Sunday, April 27, 2014

የደነበረው


የደነበረ በሬን የሚያረጋጋው ሁለተኛ አካል የለም ። በሬው መረጋጋት የሚችለው የራሱ የድንጋጤና የፍርሃት ድልቂያ በራሱ ግዜ እየሳሳ ሄዶ ጸጥ ማለት ሲጀምር ነው ።
እንደእኔ እምነት ኢህአዴግ ከደነበረው መንፈስ ገና አልተላቀቀም ። ድርጅቱ ገመድ በጥሶ መሮጥ የጀመረው በ1997 « እንከን የለሽ » ምርጫ ወቅት ነበር ። ዘጠኝ የእፎይታ አመታት በማለፉ ረጅም ቢሆንም እስካሁን እንከን የለሽ መረጋጋት አልፈጠረለትም ። ምክንያቱም ጉዳቱ ከስሜታዊ ቁስል ወደ ስነልቦና ጉዳት ሳይታወቅ ያደገ / Trauma / በመሆኑ ተመሳሳይ ግዜያትን ጠብቆ ሊገነፍል ስለሚችል ።
ያኔ በስንት ደምና አጥንት ያመጣነው ድል ድንገት ከከተማ በበቀለ እንጉዳይ / ድርጅት / እንዴት ይነጠቃል ? በሚል የአጥቢያ ድል አለቆቻችን ሳይቀሩ ቢሮ ዘግተው እዬዬ ብለዋል ። የቅንጅት ጉዳይ ያው በሚታወቀው መልኩ ከተዘጋ በኃላ በሬው እየፎገረ ማባረር የጀመረው « ሀሳብ » ን ነበር - ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን ። በዚህም በርካታ የህትመት ውጤቶች ከገበያው ድራሻቸው ጠፋ ። በሬው ይህን ርምጃ የወሰደው በግራና ቀኝ ጆሮው ላይ መርፌ እየወጉ ከሚያስፈረጥጡት አካላት አንደኛው መሆናቸውን በመረዳቱ ነው ።
ከዚያ ወዲህም ከዴሞክራሲ መብቶች አንዱ የሆነው ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ከአደገኛ ቀጠና ውስጥ መውጣት አልቻለም ። አንዴ ፈንጂ ወረዳ ስለሆንክ ግራና ቀኝህን ተመልከት ሲባል ሌላ ግዜ ቀይ መስመሩን አትጠጋ ወይም አትርገጥ ሲባል እየተሳቀቀ ቆይቷል ። በርግጥ የሀገራችን ህገ መንግስት ለዚህ መብት መበልጸግና መፋፋት በጽሁፍ ደረጃ ድጋፍ ይሰጣል ። ጋዜጠኛው አንዳንዴ ይህን እያሰበ የተወሰነ ርቀት ሲጔዝ ቢታይም ድንገት ከሩቅ የሚተኮስ ድሽቃ ከአፈር ይቀላቅለዋል ። ብእረኞቹ በሚደርስባቸው ተጽዕኖ ሲያማርሩና ሲያቃስቱ ፣ ከታፈረውና ከተከበረው ውክቢያ ጋር ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ፣ መፈክር ይሁን ቁጣ ባለየ መልኩ ሲገሰልባቸው ፣ አንዳንዴም ሲታሰሩ ማየት ብርቅ አልሆነም ።
በመሰረቱ ኦትዮጽያ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌን የህጔ አካል አድርጋ ተቀብላለች ። ይህም ግዙፍ ክሬዲት ሆኖ በየስብሰባው ምስጋና መወድስ ተዘርፎለታል ። አንዳንድ ነጭ ጥናት አቅራቢዎች < ኢትዬጽያን ተመልከቱ የህገ መንግስቷ አብዛኛው ገላ በሰብዓዊ መብት መልካም መዓዛ የታወደ ነው ፣ የኢትዬጽያን መንገድ ተከተሉ በስብዕና ፍቅር ትሰክራላችሁና > በማለት ምስክርነት ሲያቀርቡ ... እሰይ አበጀሽ የኛ ሎጋ አበጀሽ የኛ ልጅ .... እያልን ማስታወሻችን ላይ አንጎራጉረናል ። በየአለማቀፉ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ታዋቂው አንቀጽ / 19 / ሁሉም ሰው ሀሳቡንና አስተያየቱን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በማንኛውም ሚዲያ መግለጽ እንደሚችል ይደነግጋል ። ህገ መንግስታችን አባባሉን እንዳለ ወስዶ የአንቀጹን ቁጥር ብቻ ነው 29 ያደረገው ። ውበት ነበረው ። መልክ ብቻ ምን ያደርጋል ሆነ እንጂ ። በነገራችን ላይ ይህ መብት የተሰጠው  ለጋዜጠኛው ብቻም አልነበረም ።  በመሆኑም ሀሳብ መግለጫው ድልድይ በታሸገ ወይም በተሰበረ ቁጥር የመብት ግፊያና ነጠቃ እየደረሰበት የሚገኘው ብዙሃኑ ጭምር ሆነ ማለት ነው ።
ለማደግ በመፍጨርጨር ላይ በምትገኝ ሀገር ውስጥ ደፋር ፣ ነቃሽ ፣ እውነት አመላካችና ባለሶስት አይን ጋዜጠኛ አስፈላጊ ነው ። ምክንያቱም ማደግ የሚቻለው የልማት አጀንዳን እያግበሰበሱ ዴሞክራሲንና ነጻነትን በማስራብ አይደለም ። ማደግ የሚቻለው በልዩ ተዓምር ሳይሆን ጥሩና መጥፎውን ፣ ሜዳና ገደሉን ለይቶ ሚዛናዊ መስመር ማስመር ሲቻል ነው ። በተቃራኒው ለምን የድርጅቴ ሀሳብ ተብጠለጠለ ? ለምን የድርጅቴ አመራር ተተቸ ? በተቌሜ ክፍተት ሳይሆን በተክለቁመናው ለምን የገነፈለ የብእር ቀለም ተደፋበት ? ወዘተ በሚሉ እፍኝ ሰበቦች ጋዜጠኛውን ማስፈራራት ፣ ማሸማቀቅ ብሎም ወደ ወህኒ ቤት መወርወር በእውነት አሳፋሪ ተግባር ነው - መሰበር ያለበት ጭምር ።
ድርጅቱ በዚህ ረገድ ያለው ስዕል የደበዘዘ ነው ። ሲፒጄ ታህሳስ 2013 ባወጣው መግለጫ ከአፍሪካ ብዙ ጋዜጠኞችን በማሰር ኤርትራ ፣ ኢትዬጽያና ግብጽን የሚያህል የለም ። መንግስት በጸረ ሽብር ተግባር አንጂ በጋዜጠኝነት ያሰርኩት ሰው የለም ቢልም ማስተባበያው ለብዙዎች የተዋጠ አልሆነም ። ይህን መረጃ እውነት ነው ብለን ብንቀበል እንኴ በተከታታይ የተፈጸሙ ሌሎች ተግባራት ጥርጣሬ ውስጥ እንድንገባ አድርገውናል ። ለምሳሌ ፍሪደም ሃውስ የተባለው ድርጅት መንግስት 65 የዜናና አስተያየት ፣ 14 የፖለቲካ ድርጅቶች እና 27 ብሎጎች መዘጋታቸውን ግልጽ ማድረጉ ይታወቃል ። መንግስት ከድርጅቶች ጋር በርዕዬተ አለም ልዩነት ብቻ ሳይሆን ወንበርዋን ለዘለዓለም በማስጠበቅ ሹኽቻ ሊኖቆር ቢችልም ከግለሰቦች ጋር ታች ወርዶ የሚፈጥረው ግርግር ግን አሳማኝ አይደለም ። በሌላ አነጋገር የግለሰቦችን ብሎግ መዝጋት የግለሰቦችን እምነት ፣ አስተሳሰብና ፍልስፍና መርገጥ ነው ። የግለሰቦችን ብሎግ መዝጋት በሃሳብ ነጻነት አጀንዳ ዙሪያ ብዙ አለማወቅን ወይም ደንታ ቢስነትን ያመላክታል ። እንደናንተ ሳይሆን እንደእኔ አስቡ ብሎ ፈላጭ ቆራጭ መንገድን ማሳየትን ያስገነዝባል ።
ጸሀፊዎች አቌማቸው ግራም ሆነ ቀኝ ፣ ሊበራልም ሆነ ዴሞክራት ወይም እምነት የለሽ መከበር አለበት ። መንግስት በተሰደበና በተተቸ ቁጥር ብዕረኛን የሚያስር ከሆነ በነጻ ሃሳብን የመግለጽ ትርጔሜ አረዳድ ላይ ችግር አለ ማለት ነው ። እንግዲህ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ከዚህም በላይ ነው የሚሉት ። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን መብቱን ከህገ መንግስቱ በድፍረት ልጦ ማንሳትን ይጠይቃል ።
መንግስት በሪፖርቶቹና ለውጭ እንግዶች ፍጆታ የፕሬስ ነጻነት ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ መምጣቱን ከመናገር ተቆጥቦ አያውቅም ። አዳማጮቹም ዲፕሎማሲያዊ ወጉን ለመከተል ያህል እንጂ ኢትዬጽያ በፕሬስ ነጻነት 137ኛ / ከ 179/ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ሳያነቡ ቀርተው አይደለም - የአለማቀፉ ፕሬስ ነጻነት ሪፖርትን ። ምን ይሄ ብቻ በሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ተከታታይ ስኮር ካርድ ከ D በታች ውጤት ያላት መሆኑንም ያውቃሉ ። ይህ ሪፖርት የሚዘጋጀው በዴሞክራሲ ፣ ፕሬስ ነጻነትና ሰብዓዊ ልማት ውጤቶች ላይ በመንተራስ ነው ። ቀጣዬቹ አለማቀፍ ሪፖርቶች ደግሞ የከፋ ስዕል ይዘው ለመውጣት የተዘጋጁ ይመስላሉ ። ሰሞኑን ስድስት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች ባልታወቀ ምክንያት እስር ቤት ተወርውረዋልና ።
ዜጎች በታሰሩ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት እንዳላቸው ሁሉ የተያዙበትና የተጠረጠሩበት ምክንያት ወዲያው በግልጽ ሊነገራቸው ይገባል ። ሃሳብን የመግለጽ ፣ የማስተላለፍና የማሳወቅ መብት ተገዢነቱም ለብዙሃኑ ነው ። በመሆኑም ቁጥሩ የበረከተ ብሎገርና ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ምክንያቱ በግልጽ መነገር ይኖርበታል ። አርብን እየጠበቁ ማሰር ግዜ ለመግዛት የተለመደ ፖሊሳዊ አሰራር እየሆነ መጥቷል ። ህዝብንና ህጋዊነትን ማዕከላዊ አድርጌያለሁ የሚል መንግስት ግን ይህም አንደኛው ተጠየቃዊ መርህ መሆኑን በመቀበል መረጃውን ማስተላለፍ ግድ ይለዋል ።
ያም ሆነ ይህ የዚህ ሁሉ ጠለፋ መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው ? እንዲህ ለማለት የምገደደው በመንግስት በኩል መረጃው ለህዝብ ይፋ ስላልሆነ ነው ። የዚህ ክፍተት ተጠያቂ ደግሞ መንግስት ነው ። የማወቅ መብታችንን አፍኗልና ። ስለዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን ብሎ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ምላሹን መገመትም ስህተት አይሆንም ።
ከፊታችን ያለው ምርጫ ?
የሰማያዊ ፓርቲ ትከሻ መስፋት ?
የዘጠኝ አመቱ ቁስል ማገርሸት ? ታዲያ የዘጠኝ አመቱን ቁስል በዞን ዘጠኝ ብሎገሮች ማከም ይቻላል ወይም ማጣፋት ? ምንስ ያገናኘዋል ? ይህ ይህ ጠንካራ የጸሀፊዎች ቡድን መርፌ ሲወጉ እንደነበሩ የቀድሞ ፕሬሶች አይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተሰግቶ ይሆን ? ይሄኛው ግምት ሚዛን የሚደፋ ይመስላል ። ምክንያቱም እስካሁን ለንባብ ባበቋቸው ስራዎች ውስጥ የድርጅቱን ደካማ ጎን በአግባቡ ነቅሰው አውጥተዋልና ። 
ወይ የሀገራችን ፖለቲካ ... የአይኑ ቀለም ያላማረውን ሁሉ ማባረር ... የጠረጠረውን ወይም ያስደነበረውን በተገኘው ስለት
 መውጋት ወይም በሂሳብ ስሌት ማጣፋት ...
 
በዘጠኝ - አንድ ፣ በዘጠኝ - አንድ እንዲሉ ።

ያሳዝናል ።

Tuesday, April 1, 2014

ግብረሶዶማዊነት በሁለቱ ታዋቂ ጻጻሳት ልቦና


የተመሳሳይ  ታ ጋብቻ ህጋዊ የሆነበትን ቀን ተንተርሶ እንግሊዝ ሰሞኑን በግብረሰዶማዊያን ሰርግ ፈንጠዚያ ላይ ነበረች ። በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት ዴቪድ ካሜሮን ጥምረቱን « ታሪካዊ » ሲሉ አወድሰውታል ። በምድረ እንግሊዝ ይህን መሰሉ ጥምረት በ2004 የተጀመረ ቢሆንም ወደ ህጋዊ ጋብቻነት የተቀየረው አሁን ነው ።
ይህ ጋብቻ እውን የሆነው የካቶሊኩ ሊቀጻጻስ ፍራንሲስ ታዋቂ አምስት ቃላቶች « ውዳሴ » ገና ባልከሰመበት ወቅት ነው « WHO AM I TO JUDGE » ይላሉ ጆርጅ ማሪዮ በርጎሊዬ - ለመፍረድ እኔ ማነኝ ? እንደማለት ።
ከዛሬ 24 ዓመታት በፊት ናዚር ጋይድ ሩፋኤል በበኩላቸው በእንግሊዝ ተገኝተው የግብረሶዶማዊነትን ኀጢያታዊ ተግባርና የወደፊት አደገኛነት ለታዋቂ ሰዎችና ምዕመናን ትምህርት እየሰጡ ነበር « HOMOSEXUALITY IS AGAINST NATURE » በማለት - ግብረሶዶማዊነት ተፈጥሮን ይቃረናል እንደማለት ። ይህን አባባል ግን ጋዜጠኞች ታዋቂው ባለአራት ቃላቶች በማለት አላወደሱትም ። ደግነቱ ሊቀጻጻስ ሺኖዳ ዛሬ በህይወት ስለሌሉ በዚህ ዜና አያዝኑም ።
እነዚህ ሁለት ጻጻሳት በትህትናቸውና አንቱ በሚያሰኝ ስራዎቻቸው ይመሳሰላሉ ።
ጻጻስ ፍራንሲስ የአርጀንቲና ሊቀ ጻጻስ በነበሩት ግዜ የተለየ ጥቅማጥቅም አያስፈልገኝም በማለት ተራ አፓርታማ ላይ ክፍሎች ተከራይተው ምግባቸውን ራሳቸው እያበሰሉ ፣ ህዝብን መስለው በአውቶብስ እየተጋፉ ነበር የሚጔጔዙት ። የካቶሊክ ሊቀጻጻስ ሆነው ሲሾሙም ቤተመንግስት ከመግባት ይልቅ የቫቲካን ሰራተኞች በሚኖሩበት ህንጻ ላይ መኖርን መርጠዋል ። ለሳቸው ይወጣ የነበረውን የትየለሌ ገንዘብ ለሰብዓዊ ርዳታ እያዋሉ ይገኛሉ ።
ጻጻስ ሽኖዳ የግብጽን በረሃ በመምረጥ የምንኩስና ህይወትን ለብዙ አመታት አጣጥመዋል ። ከግብጽ ውጭ ገዳማትንና መንፈሳዊ ኮሌጆችን በማሰፋፋት መንፈሳዊ እውቀት እንዲጎለበትና ቁጥሩ እንዲጨምር ልዩ ሚና ተጫውተዋል ። ኢል ከራዛ የተባለ ሃይማኖታዊ መጽሄት በማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ከሰፊው ዕውቀታቸው በመጨለፍ 101 የሚደርሱ መጽሃፍትን ለንባብ አብቅተዋል ። ስራዎቹም በልዩ ልዩ ቌንቌዎች ተተርጉመዋል ።
እነዚህ ሁለት ጻጻሳት ከክርስትና ባህር የተቀዱ ቢሆንም ዛሬ አለምን በስፋት እያነጋገረ በሚገኘው ግብረሶዶማዊነት ዙሪያ ያላቸው አመለካከት በፍጹም አይገናኝም ።
ለምን ?
አይታወቅም ።
አንድ መሆን ይጠበቅበት ነበር ?
ቢያንስ በጣም መራራቃቸው እንዴት ? የሚል ጥያቄ እንዲወለድ ምክንያት ይሆናል ።
የአሌክሳንደሪያው ጻጻስ ሽኖዳ ግብረሶዶማዊነት ከተፈጥሮና ከመጽሀፍ ቅዱስ ቃል የሚቃረን በመሆኑ ሃጢያት መሆኑንና አባላቱ መንግስተ ሰማያት እንደማይገቡ ያስረዳሉ ። የካቶሊኩ ጻጻስ ፍራንሲስ የቤተክርስቲያኒቱን መመሪያ በመንተራስ ግብረሶዶማዊነትን በሁለት ከፍለው ነው ሀሳብ የሚሰጡት ። የግብረሶዶማዊነት ዝንባሌ ያለው እንደሃጢያተኛ አይቆጠርም ። ግብረሶዶማዊ ተግባርን የሚፈጽም ግን ሃጢያተኛ ነው ። < ዝንባሌ > የሚለው ቃል እንዴት ሊፈጠር ቻለ ? በግርድፉም ደጋፊነትንና አድናቂነትን ይገልጻል ። የድጋፉ መነሻስ ከምንም ተነስቶ ነው ማለት ይቻላል ? ምናልባት ይህ ደጋፊ ነገ ተጨዋች ለመሆን በእጅጉ የቀረበ ይመስላል ። መገመት የማይቻለው አሰላለፉን ነው - ተመላላሽ አጥቂ ነው ወይስ ቌሚ ተከላካይ ? ወይም እንደ ሚስት ነው የሚተውን እንደ ባል እንደማለት ።
ቅጣቱን በተመለከተም የጻጻሳቱ አመለካከት እንደሰሜንና ደቡብ ዋልታ ጫፎች የተራራቀ ነው ። ሺኖዳ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን የተወገዘና ክፉ ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ያስረዳሉ ። በኦሪት ዘሌላዊያን ምዕራፍ 20 ፡ 13 « አንድ ወንድ ከሌላው ወንድ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ቢፈጽም ሁለቱም አስከፊ ነገር ስላደረጉ በሞት ይቀጡ ። ስለመሞታቸውም ኃላፊነታቸው የራሳቸው ይሆናል » የሚለውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።
የአዲስ ኪዳኖቹ
ወደ ሮም ሰዎች 1 ፡ 27
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6 ፡ 9
የይሁዳ መልዕክት 7 የግብረሶዶማዊነትን ቅጣትና የእግዚአብሄርን መንግስት አለመውረስ የሚያስረዱ ናቸው ።
ፍራንሲስ እነዚህን ጥቅሶች በመተው የተለየ ምላሽ መስጠትን መርጠዋል ። ታዋቂ የተባለውን who am i to judge ? በርግጥ እነዚህ ተሳቢ ቃላቶች ነገር ለማሳመር ተከርክመው ቀረቡ እንጂ ሪሞርኬው ከፊት አለ - እንዲህ ነው ያሉት « አንድ ግብረሶዶማዊ ፈጣሪን ከተቀበለና መልካም ስነምግባር ካለው እኔ ማነኝ እና ነው የምዳኘው ? » አንዳንዶች ይህን አባባል የተጠቀሙት ትህትናን ለማሳየት ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ህገ መጽሀፉን ለመሸሽ ነው ብለዋቸዋል ።
እዚህ ጋ ፍጥነታችንን አቀዝቅዘን ከሀሳቦቹ  ጀርባ ሊሆን ስለሚችለው ጉዳይ የሆነ ነገር እንበል ። ሽኖዳ መጽሀፍ ቅዱስን ቃል በቃል ጠቅሰው ሞት ይገባል ነው ያሉት ። ኃላፊነቱም የሟቹ ነው ። ህግ ከውሃ የቀጠነ መሆኑ ቢታወቅም እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች ወዳልተፈለገና የከፋ ጫፍ እንደሚያደርሱም ይታወቃል ። ምክንያቱም ስሜታዊነትን አቅፈዋልና ። ለአብነት ያህል ኡጋንዳ የጸረ ግብረሶዶማዊነት ህግን ባጸደቀች ማግስት በተነሳ አመጽ አንድ ግብረሶዶማዊ ተቃጥሎ እንዲሞት ተደርጔል ። መቼም የሶዶምና ገሞራ ሰዎችም በዚህ መልኩ ነው የተፈጁት ብለን የምንከራከር ከሆነ የጻጻስ ፍራንሲስ አምስት ቃላቶች ትክክል ናቸው ማለት ነው ። እኛ ማነንና ነው ህግን የተላለፈ ሰው በጣም በተጋነነና ለቀሪው ትምህርት ሳይሆን በሽታ ሊፈጥር በሚችል መልኩ በእሳት የምናቃጥለው ? ህግ በቀለኛ መሆኑ ይታወቃል ። የበቀሉን ጉማሬ ከኃላ ኪሱ የሚያወጣው ግን መጀመሪያ ገስጾና አስተምሮ ነው ። ሰው ሲሞት እንኴን አስከሬኑን የማቃጠል ባህል መቅረት አለበት በሚባልበት ዘመን ህይወት ያለውን ሰው እንደዳመራ በመለኮስ ሰብሰብ ብሎ ወደ ሰሜን ይወድቃል ወይስ ወደ ምዕራብ እያሉ መወራረድ እንዴት ያስደስታል ? ያሰቅቃል እንጂ ።

በሌላ በኩል ጻጻስ ፍራንሲስ እንደቀድሞው ጻጻስ ተጽዕኖው በዝቶባቸዋል አሊያም የሳይንሱን እውነታ እየሸራረፉም ቢሆን መቀበል ጀምረዋል ። እንደሚታወቀው ግብረሶዶማዊነት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ሆኖ የመፈጠር ነው የሚሉ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ጣጣውን የጄኔቲክና ሆርሞን ውጤት አድርገውታል ። ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ በክሮሞዞምስ ፣ አእምሮና ሆርሞኖች ላይ ጥናቶች አከናውነዋል ። ለአብነት ያህል 400 የሚደርሱ መንታ ልጆች ላይ የተደረገ ጥናት Xq28 የተባለውን ክሮሞዞም እንደሚጋሩት ያሳያል ። ይህን ክሮሞዞምስ ጥንድ ያልሆኑ ወንድሞች አይጋሩትም ወይም በጥቂቱ ነው የታየው ። በዚህም መሰረት አንዱ ልጅ ግብረሶዶማዊ ከሆነ ሌላኛው ጥንድ የመሆን እድሉ 50 ከመቶ ይደርሳል ። እነዚህና የመሳሰሉት ጥናቶች እውነት ይኖራቸው እንዴ የሚያሰኝ ጥያቄ እየፈጠረባቸው ይመስላል ።
ዛሬ አለምን ጉድ እያሰኘ የሚገኘው ግብረሶዶማዊነት ሳይሆን የግብረሶዶማዊያን የጋብቻ ጥያቄ ነው ። ምክንያቱም ጋብቻ የተባለውን አንጋፋና ህጋዊ ተቌም እየተጋፋ በመሆኑ ። አለም ተቀብሎት የኖረው የጋብቻ ብይን እድሜያቸው ለአቅመ አዳም / ሄዋን በደረሰና በፍቅር በተግባቡ አንድ ወንድና ሴት መካከል የሚደረገው ማህበራዊ ጥምረት ነው ። እነዚህ ጥምሮች ውለዱ ክበዱ የሚለውን የሰርግ ላይ ምርቃት ከአመት በኃላ ተግባራዊ ያደርጋሉ ። ፍሬና ፍቅር ማየት የሰው ልጆች ሁሉ ጸጋ ነውና ።
ዛሬ አንድ ተማሪ « ጋብቻ የሁለት ጺማም ሰዎች ቁርኝት ነው ፣ በፍቅር ለመደንገጥና ለመሳሳብም አጔጊ ዳሌ ፣ እንቡጥ ከንፈር ፣ የተቀሰሩ ጡቶች ፣ ገዳይ አይን ፣ አመለሸጋነትም ሆነ የጎን አካልነት ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም ። በግብረስጋ ለመርካት የግድ ወርቃማ ምንተሃፍረቶች አያስፈልጉንም - ማንኛውም ቀዳዳ እንጂ » የሚል መመረቂያ ጽሁፍ ቢሰራ ማነው ትክክል አይደለም የሚለው ? ጋብቻ በትርጉም ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ በሚመጣው ቤተሰባዊ ተቌምነቱም እየተኮማተረ ነው ። ህንጻው ውስጥ ከወጉ ፣ ከእምነትና ስርዓቱ ፣ ከባህሉና ከአኗኗር ዘይቤው ጋር የማይመሳሰል ምናልባትም የሚቃረን ደባል ሰተት ብሎ ገብቷል ። ትግሉ ከቀዝቃዛው ጦርነት በላይ የጦዘውም ለዚህ ነው ።
ውጣልኝ !  - አልወጣም !
በህግ አምላክ  ?! - በህግማ ነው የመጣሁት !
እረ የሀገር ያለህ ? የመንግስት ያለህ ? - ነባሩ ትዳር በስቃይ ተተብትቦ ነጋ ጠባ ሊጮህ ነው ። ቆይቶ የሚያገኘው ፖለቲካዊ ምላሽ « ተቻችላችሁ ኑሩ  - ተከባበሩ » የሚል መሆኑ አያጠራጥርም ።
እዚህ ላይ ጻጻስ ፍራንሲስ ጋብቻን በተመለከተ አስገራሚ ለውጥ ማድረጋቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል ። የአርጀንቲና ጻጻስ በነበሩበት ግዜ « ይህ የፈጣሪን እቅድ የማጥፋት ዘመቻ ነው » በማለት ነው ተቃውሟቸውን በግልጽ አሰምተዋል ። የካቶሊክ ሊቀ ጻጻስ ሆነው ከኢጣሊያኑ ኮሬ ዴላ ሴራ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ « ጋብቻ በአንድ ወንድና ሴት የተወሰነ ነው ፣ ነገር ግን ቤተክርስቲያናችን የተመሳሳይ ጾታን ጥምረት በተለይም ከህክምና አገልግሎትና ከንብረት ባለቤትነት አንጻር መደገፍ አለባት » በማለት ልዩ ጉዳዮች በልዩነት የሚመዘኑበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል ።
ሺኖዳ ፍቅር መንፈሳዊና ንጽህ ከመሆኑ አንጻር በሁለት ተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚደረግ ጥምረትን የሚበይኑት ዝሙት በማለት ነው < ግብረሰዶማዊነት ተፈጥሯዊ እኮ ነው ? > የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር ። አንድ ሰው በዚያ መልኩ ከተፈጠረ መጸለይ ፣ መፈወስ በህክናም ማስተካከል ይቻላል ባይ ናቸው ። ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያን ሰዎች በዚህ መልክ ይፈጠራሉ ብላ እንደማታምን ይልቁንም ዝሙት መሆኑን በምሳሌ ማስረዳት መርጠዋል ። ቅዱስ አውግስቶ እና ቅዱስ ፓለጊያ ዝሙት ፈጻሚዎች ነበሩ ። ኃላ ቅዱስ እስከመባል የደረሱት በመጥፎ ተግባራቸው ተጸጸተው ራሳቸውን በማስተካከላቸው ነው ።
የግብረሶዶማዊያን ነገር « ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ ? ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡ ? » አይነት ደረጃ የደረሰ ይመስላል ። ምክንያቱም የተቀጣጠለውን እሳት በማጥፋት ረገድ የእሳት አደጋ ተከላካይ ባልደረባ በመሆን ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብለው የሚገመቱት ቄሶች ራሳቸው የእሳት ራት በመሆናቸው ።
ልክ እንደ ሺኖዳ ሁሉ የቀድሞው ጻጻስ ቤንዲክት XVI የግብረሶዶማዊነት ጥልቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ቄሶች ሊሆኑ አይችሉም ብለው ፈርመው ነበር ። ጻጻስ ፍራንሴስ ግን ግብረሶዶማዊያን ቄሶች ይቅርታ ያገኛሉ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ። ጻጻሱ እንዲህ የተናገሩት ተቸግረው ይመስላል ። ምክንያቱም በሮማን ካቶሊክ የግብረሶዶማዊያን ቄሶችን ቁጥር በትክክል ማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም በርካታ መሆናቸው ብዙዎችን ያስማማልና ። ሌላው ቀርቶ በአሜሪካ ከ1970 እስከ 80ዎቹ በነበሩት ግዜያት በሎስ አንጀለስ ታይምስ በተደረገ ጥናት 1854 ቄሶች ራሳቸውን ግልጽ አድርገዋል ። ይህም በአሜሪካ ብቻ 33 ከመቶ የሚደርሱ ቄሶች ግብረሶዶማዊያን መሆናቸውን ያመለክታል ። ይህን አሃዝ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ተከታዮችን በምትመራው ካቶሊክ መካከል መመዘን የአደጋውን ስፋት በግልጽ ሊያመላክት ይችላል ።
በርግጥ የሁለቱ ጻጻሳት የተለያየ ምስጢር ምንድነው ?
አንዱ ለዘብተኛ ሌላው አክራሪ ስለሆነ ?
አንዱ የምዕራቡ ዓለም የስልጣኔ ውጤት ሌላው የአፍሪካ ኃላቀር ባንዲራ አራጋቢ ስለሆነ ?
አንዱ የተጽዕኖ ውጤት ሌላኛው በራሱ የቆመ ስለሆነ ?
ከእነሱ እምነትና አስተሳሰብ በመነሳት የነገዋን አፍሪካ መገመት ይቻላል ?
አይታወቅም ።