Saturday, June 23, 2012

አስገራሚው የ ‹ ከቤ እና የእሙሙ › ፌስቲቫል !‎!‎




ጃፓኖች ትሁትና አይናፋር ናቸው፡፡ ወግ አጥባቂዋች ስለሆኑ በግልጽ ደፍረው ስለ ወሲብ ለመወያየት የሚያስቸግራቸው ይመስላል፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች እንዲህ ብናስብ አልተሳሳትን ይሆናል፡፡ ግን ስለ ብልት የሚዘፍኑበት፣ የሚለምኑበት፣ የሚቀልዱበት፣ አካፋን አካፋ የሚሉበት ግዜ መኖሩን ለሚያስብ ሊገረም ይችላል፡፡ አላውቃቸውም እንዴ በማለት ?!

የዓለማችን ሀገሮች የራሳቸው የሆነ ልዩ ክብረ በዓል እንዳላቸው ይታወቃል ፡፡

ሳምባ - የብራዚል ፌስቲቫል ሲሆን የሳምባ ዳንስ ውድድር ይከናወንበታል፡፡

ኤል ኮላቻ - የስፔን ፌስቲቫል ሲሆን ገና የተወለዱ ህጻናት ተደርድረው ይዘለላሉ፡፡ ዓላማው ህጻናትን ከኃጢያት ማንጻት ነው፡፡

የጦጣ ቡፌ - በታላይንድ ፌስቲቫል 600 ጦጣዋች 3ሺህ ኪ.ግራም የሚደርስ ፍራፍሬና ቅጠላ ቅጠል እንዲበሉ የሚጋበዙበት ነው፡፡ ዓላማው የራማን ጀግና መምረጥ ነው፡፡

ሆሊ ፌስቲቫል - በህንድ የሚከበር የቀለማት በዓል ነው፡፡ ሰዋች ከኒምና ከተለያዩ ቅጠሎች የቀመሙትን ቀለሞች ይወረውራሉ፡፡ ቀለሙና ፓውደሩ ገንፋንና ትኩሳትን ያድናል ብለው ያምናሉ፡፡

ማስላንታስ - በሩሲያ የሚከበር ነጻ የሆነ የቦክስ በዓል ነው፡፡ ህግ ስለሌለው ግብግቡ የሚያበቃው ተፋላሚው በደም ሲሸፈን ነው፡፡
ላ ቶማቲና - በስፔን በሺ የሚቆጠሩ ሰዋች በቲማቲም ርስ በርስ የሚደባደቡበት ፌስቲቫል ነው፡፡ ይህን ትርዒት 3 መቶ ሺህ ቱሪስቶች ይከታተሉታል፡፡

ሮስዌል - በአሜሪካ ይህ በዓል የሚከበረው ዩፎዋች በሮስዌል ያደረሱትን ጥቃት ለማሰብ ነው፡፡ በዓሉ ሰዋች ልዩ ፍጥረት የሚያስመስላቸውን ማስክ አድርገው በልዩ ልዩ ስፓርታዊ እንቅስቃሴዋች በመወዳደር ነው፡፡

ሃይማኖታዊ መሰረት ቢኖራቸውም በሀገራችንም ጥምቀትና መስቀልን የመሳሰሉ በርካታ ቱሪስት ጠሪ ፌስቲቫሎችን መጠቃቀስ ይቻላል፡፡

ሌላም የትየለሌ ፌስቲቫሎች ሊደረደሩ ይችላሉ፡፡

እነዚህና ሌሎችም ግን ከጃፓን ክብረ በዓሎች ጋር መወዳደራቸው ያጠራጥራል፡፡ በዓሉ የሚያተኩረው በሰው ልጆች አቢይ ብልቶች ላይ ነውና ፡፡ ይህን ክብረ በዓል ድንገት የሚቀላቀል በድንጋጤ ግር ቢለውም እየቆየ ሲሄድ ግን በሳቅ መፈንዳቱና መደሰቱ አይቀርም፡፡ ነገሩ የማይደፈር በመሆኑ በተለይም የጃፓን ቀጣይ ትውልድ ልዩ ሃሳቦችን እንዲያመነጩ ያግዛችዋል ነው የሚባለው፡፡

ቀኑ መጋቢት 15 ነው፡፡

በዕለቱ የወንድንም ሆነ የሴት ብልትን በስሙ ነው የሚጠሩት - አይናፋሮቹ ጃፓኖች፡፡ ለዚህም ነው የፌስቲቫሉ ስያሜም ምንም ሽፍንፍን ሳይደረግ ‹ የወንድ ብልት ፌስቲቫል! ›… ‹ የሴት ብልት ፌስቲቫል ! › እየተባለ የሚጠራው፡፡  ለጽሁፉ አስገራሚነት ፣ ለአውዱ ጥያቄና ማማር ሲባል እኔም ለዛሬ አካፋን አካፋ እያልኩ መጥራት ነበረብኝ፡፡ ግን ከጻፍኩት በኃላ ሸከከኝ ፡፡ የሞራል ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ እናም የወንዱን ‹‹ ከቤ ! ›› የሴትን ‹‹ እሙሙ! ›› እያልኩ የቅጽል ካፓርት ማልበስ አስፈለገኝ፡፡ 
·          
መጋቢት 15 ቀን የከቤ ቀን በተለይ በኮማኪ ከተማ በደማቅ መልኩ ይከበራል፡፡ ከዚህ ክብረ በዓል አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ደግሞ የእሙሙ ፌስቲቫል አለ ፡፡ እነዚህ በዓሎች የ1500 ዓመታት ዕድሜ አላቸው፡፡ የበዓላቱ መነሻዋች ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በአንድ በኩል መሬታቸው ጥሩ ሰብል እንዲሰጣቸው በሌላ በኩል ምርት ብቻ ሳይሆን ልጅ እንዲያገኙ ብልቶችን ወይም የብልት አምልኮዋችን የሚለማምኑበት ስርዓት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ጃፓን በዓለማችን አነስተኛ የወሊድ መጠን የተመዘገበባት ሀገር ናት፡፡ በመረጃው መሰረት 1.37 ህጻናት ናቸው ለአንዲት ሴት የሚደርሱት፡፡ ባለፈው ዓመት ስልጣን የያዘው ገዢ መደብ ሴቶች ተጨማሪ ህጻናትን እንዲወልዱ የሚያበረታታ ስጦታ አበርክቷል፡፡ መመሪያውን ተግባራዊ የሚያደርጉ እናቶች ለህጻናቱ ማሳደጊያ በየወሩ 280 ዶላር ይቆረጥላቸዋል፡፡

በእሙሙ ፌስቲቫል ቀን እናቶች ልጆቻቸውን አዘንጠው በፕላስቲክ፣ በእንጨት ወይም በተለያዩ ቁሳቁሶች የተሰሩ ትናንሽ የእሙሙ ምስሎችን ይዘው በዋናው አደባባይ እንዲገኙ ያደርጋሉ፡፡ 40 የሚደርሱ ሰዋች በትልቅ ቅርጽ የተሰራውን እሙሙ  በቃሬዛ መልክ ይዘው ይዞራሉ፡፡ በዕለቱ እናቶች ለልጆቻቸው ጤንነት ይጸልያሉ፡፡ በዓሉ ላይ የተለያዩ ምግቦችና ቢራዋች ይዘጋጃሉ፡፡ በበዓሉ ማብቂያ ላይ ነጭና ሀምራዊ ጣፋጭ ሩዝ ሰዋች ላይ ይረጫል፡፡

በከቤ ፌስቲቫል ቀን ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ጃፓናዊያንና የውጪ ቱሪስቶች በቦታው ይታደማሉ፡፡ በኛ ሀገር በክብረ በዓል ቀን በየመንገዱ፣ ድልድይ፣ ቆርቆሮ፣ የስልክ እንጨት ወዘተ ላይ የሚንጠለጠለው ባንዲራ ነው፡፡ ጃፓኖች በዚሁ ዕለት ከላይ በተገለጹት ቦታዋች ላይ የሚያንጠለጥሉት ሌላው ቀርቶ በአፍንጫቸው ላይ የሚያስሩት የወንድን ብልት ነው ፡፡

ይህ በዓል የሚከበረው እኛ ሀገር ቢሆን ከባንዲራው ጎን ጥቅሶችና መፈክሮች መኖራቸው ግድ ይላል፡፡ እንደው ሳስበው
 ‹‹ ከቤ ለዘላለም ይኑር ! ›› የሚል ጥቅስ ብዙ ሰው የሚይዘው ይመስለኛል፡፡
‹‹ ያለ እሙሙ ተሳትፎ
እንኳን አብዮቱ
አይነጋም ሌሊቱ ›› የሚል ሞጋች ስነ ቃልም ከወግ አጥባቂ ሴቶች ክንድ ላይ ይጠበቃል፡፡
‹‹ አርሜ ኮትኩቼ ያሳደኩት ከቤ
  አምላክ ይመስገነው ደረሰ ከሃሳቤ ›› የሚል መፈክር ደግሞ በአንዳንድ ፍንዳታዋች እጅ ቢጠፋ እንኳን እንደ መዝሙር ሲደጋግሙት ሊሰማ ይችላል፡፡
‹‹ የከቤና የእሙሙን  አቅም አሟጦ በመጠቀም የልማታችንን ቀጣይነት እናረጋግጣለን ! ›› የሚል ካድሬያዊ መልዕክት ይጠፋል ማለትማ የሰማይ ስባሪ የሚያህል ውሸት እንደ መናገር ያስቆጥራል፡፡
ተረቶቻችን፣ አባባሎቻችን፣ ዘፈኖቻችን፣ የወሬ ማጣፈጫዋቻችን፣ ቀረርቶዋችን ሁሉ ከነ ከቤ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተጋመዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሌላው ቢቀር
ራሰ በረሃ አንገተ ክርክር
ሁለት ልጆች ይዞ በጫካ የሚኖር !
የተባለችውን እንቆቅልሽ ከልጅነቱ ሳይሰማት ያደገ ማን አለ ?  ከፍ እያልን ስንሄድ ተረትና እንቆቅልሾቻችንን በሰምና ወርቅ አጠናክረናቸዋል፡፡ ካስፈለገም የአግቦና አሽሙር ብቃታችንን ከኃላ ኪሳችን እናወጣለን፡፡ ምናለፋችሁ ፌስቲቫሉ ቀውጢ የሚሆን ይመስለኛል፡፡
·          
እናላችሁ በትልቅ ቅርጽ የተሰራው ከቤ ርዝመቱ 25 ሜትር ሲሆን ክብደቱ 280 ኪ.ግራም ይመዝናል፡፡ ቪንሚንሻ ይሉታል ጃፓኖች ይህን ጣዖት፡፡ ይህን ቅርጽ በመሸከም ታዋቂውን አደባባይ መዞር፣ ማጨብጨብ፣ መዘፋፈን ፣ መጸለይ፣ በቅርጹ የተሰራ ሻማ ማብራት የተለመደ ነው፡፡ ድርጊቱ ለአንድ ወይም ለአንድ ተኩል ሰዓታት ይፈጃል፡፡ የጥንት ጃፓኖች የከቤው አደባባይ የዕድገትና የልማት ሁሉ መሰረት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በሌላ አነጋገር እናት የሆነቸው መሬት፣ አባት በሆነው ሰማይ ታረግዛለች፡፡ ይህን ተምሳሌት የሚያቀነቅን ፈላስፋ ማን ነበር ?

በመሆኑም ልጅ የሌላቸውም ሆኑ ተጨማሪ ልጅ የሚፈልጉ ሁሉ በክብረ በዓሉ ላይ በለመለመ ተስፋና ፍቅር ይገኛሉ፡፡ ክብረ በዓሉ በርካታ ቱሪስቶችን እየሳበ በመሆኑ ሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ታገኛለች፡፡ ነጋዴዋችም በእሙሙና  በከቤ ቅርጽ የተሰራ ከረሜላና ቸኮላታ ይቸበችባሉ፡፡ በእንጨትና በፕላስቲክ ቅርጻ ቅርጾች የተሰሩ ብልቶች፣ የጆሮ ጌጦች፣ የሲጋራ መተርኮሻዋች ይሸጣሉ፡፡ በተለይም ወጣት ሴቶች በወንድ ብልት የተሰራን ከረሜላ በመምጠጥ ራሳቸውን ያዝናናሉ፡፡ የሚገርመው የሁለቱም ጾታዋች ብልቶች ዋጋ እኩል 600 የን ያህል  መሆኑ ነው፡፡ በርካታ ቱሪስቶች ፌስቲቫሉ በተለይም ልጅን ይሰጣል የሚለውን ሀሳብ ባይቀበሉትም ቢራ በመጠጣትም ሆነ ቅርጹን በመምጠጥ፣ በሃገሬው ደስታና እምነት በመደሰት እንዲሁም ከከቤ ጋር የተያያዙ ቀልዶችን በማውራት ይዝናናሉ፡፡

በማይደፈር ነገር መዝናናት ብልግና ነው ሀሴት ?

መቼም የነከቤ ፌስቲቫል ይኑረን  ባይባልም ፣ ጀግንነት ነው እየተባለ የሰው ከቤ የሚቆረጥበትና  የልጃገረዶችን እሙሙ  የሚሰፋበት ሀገር ውስጥ ከመኖራችን አንጻር ለዚህ ወሬ ቢያንስ አክብሮት ሊኖረን ሳይገባ አይቀርም፡፡

ወጣቶች በከቤ የተሰራ ከረሜላ ሲመጡ



ረጅም ዕድሜ ለከቤና ለእሙሙ !!



Wednesday, June 20, 2012

‎የዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም በልሃ



አሰብ የማን ናት ?

ይህ ጥያቄ የተጠየቀው ከግንቦት 1983 በፊት ቢሆን አብዛኛው ምላሽ  ‹‹ የኢትዮጽያ ! ›› የሚል ይሆን ነበር ፡፡ ሻዕቢያና ኢህአዴግ ደግሞ ከጫካቸው ሆነው የተለየና የሰለለ ድምጽ ያሰማሉ ፡፡
ጥያቄው የተጠየቀው ግን በ2003 ዓ.ም ሆነ ፡፡
ጠያቂው ዶክተር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ናቸው ፡፡
አጠያየቁ ይፋዊ ነው ሊባል ይችላል - በመጽሀፍ መልክ ስለወጣ ፡፡

እና ምን ምላሽ አለ ?

ሻዕቢያና ኢህአዴግ ከከተማ ሆነው ደማቅና ይፋዊ ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡ ‹‹ የኤርትራ ! ›› በማለት ፡፡ ቁጥሩን በቀላሉ ማሰላት የሚያስቸግር  ህዝብ  ልብ ውስጥ   ‹‹ የኢትዮጽያ ነበረች ?! ›› የሚል የሰለለ ድምጽ ይሰማል፡፡  ድምጸቱ  የፈሰሰ ውሃ አይታበስም የሚባለውን ብሂል የሚያቀነቅን ይመስላል ፡፡ ሀገራችን ውስጥ የነበሩ ጠንካራ ፓርቲዋች ምርጫ በመጣ ቁጥር አሰብን ወደ ኢትዮጽያ ግዛት ለመመለስ እንደሚጥሩ በክርክራቸው ወቅት ያሰሙ ነበር ፡፡ እና ቢያንስ  አሪፍ ቴርሞሜትሮች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የባህር በራችን … ባሉ ቁጥር የብዙዋች የሙቀት መጠን ጣራ ያልፍ ነበርና፡፡ ይህን መለኪያ አጥኚዋች እንደ አንድ ግብዓት ቢያስተውሉት ሊጠቅም ይችላል፡፡

ዶ/ር ያዕቆብ የአሰብ ጉዳይ የፈሰሰ ውሃ ውሃ ሳይሆን የተዳፈነ እሰት ነው ባይ ናቸው ፡፡ ከኤርትራ ጋር በቦሌም ሆነ በባሌ የማትገናኘው አሰብ በስጦታነት የቀረበችው  ኢ-ፍትሃዊ በሆነ አግባብ ነው ይሉናል፡፡ አሰብን ማጣትና የባህር በር ተጠቃሚ አለመሆን በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በጦርነት የሚያስከትለውን ተጽእኖ ይተነትናሉ፡፡ የኢትዮጽያን የባህር በር ባለቤትነት ታሪክ ሳያወላዳ የሚመሰክር ሲሆን በተለያዩ ግዜያቶች በወራሪዋች ቦታው ሲያዝ ከአጼ ቴዋድሮስ ጀምሮ እስከ መንግስቱ የተደረጉ ያላሰለሱ ጥረቶችን በምሳሌነት ያቀርባሉ፡፡ በአልጀርስ ስምምነት ወቅት ኢትዮጽያ የባህር በር የማግኘት እድሏ ሰፊ የነበረ ቢሆንም ፍላጎት ባለማሳየቷ እንዳማረን ቀርቷል ሲሉም ይቆጫሉ ፡፡

እንግዲህ የዶ/ር ያዕቆብ የ ‹‹ አሰብ የማን ናት ? ›› ጥያቄ የተወረወረው ጉዳትን፣ መብትን፣ ታሪክን  ከሁሉም በላይ የህግ ጽንሰ ሀሳብን በማዘል ነው ፡፡ በ13 ምዕራፍ የተዋቀረው ይህ መጽሀፍ ኃይለኛ አጠያያቂ ሙግቶችን ይዟል ፡፡ እንተንትነው ፤

ኢኮኖሚያዊ በልሐ ፣

በቦሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ እቺ ከድህነት ተርታ የተሰለፈች ሀገር ዛሬ በቀን ሶስት ሚልዮን ዶላር ለጅቡቲ ወደብ ኪራይ ትከፍላለች ፡፡ ይህ አኀዝ እውነት ከሆነ ትንፋሽን ቀጥ ሊያደርግ አሊያም አጥወልውሎ ሊደፋ ይችላል ፡፡ ይህን ቁጥር በ265 ቀናት ስናባዛው 795 ሚሊዮን ዶላር ይሰጠናል ፡፡ ይህን የሚያሰጎመጅ ዶላር በጥቂቱ በ17  ስናበዛው ቁልጭ ያለ 13 ቢሊዮን 515 ሚሊዮን የኢትዮጽያ ብር እናገኛለን፡፡

የሀገራችን የ2005 በጀት 137.8 ቢሊዮን ብር ነው ፡፡ እንግዲህ ለወደብ የሚከፈለው ገንዘብ የበጀቱን አስር ከመቶ ያህል ይቆርሳል ማለት ነው፡፡ ቋንቋችንን ወቅታዊ እናድርገው ካልን የወደቡ ክፍያ በስድስት ዓመት ውስጥ የሚሊኒየሙን ግድብ ወጪ ይሸፍናል፡፡ ዶ/ር ይዕቆብ ደግሞ ሃያና ሰላሳ ፋብሪካዋችን ሊገነባ ይችል ነበር ይሉናል፡፡ ቻውድሪ እና ኤርዳነቢልግ የተባሉ ምሁራን ባደረጉት ጥናት ወደብ አልባ አገሮች በኢኮኖሚ ዕድገት በ1 ከመቶ ወደብ ካለው አገር ወደ ኃላ ይቀራል፡፡ ይህ ማለት ወደብ ያለው አገር በ24 ዓመት ውስጥ ኢኮኖሚው በእጥፍ እንዲያድግ 36 ዓመታት ይፈጅበታል፡፡

ሌላው ነጥብ የወደብ ርቀትን ይመለከታል፡፡ በመሰረቱ ለኢትዮጽያ ከሞምባሳ፣ ፓርት ሱዳን፣ ሞቃዲሾ፣ በርበራና ከጅቡቲ ይልቅ ይቀርባት የነበረው የአሰብ ወደብ / ከአ.አ 624 ኪ.ሜ / ነው፡፡ በሌለ ነገር ላይ ማውራት አጉል ግፍ ነው ካልተባለ በስተቀር የወደብ ርቀት መፈጠር በኢንቨስትመንት ላይ  ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡ በሀገራችን የኢንዱስትሪም ሆነ የእርሻ ውጤቶች የሚመረቱት በመሃልና በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ስለሆነ ምርቶችን ወደ ወደብ ለማዝለቅ ብዙ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ከባድ ዕቃ ለማምረት ለሚፈልግ ኢንቨስተር ወደብ አልባዋ ኢትዮጽያ የመጀመሪያ ምርጫ አትሆንም፡፡

የበልሃው ምላሽ፣

በአንድ ወቅት ጠ/ሚ መለስ ለዶ/ር ያዕቆብ ስጋት ለሆነው ሃሳብ ቀጣዩን ምላሽ ሰጥተዋል  ‹‹ ወደብ አለመኖሩ ረሃብ አያመጣም፡፡ በጎረቤት ሀገር ወደብ በመጠቀም መስራት ይቻላል፡፡ ያለ ነገር ነው፤ ስለዚህ ኢትዮጽያ ያለ ወደብ ቀረች ብለን የምንቆጭበትና የምናዝንበት ምክንያት የለም፡፡ ወደብ አለመኖሩ አይጎዳንም ፣ ሊጎዳንም አይችልም፡፡ ወደብ በነበረን ግዜ ኢትዮጽያ ድሃ ነበረች ፡፡ አሁን ወደብ የለንም፡፡ ዕድገት ግን እያስመዘገብን ነው ››

ዲፕሎማሲያዊ በልሃ፣

አረቦች ከብዙ ግዜ ጀምሮ ብቸኛ የቀይ ባህር ተቀናቃኛቸው የነበረችውን ኢትዮጽያ ከባህሩ አካባቢ አግልለው ቀይ ባህርን የአረብ ሃይቅ ለማድረግ ሲታገሉለት የነበረውን ዓላማቸውን አሳክተዋል፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ በቀይ ባህር በተለይ በአሰብ የኑክሌር መሳሪያ ቢጠመድበትና የጠላት ጦር ቢሰፍርበት፣ ለህልውናችን ስጋት የሚፈጥር ሁኔታ ቢጠነሰስ  ልታደርገው የምትችለው ነገር አይኖርም ይላሉ፡፡

ወታደራዊ በልሃ ፣

ግራና ቀኝ በጠላት የተከበበቸው ኢትዮጽያ ራሷን ለመከላከል የሚያስችል የጦር መሳሪያ ከውጭ በባህር ማስገባት የግድ ይላታል፡፡ ይሁን እንጂ ባለ ወደብ ሃገሩ ከፈለገ ይህን ያህል ብቻ ይበቃሃል ብሎ ማስተላለፍ ላይ ገደብ ሊጥልበት ይችላል፡፡ እናም የሉዓላዊነት ገዳይ ዘወትር በቋፍ ላይ ይንጠለጠላል ማለት ነው ፡፡

ወረራም ሌላው ስጋት ነው ፡፡ ጄኔራል ናፒዮር አጼ ቴዋድሮስን ለመውጋት ወደ ሀገራችን የገባው በቀይ ባህር ወደብ ነው፡፡ ወራሪዋች ከስትራተጂክ አንጻር ከየብሱ ባህሩን ይመርጣሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የቀለለ ስለሆነ ነው ፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ በስፋት ያነሱት ሌላው ነጥብ የባህር በር ባለቤትነትን ይመለከታል፡፡ ይህም አሰብ የኛ አይደለችም የሚሉ ወገኖችን ጠንከር ያለ መረጃ ለመስጠት አሊያም የተጨፈነ ልቦናን ገርበብ ለማድረግ ያለመ ይመስላል፡፡

ኢትዮጽያን የባህር በር ባለቤት ያደረጓት አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ናቸው፡፡ ግዜው ደግሞ ከ1434- 1468 መሆኑ ነው፡፡ ከዚያም በኃላ በቱርኮች፣ ግብጾችና ሌሎች መቀማማቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን አፍሪቃን ለመቀራማት ሰፊ ዘመቻ ካካሄዱ በኃላ ደግሞ ጠንከር ያሉ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ በተለይም ጣሊያን በእንግሊዝ ሃይ ባይነት ያለምንም መከላከያ ትገኝ የነበረችውን ምጽዋ በ1885 ዓ.ም በቁጥጥር ስር አደረገች፡፡ ኮሎኔል ሳሌታ 802 ወታደሮችን ብቻ ይዞ ነው የገባው፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ ቄስ ጁሴፔ ሳፒቶ የተባለ ጣሊያናዊ አሰብን አሁንም ያለማንም ከልካይ ከገዛ ከአስር ዓመታት በኃላ የተፈጸመ ነው፡፡ ይህ ቄስ ለሩባቲኖ ኩባንያ አሰብንና አካባቢውን በ8100 ማርያ ቴሬዛ የገዛው ከአካባቢው ሱልጣኖች ኢብራሂምና ሱልጣን ሀሰን በን መሀመድ ነበር፡፡ አሰብን ከነነፍሷ ሲሸጡ በሙቀቱ ምክንያት ብዙም ክትትል የማያደርገው የኢትዮጽያ መንግስት አያውቅም ነበር፡፡ አሰብ በወቅቱ ትስስርዋ ከወሎ እንጂ ከኤርትራ ጋር አልነበረም፡፡

እናም ጣሊያኖች ግዛታቸውን በማጠናከር  ‹‹ የአሰብ የኢጣሊያ  ቅኝ ግዛት ››  ይባል የነበረውን ስያሜ በመሻር  ‹‹ በቀይ ባህር የኢጣሊያ የቅኝ ግዛቶች ››  በሚል አሻሻሉት፡፡ የአሰብና የምጽዋ ግዛቶቻቸውን በማጠቃለልም በ1890  ‹‹ ኤርትራ ››  የሚል ስም ሰጥተው ቅኝ ግዛት መሰረቱ፡፡ ጣሊያኖች ለግዛታቸው ሲሉ ሁለት በባህል፣ ቋንቋ፣ ዘር ወዘተ የማይገናኙትን ሀገሮች በመጨፍለቃቸው እነሆ እስከዛሬም ግርታና ክርክር እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡
በርግጥ ኢትዮጽያ የሰሜን ግዛቶችዋና ጠረፎቿ በ1895 ዓ.ም በቱርኮች፣ በግብጾች፣ በጣሊያኖችና በፈረንሳዮች ሴራ ከተያዙባት ግዜ ጀምሮ የባህር በሮችዋን ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡

ማስረጃ - ቴዋድሮስ፣

አጼ ቴዋድሮስ እኤአ በ1855 ለንግስት ቪክቶሪያ ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡ ‹‹ ቱርኮች የአባቶቼን መሬት ልቀቁ ብላቸው እምቢ ብለውኝ በእግዚአብሄር ኃይል ይኀው ልታገል ነው …. ››

ማስረጃ - ዮሐንስ ፣

አጼ ዮሀንስ አራተኛ ስልጣን ላይ ሲወጡ የባህር በሮችዋ በወራሪዋቹ ተነጥቆ ሙሉ በሙሉ ወደብ አልባ ነበረች፡፡ እሳቸው ሰኔ 10 ቀን 1872 ለእንግሊዝ ንግስት የእርዳታ ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡
‹‹ …. ጥንቱንም በእግዚአብሄር ፈቃድ ለመንግስት የበቃሁት እርስዋ በሰጡኝ መድፍ፣ ነፍጥና ባሩድ ነው፡፡ ….. የምጽዋ በር የአባቶቼ የነገስታት ኢትዮጽያዊያን ነው፡፡ አሁንም በእርስዋ ወኪልነት እርዳታ የምጽዋን እንድይዝ ያድርጉልኝ ብዮ እለምናለሁ …. ››

ማስረጃ - ሚኒሊክ ፣

ሚኒሊክ የግዛታቸው መጠንና የሀገሪቱ ወሰን የት ድረስ እንደሚያካልል ለዓለም መንግስታት ለማስታወቅ ለንግስት ቪክቶሪያ  ‹‹ ከሃምቦሳ አንስቶ የአስልን ባህር ጨምሮ የጥንት ዜጋችን የሞሀመድ ሃንፍሬን / አፋርን ያስተዳድሩ የነበሩ / ግዛት ሙሉ ይዞ እየሄደ አረፋሊ ይደርሳል ››  የሚል ደብዳቤ ጽፈው ነበር ፡፡

በንግስት ዘውዲቱ፣ በአጼ ሃይለስላሴና በመንግስቱ ኃ/ማርያም ስርዓትም የባህር በርን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዋች መሰራታቸውን የዶ/ር ያዕቆብ መጽሀፍ ይተርካል፡፡ ዞሮ ዞሮ ኤርትራ በ1952 ዓ.ም በኤርትራ ህዝብ ተወካዮች ፍላጎትና በተመድ ውሳኔ ከኢትዮጽያ ጋር በፌዴሬሽን ስትቀላቀል ለዘመናት ትግል ሲደረግለት የነበረው የባህር ጥያቄም ምላሽ አገኘ፡፡ ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ውህደት ሲደረግ ሁለቱም ወደቦች የኢትዮጽያ ሉዓላዊ ግዛት ሆኑ፡፡ ይህ ድል በተገኘ በማግስቱ ግን የፌዴሬሽኑ መፍረስ የኤርትራን የመገንጠል ጥያቄ አስነስቶ ሻቢያ፣ ጀብሃ በኃላም ህወሃት ከኢትዮጽያ ነጻ ለመውጣት የትጥቅ ትግል ጀመሩ፡፡
እንግዲህ እነዚህን ጥረቶች ነው ህውሃትና ኢህአዴግ ለመሰረዝና ከናካቴው ለማጥፋት ሲታገሉ የነበሩት ይሉናል - ዶ/ር ያዕቆብ ፡፡ በተለይም አቶ መለስ በ1979 ኤርትራን አስመልክቶ በጻፉት መጽሀፍ ኤርትራ የኢትዮጽያ ቅኝ ግዛት ነች ማለት ትክክለኛና ሳይንሳዊ ነው … ኢትዮጽያ የ3 ሺህ ዓመት ታሪክ የላትም በማለት በግልጽ ጽፈዋል፡፡ በዚህ አባባል ኢትዮጽያ የአክሱም ወራሽ ልትሆን አትችልም፡፡ ጥንታዊ የባህር በርም ሊኖራት አይችልም ፡፡

በመሆኑም ህወሃት/ኢህአዴግ የኤርትራን መገንጠል የደገፈው ኤርትራ የኢትዮጽያ ቅኝ ግዛት ነች ከሚል እምነት በመነሳት ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዋች በካይሮ ጉባኤ ያሳለፉት የድምበር ውሳኔ የአፍሪካ አገራት ነጻ ሲወጡ በቅኝ ግዛት ግዜ የነበረው ወሰን ተከብሮ ነው ይላል፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ አባባል ጋር መመቻቸቱም ተገልጾል፡፡

በርግጥ ዶ/ር ያዕቆብ ቅኝ ግዛትን በተመለከተ ትልቅ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የቅኛ ገዢዋች ዓላማ በተገዢዋቹ ኪሳራ ለመበልጸግ፣ የሃይማኖትና የፓለቲካ እምነታቸውን ለማሰፋፋት፣ ባህልና ስብዕናቸውን ለማንቋሸሽ፣ የጌታና የሎሌ ግንኙነት እንዲመሰረት ማድረግ ነው፡፡

ታዲያ በሁለቱ ሀገሮች የነበረው ግንኙነት ከላይ የተገለጸውን ብይን ይመስል ነበር ? ኢትዮጽያዊያን የትኛውን የኤርትራዊያን መሬት ነው የቀሙት ?  ከዚህ  ይልቅ በፍቅር  ተዋልደው ኖረዋል፡፡ ኤርትራዊያን ባላቸው አቅም ሁሉ ከፍተኛ ስልጣን አግኝተዋል፡፡ እናም የኢትዮጽያ አካል የነበረችውን ኤርትራ ቅኝ ግዛት ነበረች ማለት ትንሽ እውቀት አደገኛ ነው ከሚባለው አባባል የመነጨ ነው ይላሉ - ዶ/ሩ፡፡

ኢትዮጽያ ከኤርትራ ጋር ጦርነት አድርጋ ካሸነፈች በኃላ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቦታዋች ይዛ ነበር ፡፡ በዓለማቀፍ ህግ ደግሞ ተወራሪ ሀገር ጠላቱን ካሸነፈ በኃላ ግዴታ ውስጥ ማስገባት የሚችልበት አጋጣሚ አለ፡፡ ከዚህ ግዴታ አንዱ የአሰብን የባህር በር ማስመለስ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ይህ ግን እንዳይሆን ተድርጓል፡፡ እንደውም በአልጀርስ ስምምነት አሰብና ሌሎች ቦታዋች ለእኛ እንዳይወሰኑ ብዙ ስህተቶች ሆን ተብለው እንዲፈጠሩ ተደርጓል ባይ ናቸው፡፡

-       ስምምነቱ የተፈረመው  ኢትዮጽያና ጣሊያን በ1900፣ በ1902 እና በ1908 በተፈራረሟቸው የቅኝ ግዛት ውሎች መሰረት ነው፡፡ በወቅቱ አጼ ሚኒሊክ ውሉን የፈረሙት ተገደውና ጫና ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ስምምነት በህግ ፊት ዋጋ እንደሌለው እየታወቀና ለማሸነፍ አማራጭ መፍትሄዋችን መጠቀም እየተቻለ በዛው ውል እንከራከራለን ተብሏል፡፡ ይህም አሰብን ለኤርትራ የሰጠ ምቹ ስምምነት አድርጎታል፡፡

-       በስምምነቱ ወቅት ኢትዮጽያን ከወከሉት ተደራዳሪዋች መካከል በህግ አማካሪነትና በጥብቅና ዘርፍ የተሰማራ ኢትዮጽያዊ ሰው አልነበረም፡፡

-       የድርድሩ  ዋና  አጋፋሪ ሚስተር አብዱል አዚዝ ቡተፍሊካ አልጄሪያ ከሻቢያና ከጀብሃ ጋር ለነበራት ግንኙነት ፓሊሲ ቀራጺና ለኤርትራ መገንጠል ሌት ተቀን የሰሩ ሰው መሆናቸው እየታወቀ በዝምታ ታልፏል፡፡

-       የድንበር ውዝግብ በሚፈጠር ግዜ ሀገሮች ጉዳያቸውን ወደ ዓለም አቀፍ ፍ/ቤት ይወስዳሉ፡፡ ይህ ፍርድ ቤት በቅኝ ግዛት ውሎችን ብቻ ሳይሆን ዓለማቀፍ ስምምነቶችን፣ የተደረጉ ውሎችን፣ የፍርድ ቤት ውሳኔዋችን ፣ የህግ ልሂቃን የጻፏቸውን ጽሁፎች በሙሉ ይመለከታል፡፡ ሂደቱ ባለቀ ግዜ ያልቃል እንጂ አያጣድፍም ፡፡ሆኖም ወደዚህ ፍ/ቤት መሄድ አልተፈለገም ፡፡

ዶ/ር ያዕቆብ እነዚህን ማስረጃዋች አንድ ሁለት እያሉ ይዘርዝሩ እንጂ በመንግስት በኩል አሰብን በተመለከቱ የተሰጡ ምላሾች የማያወላዱ ናቸው፡፡ የአሰብ ወደብ የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት በመሆኑ የኛ ጥያቄ ውስጥ የለም የሚል፡፡

መጽሀፉ በመጨረሻው ምዕራፎች አማራጮችን ይገልጻል፡፡ ከአማራጮቹ አንዱ አሰብን ሁለቱም ሀገሮች በጋራ ይዘውት ሁለቱም ጣምራ ሉዓላዊነት / joint sovereignty / እንዲኖራቸው ሊስማሙ ይችላሉ የሚል ነው ፡፡ ለዚህም ደግሞ ህንድና ፓኪስታን የሚፋጠጡበት የካሽሚር ግዛት፣ ፈረንሳይና ስፔን ለ700 ዓመታት የሚያስተዳድሯትን አንዶራ የተባለች ሀገር በምሳሌነት ያስረዳሉ፡፡

የዶ/ር ያዕቆብ በልሀ ልበልሃ ፣

ኢትዮጽያ የባህር በርዋ አሰብ እስካልተመለሰላት ድረስ ኢህአዴግ ከየትኛውም በጎም ይሁን መጥፎ ስራዋች የባህር በር ማዘጋቱ ከሁሉም በላይ ጎልቶ ይወጣል፡፡ አሰብ ለኢትዮጽያ እስካልተመለሰ ድረስ ዘመናት አልፈው ዘመናት ሲተኩ በግዜው ኢህአዴግ ማን ነበር ሲባል መልሱ መንገዶችን፣ ት/ቤቶችን ወይንም ሀኪም ቤቶችን ያነጸው አይሆንም ፡፡ መልሱ የኢትዮጽያን የባህር በር ያዘጋው መንግስት ነው የሚሆነው፡፡

እውነት ይህ ጥያቄ በይርጋ ይታገዳል ?
እውነት ይህ ጥያቄ ከመጠየቅ ያመልጣል ?
እውነት ይህ ጥያቄ የተለየ ምላሽ ያገኛል ?










Friday, June 15, 2012

‎ከምናብ ጋር መነጋገር‎


በሃሳብ ተቀፍድጄ… በጭንቀት ናውዤ… ውል ያለው ጉዳይ መጨበጥ ሲያቅተኝ እንደተጫነች አህያ እተነፍሳለሁ፡፡ አንድ የዳጎሰ የኪነጥበብ ማዕድን ፈልፍሎ ለማውጣት ውስጤ በሃሳብ ትራክተር ይታመሳል፡፡ ጉቶው - አለቱ ይተረማመስ እንጂ እንደ ምንጭ ኮለል ብሎ በእርጋታ የሚፈስ ምናባዊ ውጤት ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ግም…ግም…ጓ… የሚል ባዶ ጩኸት ብቻ፡፡ እንደሚመስለኝ ትራክተሩና ምናቤ ይገጫጫሉ፡፡ ምናልባትም የጉቶው ስለት ስብዕናዬን ሲወጋው እባንናለሁ፡፡ ይሄኔ ይጨንቀኝና በረጅሙ እተነፍሳለሁ፡፡  ትንፋሼ ከበስተኃላዬ በስሱ ሲንኳኳ የሚሰማውን ባዶነቴን ውጦ ለማስቀረት እንኳን አልታደለም፡፡

 እ . ፎ . ይ .  !   ብቻ ፡፡
 የተወጣጠረ ግን የማይቀደድ ትንፋሽ ፡፡

ከጠባቧ ምናቤ እወጣና ጠባቧን ቢሮዬን እቃኛለሁ፡፡ አንድ ብልጭታ አገኝ ዘንድ ፡፡ ኮርኒሱን… አምፖሉን… ግድግዳ ላይ የተለጠፉ ስዕሎችን… የቢሮ ተጓዳኞቼን አንድ በአንድ እቃኛለሁ፤ እመረምራለሁ፡፡ ድንገት አይኔ ኮርኒስ ላይ ሲቀር እንደሚከተለው አስባለሁ፡፡

‹ ከኮርኒሱ ጀርባ አይጥ ብትኖር… ከሰው ጋር የምታደርገውን ግብግብ ፣ ውጣ ውረድ ፣ ድብብቆሽ ፣ ብልጠቷንና ቅልጥፍናዋን ብቀርጽ … ›

‹‹ ኮርኒሱ አልተቀደደ ! ድርጊቱን የምትስለው በተጨባጩ ምልከታ ወይስ በአይነ ልቦና ጉዘት ? ማን ነበር ካላየሀው በመነሳት አትቀባጥር ያለው ? በርግጥ የአይጥና የጦጣ ብልጠት ዓለማቀፋዊ በመሆኑ የተረት ተረቱ መነሻነት በቂ ይሆናል፡፡ ግን በየትኛው ፍጥነትህ ነው እንደርሷ ከአንዱ ማዕዘን ወደ ሌላኛው ሸረረረር …. የምትለው ? ››

ምናቤ ሲጠይቀኝ ‹ ይህ አንፖል › ስል አንሰላስላለሁ

 ‹ ብርሃኑና ሊፈጥር የሚችለው ተምሳሌት ዕጹብ ነው፡፡ ከጀርባው ምን ሊጠና ይችላል ? ስታርተር ? ስታርተር የፈጠራ አብነት ነው፡፡ ይህን አስፈላጊ ነገር ማን ፈጠረው ? ቶማስ አልፋ ኤዲሰን ? ›

‹‹ ከዛስ ?! ›› ይለኛል የሆነ ድምጽ

‹ ኤዲሰን ማነው ? በህጻንነቱ ረባሽ ነበር ወይስ የልጅ አዋቂ ? ምን ያህል ግኝቶች አበርክቶ ይሆን ? ›

‹‹ ለምን ትጃጃላለህ ?! ››

‹ ምነው ? ›

‹‹ መጻፍ የፈለከው ታዋቂ ሰዋችና ስራዋቻቸው ነው ወይስ ወጥ ፈጠራ ? ››

ቢሮው ግድግዳ ላይ የተለበጡት ስዕሎች ያማምራሉ፡፡ በአንድ በኩል በውስጥ ቁምጣ ብቻ የሚታዩ ቆነጃጅት በሌላ በኩል የተፈጥሮ ውበት ያማልላል፡፡ ከኮረዶቹ ጀርባ ምራቅ የሚውጡ ሰዋች፣ የፈዘዙ ዓይኖች ሊታዩ ይችላሉ፡፡

‹  እርስ በርስ እንዲቦጫጨቁ ቢደረግስ ?!  ቢያሻ ተፈጥሮን እንደ ጨው መነስነስ፡፡ ተራራው፣ ወንዙ፣ ደኑና አየሩን በብዕር እጆች መኮርኮር፡፡ ከዚያም ውበት፣ ተፈጥሮና አድናቆቶችን በአንድነት ማሰናሰል ፤ በልዩነቱ ደግሞ ማገጫጨት  ›

‹‹ ከግጭቱ ምን እንዲመዘዝ ነው ያቀድከው ? ትግሉና ውጤቱ የሚፈጥሩትን ህብረ ቀለም ታውቀዋለህ ? ያ ነገርስ አዲስነት እንዳለው ርግጠኛ ነህ ? ››

ደግሞ ሲጨንቀኝ ጓደኞቼን እቃኛለሁ፡፡ አቀርቅረው ይጽፋሉ፡፡ አፍላፍ ገጥመው ያወራሉ፡፡

‹ እንደ መልካቸው ባህሪያቸውም ይለያያል፡፡ እና ለተለያዩ ገጸ ባህርያት ምስል ብጠቀምባቸውስ ? ሴራ፣ መዋቅር፣ ቅብርጥሶ ከሚባለው ድንጋጌ ጋር ማዋሃድ … ለውህደቱ ግዜ ጠብቆ የፈጠራ እንጀራ መጋገር፡፡ መቼም በከፊል አውቃቸዋለሁ ፡፡ የሳቃቸው ለዛ፣ የግንባራቸው ሙዝዣ ምንነታቸውን ሹክ አይለኝ ይሆን ? ይሄኛው ውጫዊ መገለጫ ነው፡፡ ለታሪኩ ፍሰት ግን ውስጣዊ እምነታቸውና አመለካከታቸው ነው ወሳኙ ፡፡ ማነው እኩዩ ? የቱ ነው ሰናይ  ? ሽርጉድ አብዢው  ? አፋሽ አሽርጋጅ ?  ከኔ ወዲያ ላሳር ባዩስ ? አውቆ የተኛው ? ስራን ያጌጠስ  ? በርግጥ ይህን ብቻ ማወቅ ለጀርባ ንባብ በቂ ነው ? ማህበራዊ ትስስር ፣ ከቢሮ ውጭ ያላቸው ማንነት… ይህን ሁሉ ግትልትል መረጃ ማሰባሰብ አስፈላጊ ነው ለካ  ! አዲዮስ !! ቁንጽል ነገር ይዞ መንጦልጦል ሰፊው የጭንቀት ባህር ውስጥ ይዘፍቃል ›

‹‹ለምን አርፈህ ቁጭ አትልም ?! ››

‹ ለምን ተብሎ ? ›

‹‹ ጥሩ ፈጣሪ ሳይሆን ጥሩ አንባቢ መሆን ይቻላላ ! ምናብህ ያምጣል፤ የመፍጠር ነጎድጓድ ያሰማህ እየመሰለህ ብዕር ትቀስራለህ ፡፡ ጩሐቱ ግን ዳመና ያላዘለ ነው ፡፡ ያለ ዳመና ጠብታ አይኖርም ፤ ምናብህ ውስጥ ያሉ ሴሎች ጠብታ ! እያሉ ወደ ላይ ያንጋጥጣሉ ፡፡ የደረቀው አፋቸው ጫማ አይቶ እንደማያውቅ እግር ተሰነጣጥቋል፡፡ ስንጥቁ ውስጥ የገባው ለሃጭ እንደ ደም ረግቶ ይኮሰኩሳቸዋል፡፡ ያካሉ፡፡ ጠ . ብ . ታ . ! ጩኀታቸው እንደ ነጎድጓድ ይባርቃል፡፡ አጅሬ ምናቤ ውስጥ ትራክተር አለ እያልክ ታወራለህ ››

‹ ወዲያ ! የማይረባ ፍልስፍና አትደስኩር ! ስሙን ያላስታወስኩት አንድ ደራሲ አዕምሮህ ታጥኖ ያልተቀመጠ ጋን ከሆነ አርፈህ ተቀመጥ ይላል፡፡ እንደ ገ . ዱ ሞፓስ ያሉ ደግሞ ጭንቅላት የጠጅ መጥመቂያ ይመስል ሁሌ በወይራ መቀቀሉን አይቀበሉም፡፡ ስላዩት ይጽፋሉ፡፡ አንዳንድ የዛፍ አይነቶቸን በመጥረቢያ ስለቀጠቀጥክ ብቻ አይፈለጡም፡፡ ውርወራህ ብልቱን ካገኘው ዛፉ የኮረኮሩት ያህል ፈከክ ይላል፡፡ እና የተዋበ ፈጠራ ለመስራት አያሌ መጻህፍትን መዋጥ ወይም አሊያም የኮሌጅን በር ማንኳኳት የግድ አይደለም፡፡ አነስተኛ ዕውቀትም ቢሆን ቦታ አለው፡፡ ዋናው ግብ እውቀቱ ከብርቱ ፍላጎት ጋር የሚቀጣጠልበትን የትጋት ፈንጂ ማጥመድ ነው፡፡ በርግጥ እስኪፈነዳ ድረስ ያለህን ስሜትና ፍርሃት በትክክል ለመመዝገብ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ሲፈነዳ በፍርሃት አብሮ የመፈንዳቱን ሰዋዊ ባህሪ ተቋቁሞ ተፈላጊውን ጭብጥ ለማሳየት በመጀመሪያ የጀገነ ሀሞት ለጥቆ ያልጎለደፈ ብዕር ካለህ ሁሉ ነገር አለቀ ›

‹‹ ከዛስ ? ›› የሹፈት ድምጽ

‹ የአፍዝ የአደንግዝን ለመንቀል ፈንጂ መጠመዱ ለምን አስፈለገ ማለት የዋህነት ነው ፡፡ ማለት ያለብህ ዘመቻ አንድ እንጂ ! በዘመቻ ሁለት ራስንና ሌሎችን መመልከት፡፡ ከተናጥል ግንዛቤና ልምድ፣ ከማህበረሰባዊ ትዝብትና ገጠመኝ… እንዲህ እንዲህ ከሚሰኙ አብነቶች በመነሳት የዳበረ ጭማቂ ለመፍጠር መጠበብ ፡፡ ይህ ማለት ምንም ማለት አይደለም፡፡ የምታየውን በሚገባ ማስተዋል፡፡ በተለያዩ ሁኔታና ለሰሜት ቅርበት ያላቸውን ድርጊቶች መዝግቦ መያዝ ፣ በተለይ የተመዘገቡ ድርጊቶች ምን ሊወጣቸው እንደሚችል ስትሄድ ስትቀመጥ ማንሰላሰል… የድርሰት ኩታን ለማበጀት በምናባዊ ቀሰም ማዳወር … እስኪሞሉ መግመድ… እንደገና መፍታት … በይሆናል አይሆንም እሳቤ መዋቅሩን ማዳበር … የሴራው ጡዘት እንደ ዕለት ከእለቱ ደውር እንዲከር እድል መስጠት… በመጨረሻም መጻፍ ፡፡ ይኀው ነው ፡፡ ›

‹‹ ወይ ይኀው ነው ! ጥሬ ሀሳብ ሳይገረደፍ፣ ሳይሰለቅ፣ ሳይደለዝ ኪነጥበባዊ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም ፡፡ መወሰንማ መች ይገዳል ? ድርጊትንና ምናባዊ ምጥቀትን ማቆራኘት እንጂ ፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ አያሌ መሰናክሎች ሊያጋጥሙ ያችላሉ ፡፡ ያልተረጋጋ መንፈስ ይዞ ብእር መጨበጥ የመሸከም ያህል ይከብዳል ፡፡ በዚህ መልኩ ማዕድን ቆፍሬ አወጣለሁ ማለት አይቻልም ፡፡ ››

‹ ለምን አይቻልም ? የሚቆፈረውም እኮ ይኀው ነው፡፡ ያልተመቸውን ፍቅር… የተጎሳቀለ ህይወትን… የገረጣ ረሃብን… በአጠቃላይ እንግልት ሲያቅስት መሳል፡፡ ይህ ነጸብራቅ ለሌሎችም ይሆናል ፡፡ ›

‹‹ ግን ለማን ብለህ ነው እርስ በርስህ የምትገጫጨው ? ነጋ መሸ የምታቃስተው  ? ፈጥሮ ያለፈለትስ ማነው  አንዳንዶች ለህሊና ርካታ ይላሉ ፤ እኔ ደግሞ የማይጥም መዘየጃ እለዋለሁ ፡፡ በቃ ተወው ! ተራ ፈጣሪ ሆኖ በጉራ ከማበጥ እጅን ለሽንፈት መስጠት፡፡ ››

‹ ግን እኮ የፈጠራ ትርፉ ጭንቀት ብቻ አይደለም ፡፡ ለሌሎች ቤዛ መሆንንም ያሳያል፡፡ ግን እኮ እንደዛ ፍልጥ እንጨት ብልቱን ካወክ ሁሉም ነገር ወከክ ነው የሚለው ! ›

‹‹ ይህን ሚስጢር ለማወቅ  ታዲያ ተራራ መናድ ይጠበቃል እኮ ?! ››

‹ በቃ ጭንቀት ወደዚያ !!!  -  ውጥረት ገለል በል !!! ›

Sunday, June 10, 2012

‎የአከራካሪው አባት ‹ ፕሮፋይል ›‎




‹‹ ሐውልት እንደቆመላቸው አያውቁም ነበር፡፡ ሐውልቱን ለመመረቅ ሲመጡ እንኳን ሌላ ዝግጅት እንዳለ ተደርጎ ነበር የተነገራቸው፡፡ ሪቫኑን በመቀስ ቆርጠው የተሸፈነውን ሲከፍቱት በጣም ደነገጡ፡፡ ››
ከቆይታ ቅጭምታ በኃላ የሚከተለውን በሀዘን የተዋጠ ንግግር አደረጉ
‹‹ ይህ ነገር ለእኔ አይገባኝም፡፡ ምን ስላደረግኩ ?  ማን ነኝና ? ››
ትህትናው ደስ ይላል ፡፡ የዚህ ንግግር ባለቤት ገ/መድህን ገ/ዮሐንስ ናቸው፡፡ ይህ ስም ግር ካላችሁ ብጽአ ወቅዱስ አቡነ ጻውሎስ በሚል ማስተካከል ትችላላችሁ፡፡

አከራካሪ ሀሳብ፣ አከራካሪ መጽሀፍ፣ አከራካሪ ፓለቲከኛ እንዳለ ሁሉ አከራካሪ የሃይማኖት አባትም አለ፡፡ አቡነ ጻውሎስ ምናልባትም ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ በህይወታቸውና በስራቸው ዙሪያ ሰሜንና ደቡብ ጫፍ የሚረግጡ ሀሳቦች በየሰፈሩ፣ በሚዲያ ፣ በየገዳሙ፣ በአምልኮ ስፍራዋች ሁሉ ተነግረዋል፡፡ ዛሬም እየተነገሩ ናቸው ፡፡

ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ግን በዓለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዝናና አክብሮት ያላቸውን አቡነ ጻውሎስ ሀገሬው ሊያከብራቸው ወይም ሊረዳቸው አልቻለም ባይ ናቸው፡፡ የዛሬውን አያድርገውና ወ/ሮ እጅጋየሁ የታዋቂው አቀንቃኝ መሀሙድ አህመድ ባለቤት ነበሩ፡፡ እናም እሳቸው ራሳቸው በአንድ ወቅት ብዙ ያነጋገሩ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እጅጋየሁ ይህን ጠንካራ መግለጫ ያስተላለፉት በመገናኛ ብዙሃን አይደለም - በመድብል እንጂ፡፡ ጥር 2004 ያሳተሙት መጽሀፍ  ‹‹ በሃይማኖት ሽፋን እስከ መቼ ? ›› የሚል ርዕስ አንግቧል፡፡ ጸሀፊዋ ለአቡነ ጻውሎስ በቆመው ሀውልት ዙሪያ የሚሰጠው የተሳሳተ አስተያየት እንዳስቆጫቸውና የእውነታውን ምስል የማሳየት ተልዕኮ በማንገብ ይመስላል ብዕራቸውን ያጠበቁት ፡፡

ይህን ለማስረዳት ደግሞ የትንሹን ገ/መድህን ታታሪነት፣ ሰው ወዳድነትና ጉብዝና ሳይቀር ያሳዩናል፡፡ ገ/መድህን በአካልም ሆነ በመንፈስ እየጠነከረ ሲመጣ ያተረፈውን ዝና፣ የትምህርትና የቋንቋ ችሎታ በቀጣዩ ደረጃ እንመለከታለን፡፡ ይህ ደረጃ ስፋት አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ወደ መጨረሻው እየተጠቀለለ ሲመጣ አቡነ ጻውሎስ ለራሳቸውም ሆነ ለሌላ አካል ጥቅም ያልቆሙ፣ ይልቁንም እንደ አቡነ ሺኖዳ የአርአያ አባት ሊባሉ እንደሚገባቸው ይሞግታሉ ፡፡

በመጽሀፉ አቡነ ጻውሎስ ከፓትርያርክነትም በኃላም ሆነ በፊት ታላቅ ስራ መስራታቸውን እናነባለን፡፡ በስደት ወቅት በተለይም በአሜሪካ ከሰባት በላይ የሚሆኑ ቤተክርስትያናትን መስርተው በዚያ ለሚገኙ ኢትዮጽያዊያንና የውጭ ዜጎች ለ10 ዓመታት መንፈሳዊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡

በፓትሪያርክነት ዘመናቸው የወንጌል አገልግሎት እንዲስፋፋ በርካታ ጻጻሳትን ሾመዋል፡፡ የሀገረ ስብከቶች ቁጥር እንዲጨምር፣ተወርሶ የነበረው የቅድስት ስላሴ ኮሌጅ እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ የአብነት ት/ቤቶችና የካህናት ማሰልጠኛ እንዲጠናከሩ ሰርተዋል፡፡ ከእሁድ ት/ቤት ኃላፊነት ጀምሮ የልማት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የሰሩት አቡነ ጻውሎስ 3 የሀገር ውስጥና 6 የውጭ ሀገር ቋንቋዋችን አቀላጥፈው የሚናገሩ ናቸው፡፡ መረጃው የጋዜጦች፣ የመጽሄቶችና የሬዲዮ መምርያ የበላይ ሆነው እንደሰሩም ያስረዳል፡፡ በዚህ ወቅት የነበራቸውን አመራርና ሙያዊ ብስለት ማወቅ ቢቻል ሌላውንም ስብዕናቸውን ለመገመት ያስችል ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ ቦታ ፈታኝ በመሆኑ ውስጣዊ ማንነትና ብቃት እንደ ድርቆሽ አደባባይ ላይ እንዲሰጣ ያደርጋልና፡፡

አቡነ ጻውሎስ ባከናወኑት ተግባር ከሀገር ወስጥና ከውጭ የተለያዩ ኒሻንና ሜዳሊያዋችን ተሸልመዋል፡፡ ከአሜሪካ ኤምባሲ የተሰጣቸው ላንድ ክሩዘር፣ ከስፔን ኤምባሲ ያገኙት ሊሞዚን፣ ለ18ኛው በዓለ ሲመት ከህዝብ የተበረከተላቸውን መኪና በቤተክርስትያን ስም እንዲዛወር አድርገዋል፡፡ እስካሁንም እንዲህ ያደረገ ፓትርያርክ የለም ነው የሚሉት  - ወ/ሮ እጅጋየሁ ፡፡
በርግጥ ወ/ሮ እጅጋየሁ ይህን መጽሀፍ የጻፉት እንደ ጋዜጠኛ ወይም ዳኛ መሃል ላይ ቆመው ሳይሆን አንደኛው ጫፍ ላይ ሆነው ነው፡፡ ዓላማቸው የአቡነ ጻውሎስን በእጅ ስራ የተሰራ መልክ ማሳየት በመሆኑ ጥሩ የህዝብ ግንኙነት ስራ አከናውነዋል፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን በመጽሀፉ የቀረቡት አንዳንድ መረጃዋች በሌላኛው ጫፍ ለሚገኙት ምን ያህል አሳማኝ ናቸው ? የሚለው ነው፡፡ አሁንም በጥልቀት እንየው ካልን መረጃዋቹ በርግጥ የታሹና ናቸው ? ለሚለው ጥያቄ በቂ ምላሽ መስጠት ግድ ይላል፡፡

ለአብነት ያህል ሁለት ሜትር ርዝመት ያለው ባለ ነሀስ ሐውልት ሲሰራላቸው እንደማያውቁ ተገልጾል፣ የሄዱትም ሌላ ዝግጅት እንዳለ ተደርጎ ስለተነገራቸው ነው ተብሏል፡፡  የሃገራችን የሃላፊ አማካሪዋች በርግጥ መረጃን ደብቀው ወይም አሳስተው ለመንገር ብቃት አላቸው ከተባለ በራሱ ጥሩ ወደሆነ ደረጃ ደርሰናል የሚያስብል ነው፡፡ በወቅቱ በህዝቡም ሆነ በሚዲያ የተገለጸው ሀውልቱ የተሰራው የ18ኛ ዓመት ሲመት በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ ይችን ጥያቄ አንስተው መተንተን ወይም ባለጉዳዩ የእምነት - ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ በርግጥ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ብጽዐ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስም በህይወት እያሉ ራሳቸው ያሰሩት ሀውልት በደብረ ጽጌ ማርያም ቤ/ክ ቅድስት ውስጥ መቆሙን ማጣቀሻ በማቅረብ እስካሁን እሳቸው ላይ ጥያቄ ለምን አልተነሳም ? በማለት ይሞግታሉ፡፡ ለአቡነ ሺኖዳም 3 ሐውልቶች መቆሙን በመጥቀስ ፣ ቢሰራም አሳማኝ እንጂ አሳፋሪ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሀሳብ በራሱ መጥፎ ባይሆንም መሰረታዊው ውል እንዲተበተብ ግን ያደርጋል፡፡

ሌላኛው መሰረታዊ ነጥብ ሹመቱን የሚመለከተው ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ አምስት ሊቃነጻጻሳትን ለፓትርያርክ ምርጫነት አወዳድሮ እሳቸው ማለፋቸውን እናነባለን፡፡ ይሁን እንጂ ቀድመው ስለነበሩት አቡነ መርቆርዮስና ሌሎች ጻጻሳት የስደት ሁኔታ መረጃ አልተሰጠንም፡፡  የዚህ መረጃ ተጠናክሮ አለመቅረብ አቡነ መርቆርዮስን በማባረር ጻውሎስን የሾመው ኢህአዴግ ነው የሚለውን ሰፊ አስተያየት እንዳይተባበል አድርጓል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ምዕመናን ሀሳብ ውስጥ ያለውን ‹ ህጋዊው ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ናቸው ወይስ አቡነ ጻውሎስ ? › የሚለውን ብዥታ ለማጥራት ይረዳ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ አሁንም አከራካሪ ሆኖ እንዲቀጥል ይለፍ የተሰጠው ይመስላል፡፡

 
አቡነ ጻውሎስ የቤተክርስትያን ገንዘብ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ጥቅም እንደሚያውሉም ይነገራል፡፡ ጸሀፊዋ ከዚህ መነሻ ተነስተው ባይመስልም ጥሩ ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡ በስማቸው የመጡትን በርካታ ሽልማቶች በቤተክርስትያን  ስም እንዲዛወር አድርገዋልና፡፡ የራስ ንብረት የራስ ነው ከሚለው አሰራር በወውጣት ይህን ማድረግ በርግጥም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ጸሀፊዋ  የአቡነ ጻውሎስን ታላቅነትና ንጽህና ለማስረገጥ ነው አልመው የተነሱት፡፡ ለዚህም እገዛ ያደርግልኛል ያሉት ፕሮፋይላቸውን ማጉላት ነው፡፡ ብዙ ምዕራፍ የያዘው ይህ መረጃ ግን ህዝቡ ውስጥ ያሉትን ጥያቄዋች በተፈለገው መልኩ የሚመልስ አልሆነም፡፡

·         በ1997 ዓም በልደታ ቤ/ክ የሞተው ባህታዊና የቆሰሉት ሰዋች ጉዳይ መነሳት ነበረበት፡፡ ለምን ይነሳል ካልን አቡነ ጻውሎስ የዚያን ወቅት ነበር ሽጉጥ ተኮሱ የተባለውና፡፡ ባህታዊው አቡነ ጻውሎስን በጎራዴ እገድላለሁ ሲል ይዝት ነበር ቢባልም የአይን እማኞች ሰውየው በእጁ ምንም እንዳልያዘ ተናግረዋል፡፡ የሟች ጓደኛም ፔቲሽን የያዘ ወረቀት ሊሰጣቸው ነበር ብሏል፡፡ እና የትኛው ነው ታማኝ ሀሳብ ?

·         የእንግሊዝ መንግስትም ለአቡነ ጻውሎስ የትራንዚት ቪዛ ከልክሎ እንደነበር በአንድ ወቅት አንበናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሀገሪቱ ከሚኖሩ ኢትዮጽያዊያን ጋር ግጭት  ይፈጠራል የሚል ነው፡፡ ይህ ሃሳብ ምን ያህል መሰረት እንዳለው በመጽሀፉ ውስጥ ቢታይ በጣም ጠቃሚ ነበር፡፡

·         አቡነ ጻውሎስ ሚዛናዊ አይደሉም የሚባሉት በብዙ ወገኖች ነው ፡፡ ተቃዋሚዋች ለገዢው ፓርቲ ይወግናሉ፣ ጥብቅና ይቆማሉ ይሏቸዋል፡፡ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ፍትሃዊ አስተዳደር እንዳይሰፍን ወገናዊ አሰራር ይከተላሉ ባይ ናቸው፡፡ የማህበረ ቅዱሳን አባላት ነጻነታችንን ይጋፉናል ይላሉ፡፡ ቅልጥ ያሉ ፓለቲከኛ ሆነዋል የሚላቸው መንገደኛማ ስፍር ቅጥር የለውም፡፡ በዚህ ዙሪያ የእሳቸው አስተሳሰብና ምልከታ መንጸባረቅ ነበረበት፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አልታሰበባቸውም ወይስ የማርያም መንገድ እንዲሆኑ ተፈልጎ ነው ?

·         ኢትዪጽያን የማያት እንደ ሁለተኛ ሀገሬ ነው የምትለው ቢዮንሴ ለ4 ቁጥርም ያላት ፍቅር ልዩ ነው፡፡ እናቷ የተወለዱት ጥር 4 ነው፡፡ ያገባችው ሚያዝያ 4 ነው፡፡ ልደቷ የሚከበረው መስከረም 4 ነው፡፡ የባልዋ ልደት ታህሳስ 4 ይከበራል፡፡ ወደ ሀገራችን የመጣችው ግን በዚህ ቀን አይደለም፡፡ ስራዋቿን በሚሊኒየም አዳራሽ በማቅረብ ዘፈን አፍቃሪውን ህዝብ አስደስታለች፡፡ በአቡነ ጻውሎስ ጋባዥነት የተደረገላት ስነስርዓት ግን ብዙ ምዕመናን አስቆጥቶ ነበር፡፡ መንፈሳዊ ቃና የሌለውን ዘፈን የምታቀነቅንን አርቲስት እንዴት ይጋብዛሉ ? እንደ ታቦትስ እንዴት ጥላ ተያዘላት ? ራቁት ገላን በማስተዋወቅ  ከምታቀነቅን ሴት ክርስትያኖች ምን ያማራሉ ? ዓለማዊ ዘፈንና ቤተክርስትያንስ ምንና ምን ናቸው ? እነዚህና የመሳሰሉ ጥያቄዋች ምላሽ ሳያገኙ ቆይተዋል፡፡ በምዓመናኑና በአቡነ ጻውሎስ መካከል ያለው ልዩነትም እንዲሰፋ አድርጓል ፡፡ ጸሀፊዋ በዚህ አጋጣሚ ይህን ሰበዝ መዘዝ ቢያደርጉት ማለፊያ በሆነ ነበር፡፡


ለማንኛውም ቃለ- ህይወት ያሰማልን


ገ/መድህን አርብ ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓም ነው የተወለዱት፡፡ አባታቸው ገ/ዮሀንስ ገ/ስላሴ ፣ እናታቸው አራደች ተድላ ይባላሉ ፡፡ ድቁና፣ ምንኩስናና ቅስናን አልፈው ወደ ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የገቡት በ1949 ዓም ነው፡፡ ሶስት ግዜ ብልጫ በማምጣት ከንጉስ አጼ ሃይለስላሴ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ለ15 ዓመታት በዲቁና፣ ቅስናና ምንኩስና አገልግለዋል ፡፡ በመንበረ ጽባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል መደበኛ ቀዳሽ በመሆን ለ 8 ዓመታት ሰርተዋል ፡፡  ጻውሎስ በሚል ስያሜ የኤጺስ ቆጾስነት ማዕረግ የሰጧቸውአቡነ ቴዋፍሎስ መስከረም 17 ቀን 1968 ዓም ነበር፡፡ በነገረ መለኮት ዲፕሎማ፣ ባችለርና ዶክትሬት አላቸው፡፡ የማስትሬት ዲግሪያቸው በክርስትያን ስነ ምግባር ነው ፡፡

ለሁላችንም ጥሩ ስነ ምግባር ይስጠን፡፡


አሜን !!

Tuesday, June 5, 2012

‹ በሁመራ ኖራ ይዘንባል … ሙቀት ይዘንባል … ›


ተከዜና ድልድዩ

ወታደሮች ላብ ደምን ይተካል የሚሉት ብሂል አላቸው፡፡ በሁመራ እንደ ጉድ የሚያዘንቡትን ላብ ለመተካት ውስጥዋን የሚነግሩት ‹‹ ጠጣ ! ›› የሚለውን ቃል ነው፡፡ ቀዝቃዛ ውሃ እንደ ጉድ ይጠጣሉ… ቀዝቃዛ ቢራ እንደ ጉድ ይጠጣሉ… እንደ ጉድ እየጠጡ ፊኛን ለማስተንፈስ በተደጋጋሚ ቁጭ ብድግ በማለት መከራ አይበሉም፡፡ በሁመራ የብልትን ሚና ተክተው የሚጫወቱ ቀዳዳዋች መዓት ናቸው፡፡ የተጣራ ሽንት ከብብት እየመነጨ ቁልቁል ይንደረደራል፡፡ አናትዋ፣ ግንባርዋ፣ ወገብዋ፣ እግርዋ ሁሉ ፈሳሹን እያስተነፍሱ ያግዝዋታል፡፡ ከርስዋ የሚጠበቀው መምጠጥ ብቻ ነው፡፡ በሁመራ ተማሪዋች አስካሪ ነገሮችን ዘርዝሩ ተብለው ቢጠየቁ ሙቀትን እንጂ ቢራና ድራፍትን በልበ ሙሉነት ለመጻፍ የሚያስችላቸው መሰረት ያለ አይመስልም፡፡ የማስከር ተግባሩን የተነጠቀው ቢራ ‹ ትግሌን በሰላማዊ መንገድ አፋፍማለሁ › የሚል አዲስ ስትራተጂ ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ይመስላል ፡፡ በርግጥም በሁመራ  እንደ በሶ ደረት ላይ ደስታ ጭሮ የሚወርድ ቢራ ይዘንባል …ኖራ ይዘንባል… ሙቀት ይዘንባል… ስጋት ዳምኗል …

·        የኖራው ጉዳይ ፤

ርግጥ ነው የኖራ ወይም የሲሚንቶ ፋብሪካ አላየሁም፡፡ ሰው ሰራሽ ኖራ እንዲፈጠር ወይም የሲሚንቶ ፋበሪካ እንዲቋቋም የሚያግዙ ባለሀብቶችና አስተዳዳሪዋች የሉም ማለት ግን አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው የሁመራ መሬት ለሰሊጥና ለጥጥ ምርት የሰጠ በመሆኑ ከተማዋን ቱባ ባለሀብቶች ወረዋታል፡፡ ባለሀብቶች ለምርታቸው ማስቀመጫ ያስገነቡት ሽንጠ ረጃጅም መጋዘኖች በርካታ ናቸው፡፡ የባለሀብቶችን እርሻ የሚያርሱ ትራክተሮችና ምርታቸውን ወደ አ/አበባም ሆነ ወደ ሱዳን የሚያመላልሱ ትልልቅ የጭነት መኪናዋች ያን አቧራማ መንገድ ሲተረትሩት ይውላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ነዋሪው፣ ቢሮዋች፣ መጋዘኖች ሁሉ አቧራውን ያለ ስስት ይጠጣል፡፡

ሲስልም ሆነ ሲያስነጥስ አቧራን ያፈልቅ የነበረው ነዋሪ መንገዱ እንዲሰራለት ጮሆ ጮሆ ሲታክተው ትቶታል፡፡ የአካባቢው በለሀብትም ሆነ ባለስልጣናት እስካሁን ኖራ ሆነው ለመቀጠል እንዴት እንደፈቀዱ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ እንግዲህ መንገዱ ባያድግ አቧራው ማደግ ስላለበት - ስለሚገባውም  ዛሬ ደረጃውን ወደ ኖራነት የቀየረ ይመስለኛል፡፡ ባለሀብቱ የሰሊጥ ትርፍ ባይሳብጣቸው ኖሮ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን ሲሚንቶ ለማምረት ፍቃድ ከመጠየቅ ወደ ኃላ አይሉም ነበር፡፡ ጥሬ ዕቃው የት አለና  ? አትበሉ፡፡ ምድረ ኖራ እያደር ሲሄድ ሲሚንቶ አይወጣውም እንዴ ? ብቻ መስሎኛል - የመሰለኝ ሌላም ነገር  አለ
….. አይኑን ጨፍኖ ብር የሚቆጥር ባለሀብት ያየሁ መስሎኛል
….. ጫማው በአቧራ ተውጦ ስለ ፈጣን ልማት የሚሰብክ ካድሬ ያየሁ መስሎኛል
….. በጦርነት ሳይሆን በቢሮክራሲ ተሸንፎ እንደ አቅሙ ሙቅ ሻይ ወይም ቀዝቃዛ ቢራ ታቅፎ የሚውል ነዋሪ ያየሁ መስሎኛል

·        የሙቀቱ ጉዳይ ፤

የሁመራ ሙቀት ያስጨንቃል ፡፡ በተለይም እንግዶች ስምንተኛው ዙር እንደደረሰ የቦክስ ተጫዋች ሁለመናቸው ሊሰክር ይችላል፡፡ ሙቀቱ ዓይን ስለሚያጠብ ጥቁር ቻይናዋች በብዛት እንዲታዩም ያደርጋል፡፡

በየቤቱ፣ ሆቴልና ቢሮዋች  ቋ… ቋ… እያለ የሚሽከረከረው ፋን ራዕይና ተልዕኮው ለነዋሪው የተሻለና ቀዝቀዝ ያለ ንፋስ መፍጠር ቢሆንም የተሳካለት አይመስልም፡፡ ሞቃታማ አየርን በዘመናዊ መልኩ ለአካል ማቅረቡን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ አልፎ አልፎ ሀሴት ጣራ ላይ የሚያደርስ ውብ ንፋስ ሊመገቡ ይችላሉ - የበረሃ ዛፎች ስር ቁጢጥ ካሉ ፡፡

የበረሃ ዛፍ እንዳለ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ዛፎች ጥቂት ኖረው የሚሞቱ ናቸው ፡፡ ዘራቸው ግን ለረጅም ዓመታት አፈር ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ሞተ የተባለው ዘር ጥቂት ዝናብ ሲያገኝ በፍጥነት ያብባል፡፡ ግመልና ዔሊን የመሳሰሉ በረሃ ተኮር እንስሳትም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እንስሳቱ ሙቀት ቀን ይሰበስቡና ማታ ያስወጣሉ፡፡ የተፈጥሮ ጥቃትን በተፈጥሮኛ የመቋቋም አቅም አላቸው፡፡

ለበረሃ የተሰራ ሰው አለ  ? ነው ሰው በቆይታው ነው  ቅዝቃዜንም ሆነ ሙቀትን መለማመድ የሚችለው ? ብዙዋች በሙቀቱ ሲቀልጡ ምንም የጭንቀትም ሆነ የሙቀት ምልክቶች የማይታይባቸው ሰዋችን አስተውያለሁ፡፡ ሙቀቱ የሚያቀልጠው የሰውነታቻው  ስብ ስላለቀ ወይስ የግመልን ስጦታ በሆነ መንገድ ስላገኙ ? ትዝብት ነው - የታዘብኩት ሌላ ነገርም አለ
….  ፍቅረኛሞች እንደ ፍላጎታቸው ተቃቅፈው እንዳይዝናኑ ተጽዕኖ ፈጥሯል
….. በስራ መኃል ደጋግሞ እንቅልፍን ስለሚጣራ የሚጃጃሉ ቡድኖችን ማየት ቀላል ነው
….. በአንድ ጣራ ስር፣ በአንድ አልጋ ላይ ተቃቅፈው መገኘት የሚገባቸው ባልና ሚስቶች እንዲነፋፈቁ አድርጓል
….. ህጻናት እንደ ዶሮ ጫጩት ወይም እንደ ድመት ግልግል ያለ እድሜያቸው እንዳይቀጩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይተናነስ ጥበቃ ማድረግን ግድ ይላል


·        የስጋቱ ጉዳይ ፤

ቴዲ አፍሮ በቅርቡ ባወጣው አልበሙ ስለ አስመራ ማዜሙ ይታወቃል፡፡
            ጋራው ቢከልለን ያ ተራራ
            አትወጣም ከልቤ ጓል አስመራ በማለት

እዚህ ሁመራና ኤርትራ አፍና አፍንጫ ሆነው ይታያሉ ፡፡ የከለላቸውም ርቆ የሚታየው ጋራ ሳይሆን ሰፊው የተከዜ ወንዝ ነው፡፡ ከተከዜ ማዶ ኤርትራ ከተከዜ ወዲህ የኢትዮጽያ ግዛት ነው፡፡ ከተከዜ ማዶ የኤርትራ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጽያ ወታደሮች ይታያሉ፡፡ ከተከዜ ማዶ አንዳንድ ቤቶች ወዲህ ደግሞ ለ G + 1 ታቅደው ጂ - ዜሮው አልቆ ፎቁ ላይ ያገጠጡ ብረቶች የሚታይባቸውን የሁመራ ቤቶች ይመለከታሉ፡፡

የተከዜን ውሃ ከዳር ለማንቦጫረቅ፣ አጠገቡ ፎቶ ለመነሳት፣ ዳሩ ላይ ቁጭ ብሎ ‹ ወይ ኤርትራ ያንቺ ነገር እንዲህ ሆኖ ቀረ ? › በሚል ቁዘማ እንዲሰምጡ ይፈቀዳል ፡፡ ርግጥ ከተወሰነ ሰዓት በኃላ ወደ አካባቢው ዝር ማለት ይከለከላል ፡፡ ለመዋኘትም ሆነ ወደ ማዶ ለመሻገር ግን አይሞከርም፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ፊትና ጀርባ ሳንሆን ወደ አስመራ የሚያሻግር ረጅም ነጭ ድልድይ ይታያል፡፡ ምናልባት መወጠሪያ ቢኖረው ኖሮ አዲሱን የአባይ ድልድይ የመምሰል አቅሙን ያጠናክር ነበር፡፡ ግን አሁንም ድልድዩ የጋራችን እስከሆነ ድረስ እስከ መሃል መሄድ ቢፈቀድ ጥሩ ነበር፡፡ ድልድዩ ላይ ሆኖ ለተከዜ ማንጎራጎር ወይም አንት አራም ስንኝ ለመወርወር የሚመች መስሎ ታይቶኛል ፡፡ የሆኑ መኳል የሚቀራቸው ስንኞች ወንዙን እያየሁ እንኳን ውር ውር እያሉብኝ መሰለኝ - ይኀው ብዘረግፋቸው …

ግዜ ያደናበረህ ሽንጣሙ ተከዜ
ዛሬ ግን ምንድነህ ? የማነህ ጎበዜ ?
ድንበር ነው ዓላማህ - የእሾህ መስመር
ወዲህ ወዲያ የሚሾልከውን ነፍስ ማሳጠር
ወንዝ ነህ እንዳልል ውስጤን ተናነቀው
ሀገሬው ሲጠጣህ ሲዋኝብህ አላየው
ለመሆኑ ማን ሆንክ ? ዘር ሀረግህ የት ወደቀ ?
ምርጫ  - ሪፈረንደምህ እንደምን አለቀ ?
ተናገር እንደ እኛ በካርድህ አትፍራ
‹ ሀገርን ያስማማ › ላንተ አይሆን ኪሳራ፡፡
  • o          
‹‹ በእናቴ ኢትዮጽያ - በአባቴ ኤርትራ ! ››
     ምናልክ አንተ ?!?! ማለት ነበር…

በሁለቱም አቅጣጫ የድንበር ጠባቂዋች ቢኖሩም እስካሁን ከመፋጠጥ የዘለለ የትንኮሳና የምላሽ ወጎች አለመደረጋቸውን ጠባቂዋቹ ነግረውኛል፡፡ አያድርገውና ከፍ ካለው የኤርትራ አካባቢ የትልቅ መሳሪያ ቃታ ቢሳብ ሁመራንና ነዋሪዋቿን በቀላሉ ማጣት ይከሰታል፡፡ ይህን ስጋት ይዤ ለጠባቂዋቹ ጥያቄ አቀረብኩ

‹‹ ሻዕቢያ እንዲህ ያደርጋል ብለን አናስብም፤ በፍጹም ! ›› የሚል ምላሽ ሰጡኝ፡፡ መልዕክቱ ትንኮሳ ከጀመረ የአጸፋ ጥቃቱን አይችለውም የሚል ይመስላል፡፡ በተቃራኒው ያነጋገርኳቸው አንዳንድ ነዋሪዋች ሁሌም በጥርጣሬ፣ ሁሌም በስጋት፣ ሁሌም በተጠንቀቅ እንደሚገኙ ነው ያጫወቱኝ፡፡ ለዚህም መነሻ አላቸው፡፡ አሁን በማጫውታችሁ ቦታ ባይሆንም ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጽያ ክልል ሰውን አይደለም ከብቶችን የሚያስገቡበት ሁኔታ አለና፡፡ ኢሳያስ ሞተ የሚለው ዜና የተሰማ ግዜ በመቀሌ ብቻ ሳይሆን በሁመራም ብዙዋች ጮቤ ረግጠዋል፡፡ የዚህ ስጋት መቋጫ እንዴትና መቼ ይገኝ ይሆን ?



Friday, June 1, 2012

በጣም የሚዋሸው ወንድ ነው ሴት ?



በቅርቡ መቼ ነበር የዋሹት ? በብድር ወይም በስራ ማመልከቻ  ጥያቄ ላይ ራስዋትን ከፍ በማድረግ ጥቂት ግነቶችን አቀላቅለው ይሆን ? መኪናዋትን ለማሻሻጥ ጥረት ሲያደርጉ ሁልግዜም ዘይት የማፍሰሱን ሁኔታ በመርሳት ወይም ቸል በማለት ስለመኪናዋ ብቁነት ሳይሰብኩ ይቀራሉ ?  ቢያንስ በሰባት ዓመት ዕድሜ ዝቅ ብሎ ለመታየት ጸጉርዋን ቀለም መቀባትዋ… አሊያም የሳሳውን የጸጉር ክፍልዋ በቀሪው ጸጉር ለመሸፋፈን ጥረት አድርገው መሆንዋንም ያስታውሱ፡፡ ከፍ ያለ ተረከዝ ያለው ጫማን በማድረግ ቅልጥምዋን ረጅምና ያማረ ለማስመሰል ምን ያህል ግዜ ተጨንቀው ይሆን ?  ሰው ሰራሽ ጸጉርና ጥፍር እንዲሁም ሌሎቸን የማስዋቢያ ቁሳቁሶች በመጠቀም እውነተኛው መልኬ ይሄ ነው በማለትስ ምን ያህል ባዝነዋል ?  አሁን የሆነ ከባድ ውሸት ትዝ አለዋት ;…. አይጨነቁ ! ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች እንዋሻለንና - ጥቅም ለማግኘት ወይም ስቃይን ለማስወገድ ፡፡

የውሸት ዓይነቶች፣

አራት የውሸት ዓይነቶች አሉ፡፡ ነጭ ውሸት፣ ጠቃሚ ውሸት፣ ተንኮል አዘል ውሸት እና አሳሳች ውሸቶች ናቸው ፡፡ ነጭ ውሸት እውነታው ሌላ ሆኖ  በተቃራኒ መልኩ የሚነገር ድርጊት ነው፡፡ ጠቃሚ ውሸት አንድ ሰው ሆን ብሎ ሌሎችን ለመርዳት በማሰቡ የሚፈጠር ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የአደጋ ግዜ ሰራተኞች ከሚቃጠል መኪና ውስጥ ጎትተው ያወጡትን ህፃን እናቱና አባቱ በደህና ሁኔታ እንደሚገኙ ሊነግሩት ይችላሉ፡፡ ይህም ህጻኑ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባና ለትንሽ ግዜም ቢሆን በህይወቱ እንዲቆይ ለማድረግ ነው፡፡
አሳሳች ውሸት በጣም አደገኛ የውሸት ዓይነት ነው፡፡ ምክንያቱም የሚዋሸው ሰው ለራሱ ጥቅም ሲል ሌላውን ሊጎዳ ወይም ጥቅሙን ሊጋፋ ስለሚችል፡፡ አሳሳች ውሸት  ሁለት ዓይነት መንገዶች አሉት - መደበቅና ፈጥሮ መናገር ናቸው፡፡
ተንኮል አዘል ውሸት የሚነገረው ለብቀላ ወይም ትርፍ ለማግኘት ነው፡፡ ጥሩ ዝና ያላቸው ሰዋች ለምሳሌ የፊልም አክተር፣ ባለጸጎችና ፓለቲከኞች የሚያገኙትን ጥቅም በማለም ይህን ዓይነቱን ውሸት ይጠቀማሉ፡፡ ተንኮል አዘል ውሸት ሁልግዜም በውድድር ሁኔታ ውስጥ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ተንኮል አዘል ውሸትን የሚያቀነቅኑ ሰዋች ባላንጣቸውን ወይም ማጥቃት የሚፈልጉትን ስምና መልካም ዝና በአስደንጋጭ መልኩ ያፈራርሳሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ኩባንያ በተፎካካሪው ላይ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት የገንዘብ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንዱ የፓለቲካ ፓርቲ በሌላኛው አባላት ላይ መጥፎ የዝሙት ባህሪ፣ ሙሰኝነት፣ ወዘተ እንዳለባቸው በማስመሰል ማስወራቱ የተለመደ ነው፡፡ ይህ የውሸት ዓይነት ውሸት መሆኑ በስተመጨረሻ ሊደረስበት ቢችል እንኳን ጎጂ ገጽታ አለው፡፡ ምክንያቱም አንድ ጭብጥ ጭቃ የሆነ ነገር ላይ ቢወረወር የተወሰነው ተለጥፎ መቅረቱ አይቀርምና፡፡

የውሸታሞች ዓይነት፣

‹‹ የተፈጥሮ ውሸታሞች ›› ህሊና ያላቸው ሲሆን ነገር ግን ውሸቱን ሲጠቀሙ የመጡት ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በመሆኑ በመዋሸት ብቃታቸው በጣም የሚተማመኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዋች ከተለያዩ ቅጣቶች ለማምለጥ ከቤተሰባቸው ውሸቱን የተማሩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ችሎታቸው ሲያድጉም ስለሚጠቀሙ ጠበቃ፣ ነጋዴ፣ አስማሚ፣ ደላላ፣ አክተር፣ ፓለቲከኛና ሰላይ ሆነው ለመስራት ዕድል አላቸው፡፡
‹‹ ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ውሸታሞች ›› የሚባሉት ልክ እንደ ህጻን ፣ ቤተሰቦቻቸው ለእነሱ ውሸት መናገር የማይቻል መሆኑን በማሳመን ያሳደጓቸው ዓይነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሞኝ የሆኑ ሰዋች ህይወታቸውን ያሚያሳልፉት ላገኙት ሁሉ የሁሉንም እውነት በመስበክ ነው፡፡ ለዚህ የማሳመኛ መሳሪያቸው ደግሞ ‹‹ እኔ በፍጹም ውሸት መዋሸት አልችልም ›› የሚለው አባባላቸው በመሆኑ ከሰዋች ጋር ለግጭት ያዳረጋሉ፡፡

በጣም የሚዋሸው ማነው ?

አያሌ ሴቶች በጋለ ስሜት እንደሚያማርሩት ከሆነ ከሴቶች ይልቅ የበለጠ የሚዋሹት ወንዶች ናቸው፡፡ ሳይንሳዊ ጥናቶችና ምርምሮች የሚያሳዩት ግን ሴቶችና ወንዶች የሚዋሹት በእኩል ደረጃ ነው፡፡ የሚለያያቸው ነገር ቢኖር የውሸቶቹ ይዘቶች ናቸው፡፡ የሴቶች ውሸት የሚያዘነብለው ሌሎች ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲሆን ወንዶች የሚዋሹት ራሳቸውን ጥሩ አድርጎ ለማሳየት ነው፡፡ ሴቶች ግንኙነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ለመጠበቅ ሲሉ ሲዋሹ ወንዶች ጭቅጭቆችን ለመከላከሉ ይዋሻሉ፡፡ ሴት ልጅ አንድ ወንድ አዲስ ልብስ ለብሶ ነገር ግን በጆንያ የተሞላ ድንች መስሎ ቢታያት እንኳን በጣም ቆንጆ መሆኑን ከማስረዳት ወደ ኃላ አትልም፡፡

ሴቶችና / በፍጥነት / የመዋሸት ጥበባቸው፣

በርካታ ወንዶች ትንሽዬ ውሸት እንኳን ብትሆን ሴቶች ፊት ለፊት ቆመው ለመዋሸት እንደሚከብዳቸው ያውቃሉ፡፡ ወንዱ የግድ ሴቷን መዋሸት ካለበት የሚመርጠው በስልክ ግንኙነት ይሆናል፡፡ በአንጻሩ አብዛኛዋቹ ሴቶች ከወንድ ጋር ፊት ለፊት ተገኛኝተው ለመዋሸት ያን ያህል ችግር ውስጥ የሚገቡ አይደሉም፡፡ የጭንቅላታችንን  የውስጥ ገጽታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው መሳሪያ እንደሚመሰክረው የሴት ጭንቅላት ፊት ለፊት ለሚደረግ ግንኙነት የሚረዳት ከ14 እስከ 16 የሚደርሱ ቁልፍ የአቀማመጥ ስርዓቶች ይታይበታል፡፡ እነዚህ ክፍሎች የምልክት መልዕክቶችን ለመተርጎም፣ የድምጽ ቃናንና የሰውነት መልዕክትን ለመለወጥ ትልቅ ፋይዳ የሚሰጡ በመሆኑ         ‹‹ የሴቶች ስሜት ›› በሚል መጠሪያ ይገለጻሉ፡፡
ወንድ ፊት ለፊት ለሚደረገው የመረጃ ልውውጥ የሚረዳው የአእምሮው ክፍል ከ 4 አስከ 7 አካባቢዋች ላይ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የወንድ ጭንቅላት የተፈጠረው ወይም ቀስ በቀስ እያደገ የመጣው የርስ በርስ ግንኙነት ከማዳበሩ ይልቅ የጠፈር ስራ በማከናወን ላይ በመሆኑ ነው፡፡

ሴቶች ውሸትን ያስታውሳሉ፣

በምስራቅ ካሮሊና ዩኒቨርስቲ ረዳት የስነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ኤሪክ ኤቨርሀርት እና ጓደኞቻቸው ከ 8 እሰከ 11 ዓመት በሚሞላቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች ላይ ባደረጉት ጥናት ሁለቱም ጾታዋች የሰዋችን መልክና ገጽታ የሚያስታውሱት በተለያ የአእምሮ ክፍሎቻቸው ነው፡፡ በጥናቱ መሰረት ወንዶች ነገሮችን ለማስታወስ የሚጠቀሙት የቀኝ አእምሮአቸውን ሲሆን ሴቶች የግራ ክፍላቸውን ነው፡፡ ሴቶች የግራ አእምሮአቸውን መጠቀማቸው በፊት ገጽታ ላይ የሚታዩ ጥቃቅን ለውጦችን ለይቶ ለማወቅ የረዳቸው ሆኗል፡፡
ሴቶች ራሳቸው የዋሹትንም ሆነ የትኛው ሰው የዋሻቸው መሆኑን የሚያስታውሱ ሲሆን ወንዶች ግን ውሸታቸውን ይረሳሉ፡፡             ‹ ሂፓካምፓስ › የሚባለው የአእምሮ ክፍል ትዝታዋችን የማከማቸትና ፈልጎ የማምጣት ተግባር ያከናውናል፡፡ ይህ ክፍል ኦስትሮጅን በተባለ ንጥረ ነገር የተሞላ ሲሆን ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ቶሎ የማደግ አቅም አለው፡፡ ለዚህም ነው ሴቶች የላቀ አስታዋሽ የሆኑበት ምስጢር፡፡

በውሸት ውስጥ የሚንጸባረቁ ቃላትና ሐረጎች፣

በሰዋች የዘወትር ንግግር ውስጥ አንዱ ሌላውን ለማሳመን የተለያዩ ቃላቶችንና አባባሎችን ሲጠቀም ይታያል፡፡ የማሳመኑ ጉዳይ በእውነት ላይ ተመስርቶ አሊያም እውነታን በተዛባ መልኩ አዛብቶ በማቅረብ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ታዲያ አንዳንድ የተጋነኑ ቃላቶች መረጃው የእውነት መስሎ እንዳይሰማን ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ በእውነቱ ›› ፣ ‹‹ ከልብ ›› እና ‹‹ በግልጽ ሁኔታ ›› እያለ የሚናገር ሰው ለእነዚህ አባባሎች ያለው እውነት ግን በጣም ዝቅ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡
አንዳንድ ተናጋሪዋች ‹‹ ከአክብሮት ጋር ›› … ‹‹ እጅግ የተከበራችሁ ››…. ወዘተ በማለት አድማጩን ቢደልሉም አነስተኛ ክብር የሌላቸው መሆኑ ይታወቃል ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዋች ዋና ዓላማቸው የሚናገሩት ነገር እውነት ተደርጎ እንዲቆጠር ማሳመኑ ላይ በመሆኑ የተለያዩ አገላለጾችን ከመጠቀም ወደ ኃላ አይሉም፡፡ እነሆ ጥቂት አብነቶች፣
‹‹  እመነኝ ››
‹‹ የምዋሽበት ምክንያት የለኝም ››
‹‹ ለምን እዋሻለሁ ››
‹‹ በእውነተኛ አነጋገር ››
‹‹ የምነግራችሁ እውነት ነው ››
‹‹ ለፈጣሪ ታማኝ ነኝ ››
‹‹ በእናቴ መቃብር እምላለሁ ››
‹‹ ፈጣሪን ምስክር አድርጌ … ››
‹‹ ፈጣሪ በሞት ይቅጣኝ ››

ውሸታሞችን በኮምፒውተር መያዝ ፣

በሰለጠነው የኮምፒውተር ሳይንስ ዘመን ኮምፒውተር ሰዋች መዋሸት አለመዋሸታቸውን የሚለይበት ቴክኖሎጂ እውን ማድረግ ችሏል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ፓሊግራፊ የሚባል ሲሆን የሰዋቸን አተነፋፈስ፣ የአተነፋፈስ መጨመር ወይም መቀነስን ያሳያል፡፡ ሰውየው ወይም ሴትየዋ እውነት የሚናገሩ ከሆነ ምንም ዓይነት ለውጥ አይታይም፡፡
እንደ አሜሪካ ፓሊግራፊ ማህበር መረጃ ከሆነ ባለፉት 25 ዓመታት 250 የሚደርሱ ምርምሮች ተደርገው ሁሉም የፓሊግራፊ መሳሪያን ትክክለኛነት አሳይተዋል፡፡ በቅርቡ የተደረገ ሌላ ጥናትም ይህ ዘዴ ለመቶ ፐርሰንት የቀረበ እውነት ማሳየቱ ተመስክሯል፡፡ መሳሪያው በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ቴሌቪዥን ቶክሾው ላይ የሚታይ ሲሆን ተመልካቾች የትኛው እንግዳ ንጹህ ወይም ታማኝ መሆኑን ይለዩበታል፡፡ በርግጥ ፓሊግራፊ ይህን ያህል ውጤታማ ቢሆንም በፍርድ ቤቶች አካባቢ እንደ አንድ ማስረጃ የሚቆጠርበት አሰራር እሰካሁን ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ውሸትን በድምጽ መለየት፣

በድምጽ ውሸትን ለመለየት የሚያስችሉ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች የድምጽ ቃና፣ የድምጽ ፍጥነትና የድምጽ መጠን ናቸው፡፡ አንድ ሰው በውጥረት ውስጥ ካለ የሚንሳጠጥ ድምጽ የሚፈጥር ሲሆን ፍጥነቱና መጠኑም ይጨምራል፡፡ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከሆነ 70 በመቶ የሚደርሱ ሰዋች በሚዋሹበት ግዜ የድምጻቸው ቃና ይጨምራል፡፡ ብዙዋች በድንገት ውሸቱ ሲገለጥባቸው ንግግራቸው እየተቆራረጠና በመሃሉም እያረፉ …እእ..እ…ምምም… የሚል የተንተባተበ ጽምጽ ያወጣሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ስለ መረጃው አስቀድመው ባለመስማታቸውና ባለመለማመዳቸው ነው፡፡ ሁኔታው በአብዛኛው በወንዶች ላይ የሚታይ ሲሆን ሴቶቹ ይህን መሰሉን የመንተባተብ ቋንቋ የሚቆጣጠርላቸው የአእምሮ ክፍል አላቸው፡፡

አካላዊ እንቅስቃሴን ማንበብ፣

እንደሚታወቀው ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በሚዋሹበት፣ በሚጠራጠሩበት፣ ርግጠኛ ባልሆኑበት ወይም ነገሩን ባጋነኑበት ግዜ ከእጅ አንስቶ እስከ ፊታቸው የሚታየው እንቅስቃሴ መጠን ይጨምራል፡፡ በውሸት ወቅት የሚጎላው አካላዊ እንቅስቃሴ አይንና አፍንጫን ማሻሻት፣ ጆሮን መሳብና ኮሌታን መጎተትን ይጨምራል፡፡ ለምሳሌ ያህል የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን የሞኒካ ሊውኒስኪን ክስ ፍርድ ቤት ተገኝተው ለማስተካከል በሞከሩበት ወቅት 26 ግዜ አፍንጫቸውንና ፊታቸውን መነካካታቸው ተመዝግቧል፡፡

የፒኖቺዬ ውጤት፣

ሳይንቲስቶች በሚጠቀሙበት ልዩ ካሜራ አማካይነት አንድ ሰው ሲዋሽ ደም ወደ ሰውነት ክፍሉ ሲፈስና አፍንጫው እያደገ ሲሄድ መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህ ወቅት የደም ግፊት እየጨመረ አፍንጫን እንደሚነፋና ሰውየው አፍንጫውን ደጋግሞ በማከክ እንደሚደሰት ታውቋል፡፡
በቺካጎ የሚገኘው የማሽተትና የመቅመስ ህክምና እና የጥናት ድርጅት ሳይንቲስቶች እንደሚገልጹት አንድ ሰው በሚዋሽበት ግዜ ከሰውነቱ ውስጥ ካቲኮላሚን / catecholamines/ የተባለ ኬሚካል ስለሚለቅ በአፍንጫ ውስጥ የሚገኙ ቲሹዋች አፍንጫ እንዲያብጥ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ይህን እብጠት በተለየ መሳሪያ ካልሆነ በስተቀር በግልጽ አይኖች ማስተዋል አይቻልም፡፡ በጣም የሚያስገርመው ደግሞ ሰውየው ሲዋሽ ብልቱም ማበጡ ነው፡፡ ስለዚህ ሰውየው መዋሸት አለመዋሸቱን ማረጋገጥ ካልተቻለ ሙታንቲውን ወደ ታች ማውረድ ይጠቅማል፡፡