከፊል እድለኞች ስም ሲዘረዘር ይጨበጨባል ፡፡
መ . የቤት የለሹን ነዋሪ ስቃይ ለመቅረፍ መንግስት ምርጡን ፓሊሲውን ምርኩዝ አድርጎ ጥራታቸውን የጠበቁ ቤቶችን እየገነባ መሆኑን ባለስልጣናት እያስጎመዡ ሲያቀርቡት ይጨበጨባል ፡፡
ሰ . ዕጣ የወጣላቸው ቤቶች  ቁልፍ ከሶስት ወራት በኃላ ለእድለኞቹ እንደሚሰጡ ሲገለጽ በጣም ይጨበጨባል ::
ረ . ቀሪዎቹም ሆድ እንዳይብሳቸው ‹ ይሄን ያህል ሺህ የሚደርሱ ቤቶች ግንባታ ደግሞ 80 ከመቶ ተጠናቀዋል › ሲባል ይጨበጨባል

ጭብጨባችን በቀላሉ የሚቆም አይደለም ፡፡ አንዳንዴ ጭብጨባችንና የህግ ሰዎች ጽሁፍ የትኛውን የዘር ሀረግ ቆጥረው ዘመዳሞች እንደሆኑ ይደንቀኛል ፡፡ የባለሙያዎቹን ጽሁፍ እያነበቡ ነው እንበል፡፡ አንዱ ረጅም ዓረፍተ ነገር አለቀ ሲሉ ‹ ወይም › የተባለው አማካኝ ቃል ሀሳቡን ይቀበልና ተጨማሪ ቁመት ይፈጥርለታል፡፡ ይኀው ‹ ወይም › እግሩ እስኪደክመው ድረስ ቃላቱን አንቀርቅቦ በረጅሙ ይለጋዋል ፡፡ ጎሽ በአራት ነጥብ ፋታ ልውሰድ  ነው ብለው ሲያስቡ ሌላ ‹ ወይም › ሀሳቡን ጎትቶ እንደ ሀረግ ሲያጥመለምለው ያያሉ ፡፡ እኔ የአራት ነጥብ ጥቅም ይበልጥ የሚገባኝ እንደዚህ አይነት ጽሁፎችን ሳነብ ነው ፡፡
የኮንዶ ጭብጨባም በማይታይ ‹ ወይም › የተሳሰረ ነው ፡፡ ስማቸው ጋዜጣ ላይ ለወጣ ዕድለኞች ዘመድ ወዳጅ ያጨበጭባል ፡፡ የነዎሪዎችን ደስታ የሚያብራራው የቲቪ/ሬዲዮ ፕሮግራም ሲታይና ሲደመጥ ይጨበጨባል ፡፡

ከላይ ይጨበጨባል ያልንባቸውን አንዳንድ አንቀጾች በአግባቡ ስንመረምር ግን በከንቱ የተጨበጨበላቸው ነገሮች መኖራቸውን እንረዳለን ፡፡

የማስረከቢያ ግዜ

መንግስት ቤቶችን ሲመርቅ ከ 3 ወር በኃላ ወይም በጣም በፈጠነ ሁኔታ ቁልፍ አስረክባለሁ ማለቱ የተለመደ ነው ፡፡ የፈጠጠው እውነታ ግን ይህ አይደለም ፡፡ ትልቅ ማሳያ የሚሆነው የአምስተኛና የስድስተኛ ዙር ቤቶች ጉዳይ ነው ፡፡ መንግስት ዕጣውን ያወጣው ቤቱ ሳያልቅ ምናልባትም ገና ከመሰረት ደረጃ ፈቅ ሳይል በመሆኑ የ5ኛ ዙር ዕድለኞች ሁለት ዓመት የ6ኞቹ ደግሞ ዓመት ገደማ ቤታቸውን ለመረከብ ግዜ ወስዶባቸዎል ፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር በዚህ መሃል በጣም ቢያንስ ሁለት ወይም ሶስት ግዜ ቁልፍ ልናስረክብ ነው በማለት መግለጫ ሰጥቶ ዋሽቷል ፡፡

‹‹ ጨበጣው ›› ለምን አስፈለገ ?

በአንድ በኩል ከፍተኛ የህዝብ ፍላጎት የመኖሩን ያህል በሌላ በኩል መንግስትም ይህን ክፍተት ሞልቶ እውቅናና ድጋፍ ማግኘትን ይፈልጋል ፡፡ አቅርቦቱና ፍላጎቱን ግን ማጥበብ አልተቻለም ፡፡

መንግስት እንደ ህዝብ አገልጋይነቱ የሚለካው በሚታዩ ውጤቶች መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ይሁን እንጂ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሚታቀዱ ዕቅዶች ወሩ በፈጠነ ቁጥር በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚዎችን ያስጨንቃሉ ፡፡ ታዲያ የአዲስ አበባ ቢሮዎች ዕቅድንና ውጤትን ለማጣጣም ወረቀት ላይ መደነስ ግድ ይላቸዋል ፡፡ ያልተሰራውን ተሰራ፤ የተጀመረውን ደግሞ ከዕቅድ በላይ ተከናወነ በማለት ዳንሱን ከጥሩ የቋንቋ ህብር ጋር ያዋህዱታል ፡፡ ላይ ያሉት ዳኞችም ‹‹ ለዛሬ ተሳክቶልሃል ! ›› በማለት በጥሩ ጭብጨባ ያሳልፉታል ፡፡ ይህን መሰሉ በወረቀት መወሻሸት በጣም የተለመደ ነው ፡፡ እናም ያላለቀውን ቤት አልቋል፤ ያልተጀመረው ቀጣይ ግንባታ 80 ከመቶ ደርሷል ተብሎ ሪፖርት የሚደረገው በዚህ ዓይነት የተለመደ ስልት በመሆኑ የማይፈለገውን ‹‹ ጨበጣ ›› እንዲወለድ አድርጓል ፡፡

ሌላው የአዲስ አበባ መስተዳድር ችግር ስራ ተረባርቦ እንደሚጀመር ሁሉ ተረባርቦ መጨረስ የሚባል ዕቅድ አለማወቁ ነው ፡፡ ግንባታዎች ሲጀመሩ አንድ ሁለቴ ሰብስብ ብሎ መጎብኘትና ቀጣይ አቅጣጫ መስጠት ተለምዷል ፡፡ ይህም ‹ ክትትልና ግምገማ › የተባለውን የቢኤስሲ ቅጽ ለማሳካት ግድ ስላለ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ክትትሉ 40 ከመቶው ላይ የተጀመረ ከሆነ እነ 80፤ 90 እና 100 ፐርሰንቶች ምን ይመስላሉ ብሎ የሚፈትሽ አይደለም ፡፡ ላይ ያለው አመራር አንድም በመሰላቸት አንድም ታች ያለውን አመራር በማመን / ምክንያቱም በእውቀት ሳይሆን በእምነት መምራት አስፈላጊ ነውና / የሚያመጣለትን ሪፖርት በመቀበል እንዲሳሳት ፤ ዋሾ እንዲሰኝ ብሎም እንዲታዘንበት መንገዱን ራሱ ያመቻቻል ፡፡

‹ ጨበጣው › የቱንም ያህል ሀሰት ቢሆን እንኳን አንዳንዴ ከፖለቲካ አንጻር አስፈላጊ እንደሚሆንም ግምት ውስት ማስገባት ያስፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም የደረሱ ተስፋዎች የተራቡ ሰዎችን ወዳላስፈላጊ ተቃውሞ ወይም ግጭት ከመክተት ይልቅ ‹ ጠባቂነታቸውን › እንዲያለመልሙ የሚገፋፋ ነውና ፡፡

ሁለተኛ ዙር ‹‹ ጨበጣ ››

ሁለተኛው ጨበጣ ከቁልፍ መረከብ በኃላ ያለውን ገጽታ የሚመለከት ነው ፡፡ ‹‹ ቁልፍ ማስረከብ ›› ከሚለው ሀረግ ትርጓሜ እንጀምር
፡፡ እንግዲህ በአማርኛ መግባባት እንደምንችለው አንድ የኮንዶሚኒየም ዕድለኛ ከአስተዳደሩ የቤት ቁልፍ ተረከበ የሚባለው ቤቱ አስፈላጊ የተባሉትን ግብዓቶች አሟልቶ ከተጠናቀቀ በኃላ የተዘጋውን ቤት ከፍቶ በመግባት ሲረካና ጎርደድ - ጎርደድ እያለ ሲቃኝ ነው ፡፡ በዚያ ላይ ዘመድ ወዳጅ ከኃላ ሆኖ ያን የፈረደበት ጭብጨባ ሲያዘንብለት ነው ፡፡

ይሁን እንጂ  ይህ ትርጉም ዛሬ በሰሚት ሳይት ቤታቸውን ለተረከቡ 5ኛና 6ኛ ዙር ባለእድሎች አልሰራ ብሏል ፡፡ እንዴት አላችሁ ?

ዕድለኞች አስፈላጊውን ፎርማሊቲ ካሟሉ በኃላ ከሚመለከተው ክፍል ተሰልፈው ቁልፉን ተረከቡ ፡፡ ቤታቸው ሲደርሱ ግን አብዛኛዎቹ በሮች ክፍት ነበሩ ፡፡ ‹ እንዴ ቁልፍ ሳንረከብ ቤቱ አየር ባየር ተመረቀ እንዴ ?! › ቢሉም ተሳሳቱ አይባልም ፡፡ 

እየቆዩ ሲሄዱ ግን የበሮቹ መከፋፈትን እየደነገጡ  ይረዳሉ ፡፡ አብዛኛዎቹ ቤቶች በራቸው የውሃ ልክ ክፍተት ስላለበት ፣ የመስታውት አለመኖር ፣የመክፈቻና የመዝጊያ ቁልፎች ባለመሰራታቸውና በሌሎች ምክንያቶች ሊዘጋ የቻለ አልነበረም ፡፡

መንግስት እንዴት ነው ክፍቱን የሰነበተ ቤት ቁልፍ ተረከቡ ብሎ የሚያውጀው ? እንዴትስ ነው የተጣመመ በር ፣ መዝጊያና መክፈቻው የማይሰራ ቤት ላስረክብህ እያለ የሚቀልደው ? በሩን ዘግቶ ባለማስረከቡ ምክንያት መስታውቶች እንዲሰበሩ ፣ የሽንት ቤትና የኩሽና ዕቃዎች እንዲሰረቁ ምቹ ሁኔታዎች ፈጥሯል ፡፡ ዕድለኛው ቤቱ የደረሰው በዕድሉና በነጻ ብቻ ነው እንዴ ? ለከፈለው ገንዘብ ተመጣጣኝና ትክክለኛ ዋጋ የማያገኘውስ በምን ስሌት ነው ? 
አስተዳደሩ ቁልፍ ከማስረከቡ በፊት የእያንዳንዱን ቤት ችግርና ጉድለት መፈተሸ ቢኖርበትም ይህን ‹ አብይ  › ውሳኔ ‹ ብ ›ን ገድፎ  ‹ አይ › በሚል በማንበቡ የመጣ ህጸጽ አስመስሎበታል ፡፡

ኮንዶና ጥራት

የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ የሚባለው ብሂል የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው አግሮ ስቶን ወደሚለው መልክ በተጨባጭ ተቀይሯል ፡፡ ኮንዶሚኒየምና ጥራት ሲወራላቸው እንጂ ሲመስሉ ለማየት ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ያስፈልጋል ፡፡

የግድግዳው ነገር ከተነሳ የቤቶቹ ክፍሎች የሚከፋፈሉት አግሮ ስቶን በተባለው ወጤት ነው ፡፡ ይህ ግድግዳ ደግሞ የሚሰራው አንዳንዶች የተስፋ ቡድን በሚሏቸው ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ነው ፡፡ ለነገሩ ማንም ቢሰራው ምክንያት አይሆንም ፡፡ የነገር ምክንያት የሚሆነው በምን ያህል ጥራት ሰሩት ? የሚለው ነው ፡፡ ይህ ምርት በተለይም በቻይና ፣ ማሌዥያና ሩቅ ምስራቆች ምን ያህል ውጤታማ / ከጥራትና ወጪ / እንደሆነ አንብቤያለሁ ፡፡ እውነቱን ለመናገር በኛ ሀገር ምርቱ የሚሰራው መኖሩን ለማሳወቅ ብቻ ይመስላል ፡፡  የበዛ የቸልተኝነት ጭቃ ምርቱ ፊት ላይ እንደተመረገበት ይታያል ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ቤቶች ውስጥ ገብታችሁ አካፋዩን ግድግዳ ስትመለከቱ ልታዝኑ አሊያም ሳቅ ሁሉ ሊያመልጣችሁ ይችላል ፡፡

ግድግዳዎቹ የተንገዳገዱ ፣ በቀጭን ጀምረው እንደ ዝሆኔ በሽታ ያለቅጥ ያበጡ ፣ እዚህም እዚያም የአይጥ ጉድጓድ የመሰለ ቀዳዳዎችን ያራቡ ፣ እንደ ጀማሪ ወታደር ‹ አሳርፍ ! › ቢባሉም ለመስመር መዛነፍ ቁብ ያልሰጡ ፣ ማንም እንዳይነካቸው ልመና የሚያበዙ የሚመስሉ አይነቶች ናቸው ፡፡ ብር ያላቸው ሰዎች በርግጫ ሳይሆን በኩርኩም ከጣሏቸው በኃላ አካፋዩን ግድግዳ በብሎኬት እያስገነቡ ነው ፡፡ ህጉ መንግስት የሰራውን ቤት መቀጠልም ሆነ መቀነስ አይቻልም ቢልም ፡፡ አብዛኛው ‹ መናጢ › ግን ‹ አካል ጉዳተኞችን መንከባከብ የዜግነት ግዴታ ነው ! › ለሚለው  የቆየ መፈክር ዋጋ እየሰጠ መሆኑ ታይቷል ፡፡  ይህ መፈክር እንዴት ትዝ አለው ጃል ? ይህን መፈክርስ በምን መልኩ ነው ተግባራዊ እያደረገ ያለው ? የሚሉ ጥያቄዋች ተደራርበው መምጣታቸው አይቀርም ፡፡ ትዝታውን ያጫረው ችግሩ ሊሆን ይችላል -  እንዴት ተገበረው የሚል ጥያቄ ከቀረበ -  መጀመሪያ ግድግዳዎቹ በደንብ ተደርገው በጀሶ ታሽተዋል ፡፡ ጀሶው ከደረቀ በኃላ ደግሞ እንዳቅሚቲ ቀለም እንዲፈስባቸው ተደርጓል ፡፡ ይህን ስራ የጨረሱ አንዳንድ ሰዎች ታዲያ አካፋዩን ግድግዳ እየተመለከቱ ‹‹ እውነት ያ አግሮ ስቶን ነው እንዲህ የሆነው ? ወይ ማየት ደጉ ?! ›› ይላሉ አሉ ፡፡ አንድ ቀን ድንገት ሸብረክ እንዳይል እየሰጉ ጭምር ፡፡

ከላይ እንደተገለጸው ከፍተኛ የሆነ የውጭ በር አሰራር ችግር በዝቶ ይታያል ፡፡ ወደ ማብሰያ ክፍል ስንገባ ቀድሞ የሚተዋወቀን ለዕቃ ማጠቢያነት የተገጠመው ሳህን ቢጤ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ በጣም በመሳሳቱና ሲገጠም በአንገቱ አካባቢ ጉዳት ስለደረሰበት እንደተጣመመ በሰለለ ድምጹ ነው ‹ ጌቶች/ እሜቴ እንኳን ለዚህ አበቃዋት ! › የሚለው ፡፡ ስስነቱና ኮሽኳሻነቱን እያገላበጡ ካጉረመረሙ ‹ ጌቶች/ እሜቴ እንዴ ቤት በማግኘትዋ ብቻ ሊደሰቱ ይገባል ! እንዴ ከስንት ሰልፈኛ ወይም ተስፈኛ መሃል ተመንጥቀው እንደወጡ ማሰብ ይገባል ?! › ሊልዎት ይችላል - ይኀው ሳህን ፡፡ አይልም ብለው ቅንጣት አይጠራጠሩ ! ከሁለትና ሶስት ዓመት በላይ ምን ሲሰማ የከረመ ይመስልዎታል ?!

ወደ መጸዳጃ ቤቱ ስናመራ የተሻለ ነገር እናያለን ፡፡ ግድግዳዎቹ በሴራሚክ የተለበጡ ናቸው ፡፡ መቀመጫዎቹና የእጅ መታጠቢያዎቹ ሳህኖች ለሀሜት የሚመቹ አይደሉም ፡፡ በእውነት ጥሩ ናቸው ፡፡ እዚህ ንዑስ ክፍል አቃቂር የሚወጣው ባድመ የኛ ትሁን የኤርትራ / ከህግ አንጻር / እንዳልተለየች ሁሉ የሽንት ቤቱ ሳህንና የገላ መታጠቢያው መኃል ወፈር ያለ ድንበር ሳይሰመር መቀላቀላቸው ነው ፡፡ ቀና ብለው የሚመለከቷት ትንሽ መስኮት ብዙ ቤቶች ላይ ተሰክታ እንጂ ተሰርታ ያለቀች አትመስልም ፡፡ እንደውም አንዳንድ ቤቶች የምትታየው መስኮት እና ኮፍያ ገልብጠው የሚዘንጡ የክፍለሃገር ልጆች ቁርጥ የአባት - የእናት ልጆች ይሆኑባችኃል ፡፡

ሁለተኛው ዙር ‹‹ ርክክብ ››

የከተማው አስተዳደር የነዋሪውና የመገናኛ ብዙሃን ግፊት ሲበዛበት በቅጡ ያላለቁ ቤቶችን ለማስረከብ የተገደደ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም ፡፡ ወይም ደግሞ  ‹ ጉጉው ነገር ግን ድሃው ነዋሪ ትንሽ ከጀመርኩለት ይጨርሰዋል › ከሚል ቀና አመለካከት በመነሳትም ሊሆን ይችላል ፡፡

ችግሩ ግን በዚህ ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑ ነው ፡፡ የሰሚት ሳይት ቤቶቹ ብቻ ሳይሆን አካባቢውም ለምቶ ባለመጠናቀቁ አስተዳደሩ ለሌላ ዙር ርክክብ ሳይዘጋጅ እንደማይቀር ይገመታል ፡፡ አብዛኛው ህንጻዋች ዙሪያ ገባቸው ለመፋሰሻና ለመከለያ አጥር ጥቅም ተቆፍረዋል ፡፡ ተቆፍረው ግን አልተገነቡም ፡፡ ከየጉድጓዱ የወጣው አፈር እዚህም እዚያም ተቆልሏል ፡፡ እዚህ ቁልል ላይ የሆነ ነገር ጻፍ ጻፍ ቢደረግ ብዙ ‹‹ ትክል ድንጋዮች››ን መፍጠር የሚቻል ይመስላል ፡፡

ዋና ዋናዎቹን የመኪና መንገድ ማሰብ ከቅብጠት እንዳይቆጠርብን እንተወውና አንዱን ህንጻ ከሌላው ሊያገናኝ የሚችል ቀጭን የእግር መንገድ እንኳ አይታይም ፡፡ ከህንጻዎቹ ፊት ለፊትና ኃላ የሚገኙ ክፍት ቦታዎች የራሳቸው ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ይታወቃል ፡፡ ይሁን እንጂ ሜዳዎቹ የግንባታ ፍርስራሽ፣ አፈር፣ ድንጋይ ወዘተ የሞላባቸው በመሆኑ ዕጣ ፈንታቸው ገና አልታወቀም ፡፡

እነዚህና አነዚያን የመሳሰሉ ኮተቶች ገና አልተነሱም ፡፡ ክረምት ላይ ጉድ ከሚያፈላው ጭቃ ለመከላከል የሚያስችሉ መሰረታዊ የእግር መዝለያ መንገዶች የሉም ፡፡ ይህ በራሱ የነዋሪውን ደስታ የሚያጨፈግግ ነው ፡፡ ገና ብዙ ስራዋች ይቀረዋል በሚል ቤታቸውን አዲስ በርና ቁልፍ ቀይረው የጠፉም ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ / ይህ የበር መዘጋት ደግሞ መድረሻ አጥተው ገና ከጠዋቱ ያለ መብራትና ውሃ እየኖሩ ለሚገኙ ነዋሪዋች ትልቅ ጉዳት ይፈጥራል ፡፡ ምክንያቱም መብራት ኃይልና ውሃና ፍሳሽ ብዙ ህዝብ ካልገባ አገልግሎቱን አንለቅም የሚል ብሂል አላቸውና / ለመሆኑ በዚህ መልኩ ነው እንዴ የርክክብን ‹‹ እርካታ ›› ማምጣት የሚቻለው ? ነው ኪራይ ሲቆነድደው ሮጦ ይገባል ፣ ከገባ በኃላ ደግሞ ለራሱ ጥቅም ሲል ‹ የኔን ስራ ይሰራልኛል › የሚል ስትራተጂ ተቀይሶ ነው ? ይህ ስልት አይፈጸምም - ተራ አሉባልታ ነው ከተባለ ግን አስተዳደሩ አሁን የተገለጹ ስራዎችን ለመጨረስ ቢያንስ ሁለት ዓመት ላይ የሚተኛ ይመስላል ፡፡ ምክንያቱም የአስተዳደሩ የፍጥነት ብቃት ወይም ቤዝላይን ይኀው ስለሆነ ፡፡ ነዋሪው እንደተለመደው ብዙ ካለቃቀሰ በኃላ ከእለታት አንድ ቀን ‹‹ ሁለተኛ ዙር ርክክብ ›› ያከናውናል ፡፡

ጠንጋራ አሰራሮችና ያልተወራረዱ ኪሳራዎች

የቤት ዕድለኞች ቤታቸውን የሚረከቡት ሁለት መሰረታዊ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ሲያሟሉ ነው ፡፡ የመጀመሪያው ዕጣው በወጣላቸው ማግስት የተተመነባቸውን ቅድመ ክፍያ በተባለው ግዜ ውስጥ መክፈል ነው ፡፡ ሁለተኛው ቀሪውን ዕዳ በረጅም ዓመታት የሚከፍሉት ከባንክ ጋር የውል ስምምነት በማድረግ ይሆናል ፡፡ መቼም አባታችን መንግስት ያጣ የነጣነውን እንደ እውነተኛ ልጁ ቢመለከተን ኖሮ በባንክ በኩል የሚያስከፍለንን ተጨማሪ የወለድ ክፍያ ያስቀርልን ነበር ፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህም ቢሆን ጥሩ ነው በሚለው ሀሳብ እንለፈው ፡፡

እዚህ አሰራር ውስጥ ግን ጥሩ ያልሆነ ወይም ጠንጋራ ነገር መብቀሉ ነው የሚያስከፋው ፡፡ መንግስት በሁለት መልኩ ተቃራኒ ጉዳዮችን ያከናውናል ፡፡ አንደኛው ወይም ቸር ገጽታው ቤት ተከራዮች ቤቱን ለማስጨረስ ብዙ ወጪ ስለሚያወጡ በየወሩ የሚከፍሉትን ክፍያ የሚጀምሩት ከዓመት በኃላ ነው ማለቱ ነው ፡፡ የእፎይታ ግዜ ይለዋል ሲያሰማምረው ፡፡ ዳሩ ግን ሁለተኛውን መልኩ ስንመለከት ‹ እፎይታው ወደ ወይዞታ / ወይኔ / ይቀየርብናል ፡፡

ሁለተኛው ወይም ክፉ ገጽታው ባንክ ከቤት ባለቤቶች ጋር የረጅም ግዜ ክፍያ ስምምነት ከተፈራረመ ማግስት ወለድ የማሰቡ አሰራር ነው ፡፡ መንግስት በአንድ በኩል ለዓመት ያህል ስለ ክፍያም ሆነ እዳ እንዳታስቡ አደርጋለሁ እያለ በሌላ በኩል ባንክ ገና ካልተገባበት ቤት ላይ ያለ ርህራሄ የደሃ ገንዘብን ይነጥቃል ፡፡ የእፎይታ ግዜ እያለ እንዴት ገንዘባችንን ትወስዳላችሁ ? ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ እኛ አትራፊ ድርጅት እንጂ መንግስት አይደለንም ! ›› የሚል ያልታረመ ምላሽ ይሰጣሉ ፡፡ ‹‹ የእፎይታ ግዜ የተሰጠው ዕዳውን ለመክፈል የሚጀመርበት ነው ›› በማለትም ርስ በርሱ የሚጋጭ አስተያየት ያስከትላሉ ፡፡ በነገራችን ላይ ነዋሪዎች የአንድ ወር ዕዳችሁን ባንክ ሄዳችሁ ካልከፈላችሁ ቁልፍ አይሰጣችሁም ተብለውም ተገደዋል ፡፡ ይህ ግዳጅ ለምን እንደተፈጠረም ግልጽ አይደለም ፡፡ ይህም ለእፎይታ የተሰጠችውን ግዜ በጠረባ መትቶ የዘረጋ አስመስሎታል ፡፡

ብዙ የጨነቃቸው ሰዎች የሚከተለውን ጥያቄ ራሳቸውን እየጠየቁ ስለሆነ እስኪ ይሞክሩት ዘንድ ጉዳዩን ላጋራዎ ፡፡
ዕዳ መክፈል  ወይም አገልግሎት ማግኘት ሳይጀመር ወለድን ማስከፈል ማለት ምን ማለት ነው ?

ሀ . እየኮረኮሩ ኪስን መፈተሸ
ለ . እጅን መጠምዘዝ
ሐ . ማጅራት መምታት
መ . መልስ የለውም

የባንክን አሰራር የሚነድፈው መንግስት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ መንግስት ለድሃው ካዘነ ብሎም አሰራሩ ሸፋፋ መሆኑን ከተገነዘበ ባንክን ማዘዝ ይችላል ፡፡ መንግስትን ከማርስ ባንክን ከጁፒተር የተገኙ አስመስሎ ማቅረብም ጅላጅነትን ከማጠናከር ውጪ ለእውነታው የሚጠጋ ምለሽ ሊሆን አይችልም ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ቤቱን ቶሎ የማያስረክበው መንግስት ሆኖ ሳለ ያለግዜው ወለድ የሚያስከፍለውም መንግስት መሆኑ ነው ፡፡ ቤቱን በተባለው ግዜ አስረክቦ፣ ህዝቡ መኖር ቢጀምር እንኳን የወለዱ ሂሳብ ትንሽ በተሻለ ነበር ፡፡ ያው የአንድ አመቷን  ‹ እፎይታ - ወይዞታ › በሚለው ሂሳብ አልፈነው ማለት ነው ፡፡
በየትኛውም አሰራር ቢሆን ማንኛውም ሰው አገልግሎት ላላገኘበት ነገር ወለድም ሆነ ቀረጥ እንዲከፍል አይገደድም ፡፡ ታዲያ የኮንዶሚንየም ነዋሪዎች ‹‹ እጣ ስለወጣላቸው ›› ብቻ ነው ኢ- ፍትሃዊ የሆነ ጫና ያረፈባቸው ?

በአንድ ወቅት ይህን ኢ- ፍትሃዊ ጉዳይ አስመልክቶ የተጠየቁ ኃላፊዎች ‹‹ እናዝናለን ! ›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ከጋዜጣ አንብበናል ፡፡ በርግጥ ማዘን አንድ ነገር ነው ፡፡ ሀዘን ግን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራውን በፍጹም አያካክስም ፡፡ በመንግስት ስህተትና ቸልተኛ አሰራር የሌለውን ድሃ መውቀጥ ኢ - ሞራላዊ ጉዳይ ነው ፡፡ መንግስት ከልቡም ይሁን ከአንገት በላይ ‹ እናዝናለን › ቢልም ለድሃው ግን ያልተወራረዱ ኪሳራዎች ናቸው ፡፡ ሲጀመር ድሃ ነው - በዚህ ድህነት ላይ ደግሞ ወደፊትም ድህነቱን የሚያወፍሩ ካፖርቶች እንዲደርብ ማስገደድ ፈጽሞ ትክክል ሊሆን አይችልም ፡፡ ይህን የመሰለ ጠንጋራ አሰራር ሳይውል ሳያድር መስተካከል ይኖርበታል ፡፡ ተናቦና ተማምኖ መስራት ያስፈልጋል ፡፡ ህጎችና ደንቦች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ቀጥተኛ እንጂ ያልተገባ ትርጉም እንዳያቅፉ መትጋት ግድ ይላል ፡፡

‎ሁለተኛው ሶማሌ ተራ ‎?




ከ 15 ቀናት በፊት በቁም ነገር መጽሄት ላይ የወረወርኳት ‹‹ የኮንዶ ጨበጣ ›› የምትሰኝ ጽሁፍ ከግራና ከቀኝ ልዩ ልዩ ምላሾችን አስገኝታለች ፡፡

ግራው ፤

በዚሁ መጽሄት በጥር ወር ዕትም ላይ ጉዳዩ የከነከነው አንድ የኮንዶሚንየም ነዋሪ የደረሰበትን ችግር ዘርዝሮ የጽሁፉ ርዕስ ጨበጣ ሳይሆን ለበጣ ቢባል ይገባዋል ብሏል ፡፡

ሌላ አንድ ሰው ጥቂት የቀሩ ያልተዳሰሱ ነገሮችን አስታወሰኝ ፡፡ የሌብነት ወይም የሙስና ጉዳይ ልንለው እንችላለን ፡፡ እንዴት መሰላችሁ ?

በሰሚት ሳይት ያሉ ኮንዶዎች እንደ በርና ሌላ ዕቃ ሁሉ የኤሌትሪክ መሳሪያዎችም የተገጠመላቸው አይደለም ፡፡ እናም እድለኛው እንደተለመደው ተሰልፎ ነው ዕቃዎቹ ተቆጥረው የሚሰጠው - በመርህ ደረጃ ማለት ነው ፡፡ አነዚህ ዕቃዋች ባለሙያዎቹ ሶኬት ፣ ቱ ዌይ ስዊች ፣ ዋን ዌይ ስዊች ፣ ቆጣሪ የሚሏቸውን ማለቴ ነው ፡፡

በተግባር አይን ግን ንብረቱን የሚያስረክቡ ሰራተኞች ለህዝቡ የሚሰጡት እያጎደሉ ነው ፡፡ ከአንዳንዱ ግማሽ ያህል ፡፡ ነዋሪው በወቅቱ ስንት ሶኬት እንደሚያስፈልገው መረጃ አልነበረውም ፡፡ የሰጡትን ልክ እንደ እርዳታ ተቀባይ ‹‹ እግዜር ይስጥልኝ ! ›› ብሎ ነው የተቀበለው ፡፡ ይህ ህዝብ ስንቱ እየጋጠው ትህትናው አያልቅበትም ፡፡ ችግሩ አፍጥጦ የመጣው ቤቱ ገብቶ ለሶኬት የተሰሩ ቀዳዳዋችን ሲቆጥር ነው ፡፡ ቀዳዳዋቹና የተሰጡት ቁሳቁሶች እንደ ሰማይና ምድር የተራራቁ ናቸው ፡፡ ይህን ሲያውቅ ንብረት ሰጪዋች ላይ ማፍጠጥ ጀመረ ፡፡ እነሱም በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ‹‹ በስህተት ስለሆነ መጨረሻ ላይ ይሰጥሃል ! ›› እያሉ ሸኙት ፡፡ ህዝቡም አለ ‹‹ አዋ ! ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም ! ›› የሚሰራ ሰው ሰው ይሳሳታል የሚል ጥቅስ በመጨመርም ነገረ ጉዳዩን እንደ አርማታ ያጠናከሩም ነበሩ ፡፡ ምክንያቱም ይህ ህዝብ ቡቡነቱ አያልቅበትም ፡፡

በኃላ መሳሪያውን የሚገጥሙ የኤሌትሪክ ሰራተኞች በየቤቱ ለስራ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ አሁንም ህዝቡ ‹‹ እረ ማስገጠም አልቻልንም ፡፡ አገልግሎቱ ሊያልፍብን ስለሆነ ንብረታችን ይሰጠን ? ›› በማለት መጠየቅም መለመንም አስከተለ ፡፡

‹‹ ለሁሉም ሰው አድለን ስላልጨረስን አሁን መስጠት አንችልም ፡፡ የምትቸኩሉ ከሆነ እየገዛችሁ አስገጥሙ ››
‹‹ ታዲያ መቼ ይሰጠናል ? ››
‹‹ መጨረሻ ላይ ! ››
‹‹ ይሄ መጨረሻ መቼ ነው መጨረሻው ?! ››

መጨረሻው ቅርብ ሊሆን አልቻለም ፡፡ በዚህ የተበሳጨው ህዝብ ፍትህ በሌለበት ከተማ ጉሮሮን ከመሰንጠቅ ገዝቼ ላስገጥም ማለት ጀመረ ፡፡ ይህ ህዝብ ቢበሳጭም ቻይነቱ አያልቅበትም ፡፡ እናም የኤሌትሪክ ሰራተኞች ሀሳቡን ሲረዱ አንድ ሀሳብ ሹክ ማለት ጀመሩ ፡፡ ለነገሩ ሹክታ ሳይሆን ማማከር ጀመሩ ማለት ይሻላል

‹‹ አንድ ሶኬት ውጭ የሚሸጠው 35 ብር ነው ፡፡ እዚህ ግቢ ግን 25 ብር የሚሸጡ ሰዋች አሉ ››
‹‹ ይህማ ጥሩ ነው ፡፡ በል አሳየንና እንግዛ ››
‹‹ ቆይ ደውዬ ልጠይቅላችሁ ›› ባለሙያው አንድ ሰው  ጋ በመደወል ስለዕቃው መኖር ይጠይቃል ፡፡ቀዳዳውን ቆጥሮም የሚያስፈልገውን ብር አሰሪውን ይጠይቃል ፡፡ በሩጫ ብር ብሎ ይሄድና አዳዲስ እቃዋች ይዞ ይመጣል ፡፡  ‹ እንዴት ያለ ቸር ነው › የሚሉ ነበሩ - ምክንያቱም ይህ ህዝብ ምስኪንነት አያልቅበትም ፡፡

ጥቂት ለመጠየቅና ለመጠራጠር የተፈጠሩ ደግሞ ‹‹ ለምን ብቻውን መሄድ ፈለገ ? የህንጻ መሳሪያዎች ሱቅ ሳይኖር የሚገዛው ከነማን ነው  ? ሮጦ ሄዶ ለገዛበት የአገልግሎት የማይጠይቅ የቤቶች ልማት ሰራተኛ በቢኤስሲ ነው በካይዘን ሳይንስ የተገኘ ? ›› የሚሉ ጥያቄዎችን በውስጡ ያንሰላስል ነበር ፡፡

የዚህን እውነት ማወቅ ከባድ አይደለም ፡፡ ከብዙዎች ሆን ተብሎ እየጎደለ የተሰጠው ዕቃ የመጨረሻ ግቡ ለራሱ ለባለቤቱ እንዲሸጥ በመታቀዱ ነው ፡፡ በአዲስ አበባ ታሪክ የራሳቸውን ዕቃ ከሶማሌ ተራ የሚገዙት ባለመኪናዋች ነበሩ ፡፡ ዛሬ ይህ ልምድና ተሞክሮ ተስፋፍቶና ተቀምሮ ሰሚት ሁለተኛው ሶማሌ ተራ ሆኗል ፡፡ በመንግስት ሀገር ?!

በአሁኑ ወቅት በሰሚት ኮንዶ ሳይት ዋናውን የማብሪያና ማጥፊያ / ቆጣሪ / መግጠም አልተቻለም ፡፡ እቃው አስቀድሞ ከተገጠመ በሌቦች ይሰረቃል በሚል ቀድሞ እንዲሰራ አልተደረገም ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ሶኬቶቹ እየተገጠሙ ቢሆንም የሚመለከተው ክፍል እነዚህን ዕቃዎች ለኤሌትሪክ ባለሙያዋች ማስረከብ ባለመቻሉ ስራው ቆሟል ፡፡ ሁልግዜም ሰራተኞቹ የሉም ፣ ስብሰባ ላይ ናቸው ወዘተ ነው የሚባለው ፡፡ ምናልባትም ያስፈልጋል የተባለውን ዕቃ ለመቸብቸብ እቅድ እየተነደፈለት ይሆን ? የሚል ጠርጣሪ መኖሩ ግልጽ ነው ፡፡ እረ ተቸብችቧል የሚል ርግጠኛም ጥቂት የሚባል አይደለም ፡፡ እና መብራት ኃይል ደግ ሆኖ እንኳ ለአካባቢው ኃይል ለመዘርጋት ቢፈልግ ቆጣሪው ካልተሰራ የህዝቡ ፍላጎት አይሟላም ማለት ነው ፡፡

ቀኙ ፤

‹‹ የኮንዶ ጨበጣ ›› የተሰኘው አርቲክል ያስገኘው ሌላ አዎንታዊ ምላሽም አለ ፡፡ ጽሁፉ በተለቀቀ ሳምንት የከተማው አስተዳደር ሰሚትን ጨምሮ ሌሎች የቤት ልማት ቦታዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል ፡፡ ጠበቅ ያለ ትዕዛዝም አስተላልፏል ፡፡ ‹‹ ስራችሁን እስከዚህ ወር ድረስ ካላጠናቀቃችሁ ኮንትራቱን እንቀማችኃለን  ! ››

አስተዳደሩ የህዝብን ስሜት ማንበብና ማዳመጥ ከቻለ አንድ ርምጃ ነው ፡፡ ርምጃው ሙሉ የሚሆነው ግን የመጨረሻውን ውጤት በፍጥነትም በጥራትም ማስገኘት ሲቻል ነው ፡፡ ሌላም ጥቅም አለው ፡፡ ዶ/ር መራራ ጉዲና ኢህአዴግ ጆሮ የለውም የሚል የሰላ ትችት አላቸው ፡፡ ግዜው የምርጫ ሰሞን ሆነም አልሆነም ህዝብ ፈጣን ምላሽ ይፈልጋልና መስማትና ማየት እንደሚቻል በተግባር ማረጋገጥም ፖለቲካዊ ፋይዳ ይኖረዋል ፡፡

አስተዳደሩ ሳይቶችን ከጎበኘ አራት ቀን በኃላ ወደ ሰሚት ሳመራ ሁለት አዳዲስ ነገሮችን ተመለከትኩ ፡፡ አንደኛው ዋና ዋና መንገዶችን ለመስራት ቁፋሮው መጧጧፉን ፡፡ ሁለተኛው በየብሎኩ የተቆፈሩ ጉድጓዶች ውስጥ የግንብ ስራው በተሻለ የሰው ኃይል እየተከናወነ መገኘቱን ፡፡ በርግጥ ጅምሩ እንደተለመደው የአንድ ሰሞን እንዳይሆን ጸሎት ያሰፈልገዋል ፡፡ ለማንኛውም አስተዳደሩ ስራውንም ማጧጧፍ፣ ሌብነቱንም ማስቆም፣ ዘራፊዎችንም መዳኘት ይጠበቅበታል ፡፡ ምክንያቱም ይህ ህዝብ በብዙ ሊካስ ይገባዋልና ፡፡

Thursday, November 22, 2012

የአምባገነኖች ቀልድ



ለተለያዩ ስራዎች የተለያዩ መረጃዎችን ሳገላብጥ ካሰባሰብኳቸው አምባገነናዊ ቀልዶች የተወሰኑትን እነሆ ብያለሁ ፡፡ ካዝናኗችሁ ዘና በሉባቸው ፡፡

ሂትለር በገነት

አዶልፍ ሂትለር  እንደሞተ ራሱን ከሲኦል በር ጋ አገኘው ፡፡ ሲያንኳኳ በሩን ከፍቶ የወጣው ሰይጣን ‹‹ ስምህ ማነው ? ›› ሲል ጠየቀው
‹‹ አዶልፍ ሂትለር ››
 ሰይጣን በጣም እየተገረመ  ‹‹ በምድር ላይ ምን እንደሰራህ አውቃለሁ ፤ ወደ ውስጥ እንዳላስገባህ ቦታ የለም ፡፡ በርግጥ ሲኦል ቢሆንም ለሁሉም ነገር ወሰን አለው፡፡ ለምን ወደ ገነት አትሄድም  ?››
‹‹ አላውቀውም ! ››
‹‹ ይህን መንገድ ተከተል ፡፡ በስተቀኝ በኩል ትልቅ በር ታገኛለህ ፡፡ አታጣውም ››
ሂትለር ባልጠበቀው ጥሩ እድል እየተደሰተ ወደ ገነት ተጓዘ ፡፡ በቀጣዩ ቀን የሲኦል በር ተንኳክቶ ሰይጣን በሩን ሲከፍት እየሱስን ቆሞ ተመለከተ
‹‹ እየሱስ ! እዚህ ምን ታደርጋለህ ?! ›› በግርምት ጠየቀው
‹‹ ከካምፕ ጠፍቼ ነው የመጣሁት ! አመጣጤም የፖለቲካ ጥገኝነት ለመጠየቅ ነው ›› ሲል እየሱስም መለሰ

የስታሊን ግርፍ

            ከጆርጂያ የመጡ የልዑካን ቡድን አባላት ለረጅም ሰዓታት ከስታሊን ጋር ስለ ልማትና እርዳታ ከተወያዩ በኃላ በሚደረግላቸው ትብብር  በመርካት ቢሮውን ለቀው ወጡ ፡፡ ስታሊን ሲጋራ የሚያጨስበትን ትቦ መሳይ ነገር በማጣቱ  ወዲያው አንድ ስራውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ደህንነት  ሰው ጋ ደውሎ ሲጋራ ማጨሻውን ነጥቆ እንዲያመጣ ያዘዋል ፡፡ ነገር ግን  ከ30 ደቂቃ በኃላ ዕቃውን ጠረጼዛ ስር በማግኘቱ የላከው ሰው ጋ በመደወል ትዕዛዙን ትቶ እንዲመጣ ይነግረዋል ፡፡
‹‹ አዝናለሁ ጓድ ስታሊን ! ››
‹‹ምን ተፈጠረ ?! ››
‹‹ ከልዑካን ቡድኑ ግማሽ ያህሉ እኮ ዕቃውን መውሰዳቸውን አምነዋል ፡፡ የተቀሩት ደግሞ ጥያቄው  በሚከናወንበት ወቅት አልፈዋል ›› በማለት ምላሹን በስልክ አሰማ

የመሪዎች ፉክክር

           ንግስት ኤልሳቤጥ፣ ቢል ክሊንተንና ሮበርቱ ሙጋቤ እንደሞቱ ቀጥታ ወደ ሲኦል አመሩ ፡፡ ወዲያው ንግስት ኤልሳቤጥ ‹‹ እንግሊዝ በጣም ናፍቃኛለች፣ መደወል እፈልጋለሁ፡፡ ሁሉም ሰው ምን እያደረገ መሆኑን ማወቅ እፈልጋለሁ ›› በማለት ለ 5 ደቂቃ ያህል አወራች፡፡ ከዚያም ‹‹ ሰይጣን ስንት ነው የምከፍለው ? ›› ስትል ጠየቀች
‹‹ አምስት ሚሊዮን ዶላር ›› አላት ፡፡ ቼክ ጽፋ ሰጠቸውና ወደ ቦታዋ ተመለሰች፡፡ ክሊንተን በኤልሳቤጥ ተግባር በመቅናቱ ‹‹ እኔም ወደ አሜሪካ መደወል እፈልጋለሁ ›› አለ፡፡ ለሁለት ደቂቃም አውርቶ ሂሳብ ሲጠይቅ 10 ሚሊዮን ዶላር ተጠየቀ፡፡ እሱም ቼክ ጽፎ ሰጠ፡፡
ሮበርቱ ሙጋቤም ከማን አንሳለሁ በሚል ስሜት ተነሳስቶ ‹‹ እኔም ወደ ዙምባብዌ መደወል እፈልጋለሁ ፣ ከቤተሰቤና ሚንስትሮቼ ጋር ማውራት እፈልጋለሁ ›› አለ ፡፡ ሙጋቤ ወሬውን ማቋረጥ ባለመቻሉ ለ10 ሰዓታት ያህል አወራ፡፡ ኤልሳቤጥና ክሊንተን ከየት አባቱ አምጥቶ ሊከፍል ነው በማለት መጨረሻውን ለማየት ቋመጡ ፡፡ ሙጋቤ እንደጨረሰ ሂሳብ ሲጠይቅ
‹‹ አንድ ዶላር ! ›› ሲል ሰይጣን መለሰለት
‹‹ ሂሳብ አትችልም እንዴ ?  ይህን ሁሉ አውርቼ  አንድ ዶላር ትለኛለህ ?! ››
‹‹ ባክህ እችላለሁ ! ሂሳቡ ይሔው ስለሆነ ወዲህ በል ! ››
‹‹አዝናለሁ አትችልም ! ››
‹‹ ሰውዬ ምን ነካህ ! ከሲኦል ወደ ሲኦል  እኮ ነው የደወልከው ! ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ጥሪ ነው ! ›› ሲል አምባረቀበት

የቴይለር ርህራሄ

ቻርልስ ቴይለር እና ሾፌራቸው በመኪና ወደ ዋና መንገድ ሲያመሩ አንድ አሳማ ገጩ ፡፡ አሳውም ወዲያው ሞተ ፡፡ ቴይለርም ለሾፌራቸው ‹‹ እዛ ወዲያ ወዳለው የእርሻ ቦታ ሂድና አሳማው ምን እንዳጋጠመው አስረዳ›› አሉት
ከአንድ ሰዓት በኃላ ሾፌራቸው ከእርሻው ቦታ ከሴቶች ጋር ሲመለስ ተመለከቱ ፡፡ በአንድ እጁ የወይን ጠርሙስ ፣ በሌላ እጁ ሲጋራ ጨብጧል
‹‹ ምን ሆንክ አንተ ;! ››
‹‹ ገበሬው ጠርሙስ ወይን፣ ሚስቱን፣ ሲጋራና ከእኔ ጋር ፍቅር የያዛትን የ 19 ዓመት ልጁን ሰጠኝ ››
‹‹ እንዴት ? ምን ብለህ ነግረሃቸው ነው ? ›› ቴይለር አፈጠጡ
‹‹ እንደምን አመሻቸሁ ! እኔ የቴይለር ሾፌር ነኝ ፣ እናም አንድ አሳማ ገድያለሁ ! ››

የፑቲን ስጋ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መጥፎ ህልም በሌሊት ቀሰቀሳቸውና እየተጨናበሱ ወደ ፍሪጅ አመሩ፡፡ ልክ ፍሪጁን እንደከፈቱ በመልክ በመልክ ተደርድረው የተቀመጡ ስጋዎች መንቀጥቀጥ ጀመሩ፡፡ በድርጊታቸው በመናደዳቸውም እንደሚከተለው ገሰጽዋቸው
‹‹ አትንቦቅቦቁ !! እኔ የመጣሁት ቢራ ለመጠጣት ብቻ ነው !! ››


የመለስ የጾታ ፍቃድ

አንድ ዝነኛ አርቲስት ክስ ተመስርቶበት ከታሰረ ትንሽ ቆየት ብሎ ነበር ። በዚህን ወቅት አንድ ታዋቂ አትሌት በውጭ ሀገር አስደናቂ ድል ተቀዳጅቶ ወደ አገሩ ሲገባ ጠ/ሚኒስትር መለስ አድናቆታቸውን ለመግለጽ ኤርፖርት ድረስ ሄደው ይቀበሉታል ። አትሌቱም አጋጣሚውን በመጠቀም አንድ አንገብጋቢ ጥያቄ እንዳለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይናገራል ።
« ምን ችግር አለ ጠይቃ » አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀለል አድርገው
« ቴዲ አፍሮ የተባለው አርቲስት ካልተፈታ በመጣሁበት አውሮፕላን እመለሳለሁ »
« ወዴት ? »
« ወደ ሌላ ሀገር ፣ ጥያቄዬ ምላሽ ካላገኘ ዜግነቴንም ለመቀየር እገደዳለሁ »
« ወንድም ፣ እንኴን ዜግነትህንም ጾታህንም መቀየር ትችላለህ » አሉት ቆምጨጭ ብለው

የሙሻራፍ ፈተና

ፔርፔዝ ሙሻራፍ ወደ ደልሂ ለስብሰባ ሲያመራ ከህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ቫጅፔይ ጋር አጭር ቆይታ አደረገ ፡፡ ቫጅፔይ ‹‹ ስለ ካቢኔ አባላትህ እውቀት ምን እንደምታስብ አላውቅም፡፡ የኔ ሰዎች ግን በእጅጉ ጎበዞች ናቸው ›› ይለዋል
‹‹ እንዴት አወቅክ ? ›› ሙሻራፍ ይጠይቃል
‹‹ ቀላል ነው፡፡ ሁሉም ሚንስትር ከመሆናቸው በፊት ልዩ ፈተናዎችን ይወሰዳሉ ፡፡ ቆይ አንድ ግዜ ›› ይልና አድቫኒ የተባለውን ሚኒስትር ጠርቶ ይጠይቀዋል
‹‹  ያንተ ወንድም አይደለም፣ ያንተ እህት አይደለችም ፣ የአባትህ ልጅና  የእናትህ ልጅ ማነው ? ››
‹‹ ይህማ ቀላል ነው፡፡ እኔ ነኛ ! ›› ሲል አድቫኒ ይመልሳል
‹‹ ጎበዝ አድቫኒ ! ›› ቫደፓዬና ሙሻራፍ ተገረሙ
ሙሻራፍ ወደ ኢስላማባድ ሲመለስ ስለ ሚንስትሮቹ አዋቂነት በጣም እየተገረመ ነበር ፡፡ በመጀመሪያ ስብሰባውም በጣም የሚወደውን የካቢኔ አባል ጠርቶ ‹‹ የአባትህ ልጅና የእናትህ ልጅ ማነው ? ያንተ ወንድም አይደለም ፣ ያንተ እህት አይደለችም.፣ እሱ ማነው ? ›› ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ቢያስብ መልሱ ለመጣለት አልቻለም፡፡
‹‹ ትንሽ አስቤ ነገ መልሱን ባመጣስ ? ›› ሲል ያስፈቅዳል
‹‹ እንዴታ ! 24 የማሰቢያ ሰዓታት ተሰጥቶሃል ! ›› ሙሻራፍ መለሰ
ባለስልጣኑ ሚኒስትሮች፣ የካቢኔ ጸሃፊዎችና ትላልቅ ሰዎች ጋ እየደወለ ቢጠይቅ መልሱን ማግኘት አልቻለም ፡፡ ባለቀ ሰዓት ቤናዚር ቡቶ ብልህ ስለሆነች ታውቃለች በሚል ስልኩን መታና ‹‹ የአባትሽና የእናትሽ ልጅ የሆነ፤ ወንድምሽና እህትሽ ያልሆነ ማነው ?›› ሲል ጠየቃት
‹‹ በጣም ቀላል እኮ ነው ፡፡ እኔ ነኛ !! ›› ስትል መለሰችለት ፡፡ የካቢኔው አባል ደስ ብሎት ወደ ሙሻራፍ ደወለ ፡፡
‹‹ ጌታዬ መልሱን አግኝቼዋለሁ ፤ ቤናዘር ቡቶ ናት ›› አለ
‹‹ አንተ ደደብ ! አይደለም ›› አሉ ሙሻራፍ በቁጣ ‹‹ መልሱ አድቫኒ ነው !! ››
አይ ሙሻራፍ ???

የአህመዲንጃድ ቆምጫጫ ምላሽ

የኢራኑ ፕሬዝዳንት መሀመድ አህመዲንጃድ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ተጋብዘው ስለ ሀገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ከንግግራቸው በኃላ የተለያዩ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ጀመሩ ፡፡
‹‹ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ችግር እንዳለባችሁ ምእራባዊያን ይናገራሉ፡፡ እውነት ነው ; ››
‹‹ ወረኛ በላቸው ! ዛሬ የተሻለ መብትም ሆነ ዴሞክራሲ ያለው ኢራን ውስጥ ነው ››
‹‹ እሺ እዛጋ ጆሮህን እንደ ሴት የተበሳሐው ! ›› ፕሬዝዳንቱ ለሌላ ጠያቂ ዕድል ሰጡ
‹‹ አመሰግናለሁ ፡፡ በሀገራችሁ ምን ያህል ግብረ ሶዶማዊያን ይገኛሉ ; ››
‹‹ በታላቋ አራን ይህን የሚፈጽሙ ሰዎች የሉም ! ››
‹‹ መረጃዎች የሚጠቁሙት ግን በግብረሶዶማዊያን ላይ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት እንደምትፈጽሙ ነው ›› ሌላ ጠያቂ
‹‹ ወንድሜ ጥያቄ መደጋገም ለምን ያስፈልጋል! በሀገራችን የሉም አልኩህ እኮ ! ምክንያቱም ሁሉንም ጨርሰናቸዋል ! ››

የአሳድ ትዕዛዝ

በሀገሪቱ ከተደረገ አጠቃላይ ምርጫ በኃላ አንድ ሚንስትር እየተቻኮለ ወደ ሶርያው ፕሬዝዳንት ሃፌስ አሳድ ቢሮ ይገባል
‹‹ እሺ ! ›› አለ አሳድ ካቀረቀረበት ቀና ሳይል
‹‹ የተከበሩ ፕሬዝዳንት! እጅግ በጣም ደስ የሚል ዜና ይዤ መጥቻለሁ ፡፡ በምርጫው 98.6 ከመቶ አሸንፈዋል፡፡ እርስዎን ያልመረጡት ከ 2 በመቶ በታች የሚያንሱ ሰዎች ናቸው ፤ ከዚህ በላይ ምንም የሚፈልጉ አይመስለኝም ጌታዬ ;! ››
‹‹ እፈልጋለሁ ! እፈልጋለሁ እንጂ አንተ !! ›› አለ አሳድ ካቀረቀረበት ቀና ብሎ እያፈጠጠ ‹‹ በአስቸኳይ ያልመረጡኝን ሰዎች ስም ዝርዝር ለቅመህ አምጣ !!! ››

የማኦ ፈስ

አንድ ቀን የቻይናው ሊቀ መንበር ማኦ የግል ሀኪማቸውን ዶ/ር ዣንግን ጠርተው የሚከተለውን አዘዙት
‹‹ ሆዴን በሚገባ መርምር! ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ጀምሮ በጣም እንግዳ ነገር እየገጠመኝ ነው ፡፡ በተደጋጋሚ ያስፈሳኛል ፤ ማለትም በየአምስት ደቂቃው ልዩነት… ይህ ከይሲ ነገር ሊቆም አልቻለም፡፡ እንግዳው ነገር ደግሞ ፈሱ ድምጽ የሌለው እንዲሁም ሽታው የማይታወቅ መሆኑ ነው ››
ማኦ ንግግራቸውን ከጨረሱም በኃላ ፈሱ ፡፡ ዶ/ር ዣንግን ከመድሃኒት ማስቀመጫ ሳጥናቸው ውስጥ የሆነች ጠርሙስ አወጡና
‹‹ ሊቀመንበር ማኦ ይህን መድሃኒት ለአምስት ቀናት በየአራት ሰዓቱ ልዩነት አንድ- አንድ በመውሰድ ተጠቀሙ ›› ብሎ ተሰናብቶ ወጣ
ከአምስት ቀናት በኃላ ማኦ ዶክተሩን አስጠርተው ይጮሁበት ጀመር ፡፡
‹‹አንተ የተረገምክ !! ምን ዓይነት መድሃኒት ነው የሰጠኀኝ ? አሁን ደግሞ በጣም ነው የባሰብኝ ፡፡ ትናንት በወጣቶች ስብሰባ ላይ ንግግር ሳደርግ ያለማቋረጥ እየፈሳሁ ነበር ፡፡ ድምጹ በጣም የሚጮህ ስለነበር አሳፍሮኛል ! ››
‹‹ ሊቀመንበር ማኦ አሁን የመስማትዎ ችግር ተቀረፈ ማለት ነው ›› አለ ዶክተሩ ኮስተር ብሎ ‹‹ አሁን የሚቀረኝ እንደምንም ብዬ የአፍንጫዎን ችግር ማስተካከል ይሆናል !! ››

Monday, November 12, 2012

የላቀ ክብር - ለሚገባው መሪ



ደቡብ አፍሪካዊያን የቀድሞ ጀግና መሪያቸውን አልፎ አልፎ ብቻ በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ማስታወስ አላረካቸውም ፡፡ በርግጥ በርካታ ኀውልቶችን ቀርጸውላቸዋል ፣ የመናፈሻ ቦታዎችን ገንብተውላቸዋል ፣ ሌላም ሌላ ፡፡ ይህም ለዓለም ምርጡ ሰው በቂ አይደለም ፡፡ ምግባሩ እንደ ኤቨረስት ተራራ የገዘፈ ሰው ሁሌም የስስትና የአድናቆት አይን ሊርቀው አይገባምና እንደ ሌሎች ሀገሮች በቁልፍ ማንጠልጠያ ወይም በፖስት ካርድ ላይ ማስተዋወቅም ከሰሞነኛ ጉዳይነት የሚራመድ አልመሰላቸውም ፡፡

በጥልቀት አሰቡበት ፡፡
አንድ ሁነኛ ዘዴም አገኙ ፡፡

ዓለም የሚወደውን መሪ ዘወትር እየተመለከተ ማድነቅ የሚገባው በቅርበት ኪሱ ውስጥ ሲያገኛቸው ነው ፡፡ እናም የሀገራቸውን የብር ኖት / rand / መቀየር ወደዱ ፡፡ አዲሶቹ የብር ኖቶች ባለ 10፣ 20፣ 50፣ 100 እና 200 ራንዶች ሲሆኑ በሁሉም የመጀመሪያ ገጽ ላይ የታላቁ መሪ የኔልሰን ማንዴላ የፊት ገጽታ እንዲታይ ተደረገ ፡፡ ደቡብ አፍሪካዊያን ብልሆች ናቸውና ትልቅ ገቢ ከሚያስገኙበት ዘርፍ አንደኛ የሆነውን ቱሪዝም ይበልጥ ለማስተዋወቅ በገንዘቡ የኃላ ገጽ ላይ ትላልቆቹ አምስቶች / Big Fives / የሚሏቸውን የዱር እንስሳት ማለትም አንበሳ፣ ነብር፣ አውራሪስ፣ ጎሽ እና ዝሆንን አተሙበት ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ፡፡

የሀገር መሪን በገንዘብ ላይ ማተም ለዓለማችን አዲስ አይደለም የሚል አስተሳሰብ ሊነሳ እንደሚችል አስባለሁ ፡፡ በርግጥ ሀሳቡ የሸመገለ ነው ፡፡ የማያረጀው ጥያቄ የማስተዋወቁ ሂደት ወይም የተሰጠው ዕውቅና የተከናወነው በዲሞክራት መንገድ ወይስ በኩዴታ የሚለው ይሆናል ፡፡ ሁሉንም መመዘዎች ብንጨፈልቅ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን እናገኛለን ፡፡

አንደኛው አምባገነን መሪዎች የራሳቸውን ግለሰባዊ አምልኮ / Personality Cult / ለመገንባትና ህዝቡን ጸጥ ለጥ አድርገው ለመግዛት በማቀድ ወይ በራሳቸው ሙሉ ፍቃድ አሊያም በከበቧቸው ጥቅም ፈላጊዎችና ሆዳም ካድሬዎችና አጫፋሪዎች ጎትጓችነት የሚከናወን ነው ፡፡ ሁለተኛው ለሀገራቸው ነጻነት፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና ፍትህ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት አምጥተው እውነተኛው ህዝብ / fake ያልሆነው / መሪውን ለማክበርና ለማስታወስ ሲል ያመነጨው መንገድ ነው ፡፡

እንግዲህ በብር ላይ የምናየው የፊት ገጽታ የሚፈጠረው በዚህ መሰል አግባብ ነው ፡፡ በጣም የሚገርመው ግን በሀገራቸው ገንዘብ ላይ ከወጡ መሪዎች 90 ከመቶው ያህል አምባገነኖችና የማይገባቸው መሆኑ ነው ፡፡ አንድ ከሩቅ አንድ ከቅርብ ላንሳ ፡፡

የሩቁ ፤

በርማን ከ1962 እስከ 1981 የገዟት ኒ ሊዊን በገዳይነታቸውና በአምባገነንነታቸው ይታወቃሉ ፡፡ በአንድ ወቅት ብድግ ብለው የሀገራቸውን ገንዘብ ባለ 15፣ 35፣ 45፣ 75 እና 90 ኖቶች በማድረግ ከምስላቸው ጋር አተሙት፡፡ ዓለም እንዲህ ለየት ያለ ባለ ጎዶሎ የብር ቁጥሮች ስለማትታወቅ የተለየ አትኩሮት መፍጠር መፈለጋቸው አንድ ጉዳይ ነበር ፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ባለ ‹‹ 90 ›› ብር ኖቱን የሚመለከተው ነበር ፡፡ ይህን ብር ያሳተሙት የሚያማክሯቸው ‹‹ ጠንቋዮች ›› ዘጠና ዓመት ይነግሳሉ ብለው ሹክ ስላሏቸው ነበር ፡፡

የቅርቡ ፤

በኮንጎ ነብር የሚመሰለው እንደ አዋቂ፣ ጠንካራና ተመላኪ ነገር ነው ፡፡ ይህን የሚያውቁት ሞቡቱ ሴሴኮ በነብር ቆዳ የተሰራች ኮፍያ አትለያቸውም ነበር ፡፡ በዚህ ብቻ መታወቅ ግን አላረካቸውም ፡፡ እናም የሀገራቸውን ብር በመቀየር በአንደኛው ገጽ ላይ የነብር ኮፍያና ነብራማ ፊት አሳይተው፣ ይህም አልበቃ ስላላቸው ከአጠገቸው የሚወረወር የነብር ስዕል አስለው ገጭ አሉ ፡፡ ላለማስፎገር ደግሞ ከብሩ ጀርባ ለኮንጎ የሃይል ምንጭ ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የኢንጋ ግድብ በሰፊው አዘረጉት ፡፡ ከዚያም ይህንን የግለሰብ ገጽታ ግንባታ ‹‹ ዛየርናይዜሽን ›› ብለው ለሚጠሩት አሰልቺና አደንቋሪ ፕሮፓጋንዳ ከ30 ዓመት በላይ ማቀጣጠያ አደረጉት ፡፡

ከሀገራችን ተነስተን ሩቅ እስከሚገኙት ዋልታዎች  ድረስ ብናስስ አያሌ ገዳይ፣ የህዝብ ፍቅር የሌላቸው፣ ሙሰኞችና አምባገነን መሪዎች በጉልበት  የህዝብ ሃብት የሆነው ገንዘብ ላይ ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ በጉርድ፣ በቁመት፣ በፈገግታ፣ በቁጣ፣ በስላቅ፣ ፎቶ በመነሳት የፈነጩበት መሆኑን እንረዳለን ፡፡

ርግጥ ነው አፓርታይድ የተባለውን አስከፊ ስርዓት ለማስወገድ ብጥብጥ አልባ የተባለ ሰላማዊ ትግል እንዲሁም የሲቪል አለመታዘዝ እንቅስቃሴን በመፍጠር ሀገራቸውን ነጻ ያወጡት ማህተመ ጋንዲም በብር ኖት ላይ ደምቀው ታይተዋል ፡፡ እኚህ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ መሪ ፍጹም በሆነ የሰው ልጆች ፍቅር የሚታወቁ፣ ንብረትና ሃብት ለህዝቤ እንጂ ለእኔ ወይም ለዘመዶቼ በተለየ መልኩ አይገባም ብለው በማይታመን ኑሮ ውስጥ ያለፉ፣ የታገልኩት ራሴን ለማሳበጥ ሳይሆን የህዝቤን ነጻነት ለማጎናጸፍ ነው በሚል በህንድ የማይታመን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲዘረጋ፣ ዛሬም ሀገሪቱ ተጠቃሽ እንድትሆን ያደረጉ በመሆናቸው ህዝቡ የሰጣቸው ዕውቅና የሚበዛባቸው አልነበረም ፡፡

ማህተመ ጋንዲን የሚተኩ የዓለም መሪዎች ግን በቀላሉ እየተገኙ አይደለም ፡፡ በርግጥ በአሁኑ ዘመን ከአፍሪካ ብቸኛው ተኪ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ናቸው ፡፡ እኚህ ሰው ‹‹ የዚህ ትውልድ ታላቁና ጀግና መሪ ›› መሆናቸውን ዓለም በተመሳሳይ ቋንቋ መስክሯል ፡፡ 27 ዓመታት በእስር ያማቀቃቸውን ስርዓት በይቅርታ አስተማሩት እንጂ አልተበቀሉትም ፡፡ እንደ ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ግዜንና አጋጣሚን እየተጠቀሙ የበደላቸውን ወይም በዳይ የመሰላቸውን አልገደሉም ፣ አላሰሩም ፣ ሰበብ እየፈለጉ አላስጨፈጨፉም ፡፡ በዚሁ ሰበብ ህዝቦችን አልከፋፈሉም ፣ የማይዋጥ ወይም የማይፈለግ ርዕዮት አላሸከሙም ፡፡ አንዱን እውነተኛ  ሌላውን ጸረ ህዝብ በማለት አላሸማቀቁም ፡፡ አንዱ ባማረ ቪላ ሌላውን በየመንገዱ እንዲተኛ አላስፈረዱም ፣ አንዱን ባለ ሃብት ሌላውን ለምኖ አዳሪ እንዲሆን ክፉ መንገድ አላሳዩም ፡፡ ህዝቦችን በፍቅር አቅፈው ሳሙ እንጂ አልተዛበቱም ፣ አልተሳደቡም ፡፡ ስለደማሁና ስለቆሰልኩ ስልጣን ሁሉ ለእኔና በእኔ ፍላጎት ላይ ብቻ ይመሰረታል በማለት ‹‹ ወንበሩ ›› ላይ አልተሰፉም ፡፡ ስልጣን ገደብ ይኑረው የሚል ጠቃሚ ምክር ለለገሱ  ‹‹ ስልጣን ናፋቂ… ስልጣን የሚሻ ብረት አንስቶ መድማት ይኖርበታል ›› በማለት የደደበ አስተምህሮ አላሰሙም ፡፡ በርግጥ እሳቸው ያደረጉት ፍጹም የሚያስገርመውንና ተቃራኒውን ነበር ፡፡ ለሁለተኛ ግዜ እንኳን ሳይወዳደሩ ስልጣናቸውን ለተተኪው ትውልድ ማሰረከብ ፡፡

እንደ እንክርዳድ የበዙ አምባገነን መሪዎች በየግዜው በሚፈሉባት አፍሪካ የዚህ ዓይነት ስብዓና የተላበሰ መሪ ይበቅላል እንዴ ? የዚህ ምርጥ ዘር ምንጭ እውነት አፍሪካ ነው ? ይህ ጥያቄ ነበር በወቅቱ ለዓለም ራስ ምታትና ጭንቀት የሆነው ፡፡ ወዲያው ግን ከጭንቀቱ ጥላ እየወጣ ማክበር፣ ማድነቅና በደስታ ማንባት ጀመረ ፡፡ አያሌ ውርደት የተሸከመቸው አፍሪካ በማንዴላ ተግባር መጽናናት ብቻ ሳይሆን እንደ ዔሊ የሸጎጠቸውን አንገት አውጥታ ዙሪያ ገባውን በልበ ሙሉነት መቃኘት ቻለች ፡፡ አለም ደስታ መግለጫ ቃላት ተቸገረ ፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት 250 የሚደርሱ ልዩ ልዩ ሽልማቶች ለማንዴላ የተሰጡትም በዚሁ አግባብ ነበር ፡፡ በ1993 ደግሞ የኖቤል ተሸላሚ ሆኑ ፡፡ ህዳር 2009 በተመድ ውሳኔ ሀምሌ 18 ቀን የማንዴላ የልደት በዓል ‹‹ የማንዴላ ቀን ›› ተብሎ እንዲከበር ተደረገ ፡፡

ጎበዝ ማንዴላና የዛሬ የክብር ሽልማታቸው የመነጨው እንግዲህ በሳቸው ፍላጎት ወይም በካድሬዎቻቸው ብልጣ ብልጥ የፖሊሲ ቀረጻ ምክንያት ሳይሆን ባገጠጠውና በማይካደው ተግባራቸው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ፡፡  በሌላ አነጋገር የተወሰኑ ቲፎዞዎች ተጽዕኖ ፈጥረው ባስገኙት ወፍራም ጭብጨባ ብቻ አይደለም ፡፡ አኩሪ ስራ ለሰሩ የሀገር መሪዎች ተገቢውን ዕውቅናና ክብር መስጠት ግድ ይላል ፡፡

የሰው ልጆች ፍቅር፣ እኩልነት፣ ነጻነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲን ከምንም በላይ አብልጠው ይፈልጋሉ ፡፡ አፍሪካም ለገዳይና አምባገነን መሪዎች የሚሰጠው ፕሮፓጋንዳዊ እውቅና ይቆም ዘንድ መታገል ይኖርባታል ፡፡

ረጅም ዕድሜ ለማንዴላ ዓይነቶች !!!

Thursday, November 1, 2012

እውነት ሱዳን እያሴረችብን ነው ?



አባይ በካርቱም

የጉዳዩ መነሻ ፤

በአባይ ወንዝ ላይ ‹‹ ቬቶ ፓወር ›› አለኝ የምትለው ግብጽ ኢትዪጽያ የጀመረቸውን ግድብ ለመደብደብ እቅድ መንደፏን ዊክሊክስ መዘገቡ ይታወሳል ፡፡ ከዚህ ዘገባ ይፋ መሆን በኃላ በኢትዮጽያና ግብጽ መካከል ያለው ግንኙነት መወጣጠሩ እንደቀጠለ ነው ፡፡

ግብጽ ‹ ወዳጄን › ኢትዪጽያን ለመተናኮል አላሰብኩም በማለት ማስተባበያ ብትሰጥም በ1929 በጸደቀው ስምምነት መሰረት በናይል ወንዝ ላይ ችግር ሲፈጠር የምንፈታበት ስምምነት ላይ ነው ከሱዳን ጋር የመከርነው ብላለች ፡፡ ነገሩ አልሸሹም ዞር አሉ ዓይነት መሆኑ ነው ፡፡ በወራሪዋ እንግሊዝ የጸደቀው የ1929ኙ ስምምነት ለግብጽ 55፣ ለሱዳን ደግሞ 18.5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ በዓመት እንዲያገኙ ፈቅዶላቸዋል ፡፡ በዚሁ መሰረትም ላለፉት 84 ዓመታት ሁለቱ ሀገራት ያለማንም ተቀናቃኝ ተጠቅመውበታል ፡፡

እነሆ ቤንች ላይ ተቀምጠው የውሃ ላይ ቦሊቦል ፣ የጀልባ ውድድር፣ የጠብታ መስኖ የመሳሰሉትን ጨዋታዋችና ስራዎችን  ሲመለከቱ የነበሩ ሀገሮች አጉራ ጠናኝ በማለት የአባይ ተፋሰስ ሀገሮችን ጥምረት አቋቁመው የእኩል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስምምነት እስከመፈረም ደርሰዋል ፡፡ ሞኝ ካመረረ በግ ከበረረ መመለሻ የለውም እንዲሉ የስምምነቱን የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚያበስረውን ስራ  በተግባር ለማስደገፍ ይመስላል ኢትዮጽያ 5250 ሜጋዋት የኤትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ በመስራት ለኩሳለች ፡፡ ሌሎቹም የሌላውን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ቀጣይ ስራቸውን ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

ግብጽ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የውሃው ከፍተኛ ተጠቃሚ በመሆኔና ትልቁ ስልጣንም በእኔ እጅ ያለ በመሆኑ ኢትዪጽያ የምትሰራውን ግድብ መመርመርና መረዳት አለብኝ ብትልም ኢትዪጽያ ይህን ለማድረግ መጀመሪያ ስድስቱ ሀገራት የተስማሙበት ሰነድ ላይ ፊርማሽን  አስቀምጪ በማለት ጀርባዋን ሰጥታታለች ፡፡

የግብጽ ስጋቶች ጥቂት አይደሉም ፡፡ ግድቡ በወንዙ ፍሰት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል … ወደ ግብጽ ከሚፈሰው የውሃ መጠን በ 25 ከመቶ ያህል ይቀንሳል … ኢትዪጽያ ግድቡን ለሃይል ማመንጫ አለች እንጂ ለመስኖ መጠቀሟ አይቀርም የሚሉት ዋነኛዎቹ ናቸው ፡፡ በተለይም የግድቡ ጥልቀት ከ90 ሜትር ወደ 150 እንዲያድግ መደረጉ ከኃላ የመስኖ ስራ ለማከናወን የሚደረግ መደላድል  ነው በማለት ትጨምርበታለች ፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ተደማምሮ ነው እንግዲህ ‹ የኢትዪጽያ ግድብ የብሄራዊ ደህንነቴ ስጋት ነው › እስከማለት የደረሰቸው ፡፡

በዚህ ስዕል መሰረት የዊክሊክስ ዘገባ ሀሰት ነው ለማለት ይከብዳል ፡፡ እናም የዲፕሎማሲያዊ ጥረት የማይሳካ ከሆነ ጉልበትን ለመጠቀም አቅዳለች ፡፡ ለዚህ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ‹ የቬቶ ፓወር › ያላትን ሱዳን ፈረስ ታደርጋለች ፡፡ ለጀት መንደርደሪያም በምዕራብ ሱዳን ዳርፉር የምትገኘው ‹ ኩርሲ › ናት የተመረጠችው ፡፡ አስገራሚውና አጠያያቂው ጉዳይ ሱዳን በጭብጡ ዙሪያ ትንፍሽ አለማለቷ ነው ፡፡ መቸም ግብጽ ብዙ ሴራ ብትሸርብ ከማንነቷ አንጻር አይገርምም ፡፡ በርግጥ ሱዳን ‹ ከማንም አቀርባታለሁ › የምትላትን ኢትዪጽያ ለመውጋትም ሆነ ለማስወጋት ፍላጎት አላት ? ከምን አንጻር ?  ብዙ ተጽዕኖና በደል ፈጽማብኛለች የምትላትን ግብጽ መርዳቷ ከኪሳራና ትርፍ ስሌት አኳያ እንደምን ይታያል ? ሱዳን ካላት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አንጻር በኢትዪጽያ የምትታመን ሀገር ናት ? የሚሉትን ጉዳዮች በአግባቡ መፈተሽ ተገቢ ይሆናል ፡፡

 የህዳሴው ግድብ በሱዳን ዓይን ፤

ኢትዪጽያ ግድቡን በራሷ አቅም እንደምትሰራ ይፋ ስታደርግ በማሾፍ፣ በመገረምና በመደንገጥ ውሰጥ ከነበረው ዓለም ቀድማ አስተያየት የሰጠችው ሱዳን ነበረች ፡፡ ግድቡ ከኢትዪጽያ ይልቅ ሱዳንን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋል በማለት ፡፡ የመስኖና ውሃ ሃብት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ሰይፍ አዲን ሃመድ አብደላ ‹‹ የአባይ ውሃ ሲገደብ ወደ እኛ የሚመጣውን ደለል እንዲቀንስ ያደርጋል ፡፡ ደለሉን ለማስጠረግ ደግሞ በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን ወጪ እናደርግ ነበር ፡፡ ለመስኖ እርሻና ለኃይል አቅርቦትም ያግዘናል ፡፡ በአጠቃላይም ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ የሚጠቅም ዕቅድ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ›› ብለው ነበር ፡፡

ይህ አስተያየት የመነጨው የባለሙያዎችን ጥናት  መሰረት ከማድረግ አንጻር በመሆኑ በጤናማ አይን የታየ ነው ማለት ይቻላል ፡፡  እያደር የተንሸዋረረው መረጃው ነው ወይስ የፖለቲከኞቹ አይንና ጭንቅላት የሚለው አጠያያቂ ጉዳይ ነው ፡፡ እውነቱ በውሸት የሚታይበት ወይም የሚቀለበስበት አካሄድ ግር ሲያሰኝ ‹ የሱዳን አይን እንደ ቆዳ ስፋቷ ትልቅ ነው እንዴ ? › የሚል ጥያቄ ያጭራል ፡፡ የአህያ ትልቅ ዓይን ትልቅ የማየት ችግር አለበትና ፡፡

የመሆን አለመሆን ጉዳይ ፤

 አሸባሪዎችን በገንዘብና በቁሳቁስ በመርዳት፣ ስልጠና በመስጠት በአጠቃላይ በማስጠለል ምክንያት ‹ አሸባሪ ሀገር › በሚለው ጥቁር መዝገብ ውስጥ የሰፈሩት ኩባ፣ ኢራን፣ ሶርያና ሱዳን ናቸው ፡፡ በዚህም ፍረጃ ምክንያት ሀገሪቱ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮቿ ተናግተው ቆይተዋል ፡፡ ከደረሰባት መገለልና እቀባ በተጨማሪ ምዕራባዊያን ለሀገሪቱ ጥሩ ምስል እንዳይኖራቸውና ግንኙነታቸውን እንዳያጠናክሩ ተጽዕኖ አሳድሯል ፡፡

ይህን መጥፎ ገጽታ ለማስወገድ ብዙ ሰርቼያለሁ በማለት ከተመዘገበችበት የአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ እንድትፋቅ ጥያቄም አቅርባ ነበር ፡፡ ይሁን እንጂ የለም የተባለው ሀማስ  በሀገሪቱ ውስጥ በግልጽ  የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ  ሲያዘጋጅ ታይቷል ፡፡ አሸባሪዎችን ከሀገሬ አስወጥቻለሁ ብትልም አልቃይዳና ሌሎች ድርጅቶች በሱዳን ስላለው እንቅስቃሴያቸው የሚያደርጉት የንግግር መረጃዎች ተይዘዋል ፡፡ ይህም ሀገሪቱ ያቀረበቸው ማመልከቻ እንዲዘገይ አድርጓል ፡፡ ከዚህ ምስል ሱዳን የምትናገረውን የማታደርግ ሀገር ናት እንዴ ? የሚል ጥያቄ ማመንጨት ከባድ አይደለም ፡፡

በአሸባሪዎች የምታደርገው ጨዋታ ፤

እንደ ሱዳን ለበርካታ አሸባሪዎች ድጋፍም ሆነ መጠለያ በመስጠት የሚታወቅ ሀገር መኖሩ ያጠራጥራል ፡፡ ለአልቃይዳ፣ ሂዝቦላ፣ የፍልስጤም እስላሚክ ጂሃድ፣ የግብጽ እስላሚክ ጂሃድ፣ የአልጄሪያ አርመዲ እስላማዊ ቡድን፣ እንዲሁም እስላማዊ ያልሆኑ የኢትዮጽያ፣ የኤርትራ፣ የኡጋንዳና ታንዛኒያ ሸማቂ ቡድኖችን ስልጠና በመስጠትና ቦታዎችን በማመቻቸት ትረዳለች ፡፡ በመላው ዓለም እንዲደረጉ በሚታቀዱ የሽብር ጥፋቶች ላይ ፍላጎቷን እግረ መንገድ ትወጣበታለች ይሏታል ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሎርድ ረሲስታንስ አርሚ በሚባለው የኡጋንዳ አማጺ ቡድን ጥቃት 25 ሺህ የሚደርሱ የደቡብ ሱዳን ዜጎች እንዲፈናቀሉ መደረጉን የተመድ ሪፖርት ያመለክታል ፡፡ ሱዳን ባላንጣዎን ለማጥቃት ሌላ ረጅም እጅ አላት ማለት ነው ፡፡

በሌላ በኩል ዩዌሪ ሙሴቪኒ ‹ ሱዳን ፍቃድ ብትሰጠኝ ይህን አማጺ ቡድን በሰላሳ ደቂቃ ውስጥ አጠፋዋለሁ › ብለው ነበር ፡፡ አልበሽር ይህ አማጺ ቡድን ለክፉ ቀን ስለሚጠቅማቸው የረጅም ግዜ ጓደኛቸውን ጥያቄ መቀበል አልፈለጉም ፡፡ ከራስ በላይ ንፋስ በማለት ፡፡ የአፍሪካ ህብረት በአንድ ወቅት ይህን አማጺ ቡድን ለማንበርከክ ሱዳንን ጨምሮ ከአፍሪካ የተውጣጣ ብርጌድ አቋቁሞ መላክ ሲፈልግ አሪፍ ስልት ነው ተብሎ ነበር ፤ እያደር ግን አልበሽር ለሀሳቡ ከአንገት በላይ ሆኑ ፡፡ የሱዳን የዳማ ጨዋታ በነጩም በጥቁሩም ሜዳ ላይ በመሆኑ ፋውልም ሆነ ኦፕሳይት አይታወቅም ፡፡ ይህም ግድየለሽነትን ወይም አደገኛነትን ሳይጠቁም ይቀራል ?

ሚሳይልን እንደ ሚዝል የምትቅም ሀገር ፤

በቅርቡ ያርሙክ የተባለው የጦር መሳሪያ ፈብሪካዋ ከራዳር እይታ መሰወር በሚችሉ አራት የእስራኤል ጀቶች ወድሟል ፡፡ ይህ ፋብሪካ ሮኬትና ሌሎች ከባድ መሳሪያዋችን የሚያመርት ሲሆን በኢራን፣ ግብጽና ሱዳን ሽርካነት የሚንቀሳቀስ ነበር ፡፡ የፋብሪሳው ዓላማ ሀማስና ሌሎች ተዋጊ / አሸባሪ ድርጅቶችን ማጠናከር ነው ፡፡

ሱዳን ለዚህ መሰሉ ጥቃት አዲስ አይደለችም ፡፡ በሚያዚያ 2011 ፖርት ሱዳን አካባቢ መኪና ውስጥ የነበሩ ተጠርጣሪ አሸባሪዎች ተገድለዋል ፡፡ በ2009 ሰሜን ምስራቅ ሱዳን ውስጥ ወታደራዊ ኮንቮይ ተደብድቦ 119 ሰዎች አልቀዋል ፡፡ ብዙዎቹም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አጓጓዦች ነበሩ ፡፡ በ1998 አል ሺፋ የተባለ መድሃኒት ፋብሪካ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ያመርታል ተብሎ የአሜሪካ ሚሳይል ሰለባ ሆኗል ፡፡ እስራኤል በጥቃቱ ዙሪያ ቀጥተኛ አስተያየት ሰጥታ ባታውቅም ጮክ ብላ  ‹‹ ሱዳን አደገኛ የአሸባሪዎች ሀገር ናት ! ›› ከማለት ግን ወደ ኃላ ብላ አታውቅም ፡፡ ሱዳንም ጠብ አጫሪዋንና ህገ ወጧን እስራኤል  እከሳለሁ እያለች ከመፎከር የዘለለ የተጨበጠ እንቅስቃሴ አታደርግም ፡፡ ይህም ‹ መድሃኒቱ › የተስማማት ወይም የታዘዘላት አስመስሎባታል ፡፡ ለነገሩ በ ‹ ICC › የሚፈለጉት አልበሽር ሌላውን ለመክሰስ ምን ሞራል አላቸው ?

ዞሮ ዞሮ ሱዳን አሸባሪነትንም ሆነ የአሸባሪዎችን ዓላማ መሾፈር የምትፈልግ ሀገር ከሆነች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኢትየጽያ ጥቅሞች ላይ እጆቿን ትዘረጋለች ለማለት የሚያስችል መነሻ አይኖርም ?

ጉርብትና ለመቼ ነው ?

ሁለቱ ሀገሮች ተራ ጎረቤታሞች አይደሉም ፡፡ ከናይል ወንዝ ተመሳሳይ ውሃ ጠጥተዋል ፡፡ በአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ በተመሳሳይ ቋንቋ አንድ አይነት ሀሳብ ያስተጋባሉ ፡፡ ሁለቱም የሮምን ስምምነት/ ICC / አልፈረሙም ፡፡ ፕሬዝዳንት አልበሽር የሙስሊም ብራዘር ሁድ አባል ናቸው ፡፡ የሙባረክ መንግስት ከወደቀ በኃላ ግብጽን የጎበኙ የመጀመሪያው መሪ ናቸው ፡፡ ሁለቱም ሀገሮች ዕድሜ ለቅኝ ገዢዎች ውል በናይል ውሃ ላይ ‹ Veto power › አላቸው ፡፡ ስድስቱ ሀገራት የፈረሙትን የእንቴቤ ስምምነት አይመለከተንም ብለዋል ፡፡ ሱዳን ለሁለት በመከፈሏ ሁለቱም ደስተኞች አይደሉም ፡፡

ሱዳን ለሁለት መከፈሏን ደግሞ ሀገራችን ትደግፋለች ፡፡ ይህ በራሱ ለመቃቃር አይነተኛ ጥንስስ ይፈጥራል ፡፡ የሁለቱን ሀገሮች የዘመናት የ ‹ Veto power › እንዲናድ የሰራቸው ኢትዮጽያ ገና ከጠዋቱ ትልቁን የስልጣን ካፖርት እያጠለቀች በመሆኑ አይሰማትም ማለት አይቻልም ፡፡ በ 25 ከመቶው የውሃ ድርሻዋ ደስተኛ ባትሆንም ዛሬ ትክክለኛ ድርሻሽ መቶ ሲካፈል ለአስር ሀገሮች ነው እየተባለች ነው ፡፡ የምክትል ሰብሳቢ ፈላጭ ቆራጭነት ሚናም አይኖራትም ፡፡ ይህ የመውረድና የመወራረድ ፖለቲካ የሚፈጥረው ግዜያዊ ራስ ምታትም ሚዛናዊ ብይኗን አያስትም ማለት አይቻልም ፡፡ እናም በተመሳሳይ ቀለም ከግብጽ ጋር ለመብረር ‹‹ ኩርሲ ›› ላይ መንደርደሪያ ሰርታ ጀባ ለማለት አቅዳ ከሆነስ ?

ከማያውቁት መልዓክ … ፤

የሱዳንን ግብጽ ግንኙነት እድሜ ጠገብ ቢሆንም የተመሰረተው በአሸናፊና ተሸናፊ፣ በአለቃና ምንዝር ምህዳር ላይ ነው ፡፡ 790 ማይልስ ርዝመት ያለው የድንበር ወሰን አጨቃጭቋቸዋል ፡፡ ሃይላንድ ትሪያንግል የተባለው ቦታ የሱዳን ነው ቢባልም ግብጽ በጡንቻዋ የራሷ አድርገዋለች ነው የሚባለው ፡፡ በዚህ የሚበሽቁት አልበሽር -  ሙባረክ አዲስ አበባ ለስብሰባ ሲመጡ በእጃቸው መዳፍ ውስጥ ካሉት አሸባሪዎች ጋር መክረው ሊያስገድሏቸው እንደነበር ተጠርጥሯል  ፤ እረ ተዘግቧል ፡፡

 ትንሽ ቆይቶ ደግሞ አልበሽር ‹ ግብጽ መንግስቴን ልትገለብጥ እያሴረች ነው › በማለት መጮህ ጀመሩ ፡፡ ይህን የሰሙት ሙባረክ ‹ ግብጽ የአንተን መንግስት መገልበጥ ብትፈልግ አስር ቀናት ብቻ ይበቃታል ! › ሲሉ አናዳጅና የበላይነታቸውን የሚያስረግጥ ምላሽ ሰጡ ፡፡ በነገራችን ላይ ግብጾች ይህን የመሰለ ጉራ በማምረት የሚተካከላቸው የለም ፡፡ በሀገራችን ግድብ ዙሪያም ማስተባበያ ሲሰጡ   ‹‹  የዲፕሎማሲያዊው ጥረት የማይሳካ ከሆነ ጀቶቻችን ግድቡን ደብድበው በአንድ ቀን ይመለሳሉ ! ›› ብለው ነበር ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ እንደ እስራኤልም ያደርጋቸዋል ልበል ? እኛ የምናውቀው በስድስቱ ቀን ጦርነት እነሱ ፣ ሶርያና ጆርዳን በእስራኤል ታስረው መገረፋቸውን ነው ፡፡ ታዲያ ይህን በስድስት ቀን ፣ በአስር ቀን የሚባለውን ተሞክሮ ከየት አመጡት ?  ‹ ወገኛ ! › የሚባለው ሀገር የዚህ ዓይነቱ መሆን አለበት ፡፡ ያም ሆነ ይህ ሱዳን ከነጭቆናዬ የማውቃትን ግብጽ መደገፍ ስትራቴጂያዊ ርምጃ ነው ብትል ከልካይ የላትም ፡፡ ኢትዮጽያን ደግፋ ጀግና ከምትባል ለግብጽ አድራ ተቀምቻለው የምትለው መሬት እንዲሰጣት አሳዛኝ ማመልከቻ ብታስገባ ሊጠቅማት ይችላል ፡፡

የጉዳዩ መድረሻ ፤

ሱዳንና ኢትዮጽያ ከማህበራዊና ባህላዊ ትስስር አንጻር በተለይም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸው ጠንካራ ነው ማለት ይቻላል ፡፡ ከዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም አንጻርም ሱዳን ከኢትዮጽያ የኤሌትሪክ ኃይል እና ሰላማዊ የድንበር ደህንነት ትፈልጋለች፡፡ ኢትዮጽያ የሱዳንን ነዳጅ፣ ወደብና ገበያዋ በአማራጭነት ያስፈልጋታል ፡፡

በርካታ ኢትዮጽያዊያን በፖለቲካም ሆነ በኑሮ ሲንገፈገፉ ወደዚች ሀገር ማምራታቸውም ይታወቃል ፡፡ ሁለቱ ሀገሮች በቀለም፣ በቋንቋና ስነ ጥበብ ይመሳሰላሉ ፡፡ በተለይም የስዕል፣ ዳንስ፣ ቅርጻ ቅርጽና ሙዚቃ ስራዎቻቸው  የተቀራረቡ ናቸው ፡፡ ታዋቂዎቹ ሳኢድ ከሊፋና መሃመድ ዋርዴ ሀገራችንን እንደ ቤታቸው በመቁጠር ጣፋጭ ስራቸውን አስኮሙኩመውናል ፡፡ በተለይም ሳኢድ ከሊፋ

‹‹ ጤና ይስጥልኝ እንደምናችሁ
  ጤና ይስጥልኝ እንደምናችሁ
  ከሱዳን መጣን ልናያችሁ … ›› በማለት ውስጣችንን ኮርኩሮታል ፤ እኛንም መስሏል፡፡ በብዙዎቻችንም ክብርና ሞገስ አግኝቷል ፡፡ ታዲያ ይቺ ቅርብ የመሰለች ሀገር እውነት ዛሬ ፊቷን እያዞረችብን ፣ በፖለቲካም ቋንቋ እያሴረችብን ነው ? ነው ወይስ የጠላት ወሬ ነው ? እውነት ከሆነማ የቀጣዩ ‹ ሲንግል › ግጥም ቁልጭ ብሎ ይታየኛል ፡፡ ….

‹‹ ጤና ይስጥልኝ እንደምናችሁ
  ከግብጽ ጋር አበርንባችሁ
  ጤና ይስጥልኝ እንደምናችሁ
  ‹ ኩርሲ › ላይ መሸግንባችሁ
   ጤና ይስጥልኝ እንደምናችሁ
   በናይል ጉዳይ ከዳናችሁ
   ጤና ይስጥልኝ ….

 እነሆ ሱዳን የምንሰማው ሁሉ እውነት ከሆነ ትጣሊናለሽ ፤ ማርያምን አንለቅሽም !! ከዚያ በኃላ ለቁጥር የሚታክተውን የሽለላና የቀረርቶ ዜማችንን ምንጭ እየጠቀስሽ እንደሚከተለው ታዜሚልን ይሆናል
1.
ደሞ፣ደሞ፣ደሞ ግለሌ
ገስግሶ ገዳይ በሰው ቀበሌ
ግለሌ ምሳው ግለሌ እራቱ
መለቃለቂያው ደም ራጨቱ
ገለል በሉለት አንድ ግዜ ለእሱ
ግልግል ያውቃል ከነፈረሱ
2.
የፍየል ወጠጤ ትከሻው ያበጠ ልቡ ያበጠበት
እንዋጋ ብሎ ለነብር ላከበት
የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች
ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች
እረ ጎራው - ጎራው እረ ደኑ - ደኑ ...



Friday, October 19, 2012

‎ጥቂት የ ‹ A › መሪዎችና በርካታ የ ‹ A › በሽታ ‎



እገሌ የ ‹ A › ተማሪ ነው ከተባለ ቀለሜዋ መሆኑን እንረዳለን ፡፡ ፕሬዝዳንት እንቶኔ የ ‹ A › መሪ ናቸው ከተባለ ደስ የሚሉና የተባረኩ ናቸው ብሎ ማለፍ ያስቸግራል ፡፡  ‹ A › ማለት ምንድነው ?  የተከበረው ‹ A › እንዴት ይገኛል ?  የሚለውን ሀሳብ ማጦዝ ያስፈልጋልና፡፡


የ ‹ A › መሪነት በሽምደዳና በችከላ ብቻ አይገኝም ፡፡ አንድ የሀገር መሪ እዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በክብር ሊቀመጥ የሚችለው ዴሞክራሲ የተባለውን መጠነ ሰፊ ባህር ዋኝቶ ባይጨርሰውም ውስጡ ምን እንዳለ ሲያውቅ ፣ የፕሬስ ነጻነት የተባለውን ጎምዛዛ ፣ አኞና ሆድ አጥጋቢ ማዕድ ቀምሶ ለብዙሃኑ ሲባርክ ፣ ሙስና በተባለው ‹ አሻፋጅ › ገላ ራሱም ሆነ ሌሎች ከመውደቃቸው በፊት ለሃጫቸውን እንዲቆጣጠሩ ሲሰራ ፣ የሰው ልማት የተባለውን መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት ለሟሟላት ቀን ከሌሊት ሲተጋ ነው ፡፡


የተማሪነት ዘመናቸውን በቀለሜዋነት አሳልፈው የህዝብ አስተዳደሩ ግዜም በዚሁ ካባ ደምቀው የታዩ የአፍሪካ መሪዎች ካሉ እንደመታደል  ይቆጠራል ፡፡ አንዳንድ ጎበዝ ተማሪ የነበሩ የአፍሪካ መሪዎች ሲጎለምሱ ጎበዝ ገዳይና ጀግና ፈላጭ ቆራጭ ሆነዋል ፡፡ አንዳንዶች በትምህርት ብዙም ያልተጓዙ ቢሆንም ትንሽ ከራርመው ባለብዙ ዲግሪ መሆናቸውን ያስነግራሉ ፡፡ ብዙዎቹ አዋቂና ዘመናዊ እንዲባሉ ስለሚፈልጉ የቀለም ቦሃቃ ውስጥ ገብተው አያውቁም የሚለው ወሬ እንዲነገርባቸው አይፈልጉም ፡፡

ባለኝ የንባብ መረጃ መሰረት ስለ ትምህርቱ ሳይደባብቅ ለጋዜጠኞች በይፋ የተናገረው አረመኔው ኢዲያሚንን ዳዳ ነበር ፡፡
እንዲህም አለ ፡፡ ‹‹ እኔ ምንም ዓይነት የመደበኛ ትምህርት የለኝም ፡፡ ሌላው ቢቀር የነርስ ትምህርት ቤት ሰርተፍኬት የለኝም ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ግዜ ፒኤችዲ ካለው በላይ ነው የማውቀው !! ›› መቼም ይህ ደፋር ሰው አነስተኛ የትምህርት ዝግጅቴ ለመሪነት አያበቃኝም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልጎ እንዳልተናገረ ግልጽ ነው ፡፡

ዞሮ ዞሮ የ ‹ A › መሪነት በሽምደዳ አይገኝም ። በባዮሎጂ ትምህርታችን መረጃ መሰረት
የቫይታሚን  B  እጥረት - ቤሪ ቤሪ
የቫይታሚን  C  እጥረት - አስኮርቢክ አሲድ
የቫይታሚን  D  እጥረት - ሪኬት

ከጉዳያችን ጋር ግንኙነት ያለው የቫይታሚን  A እጥረት - በደብዛዛ ብርሃን የማየት በሽታ / Night Blindness / ያስከትላሉ ፡፡
የአፍሪካ መሪዎች ባህርያት አመቱ በጨመረ ቁጥር የሚለያይ ነው ። ወደ ስልጣን ሊመጡ አካባቢና ስልጣንን እንደያዙ ተቆርቋሪነታቸው ፣ የበዛ አዳማጭነታቸውና የተንዠረገገው ቃልኪዳናቸው ብዙዎችን የሚያማልል ነው ፡፡ ምነው ይህን ሰው አባቴ ፣ አጎቴ ፣ ወንድሜ ፣ ውሽማዬ ባደረገው ባዩ ቀላል አይደለም ፡፡ የዚህ ሰው ተወዳጅ አበባ ግን ዕድሜውን ጨርሶ ሳይሆን በትዕቢትና ጥጋብ ከወዲሁ ይረግፋል ፡፡ ቀጥ ያለውና የተከበረውም ‹ A › በጉዳትና በመከራ እንደ ‹ C › እና ‹ D › መጣመም ይጀምራል ፡፡

የ2011 መረጃዎች እንደሚያስረዱት ከሆነ ከ 54 የአፍሪካ ሀገሮች የ A › ን ቦታ ያገኙት የቦትስዋናው / jeretse jan khama / ፣ የኬፕቨርዱ / Jorge carlos fonseca / ፣ የሞሪሽየስ / Navin Chandra Ragoolan / እና የጋና / John Evans Atta mills / መሪዎች ናቸው ፡፡ ተስፋ ከሚጣልባቸው የ ‹ B › መሪዎች ውስጥ ናሚቢያ፣ ደቡብ አፍሪካና ማሊን መጥቀስ ይቻላል ፡፡ ኬኒያ ፣ ታንዛኒያ ፣ ላይቤሪያና ዛምቢያ ለክፉ አይሰጥም በሚባለው የ ‹ C › ማዕቀፍ ውስጥ ናቸው ፡፡ ናይጄሪያ ፣ ሩዋንዳና ኒጀር ‹ D › ን ታቅፈዋል ፡፡ ኡጋንዳ ፣ ጊኒ ፣ ኮሞሮስ ባንዲራ የሚባለውን ‹ F › እያውለበለቡ ይገኛሉ ፡፡ ሊቢያ ፣ አልጄሪያ ፣ ካሜሮንና ኢትዮጽያ ለየት ያለ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል ፡፡ ICU የሚል ፡፡ ይህን ምህጻረ ቃል ስናፍታታው Health Service Intensive Care Unit የሚል ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡ ጥሬ ትርጉሙስ ከተባለ እዚህ ክፍል የሚመደብ በሽተኛ ፤ በሽታው ለህይወቱ በጣም አስጊ በመሆኑ በዘመናዊ የህክምና መሳሪያና ሙያተኞች ርዳታ መደገፍ እንደሚገባው እንረዳለን ፡፡ ይህን ርዳታ ባግባቡ ካላገኘ ግን መሞቱ ነው ፡፡ ኤርትራ ፣ ሱዳንና ዙምባብዌ ደግሞ < MORGUE > ተብለዋል ፡፡ የሞተ ሰው የሚቀመጥበት ክፍል መሆኑ ነው ፡፡ 

በሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽንና በምስራቅ አፍሪካ መጽሄት ዝግጅት ክፍል ይህን የመሰለ የአፍሪካ መሪዎች ስኮር ካርድ ማዘጋጀት ከተለመደ ሰነባብቷል ፡፡ 75.2 አስመዝግባ ‹ A › ባገኘቸው ቦትስዋናና 32.05 አግኝታ ICU በምትገኘው ኢትዮጽያ መካከል የ43 ነጥብ ልዩነት አለ ፡፡ የነጥቡን ስፋት ያንቦረቀቀው የዴሞክራሲ ፣ የፕሬስ ነጻነት ፣ የሙስናና የሰብዓዊ ልማት መሰረታዊ አጀንዳዎች ናቸው ፡፡ ርግጥ ነው የሞህ ኢብራሂም ኢንዴክስና የጋዜጠኞች ቡድን ነጥብ አሰጣጥ ስርዓትም ይካተታል ፡፡

አሜሪካ በአንድ ወቅት ተስፋ የሚጣልባቸው የአፍሪካ ዴሞክራት መሪዎች በሚል ስያሜ የሩዋንዳውን ፓውል ካጋሜ ፣ የኡጋንዳውን ዩዌሪ ሙሴቬኒ ፣ የኢትዮጽያዊውን መለስ ዜናዊ እንዲሁም ኤርትራዊውን ኢሳያስ አፈወርቂ የላቀ ዕውቅና እንዲያገኙ አድርጋ ነበር ፡፡ የነዚህ መሪዋች ስኮርድ ካርድ ግን ስያሜያቸውን መምሰል አልቻለም ፡፡ ካጋሜ 47.6 በማግኘት D ፣ ሙሴቬኒ 42.7 በማግኘት F ፣ መለስ 32.05 በማግኘት ICU ፣ ኢሳያስ 22.23 በማግኘት MORGUE ውስጥ ተመድበዋል ፡፡ አንዳቸው እንኳን የማለፊያውን ወገብ አለመንካታቸው በእጅጉ ያስገርማል ፤ ተግባራውም ሲታወቅ ያስደነግጣል ። 

ይህን የቤት ስራ በአግባቡ ለመከወን የ ‹ A › መሪዎችን ተሞክሮ መጠቀም ያስፈልጋል ፡፡ በነገራችን ላይ የ ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ዘንድሮን ብቁ መሪ አላገኘሁም በሚል ሂሳብ ይዝለለው እንጂ እስካሁን ለሶስት መሪዎች የ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት በመስጠት ዕውቅና አጎናጽፏል ፡፡ 
መሪዎቹ ፣
የኬፕቨርዱ - ፔድሮ ቬሮና ፓይረስ
የቦትስዋናው - ፌስተስ ጎንተባይ
የሞዛምቢኩ - ጃኪም ቺሳኖ ናቸው ፡፡
ህገ መንግስትንና ህጎችን በተፈለገ ግዜ በልክ መቅደድና መስፋት በጣም የተለመደ ፣ ቀላልና የማያሳፍር ተግባር በሆነባት አፍሪካ እነዚህ መሪዎች ከሁለት ግዜ በላይ ሀገር አንመራም በማለት በፈቃዳቸው በመልቀቅና የተሻለ መልካም አስተዳደር በመፍጠር ይመሳሰላሉ ፡፡ ሞዴል መሪዎች የተባሉትም በነዚህና በመሳሰለው የላቀ የአመራር ጥበባቸው ነው ፡፡ እንግዲህ ይህን የመሰለ ቅዱስ ተግባር በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጽያ እንዴት ይመጣል ? የሚለው ጥያቄ ነው የሚያስጨንቀው ፡፡ ምክንያቱም የነ ሙጋቤና ሙሴቬኒን መንገድ አጥብቀው የሚከተሉት አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች የሚከተለውን ያልተበረዘና ያልተከለሰ ፖሊሲ እያቀነቀኑ ነውና

 ‹‹ እኛ መሪዎች ለህዝብ ጥቅም ሲባል በተወለድንበት አልጋ ላይ እስክንገነዝ ድረስ መቆየት እንፈልጋለን !! ››
ለማንኛውም  መሪዎቻችን ዳፍንት ገደልን መንገድ የሚያስመስል ክፉ በሽታ ስለሆነ ዘወትር በጠራ ሳሙና ፣ ውሃና ፎጣ ፊታቸውንና ጭንቅላታችሁን  ቢታጠቡ መልካም  ሳይሆን አይቀርም ፡፡ 

Sunday, October 14, 2012

‎ዋሊያዎቹ ከተራራ ወረዱ‎




‹‹ የቆየ ከሚስቱ ይወልዳል ይሉሃል ይሄ ነው ›› ብሄራዊ ቡድናችን ዋሊያዎቹ ከ 31 ዓመታት ቆይታ በኃላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አለፉ ፡፡ ይህን አባባል በሌላ ቅርጽ መድገም ያስፈልጋል  ‹‹ ዋሊያዎቹ ከ31 ዓመታት ቆይታ በኃላ የአፍሪካን ዋንጫ አሸነፉ ሳይሆን መከራ የሆነባቸውን የማጣሪያ ግንብ ደርምሰው አለፉት !! ›› ማጣሪያን የደፈረ ቡድን ማለት እንችላለን ፡፡

ኩሩው፣ አይናፋሩና ግርማ ሞገስ የተቸረው ዋሊያ በኢትዮጽያ ለዛውም በሰሜን ተራራዋች  ብቻ የሚገኝ አጥቢ እንስሳ ነው ፡፡ ይህን ብርቅ እንሰሳ ለመጎብኘት ከመላው ዓለም ወደ ሀገራችን የሚያቀናው ቱሪስት ቁጥር ቀላል አይደለም ፡፡ ግና ቱሪስቶቹ እንደ ጅብ፣ የሜዳ አህያና ሌሎቹም እንስሳት በቀላሉ በቅርበት ስለማያገኙት ትንፋሽ የሚያሳጥረውን የሰሜን ተራራዋች መውጣት ይጠበቅባቸዋል ፡፡ ዋልያዋች በአብዛኛው የሚኖሩት ከ 2500 ሜትር በላይ፣ ከ 4000 ሜትር በታች በሆኑ አካባቢዎች መሆኑ ይታወቃል ፡፡

ዋሊያ በዚህ ባህሪው እሱ ተራ ወደሚለው ‹ ሜዳማ ስፍራ › ለመውረድ ፍቃደኛ ሳይሆን ህይወቱን ይገፋል ፡፡

የብሄራዊ ቡድናችን ‹ ዋሊያም › ለ31 ዓመታት የአፍሪካም ሆነ የዓለም ዋንጫ አይመቸኝም የሚል የመሰለ አስተሳሰብ ወዶም ይሁን ተገዶ በማዳበሩ ‹‹ ብርቅና በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኝ ብሄራዊ ቡድን ›› የሚል ቅጽል እስከማግኘት ደርሶ ነበር ፡፡ በርግጥ እንደ ቀንዳሙ ዋሊያ የሚጎበኙት ነጫጭ ሰዎች አልነበሩም ፡፡ በዚህ የተደፋፈሩት እነ ሶማሊያና ትናንሽ ቡድኖች ሁሉ ባገኙት ቁጥር የሚያቃጥል ጥፊና የሚያሳክክ ኩርኩም ሲያቀምሱት ቆይተዋል ፡፡ ህመሙ ቢጋባብንም ላለው ይጨመራል እንዲሉ ‹‹ ይሄ ውሽልሽል ! አሰዳቢ ! ወኔ ቢስ ! ቡድን ›› እያልን በጎን አገጩን ስናጣምም ነበር ፡፡

ዛሬ ተመስገን ሆነ ፡፡

‹ ቀንዳሙ ዋሊያ ታች ወርዶ የማይታየው ከስነ ፍጥረታዊ ግዴታው አኳያ ነው ፡፡ ታዲያ የኔ ተራራ ላይ መቆለል ምን ሊረባኝ ነው ? ተራራ ላይ ከመኖር አስተሳሰብን ተራራ ማሳከል ይሻላል › የሚል ጥሞና ውስጥ ቆየ ፡፡ ይኀው ስድቡን፣ ኩርኩሙን፣ ቁጭቱን በጉያው ይዞ የምሽት ድል አበሰረ ፡፡

በዚህም ምክንያት የአበሻ ምድር ቀውጢ ሆኖ አመሸ ፡፡ ህዝቡ አበደ ፡፡ ከመናገር ይልቅ መጮህ መረጠ ፡፡ መንገድ ሞልቶ እንዳለቀሰ ሁሉ መንገድ አጣቦ ጨፈረ ፡፡ ብርጭቆ እያጋጨ ዘመረ ፡፡ ከመተቃቀፍ  ይበልጥ አስፋልት ላይ ተንከባለለ ፡፡ ቀሪው ዓለም ‹ የኢትዮጽያ ህዝብ ምን ዓይነት ወገኛ ቢሆን ነው ለማጣሪያ እንዲህ መጠን የሚያልፈው ? › ቢል ‹ በሰው ቁስል እንጨት አይሰደደም ! › ብሎ ለመመለስ ግዜ ያጣረው መስሏል ፡፡  ‹ እረ እንደ አሪፎቹ ዋንጫ ቢያነሳ ምን ሊያሳየን ነው ? › የሚል አሽሙር ንፋሱ ቢያደርሰው የፍቅሩን፣ የአንድነቱን፣ የደስታውን፣ የድል ናፍቆቱን፣ የጥቃቱን ልክ በሀገርኛው ቀመር ለማስረዳት እንደሚያስቸግረው ይገመታል ፡፡

ሀገሬው ግን እንደ ዉጩ አይደለምና ራሱን ‹ ቃሉን የደፈረ ተመልካች ! › ብሎ የሳሳ ትከሻውን በኒሻን ሊያጥለቀልቀው ይችላል ፡፡ አምስት ጎል የገባበትን ቡድን ‹ ታሸንፋለህ ! › ብሎ ያነቃውና ያበረታታው እሱ ነውና ፡፡

እነሆ ዋሊያዎቹ ከተራራ ወረዱ ፡፡

አዲስ ታሪክ ሰሩ ፡፡

ለካስ ዋሊያ ሜዳ ላይም ሮጦ ማሸነፍ ይችላል ፡፡

ነገና ከነገ ወዲያ ደግሞ በነጮች ብቻ ሳይሆን በጥቁሮችም ቱሪስቶች ይታያሉ ፡፡

Wednesday, October 10, 2012

የተረሳው ባህል ትንሳኤ ያገኝ ይሆን ?




ኪነ ጥበብ ያዝናናል፡፡ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በአስደሳች መልኩ ቀርጾ መልሶ ለህብረተሰቡ ሲያቀርብ  ‹‹ ወቸው ጉድ ?! ›› ያሰኛል    ፡፡ ታዲያ ልንሰንቅ በምንችለው ግርምት ውስጥ  የመምህርነት ሚና አለው ፡፡ ባልተሰላቸ መልኩ የሚሰጠው ዕውቀት እንደኛ ባሉ ድሃ ሀገሮች ውስጥ ተጠናክሮ መቀጠሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ዕድገታችንን ዕውን ለማድረግ ይጠቅማል ፡፡

በተረት ፣ በወግ፣ በስነቃልና በስነግጥም ሀብታም በሆነቸው ኢትዮጽያ ‹‹ ኪነ ጥበብ ›› ሲጫወት የቆየው ሚና ቀላል አለመሆኑ ርግጥ ነው ፡፡ ቅድመ አያቶቻችን  በማህበራዊ ትስስራቸው ውስጥ በጉልህ ሲያንጸባርቁት ቆይተዋል ፡፡ በዚህ ረገድ የ ‹‹ በልሐ - ልበልሃ ›› ስርዓት በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል ፡፡

በታሪክ የመጀመሪያዎቹ ጠበቆች ካህናት፣ የህግ ምንጭ ደግሞ ብሉይ ኪዳን እንደነበሩ ይነገራል ፡፡ በሀገራችንም ተሟጋቾች የህግ ዕውቀት ያገኙ የነበረው በገዳማትና በሌሎች መንፈሳዊ ተቋማት ፍትሐ ነገስትን በማጥናት እንደነበር ‹‹ ጠበቃና ስነ ምግባሩ ›› የሚለው መጽሀፍ ያስረዳል ፡፡ በርግጥ የድሮ ጠበቆች እንደዛሬው ህግ የሚማሩበት ትምህርት ቤት አልነበራቸውም ፡፡ ትምህርት ቤታቸው አደባባይ ነው ፡፡ ጥብቅናን የሚማሩት ተረት፣ ወግ፣ ሰምና ወርቅ፣ ባህልና ስነ ግጥም በማጥናትና በመለማመድ ነበር ፡፡
የሚከተለው ክርክር ልጅነትን ለማሳወቅ የተደረገ ነው ፡፡ ተከራካሪዎቹ ምን ያህል የስነ ግጥም ብቃት እንዳላቸው እንመልከት ፡፡
ከቤት ክፉ ሰቀላ
ከልብስ ክፉ ነጠላ
ከእህል ክፉ ባቄላ
ከልጅ ክፉ ዲቃላ
መልኩ የእናሪያ / ጥቁር /
እግሩ መታረሪያ
እየው ፊቱን የተገዛበቱን
እናም አላውቅም ልጅነቱን ብሎ ይቃወማል ፡፡

መላሽም በተቃራኒው ወገን የተነሳውን እያንዳንዱ መሰረታዊ ነጥብ በመልቀም የማፍረሻ ወይም የመቃወሚያ ሀሳቦችን ይሰነዝራል ፡፡

ክረምት ያወጣል ሰቀላ
ከብርድ ያድናል ነጠላ
ቀን ያሰልፋል ባቄላ
ጠላት ይገፋል ዲቃላ
መልክም ቢጠቁር የዘር ነው
እግሩም ቢቀጥን ዘምቶ ነው
ስለዚህ ያለብህ ማወቅ ነው በማለት ጠንካራ የአጸፋ መልስ ይሰጣል ፡፡

የታወቁ ጠበቆች አደባባይ ሲሟገቱ ነጭ ልብስ ለብሰው፣ አደግድገው፣ አንዳንዴም ጎራዴ ታጥቀው፣ በቀጭን ዘንግ ወደፊት እየተወረወሩ ሲናገሩም እየጮሁ ነበር ይባላል ፡፡ ይህ እንግዲህ በክርክሩ ውስጥ ከስነ ግጥም ሌላ የትወና ጥበብም እንደሚንጸባረቅ ጠቋሚ ነው ፡፡

በአንድ ወቅት አባትና ልጅ ተጣልተው ተካሰሱ አሉ ፡፡ ይህ በሀገራችን ባህላዊ ልማድ ያልተለመደ ቢመስልም አንዳንዴ ወጣ ያለ አመለካከትና አተያይ  ያላቸው ልጆች አይፈጠሩም ማለት ግን አይቻልም ፡፡ እናም ልጅ ጉዳዩን ባህላዊው ፍርድ ቤት እንዲያይለት አመለከተ ፡፡ አባት ይህን የመሰለ ድፍረት ባይዋጥለትም ልጅ ተጠየቅ ማለቱ አልቀረም ፡፡ በህግ አምላክ ተጠየቅ !! አለ ልጅ  ወግድ !! እያለ አንገራገረ አባት ፡፡ በወቅቱ ለታዳሚው ያሰሙት ሙግትም የምጥቃታቸውን ደረጃ እንዴት አንጸባርቆ እንደነበር በቅንጭብታ እንመልከተው ፡፡

ልጅ ፤  ተጠየቅ ልጠይቅህ ?!
አባት ፤  አልጠየቅም
          ሰማይ አይታረስም
          ውሃ አይታፈስም
         መሬት አይተኮስም
         አባት አይከሰስም !!
ልጅ ፤  ሰማይ በመብረቅ ይታረሳል
         ውሃም በእንስራ ይታፈሳል
         መሬትም በማረሻ ይተኮሳል
         አባትም በጥፋቱ ይከሰሳል !!
አባት ፤ ፍረዱኝ ሰማይ ያለ መዓት ነጎድጓድ አያወርድ
         ፈጣሪ ያለ ክህደት ገሃነም አያወርድ
         ያለ እርሻ በመሬት ላይ እሳት አይነድ
         ሴትም ያለ እንስራ ውሃ አትወርድ
         አባትም ያለ ጥፋት ልጁን አይክድ
         አባት ለልጁ ዳኛ
         አትሞግተኝም ዳግመኛ !!

ልጅም በዋናነት የአባቱን የምላሽ ሰበዝ እየመዘዘ የማጣመም ወይም ሀሳቡን የማክሽፍ ተልዕኮውን ይቀጥላል ፡፡ ለምሳሌ ያህል አባት ልጄን የካድኩት ስላጠፋ ነው የሚል ሀሳብ ፈንጥቋል ፡፡ ልጅም ጥፋት የተባለውን ነገር በመዘርዘር ንጹህ መሆኑን ለማስረዳት እስከ መጨረሻው ይተጋል ማለት ነው ፡፡ ሌላው አስገራሚ ገጽታ ሁልግዜም ቢሆን ተከራካሪዎች ጥፋተኛ መሆናቸውን ልባቸው ቢነግራቸው እንኳን ከፍተኛ የራስ መተማመን እንዳላቸው የሚያሳዩበት መንገድ ነው ፡፡ ባላጋራቸውን በማስደንገጥ ከክርክሩ እንዲወጡ ከፍ ያለ ቃል ይገባሉ ፡፡ ለምሳሌ ያህል አንደኛው ፤

በልሀ ልበልሃ ልንዛብህ
የሙግት ዠሃ
ሀሰት ቢገኝብኝ በቃሌ
ቅቤ አምጥቼ በብርሌ
እሰጣለሁ ለሽማግሌ ሊል ይችላል ፡፡ ሌላኛውም

በላ ልበልሃ
ልንዛብህ የሙግት ዠሃ
ብትወነጅለኝ በሀሰቱ
ይበረታብሃል ቅጣቱ
የረታህኝ እንደሁ ተሟግቼ
ቀንጃ በሬዬን አምጥቼ
ለዕለት ጉርሴ እንኳን ሳልሳሳ
አገባታለሁ እምቦሳ


በማለት የጠነከረ ምላሽ ይሰጣል ፡፡ ከዚህ በኃላ ክርክሩን ራሳቸው ስላጦዙት ሰሚውም ሆነ ፍርድ ሰጪዎች ዳኞች ቀጣዩን ለመስማት ያቆበቅባሉ ፡፡

እስቲ ሌላ ዘወር ያለ አብነት ደግሞ እንመልከት ፡፡ አንድ በሬ የጠፋበት አርሶአደር በፍለጋ ረጅም ሰዓት ቢያሳልፍም በቀላሉ ማግኘት አልቻለም ፡፡ ሁኔታው አበሳጨው ፡፡ ጉዳዩን ዝም ብሎ መተው የለበትምና በፍለጋ ሰዓታት ያያቸውን ጥቃቅን ፍንጮች በማገጣጠም የሰፈሩን ሰው ጠረጠረ ፡፡ እናም ሊሞግተው አደባባይ አቆመው ፡፡ 

ከሳሽ ፤ የአጤ ስርዓቱን የመሰረቱን
         አልናገርም ሀሰቱን
         ሁልግዜ እውነት እውነቱን
         መጣሁ እንደ ውሃ ስፈስ
         እንደ ጋዣ ስነፍስ
         በቅሎዬ ሰጋሪ
         ሚስቴ ነጭ ጋጋሪ
         ለወታደር የለው ምሳ
         ለቀበሮ የላት ገሳ
         በሬዬ ጠፍቶ ከደጋ
         ስከተል  መጣሁ በደም ፍለጋ
         ብደርስ በፍለጋው ከደጅህ
         ሙዳ ስጋ ይዟል ልጅህ
        ስለዚህ በሬዬን ትከፍላለህ በግድህ !!

ተከሳሽ ፤ ፍየል መንታ ትወልዳለች አንዱ ለመጣፍ
           አንዱ ለወናፍ
           መጣፉ እኔ መናፉ አንተ
           እንደ ውሃ ብትፈስ በቦይ ትመለስ
           እንደ ጋዣ ብትነፍስ አጭዶ ለፈረስ
           ሚስትህ ነጭ ብትጋግር  አንድ እንግዳ አታሳድር
           በቅሎህ ብትሰግር እመሸበት ታድር
            እንዴት ለወታደር የለውም ምሳ
            እራት ጋግሮ ለራት ለምሳ
            እንዴት ለቀበሮ የላት ገሳ
            ትገባለች አርባ ክንድ ምሳ
            በሬህ ቢጠፋ ከደጋ
            አንተም ብትመጣ በደም ፍለጋ
            ከቤቴ በላይ አለ ተራራ
            መዘዋወሪያው የጅብ ያሞራ
            አሞራና ጅብ ሲጋፉ
            ሙዳ ስጋ ስጋ ስለተፉ
            ያላወቀ ልጅ ቢያነሳ
            አያስከፍለኝም ነገርህን አንሳ !!  ይለዋል ፡፡ 

ተሟጋቾቹ በግለት ሲከራከሩ ከየጎጡ መጥተው የታደሙ ሰዎች በክርክሩ መሃል    ‹‹ እውነት ነው !! በደንብ አርገህ ንገረው !! ይገባዋል !! ›› በማለት ደጋፊ ሀሳብ በማቅረብ አጋርነታቸውን ይገልጻሉ ፡፡

ይህን በመሰለ መልኩ የሚደረግ ክርክር ላይ መገኘት መንፈስን እንደሚያስደስት አያጠራጥርም ፡፡ ከዘመናዊ ህግ አሰራር አኳያ ‹‹ በልሀ ልበልሃ ›› አንዳንድ ክፍተቶች ሊኖሩበት ቢችልም ይህ ድንቅ ባህል እየተረሳና እየጠፋ መሄዱ በተለይም ኪነ ጥበብን የሚጎዳ ይመስለኛል ፡፡ ሰዎች ሀሳባቸውን በግጥምና ስነ ቃል መግለጻቸው ፣ በግጥም የሚቀርቡ ሀሳቦችን ደግሞ ያለ ምንም ችግር ማጣጣም መቻላቸው ለደራሲዎች ቀጣይና የጠነከረ ፈጠራ ምርኩዝ ይሆናል ፡፡ ጥሩ ልቦና ያላቸው ደራሲያን በበዙ ቁጥር ብዙ እንዲጽፉ ይገፋፋቸዋልና ፡፡

በልሀ ልበልሃ በአሁኑ ወቅት ለዘመናዊ ህግ አያስፈልግ ይሆናል ፡፡ ወይም አባት ነኝ ባዩ ህግ ያንተ ነገር በቃኝ በማለት ክዶት ይሆናል ፡፡ ግን በልሃውንና ዘመናዊውን ህግ እንደ ሀገራችንና እንደ ሌሎች ሀገሮች ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር በንጽጽር ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል ፡፡ በልሃውና ንጉሱ የመወሰን ስልጣናቸው አነስተኛ ቢሆንም ክብርና ሞገሳቸው ትልቅ ነው ፡፡ ፕሬዝዳንታችን ህጎችን በነጋሪት ጋዜጣ ያውጃል ፤ በልሃው የቀድሞው ማንነታችን አለመሞቱን ያውጃል ፡፡ ፕሬዝዳንታችን የሹመት ደብዳቤ ይቀበላል ፤ በልሃው ከገጠር ቅኔ ዘራፊዎችም ሆነ ከከተሜው ገጣሚዎች የተሳትፎ ጥያቄዎችን እየተቀበለ የተቀናጀ ተሳትፎ እንዲደረግ ሀሳብ ሊያመነጭ ይችላል ፡፡ ፕሬዝዳንታችን ኒሻኖችንና ሽልማቶችን ይሰጣል ፤ በልሃው በት/ቤት፣ በትያትር ቤት፣ በዩኒቨርስቲዎችና በኮንሰርቶች ውድድር እየተካሄደ ለሚያሸንፉት ሽልማት ይሰጣል ፡፡ ፕሬዝዳንታችን ይቅርታ ያደርጋል ፤ በልሃው ተሸናፊዎች በተጋነነ ቅጣት እንዳይጎዱ ይቅርታ ያደርጋል ፡፡

ታዲያ ማነው ይህ ጠቃሚ ባህል ተጠብቆ እንዲቆይ መስራት ያለበት ? እንደ እኔ እምነት ቢያንስ ይህን የህግ የበኩር ልጅ በጉዲፈቻነት ለማሳደግ የባህል መዋቅሮችና በደምሳሳው ከያኔዎች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ፡፡