Monday, November 12, 2012

የላቀ ክብር - ለሚገባው መሪ



ደቡብ አፍሪካዊያን የቀድሞ ጀግና መሪያቸውን አልፎ አልፎ ብቻ በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ማስታወስ አላረካቸውም ፡፡ በርግጥ በርካታ ኀውልቶችን ቀርጸውላቸዋል ፣ የመናፈሻ ቦታዎችን ገንብተውላቸዋል ፣ ሌላም ሌላ ፡፡ ይህም ለዓለም ምርጡ ሰው በቂ አይደለም ፡፡ ምግባሩ እንደ ኤቨረስት ተራራ የገዘፈ ሰው ሁሌም የስስትና የአድናቆት አይን ሊርቀው አይገባምና እንደ ሌሎች ሀገሮች በቁልፍ ማንጠልጠያ ወይም በፖስት ካርድ ላይ ማስተዋወቅም ከሰሞነኛ ጉዳይነት የሚራመድ አልመሰላቸውም ፡፡

በጥልቀት አሰቡበት ፡፡
አንድ ሁነኛ ዘዴም አገኙ ፡፡

ዓለም የሚወደውን መሪ ዘወትር እየተመለከተ ማድነቅ የሚገባው በቅርበት ኪሱ ውስጥ ሲያገኛቸው ነው ፡፡ እናም የሀገራቸውን የብር ኖት / rand / መቀየር ወደዱ ፡፡ አዲሶቹ የብር ኖቶች ባለ 10፣ 20፣ 50፣ 100 እና 200 ራንዶች ሲሆኑ በሁሉም የመጀመሪያ ገጽ ላይ የታላቁ መሪ የኔልሰን ማንዴላ የፊት ገጽታ እንዲታይ ተደረገ ፡፡ ደቡብ አፍሪካዊያን ብልሆች ናቸውና ትልቅ ገቢ ከሚያስገኙበት ዘርፍ አንደኛ የሆነውን ቱሪዝም ይበልጥ ለማስተዋወቅ በገንዘቡ የኃላ ገጽ ላይ ትላልቆቹ አምስቶች / Big Fives / የሚሏቸውን የዱር እንስሳት ማለትም አንበሳ፣ ነብር፣ አውራሪስ፣ ጎሽ እና ዝሆንን አተሙበት ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ፡፡

የሀገር መሪን በገንዘብ ላይ ማተም ለዓለማችን አዲስ አይደለም የሚል አስተሳሰብ ሊነሳ እንደሚችል አስባለሁ ፡፡ በርግጥ ሀሳቡ የሸመገለ ነው ፡፡ የማያረጀው ጥያቄ የማስተዋወቁ ሂደት ወይም የተሰጠው ዕውቅና የተከናወነው በዲሞክራት መንገድ ወይስ በኩዴታ የሚለው ይሆናል ፡፡ ሁሉንም መመዘዎች ብንጨፈልቅ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን እናገኛለን ፡፡

አንደኛው አምባገነን መሪዎች የራሳቸውን ግለሰባዊ አምልኮ / Personality Cult / ለመገንባትና ህዝቡን ጸጥ ለጥ አድርገው ለመግዛት በማቀድ ወይ በራሳቸው ሙሉ ፍቃድ አሊያም በከበቧቸው ጥቅም ፈላጊዎችና ሆዳም ካድሬዎችና አጫፋሪዎች ጎትጓችነት የሚከናወን ነው ፡፡ ሁለተኛው ለሀገራቸው ነጻነት፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና ፍትህ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት አምጥተው እውነተኛው ህዝብ / fake ያልሆነው / መሪውን ለማክበርና ለማስታወስ ሲል ያመነጨው መንገድ ነው ፡፡

እንግዲህ በብር ላይ የምናየው የፊት ገጽታ የሚፈጠረው በዚህ መሰል አግባብ ነው ፡፡ በጣም የሚገርመው ግን በሀገራቸው ገንዘብ ላይ ከወጡ መሪዎች 90 ከመቶው ያህል አምባገነኖችና የማይገባቸው መሆኑ ነው ፡፡ አንድ ከሩቅ አንድ ከቅርብ ላንሳ ፡፡

የሩቁ ፤

በርማን ከ1962 እስከ 1981 የገዟት ኒ ሊዊን በገዳይነታቸውና በአምባገነንነታቸው ይታወቃሉ ፡፡ በአንድ ወቅት ብድግ ብለው የሀገራቸውን ገንዘብ ባለ 15፣ 35፣ 45፣ 75 እና 90 ኖቶች በማድረግ ከምስላቸው ጋር አተሙት፡፡ ዓለም እንዲህ ለየት ያለ ባለ ጎዶሎ የብር ቁጥሮች ስለማትታወቅ የተለየ አትኩሮት መፍጠር መፈለጋቸው አንድ ጉዳይ ነበር ፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ባለ ‹‹ 90 ›› ብር ኖቱን የሚመለከተው ነበር ፡፡ ይህን ብር ያሳተሙት የሚያማክሯቸው ‹‹ ጠንቋዮች ›› ዘጠና ዓመት ይነግሳሉ ብለው ሹክ ስላሏቸው ነበር ፡፡

የቅርቡ ፤

በኮንጎ ነብር የሚመሰለው እንደ አዋቂ፣ ጠንካራና ተመላኪ ነገር ነው ፡፡ ይህን የሚያውቁት ሞቡቱ ሴሴኮ በነብር ቆዳ የተሰራች ኮፍያ አትለያቸውም ነበር ፡፡ በዚህ ብቻ መታወቅ ግን አላረካቸውም ፡፡ እናም የሀገራቸውን ብር በመቀየር በአንደኛው ገጽ ላይ የነብር ኮፍያና ነብራማ ፊት አሳይተው፣ ይህም አልበቃ ስላላቸው ከአጠገቸው የሚወረወር የነብር ስዕል አስለው ገጭ አሉ ፡፡ ላለማስፎገር ደግሞ ከብሩ ጀርባ ለኮንጎ የሃይል ምንጭ ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የኢንጋ ግድብ በሰፊው አዘረጉት ፡፡ ከዚያም ይህንን የግለሰብ ገጽታ ግንባታ ‹‹ ዛየርናይዜሽን ›› ብለው ለሚጠሩት አሰልቺና አደንቋሪ ፕሮፓጋንዳ ከ30 ዓመት በላይ ማቀጣጠያ አደረጉት ፡፡

ከሀገራችን ተነስተን ሩቅ እስከሚገኙት ዋልታዎች  ድረስ ብናስስ አያሌ ገዳይ፣ የህዝብ ፍቅር የሌላቸው፣ ሙሰኞችና አምባገነን መሪዎች በጉልበት  የህዝብ ሃብት የሆነው ገንዘብ ላይ ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ በጉርድ፣ በቁመት፣ በፈገግታ፣ በቁጣ፣ በስላቅ፣ ፎቶ በመነሳት የፈነጩበት መሆኑን እንረዳለን ፡፡

ርግጥ ነው አፓርታይድ የተባለውን አስከፊ ስርዓት ለማስወገድ ብጥብጥ አልባ የተባለ ሰላማዊ ትግል እንዲሁም የሲቪል አለመታዘዝ እንቅስቃሴን በመፍጠር ሀገራቸውን ነጻ ያወጡት ማህተመ ጋንዲም በብር ኖት ላይ ደምቀው ታይተዋል ፡፡ እኚህ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ መሪ ፍጹም በሆነ የሰው ልጆች ፍቅር የሚታወቁ፣ ንብረትና ሃብት ለህዝቤ እንጂ ለእኔ ወይም ለዘመዶቼ በተለየ መልኩ አይገባም ብለው በማይታመን ኑሮ ውስጥ ያለፉ፣ የታገልኩት ራሴን ለማሳበጥ ሳይሆን የህዝቤን ነጻነት ለማጎናጸፍ ነው በሚል በህንድ የማይታመን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲዘረጋ፣ ዛሬም ሀገሪቱ ተጠቃሽ እንድትሆን ያደረጉ በመሆናቸው ህዝቡ የሰጣቸው ዕውቅና የሚበዛባቸው አልነበረም ፡፡

ማህተመ ጋንዲን የሚተኩ የዓለም መሪዎች ግን በቀላሉ እየተገኙ አይደለም ፡፡ በርግጥ በአሁኑ ዘመን ከአፍሪካ ብቸኛው ተኪ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ናቸው ፡፡ እኚህ ሰው ‹‹ የዚህ ትውልድ ታላቁና ጀግና መሪ ›› መሆናቸውን ዓለም በተመሳሳይ ቋንቋ መስክሯል ፡፡ 27 ዓመታት በእስር ያማቀቃቸውን ስርዓት በይቅርታ አስተማሩት እንጂ አልተበቀሉትም ፡፡ እንደ ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ግዜንና አጋጣሚን እየተጠቀሙ የበደላቸውን ወይም በዳይ የመሰላቸውን አልገደሉም ፣ አላሰሩም ፣ ሰበብ እየፈለጉ አላስጨፈጨፉም ፡፡ በዚሁ ሰበብ ህዝቦችን አልከፋፈሉም ፣ የማይዋጥ ወይም የማይፈለግ ርዕዮት አላሸከሙም ፡፡ አንዱን እውነተኛ  ሌላውን ጸረ ህዝብ በማለት አላሸማቀቁም ፡፡ አንዱ ባማረ ቪላ ሌላውን በየመንገዱ እንዲተኛ አላስፈረዱም ፣ አንዱን ባለ ሃብት ሌላውን ለምኖ አዳሪ እንዲሆን ክፉ መንገድ አላሳዩም ፡፡ ህዝቦችን በፍቅር አቅፈው ሳሙ እንጂ አልተዛበቱም ፣ አልተሳደቡም ፡፡ ስለደማሁና ስለቆሰልኩ ስልጣን ሁሉ ለእኔና በእኔ ፍላጎት ላይ ብቻ ይመሰረታል በማለት ‹‹ ወንበሩ ›› ላይ አልተሰፉም ፡፡ ስልጣን ገደብ ይኑረው የሚል ጠቃሚ ምክር ለለገሱ  ‹‹ ስልጣን ናፋቂ… ስልጣን የሚሻ ብረት አንስቶ መድማት ይኖርበታል ›› በማለት የደደበ አስተምህሮ አላሰሙም ፡፡ በርግጥ እሳቸው ያደረጉት ፍጹም የሚያስገርመውንና ተቃራኒውን ነበር ፡፡ ለሁለተኛ ግዜ እንኳን ሳይወዳደሩ ስልጣናቸውን ለተተኪው ትውልድ ማሰረከብ ፡፡

እንደ እንክርዳድ የበዙ አምባገነን መሪዎች በየግዜው በሚፈሉባት አፍሪካ የዚህ ዓይነት ስብዓና የተላበሰ መሪ ይበቅላል እንዴ ? የዚህ ምርጥ ዘር ምንጭ እውነት አፍሪካ ነው ? ይህ ጥያቄ ነበር በወቅቱ ለዓለም ራስ ምታትና ጭንቀት የሆነው ፡፡ ወዲያው ግን ከጭንቀቱ ጥላ እየወጣ ማክበር፣ ማድነቅና በደስታ ማንባት ጀመረ ፡፡ አያሌ ውርደት የተሸከመቸው አፍሪካ በማንዴላ ተግባር መጽናናት ብቻ ሳይሆን እንደ ዔሊ የሸጎጠቸውን አንገት አውጥታ ዙሪያ ገባውን በልበ ሙሉነት መቃኘት ቻለች ፡፡ አለም ደስታ መግለጫ ቃላት ተቸገረ ፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት 250 የሚደርሱ ልዩ ልዩ ሽልማቶች ለማንዴላ የተሰጡትም በዚሁ አግባብ ነበር ፡፡ በ1993 ደግሞ የኖቤል ተሸላሚ ሆኑ ፡፡ ህዳር 2009 በተመድ ውሳኔ ሀምሌ 18 ቀን የማንዴላ የልደት በዓል ‹‹ የማንዴላ ቀን ›› ተብሎ እንዲከበር ተደረገ ፡፡

ጎበዝ ማንዴላና የዛሬ የክብር ሽልማታቸው የመነጨው እንግዲህ በሳቸው ፍላጎት ወይም በካድሬዎቻቸው ብልጣ ብልጥ የፖሊሲ ቀረጻ ምክንያት ሳይሆን ባገጠጠውና በማይካደው ተግባራቸው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ፡፡  በሌላ አነጋገር የተወሰኑ ቲፎዞዎች ተጽዕኖ ፈጥረው ባስገኙት ወፍራም ጭብጨባ ብቻ አይደለም ፡፡ አኩሪ ስራ ለሰሩ የሀገር መሪዎች ተገቢውን ዕውቅናና ክብር መስጠት ግድ ይላል ፡፡

የሰው ልጆች ፍቅር፣ እኩልነት፣ ነጻነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲን ከምንም በላይ አብልጠው ይፈልጋሉ ፡፡ አፍሪካም ለገዳይና አምባገነን መሪዎች የሚሰጠው ፕሮፓጋንዳዊ እውቅና ይቆም ዘንድ መታገል ይኖርባታል ፡፡

ረጅም ዕድሜ ለማንዴላ ዓይነቶች !!!

No comments:

Post a Comment