Saturday, September 8, 2018

አርበኞች ግንቦት 7 እንኳን ደህና መጣህ




ወያኔ በግዳጅ በጫነው ፖለቲካዊ አደረጃጀት ሳቢያ ህዝባቸውን ለመታደግ ሲሉ ብሄር ተኮር አደረጃጀት ፈጥረው የተንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ማክበር ተገቢ ነው ፣ በተለይም የእውነት ለታደጉትና እየታደጉ ለሚገኙት ፡፡ ሁሉን በአንዲት ታላቅ ሀገር ስም ፣ ሁሉን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ደምረን እንሰራለን የሚሉ ድርጅቶች ሲገኙ ደግሞ ክብራችን ሌላ ጋት ይጨምራል ፡፡

አስጊ ጫፍ ላይ የተንጠለጠለችውን ኢትዮጵያ ወደ መሃል ስቦ ሚዛኗንና ሚዛናዊነትን ለማስጠበቅ እሰራለሁ የሚለውን አርበኞች ግንቦት 7ን ማበረታታትና መደገፍ የውዴታ ግዴታ ሆኗል ፡፡ ለምን ? ነባራዊው የፖለቲካ ሁኔታ የሚነግረን ጥቂት የአንድነት ወይም ኢትዮጵያዊያን ሃይሎች በየትየለሌ ብሄር ዘመም ድርጅቶች ተውጠው መገኘታቸውን ነው ፡፡ ብሄር ተኮር ድርጅቶች እድል አግኝተው ምርጫ ቢያሸንፉ እንኳ በኢትዮጵያ ላይ የሚኖራቸው የመጨረሻ ግብ ግልፅ አይደለም ፡፡ ኢትዮጵያ እንዳትፈራርስ ዋስትና የሚሰጥ ጠንካራ የፖለቲካ ፕሮግራምም የላቸውም ፡፡

ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊነትን እያዜመ የሚገኘው < አዲሱ ኢህአዴግ > እንኳ የአቅጣጫና የርዕዮት መስመሩን አላሻሻለም ፡፡ አራቱ እህት ድርጅቶች ሜጀር ተግባራቸውም ሆነ ቀጣይ ግባቸው ብሄር ተኮር ድልድይ መገንባት ይሆናል ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚጠቃቅሱት በማይነር አስተምህሮት ነው ፡፡ በዚህ ስሌት ኢትዮጵያነት እንደምን ገዝፎና አሸንፎ ሊወጣ እንደሚችል ግልፅ አይደለም ፡፡ ከአቅጣጭ አንፃርም ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መንገዱን እንደማይለቅ ዶ/ር አብይ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል ፡፡ በልምድ እንዳየነው ደግሞ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዘብነት ወይም ጥብቅና ለብሄሮች እንጂ ለኢትዮጵያዊ ዜግነት አይደለም ፡፡

በብሄር ብቻ ሳይሆን በሃሳብ እና በአመክንዮ የሚወዳደሩ ጠንካራና ብስል ድርጅቶች ያስፈልጉናል ፡፡ በብሄርም ሆነ በዜግነት ማሰብ የወገንተኝነት መዳረሻ አለው ይባላል ፤ ትክክል ነው ፡፡ ፍትሃዊ ትክክለኝነት የሚመነጨው ግን የአግላይነት ድንበር ሲነሳ ነው ፡፡ የብሄር እሳቤ ትልቁ በሽታ ቀስ በቀስ ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል ወደፈጠረው የአሳማዋች ፍልስፍና የማዳረሱ ክፋት ነው ፡፡ እንደሚታወቀው በአኒማል ፋርም አብዮት ያነሱት አሳማዋች የመጀመሪያ መፈክራቸው ውብ ነበር ፡፡ < ሁሉም እንስሣት እኩል ናቸው > እያሉ ነበር የሚዘምሩት ፣ ለውጡን በሙሉ ልብ ለመደገፍ የቆሙት ፡፡ እየዋለ እያደር ግን ብሄራዊ መፈክራቸው ወይም ህገ መንግስታቸው  < እኛ የተሻልን ነን > በሚሉ አሳማዋች ተቀይሮ ALL ANIMALS ARE EQUAL BUT SOME ANIMALS ARE MORE EQUAL THAN OTHERS የሚለውን ዘረኛ አንቀፅ ተሸካሚ ሆነዋል ፡፡ ሃሳቡን የማይደግፉ ሁሉ ትምክህተኛ እየተባሉ ተዘልፈዋል ፣ እንዲሸማቀቁ ተደርጓል ፣ ከመኖሪያ ቀያቸውም ተፈናቅለዋል ፡፡ የብሄር እሳቤ ትልቁ በሽታ < እኔ ከሌሎች የተሻልኩ ነኝ > የሚል ስስታም ተቀጥላ ስለሚያመነጭ ለዘወትር ብጥብጥና ግጭት መንሳኤ መሆኑ ነው ፡፡

ይህን በመሰሉ 40 እና 50 ድርጅቶች ተውጦ ፖለቲካን መስራት ደግሞ ያሰጋል ፡፡ መቼም ቢሆን ስነልቦናዊ መረጋጋትን ፈጥሮ በኢኮኖሚውም ሆነ ማህበራዊ ሰልፍ ወስጥ ራስን ለማስገባት ያስቸግራል ፡፡ የዳር ተመልካቹን ፣ የምናገባኝ አቀንቃኙን ፣ ባለግዜዎቹ  ይዘውሩት ባዩን ያበራክታል ፡፡ ሀገር ሰልላ እንድትሞትም አሉታዊ ሚና ይጫወታል ፡፡ ለዚህም ነው ፖለቲካው በቋንቋና ብሄር ብቻ ሳይሆን በሃሳብ ይሞገት የሚባለው ፡፡ ሃገር የሚያሳድገውና የሚያስከብረው ለሁሉም የሚጠቅም የዳበረ ሃገራዊ ሃሳብ ሲመነጭ ነው ፡፡ ሃሳብ ሳይገደብ ሊፈስና ሊመነጭ የሚችለው ደግሞ አጥር ሲፈራርስ ነው ፡፡ ከጠባብና የሚያፍን ክፍል ወጥቶ ማለቂያ በሌለው መስክ ላይ እንደልብ መሯሯጥ ሲቻል ፡፡

ህዝቡ በቅርቡ የተገኘውን ለውጥ የደገፈው ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ ስለተዘመረለት ነው ፡፡ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ አንድነት ፣ ሰላምና ፍቅርን አበለፅጋለሁ ብሎ ስላሰበ ነው ፡፡ ይህ ከፍታ ደረጃውን ጠብቆ ይጓዝ ዘንድ እንደምሶሶ ጠልቀው የተቸነከሩ ድርጅቶች እዚህና እዚያ መታየት ይኖርባቸዋል ፡፡

ተወደደም ተጠላ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት ፡፡ የሚመጥናት ትልቅነቷን ጠብቆ ከተቻለም አልቆ የሚጓዝ ድርጅት ነው ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ዳግም ለማንገስ ተስፋ ከተጣለባቸው ድርጅቶች አንዱ አርበኞች ግንቦት 7 ነው ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ስለ ኢትዮጵያዊነት ሆ ! ብለው ቢዘምሩ ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ የግጥምና ዜማ ድርሰት ለማበርከት መዘጋጀት ስለሚችል ነው ፡፡ ሌላ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ድርጅት እንደ አማራጭ እስኪወጣ ድረስም ግንቦት 7 እንዳይደናቀፍ አጥርና ጋሻ ሆኖ መመከት ያስፈልጋል ፡፡ ይህ ድርጅት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስኖ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ትልቅ ትርጉም አለው ፡፡ ከመሰል ድርጅቶች ጋር ህብረት ፈጥሮ ስለሚንቀሳቀስም የተፈጠረው ኢትዮጵያዊነት እሳቤ እንዲቀጣጠልም ይረዳል ፡፡ ቢያንስ በዘውገኞች የተከበቡ ዜጎች ተስፋ እንዳይቆርጡ ተስፋ እና ዋስትና ይፈጥራል ፡፡ አርበኞች ግንቦት 7 በትክክለኛው ግዜና ቦታ የተገኘ ድርጅት ስለሆነ እንኳን ደህና መጣህ ሊባል ይገባል ፡፡

Saturday, August 18, 2018

በግማሽ ሜዳ መጫወት ...



ሶሎ ጎል ይሉታል ፈረንጆቹ ፡፡ አንድ ተጫዋች በርካታ ባላጋራዎቹን አልፎ ጎል ሲያስቆጥር ፡፡ በጥበብ ፣ አካላዊ ብቃት ፣ ብልጠትና ድፍረት መሞላትን ስለሚጠይቅ ሁሉም ተጫዎቾች ሊያከናውኑት አይችሉም ፡፡ እናም ለግብ አግቢው ከወንበር ተነስቶ የረዘመ ጭብጨባና ክብር መስጠት ግድ ይላል ፡፡

ልክ እንደ ሶሎ < ዋው > የሚያስብል ሌላ ጥበብም እለ በእግር ኳሱ ዘንድ ፡፡ ከግማሽ ሜዳ ኳስን በትክክል መትሮ ጎል ማስቆጠር ፡፡ ይህንም ሲያደርጉ ያየናቸው ጥቂት የዓለማችን ተጫዋቾች ናቸው ፡፡ ጁዋን ካርሎስ ፣ ናቢ ፍቅርና ዋይኒ ሩኒን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል ፡፡ ኤቨርተንና ዌስትሃም ሲጫወቱ ዋይኒ ሩኒ ያደረገው ምንድነው ? ከክልሉ ወጥቶ ኳሷን ወደ መሃል ያወጣትን በረኛ ሁኔታ በመገንዘቡ ኳሷ ስትደርሰው ቀጥታ ወደፊት አጎናት ፡፡ ዳኛው የተለጋውን ኳስ እንዳይነካ አፈገፈገ ... ሁለት ተጫዋቾች ባለ በሌለ ሃይላቸው ወደላይ ለቴስታ ዘለሉ ... የመጨረሻው ተከላካይ ከሩቅ የተለጋ ኳስ ከሚቆጠርብን በእጄ ለኤሪጎሬ ባስቀራት ይሻላል ብሎ ወደ ላይ ዘለለ – አላገኛትም ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግብ ጠባቂው ወደጎል ሮጦ በማያውቀው ፍጥነት እየተፈተለከ ነበር ፡፡ ልብ አንጠልጣይ ድራማ ካየን በኋላ ኳሷ ከመረቡ ጋ ተሳሳመች ፡፡

ዶ/ር አብይ በእነዚህ አብዶኛ ተጫዎቾች ይመሰላሉ ፡፡ ከግማሽ ሜዳ የጠለዟቸው የፖለቲካ ኳሶች ጅቡቲ ፣ ሱዳን ፣ ግብፅ ፣ ሳዑዲ ፣ ኡጋንዳና ኤርትራ አርፈው ድል አስቆጥረዋል ፡፡ በአንድ በኩል የዲፕሎማሲውን ግንኙነት ሲያጠናክሩ በሌላ በኩል ማንም ሀሳብ ውስጥ ያልነበሩ ዜጎችን ከእስር አስፈትተዋል ፡፡ ወደክልሎች በመጓዝ ጥበብ ፣ ብልጠትና ድፍረት የተሞላበት ሃገራዊ ምክክር አድርገዋል ፡፡ በጎሳና ዘረኝነት ክፋት ተሰነጣጥቆ ሊበተን የነበረውን ኢትዮጵያዊ ትሪ ጠግነዋል ፡፡ የተራራቁ ሰዋች በአንድነት ተሰባስበው ባዛው ትሪ ላይ ማዕድ እንዲቀርቡ ፣ የጋራ ፀሎታቸውም ፍቅር ፣ ሰላምና ኢትዮጵያዊ ድማሬ እንዲሆን መንገድ አሳይተዋል ፡፡ ርቆ የተቀበረው ኢትዮጵያዊነት ክብሩ ተመልሶ ከባንዲራ በላይ እንዲውለበለብ አድርገዋል ፡፡

ዶ/ር አብይ በአጭር ግዜ ውስጥ ያስመዘገቧቸው ድሎች አመርቂና ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም እየተጫወቱ የሚገኙት በግማሽ ሜዳ ነው ፡፡ ከትልቁ ጥያቄ አንደኛው ስንቱን ህዝባዊ ጥያቄ ከግማሽ ሜዳ እየመተሩ ማስገባት ይችላሉ ? የሚለው ነው ፡፡ ከትልቁ ጥያቄ ሁለተኛው ስንቱን እግር ሰባሪ ተከላካይ በአብዶ እየሸወዱ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚለው ነው ፡፡

ዶ/ር አብይ ብዙ ተከላካዮችን አብዶ ሰርተው አልፈው ጎል የሚያስቆጥሩት ኢትዮጵያዊነትን ከዳር እስከ ዳር ለማሳደግ ነው ፡፡ ይሁንና ጥቂትም ሳይቆይ ሲዳማው ፣ አገው ፣ ጉራጌው በኔ ልክ የተሰፋ ክልል ይገባኛል ብሎ ጥብቆ ሲናፍቅ ታገኘዋለህ ፡፡ ዶ/ር አብይ ብዙ ተከላካዮችን አብዶ ሰርተው አልፈው ጎል የሚያስቆጥሩት  እንደ < ገነት > የምንናፍቀውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እናይ ዘንድ ጥርጊያ መንገዱን ለመገንባት ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ለድሃ ዳቦ እንጂ ነፃ ስርዓት አያስፈልገውም የሚሉ አምባገነኖች በተሰነጣጠቀው መንገዳችን ላይ የሚፈነዳዳ ፈንጂ ከመቅበር ሊቆጠቡ አልቻሉም ፡፡ ዶ/ር አብይ ከመሃል ሜዳ ለግተው ጎል የሚያስቆጥሩት የማሸነፍ ረሃብን ለማስታገስና ሮል ሞዴሎችን ለመቅረፅ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ማጥቃትንም ሆነ መከላከል እርግፍ አድርገው ትተው ጨዋታ የሚያቆሙ ብዙሃንን ታያለህ ፡፡ በሌላ አነጋገር ጨዋታውን አቋርጠው በፎርፌ ማሸነፋችን ይታወጅልን የሚሉ ፡፡ እነዚህ ወገኖች በጥቂት ወይም ሚዛን በማያነሳ ምክንያት ዱላ ፣ ገጀራና ክብሪት አንስተው ቀጣዩን ጥፋት ለማከናወን የማያመነቱ ሆነዋል ፡፡ ነገር ቆስቋሾች ፣ ገዳዳ አክቲቪስቶች ፣ በቀልተኛ ፖለቲከኞች ጃስ ባሏቸው ቁጥር ለምን ? እና እንዴትን ? ሳያነሱ ዘለው ንጹሃንን የሚናከሱ ወገኖቻችን እየበዙ መጥተዋል ፡፡ እነዚህን ሁሉ መግራት ከባድ ነው ፡፡ በአንድ ቀን ምክክርና የእርቅ ጉባኤም አጀንዳውን መዝጋት አይቻልም ፡፡

ጠ/ሚ/ሩ በየክልሉ በዘር ፣ ቋንቋና ሃይማኖት የሚለኮሱ ግጭቶችን ለማብረድና ለማስታረቅ የሚሯሯጡ ከሆነ ሌላውን አንገብጋቢ ስራ መስራት አይችሉም ፡፡ የፖለቲካ መዋቅሩም ሆነ ህዝቡ ጥሩ ጎል አግቢ ስለሆኑ እሳቸውን ብቻ የሚጠብቅ ከሆነ ሽምግልና እንጂ መንግስታዊ አሰራር ውሃ ይበላዋል ፡፡ ለዚያም ነው ጠ/ሚ/ሩ በግማሽ ሳይሆን በሙሉ ሜዳ መጫወት የሚችሉበት ቋሚ አሰራር መፈጠር አለበት የሚባለው ፡፡ ለዚያም ነው ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ለግተው ግብ የሚያስቆጥሩ ኮኮቦችን ማፍራት ይገባቸዋል የምለው ፡፡

ርግጥ ነው በሀገራችን ያንዣበበውን ስጋት ለመቅረፍ ክፋትንና ድህነትን ተጭኖና አጥቅቶ በመጫወት ተደጋጋሚ ግቦችን ማስቆጠር ያስፈልጋል ፡፡ አለበለዚያ አቻ መውጣትና መሸነፍም ያጋጥማል ፡፡ አቻ መውጣት ክፋትንና ድህነትን አቅፎ መኖር ነው ፡፡ ወንድም ጋሼ ... ጌታ መሳይ... እያልከው ፡፡ ከተሸነፍክ ያለውድ በግድ < ጅቦች ለዘላለም ይኑሩ ! > የሚል መፈክር ተሸክመህ ትዘልቃለህ ፡፡ እነሱ የሚጥሉትን ቅንጥብጣቢ አያሳጣኝ እያልክ ፡፡ የሰላምና የፍቅርን ኳስ በማራኪ አጨዋወት እስከተቃራኒው ክልል ደርሶ ያማረ ጎል ማስገባት ያስፈልጋል ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ለዋናው አጥቂ ኳስ አመቻችተው የሚሰጡ ደጀኖች ፣ አጥቂው ሲደክም ጎል ማስቆጠር የሚችሉ ቁርጠኛና ጥበበኛ ተጫዋቾች መሰለፋቸው መረጋገጥ ይኖርበታል ፡፡

በየክልሉ የሚለኮሱ ጎሳዊ ግጭቶችን ለመቀነስና ለመከላከል የተጠናከረ ትምህርትና ስልጠና ግድ ነው ፡፡ ለ27 ዓመታት የዘውጌ ስርዓት በማበቡና ብሄርተኝነት የተሻለ አማራጭ ተደርጎ በመሰበኩ ኢትዮጵያዊነትን በቀላሉ ማስረፅ ሳይከብድ አይቀርም ፡፡ ይህን ስራ የሚሰሩ የሲቪክ ተቋማትን ማስፋፋት ይጠይቅ ይሆናል ፡፡ ተመሳሳይ የፖለቲካ መስመር የሚከተሉ ድርጅቶችንና ቲንክታንኮችን Add እና Tag ማድረግ ግድ ይመስላል ። በውስጥ አሰራር ደግሞ ለንቋሳ አመራሮችን እየሻሩ ፣ ጠንካሮቹ ንቃተ ህሊናን ለማዳበር የሚያስችሉ የምክክር መድረኮችን ረጅም የስራ አካልና ግብ አድርገው እንዲተጉ ማሳሳብ ይጠበቃል ፡፡

ዘረኝነትና ጎሰኝነት አይደለም በአፍሪካ በአውሮፓ መሞት አልቻለም ፡፡ ጉዳት እንዳያደርስ ሸብቦ የያዘው ግን ጠንካራ ህጋቸው ነው ፡፡ ዶ/ር አብይ የፍቅርና ይቅርባይነትን ሎጎ ከፍ በማድረግ አስተዳደራቸው እንዳይንገጫገጭ ማድረግ ቢችሉ ሸጋ ነበር – ድብቁና ውስብስቡ ፖለቲካ ግን በዚህ ቀመር የሚሰራበት አግባብ በእጅጉ የሰለሰለ ነው ፡፡ አሸባሪ ፖለቲከኞችን ፣ የዘረኝነት ፈንጂ ቀማሚዋችን ፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት ሃሳብ ፣ ክብሪትና ጥይት የሚያቀብሉ የደም ነጋዴዋችን በአጠቃላይ ህገወጦችን መስመር የሚያሲዙበት ህጋዊ ማእቀፍ ያስፈልጋቸዋል ፡፡

Thursday, August 9, 2018

የኦሕዴድ የነገ ፈተና ...




ስልጣኑ ያለው ኦህዴድ ውስጥ ነው ፤ ኦሮሚያ ልብ ውስጥ ግን ኦነግ ከፍ ብሏል ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ለዶ/ር አብይ አህመድ ፣ ለአቶ ለማ መገርሳና ለቲም ለማ ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት አለው ፡፡ ማሳያዎቹ ብዙ ናቸው ፡፡ ለምሳሌ በርካታ የሜኔሶታ ነዋሪ የሆኑ ኦሮሞዋች ሁለቱን መሪዎች በላቀ ደስታና የጀግንነት ስሜት ነው የተቀበሏቸው ፡፡ ነዋሪው የወደደው ግን ግለሰቦቹን ወይም የቲም ለማ ቡድንን እንጂ ባልሰልጣናቱ የቆሙበትን ድርጅት ጭምር አይደለም ፡፡ ድርጅታቸው የሰራውን ተግባር ዋጋ ለመስጠት አልፈለገም ፡፡ የዚህ አይነተኛ መገለጫ ደግሞ ከኢህዴድ ባንዲራ ይልቅ የኦነግ መለያ አዳራሹን ማጥለቅለቁ ነው ፡፡

በወቅቱ ባለስልጣናቱ ምን ያህል እንደተገረሙ ወይም ምን እያሰቡ እንደሆነ ማወቅ ቢቻል እንዴት መልካም ነበር ብዬ አስቤ ነበር ፡፡ ግን ስሜታቸውን ደብቀው ወይም ተቆጣጥረው መውጣት ችለዋል ፡፡ አንዳንዶች ይህ ጉዳይ ሜኔሶታ የተፈጸመው ኦነግ ለበርካታ አመታት የፓለቲካ ድልድዩን በእያንዳንዱ ሰው አካል ላይ መገንባት ስለቻለ ነው ይሉ ይሆናል ፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳ ኦ ኤም ኤን አዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀው ዝግጅትም ላይም የኦነግ ባንዲራ ግዘፍ ነስቶ ታይቷል ፡፡ አዲስ አበባና አካባቢዋ ደግሞ ኦህዴድ እንጂ ኦነግ የፖለቲካ ድልድይ ለመገንባት እድል አልነበረውም ፡፡ ከለውጡ በፊትና በኋላም ቢሆን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በተካሄዱ ሰልፎች ላይ የኦነግ ምልክት በዋዛ የሚታይ አልነበረም ፡፡ ታሪካዊና ገራሚ አባባሎችን እንዲሁም ሳቅ ጫሪ መፈክሮችን ሲያውለበልብ ያየነው ህዝብ < ኦህዴድ ደማሪ ድርጅታችን ነው > ለማለት ባይደፍር እንኳ < እናመሰግለን > የሚል ባነር ከፍ ለማድረግ እጁን ምን እንደያዘው አጠያያቂ ነው ፡፡

ነገሩ ፓራዶክስ ይመስላል ፡፡ ቄሮና የፖለቲካ ድርጅቶች ከመላው ህዝብ ጋር በመተባበር ለውጡን አፋጥነውት ይሆናል ፡፡ የትግሉ መስመር በተለይ በኢትዮጵያዊነት ሃዲድ ላይ ዳግም እንዲጓዝ ያደረጉት ግን አብይና ለማ ናቸው ፡፡ የአነዚህን ሰዎች የላቀ ጥረት ዋጋ ሳይሰጡ መጓዝ ይከብዳል _ ኢትዮጵያዊነትን ቸለል ካላሉት በስተቀር ፡፡ የአንደበት ወዳጁ ህልቆ መሳፍርት የለውም ፣ በተግባር ልብ ውስጥ ያለው ማህተም ግን ንባቡ ሌላ እየመሰለ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንደዋዛ እንድንጠይቅ እያደረገ ነው ፡፡ ህዝቡ የምንወዳችሁ እኛ የያዝነውንም ስትወዱልን ነው እያለ ነው ? የድልድይ ሚናነት ስለተጫወታችሁ እናመሰግናለን እኛ ግን ከዚህኛው ወገን ነን እያለ ነው ? ወይስ የቲም ለማ ቡድን ነገ ከኦነግ ጋር እንዲቀላቀል በንግር / Foreshadowing / ቴክኒከ እያመላከተ ይሆን ?

ዶ/ር አብይ ዋና አላማዬ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ነው ብለዋል ፡፡ መሬት ላይ የሚታየውን እውነት ተከትለን እንበይን ወይም እንገምት ካልን ማለትም ሁኔታዎች በዚሁ መልክ ከተጓዙ በኦሮሚያ የቀጣዩ ምርጫ አሸናፊ ኦህዴድ መሆኑ ያጠራጥራል / ምንም እንኳ የቲም ለማ ቡድን አባላት ወንበር ማግኘት ባይከብዳቸውም / ፡፡ ታዲያ የቡድኑ ልፋትና ጥረት ምንድነው ? ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ? ጥሩ ነው ፡፡ ግን ሽግግሩ ከኢትዮጵያዊነት ቆዳ የተሰራ ጠንካራ ኦህዴድን ለመገንባት የሚያስችል ነው ? ያጠራጥራል ፡፡ ነው ወይስ አንዳንዶች በግልፅ እንደሚሰጉት ኦህዴድ ቀስ በቀስ በህዝባዊ ማእበል እየተሸረሸረና እየተገፋ በኦነግ ሼል ውስጥ ይዋጣል ?

አንድን ሰው ከወደድክ ከነምናምኑ ነው ይባላል ፡፡ በተራ የሎጂክ ትንታኔ መሰረት ፣ ለለውጡ ትልቅ ሚና የተጫወተው ኦህዴድ እውቅና ተነፍጎት የተወሰኑ መሪዎቹ ብቻ የሚወደሱ ከሆነ ድርጅቱ የአደጋ ቀጠና ውስጥ ይገኛል ማለት ነው ፡፡ የድርጅቱ አደጋ ውስጥ መውደቅ ደግሞ የራሱ ጉዳይ ተብሎ የሚታለፍ አይሆንም ፡፡ ምክንያቱም ይህ ድርጅት ለግዜውም ቢሆን አትዮጵያዊነትን በውክልና የተሸከመ ነውና ፡፡ በተራ የሎጂክ ትንታኔ እሳቤ ኦህዴድ < ባለ ተራው > መንግስትም ጭምር ነው ፡፡ እና እንዴትስ ቢያደርጉ ነው ግለሰባዊ ዝናን ተሻግረው ፖለቲካዊ / ድርጅታዊ አሸናፊነትን የሚቀዳጁት ? ነገሩ ቀላል ይምሰል እንጂ የመሆን _ አለመሆን ጥያቄ አለበት ፡፡ የቀድሞው መሪ እንዳሉት ኦህዴድ ሲፋቅ ኦነግ ይሆናል ወይስ ኦህዴድ ሲፋቅ ለመላው ህዝብ አንድነት ይበጃል ?

የኦህዴድ የነገ ፈተና በፍጹም ቀላል አይሆንም ፡፡ ሳይንሳዊ ድጋፍም የሚፈልግ ጭምር ፡፡


Friday, March 30, 2018

የደበበ ሰይፉ የ ‹ ብርሃን ፍቅር › ምስጢር ምንድነው ?



የታላቁ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ የግጥም መጽሐፍ ‹ የብርሃን ፍቅር › ይሰኛል ። በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት በ1980 ዓ.ም ለህትመት የበቃ ቢሆንም ዛሬም እንደ አዲስ ቢነበብ የማይጎረብጥ ይልቁንም በተክለቁመናው የሚመስጥ ስራ ነው ። ማለትም የዜማው ፣ የቃላት አጠቃቀሙ ፣ መልእክቱ ፣ የቤት አመታቱ እና የስንኝ አወራረዱ የአንባቢን ቀልብ ይስባል ።

አንባቢያንና የዘርፉ ባለሙያዎችም ተክለቁመናውን መሰረት በማድረግ ያሳደረባቸውን ስሜት በአስተያየትና በሂስ መልክ ሲጽፉ ኖረዋል ። የማያረጅ ወይም ዘመን ተሻጋሪ ስራ ነውና ነገም ብዙ እንደሚባልለት አያጠራጥርም ።

ደበበ የመጽሐፉን ስያሜ ለምን « የብርሃን ፍቅር » እንዳለው ግን ምንም የተባለ ነገር የለም ። ምንም ያልተባለው ሚዛን የሚደፋ ቁም ነገር ስለጠፋ አይደለም ። እንደሚመስለኝ ትችቶቹ ከተክለቁመናው ባሻገር ያለውን ገጽታ ማየት ባለመቻላቸው ነው ። ደበበ እንደ ብዙ ገጣሚዎች አንደኛውን ትልቅ ወይም ገዢ ሃሳብ ያለው ግጥም አንስቶ ለመጽሐፍ ርዕስነት አላደረገም ፤ በውስጡ ‹ የብርሃን ፍቅር › የሚል ግጥም የለምና ። የመጽሐፉን አጠቃላይ አንድምታ በመለካትም መዞ ያወጣው ነው ለማለት በቂ አይደለም ። ይልቁንም ብርሃናዊ ሚስጢራትን በመስቀለኛ ሃሳቦች እንድንመረምራቸው የፈለገ ነው የሚመስለው ፤ ማለትም ርዕሰ ጉዳዩን ከቀጥታ እይታ ፣ ከተምሳሌት ፣ ከአሊጎሪ አውድና ከመሳሰሉት ፈትሸን እንድናይ ከተቻለም የተገለጸውን ብርሃን እንድንሞቅ ።

ደበበ በስሜት ብቻ ሳይሆን በእውቀትም የሚጽፍ ባለቅኔ በመሆኑ ይህንን አያስብም ብሎ መከራከር አይቻልም ። ጸሐፊ ተውኔትነቱና ተመራማሪነቱም ይህን ሃሳብ ለመደገፍ እገዛ ያደርጋሉ ። ለምሳሌ ያህል ገጸባህሪ ፣ ሴራ ፣ መቼት እና ቃለ - ተውኔት የተባሉ ስነጽሑፋዊ ቃላትን በመፍጠር ሙያዊ እገዛ አድርጓል ።

አጋጣሚ ሆኖ እነዚህ የአማርኛ ፍቺ ያገኙ ሙያዊ ቃላት ይጠቀሱለታል እንጂ በግጥሞቹ ውስጥም በርካታ ያልተባለላቸው ስልቶች የሚገኙ ይመስለኛል ። አንደኛው ቃላትን በሚያዝናና መልኩ ደቅሎ መልእክትን የማስተላለፍ ጥበቡ ነው ።

ለምሳሌ ያህል ‹ ልጀቱ የዘመነችቱ › በተሰኘው ግጥሙ ውስጥ ዘማኒዋ ሱሪዋን - ሱርት ፣ ጫማዋን - ጭምት ፣ ቀበቶዋን - ቅብትት ፣ ጃኬቷን - ጅክት ነው የምታደርገው ። እነዚህ ከስም ውስጥ የተደቀሉ መገለጫዋች የገጣሚውን ምናበ ሰፊነት ያስረዳሉ - አንድም ቋንቋን ከመፍጠር አንድም ምስል አከሳሰትን ከማጉላት ።

እንደ እኔ እምነት የደበበ ሰይፉን ስራዎች በጥልቀት የመረመረ ባለሙያ አንድ ተጨማሪ የግጥም አይነት መታዘቡ አይቀርም ። ከወል ፣ ሰንጎ መገን ፣ ቡሄ በሉ ፣ ሆያሆዬ እና ከመሳሰሉት ውጪ ማለቴ ነው ። ደበበ ልክ እንደ ፀጋዬ ገ/መድህን የራሱ ቀለማት ፣ አወቃቀርና ምት የሚጠቀም ባለቅኔ ይመስለኛል ። በተለይ ከግጥም አወራረዱ አንጻር የአንድ ቃል ዜማ / ሽግግር / ወይም የአንድ ቃል መድፊያን በሚጥም መልኩ በብቸኝነት ተጠቃሚ ነው ።

ሰማይና ምድር ፣ ልጅነት ፣ በትን ያሻራህን ዘር ፣ ያቺን ሟች ቀን የተሰኙ ግጥሞች የዚህ አባባል ማሳያ ናቸው ። በ ‹ ሰማይና ምድር › ውስጥ

በጀርባዪ ተንጋልዬ
አውዬ
በቅጽበት የፈተልኩትን ለብሼ
ሞቆኝ
በእኔው አለም ነግሼ
ደልቶኝ
ከፅድቁ ገበታ ቀምሼ
ጣፍጦኝ
እያለ ይወርዳል ።
አውዬ
ሞቆኝ
ደልቶኝ
ጣፍጦኝ ... የሚሉ ነጠላ ቃላት ያነከሱ ይመስላሉ እንጂ ያለክራንች ነው የቆሙት - ለዛውም ጠብቀው ። በ ‹ ያቺን ሟች ቀን › ውስጥም እንዲሁ ብቻቸውን ቁጭ ያሉት ትብነን ! ... ትምከን ! ... የሚሉ ቃላት ርግማናዊ ግዝፈታቸው ከምላሰ ጥቁር የሰፈር ሽማግሌዎች ወይም መጋረጃ ካገዘፋቸው ታዋቂ ጠንቋዮች የላቀ ነው ።

ይህ ሃይለኛ የአወራረድ ስልት በ ‹ ደበበ ቤት › ተይዞ መጠናት ያለበት ይመስለኛል ። ደበበ እንግዲህ እንዲህ ከምናውቀው በላይ ብዙ ነው ። የብርሃን ፍቅር ሚስጢርነትም ሰፊ ፍቺ የሰነቀ ነው ። በመድብሉ ውስጥ 49 ግጥሞች ተካተዋል ። ከእነዚህ ውስጥ 24 ግጥሞች ብርሃንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያነሳሉ ። 15 የሚደርሱ ግጥሞቹ ብርሃንን የሚያወሱት ፀሃይንና ጨረቃን መሳሪያ በማድረግ ነው ። ማለትም ፀሃይና ጨረቃ በተፈላጊው ቦታና አውድ በግልጽ ተጠቅሰዋል ። ዳኢቴ ፣ አዴላንቃሞ ፣ እቴቴ ፣ ዛሬ እንኳን ፣ ብቻ መገኘትሽ ፣ ሀዘንሽ አመመኝ ፣ ይርጋለም እና የመሳሰሉትን ለአብነት መጠቃቀስ ይቻላል ።

ዘጠኝ በሚደርሱ ግጥሞች ደግሞ ‹ ብርሃን › የተወከለው ራሱን ችሎ ወይም ተምሳሌታዊ ሻማ በማብራት ነው ። ሰማይና ምድር ፣ ያቺ ቆንጂት ፣ ወለምታ ፣ ስንብት ፣ መንታ ነው ፍጥረትሽ እና የመሳሰሉት እዚህ ምድብ ወስጥ የሚወድቁ ናቸው ። ለአብነት ያህል ‹ ያቺ ቆንጂት › በሚለው ግጥም

ጋሼ ላጫውትህ ትለኛለች
ያይኔን ብርሃን እየሞቀች  › የሚል ተደጋጋሚ ስንኝ አለ ። እዚህ ላይ ብርሃን የተወከለው ፍቅርና መልካምነትን ለመግለጽ ነው ።
በግጥም መድብሎች ላይ በተለይም አንድን ጉዳይ በስፋትና በጥልቀት መወቀር የተለመደ አይደለም ። ምክንያቱ የተለያየ ቢሆንም በዋናነት ግን ገጣሚው ራሱ ሊያመነጫቸው በሚችለው ውስን ሀሳቦች ባለመርካቱ ሲሆን አልፎም ተርፎም አንባቢን አሰለቻለው ብሎ መፍራቱ ነው ።

የብርሃን ፍቅር ብርሃናዊ ጨረሮቹን በተለያየ መልክ ሳይሰስት ነው የሚያደርሰን ። በርግጥ ለደበበ ሰይፉ ብርሃን ምንድነው ? ብርሃንን የሚያስረዳን የጨለማ ተቃርኗዊ ውጤት መሆኑን ነው ? ወይስ ከሳይንሳዊ ፣ አፈታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ዳራዎች ጋር የተያያዙ ሃሳቦች አሉት ?

በ ‹ እሱ ነው - እሱ › ግጥሙ ላይ
እሱ ነው - እሱ
አይን ሳይኖረው
      ለምን ብርሃን ኖረ የሚለው
እግር ሳይኖረው
      ለምን መንገድ ኖረ የሚለው
እሱ ነው - እሱ
ከቀናቴ
      ፀሃይቱን የሰረቀ
በመንገዴ
      አሜከላ ያፀደቀ
እያለ የሚበሳጨው ለምንድነው ? ይህ ግጥም የምናወራበትን የ ‹ ብርሃን › ጉዳይ በሚገባ የሚገልጽ ነው ። ምክንያቱም የገጣሚውን ያገባኛል ባይነት ደምቆ እንመለከታለን ። በተጠየቅ የሚሞግትባቸው ቃላዊ - ሃሳቦች ብርሃን ፣ መንገድ እና ፀሃይ ናቸው ። ሃሳቦቹን በቤተዘመድ ጉባኤ አይን ካየናቸው አንድም ሶስትም ናቸው ። ገጣሚው በእውቀት ፣ እድገት እና እውነት ላይ የማይደራደር መሆኑ ይሰማናል ።

የደበበ ሰይፉ የብርሃን ትኩረት አንደኛው ምንጭነት ከህይወት ተምሳሌትነት የመቀዳቱ ጉዳይ ይመስላል ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ከፈጠረ በኋላ የምድር ጨለማ የተሸነፈው በብርሃን ውልደት አማካኝነት ነው ። ፈጣሪ ብርሃንን የፈጠረው ለድምቀት ብቻ አይደለም ። በብርሃን አማካኝነት ሃይል ተሞልቶ ለፕላኔታችን መቀጠል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ። የመሬት ሰርዓተ ምህዳር የተመሰረተው በፀሃይ ከሚገኘው ብርሃን ነው ። ምክንያቱም አጽዋት የፀሃይ ብርሃንን ምግባቸውን ለማዘጋጀት ይጠቀሙበታል ። በሌላ በኩል ሰውና እንስሣት ምግባቸውን ከእጽዋት ስለሚያገኙ ሰንሰለቱ የጠነከረ ነው ።

ደበበ ሰይፉ የብርሃን ሰረገላ የማይታየውን ወይም የማይደፈረውን ነገር ሁሉ እውነት ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ መሆኑን የመረዳቱ ጉዳይም ርዕሰ ጉዳዩን አጥብቆ እንዲይዝ አግዞታል ።

ምነዋ ባየሁኝ › በሚለው ግጥም
ምነው ባየሁኝ
መሬቷን ሰቅስቄ
ዛፉን ተራራውን ቤቷን ሰዋን ሁሉ
አንድ ላይ ጠቅልዬ
በብርሃን ፍጥነት በሚምዘገዘግ ዘንግ
ወዲያ አንጠልጥዬ
እያለ ቀስተ ዳመናንና ጨረቃን ሁሉ ቀላል መጫወቻ እንዲሆኑለት ይመኛል ። ይህ ምኞት መለኮታዊ መሻትም ጭምር ነው ። ምክንያቱም መላዕክት የሚታዩት ብርሃን ባለበት ነው ። ብርሃንን ከመሬት ወደ ሰማይ ለመጓጓዝ እንደ ኤሌክትሮማግኔቲክ ሃይል ይጠቀሙበታል ። ሰዋች ጸሎትና ምሰጣ ሲያከናውኑ እንደ ሻማ አይነት ብርሃናዊ ነገሮችን የሚጠቀሙትም መለኮታዊ ግንኙነት ለመፍጠር በማሰብ ነው ።

ሌላው የደበበ ግጥሞች መሰረታዊ መለያ ፀሃይንና ጨረቃን የብርሃን ምሶሶ ወይም ኪናዊ ምርኩዝ የማድረጋቸው ጉዳይ ነው ። ከላይ እንደገለጽኩት 15 የሚደርሱ ግጥሞች ላይ ምርኩዝ ሆነው ቆመዋል ። አንባቢም በገባው መልኩ በዛቢያቸው እንዲሽከረከሩ ያደርጋቸዋል ። ገጣሚውም አልፎ አልፎ ለብቻ አንዳንዴ ደግሞ አንድ ላይ ያቀርባቸዋል ።

የጥንት ሰዋች የሁለቱን አብሮነት Duality በማለት ይገልጹታል ። ምክንያቱም እንደ ብዙ ሀገሮች አፈታሪክ ከሆነ ፀሃይና ጨረቃ ባልና ሚስት ፣ ወንድምና እህት ወይም ወንድማማቾች ሆነው ይወከላሉ ። የስው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ የሁለትዮሽ ውጤት ነው ። ሁለት እጅ ፣ ሁለት እግር ፣ ሁለት አይን ፣ ሁለት ጆሮ ወዘተ ያለው ። ይህ ጥምረት የፀሃይን ግማሽ እና የጨረቃ ግማሽ ውህደትንም ይወስዳል ። ፀሃይ የቀኝ ጎን ስትሆን ጨረቃ የግራ ናት ፤ የቀኝ ጎን ወንድ የግራ ደግሞ ሴትነትን ወካይ ነው ይላሉ ።

ደበበ ‹ አዴ ላንቃሞ › በተሰኘው ግጥም / አንድ የሲዳሞ ወንድ ነው / ተጠቃሹ ሰው ባሉት ሶስት ሚስቶችና ወንድ ሆኖ በመፈጠሩ ሲደሰት እናያለን ። በደማቅ የጨረቃ ብርሃን ታጅቦ ለሶስቱም ሚስቶች ለአዳር እንደሚመጣ ትእዛዝ ሰጥቶ እንዴት ሽር ጉድ እንደሚሉ በማሰብ ነው የሚስቀው ። ሊያድር የሚችለው ግን አንዷ ጋ ብቻ ነው ።

ብርማይቱ ጨረቃ
የብርሃን ጠበል አፍልቃ
ተፈጥሮን ስታጠምቃት
እንደገና ስትወልዳት
እያለ ነው ግጥሙ የሚዘልቀው ። እንደ ጨረቃዋ ልዩ ድምቀት ሶስቱ ሚስቶቹ ጋ በነበረው ሃያል ሙቀት እየረካ ነበር ። ምክንያቱም ሶስቱም ‹ እኔ ጋ ነው የሚያደረው › በሚል ያሻቀበ ጉጉት ጎጆውን በፍላጎት ፍላት እንደሚያነዱት ስለማይጠረጠር ። ጨረቃዋና ሴቶቹ በፈጠሩት ግለትም ሆነ ጾታዊ አንድነት የተመሳሰሉ ይመስላል ። በግጥሙ መሰረትም አዴ ላንቃሞ የወንድነቱን ፅድቅ አድናቂ ነውና ከጨረቃ በትይዩ የቆመ የፀሃይ ወገን ሊሆን ይችላል ።

ደበበ በተለይም ‹ ገና በልጅነት › እና ‹ ዛሬ እንኳን › በተሰኙ ግጥሞቹ ውስጥ ፀሃይና ጨረቃን በጋራ እየገለጸ ተጠቅሞባቸዋል ። ፀሃይን ሲያነሳ ሃይልን ፣ ህይወትን ፣ ጤናን ፣ ጥልቅ የፍቅር ስሜት መገለጫነትን በመወከል ሲሆን ጨረቃን ሲገልጻት ሚስጢርን ፣ ብቸኝነትን ፣ ውበትን የመሳሰሉትን እንድናስብ በማመላከት ነው ። የደበበ ሰይፉ የብርሃን ፍቅር ብርሃን አስሶ ፣ በብርሃን ተማርኮ ብርሃን የሚሰብክ ኪናዊ ዳመራ ነው ። ‹ የብርሃን ፍቅር › አንድ አይኑን ፀሃይ ሌላውን ጨረቃ አድርጎ ብርሃናማ መሃልየ የሚሰብክ ኪናዊ ካህን ነው ።