Wednesday, August 16, 2017

የኛ ሰፈር ቡሄ ባለ ማርሽ ነበር

ፎቶ ሸገር ብሎግ
ገና ሀምሌ ሲገባደድ ነው የቡሄ መነቃቃቶች የሚፈጠሩት ፡፡ ሂሳብ ላይ ከፍ ያለ ክፍያ እንዲደርሰን በማሰብ ቡድኑን በስድስት ቢበዛ በስምንት አባላት እናዋቅረዋለን ፡፡ ከስብስብ ምስረታ ቀጥሎ የሚመጣው የዱላ ዝግጅት ነው ፡፡ ዱላ ለመቁረጥ የምናመራው ‹‹ ዝንጀሮ ገደል ›› ወደተባለው አካባቢ ነው ፡፡ ዛሬ አካባቢውን  መኖሪያ ቤቶችና የድንጋይ ካባ ተቋማት ከበውት አንድም ዛፍ አይገኝም ፡፡  ዱላው ተቆርጦ ከደረቀ በኃላ ቆርኪ እየጠፈጠፍን ‹‹ ክሽክሽ ›› እንሰራለን - ማድመቂያ ፡፡

የማታ ማደሪያ መምረጥም  ዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ የሚካተት ነው ፡፡ ቤቱን ስንመርጥ የቤቱን  ስፋትና የወላጆችን  ባህሪ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ፡፡ ምክንያቱም ማታ ከመተኛት ይልቅ መተራረብና መሳሳቅ ስለሚበዛ ‹‹ ቁጫጭ ሁላ ! ዝም ብለህ አተኛም ! ›› ብሎ የሚያስፈራራንን አባወራ እንዲኖር አንፈልግምና ፡፡ ዳቦና ገንዘብ ያዥም ከወዲሁ ይመረጣል ፡፡ ዶቦ ያዥነትን እንደ ሸክም ፣ ገንዘብ ሰብሳቢነትን  እንደ ስልጣን ስለሚመነዘር ምርጫው ተቃራኒ ገጽታዋችን ማስተናገዱ ግድ ነው  ፡፡

ዛሬ ላይ ሆኜ  ጭፈራችንን ስፈትሸው የድራማ ስልት እንደነበረው ይሰማኛል ፡፡ ያልደከመ ጉልበታችንን  አስቀድመን የምንጠቀመው በሀብታሞች ቤቶች ላይ ነበር ፡፡

‹‹ መጣንኖሎት በዓመቱ  እንዴት ሰነበቱ / 2 ግዜ /
ክፈት በለው በሩን - የጌታዬን / 2 ግዜ /

በሩ የብረትም ሆነ የቆርቆሮ እየጨፈርን በዱላችን እንደበድበዋለን - ስሙን ማለታችን ነው ፡፡ አንዳንድ ተንኮለኛ ደግሞ መጥሪያውን ሊያስጮኀው ይችላል ፡፡ አሁን ውሾች ካሉ እንደ ጉድ ይጮሃሉ ፡፡ ክፉ ጥበቃ ካለም እንደ ውሾቹ እየጮኀ መጥቶ ከአቅማችን በላይ የሆነ ስድብ ያሸክመናል ፡፡ ‹‹ መናጢ የድሃ ልጅ ! በር ስበር ተብለህ ነው የተላከው ?  መጥሪያው ቢበላሽ አባትህ መክፈል እንደማይችል አጥተኀው ነው ፡፡ ሂድ ጥፋ ከዚህ ! ሰበበኛ ሁላ ! ››  ቆሌያችን እንደ ውሻ ጭራ በፍርሃት ይጣበቃል። ደግነቱ የዚህ ተቃራኒ አለመጥፋቱ  ፡፡ አዝማሚያው ደህና መሆኑን ካረጋገጥን  አሁን አንደኛ ማርሽ እናስገባለን ፡፡
 « … የኔማ ጋሼ
  ሆ.. !
  የተኮሱበት
  ስፍራው ጎድጉዶ
  ሆ.. !
  ውሃ ሞላበት
  እንኳን ሰውና
  ሆ.. !
  ወፍ አይዞርበት !
 እያልን እስከታች እንቀጥላለን ፡፡ ብዙ ካስለፈለፉንና ‹ ተወው ጮሆ ጮሆ ይሄዳል › እያሉ የሚያስቡ መስሎ ከተሰማን የጭፈራችን መልዕክት ይቀየራል ፡፡ ሁለተኛ ማርሽ እናስገባለን ማለት ነው ፡፡

‹‹ ላስቲክ ተቀብሮ አይበሰብስም
 አንዴ መጥተናል አንመለስም ::
 አባባ ተነሱ ኪስዋትን ዳብሱ !! ›› በማለት  በአንድ በኩል ጠንካራ መሆናችንን እያሳየን በሌላ በኩል ትዕዛዝ ብጤ እናስተላልፋለን ፡፡ መቼም አንዳንድ ሰው ግድ ስለሌለው ወይም ማስለፍለፍ ስለሚወድ ድምጹን ያጠፋል ፡፡ አሁን ገሚሱ እንሂድ ሲል ሌላው በቀላሉ አንለቅም በማለት ይከራከራል ። ብዙ ግዜ እነዚህን አስተያየቶች የሚያስታርቁ ሀሳቦች ያሉት ይመስለኛል  - ቡሄ ፡፡ አስታራቂው ሀሳብ የጨፋሪውን መዳከም የሚጠቁም ይምሰል እንጂ በንዴትና በምሬት ነው የሚገለጸው ፡፡ እናም  ንዴታችንን ለማፍጠን ሶስተኛ ማርሽ  እንጠቀማለን ::

‹‹ እረ በቃ በቃ
  ጉሮሯችን ነቃ
 በዚህ ማርሽ ተፈላጊው ውጤት ካልተገኘ የኃላ ማርሽ በመነጫነጭ ይገባል ፡፡

 ንጭንጭ አንድ !
 ‹ ይራራ ሆድዋ - እግዜር ይይልዎ ! › ሊል ይችላል አንዱ ቅኝቱን እንደጠበቀ

 ንጭንጭ ሁለት !
 ‹ አለም አንድ ነው የለም አንድ ነው  እኛን ማስለፋት የሚያሳፍር ነው › ማለትም የተለመደ ነው ፡፡ ከብዙ ልፋት በኃላ ስጦታው ከተፍ ካለ ደስታችን ወደር ያጣል ፡፡ ሳናውቀውም ማርሹ አራተኛ ገብቷል ፡፡

‹‹ አመት አውዳመት
  ድገምና
  አመት
  ድገምና
  የጋሽዬን ቤት
  ድገምና
  አመት
  ወርቅ ያፍስስበት
  እንዲህ እንዳለን
  ሆ …!
  አይለየን !!
  ክበር በስንዴ
  ክበር በጤፍ
  ምቀኛ ይርገፍ !! ›› በማለት እየተሳሳቅን ውልቅ ነው ፡፡ ወደሌላኛው ቤት ስንጓዝ በመሃሉ የምንጠቀመው የጭፈራ ስልትም አለ ፡፡ ‹‹ አሲዮ ቤሌማ ›› የሚባል ፡፡ የሬዲዮ ጋዜጠኞች ይህን ዓይነቱን መሸጋገሪያ ‹‹ ብሪጅ ›› ይሉታል ፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ሞራል ማነቃቂያ መሰለኝ የምንጠቀምበት ፡፡ የምንጨፍረው እየሮጥን ነው ፤ በል ሲለን ዱላችንን ርስ በርስ እናጋጫለን ፡፡ ምናልባት ሳናውቀው ከመስቀል ጨፋሪዋች ያጋባነው ሊሆንም ይችላል ፡፡ ብቻ ዛሬ ድረስ የማይገቡኝ ቃላቶች አሉበት ፡፡

‹‹ አሲዮ ቤሌማ
  ኦ … ኦ
  አህ እንበል
  አሲዮ ቤሌማ
  ቤሌማ ደራጎማ … ›› ለአብነት ያህል ‹ ደራጎማ › ግጥሙ እንዲመታልን የተጠቀምነው ቃል ነው ወይስ ትርጉም አለው ? 

የቡሄ ዕለት ሲርበን ለምሳ ወደ ቤት መሄድ የማይታሰብ ነው ፡፡ ዳቦ ክፍሉ በጎተራው ያለውን ንብረት ያሳውቅና እንከፋፈላለን ፡፡ ዳቦ እንኳን ባናገኝ ካላቸው ላይ ገዝተን ነው የምንበላው ፡፡ አንድ ክረምት ላይ ዝናቡ ዳቧችንን አሹቆት ነበር ፡፡ በጣም የራባቸው ዳቦውን እንደ ጨርቅ ጨምቀው የቀማመሱበት ሁኔታ ነበር ፡፡ ወደ ኃላ እየቀረ ዳቦውን በጥርሱ እየከረከመ የሚያስቸግረን ባልደረባም ነበረን ፡፡ በንዴት ስንጮህበት ‹ እንዲሁ ነው የተረከብኩት ! › ብሎ ይሸመጥጣል ፡፡

 ገና ‹‹ የወንዜው ነበረ ›› ስንል ‹‹ ነብር ይብላህ ! ›› በማለት የሚያባርሩን ሰዋች እንደው ራሳቸው ከነብር ካልተሰሩ በስተቀር በአውዳመት ይህን እኩይ  ቃል መጠቀማቸው ይገርመኛል ፡፡ ለረጅም ሰዓት ከኛ ጋር ግቢው ውስጥ ጨፍሮና አስጨፍሮን  ‹‹ በሉ የዓመት ሰው ይበለን ፤ ያኔ ደግሞ ከዚህ በላይ እንጨፍራለን ›› ብሎ በነጻ የሚሸኘንም ሰው ነበር ፡፡ ያኔ በሳቅ ከመፍረስ ጎን ለጎን ዞር ብለን በተረብ ቀዳደን እንጠለው ነበር

 ‹‹ ምናባቱ ድሮ ሳይጨፍር ያለፈበትን ግዜ በኛ ያስታውሳል እንዴ ?! ብሽቅ ! .. ገገማ ! … ጥፍራም ! … ሽውደህ ሞተሃል ?! … ›› በዛሬ ዓይን ሳስበው ግን ‹ ምን ዓይነት ፍቅር ያለው ሰው ነው ?  › እላለሁ ፡፡ አደገኛ ውሻ ለቀውብን  ስንፈረጥጥ በሳቅ ብዛት የሚሰክሩትም ጥቂት አይደሉም ፡፡ በጣም የሚገርመው ከመታ የሚገላግለውን ወጠምሻ ዱላ አዝለን ከሩጫና ፍርሃት መገላገል አለመፈለጋችን ነው ፡፡ ማታ ላይ ጉዳዩ ተነስቶ ስንተራረብ ‹ እኔ የሮጥኩት ወሻውን ሳይሆን ባለቤቱን ፈርቼ ነው › በማለት እናስተባብላለን - እንዲም አድርጎ ሽውዳ የለም ፡፡ ዞሮ ዞሮ የተፈጸመብንን ግፍ ወደሌላው በማጋባትም እንታወቃለን ፡፡ ሌላ የጨፋሪ ቡድን መንገድ ላይ ስናገኝ ‹ እዛ ቤት 10 ብር አግኝተናል › በማለት ወደ ውሻው ቤት እንዲሄዱ እንጠቁማቸዋለን ፡፡ ከዛ በተራችን ራቅ ብለን የአዳኝና ታዳኝ ትርዒቱን በሳቅ እያጣቀስን መኮምኮም ነው ፡፡

 ማታ ስንተኛ የቀኑን ውሎ እያስታወስን የምንስቅበት፣ የምንተራረብበትና የምንገማገምበት መድረክ ነው ማለት ይቻላል ፡፡ የሁላችንም ዱላ ስሩ ይታያል ፤ መሬት ሲደበድብ ስለሚውል ተቸርችፎ የተጠቀለለ ሉጫ ጸጉር ይመስላል ፡፡ ይህ የጸጉር መጠን አነስተኛ የሆነበት መሬቱን በደንብ ስለማይመታ ለጋሚ ነው ተብሎ ይተቻል ፡፡ ድምጽም ሌላው መመዘኛ ነው ፡፡ በደንብ ሲጮህ የዋለ ድምጹ እንደ አለቀ ባትሪ መነፋነፉ ይጠበቃል ፡፡ ብዙም ያልተለወጠ ከተገኘ ‹ በእኛ ላይ ሲያሾፍ ስለነበር ክፍፍሉ ላይ ዋጋውን ያገኛል ! › ይባላል ፡፡ 

ታዲያ በማግስቱ ያ - ሰው እኔ ካላወጣሁ እያለ ሲያሸብር ይውላል ፡፡ በደንብ ማውጣት የማይችሉ አባላትም ሌላው የመዝናኛ ገጸ በረከቶች ናቸው ፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ መጣንሎት በዓመቱ እንዴት ሰነበቱ ›› የምትለውን የመግቢያ ስንኝ ከጨረሰ በኃላ በምን ዓይነት ዝላይ እንደሆነ ሳይታወቅ የመጨረሻውን ‹‹ እረ በቃ በቃ ጉሮሯችን ነቃ ! ›› ላይ ፊጢጥ የሚል ያጋጥማል ፡፡ በስንት ህክምናና ስለት ልጅ እምቢ እንዳላቸው እያወቀ ‹‹ ይራራ ሆድዋ እረ በልጅዋ ! ›› የሚል ልመና በማቅረብ እኛን ለመጥፎ ሳቅ ሰዋቹን ለማሳቀቅ የሚዳርግም  አይጠፋም ፡፡ አንዳንዴ ወደማናውቀው ሰፈር ጥሩ ብር ለመስራት ሄደን በሰፈሩ ጉልቤዋች የ ‹ ኮቴ › ተብሎ የምንቀማበት ሁኔታ ያጋጥማል ፡፡ ይህ ጉዳይ ከተፈጸመ  ማታ ብዙውን የክርክር ጊዜ ሊወስድብን ይችላል ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሚወቀሰው ግን ራሱ ገንዘብ ያዡ ነው ፡፡

 ‹ ከርፋፋ ! ገንዘቡን ዝም ብለህ  ሜዳ ላይ ታስቀምጠዋለህ ?! › ሊባል ይችላል ፡፡ አንድ ሰው ገንዘብ ያዥ ሆኖ ሲመረጥ የራሱን ጥበብ መዘየድ ይኖርበታል ፡፡ ገንዘቡ በጉልቤዋች ሊበረበር ይቻላል በሚል ስጋት የሱሪው እግር አካባቢ፣ ኮሌታ ስር፣ በቀበቶው ማድረጊያ የውስጥ ክፍል ወይም በሌላ አሳቻ ቦታ ሰፍቶ በመደበቅ የማምለጫ ፋይዳዋችን ማስፋት አለበት እንጂ በድንጋጤ ንብረቱን ማስረከብ የለበትም ፡፡ ሌላው ቢቀር የተወሰኑ ወፍራም ቡጢዋችን ቢቀምስ እንኳን ‹ እረ ገና አልሰራንም ! › ብሎ መሸምጠጥ ይጠበቅበታል ፡፡

 በማታው ክፍለ ግዜ አባላቱ እየተንጫጩ ራሱን ዜሮ ማርሽ ላይ አቁሞ በጸጥታ የሚሰምጥም አይጠፋም ፡፡ ለመሆኑ የዝምታው ምንጭ ምን ሊሆን ይችላል ?  በአብዛኛው ሶስቱ ናቸው ። እዳ ፣ ነጠቃ እና ግርፊያ ::

እዳ … የሚፈጠረው በብይ ወይም በጠጠር ጨዋታ ነው ፡፡ በክረምት ገንዘብ ከሌለን ጨዋታው ሞቅ እንዲል በሚል በዱቤ እንጫወታለን - ለቡሄ ለመክፈል በመስማማት ፡፡ ብዙ የማይችሉት ታዲያ ከአሁን አሁን እናስመልሳለን እያሉ እዳው ጣራ ይነካባቸዋል  ፡፡ እናም ያስባል ፤  ብሩን አስረክቤ ቤት ምን ይሉኛል ? ድጋሚ አቤቱታ ልጠይቅ ? ልካድ ? ብክድ ምን ይመጣብኛል ? ….

 ነጠቃ … የምንለው ደግሞ በጉልቤ ቤተሰቦች የሚከናወን ነው ፡፡ ለስለስ ባለ አነጋገርና የጭንቅላት ዳበሳ ሁለት ቀን ጨፍሮ ያገኘውን ብር ይቀመጥልህ አይደል ? ይባላል … ኮስተር ባለ ግንባር ልጅ ገንዘብ ከለመደ ዱሩዬ ይሆናል ! ይባላል …  ዲፕሎማት በሆነ መንገድ አበድረኝ ሊባል ይችላል … ብቻ በብሩ እንደሌሎች የፈለገውን ማድረግ ስለማይችል የማምለጫ መንገድ ፍለጋ በሃሳብ ይኳትናል ፡፡

 ግርፊያ … የሚመነጨው ከሃርደኛ አባቶች ነው ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹ መጨፈር አንሶህ በዓመት በዓል ሰው ቤት ምናባህ ያሳድረሃል ?! › የሚል ነው ፡፡ በጨፈረበት ዱላ የሚወቀጥ … ባገኘው ገንዘብ በርበሬ ገዝቶ የሚታጠን … ያጋጥማል ብሎ መውሰድ ይቻላል ፡፡

 ብቻ ምንም ሆነ ምን  ባለ ማርሹ ቡሄ ደስታው የላቀ ነው ፡፡ በቡሄ  ገንዘብ ከማግስቱ  ጀምሮ እንቁጣጣሽን አንቨስት ማድረግ እንጀምራለን  ፡፡ ወረቀት ፣ ንድፍ ፣ ቀለም  ይገዛል ፡፡ የወቅቱ የእግር ኳስ ኮኮቦችና ሁሌም ቋሚ ተሰላፊ የሆኑትን መላዕክቶች በመኳል እንደሰታለን ፡፡ እናም ቡሄ ባይኖር ኖሮ እንቁጣጣሽ ይከብደን ነበር ፡፡ ኢንቨስት የምናደርግበትን ገንዘብ ማን ይሰጠናል ?


Monday, August 14, 2017

ከለንደኑ ውድድር ያተረፍናቸው ሽሙጥ እና ግጥሞች


የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዝናንቶን አለቀ ። ኢትዮጽያን የወከለው ቡድን ሁለት ወርቅና ሶስት ብር አጥልቆ በሰባተኛ ደረጃ ውድድሩን ጨርሷል ። ከለንደን ያገኘነው ግን ሜዳሊያ ብቻ አይደለም - ሽሙጥና ቅኔዎችም ጭምር እንጂ ። በመንፈስ አብሮ ሲሮጥ የነበረው ኢትዮጽያዊም ሲበሳጭ በሃይለቃል ፣ ሲደሰት በግጥም ግራ ሲጋባም በጥያቄ ሀሳቡን በማካፈል የማይናቅ ሚና ተጫውቷል ።

ሀገራዊ ሽሙጥ

ንዴቱ የጀመረው ገንዘቤ ዲባባ ያልተጠበቀ ውጤት ባስመዘገበችበት ወቅት ነበር ። ይቺ ብርቅ አትሌት የባለብዙ ሪክርድ ባለቤት መሆኗ ይታወቃል ። በየግዜው ሪከርድን እንደ ፋሽን ከመቀያየሯ አንጻር በለንደን ያጋጠማትን ሽንፈት ለመቀበል አስቸጋሪ ነበር -ለብዙዎች ። ከገንዘብና ከሀገር ፍቅር ስሜት ጋር በማያያዝ ሽሙጡ ፣ ስላቁ እና ዝርጠጣው ተወረወረ ። ቀስቱን ሊመክቱላት የተጉ ሰዋች ቢኖሩም ስሜቷን ከመሰበር አላዳነውም ።

ስምን መልአክ ያወጣዋል የሚል ስነቃል ወርውሮ ገንዘቤን ከገንዘብ ... አልማዝን  ከእንቁነት ጋር ብቻ ማዛመድ ኢትዮጽያዊ ፍርድ ቤትን መምሰል ነው የሚሆነው ። ፍርደ ገምድልነት ግዜያዊ ቁጣና እብሪትን ያበርድ ከሆነ እንጂ ከኋላ የተቆለለውን እውነት አይሸፍነውም ። ወርቅ የመራብ ጉጉት ታላቁን በረከት መሸፈን አልነበረበትም ። ዓለምን በተደጋጋሚ ድል ጉድ ያሰኘው እግሯ ቢሆንም እጆቿም ባንዲራን በማውለብለብ የገጽታ ግንባታን ያለ ገደብ ገንብተዋል ። አለም በብቃቷ ተማርኮ ንግስትና ጀግና ያደረጋትን አትሌት በምንም ሃይል ከከፍታዋ ላይ ማውረድ አይቻልም ። አጉል ግራ መጋባት እንጂ ።

ይልቅ በአደጋገፋችን ላይ የሚሰነዘረውን ሽሙጥ መመርመር ብንችል ማለፊያ ነበር ። አንድ አትሌት ኢትዮጽያን ወክሎ ከሀገር ይወጣል ፣ መንገድ ላይ ግን በብዙ ባንዲራዎች ይደገፋል ። የውጭ ሀገር ሰዎች የተለያየውን ባንዲራ እያዩ አንተ ከየት ነህ ? ለማነው የምትደግፈው እያሉ ይጠይቃሉ ። ባንዲራ ለባሹ በኩራት ይመልሳል ። ታዛቢው ኢትዮጽያ ስንት ባንዲራ ነው ያላት ? ስንት ስያሜ ነው ያላት ? መጀመሪያ እየተደናበረ ቆይቶ ደግሞ እያሽሟጠጠ ይጠይቃል ። መላሹ እየተቆጣ ይመልሳል ። ይኅው አዙሪት እንደቀጠለ ነው ።
ግራ የገባው ሰው ምንኛ ታደለ
ቀኝም ሆነ ግራ ያልገባው ስንት አለ - ይልሃል አሽሟጣጩ ስንኝ ...

ግጥም
‹ የማይሸነፈው › ሞ ፋራ በዮሚፍ ቀጀልቻ በር አስከፋችነት ለሙክታር እድሪስ እጅ የሰጠ ግዜ ደግሞ አሽሙረኛው ሁላ ገጣሚ ሆኖ ቁጭ አለ ። ግጥም እንደ ጉድ ዘነበ ። ስድ ንባብ በደስታ ወቅት ዋጋ ቢስ ነው ለካ ? የህዝቡ እምቅ ችሎታ አፍጥጦ ወጣ ። ማን ያልገጠመ ማን ጥቅስ ያላመነጨ አለ ? የፌስ ቡክ ግድግዳዋች ከአጫጭር ግጥሞች ጎን ለጎን በፉከራዎችና ሽለላዎች ደመቁ ። እናት ሀገርም በግልባጭ ሞገስና ውዳሴ አገኘች ። ነባር የፌስ ቡክ ገጣሚዋችም ቅኔ ዘረፉ

ጥረትና ድካም
ካልታየ በስራ
ለአራዳም አልሆነ
እንኳንስ ለፋራ አሉት ።

በርግጥ በሌላኛው ጠርዝ የሚገኘው ህዝብም ለሞ ፋራ ብልጥ የሆኑ ስንኞችን ከመጠር ቦዝኖ አያውቅም ።

Born in Somalia
Trains in California
Arsenal fan, a Gooner
Running in Londinium
A superstar, a Muslim
Cheered by the Whole stadium

አለማቀፋዊ  ሽሙጥ
አልማዝ አያና አንድ ወርቅና አንድ ብር በማሸነፍ በሰሌዳ ደረጃችን ላይ ትልቅ ሚና ተጫውታለች ። አልማዝ ፣ ወርቅ ፣ ብር ደስታዊ ትስስሮሽ በመፍጠሯ ህዝቡ ወስጥ እንቁነት ፈጥራለች ። በበጎ ያዩዋት ሁሉ የአስር ኪሎ ሜትሩን ሩጫ ተአምር ነው ብለዋል ። ለ 11 ወራት ከሩጫ ርቃ ከሶስት አትሌቶች በስተቀር ሁሉንም ደርባ ማሸነፍዋ አጀብ የሚያሰኝ ነው ። የብዙዎቹን አትሌቶች የግል ሰአት እንዲሻሻል ምክንያት መፍጠሯ እና በ 46 ሰከንድ ርቃ ማሸነፏ የውድድሩ ክስተት ነበር ።

የአልማዝ ውጤት ያልተዋጠላቸው ግን ጥቂቶች አልነበሩም ። ለምሳሌ የአውስትራሊያ የሶስት ግዜ ሻምፒዮናና አሰልጣኝ ሊ ትሩፕ አለማቀፉን ፌዴሬሽን በመውቀስ ውድድሩ ቀልድ እንደሆነ ጽፏል ። የስኮትላንድ ረጅም ርቀትና የጎዳና ተወዳዳሪ የነበረችው ኤልሳቤጥ ማኮልገን ውጤቱን እንደማትቀበለው ገልጻለች ። ሌሎችም በድረ ገጻቸው የአልማዝን ተአምረኛ እግሮች እንደሚጠራጠሩት ጽፈዋል ። በሪዮ አኦሎምፒክ ለቀረበላት ተመሳሳይ ጥያቄ የኔ ዶፒንግ ስልጠና እና ፈጣሪ ነው ብትልም ዘንድሮም ሆያሆዬው አልቀረላትም ።








LIZ mccolgan @Lizmccolgan

So from 3k to 8 k Ayana 5 k split 14:30. Until Ethiopia follow proper doping procedures i for one do not accept these athletes performances


Well they might. But I would suggest the issue is broader than simply a country. It's who trains there & how often they're tested OOC? 

Won't she be tested tonight? Why pin the blame on a country then international testing is in place? Does the UK test Mo?
 But you cheer on Farah, who has hidden with Jama Aden several years?

የዚህ ሽሙጥ ፍላጻም ወገንተኛውን ሚዲያ ያጥበረበረው ይመሰለኛል ። በሚዲያ ሽፋን ቦልት እንጂ ጀስቲን ጋትሊን አዲስ ጀግና አልሆነም ። ጀግናውን ሞ ፋራ ላቆመው መሃመድ በቂ ነገር አልተሰራም ።

ሌንሱን ሞ ፋራህና ቦልት ላይ ብቻ አነጣጥሮ ብዙ ሊመረመርና ሊባልበት የሚገባውን የአልማዝ ልዩ ስትራተጂ በዝርዝር መቃኘት አልፈለገም ። ለአዲስና ልዩ ለሆነ ዘዴ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚያከራክረውና የሚያመራምረው አለማቀፍ ሚዲያ እሱም አሽሟጣጭ ካልሆነ በስተቀር ጉዳዩን ችላ የሚልበት መንገድ ግልጽ አይደለም ።

የአልማዝ የ 10ሺህ ሜትር ስልት የእሷ ብቻ ምልክት ነው ወይም ስልታዊ ሪከርድ ነው ። ይህን ልዩ ስልት ሌሎች አትሌቶች እንዴት እውን ማድረግ ይችላሉ ? ነው ይህን ስልት መከተል አዋጭ አይደለም ? በተወዳዳሪነትና ልብ አንጠልጣይንት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ እንዴት ይታያል ? ምክንያቱም አንድ ሰው ገና ከጠዋቱ ቀድሞ ወጥቶ ማሸነፍ ከቻለ ተመጣጣኝ ውድድር እና አጓጊንት ይኖራል ለማለት ያስቸግራል ። ብዙ ሊጠናበት ግድ ቢልም ሚዲያው ሸውራራነትን መርጧል ። አሰልጣኞች የጉዳዩ ባለቤት ከመሆን ይልቅ ቅንድባቸውን መስቀል ፈልገዋል ።


ድንቄም ... ?! አለ አሽሟጣጭ

Thursday, August 3, 2017

የድርሰት ሰማይን ያደመቁ ብዕረኛ

ደራሲ አማረ ማሞ ብዙ አልተባለላቸውም ። ግን ለስነጽሁፍ ብዙ ሰርተዋል ፤ በእጅጉ ደክመዋል ። እጣ ፈንታ ሊሆን ይችላል ። አንዳንድ ያደለው በአንድ ጥሩ ስራ ስማይ ላይ ሊወጣ ይችላል ። የዚህ አይነቱ እድለኛ ባለቲፎዞም ስለሚሆን ክበባቱ ፣ ሚዲያውና ማስታወቂያው እንኮኮ ያደርገዋል ።

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ደራሲ፣ አርታኢና ተርጓሚ አማረ ማሞ ማናቸው ተብሎ አልተመረመሩም ። እኚህ ሰው ስነጸሁፍ ፍቅራቸው ብቻ ሳይሆን ህይወታቸው በመሆኑ ኖረውብታል ማለት ይቻላል ። የኢትዮጽያ መጻህፍት ድርጅት ስነጽሁፍንና ደራሲዎችን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ተጫውቷል ። እሳቸው ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ ም/ስራ አስኪያጅ ነበሩ ።

በድርጅቱ አሳታሚነት ለንባብ ይበቁ የነበሩ መጻህፍትን የሚያስታውስ አንባቢ የአቶ አማረን ድርሻ በአግባቡ ለመረዳት አያዳግተውም ። የነባርና እጩ ደራሲዋችን የአሳትሙልኝ ረቂቅ ጽሁፎችን በመለየት ፣ የተለየውን ደግሞ የአርትኦት ስራ በማከናወን በድርሰት ላይ የማዋለድና ጥሩ ቁመና የመፍጠር ህክምና አበርክተዋል ።

እንዴት ላሳትም ወይም በምን መልኩ ልጻፍ ወይም የመሳሰሉ ጥያቄዋችን አንግቦ ቢሯቸው ጎራ የሚሉትን ጥበብ አፍቃሪዋች ውሃ የሚያነሳ ምላሽ ለመስጠት አያነቅፋቸውም ። የኢትዮጽያ መጻህፍት ድርጅት ከስራ ውጪ ከሆነ በኋላ እንኳ አቶ አማረን ኪነጥበባዊ እድሞሽ ላይ ማግኘት ቀላል ነበር ። በስነጽሁፋዊ ውይይቶችም ሆነ ህትመት ምርቃቶች ላይ ከፊት በመገኘት ልምዳቸውንና ሃሳባቸውን ሳይሰላቹ አጋርተዋል ።

አቶ አማረ የበርካታ መጻህፍት ደራሲና ተርጓሚ ናቸው ። ዶን ኪሆቴ ፣ አሳረኛው ፣ እሪ በይ ሃገሬ ፣ የእውነት ብልጭታ ፣ የቀለም ጠብታ እና የልብ ወለድ ድርሰት አጻጻፍ የተስኙ ስራዋችን በጥቂቱ መጠቃቀስ ይቻላል ።

እውነቱን ለመናገር የልብ ወለድ ድርሰት አጻጻፍ የተሰኘው ስራቸው ብቻ ሽልማት የሚገባው ነው ። በ1960ዎቹ የታተመው ይህ ስራ የብዙ ድርሰት አፍቃሪያንን አይኖች የገለጠ ነው ። እንደሚታወቀው ኮሌጅ/ዩኒቨስቲ የመግባት እድል ያላጋጠማቸው የሀገራችን ደራሲዎች ጥቂቶች አይደሉም ። ብዙዎቹ ታዲያ መጽሀፉን እንደ አንድ ተቋም ክብር በመስጠት የልቦለድ ባህሪና ምንነትን እንዲሁም እንዴት መቀሸር እንደሚገባው የተረዱት ይህን መጽሀፍ በማንበብ ነው ። ለመጽሀፉ ምስጋና ይግባውና ጠንካራ ምናብና ብእር ያላቸው ደራሲዎች መፈጠር ችለዋል ።

ይህ መጽሀፍ ድንበር ያጠረው አልነበረም ። ሌላው ቀርቶ በኮሌጆችና/ዩኒቨስቲዎች ለስነጽሁፍ ትምህርት አጋዥ በመሆን ለመምህራኑም ሆነ ለተማሪዎች ትልቅ ግብዓት ፈጥሯል ። በነገራችን ላይ የራሳቸውን ማንዋል አዘጋጅተው ወይም አጋዥ ስራ አሳትመው የሚያስተምሩ ውለተኛ መምህራን ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው ። የቲያትር ኮርስ ሲሰጥ የፋንታሁን እንግዳ የተውኔት መጽሀፍ ነው ትልቅ ድርሻ የሚወስደው ። ተማሪ እየተናጠቀ ኮፒ ለማድረግ ይራወጣል ። በዚህ ረገድ ደበበ ሰይፉና ዘሪሁን አስፋው የሚታሙ አይመስለኝም ። ርግጥ ነው ብርሃኑ ገበየሁም ኋላ ላይ ተቀላቅሏል ። መሰረታዊ ስነጽሁፍ ለኮሌጅ ተማሪዋች በተለይ የአፍሪካ ስነጽሁፍን አስመልክቶ ግን ብዙ ያልተዘመረለት መምህር አለ ። መክነህ መንግስቱ የሚባል ። ርግጠኛ ባልሆንም ከኮተቤ ወደ ዩኒቨርስቲ የተዘዋወረ ይመስለኛል ። በርካታ ድርስት ነክ ስራዎችን በእንግሊዘኛ ቋንቋ አሳትሟል ። ተማሪዎችም የእሱን ስራዎች መነሻ በማድረግ የአፍሪካን ስነጽሁፍን ለማወቅና ለመመርመር አግዟቸዋል ።

የአቶ አማረ ስራ ግን ኮሌጅ ለረገጠውም ላልገባውም ፣ ለጀማሪውም ለመምህራንም ፣ ለስነጽሁፍ አድናቂም ለተመራማሪውም ዛሬም ድረስ የውለታ ሃውልት ሆኖ ቆሟል ። እንግዲህ እዚህ ሃውልት ላይ ነው ሰሞኑን የክብር ካባ እና የወርቅ ብእር የተሰቀለው ። በሸላሚው ድርጅት ማለትም በንባብ ለህይወት የፌስ ቡክ ገፅ ላይ « አይናቸውን ያልጨፈኑ የድርሰት ሰማያችንን ያደመቁ ኮኮብ ሆነው ሆነው በመገኘታቸው የዓመቱ የወርቅ ብዕር ተበርክቶላቸዋል » የሚል ጽሁፍ ይነበባል ።

ግሩም ምስክርነት ሆኖ ስላገኘሁት ደስ ብሎኛል ። በርግጥም የድርሰት ሰማያችንን ለማድነቅ የተጉ በርካታ ጸሐፊያን አሉን ። አቶ አማረ ግን ኮኮቦቹ ከመታየታቸውም በፊት ጧፍ ሆነው ተገኝተዋል ። ብዙዎችን አርመዋል ... ኮትኩተዋል ... በርካቶችም የጧፉን ብርሃን ተከትለው  መንገድ አግኝተዋል ።


ንባብ ለህይወት በአጭር እድሜው አምባሳደር ዘውዴ ረታ ፣ አዳም ረታንና አማረ ማሞን የወርቅ ብዕር ተሸላሚ አድርጓል ። መልካም ጅምር ስለሆነ ለረጅምና ላልተቆራረጠ ጉዞ ብርታቱን እንዲሰጣችሁ እመኛለሁ ። ብርታቱ ግን እንደ አማረ ማሞ ብዙ ሰርተው ያልተነገረላቸውን ብዕረኞችን  ለማፈላለግ ጭምር እንዲሆን ማድረግ ይገባል ።