Tuesday, August 28, 2012

ሞትና ንግድ





ታዋቂ ሰዋች ሲሞቱ የብዙዋች ትኩረት ወደ ሟቾቹ ይሳባል  ፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ በብዙ ምክንያቶች ነው ፡፡ ሰዋቹ በሰሯቸው ታላላቅ ስራዋች ክብርና ሞገስ ስለሚያገኙ እንዲሁም ከብዙዋቹ ታላላቅ ሰዋች ጀርባ አከራካሪና አወዛጋቢ ጉዳዮች በመኖራቸው  ብሎ መጥቅለል ይቻላል ፡፡

አንዳንድ ሰዋች ታዋቂዋቹ በህይወት እያሉ ግልብ በሆነ አድናቆትና ፍቅር ውስጥ ነው የሚያስቧቸው ፡፡ ለአድናቆታቸውና ለፍቅራቸው መሰረት የጣለላቸውን አብይ ጉዳይ ካወቁ በቂ ነው ፡፡ ታዋቂዋቹ በሞት ሲለዩ ግን ከመደናገጥና ከመሸበር ባሻገር የመጸጸትና የጥፋተኝነት ስሜት ያበቅላሉ ፡፡ ስለ ሰውዬው ማንነት የሚገልጹ ስራዋችን ከዛሬ ነገ አያለሁ፣ አነባለሁ፣ ለማወቅ ጥረት አደርጋለሁ እያሉ የቆዩበትን መንገድ ይተቻሉ ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የታዋቂ ሰዋች ህይወት ባለ ሁለት መስተዋት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ህዝቡም ሆነ አድናቂው የሚያውቀው የፊት ለፊት ገጽታቸውን ነው ፡፡ የጀርባ ህይወታቸው ከባህል፣ ፓለቲካ፣ ስነ ልቦናና ማህበራዊ ህይወት አንጻር ያፈነገጠና በግጭቶች ውጤት ያበጠ በመሆኑ በብዙ መልኩ ደብቀውት ይጓዛሉ ፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ አንድም ይህን የተደበቀ ማንነታቸውን በሌላ በኩልም አጉድሎ ያቆየውን ፕሮፋይል ለማወቅ በብርቱ ይፈልጋል ፡፡ ከሞቱ በኃላ የሚያገኛቸው ልዩ ልዩ መረጃዋች ስሎ የቆያቸውን ጀግኖች ይበልጥ ለማክበርና ለመዘከር ይረዳዋል ፡፡ ተቃራኒ በሆነው ስብዕናቸውም ለመደመም፣ ሚዛናዊ ምስክርነቱን ለመስጠት ብቻ ሳይሆን እይታውን በማስፋት ትምህርትና ልምድ ለመውሰድ ይጠቀምበታል ፡፡

ይህ የሰው ልጆች የጋለ ባህሪ ነው ፡፡ እንግዲህ ይህን  ተዝቆ የማያልቅ ፍላጎት በማንበብ ነው ‹ አቅርቦት › ፈጣሪዋች ምናባቸውን የሚያሰሩት ፡፡ ለምሳሌ ያህል የማይክል ጃክሰን ልጆች ምግብ ማዘጋጃ ክፍል ውስጥ ባለ ጥቁር ሰሌዳ ላይ ‹ I Love Daddy › ብለው የጻፉት የተለመደ ስሜትን መግለጫ ሃሳብ  ከሞተ በኃላ በ 5 ሺህ ዶላር ተሸጧል ፡፡ አርቲስቱ ጠዋትና ማታ ፊቱን የሚያይበት የቁም ሳጥን ደግሞ 25 ሺህ 750 ዶላር አውጥቷል ፡፡ የሙዚቃ ስራው  ተለቆ 170 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል ፡፡ 

ስፔናዊውን ስመ ጥር ሰዓሊ ፓብሎ ፒካሶን ብዙዋች ያውቁታል ፡፡ ግንቦት 2010  Nude, Greeen Leaves and Bust የተሰኘው ስራው ለጨረታ ቀርቦ በ105 ሚሊዮን ዶላር ተሸጧል ፡፡ ይህ ስራ በ1951 የተሸጠው በ19 ሺህ 800 ዶላር ብቻ ነበር ፡፡ የዊትኒ ሀውስተን ቀሚስ 20ሺህ 480 ዶላር፣ የኤልቪስ ፕርስሊ የሞተር ሳይክል ጃኬት 41 ሺህ 600 ዶላር አውጥቷል ፡፡ በወቅቱ ብዙም ልብ ያልተባሉ ንግግሮች፣ መሸጥ ያቆሙ ካሴቶች ወይም የፎቶ አልበሞች ተጠርዘው ለህትመት ሲበቁ ሚሊዮኖች ያለ ጥያቄ ይገዟቸዋል ፡፡ አንድም ድሮ የዘለልኩትን መረጃ አገኛለሁ በሚል አንድም ለማፍቀርና ለመዘከር ፡፡

የአገራችን የሙዚቃ ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ ሲሞት ያልደነገጠና ያላዘነ ሰው አልነበረም ፡፡ ጥላሁን እጅግ የሚከበር የመሆኑን ያህል አነጋጋሪ ማንነቶች እየተከተሉት የቆየ አርቲስት ነበር ፡፡ በተለይም በራሱ አንደበት የተገለጸው ‹‹ የሆድ ይፍጀው ! ››ን እውነተኛ ታሪክ ብዙዋች ማወቅ ይፈልጉ ነበር ፡፡ ከደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር፣ ማሞ ውድነህና አፈወርቅ ተክሌ በበለጠ መልኩ በጥላሁን ላይ የንግድ ስራዋች በስፋት ተከናውነዋል ማለት ይቻላል ፡፡ ልዩ ልዩ ፎቶዋቹ  ‹የዝነኛው…የአንደኛው …የንጉሱ .. › በሚል ማስታወቂያ ታጅበው እንደ ጉድ ተሽጠዋል ፡፡ ፎቶውን የያዙ የቁልፍ መያዣዋች፣ የማይጠገቡ ድምጾቹን ያቀፉ ዘፈኖች ፣ ማንነቱን የሚተርኩ የህትመት ውጤቶች ገበያ ላይ ውለው ብዙ አልቆዩም ፡፡ የስብሃት ገ/ እግዚአብሄር የተወሰኑ መጻህፍት ጀትን መወዳደር በቻለ ፍጥነት ታትመው አንባቢው ያለበትን ክፍተት ብቻ ሳይሆን የነጋዴዋችንም ኪስ መሙላት ችለዋል ፡፡

በቅርቡ አቡነ ጻውሎስና ጠ/ሚ/ር መለስ በሞት ተለይተዋል ፡፡ የአቶ መለስ እልፈት አቡኑን በመሸፈኑ ማየት የሚገባንን ንግዳዊ ትርዒት ገድቦብናል የሚል እምነት አለኝ ፡፡ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ እየታየ ያለው ንግዳዊ ስርዓት ግን የሚገርም ሆኗል ፡፡ በከተማችን በሁሉም ማዕዘን ሌላ ነገር ሲሰሩ የነበሩ ወይም ስራ ያልነበራቸው ወጣቶች የመለስን ፎቶ በተለያዩ መጠን በማሳተም ከሁለት እሰከ አስር ብር ይሸጣሉ ፡፡ በተለይም የቀብር ስነ ስርዓቱ እንደ ሀገራችን ፍርድ ቤቶች ረጅም ቀጠሮ የተያዘለት መሆኑን መሰረት በማድረግ አቀራረባቸውን አሳድገዋል ፡፡ የመጀመሪያዋቹ ቀናት ሲሸጡ የነበሩ ፎቶዋች ልሙጦች ነበሩ ፡፡ በሂደት ግን ፎቶዋቹ ላይ ሳቢ ጥቅሶች እንዲጨመሩበት አድርገዋል ፡፡ በአንድ ወረቀት ላይ ሁለትና ሶስት ፎቶዋችን በማካተትም የገዢውን ትኩረት ለመሳብ ጥረዋል ፤ አነጋገራቸውስ ብትሉ !! በፊት ‹ የጀግናው መሪ ማስታወሻ አያምልጣቸሁ ! › የሚል ነበር ፡፡ አሁን ደግሞ ‹ ሞቶም ስራ የፈጠረውን መለስ ዜናዊን በእጅዋ ያስገቡ ! › ወደሚለው ማዕረግ ተሸጋግሯል  ፡፡

እንደ ፎቶው አይብዙ እንጂ ሰው የበዛበት ቦታ ላይ ጥቅስ እያነበቡ በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰዋች እንዳሉ ይታወቃል ፡፡ የነዚህ ሰዋች ስነ ልቦና የማንበብ ትጋት በጣም የሚያስገርም ነው  ፡፡ ድሃ የበዛበት አካባቢ

‹‹ ድሃና አክተር ይንገላታል እንጂ አይሞትም ! ››

‹‹ ምንም ድሃ ቢሆን ባይኖረው ሀብት
ከደጃፍ ሲቀመጥ ደስ ይላል አባት ›› የሚሉ ዓይነት ጥቅሶችን ለገበያ ያቀርባሉ ፡፡ መርካቶ መንገድ ላይ የሚነግዱ እናቶች ጋ ጠጋ ብለው ደግሞ     

‹‹ እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ
   ቅማል ታገኛለች በጨለማ ዳብሳ ›› ካሉ መሃረብና መቀነቶች የግድ መላላታቸው አይቀርም ፡፡
ቤተክርስትያን አካባቢ ‹ እግዚአብሄርን ፈልጉት ትጸናላችሁም !! › የሚል ዓይነት ጥቅሶችን ከነመገኛ ቁጥራቸው ሲያንበለብሉ መልስና ብርታት የሚሹ ልቦች በፈገግታ ይቀበሏቸዋል ፡፡  ዐስርቱ ትዕዛዛትን ከሚያምር ስዕል ጋር አስደግፈው ያቀርባሉ ፡፡ በሰሙነ ህመማት ግዜ ከሰኞ እስከ እሁድ ያሉ ቀናቶች ያላቸውን ሚና በመጻፍ ጮክ ብለው ያስተዋውቃሉ ፡፡ ታዲያ ለዚህ መሰሉ አስታዋሽ ጥቅስን መግዛት አይደለም ‹ ይባርክህ ! › የተሰኘውን ብሩክ ምርቃት መጨመርስ ምን ይጎዳል ? ምንም ነው መልሱ ፤ ሰዋቹ ድንገት እንኳን አፈንግጠው

‹‹ በማያልቀው እቃ እየተነገደ
  ሴቱ በማርቼዲስ ወንዱ በእግሩ ሄደ ››  ቢሉ አንዴ በበጎ ያወጡትን ‹ ይባርክህ - ይድፋህ ! › በሚለው ለመለወጥ አቅም አይኖሮትም ፣ ባይሆን በስሱ ፈገግ ይላሉ እንጂ ፡፡ የነሱም ዓላማ ሳቅና ትኩረትን በጅምላ ማጋባት ነው - ቻይናዋች ፈገግ የማይል ሱቅ አይክፈት እንደሚሉት ፡፡ ጥቅሰኞቹ በትዕዛዝም ሊሰሩ ይችላሉ ፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ሃይገር ባስ ላይ ያየነው ‹‹ ጎበዝ የአባይ ቃል ስላለብን ጠጋ ጠጋ በሉ ! ›› የሚለው ልመናዊ ትዕዛዝ ነው ፡፡ የሰሞኑ ወቅታዊ ጥቅሳቸው ደግሞ መልኩ ተቀይሮ

‹‹ አባይ ይገደባል ፤ መለስ ይታወሳል ! ››
‹‹ የሞተው ታጋይ እንጂ ትግል አይደለም ! ››
‹‹ ቆራጡ መሪ እናከብርሃለን ! ›› የሚሉና የመሳሰሉ ሆነዋል ፡፡ ጥቅሱ ብቻ ሳይሆን አነባበባቸው ረጋ ያለና ሀዘንን አቀጣጣይ በመሆኑ ደንበኞች አላጡም ፡፡

የጠ/ሚ/ር መለስን ሞት ምክንያት በማድረግ የልብስ ነጋዴዋችም የአቅጣጫና የቀለም ለውጥ ያደረጉ ይመስላሉ ፡፡ ጥቁር ልብስ ለክፉ ቀን እንደሚፈለግ ቢታወቅም  ጥቁር መዘዝን ሊጠራ ይችላል በሚል ልማዳዊ መመሪያ ድንበር ከልለው እንደሁኔታው ብቻ የሚወዳጁት ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ ዛሬ ግን ገለልተኛ ፖሊሲያቸው እንደተጠበቀ መሆኑን በማሳየት የአሰቸኳይ ግዜ አዋጁን ዕውን ለማድረግ ተነስተዋል ፡፡ ጥቁር ሻሽ፣ ቢትልስ፣ ነጠላ፣ ሸሚዝ፣ ኮፍያ፣ ቀሚስ፣ ሱሪ ወዘተ ተፈላጊነታቸው በመጨመሩ ደፋ ቀናውን በእጥፍ አሳድገዋል  ፡፡ ፎቶ ቤቶች ቢታዘዙም ባይታዘዙም በትልቁ አጥበው መስቀል ከያዙ ቀናት አስቆጥረዋል ፡፡ በአነስተኛና ጥቃቅን በህትመት ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ቲሸርት ፣ ኮፍያ፣ የደረት ባጅ ፣ ፓስተር ወዘተ በብዛት እያመረቱ ይገኛሉ ፡፡

በየግዜው ዋጋ በመጨመር የሚታወቁት ስጋቤቶች ራሳቸውን ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር ለማዛመድ እያሶመሰሙ ይመስላል ፡፡ የት አካባቢ እንደሆነ ባይታወቅም አንድ ስጋ ቤት መጠሪያውን ‹‹ ጀግናው አይሞትም ስጋ ቤት ›› ብሎታል ፡፡ ከስያሜው አጠገብም        ‹‹ ለሀዘን የሚሆን ጥሬና ጥብስ አለ ›› በማለት ያስረዳል ፡፡  ነገና ከነገወዲያም የኢህአዴግን ስትራቴጂዋችንና የትኩረት አቅጣጫዋች እየመዘዙ ለንግድ ስራቸው ስያሜ የሚሰጡ ሰዋች እንደሚኖሩ መገመት ትክክል ነው ፡፡ ጥያቄው ግን ስያሜዋቹ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምን ያህል በአግባቡ ተቀናጅቷል የሚለው ነው ፡፡

አንድ ለአምስት የተባለውን አደረጃጀት አንስቶ ‹‹ አንድ ለአምስት ዳቦ ቤት ›› ብሎ መጥራት አሻሚነትን በአዋጅ እንደማስነገር ይቆጠራል ፡፡ የኔ አንድ ዳቦ የአምስት ሰዋችን ጉሮሮ ያረካል ለማለት ከሆነ ጠዋት ጠዋት ከውሃ ጋር የምንውጠውን ኪኒን ዳቦ እያስታወስን በአላጋጭ ፈገግታ ልንደምቅ ነው ፡፡ በርግጥ በተቃራኒው ማሰብ የሚቻል ከሆነ አምስቱ ዳቦ ለአንድ ሰው ረሃቡን ተንፈስ ሊያደርግለት ይችላል ፡፡ በየቀኑ ይህን እንዳናደርግ ግን የተቀደደው ኪሳችን እስካሁን አልተሰፋልንም ፡፡

አንድ ሌላ ነጋዴ ንግድ ቤቴ ጨዋታ በጣም የሚዳመቅበት ስለሆነ ከዛሬ ጀምሮ ‹‹ ሂስና ግለሂስ ጠጅ ቤት ›› ብየዋለሁ ሊል ይችላል ፡፡ አንባቢው ሲተረጉመው ደግሞ ‹ ይህ ሂስና ግለሂስ በጠጅ የደነበዡ ሰዋች የሚንጫጩበት መድረክ ነው ለካ ? › በማለት ቢያፍታታው ትርጉሙ አውዱን ስቷል ብሎ ለመከራከር አያስችልም ፡፡ እንዲህና እንዲህ የመሳሰሉ ነገሮች ተጠባቂ ይመስላሉ ፡፡ ነጋዴዋች በሃሳብ    ‹ በቅርብ ቀን  › የሚል ማስታወቂያ እያዘጋጁ ይመስለኛል ፡፡ ምን ሊሉ  ? ከተባለ

‹ ውሃ ማቆር ግሮሰሪ ›
‹ ድሃ ተኮር ጋዜጣ ›
‹ ቢፒአር ሁለገብ መናፈሻ ›
‹ ትራንስፎርሜሽን ጫማ ቤት › የመሳሰሉትን ፡፡

ጋዜጦችና መጽሄቶች መረጃ ከማድረስ አንጻር ወቅታዊ ሁኔታን መዘገብ ኃላፊነትና ግዴታቸው መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ሆኖም የፓለቲካውና የሃይማኖቱ  መሪዋች ማለፍ አቅጣጫዋችንና ገቢያቸውን አለወጠውም  ብሎ መናገር ያስቸግራል ፡፡ አዳዲስ ጉዳዮችን ለመጠቆም የሚጥረውን መረጃ ከላይ በመግቢያዬ እንደገለጽኩት ህብረተሰቡ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይፈልገዋል ፡፡ ይህም የህትመቶቹ ኮፒ እንዲያድግ አይነተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ፡፡ በሌላ በኩል ድርጅቶችና ግለሰቦች ከወትሮው በተለየ ምልከታ የሀዘን መግለጫቸው ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ ይፈልጋሉ ፡፡ ይህም ለጋዜጦች ያልታሰበ በረከት ነው ፡፡ እነሆ በግማሽ ዓመት ስራቸውን ሲገመግሙ ‹‹ ከዕቅድ በላይ አትርፈናል ! ›› የሚል የደስ ደስ ያለው ንግግር ይጠቀማሉ ፡፡

የባንዲራ፣ የአበባ፣ የጧፍና ሻማ ገበያም በቀላሉ የሚታይ አይደለም ፡፡ ወቅታዊውን ሞት አዘል ንግድ መዘርዘር ስለሰለቸኝ ወደፊት የሚጠበቁትን አንዳንድ ሁኔታዋች ላመላክት ፡፡ ድርጅቶች ለአዲሱ ዓመት አጀንዳ፣ ፓስት ካርድ፣ የቀን መቁጠሪያ ወዘተ ያሳትማሉ ፡፡ መረጃውን አስቀድመው ወደ ማተሚያ ቤት የላኩ ካሉ መከለሳቸው አይቀሬ ነው ፡፡ መንገድ ላይ ያሉት የፈጀው ግዜ ፈጀቶም ቢሆን ስለ መሪዋቹ ብዙ እንደሚዘክሩ ይጠበቃል ፡፡ ደብተር አሳትመው የሚያከፋፍሉ ድርጅቶች ከከባድ ይቅርታ ጋር በእቅድ የያዟቸውን ታዋቂ ስፖርተኞችና ምርጥ እጆች የተጨነቁባቸውን ስዕሎች ላልተወሰኑ ግዜ ያስተላልፋሉ ፡፡ እነሆ በግማሽ ዓመት ስራቸውን ሲገመግሙ ‹‹ ማቀድ ብቻ ሳይሆን ደራሽ ስራዋችም ያበለጽጋሉ ! ›› የሚል አባባል ያንጸባርቃሉ ፡፡

 ፊልም፣ ቲያትር፣ የቴሌቪዥን ድራማ፣ ሙዚቃ፣ የሙዚቃ ኮንሰርት መነሻውና መድረሻው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጠ/ሚ/ር መለስ ተጽዕኖ እንደሚያርፍበት ይገመታል ፡፡ በእንቁጣጣሽ ክብረ በዓል ስፖርተኛ፣ አክተርና መላዕክትን ማዕከል አድርገው ሲጓዙ የቆዩ ወጣቶች በአቡነ ጻውሎስና በአቶ መለስ ህይወት ዙሪያ ያነጣጠሩ ስዕሎች ላይ ቢያተኩሩ ምንም አይገርምም ፡፡

እንደሚታወቀው ሙዚቃ ቤቶች ከበሮው ወፈር ያለ ሙዚቃ ማሰማት አቁመዋል ፡፡ በምትኩ በድምጽ መሳሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ሙዚቃዋች እየተሰሙ ናቸው ፡፡ ለዚህ የጥበብ ስራ በርካታ ሰዋች ያን ያህል በቂ ትኩረት ይሰጣሉ ማለት ያስቸግራል ፡፡ እኔ ሳነብም ሆነ ስጽፍ በአብዛኛው የምጠቀመው በክላሲካል በመሆኑ ሊሆን ይችላል  ይህ የጥበብ ስራ ሳይታሰብ በከተማው ገኖ መውጣቱ አስደስቶኛል ፡፡ ይህ ስልት ለዘመናት አላፈናፍን ያሉትን የነሮክ፣ ሬጌ፣ ራፕ፣ ጃዝ ወዘተ የጭቆና ቀንበር የሰበረ ሁሉ መስሎኛል ፡፡ ድሮንስ አንድ ዓይነት ነገር ሲበዛ ይጎመዝዝ የለ ! ጥበቡ ልክ እንደ ቋንቋ በራሱ ሙሉ በኩልሄ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለጥሞና ፣ ለፍቅርና ራስን ለመመርመር ምን ያህል ፍቱን መድሃኒት መሆኑን እያሳየ ነው ፡፡

 ክላሲካል ህይወት ከጫጫታና ግርግር ወጪ ያላትን የማይፋጅና የማይበርድ ገጽታን በሚያስደምም መልኩ የሚያንጸባርቅ ጥበብ ነው ፡፡ የሙዚቃ የዓለም ቋንቋነት ይበልጥ ደምቆ የሚታየው በክላሲካል ነው ማለት ይቻላል ፡፡ እስኪ ለአብነት የቻይና፣ የጃፓን ፣ የሱዳንና የግብጽን ክላሲካሎች ያዳምጡ ፡፡ የሰሟቸውን ሀገሮች ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅን ረቂቅ ማንነት እንደ ቴሌቪዥን ይመለከታሉ፣ እንደ ሬዲዮ ያዳምጣሉ፣ እንደ መጸሀፍ ያነቡታል ፡፡ ፓለቲከኞች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራን የሚሰብኳቸውንና የሚመኟቸውን ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነት በረቂቅ ድምጾቹ ውስጥ ገዝፈው ያገኟቸዋል ፡፡

ነፍስ ይማር !!

Thursday, August 23, 2012

‹‹ አለሁ !! ›› ማለት






የሰው ህያውነት ተቋርኗዊ ግብሩ
ምንድነው ተብሎ ቢጠየቅ ተዓምሩ
መዛኝ... ምጡቅ ... ማህበራዊ
ጨቋኝ ... አጥፊ ... አድሏዊ
በሚል ይበየናል በቁም ሰውነቱ
በዛሬ ምህዋር ነገን በማስላቱ ፡፡
ግና የነገን ጆንያ የውስጡን ቋጠሮ
ማን ያውቃል ? ጭነቱን ድርጊቱን መንዝሮ ፡፡
ፊት ያለችው ጸሃይ የተምሳሌቷ ግርማ
ወበቅ ትደብቅ መብረቅ ፤ ብርሃን ትቀፍ ጨለማ
ማን ያውቃል ? የውሎዋን መዘርዝር
የርግማንዋንና ምርቃቷን ሚስጢር ፡፡
ልምድ ሆኖ ብቻ ‹‹ ፍጡሩ ›› አርበኛ
ነገን ይማርካል ‹‹ ፈጣሪ ›› ሆኖ ዳኛ
አለሁ ይላል ‹‹ ያደገው ›› እንስሳ
እንደዛሬው ሁሉ ነገንም ሳይረሳ
ግና ‹‹ አለሁ ! ›› ማለት
ታላቅ ዘበት ! የዘመኑ እብደት !!!

Monday, August 20, 2012

አፓርታይድ በጓሮ በር መጣ




ከዓለማችን ፈጣጣ ህግ አንዱ አፓርታይድ ነበር ፡፡ የዘር ልዩነትን የሚያራምድ ፓሊሲ በመደንገጉ ፡፡ በህጉ መሰረት ደቡብ አፍሪካዊያን ነጭ፣ ባንቱ፣ ጥቁር አፍሪካና ኤሽያ/ ህንዶች ተብሎ በተከፈለው መሰረት ብቻ ይማራሉ…ይሰራሉ.. ይኖራሉ…

ይህ ጨቋኝ ህግ ማንዴላንና ጓደኞቻቸውን ለ ‹ እረ ጥራኝ ደኑ ! › አነሳሳ፡፡ ክፉው ዘመን ከ 1948 እስከ 1994 አካባቢ ሲቆይ 21 ሺህ ዜጎችን ጨፍጭፏል ፡፡ ሁሉም የጥቁር ት/ቤቶች እንግሊዝኛንና የአፍሪካን ቋንቋ በእኩል መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለው ተቃውሞ ለማሰማት ከወጡ 20ሺህ ተማሪዋች መካከል 700 ያህሉ የጥይት ራት ሆነዋል ፡፡ በሶዌቶ ህጻናት በጥይት ሲፈነገሉ የተመለከተ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ የደም እንባ አፍስሷል ፡፡ ነጭ የደቡብ አፍሪካ ፓሊሶች ወጣቶችን በመርዘኛ ውሾች እያስነከሱ ሲዝናኑም ዓለም አልቅሷል ፡፡

የጸረ አፓርታይድን እንቅስቃሴ የሚመሩት ማንዴላና ጓደኞቻቸውም ለረጅም ዓመታት በሮበን ደሴት በእስር ማቀዋል ፡፡ በህዝቡ  ከፍተኛ መስዋዕትነትና በውጩም ዓለም ግፊት ክሌርክ በፓርቲው ላይ የጣሉትን ዕገዳ ጨምሮ ማንዴላን ለመፍታት ተገደዱ ፡፡ አዲሱ ህገ መንግስትም በፊርማ ጸደቀ ፡፡ በኃላም ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ስልጣኑ ለተገቢው ህዝብ ደረሰ ፡፡

ዓለምና ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን በቀል ቢፈሩም ማንዴላ ‹‹ ይልቅ ይቅር ተባብለን ብሄራዊ እርቅን እናንግስ  ›› አሉ ፡፡ ያልተጠበቀና የማይታመን የጀግንነት ውሳኔ ነበር ፡፡ በዚሁ መልኩ አፓርታይድ በርህራሄ ተሸንፎ ራሱን ገደለ ፡፡ በጣም ተጸጽቶም ‹ ጉድጓዴን በጣም አርቃችሁ ቆፍሩ ! › ብሎ በተወው የኑዛዜ ወረቀት መሰረት ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል ፡፡

ሰሞኑን የሞተው አፓርታይድ ተነስቶ ይሁን ወይም እሱ ሲሞት አስረግዞት የነበረው ክፋት በውል ባይታወቅም ሀገሪቱ አስደንጋጭ ጭፍጨፋ አስተናግዳለች ፡፡ በማሪካና በሎንሚን ፕላቲኒየም ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ዘወትር ጥልቅ ግድጓድ ውስጥ ከፍተኛ ስራ ብንሰራም የምናገኘው አነስተኛ በመሆኑ ደመወዝ ይጨመርልን የሚል ጥያቄ ያነሳሉ ፡፡ የሰራተኞቹ ደመወዝ ከ 4 እስከ 5 ሺህ ራንድ የሚደርስ ሲሆን ለጉልበታቸው የሚመጣጠነው ዋጋ 12 ሺህ 500 ራንድ መሆኑን ገልጸው ነበር ፡፡

ታዲያ ምን ዋጋ አለው  ? ፓሊሶቹ ቀጥታ ወደ ሰራተኞቹ በመተኮስ የ 34 ሰዋችን ህይወት አጠፉ ፡፡ 78 ቱ ሲቆስሉ 259 ያህሉ እስር ቤት ተወረወሩ ፡፡ አማረብኝ ብለው ደግሞ ‹‹ የተኮስነው ራሳችንን ለመከላከል ነው ›› የሚል ምላሽ ሰጡ ፡፡ መከላከል እንዲህ ነው እንዴ ? ሲባሉ ‹‹ መጀመሪያ ውሃ፣ አስለቃሽ ጋዝና የመሳሰሉትን ተጠቅመን ነበር ›› ብለው እርፍ፡፡ እንደው መቼ ይሆን አፍሪካ ከእንደዚህ ዓይነቶቹ ማፈሪያ ፓሊሶች ተግባር የምትጸዳው  ? የአፍሪካ ፖሊሶች ዘወትር ስልጠና ወሰደን ይላሉ - ግን መቼ ይሆን ስልጠናው ህዝብን የማክበር ምዕራፍ ላይ የሚያደርሳቸው  ? የሰው ልጅ በተለመደው አልሰር፣ ስኳር ወይም ሌላ በሽታ ይጠቃል እንጂ እንዴት የማመዛዘን ክፍተት ሰለባ ይሆናል ፡፡ ለሀገር ክብር ሲፋለሙ ስለወደቁ የዓለማችን ጀግኖች ከመስማትና ከማንበብ ይልቅ እንዴት Made in ራሳችን በሚሉት የዱላና ጥይት ተረቶች ይበልጥ ይነቃቃሉ ?

በእውነት ተስፋ ያስቆርጣል ፡፡ አንዳንድ ሰልፈኞች ዱላ፣ ቆንጨራና ጦር ይዘው ቢታዩም እነዚህን የሚመክተውና  ጸጥ የሚያደርገው ጥይት ነው ብሎ ተመጣጣኝ ትርጉም መስጠት በእውነት ያሳፍራል ፡፡ ለነገሩ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ ፖሊሶች
አትኩሮ ላያቸው - ወፍራም ስድብ
ሰው አገኘው ብሎ ለሚያስረዳው - ወፍራም ኩርኩም
የመንግስት ያለህ ብሎ ለሚጮኀው - ጥይት የሚያቅሙ ናቸው ፡፡

አሷፊ ፓርላማ፣ አጣሪ ኮሚቴ ወይም የእንባ ጠባቂ ድርጅት ድንገት ከጠየቃቸው ‹ በህጉ መሰረት ነው የሰራነው › ይላሉ ፡፡ ይህ መልስ እንግዲህ ሳያስፈቅድ የጮኀ ሌላ ትርጉም እስካልተሰጠው ድረስ ሞቱን በራሱ ግዜ የጠራ ፍጡር ነው ወደሚለው የቃላት መፍቻቸው የሚያደርሰን ይሆናል ፡፡ ይህን ዝነኛ ወታደራዊ መፍቻ መጨረሻውን አያለው ብላችሁ ከተጓዛችሁ ፖሊሶች ልክ እንደ ማዕረግ ሁሉ በአስተሳሰብም እንደሚከፋፈሉ ትረዳላችሁ ፡፡ በመሆኑም ይላል ቃላት መፍቻው  ‹ አንዳንድ ፖሊሶች ማለት ከጥይት የተሰሩ ጥቁር ድንጋዮች ናቸው ›  ፡፡ ይህ ነጻ ትርጉምማ መጨረሻው ሊሆን አይችልም በሚል ሌላ ‹ እንዴትን ? › ያነሳ ደግሞ በመጽሀፉ ማገባደጃ  ገጽ ላይ  ‹ ህልምና ቋንቋ እንደፈቺው ነው የሚባለው አባባል የዋዛ አይደለም ›  ከሚል ማጣቀሻ ጋር ይላተማል ፡፡

እና ተስፋ መቁረጥ ብቻ ሳይሆን አሳምረው መፍራት ይጀምራሉ ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች እየጮኀ እንጀራ የጠየቀውን ድሃ ሰራተኛ በላስቲክ ጥይት ቀጥ ማድረግ ይሳናቸው ነበር ?  ወደ ሰማይ መተኮስ ነው የሚቀድመው ወደ ሰው ?  ጥይቱን ወደ ሰማይ በመተኮስ ብቻ መበተን እንደሚቻል አያውቁም ወይስ አልፈለጉም ?

የደቡብ አፍሪካው የሩምታ ጭፍጨፋ የሀገራችንን አነጣጥሮ ገዳዮች አስታወሰኝ ፡፡ ምርጫ 97ትን ተከትሎ በኢትዮጽያ 193 ሰዋች በጥይት ሲሞቱ 763 ያህል ቆስለው ነበር ፡፡ በወቅቱ ጉዳዩን እንዲያጣራ የተሾመውና በአቶ ፍሬህይወት ሳሙኤል የሚመራው ቡድን   ‹ መንግስት ያልተመጣጠነ ርምጃ ወስዷል ! › በማለት ሪፖርቱን አቀረበ ፡፡ ቀደም ብሎም ሪፖርቱን እንዲያለሳልሱ በመንግስት ቢነገራቸውም ሰብዓዊና ፍትሃዊነት የሚሰማቸው ሰዋች ያባ ቢላዋ ልጅ ነን አሉ ፡፡ በርግጥ በሪፖርቱ አንስማማም ብለው ሸርተት ያሉ አባላትም ነበሩ ፡፡ ዞሮ ዞሮ ሪፖርቱ ‹ ተቃውሞ የሚበተንበት ቀላል አማራጭ የለም እንዴ ?  የፖሊስ አመለካከትስ ለምንድነው የማይቀየረው ? › የሚል አሽሟጣጭ አስተያት አቅርቦ ነበር ፡፡

የኛን ሪፖርት ለደቡብ አፍሪካዊያን አስቀድመን በግልባጭ ብናሳውቅ ኖሮ ምን ያህል በጠቀማቸው ፡፡ ለነገሩ አርቃችሁ ቅበሩኝ ያለ ስርዓት እንደ እባብ አፈር ልሶ ይነሳል ብሎ የገመተ ማን አለ ? በጅምላው የእኛን ጨምሮ የአፍሪካ ፖሊሶች የአመለካከት ችግር ካልተቀየረ ነገና ከነገ ወዲያም የሌሶቶውን ጭፍጨፋ ሃትሪክ ለማድረስ የሚሯሯጡ ጭፍኖች ይፈጠራሉ  ለማለት ያስደፍራል ፡፡ ጭንቅላታቸው ውስጥ የተጠራቀመውን  አለቃ ! ታዘዝ ! ጥይት ! ተኩስ ! ግደል ! አቁስል ! ወዘተ የተሰኙ መራራና የታሸጉ ቃላቶችን ገላልጠው መፈተሸ ይኖርባቸዋል ፡፡ ህዝብ ! ሰብዓዊ ክብር ! ርህራሄ ! ወገን ! ድሃ ! ለምን ! የሚሉ ሃሳቦችን ከመራራዋቹ ጋር ማዋሃድ ባይችሉ እንኳን እንደ ኮዳ ወይም ጥይት ማስቀመጫቸው ከቻሉ ጭንቅላታቸው ውስጥ ካልቻሉ ወገባቸው ላይ አንጠልጥለው መዞር ይጠበቅባቸዋል ፡፡ ‹ በለው ! ግደል ! › የሚል አረመኔ አለቃ ቢያጋጥም እንኳ ሀሳቦቹ ‹ ለምን ! ወገንህን ! › ብሎ ያስታውሳቸዋልና ፡፡

ለማንዴላና ለእውነተኛ ታጋዮቹ በንጹሀን ላይ የደረሰው ፍጅት ሰቆቃ ይፈጥራል ፡፡ እርጅና ተጫጭኗቸው በገጠር ሰፈራቸው የሚኖሩት ማንዴላ ስልጣናቸውን ሲያስረክቡ የመጨረሻ ንግግራቸውን በም/ቤቱ ውስጥ እንደሚከተለው ተናግረው ነበር ‹‹ የህገ መንግስታችን የመርሁ ምንጭ የሰው ልጆች ክብር ላይ የተመሰረተ ነው ፡፡ የሰው ልጅ ክብር መልካምነት ላይ መስማማት ይኖርብናል ፡፡ ታሪካዊ ባላንጣችን ከነበረው አፓርታይድ ወደ ዴሞክራሲ ያደረግነውን ሰላማዊ ሽግግር የተቀበልነው ለሰው ልጆች ካለን መልካምነትና ይህንኑ ማግኘት ከሚገባው ተገቢነት አኳያ ነው ፡፡ ዴሞክራሲያችን ለሁሉም በጎ ፍሬ ማምጣት ይኖርበታል ፡፡ በተለይም ለድሆችና ትኩረት አጥተው ለቆዩት ››

ይህ አደራ ለዚያውም ሰላማዊ በተባለው ዘመን በአይጠ መጎጦች ተበልቷል ፡፡ የፍቅር፣ ርህራሄና ነጻነት ካባ የደረቡት ማንዴላ በድርጊቱ ምን ያህል እንደሚጎዱ ማሰብ ከባድ አይሆንም ፡፡ Long Walk to Freedom በተባለው መጽሀፋቸው ‹‹ ረጅም ጎዳና የተጓዝኩት ነጻነትን ለማግኘት ነው ፡፡ ብዙ ተጨባጭ ውጤቶችን አግኝተናል ፤ አሁን ያረፍኩት ለግዜው ነው ፡፡ ረጅም ጉዞዬ ግን ገና አልተጠናቀቀም ›› ብለው ነበር ፡፡
 

የሚገርም ትንቢት ተናግረዋል ፡፡ በፍቅር፣ በፍትህና በአድልዋ ላይ የሚደረገው ጉዞ ገና የተጠናቀቀ አይመስልም ፡፡ አዝኛለሁ በማለት ምርመራ እንዲደረግ ያዘዙት ጃኮብ ዙማ አዲስ ትንሳኤ ያስገኛሉ ወይስ አፈሩን አርግፎ ራቁትን በከተማው ዳር ለቆመው አፓርታይድ ጂንስና ካፖርት ያቀብላሉ ?

Friday, August 10, 2012

‎የጀግና መንገድ‎



ኒክ ከባለቤቱ ጋር


--- እጅም እግርም የለውም ፤ ግን የዓለማችን ደስተኛ ሰው ነው ፡፡
--- እጅና እግር አለን ፤ ግን የዓለማችን ሀዘንተኛ ህዝቦች ነን ፡፡
--- < life is greater purpose > በሚል ርዕስ መጽሀፍ አሳትሟል ፡፡
--- < life is knife ! > የሚል ሰፊ ሀሳብ ውስጣችን ቢከማችም ‹ ሆድ ይፍጀው ›  ብለን ለህትመት አላበቃነውም ፡፡

ተቃርኗችን ቢዘረዘር ሰፊ ነው ፡፡ በርግጥ እሱ በአንድ ወቅት እጅግ ተከፍቶና ተስፋ ቆርጦ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል ፡፡ ጥያቄውና ጸሎቱ አንድ ነበር ፡፡ ‹ እጅና እግር ስጠኝ › የሚል ፡፡ ሰሚ ባለማግኝቱ በጣም ተከፋ ፡፡ እናም በዚህ የሚደርስበትን ሙከራ መቋቋምና መታገስ ባለመቻሉ ድርጊቱን ፈጸመ ፡፡

ለኛ ተስፋ መቁረጥና መከፋት ብርቅ አይደለም ፡፡ አንዱ ጥያቄ ሳያድግ በላዩ ላይ ሌላ ጥያቄ ስለሚረገዝ የጥያቄዋቻችን ብዛት እንደ ህዝብ ብዛታችን አስጊ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው ፡፡ ጥያቄዋቻችን ብዙ ህጻናት እንደሚያሳድጉ ቤተሰቦች አእምሯችን ውስጥ ያለ ስርዓት ይንጫጫሉ ፡፡ አእምሯችን ሰላም፣ ፍቅር፣ ፍትህ፣ ነጻነት፣ እንጀራ ወዘተ እያለ ዘወትር ይጠይቃል ፡፡ ከጥያቄዋቻችን መላመድ የተነሳ ነው መሰለኝ ጥያቄዋቹን እንደ ቤት ቁጥር ወይም ታርጋ ከማንነታችን ጋር ለጥፈናቸዋል ፡፡ እንጀራ የሚል ስም አልሰማሁም እንጂ ሰላም ፣ ፍቅር፣ ፍትህና ነጻነት የተባሉ ሰዋች በሺዋች የሚቆጠሩ ናቸው ፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ ? በተጨባጭ ያጣናቸውን ጉዳዮች በምኞት ወይም በመምሰል ለማካካስ ይሆን ? ላይሆንም ይችላል ፡፡

ለማንኛውም ስማቸውን ሳይሆን ከጀርባ ያለውን ማንነት ጠይቀው ምላሽ ያላገኙ ሰዋች መከፋታቸው ይጠበቃል ፡፡ መታገስ ያልቻሉት ውድ ህይወታቸውን በበረኪና፣ በገመድ፣ በጥይትና በመሳሰሉት ለማጥፋት ፈትነውታል ፡፡ ብዙዋች የጥያቄዋቻቸውን ግልባጭ ጆሮ ላለው ለማድረስ ከኬንያ እስከ አሜሪካ ድረስ ተበትነዋል ፡፡ በርግጥ በስደት ህይወት በቂ ምላሽ ያገኙ የታደሉና የተቀደሱ መሆን አለባቸው ፡፡ እስራኤላዊያን ግብጽ ውስጥ ለአያሌ አመታት ኖረው በተፈቀደው ግዜ መመለሳቸውን ያስታውሷልና ፡፡ ጥያቄውን ለሚመለከተው ሁሉ ያላለው የኔ ቤጤ ደግሞ ይሐው በርካታ የእህህ … ክላሲካሎችን እየደረሰ ይገኛል ፡፡ ድምጽ ሳይሆን በቂ ድፍረት ያላቸው ቢያንስ የአይዶል ውድድር ላይ
        ‹‹ እህህ ጠዋት ማታ ዋውዬ
           እህህ ሌሊት ዋውዬ  …. ›› እያሉ ይገኛሉ ፡፡ ‹ ተመስገን › የተሰኘውን ልማዳዊ መዝሙር ጠዋትና ማታ በማቀንቀን የሚታወቁት ቡድኖች ደግሞ  ‹ እነ ፍቅርና ነጻነት › በተሰኙት ስሞች እየተጽናኑ ይመስላል ፡፡

ግን ከባድ ነው ፡፡

በጦርነት ታምሶ የቆየ ቀጠናን እንጂ በጥያቄ የተወጣጠረ አእምሮን በ ‹ ማረጋጋት › መስመር ማስያዝ ይከብዳል ፡፡ በርግጥ ብርቅዬውን ‹ ደስታ › አሁንም በስም መልክ ካልሆነ በተግባር እንዴት መገብየት ይቻላል ? ተስፋ መቁረጥን እንዴት ማከም ይቻላል ?

አዋ ከባድ ነው ፤ በመሆኑም የፈጣሪ ብቻ ሳይሆን የኒክ መንገድም ሳያስፈልገን አይቀርም ፡፡
ቢቻል በአካል ልንጨብጠው ካልሆነ መንፈሱን ልንሞቀው ሳይገባ አይቀርም ፡፡   

እሱ ነው እንደ አማዞን ደን የረዘመውንና የገዘፈውን ተስፋ መቁረጥ ከርክሞ የበረንዳ አበባ ያደረገው ፡፡ እሱ ነው በክፋትና በፌዝ ያበጡ ቦርጮችን አስተንፍሶ የቅርጽ ተወዳዳሪ ያደረጋቸው ፡፡ እሱ ነው የጨካኞችን የደነደነ ልብ ሞርዶ ከውስጣቸው ከርሰ ምድር የሩህሩህነትን እንባ ማፍለቅ እንደሚችሉ እያለቀሱ እንዲያረጋግጡ ያደረገው ፡፡

እሱ ማነው ?

ሙሉ ስሙ ኒኮላስ ጀምስ ቩጂክ ሲሆን ብዙዋቹ የሚጠሩት ኒክ እያሉ ነው ፡፡ ታፍሳስ 4 ቀን 1982 በአውስትራሊያ ሆስፒታል ውስጥ ሲወለድ እጆችና እግሮች እንደሌሉት ታወቀ ፡፡ ወላጆቹ ጤነኛ በመሆናቸው ይህን ክስተት መቀበል አልቻሉም ፡፡ እንዴት ይበላል ? እንዴት ይራመዳል ? እንዴት ይሮጣል ? እንዴት ይማራል ? እንዴት ይጫወታል ? እረ እንዴት ሆኖ እንዴት ይሆናል ?  እናትና አባት ጥያቄዋቹን እያነሱ ምላሽ ሲያጡ ይንሰቀሰቃሉ ፡፡ ሰማይ ምድር ተደፋባቸው ፡፡

ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ከትልቅ ችግር ጋር መጋጨት ጀመሩ ፡፡ በአውስትራሊያ ህግ አካል ጉዳተኛ መደበኛው ት/ቤት ውስጥ ገብቶ መማር አይችልም  ፡፡ ቤተሰቦቹ ሳያቋርጡ ‹ የመብት ያለህ ! › እያሉ በመጮሃቸው ግን ህጉ ሊሻሻል ቻለ ፡፡ ኒክም የመጀመሪያው አካል ጉዳተኛ ተማሪ ሆኖ ተመዘገበ ፡፡ እንደ ልጆቹ ወንበር ላይ ሳይሆን ከፍ ያለ ጠረጼዛ ላይ ቁጭ ብሎ ልጥፍ ግራ እግሩ ላይ ባሉት ጣቶች እየታገዘ መጻፍ ለመደ ፡፡

ትንሽ ከፍ እያለ ሲመጣ ግን ከውጪውና ከውስጡ የሚደርስቡትን ጥያቄዋችና ተጽዕኖዋች መቋቋም አልቻለም ፡፡ እኔ እንዴት ከሌሎቹ ልጆች በተለየ መልኩ ተፈጠርኩ ? ለምን የሰዋች መጠቋቋሚያና መሳለቂያ ሆንኩ ? ማለት ጀመረ ፡፡ በብቸኝነትና በመገለል ቆሰለ ፡፡ ስምንት ዓመት ሲሞላው ራሱን ስለማጥፋት ማንሰላሰል የጀመረበት ግዜ ነበር ፡፡ ቢቸግረው በልጅነት ልቡ ‹‹ አምላኬ ለኔም እጅና እግር ስጠኝ ?  ›› በማለት ዘወትር በማልቀስ ይለምን ጀመር ፡፡ ሰሚ አልነበረውም ፡፡ አስር አመት ሲሞላው ራሱን ውሃ ውስጥ አስምጦ  ለመግደል ሙከራ አደረገ ፡፡ ይሁንና በቤተሰቦቹ ጥረት ከሸፈ ፡፡ በአንድ ወቅት እናቱ አንድ አካል ጉዳተኛ እንዴት ህይወቱን እየመራ እንደሚገኝ የሚተርክ ጋዜጣ በማሳየት ታሪኩን አነበበችለት ፡፡ ይህ ታሪክ በዓለም ላይ ያለው አካለ ጉዳተኛ እሱ ብቻ አለመሆኑን አስገነዘበው ፡፡ ቀስ በቀስም እጅና እግር ያላቸው ልጆች የሚያደርጉትን ነገሮች በሙሉ ያለማንም አጋዥነት ማከናወን እንዳለበት በማመን ልምምዶችንና ጥረቶችን ቀጠለ ፡፡

ውጤቱ አስገራሚ ሆነ ፡፡ ጥርሶቹን ማጽዳት፣ ጸጉሮቹን ማበጠር፣ በኮምፒውተር መጻፍ ፣ መዋኘት ፣ ቴኒስ መጫወት፣ ሰልክ ማናገርና ሌሎችንም ያለ እጆችና እግሮች ማከናወን ቻለ ፡፡ ይህም እንደ ተረገመ ፍጥረት ሲመለከቱት የነበሩ ተማሪዋች አሁን እንደ መልዓክ እንዲመለከቱት አስቻለው ፡፡

 
ኒክ በአካውንቲንግና በፋይናንሻል ፕላኒንግ ሁለት ዲግሪዋችን ከያዘ በኃላ በ19 ዓመቱ የህይወቱን ውጣውረድ ለሌሎች የሚያካፍልበት የንግግር መድረኮችን ማዘጋጀት ጀመረ ፡፡ ለዚህ ይረዳው ዘንድም  life with out limbs  የተባለ አትራፊ ያልሆነ ድርጅት አቋቋመ ፡፡ ዛሬ በት/ቤቶች፣ በእምነት ተቋማት ፣ በድርጅቶች፣ በወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያዋች፣ በእስር ቤቶች፣ በሆስፒታሎችና በስታዲየሞች እየተገኘ ህይወቱንና ልምዱን በመሳጭ የንግግር ችሎታው ያካፍላል ፡፡ በአፍሪካ፣ ኤሽያ፣ ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ሃያ ሀገራት እየተዟዟረ አስተምሯል ፡፡

ኒክ የህይወትን ቀፋፊ ጎኖች በማሸነፍ የላቁ ሜዳሊያዋችን በየግዜው አጥልቋል ፡፡ በ2005 የአውስትራሊያን የዓመቱ ወጣቶች ሽልማት ያገኘ ሲሆን የራሱን ህይወትና እንቅስቃሴ የሚያሳይ የዲቪዲ ፊልም life is greater purpose በሚል ርዕስ ሰርቶ አሰራጭቷል ፡፡ በ2009   < No arms , No legs , No worries > የሚል መጽሀፍ ከማሳተሙ በተጨማሪ < The Butterfly Circus > በሚል ርዕስ በሰራው ፊልም በአጭር ፊልም የምርጥ አክተር ሽልማት ተቀብሎበታል ፡፡ < Some thing more > የሚል ሙዚቃም  ለቋል ፡፡ የካቲት 12 ቀን 2012 ካኔ ሚያራን የተባለች ቆንጆ አግብቶ ህይወቱን በመምራት ላይ ይገኛል ፡፡

‹‹  ፈጣሪን እጅና እግር በተዓምር ስጠኝ እያልኩ እንደዛ ስለምነው ቢሰጠኝ ኖሮ እንደማንኛውም ሰው የተለመደ ህይወት ነበር የምኖረው ፡፡  በወቅቱ ተዓምር ላገኝ አልቻልኩም ፤ አሁን ስረዳው ግን ለካስ ራሴ ተዓምር ነበርኩ ››  በማለት አድማጮቹን በሳቅ ያፈርሳል ፡፡

እንግዲህ የሰው ፍቅርን፣ ፍትህን፣ የህሊና ነጻነትና ሰላምን ሲመኝ የነበረው ኒክ ማለት ይህ ነው ፡፡
ሰው በስድቡ፣ ንቀቱና ማግለሉ ‹ ንክ › ይሆናል ብሎ ሲጠብቀው ‹ ልባቸው እንዲነካ › ያደረገው ኒክ ይህ ነው ፡፡
ያጣውን ሰላም ፣ ፍቅርና ነጻነት በራሱ የጀግና መንገድ የፈታው ኒክ ይህ ነው ፡፡
እንግዲህ ፍቅር፣ ሰላም፣ ነጻነት፣ ፍትህና እንጀራ የምንለምነው ‹‹ እኛም ›› ይኀው አለን ፡፡

ተቆጥረው የማያልቁት ችግሮቻችን እንደ ኩይሳ አድገው ጫፉ ላይ የታሰረው ሰንደቅ ከኩራት ይልቅ ተስፋ መቁረጥን እያውለበለበ ነው ፡፡ ይህ የኩይሳ ምሶሶ እየደነደነ ይሄድ ወይስ ይገርሰስ ? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ የመኖር ወይም ያለመኖር ምርጫ መሆኑ አያከራከርም ፡፡ እንዴት ?  ለሚለው ጥያቄ ነው እንግዲህ የጀግና መንገድ ያስፈልገናል የሚባለው ፡፡