Tuesday, October 8, 2013

የመቻቻልን ሂሳብ ማን ይክፈል ?




መንገድ ሁሉ ስለተቦዳደሰ መንገድ የለም ፡፡ ታክሲ ሁላ ቀዳዳ መንገድ በመሸሹ ታክሲ የለም ፡፡ ይህን ችግር ያሰሉ ጥቂቶች ሲመጡ የሰው ንብ ይወራቸዋል  ‹‹ እስኪ አትራኮቱ አጭር መንገድ ነው የምንጭነው ! ›› ይላሉ ኢትዮጽያዊ የማይመስሉት ሾፌርና ወያላ ቀብረር ብለው ፡፡ ባቡሩ ይሰራልሃል የተባለው ከተሜ መስዋዕትነቱ ስለበዛበት እህህእያለ ለአጭሩ መንገድ ሁለት እጥፍ ይከፍላል ፡፡ ሁለት እጥፍ ከፍሎ እንኳ አንድ ወንበር ላይ ለሁለት መቀመጥ ከናፈቀው ቆየ ‹‹ የታክሲና የሰው ትርፍ የለውም  ! ›› የሚል አዲስ ሌክቸር በወያላው ይሰጠውና ትርፉን እንዲያቅፍ ወይም እንዲያዝል ይገደዳል ፡፡

ይህ በባቡሩ ዘመን አይደለም ቀድሞም ተለምዷል ፡፡ አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ ፡፡
 
የትራፊክ ፖሊሶችን መጥፋት ወይም ቢኖሩም ከቁብ ባለመቁጠር የታክሲ ሾፌሮችና ወያላዋች መንገደኛውን ላይ በላይ ይጭናሉ ፡፡ ተሳፋሪው ምንም ሳያማርጥ መሬት ላይ ሁሉ ይቀመጣል ፡፡ ሁለት የተለዩ መንገደኞች ግን  በሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች የጦፈ ጭቅጭቅ ጀመሩ ፡፡ ወንበር የያዘው ሰው እጥፍ ከፍዬ ሶስተኛ ሰው አላስቀመጥም ሲል የሌላኛው መከራከሪያ ለአስር ደቂቃ መንገድ ምቾት ብታጣ ምንም አይደለም የሚል ነበር ፡፡ በርግጥም ሁሉም ወንበሮች ሰዋችን ደርበዋል ፡፡ ቀስ በቀስ የክርክሩ አቅጣጫ ተለውጦ እንካ ሰላንቲያ ጀመሩ ፡፡

እንካሰላንቲያ
በሜንታ

አልተባባሉም እንጂ የጅራፉን ሰላምታ ማስጮህ ቀጥለዋል ፡፡
‹‹ ክብርና ምቾት ከፈለግህ ለምን መኪና አትገዛም ? ›› ይለዋል አትቀመጥም የተባለው በስጨት ብሎ
‹‹ ይኑረኝ አይኑረኝ በምን ታውቃለህ ?! ›› ባለ ወንበሩ ይመልሳል
‹‹ መኪና አይደለም መኪና ሰፊ የምታውቅ አትመስልም ! ››
‹‹ መኪና እንኳ እንደማይሰፋ የማታውቅ ልቅ አፍ ነገር ነህ ! ››
‹‹ እረ አንዳች ይልቀቅብህ ! ››
‹‹ ግፊያና ስድብ ከተማርክበት አውቶብስ ወደዚህ መምጣት አልነበረበረህም !  ››
ጥቂት የእንካ ሰላንቲያ ሸርተቴዎችን እየተጫወቱ ወደታች ቢወርዱ ኖሮ መናተራቸው አይቀሬ ነበር ፡፡ ሰውን እንደ ጆንያ ሲጠቀጥቅ የነበረው ሾፌር ዲፕሎማት ሆኖ ጣልቃ ገባ ‹‹ ለምን አትቻቻሉም ! አሁን አይደል ጥላችሁት የምትወርዱት ? ››

በርግጥ መቻቻል  እንዴት ?  ለምንና መቼ ነው የሚያስፈልገን  ?  በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ የጥልና ግጭት ምርት በከፍተኛ ደረጃ ከሚመረትባቸው መስኮች መካከል  ትራንስፖርት ማጓጓዣ እንዲሁም ሰልፎች ዋነኞቹ ሳይሆኑ አይቀሩም  ፡፡ ሰልፉ የዳቦ የመብራት ክፍያ ፣ የስራ ምዝገባ የሆስፒታል የስታዲየም ወዘተ ሊሆን ይችላል ፡፡
በሆነው ባልሆነው ህግና መመሪያ ማውጣት የሚወደው መንግስት ወደ ሰሚትና አያት በሚያቀኑ አውቶብሶች ላይ ያለውን ሁኔታ ቢመለከት አንድ ስራ ሊያገኝ በቻለ ነበር ፡፡ በነዚህ መስመሮች የሚጠቀሙ ሰዋች ሙዚቃም ሆነ ሬዲዮ መስማት የሚፈልጉት ከአውቶብሱ ሳይሆን ሞባይላቸውን አምቦርቅቀው በመክፈት ነው ፡፡ ምን አይነት ልምድ እንደሆነ አልተገለጸለኝም ፡፡ ለምን የጆሮ ገመድ መጠቀም እንደማይፈልጉ አልገባኝም ፡፡ ሙዚቃው ኤፍኤም ሬዲዮው ከሬዲዮው ጋር አብሮ የመዝፈን ጣጣምናለፋችሁ አንዳንዴ የሆነ የእግር ኳስ ቡድን አሸንፎ ከደጋፊዎቹ ጋር የምትጓዙ ሁሉ ሊመስላችሁ ይችላል ፡፡

ሞባይልዎ  ቢጠራ ለማነጋገር የትኛውን ሰው ‹ እባክህ ቀንስው ወይም ዝጋው ? › እንደሚሉ አይታወቅም ፡፡ ካሉም ምናገባህ !  › ወይምስትፈልግ ጆሮህን መዘጋት ትችላለህ ! › መባል ይመጣል - ይህም ነው እንግዲህ ያልተፈለገ ግርግር ውሰጥ የሚከተው ፡፡ የሆነ ፈላስፋ ወይም ደራሲ በኢትዮጽያ አውቶብሶች ውስጥ ሲጓዙ ፕራይቬሲም ሆነ ከራስ ጋር ማውራት አይቻልም የሚል ታላቅ ሀረግ  እንዴት እስካሁን ጣል አላደረገም ?  ደፋሮቹ የማስታወቂያ ሰራተኞቻችን ግን በሆነ ባስ ሲሄዱ ቀና ነው መንገዱ  ያሉ ይመስለኛል ፡፡  

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ አንበሳ ያሰራቸውን ሽንጠ ረጃጅም አውቶብሶች ሀገሬው ‹‹ አኮርዲዮን ›› እንደሚላቸው ይታወቃል ፡፡ ይህን ስያሜ አንድ ቦታ ‹‹ አባጨጓሬ ›› ሲባል ሰምቻለሁ ፡፡ በቅርቡ ደግሞ ሰሚት አካባቢ  ‹‹ ትግሬና ኦሮሞ ›› ከሚል መጠሪያቸው ጋር ስተዋወቅ ሳቅ አምልጦኛል - አይ ሰው በማለት ፡፡ ትግሬው ኦሮሞውን ይጎትተዋል የሚል ነው ፖለቲካዊ አንድምታው ፡፡ ብቸኛው አዲሱ አውቶብስ ደግሞ ‹‹ አማራ ›› ተብሏል ፡፡ እንዴት ?  የሚል ጥያቄ ለሚያነሳ ‹‹ አማራ ቀብራራ ስለሆነ ›› የሚል ምላሽ ያገኛል ፡፡

ዞሮ ዞሮ ትግሬና ኦሮሞ በሚለው ስያሜ ምክንያት ወጣቶች እስከመደባደብ ደርሰዋል ነው የሚባለው ፡፡ እኛ አቃፊ እንጂ ተጎታች አይደለንም በሚል ፡፡ እኛ የሀገር አስኳል እንጂ ቅርፊት አይደለንም በሚል ፡፡ በሀገራችን ብብሄር ብሄረሰቦች ባህል ፣ ወግና ቋንቋ መቀላለድ አዲስ ባይሆንም አንዳንዴ ስቆ ለማለፍ ወይም መቻቻል ከሰማይ ሲርቅ ይታያል ፡፡

መቻቻልን ማወቅ ወይም ለመቻቻል መስዋዕትነትን መክፈል የሚያስገኘው ጠቀሜታ ላቅ ያለ ነው ፡፡ ታክሲ ውስጥ ወያላው አስር ሳንቲም መልስ አልሰጠኝም ብሎ መሰዳደብ ወይም መቧቀስ በሂሳብ ቢተመን የሚያዋጣ አይደለም ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጓደኛዬን ወይም ሚስቴን አፍጥጠህ ተመልክትሃል በማለት ከማያውቁት ሰው ጋር ይጣላሉ ፡፡ ጉረቤታሞች በዶሮ በህጻናትና በአንድ ስንዝር መሬት ጦርነት ያወጃሉ ፡፡ ቼልሲ ከአርሴናል የጠነከረ አቋም አለው ብሎ አስተያየት የሚሰጥ ወጣት በፍጥነት ሊኮረኮም አሊያም ከድራፍት ቆይታ በኃላ  በጩቤ ሊወጋ ይችላል ፡፡

መቻቻልን ባለመቻል ክቡር ህይወት ሊጠፋና ሊጎድል ፍትህ ሊጠፋና ጭቆና ሊያቆጠቁጥ ይችላል ፡፡ ሚስቴን ሳያባልግ አይቀርም በሚል ጥርጣሬ የሰው እግር በገጀራ መቁረጥ እንደ ዛፍ መገንደስ ቀላል አይደለም ፡፡ ጓደኛዬ ጣል ጣል አደረገችኝ በማለት የሀገር ድንበር በሚጠበቅበት መሳሪያ በንጹሃን የቤት ድንበር ውስጥ እየገቡ ደም ማፍሰስ ሀገራችን ውስጥ ወጥቶ እያጨቃጨቀ ከሚገኘው የሽብርተኛ ህግ አቅም በላይ ነው ፡፡ ስቸገር አረዳኝም ብሎ መከታ የሆነውን ወንድም ጋሻ የሆነውን አባት ወይም መኩሪያ የሆነን የቅርብ ዘመድ እስትንፋስ ማቋረጥ የሰይጣን እንጂ የሰው ልጅ ተልዕኮና ግብ አይደለም ፡፡ በአንድ ወቅት የተማረኩበትን አይን በተልካሻ ምክንያት ጎልጉሎ ማውጣት በአንድ ወቅት ለማየት ይጓጉበት የነበረ ፊት ላይ አሲድ ደፍቶ ማፈራረስ የስግብግበነት እንጂ የፍቅር ቴርሞሜትርን አያሳይም ፡፡

መቻቻል አስፈላጊ ነው የሚባለው በመቻቻል እጦት ከፍተኛ አደጋ ሊደርስ ስለሚችል ነው ፡፡ መንግስታት የሃይማኖት አባቶች የህግና ስነልቦና ምሁራን ስለ መቻቻል የሚሰብኩት መቻቻል ከህግ በላይ ሆኖ አይደለም ፡፡ መቻቻል ሞራላዊ ግዴታ በመሆኑ እንጂ ፡፡ በተለይ የፖለቲካ መቻቻል በስም እንጂ በተግባር ባለመታየቱ ግጭቶችና ቀውሶች ከተሰቀሉበት የክፋት ጫፍ ባንዲራቸውን እያውለበለቡ ይገኛሉ ፡፡

መንግስት ሀገርን በህብረት ለማሳደግ የሚያስፈልገው ‹‹ ብሄራዊ መግባባት ›› ነው ሲል ተቃዋሚዎች የሀገራችን መሰረታዊ ችግር ‹‹ ብሄራዊ እርቅ ›› ቦታ ባለመስጠታችን ነው ይላሉ ፡፡መግባባትእናእርቅበቀናዎች አይን ሲታዩ ሊጠጋጉ የሚችሉ ሃሳቦች ቢሆኑም በፖለቲካው ብይን ግን እሳትና ጭድ ሆነዋል ፡፡ እርቅ የሚጠየቀው ማን ከማን ተጣልቶ ነው የምታረቀው ባይ ነው ፡፡ መግባባት ፈላጊው ማንነትን በጎሳ ከመቸርቸር ይልቅ ህዝባዊ አንድነት እንዲፈጠር የሚያስችሉ ስራዎችን አስቀድም ይባላል ፡፡ ለነገሩ የሀገራችን ፖለቲካ እናሸንፋለንእና እናቸንፋለንአቅም እንኳ ልዩነቱን የሲኦልና የገነት ያህል በማስፋት ስንት እልቂትና ጥፋት እንዲፈጠር ቀለሃ ያቀበለ ነው ፡፡

የሀገራችን ፖለቲካ ከስርዓቶች ውድቀት ከመማር ይልቅ የስርዓቶችን የሃጢያት መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት የሚያስደስተው ነው ፡፡ በመዝገበ ቃላቱ ብይን መሰረት አንዱ ህግ አስከባሪ ሌላው አሸባሪ ነው ፡፡ አንዱ መብት ጠያቂ ሌላው መብት ነፋጊ ነው ፡፡ አንዱ የነጻነት ብርሃን ሌላው የተገኘውን ብርሃን አድናቂ ነው ፡፡ አንዱ ሰጪም ነሺ ሌላው ትርፍራፊ አንሺ ነው ፡፡ አንዱ ሁሉን አዋቂ ሌላው የጭብጨባ አርቃቂ ነው ፡፡ አንዱ ለብዙሃኑ ዋስትና ሌላው የፍርሃት ፈተና ነው ፡፡ አንዱ የልማት ጓድ ሌላው የጥፋት ጉድጓድ ነው ፡፡ አንዱ ለሀገር ተቆርቋሪ ሌላው ነገር ቆርቋሪ ነው ፡፡ አንዱ የሀገር አባት ሌላው የሀገር እበት ነው ፡፡

ሃይማኖት የግል ሀገር የጋራ የሚባለውን አንድምታ ባለመቀበልም ግጭቶች ይከሰታሉ ፡፡ ባል እሳት ሲሆን ሚስት ውሃ እንድትሆን የሚመከረው ኪሳራ እንዳለው ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም ፡፡ ኪሳራው ፍቺ ከሚያስከትለው ቀውስ ስለማይበልጥ እንጂ ፡፡ በየሰፈራችን ሰውን የሚያስታርቁ ሽማግሌዎች ‹‹ ይቅር መባባል ይበልጣል ›› በማለት ተልዕኳቸውን የሚፈጽሙት በዳይና ተበዳይን አብጠርጠረው ሳያውቁ ቀርተው አይደለም ፡፡ ይበልጥ መቻቻል ያስፈልጋል ከሚል እምነት እንጂ ፡፡ በቅናት፣ በትንሽ ገንዘብና በመሳሰሉት ጉዳዮች የሰው ህይወት አጥፍተው ማረሚያ ቤት የሚወርዱ ሰዎች ቆይተው የሚጸጸቱት አስቀድመው ‹‹ መቻቻል ›› ባለማገናዘባቸው ነው ፡፡

ተወደደም ተጠላ መቻቻል ውስጥ ‹‹ ሂሳብ ›› አለ ፡፡ ሂሳቡ ሁልግዜ ለሁለቱም ወገን ሃምሳ ሃምሳ ለማካፈል አይችልም ፡፡ አንዱ ለግዜው በስሱ መጉዳት ይኖርበታል ፡፡

 ማስታወሻ፡ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ላይ የወጣ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡