Sunday, March 24, 2013

‎ከሜዳ አህዮቹ የምንማረው . . .‎





ዋሊያዋቹ የቦትስዋናዎቹን ‹ የሜዳ አህያ › በአጣብቂኝ ሰዓትም ቢሆን አሸንፈው መውጣታቸው ያስደስታል ፡፡ ለእነሱም ሆነ ለደጋፊው ፌሽታ መፍጠር ትልቅ ጉዳይ ነውና ‹ የደስታ ስካር አይለያችሁ › ብሎ መመረቅ ይገባል ፡፡

እቺ ተሸናፊዋ ሀገር ቦትስዋና በኳስ ያላት ደረጃ ዝቅተኛ ቢሆንም የብዙ የላቁ ጉዳዮች ባለቤት በመሆኗ በእጅጉ ማክበር ያስፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም ትልቁና ቋሚው ፌሽታ እነሱ ዘንድ አለና ፡፡

‹ የሜዳ አህያ › በነገራችን ላይ የቡድኑ መጠሪያ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ብሄራዊ ምልክትም ጭምር ነው ፡፡ ከጨዋታው በፊት ቀድሞ የተዘመረላቸው ብሄራዊ መዝሙርን ደግሞ ‹‹ የእኛ ምድር / ሀገር ›› ይሉታል ፡፡

እንዳልኩት የቦትስዋና ፌሽታዎች ብዙ ናቸው ፡፡ ከሚከተሉት ረጅም ኳስ አንጻር ከዋሊያዎቹ ኳስን ይዞ ውብና ማራኪ ጨዋታ እንዴት መምራት እንደሚቻል ሳይማሩ አይቀርም ፡፡ እኛ ከእነሱ ልንማራቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ግን ይልቃሉ ፡፡ አንዳንዶቹን እናንሳ ፡፡

. ቦትስዋና ከአፍሪካ ከ 1965 ጀምሮ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከመጡ ሀገሮች የመጀመሪያዋ ናት ፡፡ 9 ከመቶ የሚደርሰው አማካይ እድገቷ እንደ እኛ ሀገር ዝናብ መጣሁ - ቀረሁ እያለ የሚያስፈራራ አይደለም ፡፡ ቀጣይነቱ የተረጋገጠ እንጂ ፡፡

. የአፍሪካ አስከፊ ሙስና ሲነሳ ይቺ ሀገር በተቃራኒው ትዘከራለች ፡፡ በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት መሰረት የለም ከማለት የዘለለ ጥቂት የሙስና እንቅስቃሴ የሚታይባት የጨዋዎች ሀገር ናት ፡፡ እንዴት ቢያሳድጓት ነው ? ያስብላል ፡፡

. በሰበብ አስባቡ የፖለቲካ ፓርቲዎቿን ተሳትፎ የምትጎነትል ሳይሆን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለረጅም ግዜ ሳታቋርጥ የተገበረች አፍሪካዊ ኩራት ናት ፡፡

. የዓለማችን ውድ ማዕድን አልማዝን በገፍ ለአለም ገበያ ታቀርባለች ፡፡ የሚያስገርመው የማዕድንና ነዳጅ ሀብት አናውዟቸውም ሆነ በዚሁ ኢ - ፍትሃዊ ክፍፍል ተማረው ወደማያባራው ጦርነት እንደገቡ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ሳትሆን በፍጹም ሰላማዊና የተረጋጋ ጎዳና እየጋለበች መገኘቷ ነው ፡፡

. እቺ ሀገር ስትነሳ ፍጹም ከአእምሮዬ የማይጠፉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፌስተስ ሞይ ናቸው ፡፡ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት ጋዜጠኞች በተናጥል ቃለመጠይቅ ካደረግናቸው መሪዎች አንደኛው ነበሩ ፡፡ ትህትናቸው ፣ አካብዴ አለመሆናቸው ፣ ነጻ ሆነው በሚሰጡት ቀልዶች ተገርመን ነበር ፡፡ ለካ የእኚህ ሰው ባህሪ ልዩ የሆነው ወቅታዊውን ስብሰባ ብቻ መሰረት አደርጎ ሳይሆን ለዴሞክራሲ የተፈጠሩ በመሆናቸው ነው ፡፡ ይህንን የተረዳሁት ግን በጣም ዘግይቼ ነው ፡፡ ሀገራቸውን ለሁለት ግዜ ካስተዳደሩ በኃላ ስልጣን በቃኝ ብለው ወንበሩን ለሌላ ተመራጭ አስረከቡ ፡፡ በአፍሪካዊ ትህትናና እግዚዮታ ቢለመኑ ቢለመኑ ውስጣቸውን እንጂ ማንንም ማዳመጥ አልፈለጉም ፡፡ እሳቸው ስለ አፍሪካ የዴሞክራሲ ጥማት በጣም ይጨነቁ ኖሯል ፡፡ ይህ ለአፍሪካ ፍጹም የማይታመንና ብርቅ ሆነ ፡፡ ለካስ እንደኛ የገረማቸው ሁለት ሰዎች ነበሩ ፡፡ አንደኛው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ሲሆኑ ሁለተኛው ሱዳናዊ ቱጃር ኢብራሂም ናቸው ፡፡ ሳርኮዚ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ምሳሌ በማለት የሀገራቸውን ትልቅ ሽልማት ሸለሟቸው ፡፡ የአፍሪካን መሪዎች ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማበረታታት ተቋም የመሰረቱት ሞ ኢብራሂም ደግሞ በ 2008 የአፍሪካ ምርጥ ዴሞክራት መሪ በማለት 5 ሚሊዮን ዶላር አበረከቱላቸው ፡፡

ከኚህ መሪ በኃላ ቦትስዋና እንዴት ሆነች ? ካላችሁ መልሱ ዴሞክራሲ የበለጸገባት የሚል ይሆናል ፡፡ ምክንያቱም የማይናወጠውን መሰረት ሞይ ጥለውታልና ፡፡ የ 2011 የሞ ኢብራሂም ተቋም መረጃ እንደሚጠቁመውም የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጀርሲ ጃን ካማ 75.2 ከመቶ በማግኘት ‹‹ ኤ ›› ካገኙ አራት መሪዎች አንደኛው ሆነዋል ፡፡ ለማስታወስ ብቻ የኛ ነጥብ ተጠጋግቶ 33 ነበር ፡፡

የሀገራችን ቴሌቪዥን የኳሱን ቁጥራዊ መረጃ እንደውጪዎቹ ተንትኖ አላሳየንም እንጂ በሌላ ሌላ ያጣነውን በኳሱ ሳናካክሰው የቀረን አይመስለኝም ፡፡ እንግዲህ ኳስ ወንድማማችነት መፍጠሪያ መድረክ ብቻ ሳይሆን መማማሪያም በመሆኑ ከሜዳ አህዮቹ የምንወስዳቸው ስልጠናዎች አሉ ፡፡ ስልጠናው የማያስፈልገን ቢሆን እንኳን የሜዳ አህዮቹን በያዙት የተቀደሰ መንገድ ልናከብራቸው ግድ ይለናል ፡፡

‹‹ ኖር ብለናል ባለ ዴሞክራሲያዎቹ / ዴሞክራቶቹ / !! ››

Saturday, March 23, 2013

የድሃው ፕሬዝዳንት ሀብታም አእምሮ





‹‹ ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን
እግር የሌለው ሰው አለና ! ››

ይህች መሳጭ አባባል ከቆራጥ ድሃዋች አእምሮ በኑሮ ፍትጊያና ውጣ ውረድ ምክንያት የተፈነጠቀች ትመስላለች ፡፡ አንድ ሰው ግን ይህን አባባል የድህነት አባል ነው ብሎ ለመከራከር የሚያስችል መሰረት የለም በማለት ሞግቶኛል ፡፡

እንዴት ? - እኔ ፡፡

‹‹ ተረቱ የሚያገለግለው ለሌላ ተምሳሌት እንደ መወጣጫ እንጂ በራሱ ምሉዕ ሆኖ ለመቆም አይደለም ››

አልገባኝም ! - እኔ ፡፡

በምሳሌ ባስረዳህ ይሻላል ያለኝ ወዳጄ ትንሽ አሰብ በማድረግ የሚከተለውን ተመሳሳይ ነገር ግን የወገቡ ቁጥር ሰፊ የሆነ ጥቅስ ወረወረልኝ

‹‹ G + 1 የለኝም ብለህ አትዘን
ወያኔ ዲኤክስ የሌለው አለና ! ››

ፈገግ አልኩ ፡፡ የሞተሯ ድምጽ እየቆየ ከፍ እያለ እንደሚሄድ ቮልስዋገን ሳቄ መቦተራረፍ አበዛ - የእኔ ፡፡ ባለጸጋዎችም ሲገናኙ ከ ‹ ተመስገን › ይልቅ ብዙ አላገኘሁም ፣ ብዙ አላደግኩም የሚል ምሬትና ቅናት አቀፍ መዝሙር እንደሚያስቀድሙ ይታወቃል ፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ስለሆነ ክፋት የለውም ብሎ ማለፍም ይቻላል ፡፡ ሆኖም የድሃዎችን መሳጭና ስሜት አንኳኪ ጥቅስ ሰርቀው ለማይገባ ጥቅም ያውሉታል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው ፡፡

እንዴት ? - አንተ / አንባቢው /

የላይኛው ጥቅስ ጓደኛዬ እንደሚለው የህይወትን ከፍታ የሚያሳየው በጥቂት የደረጃዎች ልዩነቶች ከፋፍሎ አይደለም ፡፡ ምቾት ሳይሆን እሾህ ፣ ቆንጥር ፣ ድንጋይና ውርጭን ለመከላከል የጠየቀ እግር ነው ማጽናኛ ተብሎ እግር የሌለው ሰው የተጠቀሰለት ፡፡ ይህም የኑሮን ገደልንም ሆነ ግሽበት አድምቆ ያሳያል ፡፡ ምነው ትንታኔው ከአጽናኝነት ይልቅ አደንዛዥነቱ ላቀ ብትል ሃሳብህ አልተጋነነ ይሆናል ፡፡ ግን ለግዜውም ቢሆን ከደረጃ በታችና ከጤና ጎዳና የወደቀን ህይወት አንድ ሀሙስ ለማስቀጠል ማደንዘዣ መጠቀም ሳይንሳዊ ድጋፍ ሳይኖረው እንደማይቀርም መገመት ሊኖርብህ ነው ፡፡

ጫማ የሌለው ድሃ እግር በሌለው ሰው ከተጽናና አነሰም አደገ ሀብት ያለው ባለጸጋ ለምን የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ቁጥር 29 ጥቅስ እንደማያጽናናው ግልጽ አይደለም ፡፡

ምን ይላል ? - አንተ / አንባቢው /

‹‹ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል
ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል ››

ስለዚህ በማለት የመግቢያ ዲስኩራችንን እንደሚከተለው ብታጠቃልለው ስለ ቀጣዩ ርዕሰ ጉዳይ ምን ያህል እንደተቀራረብን ሊያሳብቅህ ይችላል ፡፡ < ስለዚህ  የለኝም  ብሎ አላግባብ ከማንቋረር የያዘው እንዲበዛለት ስም ያለው ተግባር ማከናወን ህሊናዊም መንፈሳዊውም ርካታ ያጎናጽፈዋል >

     +++++                                              +++++++                                               ++++++++

እንደሚታወቀው የዓለማችን ባለጸጋዎች በሁለት ዋና ዋና ምድብ ውስጥ ነው ተሰልፈው የሚገኙት ፡፡ በንግድና አስተዳዳሪነት ፡፡ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት እነ ቢል ጌትስ ፣ ዋረን ቡፌት ፣ የኢንቴል ተባባሪ መስራች ጎርደን ሙርና ሌሎችም የማቲዎስን ጥቅስ በልካቸው አሰፍተው የለበሱ ይመስላል ፡፡ ሃብታቸው በቦሌም መጣ በባሌ በቢሊየን የሚቆጠረውን ገንዘባቸውን ‹‹ ጫማና እግር ›› ሌላቸው ቡድኖች እየሰጡ በተቃራኒው የሰጡትን ያህል ያገኛሉ ፡፡

አስተዳዳሪዎቹ ልዩ መጠሪያቸው ‹‹ ፕሬዝዳንት ›› ወይም ‹‹ ጠ/ሚ/ር ›› ይባል እንጂ የሀገር ሀብትንም ጭምር ነው ወደ ግል ካዝናቸው በአግባቡ መግባቱን ነው የሚያስተዳድሩት ፡፡ በርግጥ ይህ አባባል ሁሉንም መሪ አይወክልም በማለት ማሰተካከያ እንዲገባ አስበህ ይሆናል - በውስጥህ ፡፡ እኔም በመርህ ደረጃ ትክክል ነው እንዳልኩህ ገብቶሃል ብዬ ሃሳቤን ልቀጥል ፡፡ ብዙ መሪዎች ከሚያገኙት የሚታይና የማይታይ ጥቅማጥቅም በተጨማሪ ዓመታዊ ደመወዛቸው እንደ ተራራ የተቆለለ መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ምናልባትም ተራራ ተንዶ ይግደልህ ወይስ የተቆለለ የመሪ ገንዘብ የሚል አጣብቂኝ ምርጫ ውስጥ ብትገባ  መልስህ ‹ እሳት ካየው ምን ለየው › ቢሆን ይመረጣል ፡፡ ካላመንክ ጥቂት የምሳሌ ብቻ ሳይሆን የተራራ ዘሮችን ልበትንልህ ፡፡ ሙአመር ጋዳፊ 200 ቢሊየን ፣ ሆስኒ ሙባረክ 70 ቢሊየን ፣ ቭላድሚር ፑቲን 70 ቢሊየን ፣ ስባስቲያን ፒኒራ /ቺሊ/ 2.4 ቢሊየን ፣ አሲፍ አሊ ዛርዳሪ/ፓኪስታን/ 1.8 ቢሊየን ዶላር ያገኛሉ ፡፡ ጥቂት ባለ ሚሊኒየኖርችንም እንቀላቅል ፡፡ ፊደል ካስትሮ 900 ሚሊየን ፣ ፓወል ቢያ 200 ሚሊየን ፣ ሊሙንግ ባክ/ ደ.ኮሪያ/ 23.6 ሚሊየን ፣ ማንዴላ 15 ሚሊየን ፣ አንጄላ መርክል 11.5 ሚሊየን ፣ ሮበርቱ ሙጋቤ 10 ሚሊየን ፣ መህመድ አህመዲንጃድ 5 ሚሊየን ዶላር ያገኛሉ ፡፡ ባለሺዎቹ ለምን ይቀርባቸዋል ከተባለ የባራክ ኦባማና የ ሁ ጂንታኦ /ቻይና/ 4 መቶ ሺህ ዶላርን ዋቢ ማድረግ ይቻላል ፡፡

ዞሮ ዞሮ ብዙዎቹ የስልጣን መሰረቱ የሚመነጨው ክብር ፣ ሃይልና ሀብትን ማግኘቱ ላይ በመሆኑ እንደ አንዳንድ ነጋዴዎች ‹‹ ለጋስነት የልቦና ጉዳይ ›› መሆኑን አይቀበሉም ፡፡ እምነትና ፍልስፍናቸው ‹ ጭብጦህን በአግባቡ ሰብስብ ፤ ይህም ሃብት እንዳይነጠቅ አምርረህ ጠብቅ ! › የሚል ነው ፡፡

መሪዎቹ ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት መሰረታዊ ጥቅሶች ማለትም የድሃዎችን ‹‹ ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን ›› እና የሀብታሞቹን ‹‹ ላለው ይጨመራል ›› በቀና ልቦና መመርመር ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን አልተረዱም ፡፡ ከቢሊየንና ሚሊየን ሰፊ እርሻ ወስጥ ለዘር የሚያገለግሉ ጥቂት ‹‹ ሺዎችን ›› መበተን ምን ያህል ይከብዳል ?

‹‹ አይከብድም ! ›› - ይላሉ
‹‹ ማን ? ›› - እኔና አንተ
‹‹ የኡራጋይ ፕሬዝዳንት ጆሴ ሙጂካ / jose mujica / ?/ ››
‹‹ እንዴት ? ›› - እኔና አንተ

እኚህ ፕሬዝዳንት የዓለማችን ድሃው ፕሬዝዳንት ቢሆኑም በማይታመን ልግስና ‹‹ ጫማ ከሌላቸው ›› ጎን በመሰለፋቸው ታላቅነትን ተጎናጽፈዋል ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ሌሎቹ ‹‹ አስተዳዳሪዋች ›› ዓመታዊ ደመወዛቸውን ቢሊየንና ሚሊየን ለማድረስ አልፈለጉም ፡ ሺህ ድሃ መሃል የአንድ ሃብታም መገኘት በስነልቦና ድሃ ከመሆን ወጪ ትርፍ የለውም በማለት ይሆን ? ወርሃዊ ደመወዛቸው 7985 ፓውንድ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7 ሺ 500 ፓውንዱን ወዲያው የሚሰጡት ድሃዎችን ለመርዳት ለተቋቋሙ ፕሮጄክቶች ነው ፡፡  ይህ ልግስና የደመወዛቸውን 90 ከመቶ ድርሻ  እንደሚሸፍን ልብ በል ፡፡ እኛ በየወሩ 2 እና 3 ከመቶ ለጤና ፣ ለልማት ፣ ለግድብ ወዘተ እየተባለ ሲቆረጥብን እንዴት ነው የምንሆነው ?
‹ እኛ የምንፈራው መቆረጡን ሳይሆን የሚቆረጥብን የት እንደሚገባ አለማወቃችን ነው › - ነው ያልከው ፡፡ በርግጥ ተገቢ ስጋት ነው ፡፡ በዚህ መንገድ ስንት ሰብዓዊነት የሌለውን ጅብ ስንቀልብ ነው የኖርነው ፡፡

ግን ጎበዝ ያለውን በሙሉ ሳይሳሳ የሚሰጥ ፈጣሪ ብቻ አልነበር እንዴ ? እንዲህ የሚያደርግ የሀገር መሪ አይደለም ጫካ የገባ መናኝ በቀላሉ ይገኛል እንዴ ? ሰምታችሁስ ታውቁ ይሁን ? ለመተዳደሪያ ይበቃኛል ብለው የሚያስቀሩት 485 ፓውንድ ወይም አስር ከመቶውን ብቻ ነው ፡፡

 ‹‹ በርግጥ መሪዎች ለህዝብ ፍቅር አንዲህ የቀረቡ ናቸው ? ››
‹‹ ራሳቸውንስ ይህን ያህል ይጎዳሉ ? ››
 ‹‹ ለመሆኑ እኚህ ሰው ማናቸው ? ››

አእምሮህ በተደራራቢ ጥያቄ ተጨናነቀ አይደል ?!  ለማንኛውም  ሰውየውን ለማጥናት እንሞክር ፡፡

ጆሲ ሙጂካ የተወለዱት ግንቦት 20 ቀን 1935 ነበር ፡፡ አባታቸው ስፔናዊ ሲሆኑ እናታቸው የጣሊያን ዝርያ አላቸው ፡፡ ቤተሰባቸው በስትሪላ አምስት ሄክታር መሬት ገዝተው በወይን እርሻ ይተዳደሩ ነበር ፡፡  ሙጂካ አምስት ዓመት ሲሞላቸው ማለትም በ1940 አባታቸውን በሞቱ ተነጠቁ ፡፡  ሙጂካ ወጣት በነበሩበት ግዜ ሁለት ጉዳዮች ትኩረታቸውን ስቦት ነበር ፡፡ አንደኛው ፓለቲካ ሲሆን በብሄራዊ ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ውስጥ ንቁ ተሳተፎ አደርገዋል ፡፡ ሁለተኛው ስፖርት ሲሆን ለተለያዩ ክለቦች በተለያዩ ካታጎሪዎች የብስክሌት ውድድር ሲያደርጉ ቆይተዋል ፡፡

በ1960ዎቹ ፋኖ ተሰማራ … የሚለው የኩባ አብዮት በሀገራቸውም ተጸዕኖ በመፍጠሩ ለመጀመሪያ ግዜ ከተደራጀውና ከታጠቀው የቱፓማሮ እንቅስቃሴ ውስጥ  ተቀላቀሉ ፡፡ በ1969 አካባቢ ፓንዶን ለመያዝ በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ተሳተፎ የነበራቸው ሙጂካ አራት ግዜ ያህል በመንግስት ወታደሮች እጅ ወድቀዋል ፡፡ ስድስት ግዜ ያህል በፖሊስ ጥይት ተመተዋል ፡፡ በ1971 ፑንታ ካሬታስ ከተባለ እስር ቤት ያመለጡ ሲሆን ከእንደገና በ1972 ተይዘዋል ፡፡ በ1973 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሲካሄድ ለ 14 ዓመታት ወደታሰሩበት ወታደራዊ እስር ቤት እንዲዘዋወሩ ተደርጓል፡፡ በእስር ቤት ቆይታቸው ከቱፓማሮ ፓርቲ በርካታ መሪዎች ጋር ትውውቅ ያደረጉበት ነበር ፡፡

በ1985 በሀገሪቱ ህገ መንግሰታዊ ዴሞክራሲ ሲመሰረት ከ 1962 ጀምሮ በፖለቲካና እና ወታደራዊ ወንጀሎች የታሰሩ ሰዎች ምህረት ሲደረግላቸው  እሳቸውም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆኑ ፡፡ ራሳቸውን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሰፊ ህብረት እንደሚያስፈልግ የተገነዘቡት ሙጂካና ጓደኞቻቸው ከግራ ክንፈኛ ድርጅቶች ጋር በመተባበር Movement of Popular Participation የተባለ ድርጅት መሰረቱ ፡፡ በ1994 በተደረገው አጠቃላይ ምርጫ ምክትል ሆነው የተመረጡ ሲሆን በ1999 ደግሞ ሴናተር መሆን ችለዋል ፡፡ ከ 2005 እስከ 2008 ድረስም የወቅቱ ፕሬዝዳንት ታባሬ የሙጂካን የኃላ ታሪክ በማጥናት የሀገሪቱ የእንስሳት እርሻና አሳ ሚንስትር አድርገው ሾመዋቸዋል ፡፡ በ2009 በተደረገ ሀገራዊ ምርጫ ፓርቲያቸው ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ አድርጎ አቅርቧቸው ማሸነፍ ችለዋል ፡፡ የመጀመሪያ ቀን ንግግራቸውም በአስገራሚነቱ ተመዝግቧል

‹‹ ምን አሉ ? ›› አልክ

 ‹‹ በውድድሩ ያሸነፈም ሆነ የተሸነፈ ስለሌለ በአንድነት እንነሳ ፡፡ ስልጣን ከሰማይ ይመጣል የሚባለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው ፤ ስልጣን የሚመጣው ከብዙሃኑ ልብ መካከል ነው ››

ሙጂካ በስልጣን ቆይታቸው ከፈጸሙት አስገራሚ ተግባር አንዱ ማሪዋና የተባለውን አደገኛ ዕጽ በህጋዊ መንገድ እንዲሸጥ ማድረጋቸው ነው ፡፡ እጹ በህጋዊ መንገድ እንዲያልፍ መደረጉ ሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ እንድታገኝ ብሎም የወንጀልና የጤና እንከኖች እንዲቀንሱ አድርጓል ፡፡ የተመሳሳይ ጾታን ጋብቻን ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ ያደረጉ ሲሆን ተከልክሎ የቆየውን እስከ 12 ሳምንት ዕድሜ ያለውን ጽንስ የማስወጣት ህግም ፍቃድ ሰጥተዋል ፡፡ አንድ ፕሬዝዳንት ከአንድ ግዜ በላይ መመረጥ የለበትም የሚል የጸና አቋም በማራመድ ይታወቃሉ ፡፡

የ 77 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዛሬ ሞንቲቮዶ በተባለ የከተማ ዳርቻ የፓርላማ ተመራጭ ከነበሩት ሚስታቸው ሉሲያ ቶፓላንኪና ከባለሶስቱ እግር ውሻቸው ማንዌላ ጋር ህይወታቸውን ይመራሉ ፡፡ የህይወታቸው መሰረት ልክ እንዳባታቸው ግብርና ሲሆን መኖሪያ ቤታቸውን የተመለከቱ ጋዜጠኞች ለአንድ ፕሬዛዳንት የማይገባና ፍጹም በመፈራረስ ላይ የሚገኝ በማለት ገልጸውታል ፡፡ መንግስት ያቀረበላቸውን ከቤተመንግስት የሚተካከል ህንጻ ብቻ ሳይሆን የከተማውን ህይወት ንቀው ነው አፈር ገፊነትን የመረጡት ፡፡

እኚህ ሰው የዚያ ሀገር ፕሬዝዳንት ነበሩ ለማለት የሚያስችሉ ሀብትም ሆነ ድባብ በቤታቸው ዙሪያ የለም ፡፡ ምናልባት ደህንነታቸውን የሚጠብቁ ሁለት ፖሊሶች መገኘታቸው ካልሆነ በስተቀር ፡፡ የዕለት ስራቸውን የሚያከናውኑት በአንድ ትራክተር ሲሆን አልፎ አልፎ ወደ ከተማ የሚሄዱባት ድክም ያለች የ1987 ሞዴል ቮልስዋገን አላቸው ፡፡ ትልቁ ሀብታቸውም እነዚህ ናቸው ፡፡ አንድ በህዝቡ ሲወደድ የነበረ መሪ ለምን እንዲህ በማይጠበቅና ዝቅ ባለ የህይወት ቦይ ውስጥ ማለፍ ፈለገ ? የሚል ጥያቄ መፍለቁ ግድ ነው ፡፡መልሱ የሰውየው ሰብዓዊነትና ሩህሩህነት የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱ እንዲሁም ለሌሎች ጥቅምና ዕድገት መኖር ራስንም አሳልፎ መስጠት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሳያንገራግሩ በመቀበላቸው ነው ፡፡

ይህን ከባድ ውሳኔ ለማሳለፍ በርካታ ጥቅማጥቅሞችን በመርዘም ሆነ በንቀት ማውደም ያስፈልጋል ፡፡ ስንት ነገር ያሳለፉት ፕሬዝዳንት ለእርሻቸው ውሃ የሚቀዱት ረጅም ጉድጓዶችን ቆፍረው ነው ፡፡ በቀን ለብዙ ግዜ ይቀያየሩ የነበሩትን ልብሶች ዛሬ ላውንደሪ ለማስገባት እንኳ ባለመቻል በእጃቸው ነው የሚያጥቡት ፡፡ በቤተመንግስታቸው ይቀርብላቸው የነበረው ምግብና መጠጥ ፣ ክብርና መሽቆጥቆጥ ፣ ውዳሴና የታላቅነት ስሜት ፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ዛሬ የሉም ፡፡ ቢያማቸውም ሆነ ጫና ሲበዛባቸው ለእረፍት ሀገር አቋርጠው የሚሄዱበት አግባብ አሁን ዝግ ነው ፡፡ ገንዘቡስ የታለና ፡፡ ባለፈው ዓመት ያላቸው አጠቃላይ ሀብት ሲሰላ 135ሺህ ፓውንድ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ ይህ ገንዘብ በሀብታሞቹ መሪዎቹ አይን ከታዩ የአንድ ቀን ራት ቢጋብዝ ነው ፡፡ ገንዘብ ደስታን አይገዛም የሚሉት ሙጂካ የባንክ አካውንት የሌላቸው መሆኑም ሌላ አስገራሚ ጉዳይ ነው ፡፡
በወር የገቢን 90 ከመቶ ለችግረኞች አሳልፎ መስጠት ይከብዳል ፡፡ ግን ለምን ? ተብለው በጋዜጠኞች ሲጠየቁ ‹‹ ይህን ያህል መርዳት አለብኝ ፡፡ ምክንያቱም በጣም አነስተኛ በሆነ ገቢ የሚተዳደሩ በርካታ ኡራጋዊያን አሉና ›› በማለት መልሰዋል ፡፡ ምናለ ይቺን አባባል በየደረጃው ለሚገኘው የኛ ሀገር ትንሽና ትልቅ ስግብግብ አመራር ግልባጭ አድርገው ቢልኳት ? ለማንኛውም እነዚህን አማላይ ፈታኝ ምዕራፎች ለመዝጋት መቻል ምን ያህል ጀግና መሆንን ያሳብቃል ፡፡

ሙጂካ ለቢቢሲ ‹‹ የቁሳቁስ ሃብት ደስታን መግዛት አይችልም ፡፡ ብዙዎች ድሃው ፕሬዝዳንት እያሉ ይጠሩኛል ፤ እኔ ግን ድህነት አይሰማኝም ፡፡ ድሃ ሰዎች ህይወታቸውን በውድ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የሚያሳልፉና ዘወትር ብዙና ብዙ ለማግኘት ብቻ የሚሰሩት ናቸው ›› በማለት ገልጸዋል ፡፡

እንደ መግቢያችን ሁሉ ለመዝጊያችንም መቀርቀሪያ እንፈልግለት፡፡

ለጋስ መሪዎች መስዋትነት የሚከፍሉት ምክንያቱ ላይ ነው ፡፡ ድሃ ህዝቤን እንዴት ከችግር ላውጣው እንጂ እኔ እንዴት ልበልጽግ የሚል ሀሳብ አያስቀድሙም ፡፡ እንዴት የዴሞክራሲ ፣ ፍትህና ነጻነት ጥያቄውን ሙሉ ላድርግለት እንጂ ምን ዓይነት የፍርሃት ቆብና ቱታ ላልብሰው በማለት አይጨነቁም ፡፡ ለጋስ መሪዎች ለተቋማትም ሆነ ለሀገር እንደ ቃል አቀባይ ስለሚቆጠሩ የህዝቡን የመረዳት፣ የመቀበልና የመተግበር ስሜት መማረክ ይችላሉ ፡፡ ለጋስ መሪዎች ልዩ ክህሎትና ጥበብ ያላቸውን ሰራተኞች ልብና አእምሮ መቆጣጠር አያስቸግራቸውም  ፡፡ እናም ብዙዎች ከሚጠበቀው በላይ በራሳቸው ተነሳሽነት ለመስራት አያቅማሙም ፡፡ ለአንድ መሪ ትልቁ ፈተና ህዝባዊ ፍቅር የማግኘቱ ጉዳይ በመሆኑ ብዙ ሊሰራበት የተሰጠውን አእምሮ ሳይበርዝ እንደ ማዕድን መቆፈር አለበት ፡፡

‹‹ ምን ሊያገኝ  ? ›› አልክ

እንደ አልማዝ ውድና አጓጊ የሆነውን - ቅንነት
እንደ ወርቅ ልብ የሚያሞቀውን - ሩህሩህነት
እንደ ብረት የጠነከረን - ህዝባዊነት ፡፡


Sunday, March 10, 2013

‎የሰውየው ሀገር . . . የሰውየው ነገር . . .‎




ሰውየው ተይዘዋል ፡፡
ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ ነበሩ በየጋዜጣዊ መግለጫውና በፓርላማ ስብሰባ ላይ የሚያከናንቧቸው ፡፡ አተራማሹ ፣ ማፊያ፣ አሸባሪ ፣ ወሮበላ እረ ምን የማይሰጧቸው ስም ነበር ?
ዛሬ በህመም ተይዘው ‹‹ እረ ማን ይስደበኝ ? እረ ማን ይገስጸኝ ? ›› በማለት ትችቱንም ሆነ የቀደመውን የትግል ትዝታ ያንጎራጉራሉ ለማለት አይደለም ፡፡ በህመምና በጭንቀት ክበብ ውስጥ መገኘታቸው ፈጣን የምላስም ሆነ የተግባር ምላሻቸውን አደበዘዘው ለማለት እንጂ ፡፡

እንጂማ እሳቸውስ ለማን ይመለሱ ነበር ?!
የኢትዮጽያ ባለስልጣናት የጥቅም ገመዳቸውን መበጣጠስ ሲጀምሩ ባልታሰበ ፍጥነት አይደል ባድመን መያዣ ያደረጉት ፡፡ እየፈሩ በግልጽ ባይናገሩም በሆዳቸው ‹‹ የትልቋ እስር ቤት መሪ ! ›› እያሉ ሊያሽሟጥጡ በሚችሉ የአፍሪካ መሪዎች ላይ አጋጣሚን ሰበብ በማድረግ ከመዝለፍ መች ይቆጠባሉ ፡፡ ‹ የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ › እያለ የሚያጣጥላቸውን ተመድ ጽ/ቤቱ ድረስ በመሄድ ያልተገባ መልስ ሰጥተዋል ፡፡ የትግሉ ዘመን ወጣ ውረድ ትዝ ሲላቸው የመንን ፣ መዝናናት ሲፈልጉ ጅቡቲን ወረው እንካሰላንቲያ ለመጫወት መች ወደ ኃላ የሚሉ ነበሩ ፡፡

ዛሬ ግን በህመም ተፋዘዋል ፡፡
እንጂማ ምኑ የቆረጠው ነው የሚፈታተናቸው ?! ለዛውም የሀገራቸው ሰው ፤ ለዛውም በእፍኝ ታንክ የሚታገዙ በመቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ፡፡ የአምስት ሚሊዮን ህዝብ መሪ ቢሆኑም በ 200 ሺህ ወታደሮች የተዋቀረ ጦር ሰራዊት ባለቤት መሆናቸውን ይህ ነገር ፈላጊ ቡድን አያጣውም ፡፡ ደግሞ ምናለበት የደመወዝና የፋቲክ ጥያቄ ቢያነሳ ! የሀገሪቱን ማስታወቂያ ሚኒስቴር ከቦ ሁለት ህመም የሚጨምሩ ጥያቄዋችን ይለኩሳል እንዴ ?!  በርግጠኝነት በነዚህ ጥያቄዎች ከሚፈተኑ በቢጫ ወባ ቢያዙ ይመርጣሉ ፡፡ ደረታቸው ላይ የተቀረቀረው አንደኛው ጩቤ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚለው ነው ፡፡ አንገታቸውን አላዞር ያለው ሁለተኛው ጥያቄ የ 1997ቱ ህገ መንግስት ስራ ላይ ይዋል የሚል ነበር ፡፡

ሰውየው በነዚህ ጥያቄዎች አተነፋፈሳቸው ተዛብቷል ፡፡
ወይ ታሪክና ፖለቲካ አለማወቅ ! ይፈቱ ከተባሉ የፖለቲካ እስረኞች መካከል 11 ዱ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ ሲሆን ወደ እስር ቤት የተወረወሩት የሰውየውን ህልውና ሊያቆም የሚችለውን የ ‹‹ ፍትሃዊ ምርጫ ›› ጥያቄ በማንሳታቸው ነበር ፡፡ በ1997 የጸደቀው ህገ መንግስት ደግሞ ከኢትዮጽያ በሄደ ምርጥ የአወዳይ ጫት ውብ ሆኖ ከተፈጠረ በኃላ ምርቃናው ከጠፋ በኃላ የግምግማ ጅራፍ የጮኀበት እንደነበር ሀገር ያውቀዋል ፡፡ የፕሬስ ፣ የሃይማኖት ፣ የፖለቲካ በአጠቃላይ ለኤርትራዊያን የሰጠው መብት በእጅጉ እንደ ውብ ሴት የቆነጀ ነበር ፡፡ እና ይህችን ህገ መንግስት ማሽኮርመምና ፍቅር ማስያዝ ያለበት ወጪ ወራጁ ሁላ ነው ወይስ ሰላሳ ዓመት ቆስሎና ደምቶ እዚህ የደረሰው የሰውዬው ፓርቲ ? - መልሱ ፓርቲ የሚለው ይሆናል ፡፡ እና ፓርቲዎ ምን ወሰነች ? - መልሱ የሚከተለው ይሆናል ፡፡ ‹‹ ይህችን ውብ ህገ መንግስት ከማፈራረስ እንደተዋበች ትቆይና ቋሚ ሙዚየም ውስጥ በክብር ትቀመጥ ፡፡ ሁሉም አፈጣጠሯን ያድንቅ ፡፡ እሷን የማናገር ስልጣን ግን ለርዕሰ ብሄሩ ይሰጥ ›› ይህ ህግ እንዴት አለፈ ? - መልሱ በአክላሜሽን !!

ሰውየው ተዳክመዋል ፡፡
እንጂማ እንደ ሌሎች አፍሪካዊ ሀገሮች ‹‹ ተዋበች ›› የሚል ስያሜ ያገኘቸውን ህገ መንግስት ጥላሸት ለመቀባት የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ወታደሮችን በለመደው ፍጥነታቸው ዘለው ጉብ አይሉባቸውም ነበር ፡፡ ወታደሮቹ ጥያቄያቸውን በቴሌቪዥን ማስነገራቸው ብቻ ሳይሆን ለዚህ መ/ቤት ቁልፍ የሆነችውን የሰውየውን ሴት ልጅ ኤልሳን እንደ መያዣነት መጠቀማቸው የድፍረቱን ደረጃ ከፍም ባደረገው ነበር ፡፡

ወታደሮቹ ተልኳቸውን ፈጽመው ከተመለሱ በኃላ እንኳ የሰውየው ድምጽ የተሰማው ወሬው ከቆረፈደ በኃላ ነው ፡፡ ብዙና ዝርዝር ነገር እንደሚያወሩ ቢጠበቅም ‹‹ የከሰሩ ጠላቶች ናቸው ! ›› የምትል ብጣቂ ነገር ነው ወርወር ያደረጉት ፡፡ እነማን ናቸው ? ከጀርባቸው ማን አለ ? ፍላጎታቸው ምንድነው ? ሰውየው ይህን በስድብም ሆነ በንቀት ለመመለስ አቅም በማጣታቸው መልሱ እንጃ ሆኗል ፡፡  ልክ እንደ አሁኑ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራም ይሁን የማስተካከያ ጥያቄ በአንድ ወቅት ዓለም ስለ ሰውየው መሞት ይነጋገር ነበር ፡፡ አንዳንዶች በግላጭ በደስታ ጨፍረዋል ፣ አንዳንዶች በድብቅ የውስኪና ቢራ ብርጭቆ አጋጭተዋል ፡፡ ታዲያ ሰውየው እንደምንም በገመምተኛ አካል ቴሌቪዥን መስኮት ላይ ብቅ ብለው ‹‹ የታመሙት አሉባልታውን የሚነዙት ናቸው ! ›› በማለት ጠላቶቻቸውን ኩም አድርገዋል ፡፡ ጣታቸውንም ወደ አሜሪካና ኢትዮጽያ ቀስረዋል ፡፡ ዛሬ ግን ወታደሮቹን ባሰማራው አካል ላይ ለመደንፋት አልፈለጉም ወይም አልቻሉም ፡፡

እነሆ ሰውየው ! …
ስም - ኢሳያስ አፈወርቂ
የእናት ስም - አዳነች በርሄ
የትውልድ ዘመን - 1965 / እአአ /
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት - ልዑል መኮንን
ዩኒቨርስቲ - ለሁለት ዓመት የምህንድስና ትምህርት
ማስት - ሳባ ኃይሌ
ልጆች - አብርሃም ፣ ኤልሳ እና ብርሃኔ
የሚያበሳጫቸው ጉዳይ - የወያኔ ክህደት
ሃይማኖት - ኦርቶዶክስ

ደርግ በወደቀ ማግስት በኤርትራዊያን ‹‹ ጀግና ! ›› ተብለው ሲሞገሱ የቆዩት አቶ ኢሳያስ የተቻኮለ ቢሆንም በብዙዎችም ሞገስና ክብር አግኝተው እንደነበር ይታወቃል ፡፡ ውሳኔ ህዝብ ለመታዘብ የሄዱት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በራሳቸው መጽሀፍ ላይ ‹‹ የነጻነታቸው ቀን እኔ ፣ መለስና ኢሳያስ / በስሊፐር ጫማ / ከተማ ውስጥ ዞረናል ፡፡ በእውነት ትልቅ ነጻነት ነበር የተሰማኝ ፡፡ ሱቅ እየገባን ፣ ማታ ማታ እየዞርን አንድ ሁለት ቦታ መጠጥ እየተጎነጨን ተዝናንተናል ›› በማለት በተዘዋዋሪ የሰውየውን ዲሞክራትነት አስረድተዋል ፡፡ የአሜሪካ መንግስት የወደፊቱ የአፍሪካ ዴሞክራት መሪዎች በሚል በግልጽ ዕውቅና ከሰጣቸው አራት መሪዎች መካከል አንደኛው ኢሳያስ ነበሩ ፡፡ አቶ መለስም በደህናው ዘመን ‹‹ ከኢሳያስ ጋር አንድ ሰዓት ማሳለፍ አስር መጽሀፍ ከማንበብ በላይ ልበ ብሩህ ፣ አዋቂ እና ተጠቃሚ ያደርጋል ›› በማለት ታላቅነታቸውን መስክረዋል ፡፡

ዛሬ የቀድሞው ምስክርነት መገልበጡ ብቻ ሳይሆን ሚዛናዊነቱም ያልተመጣጠነ በመሆኑ የሰውየውን ሰብዓዊ ትከሻ እስከማጉበጥ ደርሷል ፡፡ ‹‹ ተዋበች ›› ላይ የሰፈረውን መርህ ከማስከበር ይልቅ የሀገር ደህንነትን ማረጋገጥ ይቀድማል የሚለው ፍልስፍናቸው እየጠለፋቸው ነው ፡፡ በተለይም የፖለቲካ ፣ የፕሬስ ፣ የሃይማኖት ነጻነቶችን መጨምደድና ‹‹ ሳዋን ›› የመለጠጡ አሰራር ያስከተለው ጦስ ሀገሪቱንና ራሳቸውን የመጨረሻ ጠርዝ ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል ፡፡ እሳቸው በደምና አጥንት የተገነባውን አጥሬን አትነቅንቁ ሲሉ ፣ ሌሎች በአጥሩ ታፍነናል ፣ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚፈጸመው በደልና ጭቆና አንገፍግፎናል በማለት ጀርባቸውን እያዞሩባቸው ይገኛሉ ፡፡ ታማኝ ይባል የነበረው ጦር ሰራዊታቸው እንኳ ዛሬ በእሳቸው መስመር ለመሰለፍ እያንገራገረ ነው ፡፡ በርግጥ ሰሞኑን ያልተጠበቀ ድፍረት ያሳዩ ውስን ወታደሮች አዲስ የተቃውሞ ምዕራፍ መክፈታቸው ካልሆነ በስተቀር የብዙሃኑን መለዮ ለባሽና ሲቪል ማህበረሰብ ስሜት ነው ያንጸባረቁት ፡፡

የሰውየው አዲሱ ጠላት ማነው ?
ኢሳያስ እአአ ህዳር 2012 የረጅም ግዜ ወታደራዊ አማካሪ የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል ፊሊጾስ ወልደ ዮሀንስ አስረዋል ፡፡ በቅርቡ አፍንጫቸው ስር ቀርቦ በጠመንጃ አፈሙዝ አፍንጫቸውን ያለፍርሃት የጎረጎረው ቡድን መሪ እኚህ ጄኔራል መሆናቸውን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ጽፈዋል ፡፡ እኚህ ጄኔራል ቀደም ባለው ግዜ በምዕራባዊው የኢትዮጽያና ሱዳን ድንበር አካባቢ አዛዥ ሆነው አገልግለዋል ፡፡ ከፍተኛ የውጊያ ልምድ ያላቸው ጄኔራሉ በወታደሩ ዘንድም ከፍተኛ የፖለቲካ ክብር አላቸው ነው የሚባለው ፡፡ ኢሳያስ ህዳር ወር ላይ ሲያስሯቸው በወታደሩ መካከል ክፍፍል እንደሚፈጠር ወይም የተቃውሞ የመገለጥ ምዕራፍ ሊጀመር እንደሚችል ስሌት ወስጥ አልገባም ነበር ፡፡ ጄኔራሉ ሲታሰሩ የተኳቸው ጄኔራል ተክላይ/ ማንጁስ ክፍላይ ይባላሉ ፡፡ እናም በቋፍ ላይ የሚገኙት ኢሳያስ ከሞቱ ወይም ጤናቸው የከፋ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ከታወቀ ፊሊጾስ የማንጁስን ተግባር ለመገደብ ሲሉ ከታማኝ ወታደሮቹ ጋር ይህን ስራ ሊመሩ ይችላሉ - እንደ ተንታኞች መላምት ፡፡ እንደ ብዙዎች እምነት በቦታው ላይ ጥቂት ወራት ያሳለፉት ማንጁስ የኢሳያስን ቦታ ሊሸፍኑ ይከብዳቸዋል ፡፡ ፊሊጾስ ቦታውን ከተረከቡ ግን በሀገሪቱ ጠንካራ ወታደራዊ ተቋም ይዘረጋል ፡፡

ሁለተኛው ግምት ያነጣጠረው ኮማንደር ሳላህ ኦስማን ላይ ነው ፡፡ እኚህ ሰው ከ1998- 2000 ከኢትዮጽያ ጋር በተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንደ ጀግና ይቆጠራሉ ፡፡ እንዴት ቢሉ በውጊያው ወቅት ደቡባዊ አሰብን ለቀው እንዲወጡ ቢታዘዙም ትዕዛዙን ባለመቀበል የኢትዮጽያን ጦር ወደ ኃላ እንዲያፈገፍግ አድርገዋልና ፡፡ እኚህ ሰው ሌላው የሚታወቁበት ጉዳይ ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና እንድትገባ ለመንግስታቸው ሀሳብ የሚያቀርቡ መሆናቸው ነው ፡፡
እነዚህ ሁለት ወታደሮች የሰውየው አዲሱ ጠላት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመት እንጂ ኢሳያስ በቁጭትም ሆነ በህመም ጥላ ስር ሆነው ጠላታቸው ላይ ማንባረቅ አልፈለጉም ፡፡ በመሆኑም አዲሱን ጠላት በግምት እንጂ በበቂ ማስረጃ ማረጋገጥ አልተቻለም ፡፡

የሰውየው ጅራፍ !
ኢሳያስ አፈወርቂ ‹ ጭር ሲል አልወድም ! › የሚለውን ኢትዮጽያዊ ዜማ ይወዳሉ እየተባሉ ይታማሉ ፡፡ የመን ያስጮሁት ጥይት ቀዝቀዝ ካለ ጅቡቲ ፣ የጅቡቲው መፋዘዝ ሲጀምር በሶማሌ ፣ የሶማሌው ቃናው መጎምዘዝ ሲጀምር በባድመ መስማት አለባቸው ይሏቸዋል - ስም አጥፊዎች ፡፡ ይህ ሁሉ ካልሆነ ደግሞ አስመራ ላይ እውነተኛ ጅራፍ ገምደው ያስጮሁታል አሉ ፡፡ ጅራፉ በጣም ካቆሰላቸው መካከል ሁለቱን የነጻነት ልጆች ፕሬስ እና ሃይማኖትን መጠቃቀስ ይቻላል ፡፡

ሀ . የፕሬስ ነጻነት

አንድ አይናማው የኤርትራ ፕሬስ ወደ ማየት የተሳነው የተቀየረው መስከረም 2001 ነበር ፡፡ ቀደም ብሎ 11 የሚደርሱ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በንቃት ሲሳተፍ በነበረ አንድ የግል ጋዜጣ ላይ መንግስት ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንደሚገባው የሚያስገነዝብ ጽሁፍ አወጡ ፡፡ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የሚታወቁት ኢሳያስ 11 ዱን ባለስልጣናትንና ደብዳቤውን ያተሙ 10 ጋዜጠኞችን ወህኒ ቤት ወረወሯቸው ፡፡

ከዚያ የግል ሚዲያ ከህትመት ዉጪ እንዲሆኑ ተደረገ ፡፡ ማንኛውም የህትመት ዉጤት ከመታተሙ በፊት በመንግስት የጹሁፍ ዘበኞች እንዲመረመር ታዘዘ ፡፡ ጋዜጠኞች በሚደረግባቸው ወከባና የማስፈራራት ተግባር ከሀገር መሰደድ አበዙ ፡፡ ዓለማቀፉ ፕሬስ ፋውንዴሽን በ 2012 ባወጣው መረጃ መሰረት ኢሳያስ 30 የሚደርሱ ጋዜጠኞችን አስረው በመጥፎ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ አድርገዋቸዋል ፡፡ ‹‹ ማንኛውንም የውጭ ሚዲያ መረጃ እንዲያገኝ አንፈቅድም ›› የሚሉት ኢሳያስ ሀገራቸው ፍቃድ የምትሰጠው ስለ ሀገሪቱ መልካም ገጽታ ለማውራት ፍቃደኛ ለሚሆኑት ብቻ መሆኑን በአንድ ወቅት ተናግረዋል ፡፡ በአንዳንድ የተመረጡ ካፌዎች ውስጥ ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ዜጎች ጥብቅ ክትትል ይደረግባቸዋል ፡፡ በቅርቡ የወጣው የፕሬስ ነጻነት ኢንዴክስም በኤርትራ የመናገር ፣ የመጻፍና የመሰብሰብ መብቶች የተከለከሉ በመሆናቸው የመጨረሻውን 179 ኛ ደረጃ ለማግኝት ግድ ብሏታል ፡፡ ይህም ዜጎች ምን ያህል በአፈና እየተሰቃዩ መሆኑን ያመለክታል ፡፡

ለ . የሃይማኖት ነጻነት

ቁስለኛው ሃይማኖት በኤርትራ ህዝብ ሲመነዘር 40 ከመቶው ክርስትያን 60 ከመቶው ደግሞ የሱኒ ሙስሊሞች ሆኖ ይገኛል ፡፡ ከክርስትያኑ ውስጥ 24 ከመቶው ኦርቶዶክስ ፣ 10 ከመቶ የሮማን ካቶሊክ ፣ 4 ከመቶው ፕሮቴስታንትና ጆባ ሲሆኑ 2 ከመቶው እምነት የለሽ ነው ፡፡ መንግስት ዕውቅና ሰጥቶ የመዘገባቸው ኦርቶዶክስ ፣ ሉተራን ፣ ሱኒ ሙስሊም እና ሮማ ካቶሊክ ናቸው ፡፡
የኢሳያስ መንግስት ጅራፍ ግን ዕውቅና በሌላቸውም ሆነ ባላቸው ጀርባ ላይ እያረፈ በመሆኑ 3 ሺህ የሚደርሱ ክርስትያኖች እስር ቤቶችን አጣበዋል ፡፡ ብዙዎች ወደ እስር ቤት የተወረወሩት ደግሞ በብሄራዊ ውትድርና መሳተፍ ባለመፈለጋቸው ነው ፡፡ በተለይም እምነታቸው ውትድርናን የማይፈቅድላቸው ጆባዎች ዋነኛው የጥቃቱ ዒላማ ሆነዋል ፡፡

ኢሳያስ በ 1994 ባወጡት አዋጅ ለጆባ እምነት ተከታዮች የዜግነት ፍቃድ አይሰጥም ፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ከሆኑ ከስራ ይባረራሉ፣ የንግድ ፈቃዳቸው ይቀማል ፣ ከመንግስት ቤት እንዲባረሩ ይደረጋል ፡፡ በርግጥ ሰውየው ጥርሱን የነከሰባቸው ኤርትራን ለማሰገንጠል ድምጸ ውሳኔ ያዘጋጁ ግዜ ነበር ፡፡ ያኔ እነሱ ከፓለቲካ ተሳትፎ ዉጪ ነን ቢሉም ‹ ማን በሞተለት ሀገር ላይ ማን ገለልተኛ ይሆናል ! › በሚል ስሌት እንዲገረፉ ፣ እንዲገለሉና እንዲታሰሩ ሀገራዊ አድማ አስደርገውባቸዋል ፡፡
የመንግስትን ጣልቃ ገብነት የኮነኑት ፓትርያክ አቡነ አንቶኒዮስ ከቦታቸው ተነስተው የመንግስት ሹመኛ ጉብ ብሏል ፡፡ ከ 1700 በላይ የሚሆኑ ካህናት ከቤተክርስትያን አገልግሎት እንዲገለሉ ተደርገዋል ፡፡ የሃይማኖት እስረኞች ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ወይም እንዲተው ባዶ እግራቸውን በሹል ድንጋይና በእሾህ ላይ በቀን ለአንድ ሰዓት እንዲራመዱ ይደረጋል ፡፡

የሰውየው ካምፕ

ሳዋ ሀምሌ 1994 ስራ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ማለትም ግንቦት ወር ላይ ኢሳያስ የብሄራዊ ውትድርናን ጠቀሜታ አስመልክቶ ሶስት መሰረታዊ ነጥቦችን አስቀመጡ ፡፡
. ሀገሪቱን ከጥቃት ለመከላከልና አንድነት ለመፍጠር
. ወጣቱ ክፍል ለስራ ያለውን አዎንታዊ ስነልቦና ለማጠናከር
. የሻዕቢያን የ 30 ዓመት ልምድ ፣ ማንነትና ውርስ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ
በዚሁ መሰረት በአዋጅ ቁጥር 82/1995 አንቀጽ 8 መሰረት ሁሉም ዕድሜው ከ18 – 40 ዓመት የሆነው ዜጋ ብብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ውስጥ ለ18 ወራት ማገልገል ግድ ይለዋል ፡፡

ኢሳያስ የሀገሪቱ ዜጎች በተለይም ወጣቱ በአመርቂ ሁኔታ እየተሳተፈ አለመሆኑን በግምግማ ሲያረጋግጡ ‹‹ ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ያልገባ ተማሪ የከፍተኛ ትምህርቱን መከታተል አይችልም ›› የሚል ህግ አወጡ፡፡ በመሆኑም የሁለተኛ ደረጃ የመጨረሻ ትምህርት በሳዋ እንዲሰጥ ተደረገ ፡፡ ተማሪው ለግዜው በዚህ ዘዴ ተጠፍንጎ ካምፑን ቢያጣብብም በቦታው የነበረው ኢ - ሰብዓዊ አያያዝ ፣ እስራትና ግርፊያ የሰፋ ጥላቻና ስደት እንዲባባስ አድርጓል ፡፡ በተለይም ወጣት ሴቶች በወታደሮች ፣ አሰልጣኞችና አዛዦች መደፈር እጣ ፈንታቸው ሆነ ፡፡ በዚህም የተነሳ ሳዋ ‹‹ የወሲብ ካምፕ ›› የሚል ስያሜ እስከማግኘት ደረሰ ፡፡

ይህም ሴቶች ከሳዋ ለመዳን ሌሎች ያልተገቡ ዘዴዎችን እስከመፍጠር አደረሳቸው ፡፡ እነዚህ ህሊናን የሚነኩ ዘዴዎች ሆን ብሎ ማርገዝ ፣ ለምኖም ቢሆን ማግባት እና ትምህርትን ከ 10ኛ ና 11 ኛ ክፍል ማቋረጥ ናቸው ፡፡ በዚህም ምክንያት በሳዋ የሴቶች ቁጥር ከወንዶች በሶስት እጥፍ እስከማነስ ደርሷል ፡፡

በአጠቃላይ እኔና ሀገሬን በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍና ተጽዕኖ ፈጣሪ ያደርጋል ብለው የገነቡት ሳዋ በሰልጣኙም ሆነ ተራውን በሚጠብቀው ትውልድ አስፈሪ ምስል በመፍጠሩ የታሰበውን ግብ ሊመታ አልቻለም ፡፡ ባለፉት 13 ዓመታት ከአንድ ሚሊየን ዜጎች በላይ ተሰደዋል ፡፡ ሳዋን የኢሳያስ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የፓርቲ አባላት ከፍተኛ የገቢ ማሰባሰቢያ ምንጭ እያደረጉት ይገኛሉ ፡፡ ከሀገር ውስጥ ወደ ሱዳን ፣ ግብጽና እስራኤል የሚሰደዱ ዜጎችን ከድንበር ጥበቃዎች ለማሳለፍ በሚል ከ 3 – 20 ሺህ ዶላር ይቀበላሉ ፡፡

የሰውየው መልኮች

 
የኢትዮጽያ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከአልጀዚራ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ‹‹ የኢሳያስ መልካም ፍቃድ ካለ አስመራ ድረስ ሄጄ በሰላም ጉዳይ እደራደራለሁ ›› ብለው ነበር ፡፡ አንዳንዶች ጥያቄው የጠ/ሚኒስትሩን ቀናነት ያሳያል ሲሉ ሌሎች ሀሳቡን ለማቅረብ የመቻኮላቸው ፣ ጥያቄው ከጋዜጠኛው ሳይመጣ ነገር አስታከው መመለሳቸውን አልወደደውም ነበር ፡፡ 

ሰውየውም እንዲህ አሉ  ‹‹ ኤርትራ ስልጣን ላይ ካሉ ግለሰቦች መቀያየር ጋር የምታያይዘው አንዳችም ነገር አይኖርም … ››
ይህን የመሰለ አስገራሚ ምላሽ እንደሚመጣ በአንዳንዶች መገመቱ ትክክል ነበር ፡፡ ለምን ከተባለ የኢሳያስን ተቃራኒ መልኮች በልምድ ከማየት ፡፡ ሰውየው ተቃራኒ ጉዳዮችን በማከናወን አቶ መለስን ጨምሮ አፍሪካ ህብረትን ፣ ተመድንና አሜሪካንን ሲያበሽቁ መኖራቸው  ይታወቃል ፡፡ አቶ ሃይለማርያም የኢሳያስ ምለሽ ከተሰማ በኃላ በፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ የሰውየውን አተራማሽነት አስረግጠው ተናግረዋል ፤ አላርፍ ካለ ደግሞ ተመጣጣኝ ቅጣት እንደሚጠብቀው በአጽንኦት አስገንዝበዋል ፡፡ መቼም አቶ ሃይለማርያም ስለ ሰላም በሰበኩ ማግስት ይህን የመሰለ ሃይለ ቃል ለመተንፈስ የተገደዱት ዝም ብሎ አይደለም - ተረኛው የኢሳያስ በሻቂ በመሆናቸው እንጂ ፡፡

አቶ ኢሳያስ ያልተጠበቁ ወይም የማይገቡ ንግግሮችን ብቻ ሳይሆን ተግባራትንም በማከናወን ይታወቃሉ ፡፡ እንደሚታወቀው ኢሳያስ በ2008  ከኢራን ጋር ሁነኛ ስምምነት ተፈራርመዋል ፡፡ በስምምነቱ መሰረት ኢራን በአሰብ ወታደራዊ ተቋም በመገንባት የነዳጅ ማደያውን ስትጠብቅ ኤርትራም ለዚህ ልግስናዋ ገንዘብና ወታደራዊ መሳሪያዎችን ታገኛለች ፡፡ ይችው ሀገር የኢራንን የኒውክለር ፕሮግራም በመደገፏ ብቻ 35 ሚሊዮን ዶላር ተሸልማለች ፡፡ በሌላ በኩል እስራኤል በዳህላክ ደሴት ፣ በምጽዋና በአምባይሶራ አካባቢ የባህር ኃይል ተቋም ለመገንባት ያቀረበቸውን ጥያቄም ሰውየው በደስታ ተቀብለዋል ፡፡ ኢራንና እስራኤል የማይታረቅ የነገር ኮሮዋጆችን ለዘመናት የተሸከሙ ባላንጣዎች ናቸው ፡፡ ታዲያ ኢሳያስ ለሁለቱ ተቃራኒ ሀገሮች በአንድ አካባቢ የስራ ፍቃድ ሰጥተው የኤደን ባህረ ሰላጤ ሌላ የፍጥጫና የግጭት ማዕከል እንዲሆን ለምን ፈለጉ ? የቁርጥ ቀን አጋር ለሆነቸው ኢራን ፍላጎት ለምን ተገዢ አልሆኑም  ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም ፡፡

የእስራኤል ዓላማ የቀይ ባህር አካባቢንና የኢራንን እንቅስቃሴ በመሰለል መረጃ ማሰባሰብ ነው ፡፡ የኢሳያስ ግብ ግን ብዙ ነው ፡፡ የእስራኤልን ጓደኛነት በመጠቀም የአሜሪካንን ሆድ ማባባት ይፈልጋሉ ፡፡ ለእደሳ ፡፡ ብዙ ግዜ ከኢትዮጽያ በሚወሰድባቸው የአየር ኃይል ብልጫ ይንገበገባሉና አየር ኃይላቸውና ዘመናዊና ብድር መላሽ ማድረጊያው ግዜ አሁን መሆኑን ያልማሉ ፡፡ ኤርትራን ወደ እናት ሀገሯ እንመልሳለን በማለት ፖሊሲ ቀርጸው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ከእንግዲህ የሚጋፉት ከእነማን ጋር መሆኑን በእግረ መንገድ እንዲያውቁትም ይፈልጋሉ ፡፡ ኢሳያስ ይህ ዓላማቸው እንዲሳካላቸው እንጂ የባንጣዎቹ መፋጠጥ አጀንዳቸው አይሆንም ፡፡ ምክንያቱም ነብር መልኩን አይቀይርምና …

የሰውየው መጨረሻ
ከተራራ የሚገዝፉ ሀሳቦችና ውጥኖች ቢኖራቸውም ቀስፈው የያዟቸው ህመምና ጭንቀት አሜኬላ መሆናቸው አይቀርም ፡፡ አድልዋና መገለል ያብቃ በሚባልበት ዘመን አሸባሪና አተራማሽ ተብለው በተመድ በተጣለባቸው እገዳ ምክንያት ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ተገለዋል ፡፡ ይህም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እየቦረቦረው ይገኛል ፡፡ እገዳው እንዲነሳላቸው ቢጠይቁም ትኩረት የሰጣቸው ወዳጅ አላገኙም ፡፡ 30 ዓመት ደሙን አፍሶ ነጻነት ያስገኘለት ህዝብ የጀግንነት ውርሱን በ ‹‹ ሳዋ ›› አማካኝነት በጸጋ መቀበል ሲገባው ክህደት መፈጸሙ መጠቃታቸውን ያንረዋል ፡፡ በፕሬስና ነጻነት አፈና ፣ በአምባገነንነት የመጨረሻዋ ሀገር ኤርትራ ነች እያሉ ዓመታዊ ሰንጠረዥ የሚለጥፉ ክፍሎች ተግባር ያንገበግባቸዋል ፡፡

ሰውየው ተወጥረው ተይዘዋል ፡፡
በአንድ በኩል ለስለላ በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሪ / Remittance man / በመላክ ተሳትፎ እንዲያበረክቱ አውሮፓና አሜሪካ ከተላኩ ወገኖች ገሚሱ ተልዕኳቸውን ዘንግተው በየአደባባዩና በየኤምባሲው ‹‹ ኢሳያስ ይውደም ! ›› የሚል መፈክር አሰሚ መሆናቸው ሆድ አስብሷቸዋል ፡፡

ያልታገሉበትን ስልጣን ለመቀራመት በየሀገሩ ‹‹ ተቃዋሚ ›› ብለው ራሳቸውን ያደራጁ ማፈሪያ ዜጎች ተግባር ሳያንስ የሚያምንባቸው ጦር ሰራዊት መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሴራ መጎንጎን ደረጃ መድረሱ ጩህ ጩህ ያሰኛቸዋል ፡፡
የነዚህ ሁሉ ድምር ዉጤት የደም ብዛትን ያፋጥናል ፡፡ ውጥረትን ያንራል ፡፡ የአእምሮ ሽቦዎችን ያላላል ፡፡ ፍርሃትና ጥርጣሬን ያነግሳል ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ሰውየው እንደ ሀገራችን ድሃ ጎጆ ሺህ ቦታ ላይ ተሰነጣጥቀዋል ፡፡ እናም የቱ ተይዞ የቱ ይለሰናል ? አንዱን ስንጥቅ ሲደፍኑ በመድረቅ ላይ ያለው ይንጣጣል ፡፡ በመሆኑም ነባሩ ህመም ሊቀለበስ ወደሚችል ጤናማ አካልና አስተሳሰብ የመምጣቱ ዕድል የመነመነ መሆኑን ይጠቁማል ፡፡

ሌላኛው መጨረሻ ‹‹ የተነቃነቀ ጥርስ መውለቁ አይቀርም ! ›› የሚለውን ነባራዊ እውነት ከማክበር የሚነሳ ነው ፡፡ የጭቆናና የግፍ ጽዋ ሲፈስ ደካሞች ጠንካራ ይሆናሉ ፡፡ እዚህና እዚያ የወደቀው የደካሞች ድር እያበረ አስቸጋሪውን ተኩላ ለማሰር ይበቃል ፡፡ ሰውየው ምናልባት የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማቆም የሚችሉት ህዝባዊውንና አዲስ ሀሳቦችን ይዘው ቢያንስ 270 ዲግሪ መዞር ከቻሉ ነው ፡፡ ይህ እውነት ደግሞ ለአምባገነኖች ሰርቶ እንደማያውቅ ከልምድ እናውቃለን ፡፡ እናስ ? እናማ የሰውየውን አጓጉል መጨረሻ ለመመልከት የግድ ቴሌስኮፕ የማያስፈልግበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ፡፡
ክፍሉ ሁሴን የተባሉ ጸሀፊ ‹‹ በጎ ምኞት ለወዲ አፈወርቅ  ›› በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ግጥም እንደ ማጠቃለያ ሳይሆን እንደ አስደማሚ ምርቃት  በመቁጠር ርዕሰ ጉዳዬን ላጠናቅ

የማይቀረው የኢሳያስ አፈወርቂ ሞት
በምን ይሆን በጉበት ወይስ በጥይት
በእናቴ ወገን የሆኑት
መነኩሴው አያቴ እንደነገሩኝ ጥንት
ምን ቢሆን ሃጢያተኛ
እንደ ዳቢሎስ ከዳተኛ
ይሰረይለታል አሉ
የሰራው ግፍ በሙሉ
በሰው እጅ ከጠፋ ነፍሱ ፡፡
እንዲህ ከሆነ ነገሩ
በሰማይ ቤት የቅጣት ድልድሉ
ይንቀልቀል ዘንድ ዘላለም በእቶን እሳት
ሰበበኛ በሆነው ጉበቱ ምክንያት ፡፡


ማስታወሻ፡- ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 147 ላይ የወጣ ፅሑፍ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡ 

Friday, March 8, 2013

‎ደርቢው ከአጓጊ ምዕራፍ ደርሷል - THE BIG THREE



ለግማሽ ፍጻሜ የደረሱት ሶስቱ የአዲስ አበባ ክለቦች ውድድር ተጠናክሮ ቀጥሏል ፡፡ በርካታ የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን በከፍተኛ ውጤት በማሸነፍ ለጠንካራ ፉክክር የደረሱትን ቴሌ፣ ውሃና ፍሳሽ እንዲሁም መብራት ኃይል ብዙዎች ‹‹ የማይበገሩ የከተማው ደርቢዎች ›› እያሉ በመጥራት ላይ ይገኛሉ ፡፡

በክለቦች ዙሪያ ሰፊ ጥናት ያደረጉት ሙያተኞች ግን ከላይ የተጠቀሰውን ስያሜ ስሜታዊ በማለት ‹‹ The big three ›› ወይም ሶስቱ ትላልቆች በሚል ሀቀኛ ስያሜ እንዲጠሩ እያሳሰቡ ናቸው ፡፡ ለዚህ ስያሜ መሰረት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ለመንግስት ትልቅና የማይነጥፍ የገቢ ምንጭ መፍጠራቸው ፣ ለግል ባለሀብት ለመስጠት የማይታሰቡ መሆናቸው ፣ አንዱ በጉንፋን ሲጠቃ ሁሉም ጋ ቀኪያም ሳል መመዝገቡ ፣ ለህዝብ የእርካታ ወይን ብቻ ሳይሆን የምሬት አውጥ መፍጠር የሚችሉ ንጥረ ነገሮች መሆናቸው እንደ ጥቂት አብነት ሊነሳ ይችላል ፡፡

የዓመቱን ሻምፒዮናነት ክብር ለመቀዳጀት ሶስቱም ቡድኖች በደርሶ መልስ የርስ በርስ ግጥሚያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ፡፡ በቡድኖቹ መካከል ያለው ተቀራራቢ ብቃት ዋንጫው ወዴት ያመራል የሚለውን ህዝባዊ ጥያቄ ምላሽ አልባ እንዲሆን አድርጎታል ፡፡

1 .

አንዳንድ የመብራትና ውሃፍሳሽ  ደጋፊዎች ቴሌን በመፎከርና ፕሮግራሞችን ስፖንሰር በማድረግ አንደኛ እየሆነ ነው ይሉታል ፡፡ ደንበኞቼን 18 ሚሊየን አድርሻለሁ ባለ ማግስት 18 ሺህ የችግር ፖስት ካርዶችን ያሳትማል ባይ ናቸው ፡፡ ለምሳሌ ሁለት ሰዎች ጨዋነቱን ለመፈተን ሆን ብለው አጠገብ ለአጠገብ ሲደዋወሉ ‹‹ ደንበኛዎ በአካባቢው የለም ›› የሚል አይን ያወጣ ዉሸት ያሰማል ፡፡ ከፈለገ የመቶ ብር  ካርድ መሙላትዎ እየታወቀ ‹‹ ያለዎት ቀሪ ገንዘብ አነስተኛ ነው ›› በማለት እንዲያፍሩበት መንገድ ይከፍታል ይሉታል ፡፡


ስራን በጥራት ከመስራት ይልቅ መቶ ምጣድ አሙቆ እንጎቻ ለመጋገር ይንደፋደፋልም ተብሏል ፡፡ ሰዎችን በአግባቡ ማገናኘቱን ሳያረጋግጥ የሞባይል ቀፎ ሲቸረችር ይገኛል ፡፡ ትችትና ሮሮ ሲበዛበት ደንበኞችን ለማስተንፈስ አንዳንድ ‹ ቲፖችን › ያበረክታል ፡፡ ከነዚህ መካከል ካርድ ሲሞላ የ 3፣ 10 ፣ እና 15 ደቂቃዎች መመረቅ አንደኛው ነው ፡፡ የአራዳ ልጆች ይህችን ነቄ የተባለባት ማለዘቢያ ትቶ ጠንካራ ስራ ቢሰራ ይሻለዋል እያሉ ይገኛሉ ፡፡

ያም ሆነ ይህ በአንዱ አካባቢ ጥሩ እየተሰማ ሌላው ዘንድ ጤናማ ግንኙነት መፍጠር ያልቻለው ቴሌ ወደፊት የመደናቆሩን ሂደት ከወረዳ አቀፍ አውርዶ ወደ ቤት ለቤት እንዳያሸጋግረው ተሰግቷል ፡፡ በዚህ አካሄዱም የወደፊት ኢትዮጽያን ማገናኘት የተባለውን መሪ ቃል ለሚገባቸው ሸጦ ‹‹ እረ አይሰማም ፤ ይቆራረጣል ! ›› የተሰኘውን ሞዴል ስራ ላይ እንዳያውለው ተፈርቷል ፡፡
2 .

ህዝቡን ክረምት ላይ የፈረቃ እሸት ማስገመጥ ያስለመደው መብራት ኃይል ዘንድሮ ምርቱን ከወዲሁ በስፋት ገበያ ላይ ማዋል ጀምሯል ፡፡ ሰፊውን የሀገሪቱ ግዛት ያለ ስስት ማጥቆሩን ተያይዞታል ፡፡ የነዋሪውን ተስፋ ለማሳደግ ለአፍታ ብልጭ ብሎ ወዲያው ድርግም የማለቱን አሰራር ተክኖበታል ፡፡ እንደ ቴሌና ውሃና ፍሳሽ ደጋፊዎች አስተያየት ከሆነ በዚህ የብልጭ ድርግም ስልቱ በተለይም ቴሌቪዠናቸውን ያላስመዘገቡና ግብር ያልከፈሉ ነዋሪዎችን ንብረት ኃይል በማብዛት ማፈንዳቱን ይቀጥላል ፡፡ መብራት ኃይል ስለ ቴሌቪዥን ግብር ምናገባው ? ለሚሉ አናዳጅ ጥያቄዎች የመ/ቤቱ ምላሽ ‹ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እንዴት ተጣጥሞ መስራት እንደሚቻል ለማሳየት ነው › የሚል ሊሆን እንደሚችል ነው የተገመተው ፡፡


የኢቲቪ ነገር ከተነሳ የተሻለ ትኩረት ያገኙት መዝናኛና ድራማ ፕሮግራሞች ሲተላለፉ ኃይል እያጠፋ ማበሳጨቱን እንደ ዋና የስራ ግብ ጋር አድርጎ በዕቅዱ ላይ ሳያስቀምጥ አይቀርም ፡፡ ይህ ደግሞ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እንዴት ሆድና ጀርባ መሆን እንደሚቻል ማስተማሪያ መሆኑ ነው ፡፡ ይህ ድርጊት እየተከናወነ የሚገኘው ደግሞ ሀገሪቱ ኃይል ለውጭ መሸጥ በጀመረችበት ግዜ መሆኑ ነው ፡፡ በዚሁ መሰረት የመ/ቤቱ መሪ ቃል ‹‹ ለውጭ አልጋ ለውስጥ ቀጋ ›› እንዳይሆን ተሰግቷል ፡፡

3 .

በውሃና ፍሳሽ መ/ቤት ሽፋን የሚያገኘው የከተማው ነዋሪ ከ50 ከመቶ በታች ነው ፡፡ መ/ቤቱ በመጪው ሶስት ዓመት ውስጥ ሽፋኑን መቶ ፐርሰንት እንደሚያደርሰው ደጋግሞ ተናግሯል ፡፡ እንግዲህ ቢጫውን ጀሪካን ይዞ በየሰፈሩ የሚንጦለጦለው ህዝብ ቁጥር አብላጫ አለው ማለት ነው ፡፡ እውነት ለመናገር ከታክሲና ዳቦ ቤት ሰልፍ ይልቅ የቢጫ ጀሪካን ሰልፍ ውበት አለው ፡፡ በጩኀት ያልደነቆረና ብዙ ግዜ የመበተን አደጋ የሚያጋጥመው አይደለም ፡፡ ይህም አባ ቦኖ የተባለውን ውሃና ፍሳሽ የሚያኮራው ይመስላል ፡፡ ‹ ይህን ሁሉ ህዝብ ጠጥቶ እንዲያገሳና እንዲሸና የማደርገው እኔ ነኝ › እንዲል ፡፡

ምናልባት ኮታው 100 ፐርሰንት እስኪደርስ ውሃና ፍሳሽ የሚጎለው ነገር ቢጫውን ሰልፍ ህብረ ብሄራዊ የማድረግ ጉዳይ ነው ፡፡ አንድ ሃይማኖት አንድ ህዝብ የሚባለው መርህ እንደማያዋጣ የመነገሩን ያህል በቢጫው ቀለም ብቻ ድምቀት መፍጠር አይቻልም ፡፡ በዚህም ምክንያት ይላሉ የቴሌና መብራት ደጋፊዎች መ/ቤቱ አረንጓዴና ቀይ ጄሪካኖች ሰልፍ ውስጥ ገብተው ባንዲራ እንዲፈጥሩ እያለመ ነው ፡፡


ውሃ እንደ ቴሌ በጆሮ ፣ እንደ መብራት በአይን የሚገባ አይደለም ፡፡ በአፍ እንጂ ፡፡ እና ጥራት ባጠረው ቁጥር በርካቶችን ላይ ታች ማሯሯጡና ለአጓጉል ሁኔታ መዳረጉ ግድ ነው ፡፡ ሰሞኑን ይህን እውነት የዘነጋው ውሃና ፍሳሽ የከተማውን የቧንቧ ውሃ እንደ ጠላ አደፍርሶ በየቤታችን ልኮታል ፡፡ ጉሽ ጠላ ሊሆን የቀረው ከአፍ የሚተፋ ስብርባሪ እንጨቶችና ገለባዎች ብቻ አለመኖራቸው ነበር ፡፡ ነገሩ የተገለጠላቸው የአራዳ ልጆች ግን ውሃና ፍሳሽ ‹‹ መውደድ ›› እና ‹‹ ቀሪቦ ›› ማዘጋጀት ጀምሯል እያሉ ነው ፡፡ ለማንኛውም ውሃና ፍሳሽ ገና ክረምት ሳይገባ ክረምትን የሚያስታውስ ሆረር ውሃ በስፋት ማቅረቡን እንዳይቀጥል አስጨንቋል ፡፡

የደጋፊዎች እንካሰላንቲያና ተፎካካሪዎቹ ወደፊት በስህተትም ሆነ በድፍረት ሊሄዱበት የሚችለው መንገድ የስጋት ቀጠና ውስጥ ይከታል ፡፡ እና ይህ ጠንካራ ዝግጅትና ትንቅንቅ ማንን ወደ አሸናፊነት ማማ ያደርስ ይሆን ?